Monday, 21 May 2018 00:00

ከቃሌ እስከ ጉለሌ

Written by  ዳግማዊ፡ እንዳለ(ቃል ኪዳን)
Rate this item
(13 votes)


    ቃሌ…….
ሰማይና ምድር የድብቅ ፍቅራቸዉን አጣጥመዉ ከሰዓታት በኋላ ለመገናኘት ተቀጣጥረዉ ተላቀቁ፡፡ በየመንገዱ በሚገኙ ትርፍራፊ ዛፎች ላይ ያሉ ትርፍራፊ ወፎች ያረጀ ያፈጀ ዜማቸዉን እንደ ጥንቱ ያለመሰልቸት ያዜማሉ፡፡ የዉስጣቸዉ ሙቀት ከዉጪዉ ብርድ የበለጠባቸዉ ዉሻዎች በየመንገዱ እየተሯሯጡ ይዳራሉ። ጠንፌ፣ አልማዝና በለጡ እንደጉንዳን ከራሳቸዉ ሰባት እጥፍ የሚበልጥ ማገዶ ተሸክመዉ የቃሌን ቁልቁለት ቁና ቁና እየተነፈሱ ይወርዳሉ፡፡
አልማዝና በለጡ ከተሸከሙት ከባድ ሸክም የተነሳ ጉልበታቸዉን አጠራቅመዉ አልፎ አልፎ አጠር አጠር ያሉ ወጎችን እያወጉ ያዘግማሉ፡፡ ጠንፌ የልጅ ልጃቸዉ ጉልላት አብደላ ጋር በሀሳብ ጭልጥ ብለዉ ሄደዋል…
‹‹ዛሬማ እንደዉ ልክ ልኩን ነዉ የምነገረዉ፡፡ በተከበርኩበት ሰፈርማ አንገቴን ደፍቼ አልኖረም፡፡›› ብቻቸዉን ያጉተመትማሉ፡፡
ጉልላት የላምሮትን መልክ ይዞ በመወለዱ ስስታቸዉና ቅርሳቸዉ ነበር፡፡ ጉልላት ወንድ በመሆኑ የባላቸዉ ምትክ፣ ወንድማቸዉ፣ ብረት መዝጊያና መከታቸዉ ነበር። ጉልላት ኡነበርስቲ በመበጠሱ ኩራታቸዉና ከፍታቸዉ ነበር፡፡ ዛሬ ግን እኮለኔል አጥር ስር ቆሞ እንደ እብድ ዉሉ የማይጨበጥ ነገር ጧት፣ ማታ እየለፈለፈ አንገታቸዉን አስደፍቷቸዋል፡፡
‹‹ከፈለገ ጥርግ ይበል! ማን በልጁ ቆዳ የተቀበረ አለ? እድሜ ለጎረቤቶቼና ለእድሬ አንቀባረዉ ይቀብሩኛል።›› ከኑሯቸዉ ይልቅ ሞታቸዉ የሚያሳስባቸዉ የአበሻዋ እናት ጠንፌ፤ በሀሳባቸዉ ከራሳቸዉ ጋር ይሟገታሉ፤ በለጡና አልማዝ የባጥ የቆጡን ይቀባጥራሉ፡፡
ጉልላት የሟቺቷ የላምሮት ልጅ ነዉ፡፡ ላምሮት የትዬ ጠንፌ ብቸኛ ልጅ ነበረች፡፡ ላምሮትና ጠንፌ ሲኖሩ ሲኖሩ፣ አንድ ቀን ላምሮት አደገችና እላይ ሰፈር ካለዉ አብደላ ከተባለ ልጅ አረገዘች፡፡ አብደላም የላምሮት ዓይኖችና ሆድዋ ሲፈጥበት አገር ጥሎ ጠፋ። ላምሮት እርግዝናዋን ስትጨርስ ጉልላትን ወለደች። ትንሽ እንደቆየች ግን ድንገት ታማ ተኛች። ከዛም ከድንገተኛ ጀምራ ሌሎች መድሐኒት ናቸዉ የተባሉ ቅጠላ ቅጠሎችን ከሞከረች በኋላ ሲብስባት ቀበሌ አስመስክራ  ጳዉሎስ ሆስፒታል ገባች፡፡ ኋላም ሞተች። ጠንፌ በልጅ ልጃቸዉ ቢጽናኑም በላምሮት ሞት አብዝተዉ አለቀሱ፡፡ ለባላቸዉ ካለቀሱት ይበልጥ እምዬ ማርያም ለልጅዋ እንዳለቀሰችዉ ስቅስቅ ብለዉ አለቀሱ፡፡ ጎረቤቶቻቸዉ፤
‹‹ተይ እንጂ ጠንፌ  ሐዘን ማብዛት ደግ አይደለም! እግዚሐርን ይሄን ያክል አታማሪ! ደግሞም ሀኪም የሚያድነዉ የማይሞተዉን ነዉ እባክሽ አታልቅሺ›› ብለዉ ቢያጽኗኗቸዉም፤
‹‹የዚህ አገር ሀኪም የሚሞተዉንም የማይሞተዉንም አያድንም!›› ብለዉ ጉልላት አፍ ፈቶ ‘እማዬ’ ብሎ እስኪጠራቸዉ ድረስ አለቀሱ፡፡
‹‹እሺ ቆይ! እናትህንም አንተንም በማሳደግ ደከምሁኝ። አሁን በል ተራዉ ያንተ ነዉና ጡረኝ፣ አሳርፈኝ አላልሁት። በስተርጅና እንጨት ሰብሬ ቅጠል ለቅሜ ተሽክሜ ስመጣ ስታየኝ፣ ሮጠህ መጥተህ ‘ቆይ እማዬ ላግዝሽ!’ በለኝ ከድካሜ ገላግለኝ እንኳን አላልሁትም፡፡ እስከረፋዱ እያንኮራፋ ሲገላበጥ ዉሎ እኔ ከድካም መጥቼ ያበሰልኩትን ድስት ገልብጦ ነዉ የሚበላዉ፡፡ እና አሁን ለምንድነዉ በተከበርኩበት ሰፈር የሚያዋርደኝ? ለምን ነዉ አንቱ በተባልኩበት ሰፈር ስሜን በመጥፎ የሚያስጠራዉ? ነብሷን ይማረዉና ያቺ ዘልዛላ እናቱ፣ እርሱን አርግዛ ሆዷን አንቀርፍፋ የመጣች ‘ለት እንኳን ይሄን ያህል ቡና መጠጫ አላደረገችኝም፡፡ ለነገሩ የመንደሩ ልጃገረድ ሁላ ያደረገዉን ነዉ ያደረገችዉ፡፡ መቼም ‘እግዚኦ የጠንፌ ልጅ እኮ እንደኔ ልጅ ሳታገባ አረገዘች’ ብሎ ሥጋዬን ሊቦጭቅ የሚችል የለ፡፡ በዚህ ዘመን የሰዉ አፍ ዉስጥ የሚከተዉ ስህተት መፈጸም ሳይሆን ታይቶ ተሰምቶ የማያዉቅ ነገር ማድረግ ነዉ፡፡ ማን ሥራ ፈታሁ ብሎ ብሶት አደባባይ ቆሞ በለፈለፈዉ ነዉ፣ ቆሞ ለፍልፎ ባላፊ አግዳሚ አፍ ዉስጥ የሚከተኝ? ዛሬማ ልክ ልኩን ነዉ የምነገረዉ›› ጠንፌ በዉስጣቸዉ ይዝታሉ፤ በለጡና አልማዝ ከድካም በተረፈች ጉልበታቸዉ በዝባዝንኬያቸዉ ይሣሣቃሉ፡፡
ጉልላት የላምሮትን መልክ የአብደላን ጭንቅላት ይዞ አደገ፡፡ የጉለሌ ሰዎች ስለ ጉልላት አብደላ ሲያወሩ ‹ጉሌ፥ ጉልላቴ የጉለሌ ጀግና! የኡንበርስቲ መብረቅ! ኡንበርስቲን ሪከርድ እንደአበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ለመበጠስ ሲል ለጥቂት በነጠላ ጫማ በጥሶ የተመረቀ!› ይሉታል፡፡ ስማቸዉን ስላስጠራዉ የጉለሌ አድባርን እያመሰገኑ፤ እርሱን ያሞካሹታል! ጠንፌም ይሄን ሲሰሙ ደስ፣ ደስ ይላቸዋል!፡፡
እርሱ ግን እራሱን ‹ከዩኒቨርስቲ ተረግሜያለሁ!› ይላል። የሚለዉ ባይዋጥላቸዉም፣ የዩኒቨርስቲን ተመራቂን መከራከር አርብ፥ እሮብን እንደ መግደፍ ከብዷቸዉ ‹ምን ማለትህ ነዉ ጉልዬ?› ይሉታል፡፡  ጉሌም በበሶና በድንች የፈረጠመዉን አጭር ሰዉነቱን እንደ እንግሊዞች ላይ ታች እየናጠ ‹ግልጽ እኮ ነዉ፡፡ የምርቃት፥ የደስታ ቀናችሁ ነዉ ብለዉ ማቅ ያለበሱን፤ ለሥራ ብቁ ናችሁ ብለዉ የአንድ ድርጅትን አጥር እንኳ የማያሻግር ወረቀት አስታቅፈዉ፣ ዓመታትን የጎለቱን ቢረግሙን እንጂ ቢመርቁን አይደለም!› ብሏቸዉ ጥሏቸዉ ይሄዳል፡፡
ጉልላት ከተመረቀ በኋላ እግሩ እስኪነቃ አዲሳባን ቢያዳርስም በተማረበት መስክ ሥራ ማግኘት ቀርቶ የሥራ ልምድ የማይጠይቁ የሥራ ማስታወቂያዎች አላጋጥም አሉት፡፡ ጠንፌ ከጉለሌ እስከ ቃሌ፤ ከቃሌ እስከ ጉለሌ ኳትነዉ ቅጠል ለቅመዉ እንጨት ሠብረዉ ባሳደጉት ልጅ ለመጦር ባይታደሉም፤ የልጃቸዉን የምርቃት ደስታ እያጣጣሙ፣ እንደ ጥንቱ የቃሌ ተራራን እየወጡ፣ ለሁለቱ ሆድ የሚበቃ እራት ማዘጋጀታቸዉን አልተዉም፡፡
ጉልላት ከብዙ ሥራ ፍለጋ በኋላ ተስፋ ቆረጠና ዝም ብሎ ቁጭ አለ፡፡ ጠንፌ ለታክሲና ለፎቶ ኮፒ ብሎ መጠየቅ ስላቆመ ደስ ቢላቸዉም የልጅ ልጃቸዉ ኩርምት ብሎ በመቀመጡ፣ አንጀታቸዉ ተበልቶ ‹‹ምን ነዉ ልጄ ለምን?›› አሉት፡፡
‹‹እማ የሚወጣዉ ሥራ ሁሉ ቢያንስ የሁለት ዓመት ልምድ ይጠይቃል! ታድያ እኔ የት አባቴ አግኝቼ የሠራሁትን ሥራ ልምድ ነዉ የማቀርበዉ?......ምናልባት አንድ ቀን ሁለት ዓመት የሥራ ልምድ ያላችሁ ሳይሆን ሁለት ዓመት ሥራ አጥታችሁ ቁጭ ያላችሁ የሚል ማስታወቂያ ሊያወጡ ስለሚችሉ የዛኔ እንሄድላቸዋለን፡፡›› አላቸዉ መሬት በድንጋይ እየጫረ። ጠንፌ ልጃቸዉ ያለዉ ነገር ባይገባቸዉም ፊቱ ላይ ያለዉን ሀዘን አይተዉ አዘኑ፡፡
‹‹ዛሬማ ይኸዉ አቡነ ሃብተማርያምና ቅድስት አርሴማ ምስክሬ ናቸዉ፣ ልክ ልኩን ነዉ የምነግረዉ። ወለድኩት እንጂ አልወለደኝ፡፡ ፈሩ ፈሩ ማጀት አሩ አሉ!›› ወደ አቡነ ሃብተማርያምና ቅድስት አርሴማ ቤተክርስትያን አቅጣጫ ዞረዉ፣ ልክ ልኩን ሊነግሩት በዉስጣቸዉ ቃል ገቡ፡፡
ጉልላት ብዙ ጊዜ በዝምታና በመቀመጥ አሳለፈ። ሰሞኑን ግን ዝምታዉና ቁጭታዉ ሲበዛና እራሱን ሲያስጨንቀዉ ተነስቶ ቆመና መናገር ጀመረ፡፡ ከሦስት ዓመት የዩኒቨርስቲ ትምህርትና ከሁለት ዓመት ጥሞና በኋላ ጉልላት አያቱና ብዙዎቹ የመንደሩ ነዋሪዎች ‹ከዩኒቨርስቲ ተረግሜያለዉ› እንደሚለዉ ነገሩ፣ ሌሎች የማይገቧቸዉን ብዙ ነገሮች መናገር ጀመር፡፡ ጠንፌ ኩራታቸዉና ከፍታቸዉ የነበረ ልጅ ማፈርያቸዉና ዉርደታቸዉ እየሆነ መጣ፡፡ ከምርቃቱ በኋላና ተሸክመዉ የሚያመጡትን ማገዶ ካራገፉ በኋላ የጉለሌ ሰዉ ላይ ደረታቸዉን ነፍተዉ ይሄዱ የነበሩት ሴትዮ፣ አሁን የሰዉ ዓይን ቀና ብለዉ ማየት እንኳ ፈሩ፡፡
‹‹ዛሬማ ጠንፌ ምናለች ይበለኝ ልኩን እነግረዋለዉ!›› ጠንፌ ይብከነከናሉ፡፡ እነበለጡ ወሬ አልቆባቸዉ በዝምታ መጓዝ ጀምረዋል፡፡
የቃሌን ቁልቁለት ወርደዉ ወደሰፈራቸዉ መታጠፍያ ጋር ሲደርሱ ሁልጊዜም እረፍት የሚያደርጉበት ጣልያን የሠራዉ አነስተኛ ድልድይ ላይ የተሸከሙትን ለማዉረድ መታገል ጀመሩ፡፡ ጠንፌ ድልድዩ ጋር መድረሳቸዉን ሳይገነዘቡ በደመነፍስ ሸክማቸዉን አወርደዉ፣ በቅርብ ካለች ዛፍ ጥላ ሥር ለእረፍት ቁጭ አሉ፡፡
‹‹ጠንፍዬ ምነዉ ምን ሆነሻል እናቴ? አመመሽ እንዴ? ወይስ አረጀሽ መሰለኝ?›› ስትል ጠየቀች፤ ከሁለቱ አዛዉንቶች በዕድሜ የምታንሰዉ በለጡ ጠንፌ ጎን እየተቀመጠች፡፡ ጠንፌ መልስ አልሰጡም፡፡ ኮለኔል አጥር ስር ቆሞ የሚለፈልፈዉ ልጃቸዉ ጋ በሃሳብ እንደሄዱ ናቸዉ፡፡
‹‹ጠንፌ፤ አንቺ ጠንፌ እያዋራሁሽ እኮ ነዉ! የት ሄድሽ?›› በለጡ በእጇ ነቀነቀቻቸዉ፡፡ ጠንፌ እንደመባነን ሲሉ፤ አልማዝ፡-
‹‹ጠንፍዬ ምነዉ ምን ሆነሽ ነዉ የኔ እናት?›› አሉ፡፡ ጠንፌ ዕንባ በአይናቸዉ ላይ ግጥም አለ፡፡
‹‹በደካማ ጉልበቴ፣ ሰዉነቴ እንደዚህ እየተንቀጠቀጠ ከጅብና ከዉሻ ጋር ታግዬ፣ በስተርጅና የማንም ዱርዬ መጫወቻ አልሆንም፤ ቀሚሴን አላስነካም ብዬ ከጫካ ጠባቂ ጋር ዱላ ተማዝዤ፤ ደም ተፍቼ ያመጣሁትን ቅንጣት እንኳን እፍረት ሳይሰማዉ ድስት ገልብጦ መብላቱ ሳያንሰዉ፣ ጭራሽ የሰዉ መሳቂያ መሳለቂያ አደረገኝ እኮ እህቶቼ?›› ጠንፌ በዕንባ ታጠቡ፡፡ ቅድም በጀርባቸዉ ተሸክመዉት የነበረዉ የማገዶ ቅጠል ነዉ ወይስ ዕንባ?
‹‹እኛ በዚህ በለሊት፣ በዚህ በብርድ እንደ ልጆቻችን የሞቀ አልጋ ጠልቶብን ነዉ እንዴ እንደ ጅብ ጫካ ለጫካ የምንዞረዉ? የነሱን ሆድ ለመሙላት አይደለም እንዴ በመቁረቢያችን ሰዓት ባለጠብመንጃ ጫካ ጠባቂ ካላረከስኳችሁ እንጨት አትሰብሩም እያለ ሲታገለን የሚዉለዉ? የወላድ መካን ሆነን ተፈጥረን በስተርጅና እንክርት!›› ጠንፌ ተንሰቀሰቁ፡፡ በለጡና አልማዝም ያሳለፉትንም ወደፊት የሚጋፈጡትንም መከራ እያሰቡ ተላቀሱ፡፡
‹‹አይዞሽ ጠንፌ አታልቅሺ!  እንግዲህ ዕድላችን ነዉ ምን ይደረጋል? የልጅ ጡረተኞች እግዜር ከሰጠን ምን ማድረግ እንችላለን?›› በለጡ የራሷን ለቅሶ ሳታቆም፣ ጠንፌን ለማጽናናት ጀርባቸዉ ማሻሸት ጀመረች፡፡ ምናልባት ሁሉም የሚያለቅስ ከሆነ መጽናናት ያለበት ለቅሶዉን የጀመረዉ ይሆናል፡፡
‹‹አዎ! ምንም ማድረግ አንችልም፤ ስንሞትላቸዉ ምናባታቸዉ እንደሚሆኑ እናያለን!›› አልማዝ አንገታቸዉን ጉልበታቸዉ መሀል ከተዉ ተንሰቀሰቁ። ጠንፌ ነገሩን በማምጣታቸዉና ጓደኞቻቸዉን በማስለቀሳቸዉ ተሰምቷቸዉ፤ ‹‹አንቺ ጅል የሆንሽ አሮጊት ደሞ ከሞትን በኋላ የት እናያቸዋለን ብለሽ ነዉ?›› አሉ አልማዝን በሀዘኔታ እየዳበሱ፡፡
‹‹ሰማይ ቤት ቴሌብዢን ካለ ብዬ እኮ ነዉ!›› ሶስቱም ፈገግ አሉ፡፡ ፈገግታቸዉ ግን መከፋታቸዉን ማሸነፍ አልቻለም፡፡ ላፍታ ዝምታና ቁዘማ በመሀላቸዉ ሰፈነ፡፡
‹‹ቆይ ይሄ መለፍለፉን ያመጣዉ ከየት ነዉ? የሰፈሩ ጎረምሶች ሁሉ ዕድሜ ልካቸዉን ሥራ ሠርተዉ አያዉቁም። እንደዉ ቀለም የቀመሰ ሰዉ እኮ አስቸጋሪ ነዉ፡፡ ዝም ብሎ መቀመጡ ጨንቆት እኮ ነዉ!?›› አልማዝ ዝምታዉን ሠበሩት፡፡
‹‹ምን ላድርግ እንደዉ አልማዝዬ!? ሥራ መፍታት በእርሱ አልተጀመረ፡፡ አሁን እንዳበደ ሰዉ ሲለፈልፉ መዋል ምን ይሉታል? ለነገሩ በእርሱም አይፈረድ! እጦርሻለሁ ብድርሽን እመልሳለሁ ብሎ ሥራ ፍለጋ እግሩ እስኪቀጥን ተንከራተተ፡፡ እንደዉ ምን አይነት የተረገመ ዕድል ይዞ እንደተወለደ እንጃ! ያለእናት ቅስሙ እንደተሠበረ አደገ … አሁን ደሞ…….፡፡›› ጠንፌ ዳግም ዕንባቸዉን አፈሰሱ፡፡
‹‹ተይ እንጂ ጠንፌ … የምን መነፋረቅ ነዉ? አንቺም ብትሆኚ እኮ ከእናት በላይ ሆነሽ ነዉ ያሳደገሺዉ፡፡……ቆይ ግን ያባቱ ዘመዶች ሥራ እናስይዝህ ብለዉታል አልተባለም እንዴ?›› በለጡ ጠየቀች፡፡ ጠንፌ ለቅሷቸዉን እንዲያቆሙ ርዕሱን መቀየሯ እኮ ነዉ፡፡
‹‹እነሱማ ካንድም ሁለት ሦስቴ ተመላልሰዉ እኛ ጋ መርካቶ ንግድ ነግድ ብለዉት ነበር፤ እሱ አሻፈረኝ አለ። ለነገሩ እዉነቱን ነዉ!፡፡ ባዶ ሆዱንና ባዶ እግሩን ሲማር ቁራሽ ዳቦና እራፊ ጫማ ያልውረወሩለት ሰዎች፤ ዛሬ ኡንበርስት ቢበጥስ ደርሶ አዛኝ ማን አረጋቸዉ›› ጠንፌ በቁጣ መለሱ፡፡
‹‹ኧረ እንኳን ተወዉ! የምን ደርሶ አዛኝ መሆን ነዉ። ባክሽ ጠንፍዬ አጥንት ጉቶ ይፈጃል እንጂ አንድ ቀን መብሰሉ አይቀርም ይባላል፡፡ አንድ ቀን ሥራ ማግኘቱ አይቀርም፡፡ የዛኔ ልፍለፋዉን ይተዋል›› አለች በለጡ ተስፋ ባዘለ ድምጽ፡፡
‹‹አዎ አንድ ቀን ልጆቻችን ልብ ይገዙና፣ ሸክማችንን ከትከሻችን ላይ ያወርዱልናል፡፡ አንድ ቀን ሸክም ያደቀቀዉን ጀርባችንን በዘይት ያሹልናል፤ ዉርጭና ቁር ያጠቆረዉን ፊታችንን አጥበዉ ዘይት ይቀቡልናል። ዋናዉ አንድዬ ልብ ይስጣቸዉ ብቻ!›› በለጡ አድማሱን አሻግራ ተመለከተችና ፈገግ አለች፡፡ አልማዝ ደግሞ በለጡን አይተዉ ፈገጉ፡፡ በለጡና አልማዝ ፊት ላይ ያለዉ ተስፋ መቁረጥ በተስፋ ፈገግታ ተሸነፈ፡፡ ጠንፌ ግን አልተዋጠላቸዉም፡፡
‹‹ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም ይባል የለ። ዛሬ ልክ ልካቸዉን ካልነገርናቸዉ፣ ነገ ሁለት ጸጉር አብቅለዉ አፈር ድሜ ግጠን ከርሳቸዉን በሞላነዉ እንደትዬ ሸዋዬ ልጅ ዱላ አንስተዉ ሳይደበድቡን አይቀሩም፡፡ እኔማ ዛሬዉኑ ነዉ የምነግረዉ፡፡ እመቤቴ ምስክሬ ናት! ዛሬዉኑ ነዉ ልክ ልኩን የምነገረዉ፡፡››
ጠንፌ ድንገት ብድግ ብለዉ ወደ ድልድይዋ ሄደዉ፣ ሸክማቸዉን አንስተዉ መንገድ ጀመሩ። ሲሄዱ እርጅናቸዉና ድካማቸዉ ጠፍቶ፣ በአዲስ ኃይል ተሞልተዉ ነበር፡፡ አፈጣጠናቸዉ የተሸከሙ ሳይሆን የተሸከሟቸዉ ያስመስላቸዋል፡፡ የዉስጥ ሸክም ከዉጪዉ ሸክም ከበለጠ የዉጪዉ ክብደቱ አይሰማም፡፡ እነ በለጡ ግራ ተጋብተዉ፤ ‹‹እሺ አሁን ወዴት ነዉ የምትሄጂዉ? ኧረ እባክሽ ጠብቂን›› ብለዉ ከተቀመጡበት እየተንደፋደፉ ተነሱ።
‹‹ልክ ልኩን ልነግረዉ ነዉ የምሄደዉ! እኔ ጠንፌ ታፍሬ፣ ተከብሬ በኖርኩበት ሰፈር ዉስጥ አንገቴን ደፍቼ አልኖርም፡፡ ‹ለምን ተናገርሺኝ?› ካለም ጥርግ ማለት ይችላል፡፡ ማን በልጁ ቆዳ የተቀበረ አለ? መቼም ብሞት የሚቀብረኝ አላጣም፡፡ በቀዳዳ ሳንቲም ያቋቋምኩት እድሬ አሳምሮ ይቀብረኛል፡፡ ደግሞስ እናንተ ጎረቤቶቼ የት ሄዳችሁ ነዉ?›› ጠንፌ ላጥ ላጥ እያሉ የጉለሌን ቁልቁለት ተያያዙት፡፡ በለጡና አልማዝ፤
‹‹ይህቺ ሴትዮ የልጇ እብደት ተጋባባት መሰለኝ›› ብለዉ ሸክማቸዉን አንሰተዉ ተከተሏቸዉ፡፡ ጠንፌ ይዝታሉ ‹‹ዛሬማ ልክ ልኩን ነዉ ምነግረዉ፡፡ ኧረንሽ‘ቴ ጠንፌ! ነገ ተነስቶ እስኪደበድበኝማ አልጠብቅም››
‹‹ኧረ! እንዴት ነዉ የሚያበራት? ይሄ እኮ እብደት ነዉ! እብደት እኮ ጥንካሬ ይሰጣል!፡፡ መቼም በስተርጅና ማን ይሄን ያህል ሸክም ተሸክሞ ይሮጣል? ነብሷን ይማረዉና ልጇም እኮ ነካ ያደርጋት ነበር፡፡ እብደት ከዘር ነዉ መሰለኝ›› በለጡና አልማዝ ደፍ ደፍ እያሉ በርቀት ይከተላሉ፡፡
ጉለሌ…..….
ጉልላት አብደላ፤ ለሊት ለብሶት ያደረዉን ልብስ ሳይቀይርና ፊቱን ሳይታጠብ፣ የኮለኔል አጥር ስር ቆሟል። የለሊት ስካር ያልለቀቃቸዉና ዓይናቸዉ በርበሬ መስሎ የተጨናበሱ አብሮ አደጎቹ  በዙርያዉ ተኮልኩለዋል። አንዳንዶቹ ጓደኞቹ ገና ከእንቅልፋቸዉ አልተነሱም። አንዳንዶቹ ደግሞ ‘የአይን መግለጫ’ የሚቅሙት ጫት ለመግዛት ሄደዋል፡፡ አንዳንዶቹ ጫቱን መግዥያ ሳንቲም ፍለጋ ተሰደዋል፡፡
‹‹ኮነፊሽየስ እንዲህ ይላል……›› ጉልላት አብደላ ጀመረ፡፡
‹‹በናትህ ይንጋ!›› አዛጋች አንደኛዋ ሴት፡፡
‹‹ጉሌ እኮ አንዴ ከጀመረ አያቆምም! በታንክ እራሱ አታስቆሚዉም፡፡ ይልቅ ትናንት እንዴት ነበር ከሰዉዬሽ ጋር? ቀሚሴን አስወለቀኝ እንዳትይ ብቻ ባንድ ቀን!›› አለቻት ሌላኛዋ ሴት፡፡
‹‹አይ ሱሪ ነበር የለበስሁት! ቂቂቂ›› ተያይዘዉ በሣቅ ወደቁ፡፡
ጉልላት አብደላ ቀጠለ……
‹‹ኮንፊሽየስ እንዲህ ይላል…..ሚስት ባሏን ታክብር፤ ልጅ ወላጆቹን ያክብር፤ ምንዝር አለቃዉን ያክብር…››
‹‹ዝርዝርስ ድፍን ብርን ያክብር አላለም›› አንዱ ወላቃ ጎረምሳ ጠየቀ፡፡ ሁሉም አሽካኩ፡፡
‹‹…ታናሽ ወንድም ታላቁን ያክብር፤ ሕዝብ መሪዉን ያክብር›› ጉልላት ጣቱን ወደ ጎረምሳዉ ቀሰረ፡፡
‹‹ዛሬማ ልክ ልኩን ነዉ የምነግረዉ! እኔ ጠንፌ አይደለሁም! አላበዛዉም እንዴ?›› ጠንፌ ወደ መንደራቸዉ እየተቃረቡ እንደመጡ ሲረዱ፣ ድንገት ፉከራቸዉና ሽለላቸዉ ወደፍርሃት ተቀየረ፡፡ ‹‹ቆይ አንድ ነገር ብለዉ፣ ተከፍቶ እብስ ብሎ ቢጠፋስ? ካለእርሱ ማን ዘመድ አለኝ? የአንዲቷ ልጄ ምትክ - ቅርሴ ጨክኖ ቢጠፋስ? እናት የሌለዉ ልጅ እንደሁ ቶሎ ነዉ የሚከፋዉ›› እግራቸዉ መብረክረክ ጀመረ፡፡
‹‹ዘንድሮ እንደዉ አጀብ ነዉ፡፡ አያትና የልጅ ልጅ አበዱ ቢባል ጉድ እኮ ነዉ! ኧረ ተመልከቺያት እየተንገዳገደች ነዉ፡፡ መሄድም አልቻለችም እኮ!›› በለጡና አልማዝ ከጠንፌ ኋላ፣ ሱክ ሱክ እያሉ ይከተላሉ፡፡
‹‹በእኛ መካከል መከባበርና መተባበር ሊኖር ይገባል። ልጅ አባቱን ማክበር እንዳለበት፣ ቀጣሪዎች ሥራ ፈላጊዎችን ያክብሩ! የተማሩት የተመራመሩት ሥራ ፈተዉ ድንጋይ ሲያሞቁ፣ ዘመድ ያላቸዉና ትምህርት እስከስምንት፤ ዘመድ እስከአክስት ያሉት በአክስታቸዉ አማካኝነት ባለሥራና ባለደሞዝ ሊሆኑ አይገባም፡፡ በተለይ በግል ድርጅቶች ላይ ይሄ ችግር አብዝቶ ይስተዋላል!››
‹‹እዉነቱን ነዉ! የተመረመሩት እራሱ መርማሪዎቻቸዉን ያክብሩ›› አለ አንዱ አልፎ ሂያጅ ሰፈርተኛ፡፡
‹‹አታሹፉ! ጉሌ እዉነቱን ነዉ፡፡ በቃሚዎችና ባስቃሚዎች መካከል መከባበር ሊኖር ይገባል፡፡ ቀፋዮች ተቀፋዮችን ያክብሩ፡፡ ተበዳሪዎች አበዳሪዎቻቸዉን ከመደበቅና ከመሸሽ ይልቅ ያክብሯቸዉ፤ ፍቅር ይስጧቸዉ፡፡ ዛሬ በራሳቸዉ ብር ጫት የገዙ ቃሚዎች፤ ትናንት በጠብሽ ሰዓት ያስቃሟቸዉን ስፖንሰሮች ያክብሩ፡፡›› ወላቃዉ ድጋሚ ጣልቃ ገባ፡፡
ጠንፌ ወደ መንደራቸዉ አንድ ስንዝር በተጠጉ ቁጥር ግራ መጋባታቸዉ እየጨመረ መጣ፡፡ ‹‹ምና‘ባቴ ነዉ የምለዉ … እንደዉ? በመከፋት አንድ ነገር ቢሆንብኝስ? ያለርሱ ማን አለኝ በምድር ላይ?››
የመንደራቸዉ መግቢያ ጋር ሲደርሱ በርቀት የኮለኔል አጥር ስር ጉልላት እጁን እያወናጨፈ ሲያወራ ታያቸዉ። ከእግሩ ስር እኩዮቹ ተኮልኩለዋል፡፡ አላፊ አግዳሚዉ ላፍታ ቆም እያለ በግርምት ይመለከተዋል። ጠንፌ ከርቀቱ የተነሳ የልጅ ልጃቸዉ የሚያወራዉ ባይሰማቸዉም፣ ሌሎቹ የሚሉት ተሰማቸዉ፡፡ ‹‹ይሄ እብድ …የጠንፌ የልጅ ልጅ ነዉ አይደል?›› ‹‹ይሄ ለፍላፊዉ ሥራ ፈቱ … የጠንፌ የልጅ ልጅ ነዉ አይደል? ቆይ ምን ሆንኩኝ ብሎ ነዉ የሚለፈልፈዉ?›› ‹‹ይሄ የጠንፌ ልጅ ምንድነዉ በጠዋት ተነስቶ የሚለፈልፈዉ? ያገኘዉን ሥራ አይሰራም? አሮጊት አያቱን አያግዝም? ቆሞ ወሬ መሰለቅ ወግ መስሎታል!›› ‹‹ይሄ እናቱን የገፋ አሁን ደግሞ አያቱንም ሊገፋ ነዉ እንዴ? አርፎ ያገኘዉን ሥራ አይሠራም? የደሃ ሞልቃቃ እኮ አስቸጋሪ ነዉ፡፡›› ሌሎች፣ ሌሎችም … በልጃቸዉ ላይ የተሠነዘሩ ወቀሳዎች ተሰሟቸዉ፡፡
‹‹ዛሬማ ልኩን ነዉ የምነግረዉ … በተከበርኩበት ሰፈርማ አያዋርደኝም!›› በአዲስ ኃይል ቁልቁለቱን ተንደርድረዉ መዉረድ ጀመሩ፡፡
‹‹ወይ እብደት! ወይ እብደት! እያት ደግሞ መልሳ እሩጫዋን ጀመረች! አይ ዘመን! አያትና የልጅ ልጅ በጀንበር የሚያብዱበት ዘመን›› አልማዝና በለጡ ጠንፌ ላይ ደረስን ሲሉ ጠንፌ ጥለዋቸዉ ስለሄዱ ተስፋ ቆርጠዉ ማዝገም ጀመሩ፡፡
‹‹ኮንፊሽየስ እንዳለዉ፤ ሚስት ባሏን፤ ልጆች ወላጆቻቸዉን፤ ታላቅ ታናሹን፤ ምንዝር አለቃዉን እንዲሁም ሕዝብ መንግሥትን ያክብር፡፡››
ድንገት የትልቁ ግቢ በር ተከፈተና ኮለኔል ወጡ። ኮለኔሉ ቆም አሉና ጉልላትን ትክ ብለዉ አይተዉ፣ እራሳቸዉን በትዝብት ነቀነቁ፡፡ ጉልላት ኮለኔልን አይቷቸዉ፣ ንግግሩን ቀጠለ ‹‹በርግጥ እዚህ ጋር መንግሥት ስንል……››
‹‹ስማ የጠንፌ ልጅ!›› ኮለኔል ጣልቃ ገቡ፡፡ ‹‹ሌት ተቀን ስለ ግብረገብ፣ ስለ መከባበርና ስለ መታዘዝ ታወራለህ፤ እስኪ ተመልከታት እናትህን… በስተርጅና ካንተ የሚበልጥ ሸክም ተሸክማ፣ ከርስህን ለመሙላት ስትባክን!›› አሉት ከዘራቸዉን ጠንፌ ወደሚመጡበት አቅጣጫ እየጠቆሙ፡፡
‹‹እናንተም የበለጡና የአልማዝ ልጆች፤ እስኪ እናቶቻችሁን ተመልከቱ! በአሮጊት ጉልበታቸዉ ምን ተሸክመዉ እንደሚመጡ፡፡ ገልቱ ሁላ! ወግ መስሏችኋል እዚህ ተሰብስቦ ወሬ መሰለቅ! አይ ዘመን! አይ ዘመን!›› መሬት መሬት እያዩ እራሳቸዉን ነቀነቁ፡፡
ጉልላት ለአፍታ ንግግሩን አቋርጦ አያቱን ተመለከታቸዉና፤ ‹‹ኮለኔል … ህብረተሰባችን ሥር ነቀል ለዉጥ ያስፈልገዋል፡፡ እናቶቻችንን ሸክማቸዉን ማገዝ መፍትሄ አይሆንም፡፡ መፍትሄዉ ሸክማቸዉን ማስቀረት ነዉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ሥር ነቀል የሆነ ለዉጥ ነዉ የሚያስፈልገን፡፡ ይህን ለማሳካት ደግሞ ኮንፊሽየስ እንዳለዉ……››
‹‹ዝጋ ደግሞ መልስ ይመልስልኛል እንዴ? ምን አሥሬ ሥር ነቀል፣ ሥር ነቀል ይልብኛል? አንዳች ነገር ሥርህን ይንቀለዉ፡፡ በቃ ትንሽ ቀለም ቀመስን የምትሉ ሰዎች … ለናንተ ለዉጥ ሥር ነቀል ለዉጥ ብቻ ነዉ፡፡›› አሉ የንጉሡ ኮለኔል፡፡
‹‹አይደለም ኮለኔል ያልገባዎት ነገር አለ እኮ…….››
‹‹ዝጋ አልኩህ እኮ!.....›› ቁጣቸዉ ሲበረታ፣ ደጃፋቸዉ ላይ ተኮልኩለዉ የነበሩት ጎረምሶችና ጎረምሲቶች አንዳች ነገር ከመጣ ለመሮጥ እንዲያመቻቸዉ በተጠንቀቅ ተዘጋጁ፡፡ ጠንፌና ጓደኞቻቸዉ እንደ ምሥራቅ አፍሪካ አትሌቶች ተከታትለዉ ወደ ስብስቡ ደርሰዉ ተቀላቅለዉ ቆሙ፡፡
‹‹ስማ አንተ እንከፍ … ቅድምያ ሥር ነቀል ለዉጥ የሚያስፈልግህ አንተ ነህ፡፡ ከልጄ ጋር ሥራ ጀምር … እራስህንም ለዉጥ … አያትህንም እርዳ ብዬ ለመንሁ። አንተ ግን የደሃ ቅምጥል … አሻፈረኝ ብለህ እዚህ አጥሬ ሥር ቆመህ ዲስኩርህን ትደሰኩራለህ፡፡ እስኪ አያትህን ተመልከታት! በስተርጅና ይሄን ያህል ሸክም ተሸክማ ስትመጣ፣ እሮጠህ ሄደህ እንኳን ልታግዛት አልሞከርህም። ግና እዚህ ቆመህ ስለመታዘዝና ስለመከባበር ታወራለህ፡፡ እስኪ ተመልከታት! ለተሸከመ አህያ እንኳን ይታዘንለታል። አንተ ግን ከመጤፍም አልቆጠርካትም። እናንተም የበለጡና የአልማዝ ልጆች … እስኪ እናቶቻችሁን ተመልከቱ። ትንሽ እንኳን አይከብዳችሁም፤ ትንሽ እንኳን የምትበሉት እንጀራ አይመራችሁም? በነሱ ላብና ደም የተጋገረ እንጀራ እኮ ነዉ የምትበሉት፡፡››
ጠንፌ ዕንባቸዉ ከዓይናቸዉ ላይ ኩልል ብሎ ወረደ። ጉልላት የአያቱን እንባ ሲያይ እንባዉን መቆጣጠር አቃተዉ፡፡ ሲቃ ባነቀዉ ድምጽ…
‹‹ኮለኔል ቆይ በተማርኩበት ካልሠራሁ ታድያ ለምን ተማርኩ? በተማርኩበት ልሥራ ማለቴ ሀጥያት ነዉ እንዴ?›› ማውራት አቃተዉ፡፡
‹‹በሂሣብ ትምህርት የተመረቀ እንግሊዘኛ በሚያስተምርበት አገር፣ በተማርሁበት ካልሠራሁ ሥራ አልሠራም ብለህ የምትል ከሆነ አያትህ ደም ተፍታ ያመጣችውን አትብላ፡፡ ለምን ያልሠራኸዉን ትበላለህ?››
‹‹ለዚህ እኮ ነዉ ሥር ነቀል ለዉጥ ያልኮት!››
‹‹ዝጋ! እንዳትጨርሰዉ! አንዳች ነገር ይንቀልህ….›› ኮለኔል ከዘራቸዉን ነቀነቁበት፡፡ ድንገት አንድ ጎረምሳ አይኑን እያሻሸ ወደ ስብስቡ ደረሰ፡፡ ኮለኔሉ፤ ‹‹ደህና አደርክ? ነጋልህ?›› አሉት፡፡
‹‹ደህና አደሩ ኮለኔል?›› ምንም ባልሞቀዉና ባልደነቀዉ ድምጽ፣ አይኖቹን እያሻሸ መለሰላቸዉ። ኮለኔል ወደ ጎረምሳዉ ከዘራቸዉን አዘጋጅተዉ ተጠጉ። ልጁ ደነገጠና በጥያቄ ዓይን ተመለከታቸዉ፡፡
‹‹ጭራሽ በዚህ ዕድሜ … እስከዚ ሰዓት እየተጋደምክ፤ አንተን እርጉዝ ሆና የሰፋችዉን መሶብ ገልብጠህ እየበላህ……እሱ አልበቃ ብሎህ ጭራሽ የወለደች እናትህን ዱላ አንስተህ ትደበድባት?›› ልጁ አግሬ አዉጪኝ ሊል ሲል፣ ኮለኔል ጀርባዉ ላይ ከዘራቸዉን አሳረፉበት፡፡ መሬት ላይ ተንደፋድፎ እንደምንም ተነስቶ ተፈተለከ፡፡ ከእንቅልፉም ከአንጎበሩም በኮለኔል ከዘራ ነቃ፡፡ እነ ጠንፌ በእርካታ ፈገግ አሉ፡፡ በተጠንቀቅ ሲጠብቁ የነበሩት ጎረምሶችና ጎረምሲቶች ዘማዊቷን ሊከሱ እንደተሰበሰቡት አይሁዶች፤ የራሳቸዉን ሀጥያት አስታዉሰዉ በየአቅጣጫዉ ተፈተለኩ፡፡ ጉልላት ብቻ ከአያቱ ጋር ተፋጦ ቆመ፡፡
‹‹ከዛሬ ጀምሮ አንድሽ አጥሬ ስር ተቀምጠሸ ላግኝሽ። አንተ ደግሞ ከአሁን በኋላ ስትለፈልፍ ላግኝህ ብቻ! ዉርድ ከራሴ በል፡፡›› ኮለኔል ከዘራቸዉን ፊቱ ላይ ነቅንቀዉበት፣ መንገዳቸዉን ቀጠሉ፡፡ ጉልላት እሮጦ ሄዶ የአያቱን ሸክም አወረደላቸዉና
‹‹እማዬ እኔ አደርሰዋለሁ በቃ!›› አላቸዉ እንባዉ እየፈሰሰ፡፡ ጉልላትን ሲያዩ የበለጡና የአልማዝ ልጆችም ከሸሹበት እየተሯሯጡ መጥተዉ፤ የእናቶቻቸዉን ሸክም አወረዱ፡፡ ሦስቱ እናቶች ላመት በዓል ልብስና ጫማ እንደተገዛለት ህጻን በደስታ ተፍነከነኩ፡፡ ከልጆቻቸዉ ጋር ‹ኧረ እኔ እሸከመዋለሁ› ብለዉ ሊከራከሩ ቃጣቸዉ፡፡
‹‹እማዬ አንቺ ሂጂ፡፡ እኔ ይዤዉ እመጣለሁ፡፡›› አለና ጉልላት ወደ ኮለኔል ግቢ እየሮጠ ገባ፡፡
***
ተጫዋች ብጤ የመሰሉ የቀይ ዳማ ሴትዮ፤ ገርበብ ያለዉን የእጠነፌን ቤት መዝግያ ከፍተዉ ‹ቤቶች› አሉና ገቡ፡፡
‹‹አቤት ደጆች! ዉይ አንቺ ነሽ እንዴ አልማዝዬ? ግቢ ግቢ እናቴ!›› አሉ ጠንፌ፤ እንደመነሳት ብለዉ ቁጭ እያሉ።
‹‹እኔዉ ነኝ…  ምነዉ ሰዉዬሽን እየጠበቅሽ ነበር እንዴ ጠንፍዬ?›› አሉ አልማዝ፤ አንዳች ነገር እያላመጡና ስስ ፈገግታ እያሳዩ፡፡ ጉንጫቸዉ ተወጥሯል፡፡
‹‹ሰዉዬማ ጴጥሮስ ጓሮ ተኝቷል! እኔ ነኝ እንጂ ወደርሱ የምሄድ እርሱ ወደኔ አይመጣም›› አሉ ጠንፌ፤ የሚቆሉት ቡና ላይ የባላቸዉን ምስል ያዩ ይመስል ትክ ብለዉ እየተመለከቱ፡፡
‹‹ምናልባት አንድ ቀን ወደዚህ የሚመጣ አዉቶብስ ካገኙ ሊመጡልን ይችላሉ፤ ማን ያዉቃል ብለሽ ነዉ?›› አሉ አልማዝ፤ በርጩማ ስበዉ ከጠንፌ ፊት እየተቀመጡና ነጠላቸዉ ጫፍ ላይ ቋጥረዉ የያዙትን ንፍሮ ለጠንፌ እጅ መንሻ አድርገዉ እያቀረቡ፡፡ ጠንፌ የአልማዝን ጉንጭ በመገረም ተመልክተዉ፤
‹‹ጭራሽ ጉንጭሽን እንደልጅሽ ወጥረሽ መዞር ጀመርሽ? ኋላ ምች አጠናግሮ እንዳይጥልሽ›› አሉ በሣቅ ታጅበዉ ንፍሮዉን እየተቀበሉ፡፡
‹‹ምን ይደረግ ጠንፌ? ልጆቻችን አድገዉ ይጦሩናል ስንል ቅጠል መብላት አስተማሩን……ደግሞስ ምን ምች አለ ብለሽ ነዉ? የዘንድሮ ጸሀይ ቢያቆስልሽም ቁስሉን እራሱ መልሶ ያደርቀዋል፡፡ ደረቅ ዘመን!›› አልማዝ በረጅሙ ተነፈሱ፡፡
ድንገት ጉልላት በሩን በርግዶ ገባና፣ ከሬሳ ሳጥን ትንሽ አነስ ከሚል የእንጨት ሳጥን ዉስጥ ያሉትን ልብሶች ይመነቃቅር ጀመር፡፡
‹‹የጸሀዩንስ ነገር ተይዉ! እንኳን ቁስል ደም አያደርቅም፣ ጠላት አያስታርቅም ብለሽ ነዉ አልምዬ።›› አሉ ጠንፌ የልጅ ልጃቸዉ ምን እንደሚሠራ በዓይናቸዉ እየተከታተሉት፡፡
‹‹ምናልባት ከአሁን በኋላ ማንም እየተነሳ ደመላሽ፤ ደም አፋሽ እያለ ማላዘኑን ያቆማል፡፡ ለነገሩ እንደለመዱት ‘ጸሀዬ ደመቀች’ የሚለዉን አሻሽለዉ ይዘፍኑት ይሆናል፡፡ መቼም የኛ ሀገር ዘፋኞች ማሻሻል ነዉ ሥራቸዉ፡፡›› አለ ጉልላት ሳጥኑን በእጆቹ እያተራመሰ፡፡
‹‹አሁን ስለምን እንደምናወራ ሳታዉቅ ምን ጥልቅ አደረገህ?›› አሉ ጠንፌ አፍጥጠዉበት፡፡
‹‹የዘንድሮ ሰዎች ከኑሮ ዉድነትና ከጸሐዩ ኃይለኝነት የዘለለ አታወሩም ብዬ ነዉ እማዬ›› አላቸዉ፤ ቀይ መስመር ያለዉ ሸሚዝ አዉጥቶ ለመቀየር ልብሱን እያወለቀ፡፡
‹‹የእርጎ ዝምብ!›› አሉት አያቱ፡፡ ፈገግ ብሎ ሸሚዙን አስተካከለና ወደበሩ አመራ፡፡ በሩ ጋር ከመድረሱ መዝጊያዉ ተከፍቶ በለጡ ገባች፡፡
‹‹ቡናዉ አልፈላም እንዴ ወጣቶች?›› አለች ገብታ፡፡
ጉልላትን ከላይ እስከታች ገረመመችዉና…
‹‹ፕሮፌሰር ጉልላት፤ ዛሬ ወዴት ልትሄድ ነዉ እንዲህ ሽክ ያልከዉ?›› አለችዉ፡፡
‹‹ሥራ ልጀምር ነዉ!›› አለ ጉልላት የሸሚዙን እጅጌ እያስተካከለ፡፡ ሦስቱም በመደንገጥ ተመለከቱት። ሥራ መጀመሬ ይሄን ያህል ያስደነግጣል እንዴ በሚል አስተያየት በመገረም፣ ሦስቱንም ተራ በተራ ተመለከታቸዉ፡፡ እንደአያቱ ዓይኖች የሁሉም ዓይኖች በደስታ ፈክተዋል፡፡
‹‹አዎ! መኩርያ ጋር ሥራ ልጀምር ነዉ፡፡›› አለ - ይለይላቸዉ ብሎ፡፡
‹‹መኩርያ የቱ?›› ጠንፌ ጠየቁ፡፡ መኩርያን በደንብ እንደሚያዉቁት ዉስጣቸዉ እርግጠኛ ነዉ፡፡ ግን ጠፋባቸዉ፡፡
‹‹መኩርያ የኮለኔል ልጅ ነዋ!›› አልማዝ የጠንፌን ያህል ደስ ብሏቸዋል፡፡
‹‹በርግጥ ደሞዙ በድግሪ ተቀጥሮ ከመሥራት አሥር እጥፍ ይሻላል፡፡ ግን ቢሆንም በተማርኩበት ብሠራ ምርጫዬ ነበር፡፡ እኔ የፈለግሁትን ነበር የተማርኩት። እዉነት አሥራ አምስት ዓመት ሙሉ ምኞቴን አሳካለሁ ብዬ፤ በተስፋ ተሞልቼ በባዶ እግርና በቀዳዳ ሱሪ፣ የተማሪ ዓይን እንደ እሳተ እየገረፈኝ መማሬ ያሳዝነኛል።››
‹‹አይዞህ ገና ወጣት እኮ ነህ! እንዲህ ቶሎማ ተስፋ አትቁረጥ፡፡›› አለች በለጡ፡፡
‹‹እሱስ እዉነት ብለሻል! በባዶ እግሬ መማሬ እግሬን ብቻ ሳይሆን ሁሉ ነገሬን ሊያጠነክር ይገባ ነበር፡፡ ለነገሩ የመሬቱ ቁርቋሬ አሁንም ድረስ ስለሚሰማኝ፣ አሁንም እራሴን ማጠንከር እችላለሁ፡፡ ባዶ እግሬና ቀዳዳ ሱሪዬ ላይ ያፈጥ የነበረዉ የተማሪ ዓይን፤ ሊያላግጥ የሚፈለቀቀዉ የተማሪ ጥርስ አሁንም ድረስ ወላፈኑ ይጠብሰኛል፡፡ እልህ ያሲዘኛል! ለዛም ነዉ እንደልጅ እያሱ ‹ድግሪዬን አዉልቄ አገልድምያታለሁ፤ ቀን የወጣላት እንደሆን እሠራባታለሁ!› እያልኩኝ ቀን እስኪመጣ እማዬን ላግዛት፤ ድካሟን ልጋራት የወሰንኩት፡፡ በልዬና አልማዝም ከልጆቻችሁ የምሥራች አላችሁ፡፡›› ጉልላት የላምሮትን ዉብ ፈገግታ ፈግግ ብሎ ሲያበቃ፣ የሦስቱንም እናቶች ጉንጭ ስሞ ወጥቶ ሄደ፡፡ በሦስቱም ዓይን ላይ የደስታና የሐዘን ድባብ ተፈጠረ፡፡ ልጅ እያሉ የመጀመርያ ፍቅረኛቸዉ ሲስማቸዉ የተሰማቸዉ ዓይነት ደስታ፤ ኧረ እንደዉም ከዛ በላይ የሆነ ደስ የሚል ስሜት ሳይሰማቸዉ አይቀርም!

Read 3910 times