Monday, 21 May 2018 00:00

ሐገርና ሳይክል!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ - (አተአ)
Rate this item
(1 Vote)

“… በእርግጥ ህዝቦቹ ራሳችን ባህር መሆናችንን አናውቅም፣ እነሱም እኛ ከሌለን አሳዎች መሆናቸውን አልተረዱም ነበር! … “
          
   በጠዋት ሁለት ሃሳብ ወደ አዕምሮዬ ገብቶ በየተራ ያደክመኝ ነበር፡፡ አንደኛው፣ ‹‹እንዳያልፉት የለም…›› የሚል የትግል ግጥም ሲሆን ሁለተኛው፣ በጉዞዬ ላይ ያየሁት ትእይንት ነው፡፡
በመጀመሪያው ሃሳብ ከጠቀስኩት ግጥሙ መሃል ‹‹ስንቶች ተኮላሽተው - ከአረንቋ ዘቀጡ…›› የምትለውን አንጓ ወስጄ የገነባሁት ሌላ ግጥም፣ አስር ጊዜ ከአእምሮዬ ጓዳ ብቅ ብቅ ይላል፡፡
‹‹ስንቶች ተኮላሽተው - ከአረንቋ ዘቀጡ…››
ይሏት ስንኝ መጥታ
ከሃሳቤ ገብታ
አላኝክ አልተፋት - እንደ አኞ ስጋ
ካሳቤ ጥርሶች ውስጥ - ገብታ ተመስጋ
ታሰቃየኛለች - መሽቶ እስከሚነጋ፡፡
ሃሳቤን - (ኤጭ! እስኪ ተወኝ በናትህ) እለውና፣ እነዚህን የግጥም ስንኞች ራቅ አድርጌ እተፋቸዋለሁ። ትፍ ትፍ ትፍ …. እንዳያልፉት የለም መቸም ስንቱን አለፍን አይደል፡፡
***
ቀጥዬ በተሳፈርኩበት ታክሲ መስኮት ወደ ውጭ  አፈጣለሁ፡፡ የሚከናወኑ ነገሮችን በቅጡ ባልነቃ ልቡናዬ እቃኛለሁ፡፡ አዲስ አበባ እያዛጋች ነበር፡፡ ሰዎቿም ማልደው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ተኝተው እንኳን በማይተኛውና እረፍት በማያውቀው የጨጓራ ጥያቄ መሰረት ወደ ግል ትግላቸው ማልደው ገብተዋል፡፡
ለማኞች በየቦታቸው እየተሰየሙ ይታየኛል፡፡ በረንዳ አዳሪዎች በየቦታው ወዳድቀውና የማለዳው ጠል እየወረደባቸው አሪፍ እንቅልፍ አላቸው፡፡ እኔ ጠዋት ከአልጋዬ ስነሳና ከሞቀ አንሶላዬ ለመውጣት ስታገል፣ የእናትና የአባቶቼ ፀሎት ነው የሚረዳኝ! ማልጄ ብነሳም የምነቃው በኋላ ነው፡፡ እንዲያውም ከቤት ወጥቼ እየተጓዝኩም አንቀላፋለሁ፡፡
ከማዶው እግረኛ መንገድ ላይ አንድ አባት፣ ልጁን ሳይክል መንዳት እያለማመደ ይታየኛል፡፡ እንዲህ ነው’ንጂ አባት፡፡ ቁምጣውን ለብሶ ብርድ እየጠበሰው፣ ካቦርቷን ደርባ ፈገግታና ስጋት ባረበበበት ፊት የምትደሰትና ሳይክሏ ላይ ተቀምጣ ፔዳሉን ለመግፋት የምትውተረተር ህጻን፡፡ አባቷም የሳይክሉን ኮርቻ አጥብቆ በመያዝ ደግፏታል፡፡
ቀናት ይፈጃል እንጂ ይህቺ ልጅም በቅርቡ መንዳት ትችላለች ስል አሰብኩ፡፡ የሚያስፈልጋት ነገር ቢኖር ትዕግስተኛና ብልሃት ያለው አሰልጣኝ ነው፡፡ ባይሆን ስታድግ ትግሉን ሁሉ የራሷ በማድረግ እንዳያልፉት የለም ልትል ትችል ይሆናል፤
እንዳያልፉት የለም ያ ሁሉ ታለፈ
ታጋይ የህዝብ ልጅ በደሙ በላቡ ደማቅ ታሪክ ፃፈ …. (እያለች ትዘፋፍን ይሆናል፤ ሳይክሏን እየነዳች) - ከራሴ ጋር ሞቅ ያለ ፈገግታ ውስጥ እገባለሁ። ሀሳቤ ራሱ ይገርመኛል፡፡ እናም የቅድሟ ስንኝ መልሳ ትመጣብኛለች። እንዲህ የሚሉ አንጓዎችም እቀጥልባታለሁ፡-
አእላፍ ተሰውተው - ስንቶች ድል አረጉ
ስንቶችስ ጠንክረው - ለአላማቸው ተጉ?
ብዬ እጠይቅና
እጀምረዋለሁ - ያን አኞ ስንኜን - ማኘክ ከእንደገና፡፡
ፈገግ እያልኩ፣ የራሴ ልጅነትና የሳይክል ልምምዴን አስታውሳለሁ …
***
የመጀመሪያዋን ሳይክል የተቀመጥኳት ሰፈር ውስጥ ነው፡፡ ሳይክል ለመንዳት ጉጉቱ ሰቅዞ የያዘው ትንሽ ልጅ ነበርኩ፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ከሰፈር ጎረምሶች አንዱን ሳይክል ያስነዳኝ ዘንድ ለመንኩት፡፡ ትንሽ ካንገራገረ በኋላ እሺ አለኝና አንጠልጥሎ አስቀመጠኝ፡፡ እንደ ምንም እግሮቼ ፔዳሉ ላይ ቢደርሱም ከመቀመጥ በስተቀር አያሽከረክሩትም ነበር፡፡ እናም አሰልጣኜ እየገፋ ትንሽ አንሸራሸረኝ፡፡ በእውነቱ በወቅቱ ታላቅ ደስታ ተጎናጽፌ ነበር፡፡
እየገፋኝ ሰፈራችን ውስጥ ካለው ቁልቁለት ቦታ ደርሰናል፡፡ ከፊት ለፊታችን ደግሞ አዜብ እየመጣች ነበር። አዜብ ማለት የአለማማጄ ጓደኛ ነች (ፍቅረኛው ነበረች መሰለኝ!)፡፡ እናም ከፊታችን መምጣቷን ሲመለከት እንዲህ አለኝ።
‹‹እየውልህ  ሳይክል መንዳት እንግዲህ እንዳየኸው ቀላል ነው፡፡ ባላንስ ጠብቆ መሪ መያዝ፣ ፊት ለፊት መመልከት፣ ከዚያ ፔዳል ማሽከርከር፡፡ እንቅፋት ሲያጋጥምህ ፍሬኑን መጨበጥ፡፡ በቃ አሁን ውረድና ባይሆን ሌላ ቀን ትነዳለህ!…››፣ ተናግሮ ሳይጨርስ ለንቦጬን ጥዬ እለማመጠው ጀመር፡፡ ትንሽ ካንገራገረ በኋላ ሳያወርደኝ፣ ዝም ብሎኝ ወደፊት ቀጠልን፡፡
አዜብ አጠገባችን እንደደረሰች፣ ተጨባብጠውና ተሳስመው ሲያበቁ ወሬ ቀጠሉ፡፡ ሚስጥር ለማውራት ግን አልቻሉም፡፡ ብልጡና ትንሹ ልጅ በሳይክሉ ላይ ተፈናጦ አጠገባቸው ነበር፡፡ እናም ጎረምሳው እንዲህ አለኝ፡-
‹‹እንግዲህ እንዳልኩህ አድርግ! ቀላል ነው፣ ቀስ እያልክ … እናም ፍሬኑን እንዳትረሳ!..›› ከዚያም በቁልቁለቱ ቀስ አድርጎ ገፋኝ፡፡
ስነሳ በዝግታ ነበር፤ ወዲያው አየሩን እየቀዘፍኩ ቁልቁል ተሽቀነጠርኩ፡፡ ፍጥነቴ እየጨመረ ሲሄድ ይታወቀኛል፡፡ በርግጥ ሳልወድቅ መሽከርከሬም ገርሞኛል፡፡ እንደ ጥንቸል በመሬትና በአየር፣ በመንሳፈፍና በመሽከርከር መሃል ፍጥነቴ እየጨመረ ቁልቁለቱን በረርኩ፡፡ ሳስበው ማቆምም ሆነ መቆጣጠር አልቻልኩም ነበር፡፡ የማሽከርከርና የመቆጣጠር ጥበቡ ምንም ነገር ሳይገለጥልኝ ፣ የአባትና የእናቴን ፀሎት ሳላስታውስ፣ ድረሱልኝ ብዬ ሳልጮህ …. ወዘተ … ከነዚህ ሁሉ በፊት፣ ከፊት ለፊቴ ካለው የቆርቆሮ አጥር ላይ ተቀበቀብኩ፡፡
በርግጥ አዜብ ስትጮህ ሰምቼ ነበር፡፡ ጉልበቴና ክንዴ ተላልጦ፣ የጎድን አጥንቴ ላይ ውጋት እየተሰማኝና ግንባሬ ላይ ልዩ ልዩ ምልክቶችን ፈጥሬ እየደማሁ ተስፈንጥሬ ተነሳሁ፡፡
በደመነብስ ዘልዬ ቆምኩና ‹‹መንዳት ቻልኩ አይደል!?›› ስል አለማማጄን ጠየኩት፡፡ በአካባቢው ደንግጠው ተሰብስበው የነበሩት ሁሉ ሳቁ፡፡
አለማማጄም ፈገግ እያለ … ‹‹የነገርኩህን ሁሉ ረስተሃል። አሁን ማን ይሙት ሰው በትክክል መንዳት ቢያቅተው እንዴት ፍሬን መያዝ ያቅተዋል?!›› ሲል ወቀሰኝ፡፡
አሁን አድጌ የግንባሬ ጠባሳም አድጎ እዛው አለ፡፡ ጣቶቼን ሰድጄ በግንባሬ ላይ ያለውን ጠባሳ ዳበስኩት። የመጀመሪያውን ልምድ ለማስታወስ የተሰጠኝ ሜዳሊያዬ ይህ ነበር፡፡ ነገሩ ‹የማረፍ ልምዱን ሳታደርግ አትብረር !› እንደተባለው መሆኑ ነበር፡፡
እናም የቅድሟ ስንኝ መልሳ ትመጣብኛለች፡፡ እንዲህ የሚሉ አንጓዎችም እቀጥልባታለሁ …
ከአረንቋው  ባሻገር - ስንቶች አልፈው መጥተው
ከሌላ አረንቋ - በፍላጎት ገብተው
የሃብት ስኳር ልሰው
የድሃ እምባ ቀምሰው
በድህነት ቀንበር - ህዝብ እያማቀቁ
ስንቶች ተኮላሽተው - መልሰው ወደቁ?!
***
እናም በሃሳቤ እንዲህ ስል አመሰጥራለሁ፡፡ ሀገር ማለት ሳይክል ነው፣ ማንም ሰው የማሽከርከርና የመንዳት እንዲሁም በሰላም የማረፍ ልምድና ጥበብ ሳይቀስም አይነዳትም፤ ከነዳትም ጥቂት ከተንገጫገጨ በኋላ ያጋጫታል (በቃ መጨረሻው ይታወቃል)፣ ሀገራት ከተጋጩ በኋላ እንደነበሩ መልሶ የሚጠግን ጋራዥ የላቸውም፡፡ በርግጥ መልሶ የተጠገነ ሳይክል ወይም መኪና እንደ በፊቱ ያለ ዋጋ የለውም፣ ቢሆንም፣ ቢሆንም ከመንገራገጭ በኋላ ማደስና መጠገን ግድ ነው፡፡
መንግስት ማለት ደግሞ ሹፌሩ ነው (በተለይ ለመኪናው ብናስተውለው!)፤ ጥበቡን በደንብ ከቀሰመ በኋላ ነው ወደ ሜዳው የሚወጣው፡፡ ችሎታው ካለው ዳገትና ቁልቁለቱን፣ አስፓልትና ኮረኮንቹን፣ ጫካና ሜዳውን …. ሁሉም ቦታ ህጉን ጠብቆ፣ ፍጥነቱን ተቆጣጥሮ፣ እያስተዋለና እየመረመረ የሚሾፍርና የሚያሽከረክር፣ ተሳፋሪዎችን ሳያጉላላ የሚያጓጉዝ ነው። መሪው ብቁ ሲሆንም አንዳንዴ ወረድ ብሎ ሌሎችን በተገቢው የሚያለማምድና የሚያበቃ፣ ረዳቱን የእውነት ረዳቱ የሚያደርግ፣ ተገልጋዩን ደግሞ ያለምንም መድልኦ የሚያገለግል፤ ንብረቱን በስርአት የሚጠብቅና በእርሱ ደካማ የማሽከርከር ችሎታ የሌሎችን ንብረት የማያበላሽ ነው፡፡
ተመልካች ግን ያው ሁሌም ተመልካች ነው፣ ስትጋጭም በብቃት ስትነዳም ያጨበጭባል፡፡ በትክክል ከነዳህ ጎበዝ፣ ካጋጨህ ደግሞ “ያልኩህን አትሰማም” ይልሃል፡፡
***
እያልኩ እየተፈላሰፍኩና በዚያች መነሻ አንጓ፣ በሃሳቤ ያሰመርኳትን ባለጥቂት መስመር ግጥም በቃሌ እወጣታለሁ …
‹‹ስንቶች ተኮላሽተው - ከአረንቋ ዘቀጡ…››
ይሏት ስንኝ መጥታ
ከሃሳቤ ገብታ
አላኝክ አልተፋት - እንደ አኞ ስጋ
ካሳቤ ጥርሶች ውስጥ - ገብታ ተመስጋ
ታሰቃየኛለች - መሽቶ እስከሚነጋ፡፡
አእላፍ ተሰውተው - ስንቶች ድል አረጉ
ስንቶችስ ጠንክረው - ለአላማቸው ተጉ?
ብዬ እጠይቅና
እጀምረዋለሁ - ያን አኞ ስንኜን - ማኘክ ከእንደገና፡፡
ግና….
ከአረንቋው  ባሻገር - ስንቶች አልፈው መጥተው
ከሌላ አረንቋ - በፍላጎት ገብተው
የሃብት ስኳር ልሰው
የድሃ እምባ ቀምሰው
በድህነት ቀንበር - ህዝብ እያማቀቁ
ስንቶች ተኮላሽተው - መልሰው ወደቁ?!
በግጥሜ የረካሁ ይመስል ለብቻዬ ፈገግ እያልኩ ቀና ስል፣ ጠብደሉ ረዳት እጁን ወደ እኔ ዘርግቶ እያፈጠጠብኝ፤ ‹‹መጨረሻ ደርሰናል! ሂሳብ!? ›› አለኝና ከሃሳቤ አናጠበኝ፡፡
ሒሳቤን እየከፈልኩና ከታክሲው እየወረድኩ (ከመኪናው ላይ ስወርድ ሰዎች ልክ እንደተሳፋሪ ከአገራቸው ምድርም ይወርዱ ይሆን እያልኩ አስባለሁ!…) ይህችን ከአንድ መፅሃፍ ላይ ያነበብኳትን (የትግራይ ህዝብ፣ ወያኔዎቹና ሽፍቶቹ፤ ዮናስ በላይ አበበ፤ ግንቦት 2006 ዓ.ም) የትግሪኛ ዘፈን አያሰብኩ ነበር …
ባህርና ሓፋሽና ህዝብና፣
ዕጥቅና ወያናይ ሓቦና፣
ድፋዕና ጎቦታት ዓድና
ንሕና ዓሳ ኮይና
ንሡ እውን ባህርና
ዝመፀ ጸላኢ ክንድርዕሞ ኢና፡፡ (ግርድፍ ትርጉሙ - ባህራችን ሰፊው ህዝባችን፣ ትጥቃችን አብዮታዊ ወኔያችን፣ ምሽጋችን ተራራዎቻችን፣ እኛ ዓሳ ሆነን፤ እነሱ ደግሞ ባህራችን፣ የመጣብንን ጠላት እንደመስሰዋለን …).. ሃ ሃ ሃ--- ይሄ ነበር ዘፈናችን፡፡
በእርግጥ ህዝቦቹ ራሳችን ባህር መሆናችንን አናውቅም፣ እነሱም እኛ ከሌለን የማይኖሩ አሳዎች መሆናቸውን አልተረዱም ነበር፡፡ ስል እጠራጠራለሁ፣ እንዲሁም አስባለሁ፡፡
እናም … አስባለሁ፣ አስባለሁ፣ አስባለሁ …. (ማሰብ እችላለሁ ማለት፣ አለሁ  እንደማለት ነውና!)
dubito, ergo cogito, ergo sum - “I doubt, therefore I think, therefore I am”  … እንዳለው …. Descartes .

Read 1375 times