Monday, 21 May 2018 00:00

ኢ/ር ዶክተር አድማሱ ገበየሁ፣ ከ12 ዓመት ስደት በኋላ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

· የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ስርአት የአምባገነኖች መደበቂያ ነው
        · ህዝብን ማሸነፍ የሚቻለው በፍቅርና በውዴታ ብቻ ነው

   በቅርቡ “መግባባት” ፖለቲካዊ እኩልነት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን! በሚል ርዕስ ለበርካታ አመታት ያደረጉት ፖለቲካዊ ምርምር ውጤት መፅሐፍ ፅፈው ለአንባቢያን ያቀረቡት የቀድሞ የኢዴፓ መስራች እና ፕሬዚዳንት እንዲሁም የቅንጅት ም/ሊቀ መንበር የነበሩት ዶ/ር ኢ/ር አድማሱ ገበየሁ ላፉት 12 ዓታት ከኖሩበት ስዊድን ሃገር ከሰሞኑ ለእረፍት አዲስ አበባ በመጡበት አጋጣሚ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አግኝቶ ከ1997 እስካሁን የመጣንበትን የፖለቲካ ሂደት የዳሰሰ ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ ዶ/ር ኢንጅነር አድማሱ ገበየሁ በሙያቸው የውሃ ምህንድስና ሊቅ ሲሆኑ በቅርቡም ወደ ሀገራቸው ተመልሰወ በሙያቸው እንዲሁም በሌሎች ማህበራዊ ዘርፎች ለማገልገል ፍላጎት እንዳቸው ይገልፃሉ፡፡ ዶ/ር ኢ/ር አድማሱ በሰፊው የሚታወቀውን የድል ምልክት የሆነውን የቅንጅቱን የሁለት ጣት የምርጫ ምልክት ሃሳብ በማመንጨትም ይታወቃሉ፡፡


    በ97 በተደረገው ምርጫ፣ ”ቅንጅት”ን በምክትል ሊቀ መንበርነት ሲመሩ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ላለፉት 12 ዓመታት ግን በሃገር ውስጥ አልነበሩም፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያለውን ፖለቲካዊ ሁኔታ አንዴት አገኙት?
እርግጥ ነው ከ97 በኋላ በቅርብ የለሁም፤ ነገር ግን በየጊዜው ሁኔታዎችን ማወቅ እፈልግ ነበር። የዲሞክራሲ ሥርአት በዚህ ሃገር፣ በብዙ ሰዎች የሚፈለግ ጉዳይ ነው። ብዙዎችም መስዋዕትነት የከፈሉበት ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን በቅርብም ይሁን በሩቅ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ እስካሁን መሻሻልን አላየሁም። ዲሞክራሲያችን እስካሁን መሻሻል አላሳየም፡፡ ይሄን መሻሻል የማምጣት ጉዳይ በዋናነት የህዝቡ ነው፤ ቀጥሎም ስለ ህዝብ ሆነው የሚንቀሳቀሱ ሚዲያዎች በተለይም ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ ጋዜጠኞች ከ97 በኋላ በሚፈለገው መጠን ዲሞክራሲን ማገልገል አልቻሉም። በእርግጥ ይሄ የእነሱ ጥፋት አይደለም፡፡ አመቺ ሁኔታ አልተፈጠረላቸውንማ ተወቃሽ አይደሉም፡፡ ሆኖም ዘርፉ ተመናምኖ ነው ያገኘሁት፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ ጋዜጠኞች በተደጋጋሚ ለእስርና ለስደት  ተዳርገዋል። ይሄ በሀገሪቱ ከባድ ጉዳይ ነው፡፡ በፖለቲካ ዘርፍ ህዝቡን ለማገልገል የተሰማሩ ወገኖች፣ ከገዥው ፓርቲ በስተቀር፣ ሃገራቸው እንዳልሆነች፣ ህዝቡም ወገናቸው እንዳልሆነ እንደ ባዕድ ተቆጥረው፣ምንም አይነት መፈናፈኛ አጥተው ቆይተዋል፡፡ ይሄ በዚህ አስራ ሦስት ዓመት ውስጥ የተፈፀመ እጅግ አሳዛኝ ታሪክ ነው፡፡ በአጠቃላይ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሚዲያዎች፣ የዲሞክራሲ ተቋማት፣ ሲቪክ ተቋማትና የዲሞክራሲ ምንጭ የሆነው ህዝቡ ራሱ በአሳዛኝ ሁኔታ ነው የቆዩት፡፡ ህዝቡ የሥልጣኑ ባለቤት መሆን አልቻለም፡፡ አስፈላጊ መድረኮች ተነፍገውታል፡፡ ይሄ አሳፋሪ ታሪክ ነው፡፡ እኔ በግሌ ውጪም ብኖር፣ በዚህ ጉዳይ እረፍት አጥቼ፣ ውስጤም ሲቆስል ነበር፡፡
አብዛኞቹ የቅንጅት አመራሮች ከእስር ከተፈቱ በኋላ ተበታትነዋል፡፡ አሁን ላይ ሆነው ሲያስቡት ችግሩ ምን ነበር ይላሉ?
እውነቱን ለመናገር ከ1997 በኋላ በመንግስት የተሰራው ሴራ እንዲህ ነው ተብሎ ሊገለፅ አይችልም። እርግጥ ነው ትልቁ ባለድርሻ መንግስት ይሁን እንጂ ሌላው የአንበሳውን ድርሻ የምንይዘው እኛ ተዋናዮቹ ነን። እንደ ህዝብ አነቃናቂ መሪ ወደ ኋላ ተመልሰን፣ ትንሽ በመሆናችን እኔ በበኩሌ ያሳዝነኛል፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ተሳታፊ በመሆኔ፣ በፈፀምኩት ጥፋት በግሌ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ምንም ይሁን ምክንያቱ እኛ የሚጠበቅብንን፣ የድርሻችንን አላደረግንም ነበር። በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እዚህ ያለውን መከራና ስቃይ መቅመስ ሲገባኝ፣ ለስደት መዳረጌም ውስጤን በጣም ጎድቶታል፡፡ ሆኖም ግን በአንድ በኩል በራሴ ኃላፊነት ስር ያሉ ቤተሰቦቼም ሆኑ ሌሎች ወገኖች ህይወታቸው እንዲቀጥል ማስቻሌ ደስ ይለኛል፡፡ በአጠቃላይ ግን በሀገር ደረጃ የሰራሁት ስህተት አመዝኖ ይታየኛል። ይህን ተረድቼም የበደልኩትን ለመካስ ባለኝ ሁሉ እታገላለሁ። በስደት እድሜዬ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ኅሊናዬ ስመለስ፣ ባለሁበትም ሆኜ አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ ብዬ ሞክሬያለሁ፡፡ ምንም ይሁን ምን እዚሁ የህዝብን ትንፋሽ እያዳመጡ፣ ከህዝብ ጋር አብረው መከራቸውን እያዩ፣ እየታሰሩ እየተፈቱ፣ የሚችሉትን ያህል የሰሩ ሰዎች በጣም የምቀናባቸው፣ በጣም የማከብራቸው ናቸው፡፡ ያንን ባለማድረጌ ትንሽ ቅስሜ ስብር ቢልም የሰሩትን ስራ ሁሉ ከማድነቅ ወደ ኋላ አልልም፡፡ ማድረግ ያለብኝን ግን ወደፊት አደርጋለሁ፡፡
የኢዴፓ መስራችና ሊቀ መንበር ነበሩ ---
ኢዴፓ መድህንን ፕሬዚዳንት ሆኜ ለሁለት የምርጫ ጊዜያት አገልግያለሁ፡፡ ዶ/ር ኃይሉ አርአያም ም/ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ኢዴፓንም ሆነ ሌሎች ፓርቲዎችን ያን ያህል በጥልቀት አልተከታተልኩም። ፓርቲዎችን በድምሩ ነበር የማያቸው፡፡ በአንድ በኩል ተቃዋሚን የሚወክል፣ በሌላ በኩል ገዥው ፓርቲ አድርጌ፣ በሁለት ዘርፍ ነበር በጥቅሉ የምከታተለው፡፡ እኔ አሁን ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ውጪ ነው ያለሁት። ይሄን የወሰንኩት በራሴው ምክንያት ነው፡፡ አንድ ሰው ከሃገሩ ከወጣ፣ በየዕለቱ እወክለዋለሁ ከሚለው ህዝብ ጋር ካልሆነ፤ በምንም መልኩ አመራርነትም አባልነትም አያስፈልገውም የሚል ነው እምነቴ፡፡ የፖለቲካ ስራ በህዝብ መሃል የሚከወን ነው፡፡ ምክንያቱም ባለቤቱ ህዝብ ነውና፡፡ ስለዚህ የሌለሁበትን የተቃውሞ ፖለቲካ፤ በጥልቀት አልተከታተልኩትም፡፡
ባለፉት 27 ዓመታት የዲሞክራሲ ሥርአት ግንባታ የት ደርሷል ይላሉ?
ዲሞክራሲያዊ ስርአት ተገንብቶ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገው አይነት የፖለቲካ ስርአት ለመፍጠር ገና አልጀመርንም፡፡ ምክንያቱም ለመጀመሩ ምልክት የሚሆኑ ነገሮች በበቂ መጠን አልታዩም፡፡ ሃሳብን በነፃ መግለፅ ተግባራዊ ካልተደረገ ምን ፖለቲካ አለ? ሰዎች የሾሟቸውን እንኳ ለመቆጣጠር በነፃነት መደጀራት አለባቸው፡፡ ይሄ ተፈጥሯል? ምርጫ ራሱ የግል አይደለም። አንድ ፓርቲ በሚሊዮን ተደግፎ ከተመረጠ፣ የመረጡት 1 ሚሊዮኖች የፓርቲው እምነት አራማጆች ናቸው ማለት ነው። ይሄ ቀላል አይደለም፤ ስሜታቸው፣ ፍላጎታቸው፣ ግንዛቤያቸው---በመረጡት ፓርቲ ውስጥ አለ ማለት ነው፡፡ ይሄ በመሆኑ አንድ ማህበር ናቸው፡፡ በ97 ቅንጅትን ሚሊዮኖች ሲመርጡት፣ የማህበሩ አባል ሆኑ ማለት ነው፡፡ የፓርቲውን መብት መንግስት ጣሰ ማለት፣ የሚሊዮኖቹን ሃሳብና ፍላጎት ደፈጠጠ ማለት ነው፡፡
ብዙ ጊዜ በዓለም ላይ ያለው ዲሞክራሲ የሚቸገረው፣ የዲሞክራሲን የመጀመሪያ ትርጉም ትቶ፣ ሁለተኛውን ትርጉም በመያዝ ነው፡፡ ቀዳሚው የዲሞክራሲ ትርጉም፤ አንድ ዜጋ ራሱን በሚመለከት በሚሰጥ የውሳኔ ሂደት ውስጥ ራሱ ቀጥታ ወይም ተወካዩ መሳተፍ አለበት ይላል። ይሄ የዲሞክራሲ የመጀመሪያ ትርጉም ነው። ሁለተኛው ትርጉም፤ አብዛኛው በወሰነው ይፀናል፣ የጥቂቶቹ ድምፅ በብዙኃኑ ይገዛል ነው የሚለው፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ዲሞክራሲ የሚቸገሩት የመጀመሪያውን ትርጉም እየሳቱ ነው፡፡ በመፅሐፌ ለምሳሌ፣ ስለ አብላጫ ድምፅ የምርጫ ስርአት አስቀምጫለሁ፡፡ በዚህ ስርአት ውስጥ የሚንፀባረቀው ሁለተኛው የዲሞክራሲ ትርጉም ነው፡፡ አብላጫ የምርጫ ስርአት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዘንናል፡፡ አብዛኛው ማህበረሰብ የወከለውን ተወካይ በሚፈልገው ቦታ፣ በውክልና እንዳይቆምለት የሚያደርግ ነው፡፡ አሁን በአፍሪካ ውስጥ ብዙ አገሮች፣ ”ዲሞክራሲ - ዲሞክራሲ” ይላሉ እንጂ ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡ ይህ የሆነው በአመዛኙ የያዙት የአብላጫ የድምፅ ስርአት ምርጫ ስለሆነ ነው። እንኳን ብዙ አይነት ማህበረሰብ ባለበት አፍሪካ፤ ለትንሽ አገርም ቢሆን አብላጫ የድምፅ ስርአት የሚበጅ አይደለም። አምባገነኖች ግን ይህን የምርጫ አይነት ይወዱታል። ምክንያቱም ሽፋኑን ምርጫ አድርገው፣ ያለ ነቀፌታ “ዲሞክራሲ ሰፍኗል” እያሉ፣ ውስጡን ግን የአንድ ፓርቲ ሰዎች እየተለዋወጡ፣ አለፍ ሲልም አንድ ሰው ብቻውን “ከስልጣኔ ሞት ያንሳኝ” በማለት የሙጥኝ ብሎ በንግስና ይቆያል፡፡ ይህ አይነቱን የምርጫ ስርአት ያመጣው ሰው፣ ከንጉስ ያነሰ ስልጣን የለውም። የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ስርአት፤ የአምባገነኖች መደበቂያ ሽፋን ነው፡፡ አስፈላጊው የምርጫ ስርአት “የመግባባት ዲሞክራሲዊ ስርአት” ነው፡፡
“መግባባት” የተሰኘው መጽሐፍዎ በዋናነት የሚያቀነቅነው ፖለቲካዊ ሃሳብ ምንድን ነው?
በመፅሐፉ ላይ የህግ የበላይነት፣ ዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት ጉዳዮች በጉልህ ተነስተዋል፡፡ የህግ የበላይነት ጉዳይ ለአንድ ስርአት ጉልህ ነው፡፡ ህፃናት ራሱ የሚጫወቱት ጨዋታ ሊቆይ የሚችለው፣ የጨዋታው ህግ እስከተከበረ ብቻ ነው፡፡ ህግ ሲፈርስ፣ ይበታተናል ይፈርሳል፡፡ በመንግስት ስርአት ውስጥም የህግ የበላይነት የዚህ አይነት ሚና አለው፡፡ ምናልባት በየጊዜው የሚጎረብጡ ህጎች ህግን ተከትለው ሊሻሻሉ ይችላሉ፡፡ የሚሻሻሉትም በህግ የበላይነት ስር ሆነው ነው፡፡ ህግና ስርአት አለ የሚባለው ወረቀት ላይ ስለሰፈረ ብቻ አይደለም፡፡ በተግባር መገለጥ አለበት። ከህግ የበላይነት ጋር ተያይዞ ደግሞ የሰብአዊ መብት፣ ሁላችንም በግላችን ያለን ተፈጥሮአዎ መብት ነው። የትኛውም ህግ ሊሽረው የማይችለው ነው፤ ሰብአዊ መብት፡፡ በህይወት መኖር፣ ከአካልና ህሊናዊ ጉዳት የመጠበቅ መብት፣ የሰብአዊ መብት ብለን ልንጠቅስ እንችላለን፡፡ ይሄን መብት የሚገፍ ሁሉ ህግ ነው ብለን ልንቀበል አይገባም፤ ልንታገለው ይገባል፡፡ መሻር አለብን። የሚገባንን የሰውነት ክብር የሚያኮስስ ሁሉ፣ መታገል አለብን፡፡ በመፅሐፌ ያነሳሁትም ይሄን ነው፡፡ ሌላው የዲሞክራሲ ጉዳይ ነው፡፡ የዲሞክራሲ ስርአት በምንም መልኩ፣ ሰብአዊ ክብራችንን ከነካ፣ የህግ የበላይነትን ከተጋፋ መታረም አለበት፡፡ ከህግ የበላይነትና ከሰብአዊ መብት ጋር የሚጋፋ ከሆነ ወትሮውንም ዲሞክራሲ አይደለም፡፡ ዲሞክራሲ፤ የእነዚህን ጥጋት ጠብቆ ነው መራመድ ያለበት፡፡ እነዚህ ሶስት አካሎች የራሳቸውን መስመር እየጠበቁ፣ የኛን የዜጎችን መብት መጠበቅ አለባቸው ነው፤ አጠቃላይ ትንታኔው፡፡ “መግባባት” ስንል፤ ሁለት ነገሮች በውስጡ አሉ፡፡ አንደኛ፤ ወደ አንድ የጋራ ነገር መምጣት ማለት ነው፡፡ ወደ መግባባት ለመምጣት ደግሞ ስርአት ነው የምናበጀው፡፡ መግባባት ማለት አንድ አይነት ሃሳብ መያዝ መቻል ማለት ሳይሆን ችግሮች በሚፈቱበት ሁኔታ ላይ ተቀራራቢ ወይም አንድ አይነት ሃሳብ ላይ መድረስ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- የምርጫ ውጤት በመቀበል ላይ መግባባት ሲፈጠር “መግባባት” እንለዋን፡፡ “የመግባባት ዲሞክራሲ”፤ የህሊና ፍርድ ነው መነሻው፡፡
በመፅሐፍዎ መግባባትን ከምርጫ ጋር አያይዘው የሚገልጹበት ሁኔታ አለ፡፡ እስቲ ያብራሩልን?
በህግ የመምረጥ መብት የተሰጠው ሁሉ፣ የሚሰጠው ድምፅ ዋጋ ሁሉ፣ ከሁሉ እኩል ነው ካልን፣ ውጤቱም እኩል መሆን አለበት ነው - ፅንሰ ሀሳቡ፡፡ 100 ሰዎች የመረጡት እና 200 ሰዎች የመረጡት ድምፅ በእኩል መመዘን አለበት፡፡ ይህ ማለት 100 ድምፅ ያገኘው አንድ መቀመጫ ቢያገኝ፣ 200 ያገኘው ደግሞ 2 ማግኘት አለበት ማለት ነው፡፡ ይህ ቀመር ተግባር ላይ ሲውል፣ የ100ዎቹ መራጮች ድምፅ፣ መሬት ላይ አይወድቅም ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለውን የምርጫ ስርአት ነው ልንከተል የሚገባው፡፡ ይህን ሃሳብ ነው መፅሐፌ ላይ በሰፊው ያብራራሁት፡፡ የተመጣጠነ የምርጫ ስርአት፤ እያንዳንዱ ዜጋ የሚሰጠው ድምፅ ዋጋ እንዳለው ያረጋግጥለታል። ወደ “መግባባት ዲሞክራሲ” ለመግባት ተመጣጣኝ የምርጫ ስርአት ተግባር ላይ መዋል አለበት፡፡ ተመጣጣኝ የምርጫ ስርአት ከሌለ፣ “መግባባት” ዲሞክራሲ ውስጥ መግባት አንችልም፡፡ በሩ እሱ ብቻ ነው፡፡ “የመግባት ዲሞክራሲ” ቀመር የሚያስቀምጠው፣ ልክ የፓርላማው መቀመጫ በተመጣጣኝ የድምፅ ስርአት እንደሚያዘው ሁሉ፣ የመንግስት ስራ አስፈፃሚውም ወይም ካቢኔውም በዚሁ ቀመር ይዋቀር ነው የሚለው። የካቢኔ ቦታ ላይም በተመጣጣኝ የምርጫ ስርአቱ ቀመር መሰረት በስራ አስፈፃሚ ውስጥ በዚህ መንገድ ተመጣጣኝ ውክልና ካለ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ አስፈፃሚውን በሚገባ ለመቆጣጠር ያለው ስራም ሊሰራ ይችላል። በአብላጫ የምርጫ ስርአት ግን ዋናው የፓርቲውና የጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎነት ነው የሚጠበቀው፤ ምክንያቱም ስልጣን በሙሉ ተጠቅሎ እጃቸው ይገባል። በዚህ “መግባባት ዲሞክራሲ” ቀመር ግን ከስልጣን ለሁሉም እንደየመጠኑ ይከፋፈላል፡፡ ይህ ሲሆን ስራ አስፈፃሚው እየተከራከረ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ማለት ነው፡፡
ሁሉም አካል ከመንግስት የስልጣን እርከኖች እንዲሳተፍ በማድረግ፣ የኔነት ስሜትን ይፈጥራል ማለት ነው፡፡ አንድ ፓርቲ ብቻውን ሀገሪቱን እንደፈለገ የማድረግ እድል እንዳይኖረው ያደርጋል፡፡ ሌላው የመግባባት ዲሞክራሲ ጥቅሙ፣ አንድ ስርአት የሰራውን ተከታዩ እንዳያፈርስ ያግዛል፡፡ እኛ ደግሞ ይህን አይነቱን ስርአት ለመጀመር እድላችን ሰፊ ነው። ለምሳሌ አሜሪካ ይህ ሃሳብ ይተግበር ቢባል ለስንት መቶ አመታት የተሰፋውን ድሪቶ ማፍረስ ይከብዳል። እኛ ግን ብዙም ስላልደረትን በቀላሉ ከንፁህ ጨርቅ መልበስ መጀመር እንችላለን። በነገራችን ላይ ዶ/ር አብይ አህመድ ካነሷቸው ሃሳቦች፤ በትምህርት ጥራት ላይ ያላቸውን አቋም ወድጄዋለሁ። ትምህርት የግለሰቦችን ግንዛቤና ኃላፊነት የመሸከም አቅም ከፍ ስለሚያደርግ፣ ከፍተኛ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ነው። ትምህርት የሁሉም መንገድ ነው፡፡ የአስተሳሰብ መሰረትም ትምህርት ነው። ዶ/ር አብይ በዚህ ሃሳባቸው ልቤን ነክተውታል፡፡ ሁሌም ስጨነቅበት የነበረውን ነው የነኩልኝ፡፡
ብሔራዊ መግባባት እና እርቅ ተደጋግሞ የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ መግባባት ሲባል ምን ማለት ነው? እርቅስ ምንድን ነው? ማን ከማን ጋር ነው የሚታረቀው?
ማንኛውም ሰው መግባባትን መቀራረብን፣ መታረቅን ቢያነሳ፣ በጎ ነገሮች ስለሆኑ ጠቀሜታ አላቸው፡፡ እነዚህን በጎ እሳቤዎች ከዳር ለማድረስ የሚሰሩ ሁሉ በጎ እያደረጉ ነው እላለሁ፡፡ ለ18 ዓመታት ሳጠና እና ስከታተለው የነበረው አንዱ ጉዳይ፣ ይሄ የመግባባት ጉዳይ ነው። መተባበር፣ መተጋገዝ፣ መካተት አለመገለል፣ ስልጣን ለህዝብ የቀረበ መሆን የመሳሰሉት በጎ እሳቤዎች ናቸው፤ የመግባባት መርሆዎች፡፡ የእነዚህ ሃሳቦች መግነን ነው ዘለቄታ ያለው እርቅን የሚፈጥሩት፡፡ መግባባትና እርቅ፤ ከዚህ አንፃር ነው መተርጎም ያለበት፡፡ በጎ እሳቤን ለማጉላት፣ የቅሬታ ምንጮችን ማደብዘዝ ነው - የእርቅ መንገዱ፡፡
የፖለቲካ አደረጃጀቱ ከላይ ወደ ታች ሳይሆን ከታች መሰረት እየረገጠ፣ ወደ ላይ እየጠነከረ የሚሄድ መሆን አለበት፡፡ ይሄ ካልሆነ አመራሩ ሁሉ አሽከርና ሎሌ አይነት ነው የሚሆነው፡፡ የመግባባት ጉዳይ እነዚህን ሁሉ ያካትታል፡፡ ምክንያቱም የስር መሰረት ካልያዘና አፈንጋጭ ከሆነ፣ አፈር ሲባሉ ድንጋይ፣ ድንጋይ ሲባሉ ውሃ እንዳቀለቡት የሰናኦር ግንበኞች ነው የሚሆነው፤ አገሩ ሁሉ፡፡ መግባባትም መታረቅም፣ ከዚህ አንፃር ነው እኔ የምመለከተው፡፡ በጎ ነገርን ማቀንቀን ነው፤ ተስፋ ተፈላጊ ነገር ነው፤ ጨለምተኝነት ደግሞ ለዚህ እንቅፋት ነው፡፡
የዶ/ር አብይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣት እንዴት ይመለከቱታል?
በመጀመሪያ በመገናኛ ብዙኃን ያየሁት አቶ ለማ መገርሳን ነበር፡፡ አቶ ለማ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል መካከል ስለተፈጠረው ግጭት ንግግር ሲያደርጉ፣በጥንቃቄ ነበር ያዳመጥኩት፡፡ በንግግራቸው በጣም ነበር የተደመምኩትና የተደሰትኩት፡፡ ከክልል አልፈው፣ ኃላፊነት ተሰምቷቸው፣ ልክ እንደ አንድ ዳኛ፣ አመጣጥነው መናገራቸው አስደንቆኛል፡፡ በዚያው ቅፅበት ነው ሰውየው፤ ባህሪያዊ ፀጋ አላቸው ብዬ ያመንኩት፡፡ ወዲያው ነበር ፌስ ቡክ ገፄ ላይ ሙሉ ንግግሩን የለጠፍኩት፡፡ ሃሳባቸው ወርቅ ነበር። ተስፋዬን ነበር ያለመለሙት፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን ደግሞ የዶ/ር አብይን ንግግሮች፣ ከተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች፣ ማግኘትና ማዳመጥ ቻልኩ፡፡ ሰውዬው መልካም መልካሙን ነገር የማየት፣ የወደፊት ተስፋን አሻግሮ የመመልከትና ተስፋ ሰጪ ነገሮችን የመፈንጠቅ ልዩ ክህሎት አላቸው፡፡ በእንግሊዝኛም በአማርኛም ያደረጓቸውን የተለያዩ ንግግሮች ሰብስቤአቸዋለሁ፡፡ ሁሉም እንከን አልባ ንግግሮች ናቸው፡፡ በዚህ ሰውየውን ከጅምሩም ተስፋ ጥዬባቸው ነበረ፡፡ ከዚህ ተስፋ በመነሳት ልክ በፓርላማው ንግግር ሲያደርጉ፣ እኔም ንግግራቸውን ለፌስቡክ ተከታታዮቼ፣ በቀጥታ ሳደርስ ነበር፡፡ ንግግሩ በጎ በጎ ነገር ይበዛዋል፡፡ ተስፋ ፈንጣቂ ነበር፡፡ አቶ ለማ፣ ዶ/ር አብይ፣ አቶ ገዱ የያዙት ነገር ከባድ ትግል ነው፡፡ በነሱ አቅም ብቻ ከዳር ይደርሳል የሚል እምነት የለኝም። ያለንን ሁሉ አዋጥተን ልንረዳቸው ይገባል፡፡ ስልጣን ባይኖረን የዜግነት ግዴታችንን ተጠቅመን፣ ቢያጠፉ እየወቀስን፣ ቢያለሙ እያበረታን፣ የለውጡ አካል መሆን አለብን፡፡ ወቀሳው የሚያስፈልገው በድጋፍ ጭብጨባችን ደንዝዘው፣እንዳይዘናጉ ነው፡፡ ለነሱም ይረዳቸዋል፡፡
የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ  ፈተናዎች ምን ይመስልዎታል?
እኔ ብዙ ተስፋ ነው የሚታየኝ፤ ከተግዳሮቱ ይልቅ። ከኢህአዴግ ጎራ የነበሩ ሰዎች፣ ወደዚህ የለውጥ መንፈስ ያመጡናል ብዬ በህልሜም በእውኔም አስቤ አላውቅም፡፡ ከመጡበት ሂደት በላይ ከእንግዲህ የሚገጥማቸው ፈተና ያለ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ አላቸው፤ ይሄ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ አብዛኛው ከደገፋቸው ፈተና የሚመስሉትን በቀላሉ ማለፍ ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ ፍላጎቱ ያፈገፍጋል ተብሎ አይታሰብም። ትልቁ ፈተና  የኢትዮጵያን ህዝብ ልብ መግዛት ነው፡፡ ይህን ደግሞ አልፈውታል፡፡ በመሳሪያ ኃይል አይደለም የህዝብን ልብ የገዙት፡፡ በአንደበታቸው ነው፡፡ የመሳሪያ ኃይል ህዝብን ያሸብራል እንጂ  አያሸንፍም፡፡ ህዝብን ማሸነፍ የሚቻለው በፍቅርና በውዴታ ብቻ ነው። ህዝቡ ይህን ውጤት መጠበቅ አለበት፤ አለበለዚያ ሊቀለበስ ይችላል፡፡ እነሱ የያዙትን እንዲቀጥሉ ህዝብም እየደገፈ ወደ መጨረሻው ውጤት መሄድ አለበት፡፡ ህዝብ ነቅቷል፡፡ ደግ ደጉን የሚያበረክት ከሆነ፣ሁላችንም እንቅልፍ ወስዶን እናድራለን፡፡ ግን እንዳይቀለበስ አስተማማኝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ከጠ/ሚኒስትሩ  አመራር  ምን ይጠበቃል ይላሉ?
ካድሬያዊ የተበላሸ የአሰራር ሰንሰለትን ማጥፋት አለባቸው፡፡ ሃገሩን ማገልገል የሚፈልግ ምሁር ሞልቷል፡፡ ጨዋነት ደግሞ ወሳኝ ነው፤ ፖለቲካውን የጨዋ ያድርጉት፡፡ እነ ዶ/ር አብይ፤ በጨዋነት ፖለቲካውን እንደ ጀመሩት፣ ከላይ እስከ ታች የጨዋ ፖለቲካ ያድርጉት፡፡ ሌላውን ሁሉ ትተው ፖለቲካውን የጨዋ ያድርጉት፡፡ አመራሮች በህዝቡ የተመሰከረላቸው ጨዋዎች ከሆኑ፣ ቢማሩ ባይማሩ ግድ አይሰጥም፡፡       

Read 4737 times