Monday, 21 May 2018 00:00

ጠ/ሚኒስትሩ በውጭ ሃገራት የታሰሩ ኢትዮጵያውያንን ማስፈታታቸውን ቀጥለዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)

  በሳኡዲ አረቢያ የታሰሩ 1 ሺ ኢትዮጵያውያን ዛሬ ይፈታሉ

    ከትናንት ጀምሮ በሳኡዲ አረቢያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፤ ኢትዮጵያውያን እስረኞች እንዲፈቱ ለሃገሪቱ መንግስት ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት በማግኘቱ በተለያዩ ወህኒ ቤቶች የታሰሩ 1 ሺ ኢትዮጵያውያን ዛሬ ይፈታሉ ተብሏል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ጥያቄ መሠረት የሣኡዲ መንግስት በተለያዩ የሃገሪቱ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እስረኞችን ለመፍታት ተስማምቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሣኡዲ የመጀመሪያ ይፋዊ ጉብኝታቸውን እያደረጉ ያሉት በሃገሪቱ ልዑል አልጋ ወራሽ ቢን ሠልማን አብዱላዚዝ የቀረበላቸውን ግብዣ ተከትሎ ሲሆን በዚህም በዋናነት በሁለቱ ሃገራት የወደፊት ግንኙነት፣ በእስረኞችና በትውልደ ኢትዮጵያዊው ባለሃብት ሼህ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ጉዳይ መወያየታቸው ታውቋል፡፡
በሣኡዲ አረቢያ የተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በውል እንደማይታወቅ የጠቆሙት ቃል አቀባዩ በዛሬው ዕለት 1 ሺ እስረኞቹ ያለ ቅድመ ሁኔታ እንደሚፈቱ የሃገሪቱ ልዑል አልጋ ወራሽ ቃል ገብተዋል፡፡ በሼህ አላሙዲ የፍቺ ጉዳይ ግን የተባለ ነገር የለም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ጉብኝታቸው በሳኡዲ አረቢያ በህክምና ስህተት ምክንያት ላለፉት 12 ዓመታት በሆስፒታል የአልጋ ቁራኛ ለሆነው ኢትዮጵያዊ ታዳጊ መሃመድ አብዱላዚዝ የሳኡዲ መንግስት ካሳ እንዲከፍለው ጠይቀዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ የታዳጊውን ወላጆች አግኝተው ያነጋገሩት ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግስትም ለታዳጊው አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ቃል መግባታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ታዳጊ መሃመድ አብዱላዚዝ የ4 ዓመት ህፃን ሳለ ናጋጠመው ህመም ቀዶ ጥገና ለማድረግ በገባበት የሳኡዲ ሆስፒታል በተፈጠረ የህክምና ስህተት ላለፉት 12 ዓመታት ራሱን ስቶ የሆስፒታል አልጋ ቁራኛ ሆኖ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ታዳጊው በተኛበት የሆስፒታል አልጋ ላይ በአካሉ እያደገ ቢሆንም ላለፉት 12 ዓመታት መናገርም ሆነ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ አይችልም ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል በሳኡዲና በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ውስጥ በአይነቱ አዲስ ስምምነት ነው የተባለው ሁለቱን ሃገራት በኤሌክትሪክ ሃይል የማስተሳሰር ጉዳይ ሲሆን ለዚህም ጥናት እንዲጀመር መሪዎቹ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሣውዲ የሚያደርጉትን ጉብኝት ነገ አጠናቅቀው ወደ ሃገር ቤት የሚመለሡ ሲሆን በቀጣይም በጋምቤላና ነቀምት ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታ አልሲሲ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ግብፅን እንዲጎበኙ ትናንት ጥሪ ማቅረባቸውን አል ሃራም ዘግቧል፡፡ የግብፅ ፕሬዚዳንት አልሲሲ በዋናነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪውን ተቀብለው ወደ ካይሮ የሚያቀኑ ከሆነ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ውይይት ለማድረግ እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።

Read 7143 times