Monday, 21 May 2018 00:00

የዳንጎቴ ሥራ አስኪያጅና ባልደረቦቻቸው ገዳዮች እየተፈለጉ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

“ሥራ አስኪያጁ ለማምለጥ ሞክረው ነበር”

    ባለፈው ረቡዕ በጠራራ ፀሐይ በጥይት ተደብድበው የተገደሉት የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ህንዳዊው ዲፒ ካማራ ገዳዮች እየተፈለጉ ሲሆን ሥራ አስኪያጁ ከገዳዮቹ ለማምለጥ ሞክረው እንደነበር ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
በኢትዮጵያ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ የሽያጭ ገበያ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ታሪኩ ዓለማየሁን ማነጋገሩን የጠቆመው ብሉምበርግ፤ የሥራ አስኪያጁ፣ ፀሐፊያቸውና ሹፌራቸው ግድያ የተፈፀመው ፋብሪካው አጠገብ መሆኑን እንደገለፁለት ዘግቧል፡፡ በናይጀሪያ ሌጎስ የሚገኙት የዳንጎቴ ሲሚንቶ ዳይሬክተር ኢድዊን ዲቫኩማር በኢሜይል ለብሉምበርግ እንደገለፁትም፤ ሥራ አስኪያጁ ግድያው ሲፈፀምባቸው ሮጠው ለማምለጥ ሙከራ አድርገው ነበር፤ ገዳዮቹ የመኪናውን አሽከርካሪ በድንጋይ መተው አቅጣጫውን እንዲስት ባደረጉበት ወቅት ሥራ አስኪያጁ ከመኪናው ላይ ወርደው ሮጠው ለማምለጥ ሲሞክሩ ገዳዮቹ እግራቸውን በጥይት መተው ከጠሏቸው በኋላ በተደጋጋሚ ተኩሰው እንደገደሏቸው ገልፀዋል፡፡ ገዳዮቹ ሶስቱን ሟቾች በ15 ያህል ጥይቶች ደብድበው መግደላቸውን ቢቢሲ የአይን እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ የሥራ አስኪያጁ አስክሬን ወደ አገራቸው የተላከ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የግለሠቦቹ ገዳዮች በአፋጣኝ በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ያገኛሉ ብለዋል፡፡
የህንድ ኤምባሲ እንዳስታወቀው፣ በኢትዮጵያ የናይጄሪያዊ ቢሊየነር ንብረት የሆነውን ዳንጎቴ ሲሚንቶን ከአንድ አመት ተኩል በላይ ሲያስተዳድሩ የቆዩትና ባለፈው ረቡዕ አመሻሽ ላይ በጥይት ተደብድበው የተገደሉት ደፒ ካማራ አስክሬን ከትናንት በስቲያ ለቀብር  ወደ ሃገራቸው ህንድ ተልኳል፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ግድያውን በፅኑ አውግዞ በስራ አስኪያጁ ዲፒ ካማራ፣ በፀሃፊያቸው ወ/ሮ በአካል አለልኝና በሹፌራቸው አቶ ፀጋዬ ግደይ ላይ ግድያ የፈፀሙትን ወንጀለኞች በቁጥጥር ስር አውሎ ለፍርድ ለማቅረብ እየሰራ ነው ብሏል፡፡
ወንጀለኞቹን ተከታትሎ ለመያዝ ሠፊ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ የገለፀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት በበኩሉ የህብረተሰቡን ትብብር ጠይቋል፡፡
ግድያ የተፈፀመባቸው የስራ አስኪያጁ ፀሃፊ የሶስት ልጆች እናት እንደነበሩ ታውቋል፡፡
ዳንጎቴ ሲሚንቶ ከአካባቢው ማህበረሠብ ጋር የገባውን ውዝግብ በቅርቡ በሃገር ሽማግሌዎች አማካይነት በእርቅ የፈታ ሲሆን ደፒ ካማራ በአካባቢ ሽማግሌዎች “ገለታ” የሚል ስም ወጥቶላቸው እንደነበር ታውቋል፡፡

Read 6795 times