Sunday, 13 May 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)

 “ተጨማሪ የነፃነት ቀን!! ሌላ የባንዲራ ከፍታ!!”
              
    “መልዐኩ ባቦክን ጠራው”… ይላል የቮልቴር ተረት።
ባቦክም…. “አቤት” አለ፡፡
“ወደ ፔሪስ ፖሊስ ሂድ”
“እሽ…. ከዚያስ?”
“አውድማት” አለው፤ ወደ ከተማዋ አቅጣጫ እየጠቆመው፡፡
ባቦክም ከተባለችው ከተማ ደረሰ፡፡ ከተማዋ በሽቅጣለች፡፡ ህገ ወጥነትና ብልግና ነግሶባታል፡፡ ትሁት፤ ደግና ጨዋ ነዋሪዎችም ነበሩባት፡፡ ባቦክ ምን ማድረግ እንዳለበት አሰበ፡፡
የዛሬ ሳምንት ሚያዝያ ሃያ ሰባት፤ የድል በዓል ቀን ነበር፡፡ “ወድቃ የተነሳችው” ባንዲራ ከፍ ያለችበት!!...ወዳጄ፤ የነፃነት ዋጋ ውድ ነው፡፡ ስቲቭ ቢኮ፤ አብዲሳ አጋ፣ ቼጉቬራ፣ ደስታ ዳምጠው፣ ናታን ሃሌና ሌሎች ብዙ፣ በጣም ብዙ ሌሎች… ከከፈሉት ዋጋ በላይ!!
ነፃነትና ጦርነትን ስናስብ የማይነጣጠሉ እያደረግን፣ አንድ እንደሆኑ እያስመሰልን ነው፡፡ አንዳንዴ ልክ እንሆናለን፡፡ አንዳንዴ እንሳሳታለን። ሁለቱም ምክንያቶች አላቸው፡፡ ምክንያት ደግሞ የአእምሮ ብስለት መለኪያ ነው፡፡ ጦርነት ከሌለ ነፃነት አለ፤ ነፃነት ካለ ጦርነት የለም --- ስንል … በአጋዥ ሃሳቦች (Premises) ያልተደገፈ ግንዛቤ ወይም የሀሳብ ፍረጃ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን፡፡ ሀሳብ የግልና የጋራ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል!!
ጦርነት የጋራ ሀሳብ በሚሆንበት ጊዜ በጋራ የመሞት ዕድል አለ፡፡…ምክንያቱ ምንም ይሁን ምንም። ነጭና ጥቁር ተብሎ ልዩነት በግልፅ ካልተነገረ፣ ውጤቱም ውስጥ ቅዥት አይጠፋም፡፡ ነፃነት የጋራ ሲሆን እንደ ጦርነት “የ ጋራ ሞት” ውጤቱ ዝብርቅርቅ አይደለም። ዋነኞቹ የጋራ ጉዳዮች ጥቂት ናቸው። ለምሳሌ የአገር ሉዓላዊነትና ድንበር ማስከበር፤ ለባንዲራ ክብር መስጠት ወይም በዴሞክራሲያዊ ስርዓት መተዳደር ሊሆን ይችላል፡፡ ሀሳባችን ውስጥ የምናብላላው ነፃነት ግን እያንዳንዳችን በምንገኝበት የአኗኗር ዜይቤ፣ በፖለቲካ አመለካከታችን፣ በአገር ሃብት ላይ ባለን መብትና ተጠቃሚነት እንዲሁም በማህበራዊና የርስ በርስ ግንኙነታችን ይገደባል፡፡
ዞሮ፤ ዞሮ የነፃነትም ሆነ የጦርነት ሥራ ሀሳብ ሰው ነው፡፡ ሰው በሃሳቡ ይመዘናል፡፡ ሀሳብ ደግሞ ባሳቢው የማሰብ ዓቅም ልክ ይሰፈራል፡፡ አሳቢ ያመረተውን ሀሳብ ከስሜቱ ጋር ለማስታረቅ፣ አውጥቶና አውርዶ እሚበጀውን ይወስናል፡፡ የወሰነውን ነገር በጎም ሆነ ክፉ ‹ትክክል› ከመሰለው፣ ባለቤትነቱ ይፀናለታል፡፡ ይሄኔ ለራሱ ያጨበጭባል፡፡ ሀሳብ አላማ ሆነ ማለት ነው፡፡ ሰውየው አላማውን ስራ ላይ ለማዋል ድጋፍ፣ አመቺ ጊዜና አቅም ካላገኘ፣ እስኪመቻችለት ያቆየዋል። አጋጣሚ ሲሞላለት ከተኛበት ቀስቅሶ ያቆመዋል፡፡ ህልም ዕውን ሆነ! (dream comes true) እንዲሉ!!
ዓላማው፡- የውጊያና የጦርነት፣ የሃይማኖትና የእምነት፣ የስልጣንና የገዢነት፣ የክብርና የማዕረግ፣ የሃብትና የንብረት፣ የጥበብና የሳይንስ፣ የፍልስፍናና የርዮተ ሊሆን ይችላል፡፡
የዛሬው የኛ ሃሳብ፤ የነፃነት ቀናችንን ማስታወስ ነው፡፡ ሰውዬአችን ደግሞ ሞሶሎኒ፡፡ በእግረ መንገድ፤ የጅምላ ፍረጃን (Generalization) ስህተትነት መረዳት ነው፡፡… ሞሶሎኒ የፋሽስዝም ክህነት ተቀብሎ የደቆነው በልጅነቱ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የፈላጭ ቆራጭነት ምኞቱ፣ አገርን ጠቅልሎ የመጉረስ (totalitarianism) ቅዥቱ አእምሮውን አሳምሞታል። ስልጣን እንደ ጨበጠ ጦርነትን ለፋሺስታዊ ህመሙ ማስታገሻ ሊያደርገው ፈለገ፡፡ የራሱ ያልሆነውን የራሱ ለማድረግ፣ ነፃነትን በባርነት ለመተካት፣ ባረጀ ሀሳብ የተጫነ ጦር፣ ወደ አገራችን አሰማራ፡፡
አንዳንዶች የጊዜው መንግሥት በድሎናል በሚል ለበቀል ሲሉ ተባበሩት፣ አንዳንዶቹ በጥቅም ተታለሉ፣ አንዳንዶች በመገደድና አማራጭ በማጣት ከጎኑ ተሰለፉ፣ አንዳንዶች ፍልስፍናውን ወደው በወዶ ገብነት ታጠቁ፡፡ ቆራጦቹ ግን ተፋለሙት፡፡ በዱር በገደል እየተዘዋወሩ ወጉት፡፡ “እፎይ” የሚልበት፣ ትንፋሽ እሚወስድበት ጊዜ አሳጡት፡፡ ዕብሪተኛ፤ ምሱ ውርደት ነውና፣ ፋሽዝም የማታ ማታ ተዋረደ፡፡
ያገራችንን ፀሃይ የጋረደው ደመና፣ ቀስ በቀስ ተገፈፈ፡፡ ነፃነት ለባለቤቷ ተመለሰች፡፡ ሚያዝያ ሃያ ሰባት ብርሃን ወለደች፡፡ “ብርሃንም ሆነ!!” እንዲሉ!!
ሚያዝያ ሃያ ሰባትን ስናስብ፣ ሲልቪያ ፓንክረስትንና ጓደኞቿን፣ እነ ሳቤሪዮ ስፔሬሎን፣ የኩባ የቼክና የሌሎች ብዙ ሀገራት ዜጎች፣ ከጎናችን ሆነው የተዋደቁትን ሁሉ እናስባለን፡፡ ዲትሮይት በወዶ ዘማችነት የተመዘገቡ፣ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ወንድሞቻችንን እናስታውሳለን፡፡ ሚያዝያ ሃያ ሰባት የነሱም ናት!!
ወዳጄ፡- በጦረኞችና በእብሪተኞች ጭንቅላት ውስጥ በተፈጠሩ ሀሳቦች ትላልቅ ስልጣኔዎች ተንደዋል፡፡ አላስፈላጊ ጦርነቶች፤ከጊዜ ወደ ጊዜ እያወቀና እየሰለጠነ የመጣውን የሰው ልጅ እየደጋገሙ ወደ ኋላ መልሰውታል፡፡ ችግርና መከራ እንደ ተጫነው፣ እንዲኖር አድርገውታል፡፡… አማልክቶቹ ሲስፐሰን እንደቀጡት!!
“War reduced man again to his beginnings; like sysiphus, civilization has repeatedly neared its zenith only to fall back into barbarism and begin `decapo` its up ward travail” በማለት ዱራንት ያረጋግጥልናል፡፡
ታላቁ ቺ ቸሮ ደግሞ ማናቸውም ዓይነት ጦርነት ያንገፈገፈው ይመስላል፡፡ “ተገቢና ትክክለኛ ከሚባለው ጦርነት፣ የማይረባ ሰላም ይሻላል” (I prefer the most unfair peace to the most righteous war) በማለት ይሞግት ነበር፡፡ ክብራቸውንና ነፃነታቸውን የሚያስቀድሙ ወገኖች ግን አልተቀበሉትም፡፡… የጦርነት ጥሩ ባይኖርም ለነፃነት ከመዋጋት የሚበልጥ ክብር የለም ብለውታል፡፡ ይህንኑ ሃቅ እኛም ለሞሶሎኒ በደማችን ፅፈንለታል፡፡
ሞሶሎኒ በፎከረበትና በአቅራራበት መንገድ፣ ተመርቆ በተሸኘበት አደባባይ፣ በራሱ ፓርቲ አባሎች ተዘቅዝቆ እንዲሰቀል ያስፈረደበትም፣ ይኸው እውነት ነው፡፡ የገዛ ወገኖቹና ምልምሎቹ፣ በአሮጌው ሀሳቡ ጠቅልለው፣ ወደ መቃብሩ ወርውረውታል፡፡
ወዳጄ፡- ሁሉም ጣሊያን ፋሽስት አይደለም። አንድ ነገር ልብ በልልኝ! ሁሉም ፋሽስት ክፉ አይደለም። ፋሺዝም ሀሳብ ነው፣ የፓርቲ ፍልስፍና ነው፡፡ ሀሳብ በተሻለ ሀሳብ፣ ፍልስፍናም በፍልስፍና ይለወጣል፡፡ ሀሳብን መቀየር መብትም ስልጣኔም ነው። ቀኖናዊነት ድንቁርና ነው፡፡ የአንድ ፓርቲን ሰዎች በአንድ ሀሳብ ጠቅልሎ መፈረጅም ተገቢ አይደለም። በውስጣቸው ታርመው የሚቀኑ የህዝብ ወገኖች አሉ። አዲሶቹ አሮጌዎቹን፣ በአሮጌ ሀሳባቸው ገንዘው፤ የገዛ ጎራዴያቸውን ቀምተው እንደነ አቲላ ዘሃን፣ እንደ ሞንጎሊያው ጂንጅስካን ወይ እንደ ግብፅ ፈርዖኖች በታሪክ ሙዚየም ያኖሯቸዋል፡፡ ያለንበት ዘመን አዲስ ነው፡፡ Nuclear Era!!... አዲስ ሀሳብ ያስፈልገናል። ሚያዝያ ሃያ ሰባትን የምናከብረው የአዲስ ቀን መጀመሪያ፣ የባንዲራችን ከፍታ በመሆኗ ነው!!...ሌላ ተጨማሪ የነፃነት ቀን ያስፈልገናል፡፡ ተጨማሪ የባንዲራ ከፍታ እንሻለን!!
* * *
ወደ ተረታችን ስንመለስ፤ ባቦክ ስለታዘዘበት ጉዳይ ሪፖርት ለማድረግ ወደ መልዐኩ ተመለሰ፡፡
“እህሳ?”
በታወቀ ጠቢብ አሰርቶ ያመጣውን ማሰሮ ሰጠው። ማሰሮው ወርቅና አልማዝን ጨምሮ ከሁሉም ዓይነት የድንጋይና የብረት ንጥረ ነገሮች የተሰራ ነው፡፡ ሁሉም ከአንድ አፈር፣ ከአንድ መሬት የተገኙ ናቸው፡፡
“ስበረው!” አለ ባቦክ፡፡ መልዐኩ የያዘውን ማሰሮ መረመረ፡፡ ፔረስ ፖሊስን ማውደም፣ መልካም ነገሮቿን ማውደም መሆኑን ተረዳ፡፡ “የጅምላ ፍርድ (Generalization) ተገቢ አይደለም” ሲል አሰበ፡፡
በነገራች ላይ `ሚያዝያ ሃያ ሰባት` የተማርኩበት ት/ቤት መጠሪያ ነው፡፡ እግረ መንገዴን ባስታውሰው ምን ይለኛል? (ታሪካዊ ት/ቤት መሆኑም አይደለም!)
ሠላም!

Read 1119 times