Sunday, 13 May 2018 00:00

ለባለጁ (ጠይቡ) ፍትህ እና ነፃነት!

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

(ከ1ኛ - 3ኛው ችሎት / The Third Court)
               

    እንቆቅልሽ/ህ
‹‹ብላ በአፈ ገጽከ››ን ገድፎ
ጠቢብ ወገኑን እሚረግም ረጋ  
ረጋ ሰራሽ አጥር ተደግፎ
ሰዳቢ ኗሪውን ላቡን አንጠፍጥፎ
ያ ምድር የማነው
ከዓለም ጭራ ተሰልፎ
የሚጠወር እጁን አጣጥፎ?!
ሀገር ስጠኝ . . . ?
ፍትህ፤ ሲሰምር፤ በአብሮ መኖራችን ውስጥ ለሚደነቀሩ የትየለሌ ተግዳሮቶች ሁሉ ቁልፍ። ምናልባትም የዓለሙ ሁሉ መከራ መክያ፡ የማህበራዊ መስተጋብራችን መንኩራኩር መላወሻ ሀዲድና የሰው ልጆች እኩልነት መረጋገጫ፣ የእውቀት ጥግ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፡፡ ወደ የሰው ልጆች የነጻነት አጽናፍ መሸጋገሪያ ድልድይ፡፡ ነፃነት፤ ሰላምና እረፍት ነው፡፡ ከባርነት ‹‹እስራት›› የመፈታት መልካም ዜና። ከአካልም ሆነ ከስነ ልቦና ወህኒ መላቀቅ ለስጋም ለነፍስም ደስ ያሰኛል፡፡ ታዲያ፤ እንደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለች የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት የነበረችና በድንገት ዘመናት መሀል ላይ ከትናንት ወደ ነገ መሸጋገሪያ ድልድዩ የፈረሰባት/የተሰወረባት ምድር፤ ካንቀላፋችበት ነቅታ ዳግም ለእድገት የምትታትር ሀገር፤ ዜጎቿ ከተቀፈደዱበት የኋላ ቀር አመለካከት እስረኝነት ነጻ ካልወጡ፣ የነባሩ አስተሳሰብ ደዌ ሽባ ያደረገው ሕዝብ፣ ሙሉ ለሙሉ ነፃ ሕዝብ ነን ለማለት አቅም አይኖረውም። የህሊና ባርነት ሰንኮፉ ላንዴው ካልተነቀለ በቀር፤ ተደብቆ ይቆይ እንጂ፤ የተጣባው ልክፍት ድንገት እያገረሸ ሊያስጓራ እና እንደ ፊጋ በሬ ምስኪናኑን በግፍ እየወጋ ሊገድል አሊያም ክፉኛ ሊያቆስል ይችላል - አንድም በአካል፤ ወይም የበደል ምርቅዙ እየመዘመዘ፣ እህህ! በሚያሰኝ ድኖ በማይድን የስነ ልቡና ቁስል፡፡ ከከረመው የባርነት ቀንበር አላቅቆ፣ ሰንሰለቱን በጣጥሶ አርነት እሚያወጣ አንዳች የወል ኃይል፤ ቻይናዎቹ Cultural revolution ብለው የፈጸሙትን አይነት ህመማችንን/እብደታችንን አገናዝቦ፣ በልካችን ተመጥኖ (dosage) እሚወሰድና እሚያሽረን ፍቱን ኮሶ ያሻናል፡፡ ያኔ ዜጎች ከእስራታቸው ተፈትተው ነጻ ሰው ይሆናሉ፤ አመለካከታቸውም የሰውን ዘር ሁሉ በወል ዓይን በሚያይ ጤናማና የጋራ ነጻ አስተሳሰብ ውብ ዜማ ይቃኛልና . . .
መሰረቱ
የህይወት ግንድ - ስር
አብሮ የመኖር ምስጢር
የጥንድ ሀብት የጋራ እድር
.       .       .      ፍቅር ፡፡
የአንድ ሀገር ዜጋ እንደ ዳር ድንበሩ መከበር አብሮም በኋላ ቀር አመለካከቶች ከተጠፈነገ ማንነቱ እስረኝነት ተላቅቆ፣ የህሊና ነጻነትን ክብር Consciousness ሲቀዳጅ፤ በምድሩ ላይ ሁሉንም ያማከለ አንድነት፣ ያልተገደበ የእርስ በርስ ግንኙነት፡ ንጹህ ፍቅርና የወል ሰላም ይሰፍናል፡፡ መንፈሳዊ ጸጋውን ከቃተተም እርግማኑን ሰብሮ በረከትን ይቀዳጃል። ሰው ከዘርፈ ብዙ ‹‹እስራቱ›› ሲፈታ በምድርም በሰማይም ደስታ ይሆናልና፡፡ የተኮደኮደበት ቀንበሩ ተሰብሮለት፡ የተከረቸመበት እግር ብረቱ ወልቆለት፤ ተነጥሎ ከከረመበት ግዞት፡ታፍኖ ከሰነበተበት አዘቅት ወጥቶ የነጻነትን አየር መተንፈስ ሲጀምር፤ በምድር፡ ሰው ከናፈቃቸው ቤተሰቡና ወዳጅ ዘመዶቹ ጋር ሲገናኝ ብስስራት ነው፡፡ ለንስሐ ሲበቃ፣ ከኃጢአት እስራቱ ሲፈታም እንዲሁ፤ የወንጌሉ ቃል በምሳሌ እንደሚያስተምረን . . . መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፥ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል፡፡ ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላቸዋል። እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።  . . .
ማዘዝ ቁልቁለቱ
ስበር ስልህ ስበር! ብረር ስልህ ብረር!
ተኩስ ስልህ ተኩስ! ግደል ስልህ ግደል!
ለሙሴ የተሰጠሁ - አሮን የተረከኝ፤
የኦሪት ህግ ነኝ - ሀዲስ እማያውቀኝ!
                     (ለአንዳንድ አለቆች)
የምድራዊውን ሰው ፍረጃና ፍርድ በተመለከተ . . .
ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘችን ሴት ወደ እርሱ አመጡ በመካከልም እርሱዋን አቁመው መምህር ሆይ፥ ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች። ሙሴም እንደነዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዘዘን፤ አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ? አሉት።የሚከሱበትንም እንዲያገኙ ሊፈትኑት ይህን አሉ። ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ፤መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ። ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው። ደግሞም ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ። እነርሱም ይህን ሲሰሙ ሕሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንድ አንድ እያሉ ወጡ፤ ኢየሱስም ብቻውን ቀረ ሴቲቱም በመካከል ቆማ ነበረች። ኢየሱስም ቀና ብሎ ከሴቲቱ በቀር ማንንም ባላየ ጊዜ። አንቺ ሴት፥ እነዚያ ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? የፈረደብሽ የለምን? አላት።እርስዋም፦ ጌታ ሆይ፥ አንድ ስንኳ አለች። ኢየሱስም፦ እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ አላት።
ያመንዝራዋ ሴት ድንጋዮች
. . . . . . . . . . . . . . . .
አፈሩ ልባችን ላይ ... ጽፎብናል
በ‹‹ሂጂ ወደ መሰሎችሽ›› ቀላቅሎናል
እና ማ ማንን ለምን ያገልላል?
ህእ!!!
ከውድቀት የሚነሳው የሰው ዘር ታሪክ ከኦሪት ጀምሮ በዚሁ በእስራት/ባርነት እና የነጻነት ገድል የተዘመዘመ ይመስላል፡፡ ለዚህም ይሆናል የጥንቱ ዓለም ታሪክ ጸሐፊያኑ፤ ነፃነትን በሚቃትት የላቲን ቋንቋ፤ Fiat justitia, ruat coelum ‹‹ፍትህ በምድር ከተፈጸመች፤ መንግሥተ ሰማይ ትወርዳለች›› ማለታቸው፡፡ (በዘወትር ጸሎታችን ‹‹አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፡፡›› ብለን እንደምንለማመነው፡፡ ‹‹እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፤ በደላችንን ይቅር በለን›› የምትለዋን ሀረግ በቀላሉ አነብንበናት ስናልፍ ግን ‹‹እውነት?›› ብዬ ላፍታ እደመማለሁኝ፡፡) ከዘመናት በኋላ እጹብ ድንቅ ባለቅኔ ሆኖ የተፈጠረው ሚልተን Milton ደግሞ Justice with mercy ይለዋል - ፍትህ ከምህረት ጋር ሲሰፍን። በነገራችን ላይ፤ እንግሊዛዊያኑ ‹‹አንደኛው ያገራችን ገጣሚ ማን ይመስልሀል? ይሉህና - ሼክስፒር ነዋ! ስትል፤ አይደለ...ም ጆን ሚልተን ነው እንጂ! ብለው ይመልሳሉ አሉ፤ እህ! ሼክስፒርሳ?! ስትላቸው - እርሱማ የመላው ዓለም ነው!!!››፡፡
ቦረቦር
የዘር ሰባራ ለሚያሸትቱ  ፍትህ ከዙፋኑ ወርዳ
አጋርንም  ይመልሳታል  ባሪያዋ ስትሄድ ተሰድዳ፤
ሣራም  መካን ሆና ላትቀር  ዘሯ ይቀጥል ዘንድ ወልዳ፡፡
.       .       .
እንደ ነቢዩ ኤርሚያስ  ወደ ሸክላ ሠሪው ቤት ጉዞ
ሰውን በአምላኩ እጅ እንዲያይ ፥ ሸክላን በሠሪው እጅ ተይዞ፤
ፍጡሩን ከአፈር ባበጀው በሰማይ አምላካችን ታዝዞ፡፡
ብቃቱን በግልጥ ያሳየህን ዜጋህን ከፍ ከፍ አድርጎ ማክበር ይሉሀል እንዲህ እንደ እንግሊዞቹ ነው፡፡ እንኳንስ ለ1ሺህ 625 ዓመታት ጠፍንጎ ካንበረከከን ከእስክንድርያ እግረ ሙቅ የመንበረ ማርቆስ ፍትሐ ነገሥት ‹‹ኢትዮጵያ የራሷን ሊቅ አትሾምም››፤ ተብታቢ ሕግ የቀረ በሚመስል የድንቁርና አመለካከት ዛሬም ድረስ ተሸብበን ‹‹እየተቧደንን - ያገለገሉንን እያገለልን - ያዳኑን እያደንን››  ቁም ስቅላቸውን ልናሳያቸው ይቅርና! . . . ለምሳሌ፤ እንደ . . . ለሺህ አመታት እምንኮራባቸውንና በዓለም ዙሪያ ስማችንን በአድናቆት ያስጠሩልንን የአክሱም ሀውልት፣ የፋሲለደስ ግምብ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ጢያ ድንጋይ ትክል፣ ኮንሶ ሀውልት . . .ወዘተ. ቅርሶቻችንን ተጠብበው ያነጹልንን፤ ጥንታዊ ታሪካችንን ብራና ፍቀው የደጎሱልንን፣ ለሦስት ሺህ አመታት ተቆራኝተናት እምንኖረውን እስትንፋስ ማስቀጠያችንን አንዲቷን ማረሻችንን፣ ሞፈር እና ድግሩን፣ ምጣድ፣ ድስት እና ጀበናችንን፣ መኖሪያ ታዛችንን፤ መዋቢያዎቻችንን  የሀገር ልብስ የጥበብ አልባሳቶቻችንን፤ ጉትቻና ድሪ ሀብልና አምባራችንን፣ የነጋዴውን መጫኛ፡ የከብቶቹን መራቢያ፣ የፈረሱን ኮርቻ፣ የቤተ መንግሥታቱን አንጡራ ቅርሶችና የቤተ መቅደስ ንዋየ ቅዱሳቶቻችንን፤...አረ ስንትና ስንቱን (ዛሬ እንዲህ በዘመናዊ ቁሳቁሶች ሳንንበሻበሽ በፊት) የእለት ተእለት መጠቀሚያ ቁሳቁሶቻችን ሁሉ! . . . ከምንም በላይ ደግሞ አገራችን ኢትዮጵያ በታሪክ ዘመኗ ሙሉ እንዳትደፈር፣ በሉዐላዊነት ታፍራና ተከብራ ትኖር ዘንድ በየጊዜው የተቃጡትን ወረራዎች ለመመከት ያስቻለውንና በተለይም በጀግኖች አያቶቻችን የአይበገሬነት ጀብድ ዘወትር ለምንኩራራበት (በባርነት ጨለማ ይዳክሩ ለነበሩቱ ለአለም ጥቁር ሕዝቦችም ሁሉ የነጻነት ቀንዲል ብርሃን ለፈነጠቀው) የአድዋ ጦርነት እፁብ ድንቅ ታሪካዊ ገድል፤ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን ወራሪ ጠላት ድል ለማድረግ ኢትዮጵያዊያን ዘማቾች በጦሩ አውድማ የታጠቁትን ጋሻና ጦር፣ ሰይፍና ጎራዴ . . . ወዘተ. የሰሩልንን - እሚሰሩልንን ባለጅ/ጠይባን ዜጎቻችንን፤ ክብር መስጠት ቢሳነን ጭራሹኑ ‹‹በቃ እንዲሁ ሳይህ የዓይንህ ቀለም አስጠላኝ!›› ወይም ‹‹ከቶ ስለምን እንዲህ በጣም ቻልክ?!›› በሚመስል አጉል ጠባይ፣ ልናከብራቸው ሲገባ በከንቱ ውንጀላ እያሳቀቅን እንደምንወቅስ፣ እንደምናረክስ፣ እንደምንከስሳቸው ያገራችን ባለጆች . . .
ቅጥቀጣ
አንተ ለገበሬው ማሳ ማረሻውን ትቀጠቅጣለህ፤
በመሀል በላተኛ!
ገበሬው በንቀት፤ አንተ በዘር መድልዎ፤
ትቀጠቀጣለህ!
ይሁን . . .
ከወራት በፊት በሰሜን ሸዋ ኢጂሮ ነዋሪዎች ባለጅ ዜጎቻችን ላይ የደረሰው የጅምላ ግድያ ሙከራ፣ ማሳደድ፣ በሌሊት የቤት ቃጠሎና ከመኖሪያ ርስት መፈናቀል፤ ከሁለት ወራት በፊት አዲስ አበባ ከተማ ቀጨኔ መንደር ውስጥ የመቀበሪያ ስፍራው አወዛጋቢ ሆኖ የነበረውንና የጉዳዩ አነጋጋሪነት በውጪ ሀገራት/እስራኤል . . .የዜና መገናኛዎች የተዘገበውን የይሁዲ እምነት ተከታይ የነበረውን የሸክላ ስራ ባለሙያውንና ሰአሊና ቀራፂ አሳልፍ ተከተልን፣ የህልፈት አጋጣሚንም ጨምሮ (በባለጅነት ሙያቸውና አንዳንዶቹንም በአያት ቅድማያቶቻቸው ነባር እምነት የአይሁድ ኃይማኖት ተከታይነታቸው እሚደርስባቸው ግፍ ማሳያ) የቅርብ ጊዜ አጋጣሚዎችን እዚህ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሌላውም፤ ባሳለፍነው የሚያዚያ ወር መጀመሪያ ሳምንት፤ ኢቲቪ በዜና ሽፋኑ ካነጋገራቸው የጎንደር ባለጆች መካከል አንዱ ቀጥቃጭ ማረሻውን እያወዛወዘ ‹‹ይህቺን ሰርተን እስክንሰጣቸው ይለማመጡንና እጃቸው ካስገቡ በኋላ ግን በሌሊት መጥተው ጥቃት ያደርሱብናል!›› ብሏል በገሀድ፡፡ ‹‹የአውሬዎች እንኳ መብት በተከበረበት በዚህ ዘመን!›› ብሏል ሌላኛውም ምስኪን ጠይብ፡፡ በበኩሌ፤ በዚያ ሆድ የባሰው ቅሬታ ባዘለው በወጣቱ በሀዘን የሚያባባ የፊት ገጽታ ላይ የሚነበበው ጥልቅ ስሜትና ‹‹በዚህ ዘመን!›› አባባሉ ‹‹አባቶቻችንስ እሺ ያለእዳቸው ሲሰቃዩ ኖሩ፤ እኛም በሰማእታት ታጋዮች የተጎናጸፍነውን/የተባልነውን ሕገ መንግሥቱ የሰጠንን የዜግነት መብት፣ የህግ እኩልነት፣ የኃይማኖት ነጻነት...ወዘተ ከቶ እንዴት እንነፈጋለን?!›› የሚል በቁጭት እሚያንገበግብ ዘመኑን እሚያጠይቅ መልእክት ነው ያስተላለፈልኝ . . .
እንቆቅልሽ - ጢቅታ
‹‹ማሳ ማረሻህን፤ መኖሪያ ቤትህን
ምግብ ማብሰያህን፤ እርቃን ልባስህን
መዋቢያ ጌጥህን ደክሜ እሰራለሁ፤
ላንተ ቀድሜ ባውቅ ‹‹ብልህ›› ነኝ አምናለሁ
በላኸኝ ካልክ ና! እተፋብሀለው!››እ
እናም እንግዲህ፤ በዚህ መልኩ ላለፉት ሺህ ዘመናት ሰራተኛ ወገኖቻችንን በገፋናቸው መጠን፤ አክብረን ባንንከባከባቸው እንኳ የዜግነት ነጻነታቸውን ባንነፍጋቸው ብቻ፤ በምርታማነታቸው የበለጠ መጠቀም፤ ሙያቸውን ከባህላዊ - ወደ ጎጆ ኢንዱስትሪ ማሳደግ ሲቻለን፤ ከዜጎች ትጋት ማግኘት ሲገባን በምናጣቸው የልማት ግብዐቶች እየተጎዳን፤ እያሳለስን ለባእዳን እርጥባን እጃችንን እየዘረጋን፤ በአለም ላይ በሚሰጣው የተረጂነት አጉል መልካችን ውሎ አድሮ ለመቆጨት፡፡ ወሩ ግንቦት ነውና አንድ የቀድሞ ቁጭት ከ‹‹የቀድሞው የግንቦት ሰው›› ቆንጥረን እንዋስ . . . ‹‹ጥንት አክሱምን፡ላሊበላን፡ፋሲል ግምብን የሰራን ሕዝቦች፤ ዛሬ አክሱም ሀውልት ከተወሰደበት ተመልሶ ሲመጣ መልሰን መትከል አቃተን!›› የቀ.ቀ.የኢ.ፌ.ዴ.ሪ.ጠ.ሚ/ር መለስ ዜናዊ - የነጻነት ታጋይ፡፡
(እኮ!!! ጥቂት ዓመታት አስቀድሞ፤ በዋዜማው፤ በሀውልቱ መምጣት ዜና መነሻ የተቋጠረው ስንኝ ይኸው . . .ነቢይ መኮንን ነቅሶት ነበር ከመጽሐፍ በፊት እዚሁ ጋዜጣ ላይ ሲታተም . . .)
የቅድማያቶች መስተዋት
አክሱም ተመልሶ ሊመጣ? እሺ ቤት ለእምቦሳ ይምጣ፡፡
የትናንት አያቶችን ህልም ፤ የጥጋብ ዘመንን ትልም
የጥበብ ቆሌን ከጠራ የጥበብ አድባርን ካመጣ፤
ግና በትናንት ክህሎት በታሪክ ትውፊት መሰረት
ላለፈ ውበት መልካችንን ሆኖን ራስ - ማያ መስተዋት
እኛኑ ካልመዘንንበት - ነጋችንን ካላየንበት
ለእንቅልፋም አዝጋሚ ጉዞ  የ‹‹ነበርንኮ›› ወግ ጥረቃ
ዛሬያችንን አዘናግቶ አሁናችንን ካሳጣ
ወቅሶ ካላባነነን ለምና ሌላ ‹‹እንቅልፍ›› ይምጣ!
ይህን ኢትዮጵያዊያን ባለጅ ዜጎቻችንን፤ የሲቃ ሰቆቃ ህይወት እንዲገፉ አፍኖ አስሮ ያኖረውንና ዛሬም ድረስ የቀጠለውን፤ ለረዥም ዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን አጉል አመለካከት ለማስቀረት፤ ከ120 ዓመታት በፊት፤ ለሀገር እድገትና ስልጣኔ ታላቅ ጥረት አድርገው ባለፉት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በእምዬ ምኒልክ የታወጀ ‹‹ሠራተኛውን በሥራው የምትሰድብ ተወኝ፡፡›› የሚል አዋጅ ታውጆ  ነበረ . . .
‹‹ከዚህ ቀደም ብረት ቢሠራ ጠይብ፡ ሸማ ቢሠራ ሸማኔ፤ ቢጽፍ ጠንቋይ፤ ቤተ ክርስቲያን ቢያገለግል ደብተራ እያላችሁ፤ አርሶ ነጩን ከጥቁር አምርቶ የሚያገባውን አራሽ ከዘውድ ይበልጣል የሚባለውን ገበሬ እያላችሁ፤ ነጋዴን ነግዶ ወርቁን ግምጃውን ይዞ ቢገባ አንተ ነጋዴ ገጣቢ እያላችሁ፤ በየሥራው ሁሉ ትሳደባላችሁ ልጁ ምናምን ሥራ የማያውቀው ሰነፉ፡ ብልሁን እየተሳደበ አስቸገረ፡፡ ቀድሞም ይህ ሁሉ ፍጥረት የተገኘው ከአዳምና ከሔዋን ነው እንጂ ሌላ ሁለተኛ ፍጥረት የለም፡፡
ይህ ሁሉ ካለመማር የተነሣ ነው፡፡ አዳምንም ብላ በአፈ ገጽከ ብሎታል፡፡ይህ ከቀረ ሁሉ ቦዘንተኛ ከሆነ መንግሥት የለ፤ አገር የለ፡፡በወዲያ አገር ግን በኤሮፓ ሁሉ አዲስ ሥራ አውጥቶ መድፍ፡ ነፍጥ ባቡር ቢሠራ ሌላውንም እግዚአብሔር የገለጠለትን ሥራ ሁሉ ቢሠራ መሐንዲስ እየተባለ እየተመሰገነ ሠራተኛውም ብዙ ይጨመርለታል እንጂ በሥራው አይሰደብበትም፡፡እናንተ ግን እንዲህ እየተሳደባችሁ አገሬን ባዶ ልታደርጉትና ልታጠፉት ነው፡፡እንግዲህ ግን እንዲህ ብሎ የተሳደበ እኔን የሰደበ ነው እንጂ ሌላውን መስደብ አይደለም፡፡ . . . (ጥር07 ቀን  09) ዓ.ም - አጤ ምኒልክ - ከጳውሎስ ኞኞ - ገጽ 238/39)
ምዝ
ሸማኔ አማከረኝ
ተስሎ ይዞ ምስሏን፤
ማተብ ክር ያንገት እምነቷን
ብጣሽ ክር ገሀድ እውነቷን፤
‹‹አንተ ቀሚስ ስራ ፤ እኔ መቀነቷን
የጋራ ‹ሀገራችን› ቀረች ራቁቷን፡፡››
እንዲሁም፤ ከመቶ ሰባት ዓመታት በኋላ በዚህ ዘመን፤ ሌላኛው ‹‹የግንቦት ሰው›› የነጻነት ታጋይ በረከት ስምኦንም፤ የ1997ቱን የሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ በጻፉት ‹‹የሁለት ምርጫዎች ወግ - ዳናን የገታ አገራዊ ሩጫ›› በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ገጽ 200 ላይ፤ ስለነዚሁ ባለጅ ወገኖቻችን ቀጣዩን ትውስታቸውን አስፍረዋል . . .
‹‹ባደግኩባት የጎንደር ከተማ በልጅነቴ ይነገር የነበረ አንድ አጉል እምነት ይታወሰኛል፡፡ የጅብ ቆዳ በ‹‹ቡዳ ከመበላት›› ይከላከላል የሚል፡፡ ድሮ ድሮ አንጠረኞች ከፋ በደል ይፈፀምባቸው በነበረበት ዘመን፣ ለስራው ንቀት የነበራቸው ፊውዳሎች በዚህ ሙያ የተሰማሩ ወገኖችን ሁሉ በእጅጉ ዝቅ አድርገው ይመለከቱዋቸው ነበር፡፡ አንጥረኞቹን ከሰው ዘር ያልተፈጠሩ በማስመሰል የማይሰጡዋቸው ስያሜም አልነበረም፡፡ አለፍ ሲልም ቀን ሰው ሌሊት ደግሞ ጅብ እንደሚሆኑ፤ ሰውን እንደሚበሉ፤ ስለዚህም የሞተ ጅብ አግኝቶ ከቆዳው ጥቂት ቆርጦ የያዘ፤ ወይም ደግሞ በክታብ መልክ አንገቱ ላይ ያሰረ ሰው ፈፅሞ በቡዳ እንደማይበላ ይሰብኩ ነበር፡፡ የፊውዳሎቹ ኋላ ቀር አስተሳሰብ በወቅቱ በላይነት የነበረው በመሆኑ፣ ህብረተሰቡም ንቀቱንና ጥላቻውን ከመጋት አልፎ የሞተ ጅብ በተገኘ ቁጥር ከቆዳው ለመሻማት ይራኮት እንደነበር ይነገራል፡፡ በእርግጥ ሲራኮት በዓይኔ ባላይም፡፡››
እኛ ግን ሰሞኑን እንኳ ኮንደሚኒየም ደረጃ ላይ የተገኘ ጅብ፤ በምን መልኩ ቅርጫ እንደተደረገ በፌስ ቡክ ገጽም አይተናል፡፡በልጅነታችንም አፋችንን ይዘን በታላቅ መገረም፣ በሩቁ ስላየን ነበር፣ የትዝብት ስንኝ የቋጠርነውም . . .
ኩኩ መለኮቴ
አንድ ቀን ጅብ ሞቶ ሰዳቢዎች ሰፈር
ስጋውን ሲሻሙ ብልቱ ሲመተር
ለቡዳ መድኃኒት ይሆናል እያሉ
ከበርበሬ ጋራ ፈጭተው ይበላሉ
ጅብን እየበሉ ሰውን ጅብ ይላሉ፡፡
ኩኩ መለኮቴ እሷ በበላችው
ኩኩ መለኮቴ . . .
ትውስታቸውን ስላጋሩን ምስጋናችንን እያቀረብን፤ የዴሞክራሲ ብርሃን በፈነጠቀልን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ውስጥ አድገን እዚህ የወገናችንን ብሶት የሚያንፀባርቅ መልእክት ስንጽፍ፤ ይህን ዘመን ላወረሱን (ከእነ ችግሮቹም ቢሆን) ለሰማእታቱ ታጋዮች ያለንን ላቅ ያለ ክብር በመግለጽ ነው፡፡ እናም ታዲያ በ21ኛው ክ/ዘመን ላይ በሉላዊ አስተሳሰብ Global thinking በሚዘወር ዓለም ሆነን፤ ይህ ለአመታት መቋጫ ያጣው የባለጁ ወገናችን ጉዳይ፤ የአንድ ሀገር ዜጎች ሆነን ሳለን፤ ግን፤ በቃ ልክ እንደ ‹‹የሁለት ፍጥጫዎች ውግ›› ከቋጥኝ ገዝፎ የከበደ ሸክም መሆኑ ቀጥሏል፡፡ እንዳደጉበት መንደር፤ ከገጠሩ ነዋሪዎች ተወልዶ ወደ ዋና መዲናችን በመጣው የባለጁ አሉታዊ ፍረጃ፤ የጠይቡን ኑሮ በመሸበብ፡ ውብ እድሜ ዘመኑን መከራ እያነከተው ዓመታቱ ቢነጉዱም፤ እንኳንስ ፍትሀዊ፡ ዘላቂ፡፡ እረፍት ሰጪ፡ ነጻነቱን ሊያቀዳጅ የሚያስችለውን ተስፋ ፈንጣቂ መፍትኄ ሊያገኝ፤ እውነተኛ ፍትህን ሊጎናጸፍ ቀርቶ፤  ‹‹?ናን የመታ ከተማዊ ጡጫ›› ነት የደረሰ፤ ብዥታና ግራ መጋባት ያጠላበት፡ የባይተዋርነት ሀዘን ያረበበበት . . . ወዘተ. ‹‹*ያሁያ››፡፡ የታታሪው ባለጅ እና ምስኪን ጠይብ ወገኖቹ ዘመን ያስቆጠረ የ‹ሆድ ካገር ይሰፋል› ትእግስት፤ ጥልቅ ትዝብት እና በዝምታ የተለጎመ ምላሽ መልክም፤ (ስንኝ እና ሀሳብ እያሰናሰልን ነውና) በትግል ዘመን እንደተጻፈው ተወዳጁ ግጥም አርእስት - ‹‹መቸስ ምን እንላለን›› የሚል ይመስላል፡፡
እንቆቅልሽ - አጥሩ
ሀገር እንድታድግ መቼ ተባብረናል
በእጅ ያለ ወርቅ ሆነን አጥር ቆሞልናል
በእምነት ደቁሰው አሽቀንጥረውናል
ከአመት አርባ ሳምንት በዐል አርገውልናል
የጦቢያን ‹‹ጠቢባን›› ቡዳ ብለውናል፡፡
(በደስታ ተክለወልድ መዝገበ ቃላት ፍቺ - ጠይብ - ባለጅ፡ ቀጥቃጭ፡ ብረት ሰሪ፡ ሸክለኛ፡ አንጥረኛ፡ ሸማኔ፡ ፋቂ፡ ዐራቢ፡ አናጢ፤ ትርጓሜው ብልህ፡ ፈላስፋ፡ ስራን ሁሉ አዋቂ ማለት ነው፡፡ በብሉይም ጥበብና እውቀት ማስተዋል የመላባቸው ባስልኤልና ኤልያብ ሌሎችም ነበሩ . . .በስራ ፈቶች ዘንድ ግን ጠይብና ቡዳ የስድብ ስም ነው፡፡ ሸክላ ቧጣጭ፡ ብረት አዝባጭ፡ቁቲት በጣሽ፡ ጠፈር ነካሽ ይሉታል፡፡ወንጀልን እይ፤ያማርኛ ገበታዋሪያን ተመልከት፡፡ ባረብኛም ጠይብ ይን አጥብቆ ደግ ማለፊያ ማለት ነው፡፡
እንቆቅልሽ - አጥሩ
‹‹ሰው በበላንማ በቻለ አንጀታችን
እናደርገው ነበር መንግሥቱን በጃችን፡፡››
እንድታድግ ሀገር አባይ እንዲከተር፤
ሰው መብላት አሳዩን? ወይ እንተባበር?
ብቻ ‹‹አጥሩ›› ይሰበር!››እ
ሀገር ስጠኝ . . . ?
ለዚህም ይሆናል፤ የሰው ልጆች በነፃነትና እስራት/ባርነት ጉዳይ ላይ፤ አስቀድሞ እግዚአብሔር፤ ከአንድያው ውኃ፡ ጠፈሩን ሦስት ቦታ ከፍሎ፡ ሰማይ፡ የብስ፡ ባህር ብሎ እንደጠራው ሁሉ፤ የሰው ልጅም በታሪክ ዘመኑ ከተ/ሚመላለሰባቸው የእስር እና ነጻነት ድርሳኑ በመነሳት፤ ከሰማይ የሚወርደውን የፈጣሪን ፍርድ አንደኛ ችሎት፡፡ ዜጎችን በእኩልነት የሚያስተዳድረውን (ሲሰምር) የምድር ህግ ፍርድ ሁለተኛ ችሎት፡፡ እና ሚዛናዊ ባልሆነ የፍርድ ሂደት ያልተገኘውን፡ (ሳይሰምር ሲቀርና ሲንገጫገጭ)  የምድር ህግ ፍትሀዊነት የነፈገውን ፍትህ በብርቱው የተጠሙቱ ግፉዐኑ የሚንከላወሱበትን የህሊና ሱባኤና ገቢር ደግሞ - ሦስተኛው ችሎት  The Third Court ብሎ ከመሰየም ደርሷል የሰው ልጅ፡፡ ግንዛቤ ይፈጥራሉ የሚባሉ ምሳሌዎችን እንደቆነጣጥረው ሁሉ፤ የግንቦት ወር አመታዊ የህትመት መታሰቢያዋ ወር በመሆኑም ነው፤ዬህን ለሀገር እድገት ማነቆ የሆነ አንገብጋቢ ሀሳብ በግንቦት ወር 1996 ዓ.ም ለንባብ ከበቃቸው፤ በይዘቷ ባመዛኙ ለተነሳው ርእሰ ጉዳይ እንድትሆን ከተከተበችውና መታሰቢያነቷንም ‹‹ላገሬ ባለጆች›› የሚል አበርክቶ በፊት ገጽዋ ላይ ካኖረችው ከ‹‹ብርሃን እና ጥላ›› ነባር የ‹‹ዝክረ ጠይብ ስንኞች›› ጋር መሸመናችን . . .
ቀበሎ
ፈጽማ ያልዳነች ዓለም ዛሬም አለች
ምህረት ያልጎበኛት ያኔ በአዳም ከስራ፤
እንደ ፈርዖን ቤት ጡብ ሸማህን ደራርብ
‹ያዕቆብ›  አይዞህ ስራ፤
አዳም እና ሔዋን
አሕዛቡ ሁሉ ኃጢአትን ሰርተዋል፤
ዓይናቸው ሲገለጥ ይተፋፈራሉ
እርቃን መሸፈኛ ሸማ ያሻቸዋል፡፡                                  
(‹‹ያ . ሁ . ያ›› - ያለበት - ሁኔታ ነው - ያለው፡፡)

Read 2342 times