Sunday, 13 May 2018 00:00

አራቱ ቅድመ እውነታዎች

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

  አንድ ሰሞን “ሁለት - ሲደመር - ሁለት አራት ነው” የሚሉኝ ሰዎች ጋ ሆን ብዬ ለመጠጋት ስፈልግ፤ “ሁለት ሲደመር ሁለት … አራት ሊሆን ይችላል፤ ጥያቄው ማን ደምረው አለህ? ነው”
እላለሁ፡፡ ተራ ውዝግብ ነው፡፡ አራት የማይቀየሩ ነገሮች አሉ፡፡ ሁሉም የምናውቀው ነገር ከእነዚህ አራት መነሻ እውነቶች የመጣ ነው፡፡ የማይናወጡ እውነቶች ናቸው፡፡ ከአመክንዮም ሆነ ምክንያታዊነት የሚቀድሙ ናቸው፡፡ በእነዚህ አራት ነገሮች ውስጥ ያልተገለፀ ነገር ህልውና እንኳን የለውም፡፡ ቢኖረውም፤ ለሰው ልጆችም ሆነ ለምድራዊ መመዘኛ ሊገባ የሚችል አይሆንም፡፡ ካንት እነዚህን አራት ነገሮች (Catagories) “a priori” ብሎ ይጠራቸዋል፡፡
አንደኛው ነገር፡- “Quantity” ነው፡፡ ቦታ (space)፣ አካል  (body)፣ ቁስ  (Matter) የሚሉትን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡
ሁለተኛው ነገር፡- “Quality” ነው፡፡ “መቼ?” የሚለውን የጊዜ ፅንሰ ሀሳብ ሁሉ በዚህ ቅድመ ነገር ውስጥ ይካተታል፡፡ ስለ “ኳንቲቲ” ስናወራ፣ “ኳሊቲ” ዘወትር በውስጡ አለ፡፡ … የዚህ ተራራ ህልውና … ድንጋዩ እና ያሳለፈው ዘመን ነው፡፡
ሦስተኛው ነገር፡- ህልውና ራሱ ነው፡፡ ፈረንጆች “being” ይሉታል፡፡ “መሆን” ልለው እችላለሁ፡፡ በህልውና ያለ ነገር፣ በጊዜ እና ቦታ የሚይዘው ስፍራ እስካልተገለፀ ህልውናው አጠራጣሪ ነው፡፡ በጊዜ እና በቦታ መልክ ህልውና ባይኖረው እንኳን በሀሳብ ደረጃ ምን እንደሆነ ማስረዳት ያሻል፡፡
አራተኛው ነገር፡- ሀሳብ (concept) ነው፡፡ ሀሳብ ሁሉ ከማዛመድ ወይንም ከመለያየት የሚወለድ ነው። ሀሳብ ማለት “Relation” ነው፡፡ የሰው ልጅ አእምሮ አንድ ነገር ከተቃራኒው ጋር ያለውን ግንኙነት ወይም ከተመሳሳዩ ጋር ያለውን ዝምድና በማነፃፀር ብቻ ነው ማሰብ የሚችለው፡፡ “ማሰብ” ማለት ተመሳሳዮችን ማገናኘት እና ተቃራኒዎችን መለያየት ይሆናል፤አንድ ጊዜ … ወይም ተመሳሳዮችን ከተቃራኒዎች ጋር ማዳቀል ይሆናል ሌላ ጊዜ፡፡…. ሳይንቲስቶች ብዙውን ጊዜ ህልውና ያለውን ነገር የሚፈልጉት በጊዜ እና ቦታ ላይ ነው፡፡ ወይንም በሀሳብ ደረጃ ህልውና ያለው ነገር በአካል እና ጊዜ ልኬት ላይ ካልተረጋገጠ “ሳይንስ” ብለው አይጠሩትም፡፡
ስለዚህ ቅድም “ሁለት ሲደመር ሁለት አራት ነው” የሚሉትን “ማን ደምረው አለህ?” ስላቸው … “ማን አስብ አለህ?” እያልኳቸው መሆኑ አሁን ግልፅ ሆኖልኛል፡፡ “2+2 = 4” ከሚለው አረፍተ ነገር የሚቀድመው “መደመሩ” ነው፡፡ ከውጤቱ በላይ ማገኛኘቱ የአእምሮ ተፈጥሮ ነው፡፡ ግን እኔ “ማን ደምረው አለህ?” ስልም ከአእምሮ ተፈጥሮ ውጭ ሆኜ አይደለም፡፡ … ማገናኘት፣ መለያየት እና እንደገና ማገናኘት … እንደገና መለያየት እስካለ ማሰብ ይኖራል። ማሰብ እንዲኖር ህልውና ያላቸው ነገሮች (beings) እንዲሁም -- ጊዜ እና ቦታ ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህ አስፈላጊ ነገሮች ደግሞ የሚነፃፀሩት፣ የሚጣመሩትም ሆነ የሚለያዩት በሰው አእምሮ ተፈጥሮ ውስጥ ነው፡፡
ለምሳሌ፤ ታሪክ የጊዜና የቦታ እንዲሁም የሰው ሀሳብ ጥምረት ነው፡፡ የሰው የአእምሮ የማጣመር ሀይል ሳይታከልበት ጊዜ እና ቦታ ላይ የተካሄደውን መደመር ወይም መመዝገብ አይችልም፡፡ (እርግጥ እዚህ ላይ አንድ ምሁር በአንድ አጋጣሚ የጠቀሱትን ነጥብ መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡ … ሁሉም ሰው ክስተትን በአዕምሮው ተፈጥሮ (እያጣመረ እና እያለያየ የመገንዘብ አቅም ቢኖረውም … የታሪክን ሁነት ግን በተለይ ለመተንተን የዘርፉ ባለሙያ ስራ ነው … ብለዋል፡፡)
ካንት እነዚህን አራት መሰረታዊ ቅድመ ነገሮችን ሲተነትን፤ ሄግል ግን ያተኮረው አራተኛው ነጥብ ላይ ነበር፡፡ በአእምሮ ምክኒያት ነገራት የሚፈጥሩትን “Relation” በማስተዋል፣ ከእነ አሪስቶትል ሎጂክ የሚቀድም የሎጂክ ቅድመ ህግን ተነተነ፡፡ ይኼ የሎጂክ ህግ ቅድመ ሀሳብ ወይም ከማሰብ አስቀድሞ አእምሮ የሚያስብበት የተፈጥሮ ህግ ተብሎ ይታወቃል፡፡ ህጉ “ዲያሌክቲክስ” ይሰኛል፡፡ የሄግል ዲያሌክቲስክ፣ ከአሪስቶትል “ዲያሌክቲክስ” የሚለየው የሀሳብን ምክኒያታዊነት መስመር ከመከተል በፊት ሀሳብ በተፈጥሮ መስመር መጀመሪያ እንዴት እንደሚሰራ ስለተነተነ ነበር፡፡
የሰው ልጅ የምንም አይነት ነገርን ህልውና የሚረዳው በማነፃፀር ሂደት ነው፡፡ በተረዳው መጠን መዝኖ አንድ መላምት ያቀርባል፡፡ ለምሳሌ “2” የተባለችዋ ቁጥር በአንድ ህልውና ላይ ያሉ የተለያዩ ነገሮችን ለመወከል የሰጠው መላምት ነው፡፡ የነገሮቹን “ምንነት” ከማወቁ አስቀድሞ “ሁለት ነገሮች” በጊዜ እና ቦታ ላይ እንደሚገኙ ከተገነዘበ በኋላ ነው፣ “ሁለት” የሚለውን “thesis” (አንብሮ) የሚሰይመው፡፡ …
አንብሮውን የሚያጋባው ከተፃማሪ ጋር ነው፡፡ “2+2” ብሎ፡፡ ተፃምሮን “antithesis” ልንለው እንችላለን፡፡ “4” (አራት) የሁለቱ የተነጣጠሉ ነገሮች ጋብቻ ውጤት ነው፡፡
ከውጤቱ ግን ሂደቱ እውነት ነው፡፡ እውነት የሆነው በተፈጥሮ አእምሮአችን የተሰጠው የእውቀት ዘዴ በመሆኑ ነው፡፡ ሂደቱ ሀሳብ እስካለ ድረስ ተመሳሳይ ነው፡፡ ውጤቱ ግን ቋሚ አይደለም፡፡ አንድ ውጤት በተለየ ማነፃፀሪያ ከቀድሞው በተለየ መንገድ የሚዛመድበትን አጣማሪ ሊያገኝ ይችላል፡፡ “ሁለት” ከ “ሁለት” ጋር መደመር ብቻ ሳይሆን መቀነስም እንዳለበት የሚያስብ ይኖራል፡፡ ወይንም መባዛት፣ አልያም መካፈል፡፡
የማይለወጠው የሰው ልጅ አእምሮ ስለ አንድ ነገር … (ነገርየው being, quality or quantity ሊሆን ይችላል) …. ማወቅ የሚችለው ነገርየውን በተቃርኖም ሆነ በተፃምሮ ወይንም አጋኖ … ከሌላ ጋር አነፃፅሮ በመመዘን ብቻ ነው፡፡ ሁለት ወይ ሶስት ነገሮችን ካላነፃፀረ፣ አንድን ነጠላ ነገር እንደ ራሱ ማንነት፣ ምንነቱን ሊረዳ ፈፅሞ አይችልም፡፡
ስለ እውነት ለመረዳት ውሸትን ማነፃፀሪያ ያደርጋል። ውሸት ምን ማለት ነው? ሲል እውነት ምን ማለት ነው? የሚለውንም ማወቅ ይኖርበታል፡፡ “እውነት የራሷም የውሸትም ማስረጃ ናት” እንዲሉ ዶ/ር እጓለ ገ/ዮሐንስ። በተጨባጭ ምድር ላይ የሌሉ አማልዕክቶችን እንኳን ለመረዳት ከሰው ጋር በማነፃፀርና በሰው አቅምና በሀሳባዊ ፍላጎቶቹ መሀል ዘወትር ዝምድና እና ተቃርኖን በማነፃፀርና በመመዘን ነው፡፡
ጊዜ እና ቦታ የሚባሉት ልኬቶችን እንኳን መገንዘብ የሚችለው በተናጠል እንዳላቸው ማንነት አይደለም። ካንት ጊዜ እና ቦታን “Medium of perception” ይላቸዋል፡፡ እነሱም ቢሆኑ በራሳቸው ያሉ ልኮች ሳይሆን አእምሮ እውነታን ለመረዳት የሚጠቀምባቸው የመግባቢያ ቋንቋ ናቸው፡፡ ….
እናም ካንት አራቱ ቅድመ ነገሮች አላቸው እንጂ … አራቱም በአእምሮ ውስጥ ግን እንደ ስሜት ህዋሳት ሆነው እውነታን ለመረዳት ከመጥቀም ባሻገር ያላቸው ራሳቸውን የቻለ ህልውና ምን እንደሆነ ግልፅ አይደለም፡፡
ምክኒያቱም፤ ሰው የሚያውቀው ወይንም ለማወቅ አቅም የተሰጠው ነገር ሁሉ በተፈጥሮው ወይም በአእምሮው ስለሆነ … አእምሮው በዙሪያው ያለውን አለም የሚተረጉምባቸው ቅድመ ነገሮች … አእምሮውም ናቸው፡፡ … በመሆኑም “አራቱ - ቅድመ ነገሮች” ማለት አእምሮ ማለትም ናቸው … በአጭሩ፡፡
“ጊዜ” ያለ አእምሮ፣ “ቦታ” ያለ አእምሮ፣ “ህላዌ” (being) ያለ አእምሮ፣ ማሰብ (relation) ያለ አእምሮ … ትርጉማቸውን ከአእምሮ ባልተነካካ “ንፁህ” መልኩ ለመፈለግ ሰው ሆኖ የሞከረ የለም፡፡ በአእምሮ ውስጥ ሆኖ መፈለግ የሚቻለው በእነዚህ መሰረት ብቻ ነው፡፡
አራቱ አብይ ቅድመ ነገሮች የሚያመለክቱት አእምሮን ነው፡፡ አዕምሮ እውነታን የሚተረጉምባቸውን መንገዶች፡፡ … ስለዚህ “2+2” … “አራት” መሆኑ የማይቀረው ስለፈለግን ወይም ስለተስማማን ሳይሆን፣ የአእምሮ ቁልፍ የሚከፈተው በዛ መሰረት ነገራትን በማገናኘት ስለሆነ ብቻ ነው፡፡    

Read 2247 times