Print this page
Sunday, 13 May 2018 00:00

ቄደር

Written by  ዳግማዊ፡ እንዳለ(ቃል ኪዳን)
Rate this item
(13 votes)

 ‹‹--አንድ እንሁን፡፡ በአንድነታችን ዉስጥ ግን ክፍተት ይኑር፡፡ በክፍተቱ ዉስጥ ከሰማይ መስኮቶች የሚወጡ ነፋሳት ይደንሱ፡፡ አንዳችን አንዳችንን እናፍቅር፡፡ ፍቅራችንን አንድ ለማድረግ ግን በፍጹም እንዳንሞክር፡፡ ይልቅ ፍቅራችን በነብሶቻችን ዳርቻ መሀከል እንደሚንቀሳቀስ የባህር ዉሃ እንዲጫወት እንተወዉ፡፡ አንዳችን የአንዳችንን ጽዋ እንሙላ፡፡ ከአንድ ጽዋ ግን ፈጽሞ እንዳንጠጣ፡፡--”

         ከለስላሳ ዝናብ በኋላ የጠየመው የጠዋት ሰማይ፣ ቀዝቃዛ አየር ተጎናጽፏል፡፡ ክርስትያኑ ውጪ ካላደረ (ጥምቀት ካላለፈ) አይቆምም የሚባለዉ የጅግጅጋ ቅዝቃዜ፣ ፊትን ለመታጠብ እንኳን ያሳቅቃል፡፡ በ06 ቀበሌ ወገብ ላይ በሚገኘው ሰናይ ሆቴል ግቢ ውስጥ ከዋናው መጠጥ ቤት በስተግራ ጥግ ላይ ቁጭ ብለው፣ በደመነፍስ ቢራቸዉን አንስተው እየተጎነጩ በሀሳብ የተከዙት ሁለቱ ጓደኛሞች፤ ከቀዝቃዛው አየር ጋር የሚመሳሰለው ለስለስ ያለው ሙዚቃ ትካዜአቸውን አጅቦላቸዋል፡፡ ሙዚቃው ከሆቴሉ ሳይሆን ጠባቧን አስፋልት ተሻግሮ ካለች ትንሽ ሙዚቃ ቤት ነው የሚመጣው፡፡
አንደኛው ጎረምሳ በጥልቀት ሲያስብ ከቆየ በኋላ ቢራዉን አንስቶ ጎንጨት አለለትና፤ ‹‹ነገርሁ እኔ ካሁን በኋላ የማንንም ሴት ፍላጎት ማሟላት እና ህልም ማሳካት አልፈልግም፡፡ የኔንም ህልምና ፍላጎት ለማሟላት ስል በማንም ሴት ህይወት ዉስጥ መንገድ አልጠርግም፡፡ በቃ ከኔ የሚገጥም ወይ የኔን የሚመስል ህልም ያላት ሴት እስክትመጣ ድረስ በትግስት እጠብቃለሁ!›› ጠረጴዛዉ ላይ ከተደረደሩት ባዶ የሐረር ቢራ ጠርሙሶች ጎን ከተቀመጠ የ”ቤንሰን ኤንድ ጆንስ” ሲጋራ ፓኮ ውስጥ አንዲት ሲጋራ መዝዞ፣ ወገቧ ላይ ቆረጣትና፣ በእጁ ይዞ ሲያፍተለትለዉ በነበረ ላይተር ለኮሳት፡፡
የትንሿን ሙዚቃ ቤት ትንሽ መስኮት አፈትልኮ ወጥቶ በሚመጣዉ ለስለስ ያለ ሙዚቃ ታጅበው፣ የሆቴሉ መለያ የሆነውን በቃሪያና በሽንኩርት ተከሽኖ የሚሠራውን ዱለት በእንጀራ እየጠቀለሉ የሚጎርሱ፤ የአገሩ መለያ የሆነውን ፉል በዳቦ እያጣበቁ የሚውጡ ቁርስ አድራጊዎች፤ ሲጋራቸውን እየማጉ ሐርር ቢራቸውን የሚጨልጡ አንጎበር አራጋፊዎች፤ የጫት ገበያ ሰዓት እስኪደርስ ሦስት ወይ አራት ሆነው በቡድን ተቀምጠው፣ ቢራ እየጠጡ የሚሳሳቁ ሴቶችና ወንዶች ክብ ቅርጽ ያለውን ዋናውን መጠጥ ቤት እንደ ጥድ ከበዋል፡፡ ሺቲ ለብሳ፣ ሻርፕ ተከናንባ ገልመጥ ገልመጥ እያለች ቢራ የምትጠጣ ቀይ ቆንጆ ልጅ፣ ከሁለቱ ጎረምሶች ጀርባ ብቻዋን ተቀምጣለች፡፡ ልጅቱ ለመቆንጀት ብዙ መልክ ፈጅታለች፡፡ ቄንጠኛ ቢራ አጠጣጧ አፏን ላመል ያህል ብቻ ስለሚያስከፍታት፣ ስትጠጣ አፏን ጭራሹን የምትከፍት አትመስልም። አንደኛዉ ጎረምሳ፤ ከጓደኛው የምሬት ወሬ ሲያርፍ፣ አልፎ አልፎ ዓይኑን ሰዶ ይዳብሳታል፡፡ ልጅቱም ይሄን ስላወቀች ቄንጠኛ አጠጣጧን ይበልጥ አቄንጣዋለች፡፡
ዋናው መጠጥ ቤት ውስጥ ያሉ የውጪው ቅዝቃዜ የማይሰማቸው ቆሞ ጠጪዎች ደግሞ ለስላሳው ሙዚቃ አስገድዷቸው በቆሙበት አንገታቸዉን ወይ ትከሻቸዉን ከሙዚቃዉ ምት ጋር አስተካክለዉ ያወዛዉዛሉ፡፡ ስድስት ሰዓት ሞልቶ ጉዞ ወደ ጫት ተራ እስኪጀመር ድረስ ግን የተከዙትም፣ ያልተከዙትም፤ የተቀመጡትም፣ የቆሙትም የሞሉትን መለኪያ ከማጉደልና ሌላ ከማስሞላት አልቦዘኑም፡፡
የቅድሙ ጎረምሳ የጀመረዉን ወሬ ምርር ባለ አንደበት ቀጠለ፤ ‹‹የእዉነት እኔ ሰልችቶኛል! እንደ ባንክ ብድር የማንንም ህይወት ስገነባ መኖር አልፈልግም፡፡ እንዴ የኔስ ህይወት? የኔስ ህልም?››
‹‹ቆይ! ያንተን ህልም እስካሁን ካወቅኻቸዉ ሴቶች ወይ ወደፊት ከምትተዋወቃቸዉ ሴቶች የሚለየዉ ምንድን ነዉ? ይሄን ያህል ምን የተለየ ህልም ኖሮህ ነዉ እንደዚህ የምትማረረዉ? አትቃምና አታጭስ ማለታቸዉ፣ የመቃምና የማጨስ ህልምህን አጨለመብህ እንዴ? ደሞስ  የአንዳቸዉን ቃል እንኳን አክብረህ፣ ከመጠጣትና ከመቃም ተቆጥበህ ታውቃለህ? ብታጣ፣ ብታጣ እንኳን የመዉሊድ መደብርንና የሙስጠርያን መደብ ጠንተህ፣ በብድር ከመቃም ትመለሳለህ?›› ሌላኛው ጎረምሳ በግርምት ጠየቀ፡፡
‹‹ቆይ ድፍን ጅጅጋ ላይ ካሉ ሴቶች ለምን እኔ የምወዳቸዉና የምይዛቸዉ ሴቶች ብቻ አትቃምና አታጭስ የሚሉ ሆኑ? ሁሉም ፍቅረኛሞችና ባለትዳሮች አብረዉ ቅመዉ፤ አብረዉ መርቅነዉ ነዉ በሰላም የሚኖሩት፤ ገንዘብ ቢያጡ እንኳን የሠላሳ ብር ቃጨሮ ገዝተዉ ተካፍለዉ በሚቅሙበት አገር ላይ፤ እኔ ላይ ማን አስደግሞብኝ ነዉ የያዝኳት ሁላ ‹ዲ.ኢ.ኤ› ኤጀንት የምትሆንብኝ?››
‹‹ቆይ እሷ መች አትቃም አለችህ? ባለፈዉ አብራችሁ ስትቅሙ አልነበር እንዴ? ወይስ የመጨረሻዉ ጫት ነበር?››
‹‹እሷም ብትለኝ አላቆምም፡፡ ካሁን በኋላ በራሴ ሳንባና ጉበት ገብቶ ማንም እንዲፈተፍት አልፈልግም! የሚገርመዉ እኮ አታጭስና አትጠጣ የሚሉት እንዳትሞትባቸዉ ብለዉ ሳይሆን ሲጋራ ሲጋራ እንዳትሸታቸዉ፤ ሠክረህ እቤት ስትገባ ሆድህ ያባዉን በብቅል በርትተህ እንዳታወጣባቸዉ ነዉ!፡፡››
ጓደኛዉ ከት ብሎ ሣቀና፤ ‹‹ይቺ ልጅ ደህና አድርጋ እያሳበድችህ ነዉ፡፡ አቦ ተዋት በቃ! ባልጠፋ ሴት ምን እንዲህ ያማርርሀል? ድሮም ቢሆን ያረጀ ፍቅር እንደዚህ ነዉ፡፡ ፍቅርና ገንፎ ትኩስ ትኩሱን ነዉ የተባለዉ እዉነት ነዉ፡፡….እኔ ግን ጓደኛዋ ተመችታኛለች፡፡ ስልክዋን እስከምቀበል ብቻ ትንሽ ታገስና ትፋታታለህ ቂቂቂ--›› አስካካበት፡፡
‹‹እሷ ብቻ አይደለችም ሁሉም ሴቶች እራስ ወዳድ ናቸዉ፡፡ ዕድሜህን በዕድሜአቸዉ ልክ ሊሠፍሩልህ ይፈልጋሉ፡፡ ሃያ ሦስት እያለች እንዉለድ ስትላት ‹አንተ እራስህ መወለድህ ይገርመኛል! በሁለት ኪሎ የገንፎ እህል ልታርሰኝ ነዉ እንዴ? የደሃ ደሃ!› ብላ ስታላግጥብህ የነበረች ሴት፣ ከአሥር ዓመት በኋላ ወዳንተ መጥታ፣ ልክ ትናንትና እንዉለድ ብለህ እንደጠየቅኻት፤ ‹በቃ እሺ እንዉለድ!› ትልሀለች፡፡ ምናልባት እኮ በአሥር ዓመት ዉስጥ የአንድ ኪሎዉን መግዣ ብር አጥፍተኸዋል፡፡ ወይ የዛኔ ለሁለት ኪሎ ብለህ የያዝከዉ ገንዘብ፤ አሁን እሩብ አይገዛ ይሆናል፡፡›› ሲጋራዉን አቀጣጠለና በአዲስ ኃይል ቀጠለ፡-
‹‹የምር ሠላሳዎቹን ፉት ሲሉ አብረሃቸዉ ዕንቁላል ማምረት እንደምታቆም፣ ካልወለድን ብለዉ ወጥረዉ ይይዙሀል፡፡ ህይወት ያለ ጋብቻና ያለ ልጅ ከንቱ እንደሆነ ይሰብኩሀል፡፡ ትናንት በአምቦ ዉሃ እየበረዝክ የምታጣጥማት ህይወት፤ ዛሬ በማር እንኳን አልጥም ትልሀለች፡፡ ያከስሩሀል፡፡ በየአሥር ዓመቱ ወደ ህይወትህ እየተመላለሱ ያከስሩሀል!፡፡››
ጓደኝዬዉ በማጽናናት ጀርባዉን ዳበሰዉና ‹‹ዋናዉ እኮ የምትወዳት ልጅ ወዳንተ ተመልሳ መምጣቷ ነዉ፡፡ ለምን ይሄ ነገር አይገባህም ቆይ? እስከ መቼ ነዉ በላይ አገር ደረቅ ኩራትህ ተሞልተህ፣ እየተጎዳህ የምትኖረዉ? የምትወዳት ልጅ እንዉለድ እያለችህ እዚህ ከኔ ጋር ቢራ ስትጠጣ አያንቅህም? ከስንቱ ያጣላችህ፤ ስም ያሰጠችህ ልጅ ተመልሳ መጥታ አስወልደኝ ካለችህ፣ ዘለህ ጉብ ማለት ነዉ ያለብህ፡፡ እንደዉም ተመስጌን በል! አንድ ልጅ ከሌላ ወልዳ፣ ‹ለልጄ ወንድም ወይ እህት አስወልደኝ› ብትልህስ ኖሮ? ይልቅ አሁን ቢራዉን አቁምና ጂንህን ተወግተህ ሂድላት፡፡ አቦ እኔም ቢሆን እስኪ አጎት ልሁን! ቂቂቂ--››
‹‹አንተ ምን አለብህ አሹፍ!›› ጎረምሳዉ በምሬት ቢራዉን አንስቶ ጨለጠዉና ሌላ ሲጋራ ለኮሰ፡፡
‹‹አላሾፍኩም የምሬን ነዉ፡፡ ደግሞ አንድ ነገር እወቅ! ሴቶቹ በዚህ ዕድሜ ትዕግስታቸዉ አፍንጫቸዉ ላይ ነዉ፡፡ ወደደችህም አልወደደችህም በዙርያዋ ካሉት ሁሉ አንተን አስበልጣ፤ አንተን መርጣ መጥታ ነዉ አግባኝ፣ አስወልደኝ ያለችህ፡፡ ‹ዕንቁላል ጋሪ አይደለም፣ አይጠብቅም ቆሞ!› ሲሉ አልሰማህም? ወይስ እኔ እንዳንተ ሆኜ ሄጄ ላስረግዝልህ? ቂቂቀ--››
‹‹ሁሉም ሴቶች እንዳቅማቸዉ ያስጨንቁሀል! የናቷን ነጠላ ቀዳና አጣጥፋ እግሮቿ መሀል ከምከተዉ አንስቶ ብራንድ እየጠቀሱ የሚቦን፣ የማይቦን፣ ምልክት የሚያወጣ ወይ የማያወጣ እያሉ ሞዴስ የሚያማርጡ ሴቶች ሳይቀሩ፣ የህልማቸዉ ማሳኪያ እንድትሆንና ለወራቶች የ”አበባ ጭማቂያቸዉን” እንድታቆም ያጩሀል፡፡ ከዛም በዲስኩራቸዉ እየሞሉ ሊያበቁህ ይጣጣራሉ፡፡ ከነቃህ ደግሞ ይዝቱብሀል! ሻንጣቸዉን እየሸከፉ ጥለዉህ እንደሚሄዱና ብቸኛና ሽማግሌ ሆነህ እንደምትሞት እየነገሩህ  ያስፈራሩሀል፡፡››
ጓደኝዬዉ በግርምት ጠየቀ፤ ‹‹ቆይ አንተ ከእሷ መዉለድ አትፈልግም?››
‹‹አልፈልግም አልወጣኝም!›› ጎረምሳዉ መለሰ፡፡
‹‹ታድያ ምን ይጠበስ ነዉ የምትለዉ? አቦ ልጠጣበት በጠዋቱ አዛ አታድርገኝ!››
‹‹እኔ የምለዉ፣ የማንንም ህልም ማሳኪያ መሆን አልፈልግም ነዉ፡፡ ከረጅም ዓመታት በኋላ እወድሀለሁ ብላ ተመለሰችና አብራኝ ሆነች፡፡ ከዛም ቂጤ እንኳን ሳይቀመጥ ቶሎ መጋባትና መዉለድ አለብን ካለበለዚያ ግን……››
‹‹መዪ/አይ/! መዪ! እንደዛ አይደለም--›› ጓደኝየዉ አቋረጠዉ፡፡ ‹‹እሷ እወድሀለዉ ብላ አልተመለሰችም። ከእለታት ባንዱ ቀን ጅግጅጋ ሆቴል ጋ  ቆመህ ባጃጅ እየጠበቅህ ሳለ ተገናኛችሁ፡፡ ከዛ ምሳ ካልጋበዝኩሽ ሞቼ እገኛለሁ ብለህ፤ ያዝልኝ ብዬ በሰጠሁህ ብር በኮንትራት ባጃጅ ይዘህ ሄደህ፣ አበሩስ አስገብተህ፣ ክትፎና ቢራ ጋበዝካት፡፡ ከዛ ደግሞ አወዳያችሁን ገዝታችሁ ወደ ቤት ሄዳችሁና ፏ አላችሁ፡፡ እኔ ደግሞ ብሬን ላንተ አስረክቤ፣ የምቅምበት አጥቼ እራብሳ ቅሜ ዋልኩ፡፡ ከዛም ሲመሻሽላችሁ ቤተልሔምና ሮማን ስትጠጡ አመሻችሁና አብራችሁ አደራችሁ፡፡ ከዛ በዛዉ ቀጠላችሁ፡፡ እንደዛ አይደል ታሪኩ? እንደዛ ነበር የነገርከኝ፡፡›› በጥያቄ ዓይን ተመለከተዉ፡፡
‹‹አቦ ተዋ! ብርህ ተሰጠህ አይደል እንዴ? ሁልጊዜ ይሄን ነገር እያነሳህ ለምን ትጨቅጭቀኛለህ?”
‹‹አቦ እኔ ምንም አልጨቀጨኩህም! አንተ ነህ እንጂ የማይሆን ነገር እያወራህ ሰዉ አዛ የምታደርዉ። አቦ እንዉለድ ካለችህ ሄደህ ዉለድ፡፡ ቆይ መዉለድ ትችላለህ አይደል? ለነገሩ ከጅግጅጋ ድሬዳዋ ድረስ እንዲያስወርዱ የላካቸዉ የ05 ቀበሌ ሴቶች ብቻ መዉለድ ለመቻልህ በቂ ማስረጃ ናቸዉ ቂቂቂ--››
‹‹እሺ መዉለድ ባልችልስ ኖሮ? ጥላኝ ልትሄድ አይደል?......አየህ ወዳኝ ሳይሆን ህልሟን ልታሳካብኝ ነዉ የፈለገችኝ!››
ጓደኛዉ እምባ እስኪወጣዉ ድረስ ከት ብሎ ሣቀና፤ ‹‹አቦ ምን ዓይነቱ ሰዉዬ ነህ ግን?›› ብሎ እራሱን ነቀነቀ፡፡
‹‹ምን ያሥቅሀል? እዉነቴን እኮ ነዉ፡፡ እሺ ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ ተመልሳ መጥታ፣ አብሬህ ልሁን ስትለኝ አሜን ብዬ ልቀበላት?›› ጎረምሳዉ አፈጠጠ፡፡
‹‹እኔ እኮ የላይ አገር ሰዎች በጣም ነዉ የምትገርሙኝ፡፡ የምትወዳት ልጅ እኮ ነዉ ተመልሳ የመጣችዉ! ለምን ከመቶ ዓመት በኋላ አትመጣም፤ የምትወዳት ልጅ አብረን እንኑር፣ ልጅ እንዉለድ ካለችህ፣ አዬ/እሺ/ ብለህ ጎትተህ ማስገባት ነዉ ያለብህ። ሁሉ ሞልቶልህ ሳለ ለምን የጎደለ ፍለጋ ትባክናለህ?›› ጎረምሳዉ ጭንቅላቱን በእጆቹ ፈትጎ በረጅሙ ተነፈሰ። ጓደኛዉ ቀጠለ፤
‹‹ልጅቷን ትወዳታለህ፤ ከሷ ልጅ እንዲኖርህ ትፈልጋለህ አይደል? ታድያ ከዚህ ዉጪ ምን ያስፈልግሀልህ? በእዉነት ተነስተህ ሂድና የራስህ ብቻ አድርጋት፡፡ ሂድና ከሁሉ ተሽለህ አሳያት፡፡ ማንንም እንዳትመኝና እንዳታይ አድርገህ አኑራት፡፡ የእዉነት ይሄን ቢራ አስቀምጥና ሄደህ አስረግዛት! ካለበለዝያ እኔ እራሴ ሄጄ ነዉ የማስረግዝልህ፡፡ ለሦስት ሴቶችና ለአራት ልጆቻቸዉ መሽሩፍ እንደምቆርጥ እያወቅህ፣ ሌላ እንዳስወልድ እልህ አታሲዘኝ፡፡ እኔ ሌላ ወጪ አልፈልግም!›› ቀልድና ቁምነገሩ የማይታወቀዉ ጓደኛው፣ ንግግሩን ሲጨርስ ቢራዉን ተጎነጨ፡፡
‹‹እኔ እኮ የጅግጅጋ ልጆች ግርም ትሉኛላችሁ! የምትፈልጓት ልጅ በመጨረሻ የናንተ ትሁን እንጂ የትም ዞራ ብትመጣ ግድ የላችሁም፡፡››
‹‹የሸገሮቹ አካብዴዎች ስለሆናችሁ እኮ ነዉ! የወደዷትን የራስ ከማድረግ ሌላ ምን የሚያስደስት ነገር አለ ብለህ ነዉ?››
‹‹በእዉነት አሥር ዓመት እንኳን ኖሬ ልቀበለዉ ያልቻልኩት ይሄን ነገር ነዉ፡፡ እንዴት የምትወዳት ሴት ከሌላ ሰዉ ጋር ሆና ተመልሳ ስትመጣ፣ አሜን ብለህ ትቀበላታለህ?››
‹‹ያዉ አንተ እንደተቀበልካት ነዋ! ቂቂቂ--›› የጎረምሳዉን ጭንቅላት በእጁ እያሻሸ፣ጓደኝየዉ የሹፈት ሣቅ ሣቀ፡፡
‹‹መዪ/አይ/! እኔ አልተቀበልኳትም!›› አለ ጎረምሳዉ፤ ፈርጠም ለማለት እየሞከረ፡፡
‹‹አቦ አብረሀት አደርክ አይደል እንዴ? ከዚህ በላይ ምን ሊመጣ ነዉ? ቆይ ድሮ ጥላህ ከሄደች በኋላ ምኗን ነዉ የጠላኸዉ? ሌላ ያቀፈችበትንና የታቀፈችበትን አካሏን ሳትጠላ ሌላ ምኗን ልትጠላ ትችላለህ?›› ያነሳዉን ቢራ ሊጎነጭ ወደ አፉ አስጠግቶ፣ በጥያቄ ዓይን ጎረምሳዉን ተመለከተ፡፡
‹‹ልቧን ነዉ የምጠላዉ፡፡ እኔ ልቧን አላምነዉም። ልቧ የማንና ከማን እንደሆነ አላዉቅም፡፡ አንድ ጓደኛዬ ሚስቱን ከሌላ ሰዉ ጋር መንገድ ላይ ስትሣሣቅ አይቶ የጻፈዉ ግጥም ትዝ አለኝ፡፡ ግጥሙን ሚስቱ እንድታየዉ ብሎ በትልቁ ጽፎ ግድግዳዉ ላይ ለጥፎት ነበር፡፡ ሚስቱ ግን ሲያሣሥቃት ከነበረዉ ሰዉ ጋር በዛዉ ሄዳ ኖሮ አልተመለሰችም፡፡
‹አገር ምድሩን ቢያስስ
ምድረ አዳምን ቢያዳርስ
ገላሽማ ዞሮ ይመጣል
ተፈትጎ አምሮ እንደገብስ
በድንሽማ ቤቱ ይገባል
ግና…
ቀልቤ ደርሶ የማይወደዉ
ፍቅሬ አልጫ የሆነበት
ልብሽን ነዉ የማላምነዉ፡፡› ይላል ግጥሙ፡፡ እኔም የሷን ልቧን ነዉ የማላምነዉ?›› ጎረምሳዉ መለሰ፡፡
‹‹ቆይ የዛኔ አብራህ ብትሆን ኖሮስ፣ ልቧ አንተ ጋር መሆኑን በምን እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ? አግብተህ ሠላሳ፣ አርባ ዓመታትን አብርሀት ኖረህ፤ ደርሰዉ ልጆቻቸዉን የወለዱ ልጆችን ከሷ አፍርተህ እየኖርክ እንኳን ልቧ አብሮህ እንደሆነ ምን ማረጋገጫ አለህ? የሚስትህ ልብ፣ ልጅ እያለች መኪና የበላዉ ወይ ወንዝ የወሰደዉን የህጻንነት የዕቃቃ ጨዋታ ባሏን እያሰበ እለት እለት እንደማይደማ ምን ማረጋገጫ አለህ? በላብ ተጠምቀህ ከፍ ዝቅ እያልክ የምትተኛት ሚስትህ፤ ልትወድህና እራሷን አሳልፋ ልትሰጥህ የምትታገል ግን ያልቻለች ብትሆንስ? የፍትህወት የመሰለህ ላቧ ከጭንቀት የመነጨ ወይ የሷ ያልከዉ ላብ መንዲ ገላህ ያመነጨዉ የራስህ ላብ ላለመሆኑ ምን ማረጋገጫ አለህ?......እዉነቴን ነዉ ስትተኛት ማቃሰቷ የጭንቀት እንጂ የፍቅር እንዳልሆነ ምን ማረጋገጫ ሊኖርህ ይችላል? አልጋ ላይ ከሴት ጋር የያዘችዉ የምትወደዉ ፍቅረኛዋ ትዝ እያላት፣ ገላህ እንዳባጨጓሬ እንደማይቀፋትና እንደማይኮሰኩሳት ምን ማረጋገጫ አለህ? የሚያቅለሸልሻት በሆድዋ ከአንተ የቋጠረችዉ ጽንስ ሳይሆን አንተን ማየቱ ላለመሆኑ ምን ማስረጃ ታመጣለህ? የእርግዝና ጊዜዋ ፊት ለፊት እያየችህ ቋቅ ለማለት ዕድል ሰጥቷት ቢሆንስ?›› ጓደኝዬዉ ንግግሩን አብቅቶ፣ ቢራዉን አንስቶ ያወራዉን ያህል ተጎነጨ። ጎረምሳዉ ግራ በመጋባት ዝም አለ፡፡ ሲጋራዉን በረጅሙ ልምጥጥ አድርጎ ሳበና መልሶ ተፋዉ፡፡ ጓደኝዬዉ ግን ቀጠለ፤
‹‹የድሮ ፍቅረኛችሁን ስታገኙ ትዳር ላይ ብትሆን እንኳን አብራችሁ ለማደር አትግደረደሩም፡፡ ለቁም ነገር ሲሏችሁ ግን እንደ ፖለቲከኛ የድሮ ታሪክ እየመዘዛችሁ እንደ ከዘራ ለማጣመም ትጥራላችሁ፡፡ ማንም በማንምና በምንም እርግጠኛ መሆን አይችልም፡፡ ልብህ እሷን እሷን የሚልህ ከሆነ--- ሂድና አግብተህ አስወልዳት!››
‹‹አንተ ምንም አልገባህም!›› አለና ጎረምሳዉ፣ ወደ ጭሱና ትካዜዉ ተመለሰ፡፡ ጓደኝየዉም፣ አስተናጋጁን ጠቅሶ ቢራ እንዲያመጣ ላከዉ፡፡ አስተናጋጁ አስቀድሞ የተዘጋጀበት ይመስል ወድያዉኑ ሁለት ቢራ ይዞ መጥቶ፣ ቅዝቃዜዉን በእጃቸዉ እንዲለኩት አደረገና ከፍቶላቸዉ ሄደ፡፡ ድንገት አንድ ሽርጥ የለበሰና ጺሙንና ጸጉሩን ቀይ ቀለም የተቀባ ሽማግሌ ሰዉዬ ገብቶ፣ በየጠረጴዛዉ እየዞረ፣ ያለ ልመና ቃላት እጁን እየዘረጋ፣ የሰጡትን ያለ ምስጋና እየተቀበለ፤ ዝም ያሉትንም ሳይቀየም አልፎ እየሄደ፣ እነሱ ያሉበት ጠረጴዛ ጋር ደረሰና፣ እጁን ዘረጋ፤
‹‹አላህ ኩሲዮ›› አሉት በአንድነት፤ እሽቅድድም በሚመስል ድምጽ፡፡ ድንገት የጓደኝየዉ ስልክ ‹ማሬ፣ ማሬ፣ ማሬ፣ ማሬ› የሚል ሙዚቃ አሰማች፡፡ ጎረምሳዉ ስልኩን አዉጥቶ አየና፤
‹‹ኦዮ እየደወለች ነዉ፡፡ ዛሬ ሄጄ ፍሪጇን ካልሠራሁላት ትገለኛለች፡፡ በቃ በኋላ ጫቴን ይዤ ቤት እመጣለሁ፡፡ ካለች እሷንም ጥራትና ትካድመን። በዛዉም አንተ እምቢ ካልካት ከኔ መዉለድ እንደምትፈልግ እጠይቃታለሁ! ቂቂቂ--›› ይደርስብኛል ያለዉን ያህል ብር ከኪሱ አዉጥቶ ሰጠዉና ወደ በሩ አመራ፡፡ ቅድም እጃቸዉን የዘረጉለት ሽማግሌ፣ ድጋሚ በሩ ላይ ሲያገኙት እጃቸዉን ዘረጉለት፤
‹‹አላህ ኩሲዮ›› ብሏቸዉ፣ ብቻዋን ቁጭ ብላ ቢራ የምትጠጣዉን ቆንጆ ቀይ ልጅ ጠቅሷት ወጣ፡፡ ሽማግሌዉ ምንም ሳይሉት፣ ተከትለዉት ወጡ፡፡
ጎረምሳዉ የተቀበለዉን ብር ኪሱ ከተተና ግማሽ የሚደርሰዉን ቢራዉን አንስቶ፣ በአንድ ትንፋሽ ጨልጦ፣ አስተናጋጁ ሌላ እንዲያመጣለት በእጁ ምልክት አሳየዉ፡፡ ከዛም አንድ ሲጋራ መዞ አዉጥቶ፣ የልማዱን ከላዩ ላይ ቆርሶ ለአድባሯ ወረወረላትና ለኮሰዉ፡፡ ቀዝቃዛዉ አየር መሞቅ ጀምሯል፡፡ ትዝ አለችዉ፡፡ እሷን ሲያስብ ልቡ እንደ አየሩ መሞቅ ጀመረ። ከወደድኳት ዋናዉ የኔ መሆኗ እኮ ነዉ ሲል አሰበ፡፡ ጓደኛዉ ያለዉን ነገር ለመቀበልም ላለመቀበልም ተግደረደረ፡፡ እንድትወደዉ ይፈልጋል፡፡ አብረን እንኑርና ልጅ እንዉለድ ማለቷ ግን የመዉደዷ መገለጫ መስሎ አልታይ ብሎታል፡፡
‹‹ዕድሜዋ ሊያልፍባት ሲል መጥታ እንዉለድ ትለኛለች እንዴ? የዛኔ ለሻይ እንጠጣ እንኳን እጅ መንሻ ይዤ እንደ ደጃዝማች ደጅ ስጠናት፣ ከባለ ባጃጅ ጋር ሽዉ ብላ አልሄደችም?...›› ጢቅ እንደሚሉት ምራቅ፣ የንቀት ፈግግታ ፊቱ ላይ ብልጭ አደረገና የመጣለትን ቢራ አንስቶ ተጎነጨ፡፡ ወድያው ደግሞ ሌላ ሀሳብ መጣበት፤
‹‹ግን ደግሞ አሁንስ ቢሆን መቼ ፈላጊ አጣች? ከአሥር ዓመት በኋላም ይበልጥ አማረች እንጂ ምን ጎደለባት? በዚህ ሁኔታዋ እንኳን ማን የማይፈልጋትና የማይመኛት አለ? ስንቱ ጎረምሳ የሱ ሆና ቁልቢ ገብሬል ዣንጥላ ይዞ ለመሄድ አስፍስፎ እየጠበቀ ነዉ? ቆይ ግን ችግሬ ምንድን ነዉ? ለምንድነዉ እኔን መዉደዷን ያላመንኩት? ለራሴ ያለኝ አመለካከት የወረደ ነዉ እንዴ? ወይኔ ጉዴ! ይሄኔ ይህቺን የመሰለች ቆንጆ ለኔ አትገባም ብዬ አስቤ ብቻ እንዳይሆን!›› እየሞቀ ባለዉ አየር እየተፍታታ የነበረዉ ሰዉነቱ፣ በጭንቀት ተወረረ። የጫት ሰዓት ገና ቢሆንም አስተናጋጁን ጠርቶ ሂሳብ ከፈለና ተነስቶ ወጣ፡፡ አንድ እጁን ከኪሱ ከቶ፣ በአንድ እጁ ላይተሩን እያፍተለተለ፣ ወደ ፈረሱ አደባባይ - ወደ ጫቱ ተራ ወረደ፡፡ እየሄደ እንደዚህ አሰበ፤
‹‹ፍቅር ምንድነዉ? የፍቅር ተቃራኒዉስ ምንድነዉ? ጥላቻ ለፍቅር ተቃራኒ ትርጉሙ ሆኖ የመቆም ብቃት አለዉ? ማነዉ ከእርቃን ገላ ይልቅ የፍቅረኛዉን ዉብ ፈገግታን አስበልጦ፤ እዉነተኛ አፍቃሪ ተብሎ ለመጠራት ጽናት ያለዉ? ማነዉ ‹‹በደስታም በመከራም ጊዜ አልለይም›› ብሎ ከመማል  ይልቅ ‹‹ፍቅር ካለ መከራ የሚባል የለም!›› ብሎ በፍቅር ሀሴት የሚያደርገዉ?
እሺ አብሮ መሆን ማለት ምን ማለት ነዉ? አብሮ አለመሆንና መለያየትስ? ማን ከማን ጋር ነበር እና ነዉ የሚለያየዉ? እንደቤተ-መቅደስ ምሶሶዎች ተራርቀን ቆመናል ብለን እየተቀኘን፣ እንዴት አብረን ነን ለማለት ደፈርን? እሺ ምሶሶ ሆነን ተራርቆ በመቆም፣ የትኛዉን ቤተ-መቅደስ ነዉ የደግፈነዉ? ያንዱ ምሶሶ መጉደልስ ቤተ-መቅደሱን ያፈርሰዋል?
ምንድነዉ ከሷ ማረጋገጥ የምፈልገዉ? እንደምትወደኝ ነዉ ወይስ ሌላ የምትወደዉ እንደሌለ ነዉ? ለምንድነዉ ከሷ አብሮ መሆኑ አንዲህ የጎረበጠኝ? አትወደኝም ብዬ ስለማስብ ወይስ ልትወደኝ አይገባትም ብዬ ስለምሰቅላት? ብዙኃኑ ያፈቀረዉን አጥቶ ከተስማማዉ ጋር አብሮ በሚኖርባት ህይወት ዉስጥ እኔ ካፈቀርኳት ጋር ልኖር እንደሆነ አስቤ እስከ ካራማራ ተራራ ጮቤ መርገጥ ለምን ተሳነኝ?›› ወደ ግራ ታጥፎ፣ ቤተልሔም ሆቴል ጋር ሲደርስ፣ አንድ ባጃጅ ግራ ትከሻዉን መቶት አለፈና ከሰመመኑ አነቃዉ፡፡ የባጃጁ ሹፌር ፍጥነቱን ሳይቀንስ አከታትሎ ሰድቦት ሄደ፡፡ ጎረምሳዉ የቀረዉን አስፋልት በጥንቃቄ ተሻግሮ መብራት ኃይሉ በር ላይ ተረጋግቶ ቆመና እንደገና ወደ ሀሳቡ ተመልሶ፣ የኮብልስቶኑን መንገድ ተያያዘ፡፡
‹‹ፍቅርና አብሮ መሆን አንድ ነዉ እንዴ? እዉነት ማለት ብዙኃኑ የተስማማበት ከሆነ በርግጥ እንደዛ ይሆናል፡፡ ‹ካላፈቀርሺኝ ላፈቅርሽ አልችልም›፤ ‹ስሜቴን ካልተጋራኸኝ እንዴት ብቻዬን ላፈቅርህ እችላለሁ› ወዘተ.. የመሳሰሉ እሮሮዎችን ከትልቁም ከትንሹም ዘፋኝ አፍ መስማት የተለመደ ነዉ፡፡ የፍቅር ወጌሻዎቻችንም ‹ካላፈቀረችህ አታፍቅራት› የሚል ጨርቅ አፋችን ዉስጥ ጠቅጥቀዉ፣ የልብ ዉልምታችንን ሊመልሱ ሲታገሉ ይዉላሉ፡፡ ስብራታችንን ‹ሰጥቶ መቀበል ነዉ የፍቅር ትርጉሙ› በሚል ቀርከሀ አስረዉ ሊጠግኑልን ይጥራሉ፡፡ ታድያ እኔ እንዴት ከሌላ ጋር ሆና አፈቀርኋት? በርግጥ አልጠበቅኳትም፡፡ ያልጠበቅኳት ግን ስለማልወዳት ሳይሆን ትመለሳለች ብዬ ስላላሰብኩ ይሆናል፡፡ ብጠብቃት ኖሮ መምጣቷን ሳይ፣ በጣም ደስተኛ እሆን ነበር፡፡ አሁንስ -- ግን ለምን ደስተኛ ለመሆን አልሞክርም?›› ኤዶም ሆቴል ጋር ሲደርስ ሌላ ባጃጅ ቀኝ ትከሻዉን ገጭቶ፣ ድጋሚ ከሰመመኑ አነቃዉ፡፡ ይሄኛዉ ባለባጃጅ አልተሳደበም። ወደ እግረኛ መንገድ ወጣና፣ በግራ ያለዉን ቅያስ ይዞ መንገድ ጀመረ፡፡
‹‹የእዉነት የምወዳት ልጅ እንደምትወደኝና አብራኝ ለመሆን ፈቃደኛ እንደሆነች ስትነግረኝ መደሰት ነዉ ያለብኝ፡፡ እኔ አፈቅራታለሁ፡፡ እሷም አፈቅረሀለዉ ብላኛለች፡፡ ደግሞ ልጄን ካረገዘች ቢያንስ ዘጠኝ ወር አብራኝ ትሆናለች፡፡ መቼም ዘላለም አብራኝ እንድትሆን ማድረግ አልችልም፡፡ ቆይ ግን ነገ ተነስታ ‹ላንተ ያለኝ ፍቅር አልቋል ብትለኝስ?› ድንገት ሻንጣዋን አዘጋጅታ ‹ለልጁ ማሳደግያ መሽሩፍ ቁረጥ! እኔ ግን ቻዎ› ብትለኝስ? የሷን ህልም አሳክቼ፤ አየር ላይ ልቀር ነዉ? የዕድሜ ግዳጇን በኔ ልፋት ተወጥታ እንደንስር ታድሳ፣ ድጋሚ ጥላኝ ለአሥር ዓመት ልትበር?›› ጠጅ ቤቱ ጋር ሲደርስ ሌላ ባጃጅ ግራ ትከሻዉን ታኮት አለፈ፡፡ ባጃጁ ፍጥነቱን አልቀነሰም፡፡ ዳሩን ያዘና መንገዱን ቀጠለ፤
‹‹የኔ ህልም ግን ምንድን ነዉ? ምን ዓይነት ዓላማ አለኝ?›› እራሱን ጠየቀ፡፡ መልስ አጣ፡፡ መልስ በማጣቱ ተገረመ፡፡  በመገረሙ ደግሞ ተናደደ፡፡ መገረፍ እንጂ መገረም አልነበረብኝም ሲል አሰበ፡፡
‹‹ታድያ የራሴ ህልም ከሌለኝ የሷን ህልም ባሳካላት ምንድነዉ ችግሩ? ያዉም የምወዳትን ልጅ ህልም ማሳካት!? ግን ከወለደች በኋላ እኔ ልጅ እንጂ ባል አልፈልግም ብላ ብትገፋኝስ? ቆይ ግን ምን እና ማን ስለሆንኩ ነዉ፤ እሷን ዘላለም የኔ ላደርጋት የምመኘዉ? ጥላኝም ከሄደች ትሂድ! ይሄን ያህል ዓመት እንኳን በትርፍራፊ ትዝታዎቿ አይደል እንዴ እየተደሰትኩ የኖርኩት? አሁን ከሷ አንሶላ ከመጋፈፍ አልፌ ማህጸኗን ላይ እንደ ጠላ ጥንስስ ለመጠንሰስ ከበቃሁ አነሰኝ? ደግሞ ከጠመቅሁት ጠላ ፍቅርን እየቀዳሁ ከመጠጣት ማን ያግደኛል? እንዴ የምን መጨነቅ ነዉ? በቃ አብራኝ ከሆነች ሆነች ካልሆነ ግን ‹ላንተ ያለኝ ፍቅር አልቋል። አሰናብተኝ በቃ!› ካለችኝ፣ እግሯ ላይ ተደፍቼ፣ ‹አትሂጂ የኔ እመቤት! እኔ ጋ ያለዉ ፍቅር ለሁለታችንም ይበቃል› እያልኩ፤ በኩርማን ፍቅር አልገበዝም፡፡ ግን ቆይ ይሄ ፍቅር የሚሉት ነገር ያልቃል እንዴ? ወይስ ፍቅርን የሚመስል ሌላ የሚያልቅ ስሜት አለ?››
ኮብልስቶኑን ጨርሶ አዲሱ አስፋልትን ተሻገረና እግረኛ መንገዱ ላይ ወጥቶ ወደ ቀኝ መንገድ ጀመረ። የፈረሱ አደባባይ ከጀርባዉ የሙስና ሠፈር ትላልቅ ሕንጻዎችን ደጀን አድርጎ ቆሟል፡፡ አደባባዩ ላይ ያለዉ የፈረሰኛ ሀዉልት እንደ ድሮ ነገስታትና ጦረኛ በፈረሱ ሥም ነዉ የሚጠራዉ፡፡ ሁሉም ‹ፈረሱ ጋ ና ወይ ፈረሱ ጋር ነኝ› እያለ ነዉ አቅጣጫ የሚናገረዉ፡፡ ጎረምሳዉ ፈረሱ ያለበት አደባባይ ጋ ሲደርስ ወደ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስትያን የሚወስደዉን ዋና መንገድ ይዞ ታጠፈና ጫት ተራዉ ጋ የደምበኛዉ መደብ ጋ ሄዶ ቆመ፡፡ ጫት ነጋዴዎቹ እስኪመጡ ተኮልኩለዉ የሚገኙ ብዙ ጫት ገዢዎች መደቡን ለመከለል በተሰራዉ ወራጅ እንጨት ላይ ቁጭ ብለዉ ወረፋ ይዘዋል፡፡ ጎረምሳዉ፤ አንድ ድንጋይ ፈልጎ ተቀመጠና ዳግም በሀሳብ ተዋጠ፡፡
‹‹እሺ አብሬአት ልሁን፡፡ ግን አብሮ መሆን ምንድን ነዉ? ማን ከማን ጋር ነዉ አብሮ የሚሆነዉ? አሥር ዓመት ሙሉ እኔ እያፈቀርኳት እሷ አሥር ፍቅረኛዎች ትቀያይር ነበር፡፡ ግን እሷን ሳላስብ ያደርኩበት ቀን የለም፡፡ ዉሃና ግጦሽ እንደሚከተል ከብት አርቢ፣ የእሷን አዳዲስ ጎጆዎች እየተከተልኩ ቤት ተከራይቻለሁ፡፡ እና አሁን አብራኝ አልነበረችም ይባላል? እኔም እሷን እንደ ጸሐይ ከርቀት እያየኋት ብዙ ሴቶችን እንደ አቧራ ቅሜአለሁ፡፡ ሲያንስ ለቀናት ሲበዛ ለሦስት ወራት ከጥቂት ሴቶች ጋር አብሬ ኖሬያለሁ፡፡ ግን እነሱን አቅፌ ተኝቼ፣ እሷን አስባት ነበር፡፡ እሷ፤ አብሬ ስሄድ አትኩራ ያየቻትን ሴት እንደ ቤት ሠራተኛ፣ የዛኑ ቀን አሰናብቼ አዉቃለሁ፡፡ እና ከነዛ ምስኪን ሴቶች ጋር አብሬ ነበርኩ ነዉ የሚባለዉ? ከሷ ጋር አብሬያት አልነበርኩምስ ሊባል ይቻላል? እዉነት አብሮ መሆን ምን ማለት ነዉ? ማን ከማን ጋር ነዉ አብሮ ያለዉ? አቅፏት ይተኛ የነበረዉ ባሏ ወይስ እያሰብኳት ያደርኩት እኔ ነኝ አብሬአት የነበርኩት? ከእኔስ ጋር ማን ነበረ? አቅፌአት ያደርኩት ያቺ ልጅ ወይስ ሳስባት የነበረዉ እሷ? እዉነት አብሮነት ብሎ ነገር የለም፡፡ ሁላችንም ከማይታወቀዉ ተነስተን ወደማይታወቀዉ የምንሄድ ብቸኛ መንገደኞች ነን፡፡ የቀረቡን የመሰሉንን የመንገዳችን አጫፋሪዎች፤ በመንገዳቸዉ የምናጫፍር ብቸኞች ነን፡፡ ጉዟችን በጭለማና በክረምት ሆኖብን፣ ከመንገዳችን አሻግረን ማየት የቻልናቸዉንና አሻግረዉ ሊያዩን የቻሉትን፤ ድምጻቸዉን መስማት የቻልነዉንና  ድምጻችንን መስማት የቻሉትን ዘመድ የምናደርግ ባዕዶች ነን፡፡
የመንገዱ ስፍር ልክ እንደመንገደኛዉ ቁጥር አይነኬና አይጠጌ ሊሆን ይችላል፡፡ ካንድ ሰዉ በላይ ሊሄድባቸዉ የማይችሉ እልፍ አዕላፍ መንገዶች፣ ሁለት እግሮችን ብቻ ይጠብቃሉ፡፡ አንድ መንገድ ለሁለት እግሮች ብቻ! የወለዱን፤ በደም የተዛመዱንም መንገዳቸዉ ከመንገዳችን ቅርበት እንጂ አንድነት የለዉም፡፡ በፍቅር ለጥቆም በጋብቻ የሚዛመዱንም ቢሆን መንገዳችንን የማይጋሩን ባለመንገዶች ናቸዉ፡፡ እሷም በመንገዷ ስትዞር እንጂ እኔ መንገድ ላይ ተገኝታ አይሆንም። ከአሥር ዓመታት በፊት ከኔ እልፍ ክንድ ይርቀዉ የነበረዉ መንገዷ ቀርቦኝ እንጂ አሁን የኔ መንገድ ላይ ተገኝታ አይደለም፡፡
ግን የማን ጥፋት ነዉ ይሄ? ደግሞስ አብራኝ እንድትሆን፣ አንድትቀርበኝ እፈልግ አልነበረ እንዴ? ፍቅር ምናልባት ከመንገዳችን በቅርብ መንገዱ ከሆነ ሰዉ የምናገኘዉ፣ መነሻና መድረሻችንን አለማወቃችንን የሚያስረሳ ሥካር ነዉ፡፡ ለመሥከር ደግሞ መጠጡ እንጂ ጠርሙሱ አይጠቅምም፡፡ አሁን እንዲሁ መጠጣት እየቻልኩኝ፣ ካላጠጣሽኝ ማለት ነበረብኝ?
ድሮ አላፈቀረችኝም ማለት ትጠላኝ ነበር ማለት ነዉ እንዴ? ጥላቻ ፈጽሞ የፍቅር ተቃራኒ ሆኖ ሊቆም አይችልም፡፡ አለመጠጣትም የስካር ተቃራኒ አይደለም። ፍቅር ኃያል ሳይሆን ኃይል ነዉ፡፡ ኃይል ደግሞ አይፈጠርምም አይጠፋምም፡፡ ፍቅርንና አብሮነትን አንድ አድርጎ ማየት፣ ፍቅርን ክብር ማሳጣት ነዉ፡፡ ተዳሳሽና ተጨባጭ ነገር በሌላት ሕይወት ዉስጥ ያዉም አፍቅሬሀለዉ ላለችኝ ተፈቃሪዪ፣ የባለቤትነትና የይዞታ ማረጋገጫ መሻቴ እብደት ነዉ፡፡ እኔ እራሱ የማንም ሳልሆን፤ እሷን የራሴ ለማድረግ መጨነቄ ምን ቢነካኝ ነዉ? እዉነት መንገዳችን ለየቅል ሆኖ ሳለ፣ በአንድ እግር ለመሄድ ለምንስ እንመኛለን? ካንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ እያልን እየተረትን፣ አንድ አካል አንድ አምሳል ለመሆን መሮጣችን፤ ባንድ ክር ለማሰብ እላይ ታች ማለታችን ለምን?›› ጎረምሳዉ በትዝብት እራሱን ነቀነቀና ፈገግ አለ፡፡ ከዛም ከተቀመጠበት ድንጋይ ላይ ተነስቶ ቆመ። ቁመቱ አሻግሮ ከሚያየዉ ከፈረሱና ፈረሱ ላይ ቁጭ ካለዉ ሰዉዬ የሚተልቅ መስሎ ተሰማዉ፡፡
እንደገና ፈገግ አለ፡፡ ወደ ልጅቱ ቤት ሊሄድ ቆረጠ። ለመሄድ መነሳቱንና መቁረጡን ሲያስብ፣ አብሯት ለመኖርና የልጆችዋ አባት ለመሆን ቸኮለ። ዙርያ ገባዉን እየቃኘ፣ ባጃጅ ፍለጋ ዓይኖቹን አንከራተተ፡፡ የጅጅጋ ባጃጆች ከየትም አቅጣጫ ሊመጡ እንደሚችሉ ያዉቀዋል፡፡ ዞር ሲል ሮማን ሆቴል ካለበት ቅያስ ዉስጥ የሚወጣ አንድ ባጃጅ ሲያይ በእጁ ምልክት አሳየና አስቆመዉ፡፡ እግሩ ወደ ባጃጁ መንገድ እንደጀመረ የጫቱን መሸጫ መደብ ዙርያ የተኮለኮሉት ጎረምሶች መራኮት ጀመሩ። ለጫት ነጋዴዎቹ ክብር ታላቅ ሆታና ጭብጨባ ተደረገ፡፡ የጉርሱምን ጣፋጭ ለዉዝ በካኪ ሞልተዉ የያዙ ህጻናት ጫት ገዝተዉ የሚሄዱትን ሰዎች ተስፋ አድረገዉ መሰብሰብ ጀመሩ፡፡ ጎረምሳዉ ጫት ሻጯ መምጣቷን ካለዉ ትርምስና ሁካታ ሲረዳ በረጅሙ አዛጋ፡፡ ቢሆንም ጫቱን እንደ ሌላዉ ጊዜ ተሻምቶ አለመግዛቱ ቅር ሳይለዉ ወደ ባጃጁ ገባና ተደላድሎ ተቀመጠ፡፡ በኋላ ከሚስቴ ጋር መጥቼ እገዛለሁ ብሎ አሰበ፡፡ ባለሚስት ሊሆን እንደሆነ ሲሰማዉ ይበልጥ ደስ አለዉና ፈገግ አለ፡፡
የባጃጁ ሹፌር የጎረምሳዉ ፈገግታ ሳይበግረዉ ወዴት እንደሚሄድ ከጠየቀዉ በኋላ ባጃጇን እዛዉ ጋር አዞረና በመጣበት መንገድ ተመለሰ፡፡ ባጃጁ መንገድ ሲጀምር ጎረምሳዉ፣ በካህሊል ጅብራን ‹ዘ ፕሮፌት› መጽሀፍ ላይ ነብዩ አልሙስተፋ አንድ ስለመሆን የተናገረዉን እያስታወሰ ለራሱ በለሆሳስ አነበነበ፤
‹‹አንድ እንሁን፡፡ በአንድነታችን ዉስጥ ግን ክፍተት ይኑር፡፡ በክፍተቱ ዉስጥ ከሰማይ መስኮቶች የሚወጡ ነፋሳት ይደንሱ፡፡ አንዳችን አንዳችንን እናፍቅር፡፡ ፍቅራችንን አንድ ለማድረግ ግን በፍጹም እንዳንሞክር። ይልቅ ፍቅራችን በነብሶቻችን ዳርቻ መሀከል እንደሚንቀሳቀስ የባህር ዉሃ እንዲጫወት እንተወዉ፡፡ አንዳችን የአንዳችንን ጽዋ እንሙላ። ከአንድ ጽዋ ግን ፈጽሞ እንዳንጠጣ፡፡ የያዝነዉን እንጀራ እንሰጣጥ፡፡ ከአንድ መአድ ግን በፍጹም እንዳንቆርስ፡፡ በአንድነት እያዜምን እና ዳንኪራ እየረገጥን እንደሰት፤ ከዛም ብቻችንን እንድንሆን እንፈቃቀድ!›› ከመደሰቱ ብዛት ባጃጁን እሱ እንደሚነዳዉ ተሰማዉ፡፡

Read 4790 times