Sunday, 13 May 2018 00:00

የአ.አ.ዩ የሥነ ጥበብ ተማሪዎች ለጠ/ሚኒስትሩ አቤቱታ አቀረቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 ከፖለቲካ ነፃ የሆነ የስነ ጥበብ ም/ቤት እንዲቋቋም ጠይቀዋል
                
   ከፖለቲካና ከሚኒስቴር መ/ቤት አሰራር ነፃና ገለልተኛ የሆነ የስነ ጥበብ ምክር ቤት እንዲቋቋም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ጥበባት ኮሌጅ ተማሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ በፃፉት ደብዳቤ ጠይቀዋል፡፡
400 የዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የስነ ጥበባት ትምህርት ክፍል ተማሪዎችን ፊርማ የያዘውና ሰሞኑን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተላከው የአቤቱታ ደብዳቤ መረዳት እንደተቻለው፤ የስነ ጥበብ ስራዎች በህገ መንግስቱና በአለማቀፍ ስምምነቶች በተቀመጡ ድንጋጌዎች መሰረት፣ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነፃ እንዲሆኑ ተጠይቋል፡፡
“ራሳችንን በራሳችን የምናስተዳድርበት ዘዴ ተፈጥሮልን፣ የስነ ጥበብ ምክር ቤት እንዲቋቋምልን እንጠይቃለን” የሚሉት ተማሪዎች፤ “እስካሁን ከመንግስት አሰራርና ከፖለቲካ ጋር የተቆራኘ መሆኑ፣ ከየትምህርት ማዕከላቱ በዘርፉ ተመርቀው የሚወጡ ጥበበኞችን ለአድሏዊ አሰራር አጋልጧል፣ ስራ አልባም አድርጓል” ብለዋል፡፡
“ከተመረቅን በኋላ የራሳችንን የጥበብ ስራዎች የት እናሳይ? የሚለው በእጅጉ ያስጨንቀናል” የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ “በጥቂት ግለሰቦችና በመንግስት የተያዙት ቤተ ጥበባትም ቢሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የተወሰኑ በመሆናቸው፣ የክልል ባለሙያዎች በእጅጉ እየተጎዱ ነው” ብለዋል፡፡
“በገለልተኝነት የሚቋቋመው የኪነ ጥበብ ምክር ቤትም በዋናነት በሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች ኖረውት፣ የጥበብ ማዕከላት በየአካባቢው የሚስፋፋበትን መንገድ ያመቻቻል” ሲሉ አብራርተዋል ተማሪዎቹ፡፡
“ሙዚቃ፣ ቲያትር፣ ፊልምና ስዕልን ጨምሮ በርካታ የሥነ ጥበብ ዘርፎች በመንግሥት ተቋማትና ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ስር በመሆናቸው፣ የስነ ጥበብ እድገት አዝጋሚና በፖለቲካ የተቃኘ ሆኗል” ያሉት ተማሪዎቹ፤ “በገለልተኛ ም/ቤት ቢመራ በነፃነት መስራት ያስችለዋል፤ እድገቱም ይሰፋል” ብለዋል፡፡

Read 1408 times