Monday, 14 May 2018 00:00

የዶላር መንገድ - የሚያዛልቀንና ውጤት የሚያስገኝልን ሁነኛው መንገድ የትኛው ነው?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)

• የግል ኢንቨስትመንት የሚስፋፋበትና ኤክስፖርት የሚያድግበት መንገድ! ይሄ ነው የሚያዋጣን!
• የዳያስፖራ ዶላርስ? መልካም ነው። ግን፣ በእቅድ በዘመቻ ማሳደግና ማቋረጥ አይቻልም።
• ወደ ውጭ የሸሸ ዶላር መመለስስ? ጥሩ። ግን፣ ተቀጥላ ችግር እንጂ ዋና ችግር አይደለም።
• የነዳጅ ወጪን መቆጠብስ? ይሁን። ግን፣ ኢትዮጵያ በነዳጅ ፍጆታ የዓለም “ውራ” ናት።
• ዶላር መበደርስ? በተቃራኒው፣ የዶላር እጥረት የሚያባባብስ ሆኗል - የብድር እዳና ወለድ!
• እርዳታስ? ከኢኮኖሚ እድገት ጋር የተራራቁ የአውሮፓ አገራት፣ እርዳታ ሊጨምሩ? አይሆንም።
    
    በአጭሩ፣ ሌላው ሌላው ሁሉ፣ ተቀጥላና ቅርንጫፍ ነው። ዋና ችግሮችና መፍትሄዎች፤
ሁነኛውና ዘላቂው መንገድ፣ የግል ኢንቨስትመንትንና ኤክስፖርትን አለማደናቀፍ!
መንግስት፣ ከውጭ በገፍ እንዳይበደርና በከንቱ ሃብት እንዳያባክን፣ ልጓም ማጥበቅ!
ለተቋም መሪ፣ በተለይ ደግሞ መንግስትን የመሰለ ግዙፍ ተቋምን ለሚመራ ሰው፣… ከሁሉም በላይ፣ ቀዳሚና ትልቁ ስራው፣… ዋና ዋና መርሆችንና አላማዎችን… አንጥሮና አጥርቶ፣… 1፣ 2፣ 3… እያለ በግልፅ ማሳየት፣… ዋና ዋና የተግባር ዘዴዎችንና መሰረታዊ ትኩረቶችንም፣… በጥንቃቄ ለይቶ፣… 1፣ 2፣ 3 ብሎ ማስረዳት ነው።
ይሄ ነው ከባዱና ዋናው የመሪ ስራ! አለበለዚያ፣ መያዣ መጨበጫ የሌለው ውጥንቅጥ ውስጥ፣ ጭራና ቀንዱ የተደበላለቀበ፣ የእልፍ አእላፍ ጉዳዮች ግርግር ውስጥ ተተብትቦ መቅረት ይሆናል መጨረሻው።
ይህንን በሚገባ በመገንዘብም ይመስለኛል፣ ጠ/ሚ አብይ አህመድ፣ በየአካባቢው በርካታ ንግግሮችን በጥንቃቄ ለማቅረብ የመረጡት - ከሌሎች ስራዎች ሁሉ ቅድሚያ በመስጠት። (በዚያውም፣… በሦስት ዓመታት ቀውስ ጋር የተናጋውን አገር ለማረጋጋት፣ ክፉኛ እየተሸረሸሩ የመጡ የአገር ስረመሰረቶችንም ለመደገፍ፣ እንዲሁም ከየአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በሚደረጉ ውይይቶች፣ የተወሰኑ ጠቃሚ ሃሳቦችን አልያም አሳሳቢ ጉዳዮችን ለማዳመጥ እንደሚጠቅማቸው አያጠራጥርም)።
ዋናው ስራ ግን፣ መርሆችን፣ አላማዎችን፣ የተግባር ትኩረቶችን፣… በግልፅ ማስረዳት ነው! ይሄ፣ ለተቋም መሪ፣ የሁልጊዜ ዋና ስራ ነው። ጠ/ሚ አብይ፣ እስካሁን እንዳደረጉት፣ ወደፊትም ይህን ስራ ትኩረት እንደማይነፍጉት ተስፋ አደርጋለሁ።
በተቃራኒው፤ ዋና መርሆችንና አላማዎችን… 1፣ 2፣ 3… በማለት አንጥሮና አጥርቶ አለመግለፅ፣… የተግባር ትኩረቶችንም፣… 1፣ 2፣ 3… በማለት ማስረዳት አለመቻል፤ ወይም ቸል ማለት፣… መጨረሻው ኪሳራ ነው። ሙሉ ለሙሉ ቸል ማለት ብቻ አይደለም ችግሩ። ትንሽም ቢሆን ቸል ማለትም ሆነ መሰልቸት፣ በጣም ጎጂ ድክመት ነው። ካስፈለገ፣ እልፍ ጊዜ እየተደጋገሙ ለመናገርና ለማስረዳት መሞከር ነው የሚሻለው። ቢሰለችም እንኳ!!
ለነገሩ፣ ዶ/ር አብይ፣ ሃሳባቸውን በንግግር የመግለፅ ብቃታቸው ድንቅ ነው። በዚያ ላይ፣ የንግግር ብቃት ቢኖራቸውም፣ ንግግርን በቅድሚያ በፅሁፍ በወጉ የማዘጋጀት ጥቅም ከፍተኛ እንደሆነ፣ በትክክል የተገነዘቡ ጠንቃቃ መሪ ይመስላሉ።
ለማንኛውም፣ ዋና አላማና ዋና የተግባር ትኩረቶች፣… በጭራሽ ለአፍታም ቢሆን እንዳይደበዝዙ፣ ከዝርዝር ጉዳይ ጋር በዘፈቀደ ተቀላቅለው እንዳይበረዙ መትጋት የግድ ነው። ለብዥታም ሆነ ለዝብርቅርቆሽ ሰበብ ላለመስጠትም መጠንቀቅም ያስፈልጋል።
መትጋትና መጠንቀቅ መቼ? በምን ጉዳይ ላይ? ሁሌም፣ በሁሉም ጉዳዮች ላይ። ዋና ምሶሶና ግንድ፣… ከተቀጥላ ቁሳቁስና ቅርንጫፍ ጋር እኩል በዘፈቀደ ተቀላቅለው፣ ነገሩ ሁሉ ከተዘበራረቀኮ፣… “መላም የለው!” ይሆናል ስራው ሁሉ። ለዚህም ነው፣ ዶ/ር አብይ፣… እንደአጀማመራቸው ወደፊትም፣ ሃሳባቸውን በግልፅ ለማሳወቅና ለማስረዳት በጥንቃቄ ከመትጋት አይዘናጉም ብዬ ተስፋ የማደርገው - በንግግርና በውይይት።
ትጋትና ጥንቃቄ ተዘንግቶ ይቅርና፣ ሳይዘነጋም… ኋላቀር አገር ውስጥ፣ ዋና ጉዳይና ተቀጥላ ቅርንጫፎች በቀላሉ ነው የሚዘበራረቁት። ከእነዚህ መካከል፣ አንዱን በምሳሌነት ላንሳ - ከባለሃብቶች ጋር ያደረጉትን ውይይት።
የብዙ ባለሃብቶች ጭብጨባ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከባለሃብቶች ጋር በፍጥነት ለመወያየት መምረጣቸው አይገርምም። በነባር ድህነት ላይ ቀውስ ታክሎበት፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየተፍረከረከና የዜጎች ኑሮ እየተናጋ እስከመቼ ሊቀጥል ይችላል? በፍጥነት ካልተሻሻለና ካላገገመ፣ ኢንቨስትመንት ተስፋፍቶ፣ የስራ እድል በብዛት ካልተፈጠረ፣ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ወደ ጤናማ ጎዳና ካልገባ፣… የጊዜ ጉዳይ እንጂ፣ ወደ አስፈሪው መዘዝ መንሸራተት አይቀሬ እንደሚሆን ምን ይጠየቃል? ውይይት ሲያንስ ነው። በዚያ ላይ፣ ጠ/ሚ አብይ እንደተናገሩት፣ በተግባር በእውን… ሃብት ለማፍራት የበቁ ስኬታማ ባለሃብቶች፣ በስራ እና በሃብት ፈጠራ ላይ፣ የላቀ እውቀትና ብቃት ያላቸው ሰዎች ናቸው።
የስራ እድሎችን በሚፈጥር መንገድ፣ ለዘመናዊ እርሻና ለኢንዱስትሪ ቀዳሚ ትኩረት እንደሚሰጡ የገለፁት ጠ/ሚ አብይ፣ ባለሃብቶች ይህንን በማገናዘብ ለተጨማሪ ስራ እንዲነሳሱ ጠይቀዋል። በመንግስት ፕሮጀክቶች ዘንድ የሚታየውን የሃብት ብክነት የሚገታ መፍትሄ ማበጀትም ሌላው ዋና ጉዳይ ነው ብለዋል። እድገት የማይታይበት የኤክስፖርት ድንዛዜና የውጭ ምንዛሬ እጥረትም ከቀዳሚ ትኩረቶች መሃል ጉልህ ቦታ እንዳላቸው ተናግረዋል - ጠ/ሚ አብይ።
እነዚህን ዋና ዋና ጉዳዮችን አንድ ሁለቴ ከዘረዘሩ በኋላ፣ ተቀጥላና ቅርንጫፍ ጉዳዮችንም አንስተዋል። የጥቁር ገበያ የዶላር ምንዛሬ መረን እንዳይለቅ፣… ዶላር ወደ ውጭ አገር ወስደው ያስቀመጡ እንዲመልሱና አገር ውስጥ እንዲሰሩበት፣… በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት የሚልኩት ዶላር እንዳይቀንስ፣… እንዲሁም ቤንዚንን በቁጠባ ስለመጠቀም ተናግረዋል።
አሳዛኙ ነገር፣… ቅድሚያ የተሰጣቸው ዋና ትኩረቶች ተዘንግተው፣… በየሚዲያው ዋና መነጋገሪያ ሆነው የሰነበቱት ጉዳዮች፣ እነዚህ ተቀጥላ ቅርንጫፎች ናቸው። በባለሃብቶች ሳቢያ፣ ዶላር ከአገር የጠፋ ሲያስመስሉ ነው የሰነበቱት።
ዶላር የጠፋው ግን፣ በመንግስት የምንዛሬ ተመን ሳቢያ ኤክስፖርት ስለደነዘዘ፣ እንዲሁም በመንግስት የውጭ እዳና ወለድ ሳቢያ፣ በዓመት 1.5 ቢሊዮን ዶላር እስከመክፈል በመደረሱ ነው። እውነታው እንዲህ ግልፅ ቢሆንም፣ ብዙ ጋዜጠኞችና ምሁራን፣ ብዙ ፖለቲከኞችና ዜጎች፣… እንደተለመደው፣ ባለሃብቶች ላይ ማላከክ ይቀናቸዋል።
እንዲያውም፣ እዚያው ስብሰባ ላይ፣ ብዙ ባለሃብቶች ሞቅ ባለ ጭብጨባ አዳራሹን ያደመቁት፣ “ያሸሻችሁት ዶላር ብትመልሱ ይሻላል” የሚል ንግግር ሲሰሙ ነው። ለሌላ ባለሃብት የተሰነዘረ ንግግር ይመስል!
አስገራሚ ነው። ሃብትንና ቢዝነስን የሚያጣጥል ኋላቀር ባህል፣ እጅጉን ስር በሰደደበት አገር ውስጥ መሆናችንን እንዳንዘነጋ የሚያስታውስ አጋጣሚ ነው። ብዙ ባለሃብቶችና የቢዝነስ ሰዎችም ጭምር፣… ቢዝነስንና ሃብት ማፍራትን እንደትልቅ ቅዱስ ነገር አይቆጥሩትም። እናም፣ “ለሌላ ባለሃብት” የተነገረ ይመስል፣ ብዙዎች ያጨበጭባሉ።
ዋና ዋናዎቹ ጉዳዮች፣ በዚህ መንገድ በቀላሉ እንዲደበዝዙና በተቀጥላ ጉዳይ ተውጠው እንዲቀሩ የሚያደርጉ፣ እልፍ የስህተት ሰበቦችና የአስተሳሰብ ጉራንጉሮች የበዙባት አገር ውስጥ መሆናችንን አለመርሳትና ሁልጊዜም መጠንቀቅ ያሻል።
ለመሆኑ የዶላር እጥረት ዋና ዋና ጉዳዮች፣ አሳሳቢ ችግሮችና መፍትሄዎች ምንድናቸው?

የዳያስፖራ ዶላር?
በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚልኩት ዶላር ቀላል አይደለም። ከኤክስፖርት ይበልጣል። በዚያ ላይ ብዙ ሳይዋዥቅ እያደገ መጥቷል። ግን፣ “የዳያስፖራ ዶላር በ50% እንዲያድግ”… በማለት ማቀድና ዘመቻ ማካሄድ፣ ከንቱ ድካም ነው። ለነገሩ፣ “የዳያስፖራ ዶላር በ50% እንዲቀንስ” በማለት መቀስቀስና ለዘመቻ መጮህም፣ ከንቱ ክፋት ከመሆን አያልፍም። ለምን? መንግስትን ለመደገፍ ወይም ለመቃወም ብሎ ሳይሆን፣ ለቤተሰብና ለወዳጅ ብሎ ዶላር የሚልክ እያንዳንዱ ሰው፣ የራሱ ኑሮና የራሱ እቅዶች አሉት። አብዛኛው “ዳያስፖራ”፣ በፖለቲካ ፕሮፖጋዳና በተቃውሞ ዘመቻ እየተነዳ አይደለም ዶላር የሚልከው።

ብድርስ?
የመንግስት የውጭ ብድር፣ ውሎ ሳያድር ገንዘቡ እየባከነ፣ የዶላር እጥረትን ሲያባብስ እንጂ ሲያቃልል አይታይም። የብድር ነገር ባይነሳ ነው የሚሻለው። ከጣሪያ በላይ ተቆልሏል። በዚያ ላይ፣ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፣ አያዛልቅም። እንዲያውም፣ አሁን እንደምናየው፣ ጣጣው ይበዛል - የወለድና የእዳ ክፍያው ከብዷል። የዶላር እጥረትን ካባባሱ ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ይሄው ነው። ሌላኛው ዋና ምክንያት ደግሞ፣ በመንግስት የምንዛሬ ተመን ሳቢያ ኤክስፖርት መደንዘዙ!

እርዳታስ?
ለጋሾቹ አገራት ራሳቸው፣ በኢኮኖሚ ችግር በተጠመዱበት በዛሬው ዘመን፣ ተጨማሪ እርዳታ ከየት ይመጣል? የተለመደው ያህል እርዳታ ባይቋረጥም፣ ተጨማሪ እርዳታ በገፍ ለማግኘት መጠበቅ ግን፣ ከንቱ ነው። የማይረባ ምኞት!
በተለይ የአውሮፓ አገራት፣ ጃፓንም ጭምር፣ እስከ መቼ… በኢኮኖሚ ድንዛዜ እየተላወሱ እንደሚቀጥሉ፣… ከቁጥር የሚገባ እድገት  ለማስመዝገብስ ስንት ዓመት እንደሚፈጅባቸው አይታወቅም። በአሁኑ አያያዛቸው ግን፣… የኢኮኖሚ ድንዛዜ እየባሰባቸው፣ ተጨማሪ ቀውስ እየተደጋገመባቸው፣ ለበርካታ ዓመታት እየተናጡ የሚቀጥሉ ይመስላል። ይሄ የሚገለጥልን ገና ዛሬ ከሆነ ዘግይተናል። ከቀውስ ሳይላቀቁ 10 ዓመት ሞላቸውኮ። እንደ ድሮው፣ የእርዳታ በጀት መጨመርም ትተዋል - 10 ዓመት ሞላቸው።  
ለነገሩ፣… በእርዳታ ላይ “መተማመን”፣ እርዳታን… “የኑሮ መንገድ” ማድረግ አይቻልም። “እርዳታ” እና “መተማመን”፣… ሁለት አብረው የማይሄዱ ቃላት ናቸው። ሰው፣… ውጤታማ ለመሆን ቢያቅድ መተማመኛ አለው - በራሱ ተማምኖ ነው፤ በራሱ አእምሮና በራሱ ጥረት፣ በራሱ ብቃትና ፅናት ላይ ተማምኖ ነው፣ እቅድ የሚያወጣው። “ተጨማሪ እርዳታ ለማግኘት እቅድ ማውጣት” ግን… አስቂኝ ነው። እርዳታ፣ የችግር አደጋን ለማለፍ፣ አጣብቂኝ ውስጥ ተቀርቅሮ ላለመቅረት ትንሽ መፈናፈኛ ለማግኘት፣ ወይም ደግሞ ለአጭር ጊዜ ለመደገፍ ያህል ያግዛል እንጂ… በቃ፣ እርዳታ በተፈጥሮው፣ ዘላለም እያደገ ሊቀጥል አይችልም።
እንዲያውም፣  “እርዳታና ድጎማ”… ሁልጊዜ እያደገ እንዲቀጥል በመመኘት ሳቢያ ነው፣ ከትልቅነት የመውደቅ አደጋ የበረከተ የመጣው። “የመንግስት የአገር ውስጥ ድጎማና እርዳታ” ነው፣ እነ አውሮፓን ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ያራራቃቸው። 1% እድገት ስር ተቀርቅረዋል። ይሄ፣… ከምር “እድገት” አይደለም። በርካታ የአውሮፓ አገራት ግን፣ የስልጣኔና የእድገት አርአያ የነበሩ አገራትም ጭምር፣ ይሄውና አስር ዓመታቸው ከ1% ጋር እንደተጣበቁ። ከዚህ የኢኮኖሚ በሽታ ጋር፣ የአውሮፓ ፖለቲካም ጤና እያጣ መምጣቱን አትዘንጉ። በአጭሩ፣ ከነ አውሮፓ፣ ተጨማሪ እርዳታ ለማግኘት መመኘት ቢቀርብን ይሻላል። ማቀድማ ሞኝነት ነው።
“የአየር ንብረት ለውጥ”፣ “የካርቦን ልቀት”፣ “የአካባቢ ጥበቃ” በሚሉ የጥፋት ፈሊጦች አማካኝነት፣… እጥፍ ድርብ እርዳታ የማግኘት ጭፍን ምኞቶች አሁንም አልተገቱም። ለምን? የአለምን የኢኮኖሚና የፖለቲካ በቅጡ ባለመገንዘብ ሊሆን ይችላል። ሺ አለማቀፍ ስምምነት ቢፈረም፣ እልፍ ጉባኤ ቢካሄድ፣… በስምምነትና በጉባኤ፣… የአውሮፓን ኢኮኖሚ ከቀውስ ማውጣት አይቻልም።
እንኳን ዛሬ ይቅርና፣ ያኔ ከ7 ዓመት በፊትም ቢሆን፣… “የአካባቢ ጥበቃ”፣ “የአየር ንብረት፣… የካርቦን ልቀት”… የሚል ቁማር እንደማያዋጣ ማወቅ ይቻል ነበር። በእንዲህ አይነት ቁማር፣ “መበላት እንጂ መብላት አይቻልም” የሚለው ምክር፣ የዛሬ 7 ዓመት ሰሚ አላገኘም። መንግስት፣ ቢያንስ ቢያንስ ዛሬ ይህንን ምክር መስማትና ማገናዘብ ቢጀምር ይሻለዋል። አለመስማትና አለማገናዘብኮ፣… እውነታን አይለውጥም።
“እጥፍ ድርብ እርዳታ ለማግኘት አትጠብቁ” የሚለውን ምክር መንግስት ያኔ ስላልሰማ፣ መስማት ስላልፈለገ፣ እጥፍ ድርብ እርዳታ አገኘ? አላገኘም። ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ፣ የለጋሾች እርዳታ፣ ስንዝር ፎቀቅ አላለም።
በጥቅሉ፣… የዶላር እጥረትን ለማቃለል፣ እርዳታ መፍትሄ አይሆንም። ብድርም፣ እዳው ተቆልሎ የዶላር እጥረትን የሚያቃልል ሳይሆን የሚያባብስ ሆኗል። የዳያስፖራ ዶላር፣ ብዙ ሳይዋዥቅ ቀስ በቀስ እየጨመረ ቢመጣም፣… የዚያኑ ያህል ደግሞ፣ በዘመቻና በእቅድ እጥፍ ድርብ እንዲጨምር ማድረግ አይቻልም - በተፈጥሮው… ብዙም አይዋዥቅም። በተቃውሞም ሆነ በድጋፍ ዘመቻ፣ የዳያስፖራን ዶላር መገደብም ሆነ ማጉረፍ አይቻልም። በቦይኮት አልያም በፕሮፓጋንዳ ተነሳስቶ፣ “ከዛሬ ጀምሮ ለቤተሰብ ዶላር መላክ ትቻለሁ።… ከዛሬ ጀምሮ እጥፍ እልካለሁ” ብለው የሚወስኑ ጤና የጎደላቸው ጥቂት ሰዎች ቢኖሩ እንኳ፣ እንዲህ የሚሳከርበት ጤናማ ሰውስ ስንት ይኖራል? ዜሮ! አብዛኛው ሰው፣ ቤተሰብ ወዳጆቹን አስቦ፣ ኑሮውን አመዛዝኖ፣ የአቅሙን ያህል ይልካል እንጂ፣ ቦይኮትንና የቦንድ ሽያጭን እያሟገተ አይወስንም።

የነዳጅ ቁጠባስ?
ጥሩ። ትንሽም ብትሆን መቆጠብ ጥሩ ነው። ግን፣ የኢትዮጵያውያን የነዳጅ ፍጆታ፣… ከመነሻው የእንጥፍጣፊ ያህል በጣም ትንሽ ነው። ከ3ሺ ሊትር ቤንዚን፣ 1 ሊትር ብቻ ናት የኢትዮጵያውያን ፍጆታ። ከዚህች ውስጥ ያን ያህልም መቆጠብ አይቻልም። የእንጥፍጣፊ እንጥፍጣፊም ቢሆን መቆጠብ ይጠቅማል ከተባለ፣ ጥሩ! ይሁን። ዋናው ነገር ምንድነው? እፍኝ የማይሞላ ዶላር በመቆጠብ፣ የዶላር እጥረትን ማቃለል አይቻልም ለማለት ፈልጌ ነው።    
የሸሸ ሃብትን ማስመለስስ?... የሸሸ ሃብት? ዋናዎቹና ግዙፎቹ ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ “የሸሸ ሃብት ማስመለስ”… ብንል ያዋጣል ወይ ነው ጥያቄው። እፍኝ ያህል ዶላርምኮ፣ ከሸሸበት ቢመለስ አይከፋም ለማለት ከሆነ፤ አዎ አይከፋም። ግን፣ “አይከፋም፣ እፍኝ ያህል”… እያልን ብንውል፣ መፍትሄ አይሆንም።
አዎ፣ እነዚህ ሁሉ፣ የየራሳቸው የተወሰነ ጥቅም ሊያስገኙ የሚችሉ ተቀጥላና ቅርንጫፍ ጉዳዮች መሆናቸው አያጠራጥርም። ችግሩ ምንድነው? ተቀጥላና ቅርንጫፍ ጉዳዮች፣… እንደ ዋና ጉዳይ ሆነው እየገነኑ፣… ዋና ዋናዎቹን ጉዳዮች እንድንዘነጋ ያደርጋሉ።

Read 3846 times