Sunday, 13 May 2018 00:00

የሴቶች አለባበስና የወንዶች የጡት ፍርሃት

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (brooha3212@gmail.com)
Rate this item
(5 votes)

 ሰሞኑን በኢትዮጵያውያን ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የመነጋገሪያ ርዕስ ከሆኑት ነገሮች ውስጥ አንዱ ዘመናዊ (ወሲብ ቀስቃሽ) የሴቶች አለባበስ ነው፡፡ ይህ አጀንዳ ወደ ማህበራዊ ሚዲያዎች እንዲመጣ አፋጣኝ ምክንያት የሆነው ሰሞኑን ታዋቂ ሴት አርቲስቶቻችን በሰርግና በሌሎች የግል ፕሮግራሞቻቸው ላይ ለብሰው የተነሱት ፎቶ፤ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ መለቀቁ ቢሆንም፣ ዘመናችን የብሄሮች ዘመን መሆኑ ደግሞ ረጅም የጀርባ ድጋፍ እንዲኖረው አድርጎታል፡፡
እንደሚታወቀው በብሄሮችና ብሄረሰቦች ዘመን ላይ ዋነኛ ማጠንጠኛው ማንነትና ባህል ነው፡፡ አለባበስ በባህል ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ እናም እያንዳንዱ ብሄር የራሱን ማንነትና ባህል በሚያቀነቅንበት ዘመን ላይ ከብሄሩ ባህል ወጣ ያሉ አለባበሶች ሲታዩ መንጫጫት የዘመኑ ፋሽን ሆኗል፡፡
ዘመናዊ የሴቶችን አለባበስ ክፉኛ በመቃወም ረገድ ትልቁን ስፍራ የሚይዙት ደግሞ ወንዶች ናቸው። እኔም በዚህ ፅሁፌ ውስጥ የምዳስሰው ወንዶች፤ ዘመናዊ የሴቶች አለባበስ ጉዳይ፣ ይሄንን ያህል የሚከነክናቸው፣ እውን ለባህላቸውና ለሃይማኖታቸው ጠበቃ ሆነው ነው? ወይስ ከውስጥ ሌላ ገፊ ምክንያት አላቸው? የሚለውን ሐሳብ ይሆናል፡፡
ዘመናዊ የሴቶች አለባበስ አጨቃጫቂ ሆኖ ወደ ህዝባዊ አደባባይ መውጣት የጀመረው በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው፡፡ ክስተቱም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተዘጋጀው የሴቶች የፋሽን ውድድር ጋር የተገናኘ ነው፡፡ በአሜሪካ ኤምባሲ ደጋፊነት የተዘጋጀው ይህ የሴቶች የፋሽን ውድድር በሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለምና በአሜሪካ ጥላቻ ነደው ለነበሩት፣ የዩኒቨርሲቲው ወንድ ተማሪዎች የተቃውሞ መነሻ ሆኖ ነበር፡፡ በመሆኑም በወቅቱ የተቃውሞው መነሻ ርዕዮተ ዓለማዊ እንጂ የስነምግባር አሊያም የባህል ጉዳይ አልነበረም፡፡ ለምስራቁ ርዕዮተ ዓለም ተጋላጭ የነበሩት ተማሪዎች፣ የምዕራቡን የባህል ተጋላጭነትን በመቃወም ነገሩን ሙሉ በሙሉ አስቆሙት፡፡
ይሄ ከሆነ ከ20 ዓመታት በኋላ፣ ያን ጊዜ በዩኒቨርሲቲው ተቃዋሚ የነበሩት ተማሪዎች ወደ ስልጣን የመጡበት የመንግስት ለውጥ ተካሄደ። ይሄንን የ1983ቱን የመንግስት ለውጥ ተከትሎም ኢኮኖሚያችንም ከሶሻሊዝም ወደ ካፒታሊዝም ሥርዓት ተሸጋገረ፡፡ ያን ጊዜ ነበር ለረጅም ዘመናት፣ በረጅም ተራሮቻችን ከልለን ያቆየነው ባህላችንም፣ እንደ በፊቱ መከልከል በማይቻል ደረጃ ለካፒታሊስታዊው ባህል መጋለጥ የጀመረው፡፡ ይህ ካፒታሊስታዊ ባህል ከገለባበጠብን ነገሮች አንደኛው የሴቶቻችን አለባበስ ነው፡፡
በድሮው ባህል የሴት ውበት የሚያተኩረው ከአንገት በላይ ነበር - መልክ ላይ ብቻ፡፡ ይሄ የውበት አመለካከት ግን በመልክ ቆንጆ ለሆኑ ሴቶች ብቻ ያደላ በመሆኑ፣ የሰውነት ቅርፃቸው ለሚያምርና ለፉንጋ ሴቶች ተመራጭ የውበት መስፈርት አልነበረም። ካፒታሊስታዊው ባህል ግን መላውን የሴትን ልጅ አካል የውበት ምንጭ አድርጎ አመጣው፡፡
እንደ አብዛኛዎቹ አባታዊ ባህሎች (Patriarchal Culture) ሁሉ፣ የእኛ ባህልም የሴት ፍርሃት አለበት። ባህላችን የሴትን ልጅ አካልና ውበት መቋቋም አይችልም፡፡ ይሄንን አቅመ ቢስነቱን ለመሸፈን ደግሞ ሴቷን “አሳሳች” እያለ ጣቱን ወደ እሷ ይቀስራል፡፡ ሊበራሊዝም፤ ሴትን ልጅ ከእነ ተፈጥሮዋ ወደ አደባባይ ሲያወጣት ግን፣ ያን ጊዜ እኛም ከፍርሃታችን ጋር መጋፈጥ ግድ ሆነብን፡፡
ለካፒታሊስታዊው ባህል ተጋላጭ መሆናችንን ተከትሎ፣ ከፍተኛ የባህል ግጭትና ቀውስ ውስጥ እንድንገባ ያደረገንም ካፒታሊስታዊው የውበት መገለጫ፣ “የሴቶች የመራቢያ የአካል ክፍሎች” አካባቢ ላይ ማተኮሩ ነው፡፡ ይሄም የሴቶችን አካል በመሸፈን ላይ ለተመሰረተው የድሮው ባህላችን፣ ይህ አዲሱ የውበት መስፈርት በጣም የሚረብሽ ነበር፡፡ ለዚህም ነው እኔም በ2003 ላይ ባዘጋጀሁት “ፍልስፍና - 1” መፅሐፌ ላይ፣ ዘመናዊውን የሴቶች አለባበስ፣ “በባህላችን ውስጥ ማህበራዊ ሴሰኝነትን በማስፋፋት ማህበራዊ እሴቶቻችንን በከፍተኛ ደረጃ እየደረመሰ ይገኛል” በማለት ጠንከር ያለ ትችት የፃፍኩት - የባህሉ ጠበቃ ሆኜ፣ ልክ ባህል የማይለወጥ፣ ዘላለማዊና ግዑዝ ነገር አድርጌ በመቁጠር ነው፡፡
የባህል ቀውሱ ሲሰክንና ሽግግሩም ሲጠናቀቅ፣ እንዲሁም አዲሱ የሴቶች አለባበስም መለመድ ሲጀምር ግን እኔም የሴቶችን አለባበስ የምመለከትበትን መነፅር ቀየርኩ - ከባህላዊ/ሃይማኖታዊ መነፅር ወደ “የኃይል ግንኙነት (Power Relation)” መነፅር፡፡ ለዚህም ነው በ “ፍልስፍና-2” መፅሐፌ ላይ (2006) ሐሳቤን በይፋ መቀየሬን በግልፅ የተናገርኩት፤ ምክንያቴ ደግሞ ዘመናዊ የሴቶችን አለባበስ የምመለከትበትን መነፅር በመቀየሬ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ወንዶች ዘመናዊ የሴቶች አለባበስ ላይ የሚያነሱትን ጥያቄ፤ “የሥነ ምግባር፣ አሊያም የባህልና የሃይማኖት ጥያቄ” አድርጌ አላየውም፡፡ ጥያቄው ከዚያ የተሻገረና በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለ፣ የኃይል ግንኙነት ጥያቄ አድርጌ ነው የምመለከተው፡፡
የወንዶች ተቃውሞ ከላይ ከላይ እንደሚታየው፣ የአለባበስ ሥነ ምግባር ላይ ያነጣጠረ አይደለም። ከላይ ከላይ ስናየው እንደዚያ ሊመስለን ይችላል። በእርግጥ መፅሐፍ ቅዱስም ሆነ ቁርአን፣ ሴቶች እንዲከናነቡ ያዛሉ። ሆኖም ግን ጥያቄው፤ እውን ወንዶች የሴቶችን ዘመናዊ አለባበስ የሚቃወሙት፣ ከሴቶች ይበልጥ እነሱ ለሃይማኖታቸው ተቆርቁረው ነው? አይደለም!! ወንዶችን እንዲህ የበለጠ ተቆርቋሪ አስመስሎ ያወጣቸው ገፊ ኃይል ሌላ ነው፡፡ ጉዳዩ በኃይል ግንኙነት ውስጥ ወንዶች በሴቶች እየተበለጡ መምጣታቸው ነው፡፡
በመሆኑም የኔ ክርክር፣ ዘመናዊ የሴቶችን አለባበስ፤ ከባህልና ከሃይማኖታዊ ክበብ አውጥተን “ለምንድነው ወንዶች የማህበረሰቡ፣ የባህሉ፣ የሃይማኖቱ፣ የኢኮኖሚውና የፖለቲካው መሪ በሆኑበት ዘመን ውስጥ ሁሉ ሴቶች እንዲከናነቡ ህግ ሲያወጡ የኖሩት?” የሚለው ጥያቄ ላይ የሚያጠነጥን ነው። ይሄንን ጥያቄ ጠለቅ ብለን ስንመረምረው፣ ጉዳዩ የሥነምግባር ወይም የባህል ሳይሆን “የሃይል ግንኙነት(Power Relation)” ሆኖ እናገኘዋለን። አዎ!! የሴቶች አለባበስ የባህልም ሆነ የሃይማኖት ጉዳይ ሳይሆን በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለ የሃይል ሚዛን ፉክክር ነው።
ወንዶችና ሴቶች የሃይል ምንጫቸው የተለያየ ነው። የወንዱ የሃይል ምንጭ “ጉልበቱ” ሲሆን፣ የሴቷ የሃይል ምንጭ ደግሞ “አካሏ” ነው። የወንዱ የሃይል ምንጭ ላይ የሴቷ ሃይል ደካማ ሲሆን፣ የሴቷ የሃይል ምንጭ የሚገኝበት ቦታ ላይ ደግሞ የወንዱ ሃይል ደካማ ነው። ስለዚህ የሱ የሃይል ሚዛን ደካማ የሚሆንበት ቦታ ላይ ሴቷ ሃይሏን እንዳትጠቀምና ሁልጊዜ በእሱ የሃይል ሚዛን ስር ተንበርክካ እንድትኖር፣ የሴቷን የሃይል ምንጭ፣ በባህልና በሃይማኖት ስም ያደርቅባታል።
ከሁሉም በላይ ግን ከኢንዱስትሪ አብዮት በኋላ “ጉልበት” የሃይል ምንጭ የመሆኑ ነገር እየቀረ መሄዱ፣ ወንዱን ይበልጥ አቅመ ቢስ እያደረገው ሄዷል። ድሮ አካል ብቸኛው “የስራ መሳሪያ” (power of production) ነበር። “የስራ መሳሪያ” ደግሞ የሃይል ምንጭ ነው። ከኢንዱስትሪ አብዮት በኋላ ግን ማሽኖች አካልን እየተኩ የስራ መሳሪያ መሆን ጀመሩ። ወንዱ አቅመ ቢስ መሆን የጀመረው ያኔ ነው - የሃይል ምንጩ በማሽኖች መተካት ሲጀምር።
ከዚህ በተጨማሪ፣ ማሽኖች ሲመጡ የአካል ሚና ከስራ መሳሪያነት ወደ ሌላ ሚና መሸጋገር ነበረበት። ይሄኔ ነበረ ሴቶች አካላቸውን “የውበትና የደስታ ምንጭ” ማድረግ የጀመሩት። ሴቷ ኃያል ሆና የወጣችው ያኔ ነው። ይሄም በወንዱ ውስጥ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሮበታል። ወንዱ ሴቷን፤ “የድሮ የአለባበስ ስነምግባርን” እያነሳ የሚቃወማት፣ አካሏን የውበትና የደስታ ምንጭ አድርጋ እንዳትጠቀምና ወደ ቀድሞው ደካማነቷ ለመመለስ ነው።
ሴቷ አካሏን የውበትና የደስታ ምንጫ አድርጋ ስትጠቀምበት፣ ወንዱ ግን ከስራ ያሳረፈውን አካሉን ምን ያድርገው? ከሴቶች ይልቅ ወንዶች በከፍተኛ የድብርት ስሜት የሚሰቃዩት ለዚህ ነው። ከዚህ ድብርት ለመውጣት እሱም እንደ ሴቶች አካሉን የውበትና የደስታ ምንጭ አድርጎ እንዳይጠቀምበት ተፈጥሮ ፀጋዋን ነፍጋዋለች። እናም በማሽኖች ግፊት፣ አካል ከስራ ጡረታ መውጣቱ፣ የወንዱን የሃይል ምንጭ እያደረቀው ሄዷል። ወንዱ ይሄ ደካማነቱ እንዳይገለጥበት ሴቷን የድሮውን የአለባበስ ስነምግባር እያመጣ፣ እሷም አቅመ ቢስ እንድትሆን ይጥራል። በዚህ ረገድ ወንዱ ሴቷን ማስገደድ ስለማይችል ያለው አማራጭ፣ የሃይል ምንጩን “ከጉልበት” ወደ “ዕውቀት” ማሸጋገር ነው። እሱ የሃይል ምንጩን እያሸጋገረ፣ እሷን ግን አሁንም የሃይል ረሃብተኛ እንድትሆን ይፈልጋል።
ችግሩ ግን 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ “የግለሰብ ነፃነትና እኩልነት” የሚባሉ አዳዲስ እሴቶች መምጣታቸው ነው። እናም በዚህ ዘመን ላይ “ዕውቀት” ለሁለቱም - ለወንዱም ለሴቷም - እኩል የሃይል ምንጭ እንዲሆን፣ ለሁለቱም እኩል ዕድል ተሰጥቷቸዋል። ይሄን ዕድል ተጠቅመው ወንዱና ሴቷ የዕውቀት ባለቤት ቢሆኑ እንኳ፣ ሴቷ ግን ሌላ ተጨማሪ የሃይል ምንጭ አላት - አካሏ/ውበቷ። በመሆኑም በ21ኛው ክ/ዘ ላይ የወንዱ የሃይል ምንጭ “ዕውቀቱ” ብቻ ሲሆን፣ የሴቷ የሃይል ምንጭ ግን ሁለት ናቸው - “ዕውቀትና ውበት”። በመሆኑም ወንዱ በሃይል ሚዛን እየተበለጠ ሄዷል። ይሄንን ደካማነቱን ለማካካስና የሃይል ሚዛኑን ከሴቷ ጋር ለማስተካከል፣ ከአካሏ የሚመነጨውን ሃይል ለማድረቅ፣ “ውበትሽን/አካልሽን ሸፍኝልኝ” እያለ ይገኛል። ምስኪን ወንድ!!!!

Read 11567 times