Sunday, 13 May 2018 00:00

“ዶቻ!” (ብረድ) ማለት ያስፈልጋል

Written by  በላይነህ አሰጉ ሙኩሎ
Rate this item
(2 votes)

      በሴይንት ፒተርስቡርግ/ ሌኒንግራድ ተብሎ በሚታወቀው ከተማ አንድ የፒተር ዘ ግሬት ሐውልት አለ፤ ልክ አራዳ ጊዮርጊስ ያለውን የምኒልክ ሐውልት የመሰለ፡፡ የምኒልክ ሐውልት ላይ ያለው ፈረስ ፊቱን ጣሊያኖችን ድል ወዳደረጉበት ወደ አድዋ የመለሰ ሲሆን፣ የፒተር ዘ ግሬት ሐውልት ደግሞ ወደ አውሮፓ መውጫ መስኮት ብለው ከሰየሟት ሴይንት ፒተርስቡርግ በቀላሉ ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ መግባት ወደሚያስችላቸው ወደ እንግሊዝ ባህር ነው ፊቱን ያዞረው፡፡ የፒተር ዘ ግሬት ራዕይ፣ ሩሲያ በእንግሊዝ ባህር በኩል ወደ አትላንቲክ ውቂያኖስ፣ በጥቁር ባህር በኩል ወደ ሚዲትራኒያን ባህር፣ በቭላዲቮስቶክ በኩል ወደ ፓሲፊክ ውቅያኖስ ያለ ከልካይ መግባት ትችል ዘንድ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነበር፡፡ በዚህ መልክ አገሪቱ ወደ የትኛውም የዓለም ክፍል በሰላምም ሆነ ለጦርነት ባመቻት ሁኔታ ፈቃድ ሳትጠይቅ መድረስ ትችላለች፡፡ ድንገት ክፉ ቀን ቢመጣ ብለው አገራቸውን ለመከላከል፡፡ ይህ ነው የትላልቅ መሪዎች ራዕይ፡፡
በሁለቱ ሀውልቶች መካከል ያለው ሌላው ልዩነት በፒተር ዘ ግሬት ሐውልት ላይ ካለው ፈረስ ኋላ ወደ ጭራው ሊጠጋ የሚሞክር አንድ ትልቅ እባብና አውሎ ንፋስ አለ፡፡ ሀውልቱን በጎበኘሁበት ወቅት ይህ ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ብዙም አስቸጋሪ ባይሆንም፣ ምንን ለማመላከት እንደዚያ እንደተቀረጸ አስተርጓሚዬን ጠየቅኳት፡፡ አገርን በማስፋፋቱ ዘመቻ ንጉሱ ያለፈበትን መከራና አሁንም እየተከተሉት ያሉትን ችግሮች አመላካች ነው አለችኝ፡፡ በእኛስ አገር ቢሆን ትናንትናም ሆነ ዛሬ የዚህ ዓይነቱ አደናቃፊ ተንኮል ሸራቢ መች ጠፍቶ ያውቃል? አይኖርም ብለንስ ለመገመት የሚያደፋፍረን ምን ልምድ አለን?
በሰሜን ዑማውያን ዘንድ (ጋሞ፣ ጎፋ፣ሳላይታ፣ ኮንታ…) በአንድ ቤተሰብ፣ አካባቢ፣ አገር ላይ ሁኔታዎች የከፉ ሲሆኑ፣ ችግር ሲጠና፣ መግቢያ መውጫው ግራ ሲገባና ሁሉም ነገር ሲወጣጠር … አባቶች ይሰበሰባሉ። ሁሉም ነገር ከፋ፣ በሽታ ፈጀን፣ ቤተሰባችን እያለቀ ነው፣ ዝናቡ ጠፋ፣ አውሬው ሰብሉን፣ ከብቶቻችንም ሆነ ሰውን ጭምር ያሳድድ ጀመር፡፡ ይህ ከምን የመጣ ነው? እየተባባሉ ይወያያሉ፡፡ በባህሉ ወግ “አዋቂ” ይፈለጋል፡፡ ጠጠር ይጣላል፣ ‘ሹቻ ቆሮ’ ይባላል፣ በግ ይታረዳል፣ አንጀት ይታያል፣ ቦርዴ ይጠመቃል፣ ቆሎ ይቆላል፣ “ያርሾ” ይባላል፡፡ ብቻ መላ ማፈላለጊያ ነው። ይህ ሁሉ ከተደረገ በኋላ መንስዔው ይህ ነው ተብሎ ይተረጎማል፡፡ በአገርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ የተጣሰው ወግና ሥርዓት ይለያል፡፡ ከዚያም ሽማግሌዎች ይነሱና ጥፋቱ እንዳይደገም ለተሠራው ጥፋት ፈጣሪ፣ የአያት ቅድመ አያታቸው ወግና ሥርዓት በመጣሱ ይቅርታ እንዲደረግላቸው፣ የደረሰው ችግር እንዲፈታ ይመርቃሉ፡፡ በሽታ ከመካከላችን ይጥፋ፣ ጦርነቱ፣ መብረቁ፣ ጎርፉ፣ ናዳው ተወን፣ አውሬው በስፍራህ ዋል፡፡ እየተባለ ይመረቅና “ዶቻ!”/ብረድ ይባላል። ይሁኔ በላይ «ሰከን አርገው» ያለው ዓይነት ነው፡፡ ትክክል ይሁን አይሁን በደፈናው መናገር ያስቸግራል፡፡ እዚህ ላይ የተነሳሁበት ዓላማ ችግሩ ሲበዛ፣ ሁኔታዎች ሲወጣጠሩ በዝምታ አይታይም፣ መላ መፈለግ ይኖርበታል ለማለት ነው፡፡
ገጣሚው (ኃይሉ ጎሞራው ይመስለኛል).
«ችግሩ ሲበዛ ሁኔታው ሲወጠር
ውጥረቱ እንዲላላ የላላውን ወጥር»፤  ያለው ዓይነትም ሊሆን ይችላል፡፡
ብቻ ውጥረት ለማንም አይበጅም፣ እጅግም ሲወጠር ይበጠሳልና ነው፡፡ ውጥረቱን ለማርገብ ደግሞ ዋንኛውን ሚና የሚጫወቱት ሸምገል ያሉ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ሽማግሌ በሚከበርበት አካባቢና ዘመን፡፡ እኔ ሰባዎቹን እያጋመስኩ ስለሆነ ሽማግሌ ከሚባሉት፣ ማለትም ሦስት መንግሥት ከበሉት፣ በሦስት መንግሥት ከተረገጡት ወይም በሶስት መንግሥት ውስጥ ሆነው ከረገጡት አንዱ ነኝ፡፡ የእኔን ትውልድ “ጉደኛ ትውልድ” ብዬ ነው የምጠራው፡፡ ሦስት መንግሥት ማየታችን ብቻ አይደለም ጉደኛ የሚያሰኘን። ሦስት የተለያየ ርዕዮተዓለም፡- ዘውዳዊ፣ ወታደራዊ ሶሻሊስታዊ እንዲሁም አብዮታዊ ዴሞክራሲዊ ነኝ የሚል መንግሥት አየን፡፡ የትኛው አገር እና ዘመን ትውልድ ነው የተለያዩ ሥርዓቶችን በማየት ከ’ኛ ጋር ሊወዳደር የሚችል? እስኪ ከማንኛውም የዓለም ክፍል አንድ አምጡ! የሚኖር አይመስለኝም፡፡
ፊውዳል፣ ተራማጅ፣ ቀኝ መንገደኛ፣ አናርኪስት፣ ፋሺስት፣ ጠባብ ትምክህተኛ፣ ልማታዊ፣ ነውጠኛ፣ ኪራይ ሰብሳቢ … እየተባባለ፣ የተበላላ አንድ ትውልድ ከየት ይመጣል፡፡ በቀይ ሽብር ነጭ ሽብር ለህይወቱ ሳይሳሳ ለዓላማው የተላለቀው ትንታግ ትውልድስ ቢሆን፡፡ በዚህ ስርዓት ውስጥ የእሳት እራት እየሆነ ያለቀው ትውልድ ታሪክ ብዙም ተዘክሯል ብዬ አልገምትም፡፡ ብዙ እጅግ ብዙ ምስክርነት ይቀረዋል። ከዚያ በላይ ስንቱን የውጭም ሆነ የውስጥ ጦርነት አብረንም፣ ተለያይተንም ተጋፈጥን፡፡ ያን ሁሉ አሳልፈን ይኸው እዚህ ላይ ደረስን፡፡ ከዚህ በላይ “ጉደኛ ትውልድ” መሆን ከየት ይመጣል? ይኸ ሁሉ አስተምሮናል፣ አስተዛዝቦናል፣ አለያይቶናል፣ የጎሪጥ እንድንተያይ አድርጎናል፣ አንድ አድርጎም አጠናክሮናል።
ከዚህ ሁሉ ተምረን ጠንካራ መሆን ነበረብን፡፡ ገዳይም፣ ሟችም፣ ዘራፊም፣ ተዘራፊም እኛው በኛው ነበርንና ከዚህ ሁሉ ካተረፍነው ጥሩ ነገር ይልቅ ኪሳራው እንደሚያመዝን ተረድተን ወደ ልቦናችን ተመልሰን መተሳሰብ፣ መረዳዳት፣ ጠንክረን አገራችንን ለመገንባት መነሳት ነበረብን፡፡ እኛ ግን አሁንም እርስ በርሳችን ጣት እየተቀሳሰርን ነን፡፡ መካሰሱ እስከ ዛሬ አላዋጣም፣ ወደፊትም አያዋጣምም፡፡ አንዳንዴ ከሳሽና ተከሳች ማን ሊሆን እንደሚችል ውሉ ይጠፋብናል፡፡ ከትናንትና ወዲያ በነበረው፣ በትናንትናው ከሳሽ ሆኖ የሚቀርብ፣ በዛሬው ራሱ ተከሳሽ የሚሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነውና፡፡ አንዱ ግለሰብ ራሱ በአንዱ ወቅት ብቻ ከሳሽም ተከሳሽም የሚሆንበት አጋጣሚ ሁሉ ይኖራል፡፡ እዚህ ላይ ነው ሁሉን ትቶ “ዶቻ!” ማለት የሚያስፈልገው፡፡
ዶ/ር ዐቢይ ከወጡበት ወቅት ጋር የሚመሳሰል አንድ ምሣሌ ልንገራችሁ፡፡ እ.ኤ.አ በ1989-1990 (በኛ 1982) ሶቪየት ህብረት ሞስኮ ነበርኩኝ፤ ለስልጠና፡፡ ጎርባቾቭ ፔሬስትሮይካ እና ግላስኖስት የሚል መርህ አውጥቶ መላው ሶሻሊስት ካምፕ በለውጥ ማዕበል በተናወጠበት ወቅት፡፡ በወቅቱ በተለይ ሩሲያ በሦስት ወጋግራ ተወጥራ ነበር፡፡ በአንድ ወገን የቀድሞው ሁኔታ እንዲቀጥል የሚፈልጉ የፓርቲ አባላት፣ በተለይ ጠና ያሉትና ተጠቃሚ የነበሩት፣ በሁለተኛው ጎራ ፔሬስትሮይካን አጠናክረን በዝግታ እንሂድ የሚሉ የጎርባቾቭ አስተሳሰብ ደጋፊዎች፣ በሦስተኛ ወገን ደግሞ “ፔሬስትሮይካም በቂ አይደለም፤ አሁኑኑ ወደ ሊበራል ዴሞክራሲ መሄድ አለብን” የሚሉና “ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ ተታለናልና አሁን አጋጣሚውን ተጠቅመን ወደፊት ካልገፋን፣ ለሦስተኛ ግዜ ልንታለል እንችላለን” በማለት የተሰለፉ፣ በየጎራው ተሰባስበው ይፋለማሉ፡፡
ሁለት ጊዜ ተታለናል የሚሉት አንዱ ገና ሶሻሊዝም ታውጆ፣ የመሬት ከበርቴዎችና ከፍተኛ ባለሀብቶች ንብረት በተወረሰበት ወቅት ምርት ቀንሶ መሠረታዊ አቅርቦቶች በከፍተኛ ደረጃ ጠፍተው፣ ህብረተሰቡ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጥ እንኳን እስኪያጣ በመቸገሩ ሌኒን፤ አዲሱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ (NEP) የሚል ዕቅድ ነድፎ፣ ግለሰቦች እንዲያመርቱ፣ የራሳቸው ምርት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረጉ፣ ህብረተሰቡ ከችግሩ ትንሽ ተንፈስ አለ፡፡ ሌኒን ቀደም ሲል በጥይት ጭንቅላቱ ላይ ተመትቶ ስለነበረ ይኸው አገርሽቶበት ታሞ እቤት ሲውል ታዲያ ስታሊን ስልጣን ላይ ወጣ፡፡ “ሌኒን ያደረገው ትክክል አይደለም” በማለት ወደ ቀድሞው ፖሊሲ ተመለሰ። ትልቅ አምባገነንም ሆነ፡፡ ሩሲያ በርካታ የልማት ሥራዎችን በግዳጅ ብታከናውንም እስሩ፣ ግድያው፣ መሰደዱ እጅግ የከፋ ነበር፡፡ የህብረተሰቡ ኑሮም ተመሰቃቀለ፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ከስታሊን ሞት በኋላ ክሩስቼቭ መጣና ስታሊንን አውግዞ፣ በመጠኑ የተሻለ ፖሊሲ በማውጣቱ ሁኔታዎች ተሻሻሉ፡፡ እንዲያውም በዚያን ጊዜ የቀረበ አንድ ቀልድ መሳይ እውነታ አለ፡፡ ክሩስቼቭ በኮሙኒስት ፓርቲው ጉባዔ ላይ ስታሊንን ሲያወግዝ፣ ከተሳታፊዎች አንዱ እንደተቀመጠ፤ “ያን ሁሉ ሲያደርግ አንተ የት ነበርክ?” ይለዋል፤ አብሮት ይሠራ እንደነበረና በወቅቱ መቃወም እንደነበረበት ለመጠቆም በሚመስል መልኩ፡፡ ክሩስቼቭም ወዲያው፤ “አሁን የተናገረው ማነው? እስኪ ብድግ በል!” ይለዋል፤ በቁጣ ዓይነት። በፍርሀት የተሸበበ ህብረተሰብ፣ ፊትለፊት ለመናገር አይደፍርምና ተናጋሪው ፀጥ ይላል፡፡ በዚህን ጊዜ ክሩስቼቭ መልሶ፤ “በወቅቱ እኔም እንዳሁኑ እንዳንተ ነበርኩ” አለው ይባላል፡፡ ክሩስቼቭንም በበራዥነት ከስሰው እንዲያውም “በክሬምሊን ቤተ መንግሥት ውስጥ በእብነ በረድ አዳራሽ አሠርተህ የባህል ቅርሳችንን መልክ አሳጥተኸዋል” ሁሉ ተብሎ ከስልጣን ተባረረ፡፡ ይህን ያየው ህብረተሰብ ነው፣ አላምን ብሎ በኃይል ወደፊት ለመግፋት ይወጥር የነበረው፡፡         
ውጥረቱ ተጋግሎ እያለ የፔሬስትሮይካ ደጋፊዎች፣ ”ሰላማዊ ሰልፍ እንወጣለን” ብለው አንድ እሁድ ፕሮግራም ያዙ፡፡ ኮሙኒስቶቹም “እነሱ ከወጡ እኛም እንወጣለን” ብለው ለደጋፊዎቻቸው በሙሉ ጥሪ አቀረቡ፡፡ የሊበራሊዝም ደጋፊዎችም እኛስ አሉ። ሞስኮ ውጥረት በውጥረት ሆነች፣ ግጭት የማይቀር መሰለ፣ የእልቂት ደመና በአየሩ ላይ አንዣበበ፡፡ በተለያዩ ወቅቶች በሞስኮ አደባባዮች ደም የለመደው ጋንጩር፤ ክራንቻውን አግጦ፣ ዓይኑን አፍጦ፣ በየፎቁና ዛፉ ላይ ተቀምጦ የሚፈነጥዝ መሰለ፡፡ በጠቅላላው ህብረተሰብ ዘንድ ፍራቻ ነገሰ፡፡
በውጭ አገር ዜጎች ላይ ደግሞ የበለጠ ፍራቻና ሽብር ተነዛ፡፡ በወቅቱ ሥራ የሌለውና ተጠቃሚ አይደለሁም የሚለው ሩሲያዊ ደግሞ ለችግሩ መንስዔ አድርጎ ይቆጥር የነበረው ከውጭ፣ በተለይም ከአፍሪካ ሶሻሊስት አገሮች የሚመጣውን ቁጥሩ እጅግ የበዛ ተማሪ ስለነበረ ጥቃቱ በእኛ ላይ ያነጣጠረ እንደነበረም መምህራንና የትምህርት ማዕከሉ አስተዳዳሪዎች ነገሩን፡፡ በምንም ዓይነት ከቅጥር ግቢ እንዳንወጣም አስጠነቀቁን፡፡ በሰው አገር ሆናችሁ እፍኝ በማይሞላ ስብስብ ላይ በምልዓተ ሕዝቡ በሚባል ደረጃ ጥቃት ሊሰነዘር ይችላል የሚል ዜና ሲሰማ የሚኖረውን መረበሽ አስቡት፡፡ ሁላችንም ዕለቱ ደርሶ የሚሆነውን እስክናይ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በቴሌቪዥን ላይ እናፈጥ ጀመር፡፡ ለማንኛውም ተብሎ ሠራዊቱ በተጠንቀቅ ላይ መሆኑ ሁሉ ተወራ፡፡ ሕዝብ ከተቆጣ ሰራዊት አይመልስም፡፡ ራሱስ የቁጣው አካል አይደል?
የተባለው ሰልፍ እሁድ ሊደረግ ቅዳሜ ማታ፣ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ዜና እወጃ ላይ ለየት ያለ ዜና ተነገረ፡፡ ዜናው የነገውን ሰላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ፣ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ፓትሪያርክ አሌክሲ መግለጫ ስለሚሰጡ አድምጡ የሚል ነበር፡፡ ኮሙኒስት አገር ነው፡፡ መግለጫ የሚሰጡት ደግሞ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ናቸው፡፡ ምን መልዕክት ያስተላልፉ ይሆን? የትኛውን ወገንስ ደግፈው? የወቅቱን ሁኔታ ላጤነ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረው መልዕክት መገመትም አጠራጣሪ ነበር። ሰዓቱ ደረሰና በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ አሉ፡፡ እኒያ መለኮታዊ ግርማ የተላበሱና ተወዳጁ የሩሲያ ፓትሪያርክ፣ በመስቀላቸው አራቱንም ማዕዘን አማተቡና ተመልካቹን ሁሉ ባረኩ፡፡ ከዚያም፤
«ውድ የሞስኮ ከተማ ነዋሪዎች! የነገውን ሰንበት በቤታችሁ ሆናችሁ ዓምላክን ምህረት ለምኑ፡፡ ለዚህች አገር ፀልዩ፡፡ ነገ ማናችሁም ከቤታችሁ እንዳትወጡ እማጸናችኋለሁ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ሌላ ስፍራ እንዳትወጡ» የምትል ብቻ ነበረች መልዕክቷ። ልብ በሉ! ክርስቲያኖች አላሉም፣ ለምልዓተ ሕዝቡ ነው መልዕክት ያስተላለፉት፡፡ በዚያ አገር ሁኔታና በተላለፈችው መልዕክት መጠን ይህን ሁሉም ሰው ይቀበላል ብሎ ማመን አስቸጋሪ ነበር፡፡ ግን ሆነ፡፡ ሰው ሁሉ መልዕክታቸውን አክብሮ፣ እሁድን እቤቱ ዋለ፣ አንድም ሰው ሰልፍ ሳይወጣ ቀረ፣ ተፈርቶ ጦሩ ሁሉ ጣልቃ እንዲገባ የተዘጋጀለት ግጭት ውሃ ፈሰሰበት፡፡
“ዶቻ!” ማለት ይኼ ነው፡፡ ጭራውን ቆልቶ፣ ቀንዱን አሹሎ፣ ጥርሱን አግጦ ደም ማፍሰስ በለመደባት ከተማ፤ አሁንም ለመቦረቅ የተዘጋጀ ጋንጩር ሁሉ ኩምሽሽ አለ፡፡ ደስ አይልም? እንዲህ ያሉ በእምነቱ ተከታዮችም ሆነ በሌላው ዘንድ ተሰሚነት ያላቸው አባት ማግኘት መታደል ነው፡፡
እኛ ምን አጣንና ነው እንዲህ ማድረግ ያልቻልነው? በባህላችን በርካታ ጠብን የሚያበርዱ ልማዶች አሉን። የዛሬውን አያድርገውና ነፍስ የገደለ ቤተክርስቲያን ገብቶ ከደወለ ከደመኛው ይታረቅ የነበረባት አገር፣ የተጋጋለ ጦርነት እየተካሄደ እናቶች ዘንግ ይዘው፣ ቅጠል አንጥፈው በጦረኞች መካከል ቆመው ጦርነቱን ቀጥ ያደርጉ የነበረባት አገር፣ በኢራ ካዎው አማካይነት፣ ወይም በመስጊድ በሚደረግ ዱኣና በቤተ ክርስቲያን በሚደረግ ምህላ በድርቅ ዘመን ዝናብ ይዘንብባት የነበረች አገር፣ … ዛሬ እንዴት እሳቱን የሚያራግብ እንጂ የሚያዳፍን አዕምሮ አጣን? ጎረቤት ከጎረቤት፣ ባል ከሚስት፣ አባት ከልጆች ካልተስማሙ እንቅልፍ ይነሳቸው የነበሩ አባቶች በነበሩባት አገር ምን አጥፍተን ነው አገር ስትናወጥ፣ ወገን እርስ በርሱ ሲባላ በዝምታ የምናየው?
እዚህ ላይ አያለን ነው ዶክተር ዐቢይ «የጂኑን ጠርሙስ» በርቅሰው የውጡት፡፡ አይነኬ የነበሩትን ብሔራዊ እርቅ፣ የአገር አንድነት እያቀነቀኑ፣ የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸውን እንደተቃዋሚ/ተቀናቃኝ ሳይሆን እንደ ተፎካካሪ ወንድሞቻችን ማየት አለብን ያሉት፡፡ ይህን ሀሳብ ነው ወደፊት መግፋት የሚኖርብን፡፡ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ሁሉ እንጂ የተወሰኑ ቡድኖች የግላቸው የሚያደርጓት አይደለችም። ቀድሞም ሆነ ዛሬ የተለያዩ መሪዎች የተለያየ ካባ እየለበሱ ፈንጭተውባታል፡፡ ዛሬ ግን ከበረታን ከፈጣሪ ጋር ያንን ታሪክ ማድረግ የምንችል ይመስለኛል፡፡   
ጽሁፌን ከማጠናቀቄ በፊት ለጠ/ሚኒስትሩ ጥቂት ነጥቦችን ማስታወስ እወዳለሁ፡፡ አያውቁትም ብዬ ሳይሆን ለምናልባቱ ብዬ ነው፡፡
መሪ፣ በተለይም የአገር መሪ ዓላማውን ቀይሶ፣ ዕቅዱን ዘርግቶ አፈጻጸሙን ያስተባብራል እንጂ ራሱ የዕለት ተዕለት ሥራዎችን አይከውንም። አደርጋለሁ ቢልም አይችልም፡፡ ተወጣጥሮ ራሱንም ህብረተሰቡንም ይዞ ገደል ከመግባት በቀር የሚያተርፈው ነገር የለም፡፡ በእኔ ዕድሜ ያየሁት፣ ሁሉንም ሰው ባለማመን፣ ኃላፊነትን በሞላ በቁጥጥራቸው ስር አድርገው ሲውተረተሩ ተዘርጥጠው ሲወድቁና እኛንም ይዘው ሲከሰከሱ ነው፡፡ ስለዚህ ተንኮል ተንኮሉን ትተው ጥሩዎችን መጠቀም እንዲችሉ ከማኪያቬሌ አንዲት ነገር ማንሳት እሻለሁ፡፡ «ለአንድ ልዑል ብቃት ያላቸው ሚኒስትሮች መሾም ወሳኝ ነው» ይላል፡፡ ብቃት የሚለካው ከመሪው ዓላማ አንጻር ነው፡፡ ለአምባገነኑ ብቃት ማለት ያንን ዓላማ ማስፈጸም መቻል ነው፡፡ ለዘረኛው ብቃት ማለት ዘረኝነትን በብቃት ማስፋፋት …፡፡ ስለዚህ እርስዎ ለተነሱበት በጎ ዓላማ ብቃት ያለው መሪ ሊኖረዎ ይገባል፡፡ አንድ ካፒቴን ጀልባውን በብቃት የተፈለገበት ደረጃ ለማድረስ ብቃት ያላቸው ቀዛፊዎችና ቴክኒሽያኖች እንደሚያስፈልጉት ማለት ነው፡፡
ከፖለቲካ ደላሎች መጠንቀቅ፡፡ እዚህ አገር፣ (የሌላውን ሀገር ስለማላውቅ ነው) ለግል ጥቅማቸው የአዛኝ ቅቤ አንጓች ሆነው የሚቀርቡ ሞልተዋል፡፡ አንድ ግዜ በስልጠና ላይ የሰማሁትን የደላላ ታሪክ እዚህ ላይ ባስታውስ ደስ ይለኛል። በዓለም ላይ ከፍተኛውን የድለላ ሥራ ያከናወነው ግለሰብ እንዲህ አድርጓል፡፡ አንድ ገበሬ አንዲት ላም ብቻ አለችው፡፡ ደላላው “ያችን ላም በምታልብበት ግዜ ሌላ ሥራ ልትሠራ ስለምትችል ማለቢያ ማሽን ግዛ” ይለዋል። “ለማለቢያ ማሽኑ የምከፍለው በቂ ገንዘብ የለኝም” ሲለው “የተወሰነውን በጥሬ ገንዘብ ክፈለውና ለቀሪው ላሚቱን በቅድሚያ ክፍያነት አስይዛት፡፡ ባለ ማሽኑ ወተቷን እየተጠቀመባት ቆይቶ ብድሩ ሲጠናቀቅ ይመለስልሃል” አለውና በዚያ መልክ አሻሻጠ፡፡ ከሁለቱም የድለላውን ተቀብሎም እብስ አለ፡፡ ስለዚህ በአፉ አለሁ አለሁ የሚለውና የሕዝብን እንባ አለቅሳለሁ የሚል ሁሉ መርከቢቱን ለመቅዘፍ አይረዳዎትም፡፡
እኔ የምሰጋው ትልቁ ችግር የሚመጣው በእርስዎ ዓላማ ምክንያት ተጎዳሁ ከሚሉት ወገኖች ነው። ይህ ክፍል፣ በተለይ ጥቅሙን ያገኝ የነበረው ከህብረተሰቡ መበደል በመሆኑ፣ አጉል የጥቅም መንገዱ የተዘጋበት ሲመስለው በዝምታ አለማለፍን ሊመርጥ ይችላል፡፡ የርስዎ መምጣትና መስመር መቀየር (እኔ ትክክለኛውን መስመር መያዝ ነው እላለሁ) አስኮርፏቸው ተንኮል ከመሸረብ፣ በየመንገዱ አሽክላ ከመዘርጋትና አስመሳይ ወኪሎቻቸውን አስገብተው ውስጥ ውስጡን ከመቦርቦር አይመለሱምና በርካታ ዓይንና ጆሮ ያስፈልግዎታል፡፡ በሌላ ጫንቃ ተንዘራጦ ሳይሠራ መብላት የለመደ፣ ሕዝቡን መዝረፍ ኑሮው ያደረገ፣ በዙሪያው የራሱን ዘር ማንዘርና ደጋፊ ብቻ የኮለኮለ፣ ይህ ይቅር ሲባል ለመቀበል ይከብደውና ትንሽ ሳንካ ስትገኝ እሷን እያራገበ፣ ችግሩን የርስዎ መምጣት ውጤት ለማስመሰል አይቦዝንምና ይጠንቀቁ፡፡ ይህን ለመገንዘብና በተግባርም ለመተርጎም ያለዎት ልምድም ሆነ የህብረተሰቡ ድጋፍ ይረዳዎታል ብዬ አምናለሁ፡፡ በጎርባቾቭ ላይ በተለያየ አቅጣጫ ይደረግ የነበረው ጉትቻ፣ የምዕራቡን ዓለም ድጋፍ አገኘና የልሲንን ጣለባቸው፡፡ ሩሲያን የመሰለ ታላቅ አገር መጫወቻ ሆነ፡፡ ምዕራቡም መሳቂያ መሳለቂያ አደረጋት፡፡ ሰሞኑን በአንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ የየልሲንን ዶኩሜንታሪ ፊልም ያሳይ ነበረ፡፡ እኛ ጃምቦ ከምንለው ብርጭቆ እጥፍ በሚሆን ድራፍት በአንድ ትንፋሽ ጭልጥ ሲያደርጉት ያሳዩ ነበር፤ ገድላቸውን፡፡ ምን ያደርጋል ትልቅ አገር ትልቅ ነውና፣ ፑቲንን ጣለባቸው፤ ብድር መላሽ፡፡          
በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትራችን፤ሰው በጠማን ግዜ የተገኙ ነዎትና ጠንቀቅ ያለ ጉዞ፣ ያላሰለሰ ሕዝባዊ ተሳትፎ፣ የሚያስቀና ስኬት እመኝልዎታለሁ። ሁላችንም (በዳይም ሆነ ተበዳይ) በማዕበል ከተናወጠችው መርከብ በዝግታ ምድር ላይ አርፈን መህልቃችንን እንድንዘረጋ መጣር ይኖርብናል እላለሁ። ለዚህ ልዑል እግዚአብሔር ብርታቱን፣ ትዕግስቱንና ጽናቱን ይስጠን፡፡ ፈጣሪ ከዶ/ር ዓብይ ታላቅ ዓላማ ጋር ይሁን፡፡ አሜን!

Read 1764 times