Sunday, 13 May 2018 00:00

መልስ የሚሹ ሁለት መሰረታዊ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ሁሴን አዳል መሐመድ (ዶ/ር)

    ብሔር ወይስ ብሔረሰብ?
የቀበሌ፤ ወረዳ፤ ዞን ወዘተ ሕዝብ፤ ሕዝብ ነው፤
የብሔረሰብ ሕዝብ፤ ሕዝብ ነው፡፡
የብሔር ሕዝብ፤ ሕዝብ ነው፤
የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ሕዝብ ነው፡፡
ሕዝብ = አገር
አገር = ሕዝብ
ብሔር/ብሔረሰብ ሕዝቦች እያሉ በደፈናው ማነብነብና መጻፍ በአገራችን የተለመደ ነገር ሆኗል፡፡ የማህበረሰባዊ ጽንሰ ሓሳብ መግለጫዎች የሆኑት ሁለቱ ቃላት፤የአገራችን ፖለቲካ ንድፈ-ሓሳብ ማጠንጠኛ እንዲሆኑ በመደረጉ የማንም ባለ ወቅት ፖለቲከኛ ሰው፤ የፖለቲካ አፍ መፍቻ ይሁኑ እንጂ ከአገራችን ሕዝብ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር በእነዚህ ሁለት ቃላት መኻል ያለው አንድነትና ልዩነት በትክክል የሚታወቅ አይመስልም፡፡ ይህ ሆኖ እያለ ግልጽ ካልሆነ ጽንሰ-ሓሳብ ላይ ተነስቶ ቃላቱን የሕገ መንግሥት አንቀጽ አድርጎ እስከ መሄድ የተደረሰው በድፍረት መሆኑ በእጅጉ ያስገርማል፡፡
ብሔር/ብሔረሰብ፤ የማርክሲስት/ሌኒኒስት የማህበረሰብ ዕድገት ታሪክ፣ ቁስ አካልነት፣ ፍልስፍና ጽንሰ-ሐሳብ ሲሆን አንዱ ወይም ሌላው የሚገለጸው ከህብረተሰብ ታሪክ ወቅት ጋር ባለው ተዛምዶ፣ በአንድ የተወሰነ የታሪክ ወቅት የሚኖር ማህበረሰብ በማለት እንጂ በግል ስሜት አይደለም፡፡ ብሔረሰብን በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ማለትም በፊውዳላዊ ወይም ቅድመ ካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ደረጃ ውስጥ የሚገኝ ማህበረሰብ እንደሆነ ሲገልጹ፤ ብሔር ደግሞ ከፊውዳሊዝም መክሰም በኋላ ከካፒታሊዝም ማደግ ጋር ተያይዞ የተዋሃደና በከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ያለ፣ የጋራ ኢኮኖሚ ሕይወት ያለው ማህበረሰብ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ ጽንሰ-ሐሳብ አኳያ አሁን በአንድ ክፍለ ዘመን እየኖሩ ካሉት የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ሕዝቦች የትኛው፣ በየትኛው የታሪክ ወቅት እየኖረ ነው? ኢትዮጵያ አሁን በስንት የታሪክ ወቅት ውስጥ ትገኛለች? ብሔሩ የየትኛው አስተዳደር ክልል ሕዝብ ነው? ብሔረሰቡስ? ደቡብ፤ ኦሮሞ፤ አማራ፤ ትግራይ፤ ሱማሌ፤ አፋር፤… ብሔር ወይም ብሔረሰብ ለመሆን አሟልተው የተገኙት መስፈርት ምንድን ነው? የትኛው በፊውዳሊዝም ስልተ-ምርት ይገኛል? ወደ ካፒታሊስት ስልተ-ምርት እየገሰገሰ ያለ ወይም የሚያደርገውን ሽግግር ያጠናቀቀው የትኛው ነው? እያንዳንዱ መልስ የሚያሻው ጥያቄ ነው፡፡ ስለ ፌደራሊዝምና ዲሞክራሲያዊ ብሔረተኝነት የሚኖረን ዕውቀት፣ ከማነብነብ እልፍ እንዲል ከፈለግን፣በሁለቱ ላይ የጠራ ግንዛቤ መያዝ ያስፈልገናል፡፡
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (ቀ.ኃ.ሥ.ዩ) ታጋይ ተማሪዎች የተራገበው፣ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ያልተመሰረተው የማርክሲስት/ሌኒኒስት፣ የብሔር/ብሔረሰብ ጽንሰ-ሓሳብ፣ የሜዳ ትግል ስልት የመረጡትን ወጣቶች፣ በአገራችን ታሪካዊ ጠላቶችና ባልነቃ ብሶተኛ ሕዝብ ድጋፍ፣ ለሁለት አስርተ ዓመታት ጫካ ውስጥ አክርሞ፤ በጦር ሜዳ ያልተሰውቱን ታጋዮች፣ ለቤተ መንግሥት ከማብቃቱ በስተቀር በጽንሰ-ሓሳቡ ላይ የጠራ ግንዛቤ ባለመያዙ፣ ለችግሩ መቋጫ የሚሆን መፍትሔ እስከ አሁን አልተገኘም፡፡ አገራችን ሌላ ዙር ትርምስ የሚጠብቃት ይመስላል፡፡ በደርግ ላይ ድል መቀዳጀት፣ አጼ ምኒልክ ቤተመንግሥት ካስገባ በኋላ፣ ቀ.ኃ.ሥ.ዩ ተጠንስሶ፣ ጫካ ውስጥ ተደፍድፎ፣ የፈላውን ያልጠራ ጽንሰ-ሓሳብ የመንግሥት/ገዥ ፓርቲ የፖለቲካ ሰነድ በማድረግ፣ ማንኛውንም ሓሳብ ሳያቅማሙ የሚቀበሉ ዜጎችን ከየብሔረሰቡ ተወላጆች አስጠግቶ በመጋት፣ በእነርሱ መንኩራኩርነት ለማስፋፋት የተደረገው የትግል እንቅስቃሴ፤ ሕዝባችንን ለእንግልት፤ አገራችንን ለውርደት አጋልጧል፡፡
በቅጡ ካልተረዱት ጽንሰ-ሓሳብ በመነሳት የጠባብ ብሔረተኝነት ትግል አስፈላጊነትን በእንጭጭ አእምሯቸው በመቀበል፣ ለአገራችን ታሪካዊ ጠላቶችና የገዥ መደብ ዝንባሌ ለነበራቸው ቡድኖች ፍላጎት ማሳኪያ በረሐ ገብተው፣ የተደናበረው ትግል ትሩፋት ተቋዳሽ ሆነው ከቆዩ በኋላ፣ ዘግይተውም ቢሆን ሁኔታዎችን በሰከነ አእምሮ ማገናዘብ የቻሉ፣ ራሳቸውን ወደ ዳር ያገለሉ፣ አንዳንድ የቀድሞ ወጣቶች/የአሁኖቹ አዛውንቶች፣ ላሳለፉት የዜሮ ድምር የበረሐ ትግል ፍጻሜ፣ በየተራ እየተጸጸቱ ንስሐ በሚገቡበት በአሁኑ ጊዜ፣ “ጉድ ሳይሰማ አይታደርም” እንዲሉ፣ የአገራችንን የመከራ ዘመን ለማራዘም መጥበብ በማይችል ብሔረሰብ ስም ጭምር የጠባብ ብሔረተኝነት ትግል ጥንስስ የሚጠነስሱ፣ የማህበረሰብ ክፍሎች ብቅ ብቅ ማለታቸው አስደንጋጭ ነው፡፡
እዮሃ! እዮሃ!
የጎመኑ ዘመን ውጣ፤ የጮማው ግባ እንዲሉ፤
የብሔረሰብ ፓርቲ ዘመን ይሻር፤
የርዕዮተ ዓለም ፓርቲ ዘመን ይንገሥ፡፡
--እንደ ማለት፣ የጠባብ ብሔረተኝነት ገመድ በመጓተት፣ አገራችን ከአንዱ የዘመን አሮንቃ ወጥታ በሌላ የዘመን አሮንቃ! ውስጥ እንድትርመጠመጥ ይተጋሉ፡፡ በወዳጅና ጠላትነት ሁልጊዜ በደም ስንፈላለግ እንድንኖር ይሻሉ፡፡ ቀጥሎ የቷን “ብሔር”፣ “ህብረተሰባዊ ዕረፍት ለማሳጣት” ነው፡፡ እሺ ቀጥሎስ? ወደ ቀድሞ ገናናነታችን የሚመልሱን ሠረገላዎች፣ የብሔረሰብ ፓርቲዎች ይሆኑ እንዴ? በርካታ ብሔረሰቦች ሕዝቦች በሚኖሩባት ውድ አገራችን፣ የሚፈጠር የፖለቲካ አስተሳሰብ ቅኝት፣ ሁሉንም የአገሪቱን ዜጎች ሊያሳትፍ ከሚችል የጋራ ርዕዮተ ዓለም አውድ ይልቅ በብሔረሰቦች ልዩነቶች ላይ እንዲመሰረት የሚደረግበት ምክንያት ምንድን ነው? እርግጥ ነው፤ የፖለቲካ አስተሳሰብ ቅኝትን በርዕዮተ ዓለም አውድ ላይ እንዲያተኩር ማድረግ የፖለቲከኛን የአስተሳሰብ ከፍታና በሰፊ የፖለቲካ ስነ ምህዳር ውስጥ በነጻ መወዳደርን ይጠይቃል፡፡ ይህ አቅም በሌለበት፤ ዘወትር በኪራይ ሰብሳቢነት ለመኖር በጠባብ ብሔረተኝነት የፖለቲካ አንቀልባ መታዘል፣ አዋጭ የፖለቲካ አማራጭ ይሆናል፡፡   
ኤሎሄ ኤሎሄ፤
ለማ ሰበቅታኒ፡፡
ከእንግዲህ ወዲያ የብሔረሰብ ፓርቲ ስህተት፣ ያለፈ ታሪካችን አካል ሆኖ መቅረት እንጂ መቀጠል የለበትም። ምንም እንኳ ለጠባቦች የኪራይ መሰብሰቢያ፣ጊዜያዊ የንግድ ፈቃድ ወረቀት ሆኖ ቢያገለግልም ያለፈው ስህተት ያስከተለው ዕዳ፣ የብሔረሰቡ ሕዝብ ዕዳ ብቻ ከመሆን አልፎ ለሌሎች ብሔረሰብ ሕዝቦች በአጠቃላይ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተረፈ የጋራ ዕዳ ነው፡፡ እርግጥ የአማራ ብሔረሰብ ሕዝብ በይበልጥ ስለመጎዳቱ አስረጂዎች በግልጽ እየቀረቡ ይገኛል፡፡
የብሔረሰብ ፓርቲ፤ ዘመን ተሻጋሪ፣ መልካም ውርስ አይደለም፡፡ ጠባቦችን ላለፈው ስህተታቸው ንስሐ ለማስገባት ግፊት ማድረግ እንጂ ፈለጉን በመከተል አዳዲስ የብሔረሰቦች ፓርቲዎችን መፍጠር ለምንወዳት አገራችን፤ ኢትዮጵያ አንድነት መቀጠል አይረባንም፡፡ አገራችን ተነጣጥለው የቆሙ ብሔረሰቦች ሕዝቦች የሏትም፡፡ ለምሳሌ በአማራ ሕዝብ ስም ጠባብ የብሔረሰብ ፓርቲ አቋቁሜ እታገላለሁ የሚል ቡድን ቢነሳ፣ ሁኔታው ከማስደንገጥ አልፎ ያስፈራል፡፡ ይህ የማይቀር የሚሆነው ሌሎች ከጠባብነት ሐዲድ መውጣት ተስኗቸው፣ ያንኑ የጠባብነት ገመድ ነክሰው ባሉበት እየረገጡ ከቀጠሉ ብቻ እና ብቻ መሆን ይኖርበታል፡፡ ያኔ! ለአማራ ሕዝብ መጥበብ የሕልውና ጥያቄ ስለሚሆንበት የጠባብ ቡድን ዓላማን መሸከም የግድ ይላል፡፡ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ፤ ለኢትዮጵያ አንድነት ዘብ የሚቆም ትምክተኛ ሕዝብ በመባል በጠባብ ቡድን ኃይሎች ሲጠራ የኖረ ታላቅ ሕዝብ፤ እሱነቱን እንደ ባዶ ስልቻ አቅልሎ ወደ እዚህ ዝቅተኛ ደረጃ መድረስ ግድ ከሆነበት የጠባብነት ትግሉን ፈር ለማስያዝ፣ በመጀመሪያ የአማራ ሕዝብን አገር ወሰን ዳርቻ ማስመር፤ ብሎም ከዳር ድንበሩ ውጭ ስለሚኖረው የአማራ ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ሁነኛ አቅጣጫ ማስቀመጥ ግድ ይለዋል፡፡
“የእኛ ቡድን ብሔር መሬት ያን ሁሉ ያጠቃልላል”፤ “ጨቋኟ የአማራ ብሔር፣ ህብረተሰባዊ ዕረፍት አታገኝም” እያለ ሲወተውት የነበረ ጠባብ ቡድን፤ በምስጢር የነደፈው የአስተዳደር ክልሎች አወቃቀር ለአገራችን እንደ ማይበጅ አንዳንድ ነባር የቡድኑ አባላት በጸጸት ስሜት ምስክርነት እየሰጡ ነው፡፡ የኤርትራ ከእናት አገሯ መገንጠል፤ አገራችን የባህር በር ማጣት፣ ኢሕአዴግ የፈጸመው ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት/ንዝህላልነት መሆኑን ሳያወላውሉ በማውገዝ፣ ላለፈ ክረምት ቤት ከሚሠሩ ነባር ታጋዮች ጎን ለጎን፣ ልቦና የማይገዙ ደቀ-መዝሙሮች መኖራቸው ያስገርማል፡፡
ፌደራሊዝምና ዴሞክራሲያዊ ብሔረተኝነት፤ “የአገራችን ሕልውናና የአብሮነት መሰረቶች” ናቸው የሚለውን ጥርት ያለ ሐቅ የሚክድ ዜጋ ያለ ይመስል፣. ዘወትር ንግግር በማሳመር፣ እምቧ ከረዩ የሚሉ አንዳንድ የመንግሥት/የገዥ ፓርቲው ባለስልጣናት አሉ፡፡ ችግሩ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ አለመተግበሩ ስለመሆኑ መናገር ድክመት መስሎ ይታያቸዋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ብሔረተኝነት ያለ መከባበርና መዋደድ አይመጣም፡፡ በፌዴራሊዝምና ዴሞክራሲያዊ ብሔረተኝነት ዙሪያ በአገራችን የነበረው ያለፈ ዘመን መልካም ገጽታ፤ በአሁኑ የአስከፊ ዘመን መስታወት ውስጥ በግልጽ እየታየ ለመሆኑ ከዚህ በላይ ማስረጃ የለም፡፡ እስካሁን ድረስ በአገራችን የሰፈነውን የአተገባበር ጉድለት መንስዔ፤ ዓላማና ግብ እንደዚሁም ፋይዳ የሚያውቁት ምስጢረኞቹ ብቻ ነበሩ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የምስጢሩ እሽግ ፖስታ ተከፍቶ በመነበቡ ምክንያት ምስጢሩ ለአብዛኛው ዜጎች ግልጽ ሊሆን በመቻሉ፣ ሕዝቡ በዕውቀት ላይ ለተመሰረተ ትግል ተነሳስቷል፡፡
ባለፉት 27 ዓመታት አገራችን ክፉኛ አዘቅት ውስጥ የወደቀችበት ችግር መንስኤው የፌደራሊዝም ቅርጸ-መንግሥት መዘርጋቱ ሳይሆን የፌደራሊዝም ስርዓቱን ያዋቀርንበት መርህ-አልባ የአወቃቀር ንድፍ ነው፡፡ ጥቂት መገለጫዎችን እስቲ እንይ፡
አንዳንዴ ቋንቋን ወሳኝ መስፈርት በማድረግ ማህበረሰቦች የምንነት ጥያቄ ይዘው እንዲቀርቡ በማድረግ ለቀረበ የምንነት ጥያቄ አስቸኳይ ምላሽ ይሰጣል፤ አዲስ የአስተዳደር ክልል ወዲያውኑ ይፈጠራል ወይም ማህበረሰቦች ወደ አንዱ ክልል ይካተታሉ፤
ቋንቋውን ባይችልም ተካትቶ ሲያበቃ፣ ቋንቋ እንዲማር የሚወሰንበትም አለ፤
ቋንቋው ጭራሽ በመጥፋቱ የተነሳ በሚናገሩት ቋንቋ ብቻ ከሌላው ምንነታቸውን መለየት የሚያስቸግሩትን የማህበረሰብ ክፍሎች፤ በመንግሥት ድጋፍ፤ የምንነት መጠሪያ ስም አውጥተው ከነባር የማህበረሰብ ዘውግ እንዲለያዩ ይደረጋል፤  
የምንነት ጥያቄ ማቅረብ የሚያስጠይቅበት እና የምንነት ጥያቄ እንዲቀርብ ግፊት የሚደረግበት ክልል ጎን ለጎን አለ፡፡
“ከልጅ ልጅ ቢለዩ በሞት ይለዩ” የሚሉ ማህበረሰቦች ደግሞ ጆሮ ዳባ ልበስ ይባላሉ፡፡
በማይመስለን ክልል ተቀርቅረናልና፣ መልሱን፣ የሚሉ ማህበረሰቦች ደግሞ መከራ ይከፍላሉ። ማህበረሰቦቹ ይመስለናል የሚሉት ክልላዊ አስተዳደር፤ አንዴ አሳልፎ ለሌላው ስለሰጣቸው ፊት ይነሳቸዋል፤ የወሰዳቸው ክልል ደግሞ መብታቸውን በመጠየቅ፣ ክፉኛ አሳጡኝ በሚል “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ድርቅና ነገሮችን ሁሉ ያጠብቅባቸዋል፡፡ መብትን መጠየቅም ስለሚያስጠይቅ ማህበረሰቦቹ በ”እከክልኝ፣ ልከክልህ”ተደጋግፎት ይሰቃያሉ፡፡
ማህበረሰቦቹ በሰሚ ዕጦት፣ ከሁለት የወጣ ጎመን ሆነው በመንከራተት፣ከመጠውለግ ወደ መድረቅ ተጠግተዋል፡፡ የወልቃይት፤ የራያ ሕዝቦች ችግር ይኸው ነው፡፡
ብሔረሰባዊ ምንነት ተፈጥሯዊ የሆነና ማንኛውም ሰው ከተገኘበት ብሔረሰብ ጋር አብሮ የሚወለድ ወይም በማህበራዊ መስተጋብር በሚፈጠር አጋጣሚ ወይም በምርጫ የሌላውን ብሔረሰብ ምንነት በመያዝ ሊገኝ እንደሚችል ተቀባይነት ያገኘ መርህ ነው፡፡ ከዚህ መርህ አንጻር የአንድ ብሔረሰብ ቋንቋ ተናጋሪ መሆን ብቻውን ለብሔረሰባዊ ምንነት አያበቃም፡፡ ቋንቋ ብቻውን ብሔረሰባዊና አገራዊ ምንነትን ገላጭ ዋና መስፈርት ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ በሚናገሩት ቋንቋ ብቻ ማህበረሰቦችን፣ የዚህ ብሔረሰብ አባላት ናቸው ማለት ቋንቋ የሚጋሩ የሁለት ጎረቤት አገሮች ማህበረሰቦችን፣ የአንድ አገር ዜጎች ናቸው ማለት ያለመቻል ያህል ነው፡፡
ለሚቀርቡ የምንነት ጥያቄዎች በርካታ መስፈርቶችን ተጠቅሞ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ የማህበረሰቡን ታሪካዊ ዳራ አጥንቶ፤ በማህበረሰቡ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ፤ በጥንቃቄ ተመልክቶ፣ በወቅቱ መልስ የማይሰጥ ከሆነ፣ እንዲሁም አድሏዊ አሰራር ካለ፤ የቃልና የተግባር አንድነት እጥረት አጋጥሟል፤ ተቀባይነት አግኝቷል የሚባለው መርህ ተጥሷል ማለት ነው፡፡ ለምንነት ጥያቄ መልስ በሚጠብቅ ማህበረሰብና ጉዳዩ በሚመለከተው ውሳኔ ሰጭ አካል መኻል፣ የጥቅም ግጭት የወለደው ቅራኔ ይታያል፡፡ እቅጩን ለመናገር ደጋግሞ መነገር ያለበት ጉዳይ በአገራችን የደረሰው ህብረተሰባዊ ችግር መንስዔው ለድብቅ የቡድን ፍላጎት ማሳኪያ ሲባል፣ በፌደራሊዝም ስም፣ ሕዝቡን በቋንቋ ግድግድ አጥር አካልሎ በማናቆር የተፈጠረው የመልካም አስተዳደር ችግር ነው፡፡ ሕዝቡ የሚያነሳቸው ኢ-ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍል፤ ሙስናና ሌሎች ጥያቄዎች፣ በተዋረድ የሚገኙ የዋናው ችግር መገለጫዎች ናቸው፡፡
በብዝህነት ላይ ሲያተኩር ለሕዝቦች አንድነት ዝቅተኛ ትኩረት የሰጠው በብሔረሰብ ምንነት መስፈርት ላይ የተመሰረተው አዲሱ የአስተዳደር ክልሎች አወቃቀር፣ ወደ ፊት የሚያስከትለውን ችግር ባለማጤን ማህበረሰቦችን ያለ ይሁንታቸው ለዘመናት አብሮ በመኖር በጋራ ከመሰረቱት የማህበረሰብ ዘውግ በማፈናቀል ለያይቷቸዋል፡፡ የአካባቢ አስተዳደር አወቃቀሩ በአካላዮቹ ራዕይ መሰረት፤ በቋንቋ ልዩነት ላይ የተገነባ በመሆኑ ዜጎችን በአገራቸው የሚኖሩ ባይተዋሮች አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ሆኖ እያለ አዲሱ የአስተዳደር ክልሎች አወቃቀር ተበታትነው የቆዩ የብሔረሰብ ሕዝቦችን አንድ ላይ በማሰባሰብ በብሔረሰቦች ሕዝቦች መካከል ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ያስቻለን ህብረተሰባዊ ዕድገት ነው በማለት ይቀለዳል! “ዓሳን ከባሕር አውጥቶ ማንሳፈፍ፣ ለጭልፊት ርሕራሄ ይመስላታል” እንዲሉ አበው! ዳሩ ግን ምንም ያህል ጠቃሚ ይሁንም አይሁንም፤ አዲሱ የአካባቢ አስተደደር ክልል አወቃቀር የተከናወነው ከሕዝብ ውሳኔ ውጭ ነበር፡፡ የባለራዕዮችን ውሳኔ ዝም ብሎ እንዲቀበል ነው የተደረገው፡፡ ሕዝቡ ከክልል ስያሜ አሰጣጥ ጀምሮ አልመከረበትም፡፡ ክልሎች በመነሻው ላይ በቁጥር ተሰየሙ፤ ቀጥሎ ስም ሲወጣ እያንዳንዱ ስም እንዴት እንደወጣ ሕዝቡ አያውቅም። በመጨረሻም ያስከተለው ውጤት ታየ፡፡ አብዛኛው ዜጋ የስነልቦና ጉዳቱን ተሸክሞ፣ ከዚህ የተሻለ ቀን በተስፋ እየጠበቀ ነው፡፡   (ይቀጥላል)

Read 2453 times