Wednesday, 09 May 2018 00:00

በአለማችን የ1.739 ትሪሊዮን ዶላር ወታደራዊ ወጪ ተደርጓል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  አሜሪካ 610 ቢ. ዶላር፣ ቻይና 228 ቢ. ዶላር፣ ሩስያ 66.3 ቢ. ዶላር አውጥተዋል

    የአለማችን አገራት ለወታደራዊ ጉዳዮች የሚመድቡት በጀትና አመታዊ ወጪ እየጨመረ መምጣቱንና ባለፈው የፈረንጆች አመት በአለማችን በድምሩ 1.739 ትሪሊዮን ዶላር ለወታደራዊ ጉዳዮች ወጪ መደረጉን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ስቶክሆልም ኢንተርናሽናል ፒስ ሪሰርች ኢንስቲቲዩት የተባለው አለማቀፍ የጥናት ተቋም ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ አለማቀፍ ወታደራዊ ወጪ በ2016 ከነበረበት የ1.1 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ይህም ለሰላም አማራጮች ትኩረት መነፈጉን የሚያመለክት አደገኛና አሳሳቢ ክስተት ነው ተብሏል፡፡
በ2017 የፈረንጆች አመት ከፍተኛውን ወታደራዊ ወጪ ያወጡት ቀዳሚዎቹ አምስት የአለማችን አገራት አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ሩስያና ህንድ ናቸው ያለው ተቋሙ፤እነዚህ አገራት በአመቱ በአለማችን ከተደረገው አጠቃላይ ወታደራዊ ወጪ 60 በመቶ ያህሉን እንደሚሸፍኑም አመልክቷል፡፡
አሜሪካ በአመቱ ከአለማችን አገራት ከፍተኛውን የ610 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ወጪ በማውጣት ቀዳሚነቱን መያዟን የጠቆመው የተቋሙ ሪፖርት፤ ይሄም ሆኖ ግን ወጪው ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ባለበት መቀጠሉንም አክሎ ገልጧል፡፡ ላለፉት ከ20 በላይ አመታት ወታደራዊ ወጪዋን ከአመት አመት እየጨመረች የመጣቺው ቻይና፤በ2017 የፈረንጆች ዓመትም ወጪዋን በ5.6 በመቶ በማሳደግ፣ በድምሩ 228 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጓን የተቋሙ ሪፖርት ጠቁሟል፡፡ ሩስያ እ.ኤ.አ ከ1998 ወዲህ ወታደራዊ ወጪዋን ለመጀመሪያ ጊዜ ቀንሳለች ያለው ተቋሙ፤ የአገሪቱ ወጪ በ2016 ከነበረበት በ20 በመቶ ቅናሽ በማሳየት፣ በ2017 የፈረንጆች አመት 66.3 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንና ቅናሹ ከአለማችን አገራት ከፍተኛው መሆኑንም አመልክቷል፡፡

Read 1260 times