Monday, 07 May 2018 09:47

ትራምፕ ለኖቤል የሰላም ሽልማት እንዲታጩ ተጠየቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“ትራምፕ የኖቤል የሰላም ሽልማት የሚገባቸው ታላቅ ሰው ናቸው!” - የደቡብ ኮርያው መሪ

      የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኮርያ ልሳነ-ምድር ሰላምን ለማስፈን ላደረጉት ጥረት እውቅና ሊሰጥ ይገባል ያሉ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት፣ ፕሬዚዳንቱ ለመጪው የፈረንጆች አመት 2019 የታላቁ የኖቤል የሰላም ሽልማት በዕጩነት እንዲቀርቡ ለሽልማት ተቋሙ በላኩት ደብዳቤ መጠየቃቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት የሆኑት እነዚሁ 18 ፖለቲከኞች ባለፈው ረቡዕ በኖርዌይ ለሚገኘው የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ በላኩት ደብዳቤ፣ ትራምፕ በኮርያ ልሳነ ምድር ጦርነት እንዲያበቃ፣ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ እንዳይውልና በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ላበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ፣ የ2019 የኖቤል ሰላም ተሸላሚ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡
ሪፐብሊካኑ ትራምፕ ለኖቤል ሽልማት በዕጩነት እንዲቀርቡ ለተቋሙ ጥያቄውን ያቀረቡት የደቡብ ኮርያው ፕሬዚዳንት ሙን ጄኢን፤”ትራምፕ የኖቤል ሽልማት የሚገባቸው ታላቅ ሰው ናቸው” ሲሉ ባለፈው ሰኞ በይፋ መናገራቸውን ተከትሎ መሆኑንም የጠቆመው ዘገባው፤የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም በ2009 የኖቤል የሰላም ሽልማት ማሸነፋቸውን አስታውሷል፡፡
በተቋሙ ህግ መሰረት፤ ለኖቤል ሰላም ሽልማት ዕጩዎችን የሚያቀርቡት፣ የአገራት ብሄራዊ ህግ አውጪ ተቋማት አባላት፣ ፕሮፌሰሮችና ከዚህ ቀደም ተሸላሚ የነበሩ ግለሰቦችና የመሳሰሉት ብቻ ናቸው ያለው ዘገባው፤ተቋሙ ለሪፐብሊካኑ ጥያቄ ምን አይነት ምላሽ እንደሰጠ አለመታወቁን ጠቁሟል፡፡
የኖቤል የሽልማት ኮሚቴ ለዘንድሮው ሽልማት 330 ዕጩዎችን መመዝገቡን ያመለከተው ዘገባው፤አሸናፊዎቹም በመጪው ታህሳስ ወር ላይ ይፋ ይደረጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል፡፡

Read 1822 times