Monday, 07 May 2018 09:30

ተውላጠ ፍጥረት!

Written by  ደረጀ ኅብስቱ
Rate this item
(1 Vote)

 ‹‹ሰው ሲፈጠር አንድ ነው፤ ልዩነት የሚባዛው በሁለት መንገዶች ይመስለኛል፤ አንደኛው ያንኑ አንዱን በመፈላለጥ ነው፤ በቀለሙ፣ በዓይኑ፣ ባፍንጫው፣ በከንፈሩ፣ በቁመቱ፣ በውፍረቱ እየተከፋፈለ ይባዛል፤ ሰዎች በማናቸውም ምክንያት ሲከፋፈሉ ሰውነታቸው ያነስና የሰው ሽርፍራፊዎች ይሆናሉ፤›› ይሉናል ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፡፡ የአባቶቻችን ፍልስፍና ‹‹ሰው ሲፈጠር አንድ ነው›› ከሚለው ሃሳብ ከፍ የሚል ሲሆን  የሰው ልጅ በፈጣሪው አርአያና አምሳል የተሰራ ስለሆነ እጅግ የተከበረ ነው ይላሉ፡፡ ሰው ሁሉ እኩል ነው፤ አንደኛው ከሌላኛው በገጽታ፣ በእይታ ላይ ተመስርተን እንለየዋለን እንጂ ውስጠ ጥንተ ፍጥረቱ አንድ ነው፡፡ መሰረታዊ ተፈጥሯዊ ማንነቱን፣ የአንዱን ሰው ከሌላው ሰው መለየት አይቻልም፤ ባካሄዱ፣ ባለባበሱ፣ ባነጋገሩ፣ ባስተያየቱ አንዱን ሰው ከሌላው ሰው ከፋፍለን ልናውቅ እንችላለን (በአባቶቻችን ትምህርት መሰረት፤ አዳም ሲፈለጥ ሔዋን ተገኝታለች)፡፡ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም “እንዘጭ እንቦጭ” መጽሐፍ የመሃል ገጽ ላይ  የምናገኘው ርዕስ ‹ተውላጠ ፍጥረት› ይላል፤ የኅላዌ ፍልስፍናቸውን ያሳዩበት ምዕራፍ ስለሆነ በትንሹ እየጠቃቀስን እንወያይባቸው፡፡
ባህል ማህበረሰቦች የሚፈጥሩት ጣጣ እንጂ ከሰው  ጋር አብሮ የተፈጠረ አይደለም፤ አይን፣ እጅ፣ እግር፣ ጭንቅላትና ሌሎችንም የውስጥ የውጭ አካላቱን በተፈጥሮው ሰው በመሆኑ ከእናቱ ማህፀን  ሲወጣ ተፈጥሮ ‹‹አሟልታ›› ትለግሰዋለች እንጂ ከተወለደ በኋላ በተገኘበት የህብረተሰብ ክፍል ችሮታ የሚሰጡት አይደሉም፡፡ ማሰብ መቻል፣ ባለ ስሜት መሆን፣ ባለ ፈቃድ መሆን፣ ማገናዘብ፣ የመበየን ችሎታ ባለቤት መሆን በተፈጥሮው ‹ሰው› በመሆኑ የሚያገኛቸው ማንነቱ እንጂ በማህበረሰቡ የሚበየኑለት ክህሎቶች አይደሉም፡፡ ‹ሰው› የተባሉ ተፈጥሮዎች ሁሉ ከማህበረሰቡ በድርጎ የሚያገኛቸው ሳይሆኑ ‹ሰው› በመሆኑ ብቻ የተቀዳጃቸው ናቸው። የፈረንሳዩ ፈላስፋ ዣን ፖል ሳርተር፤ ‹‹existence comes before essence, that we always begin from the subjective›› ይለናል፡፡
የፕሮፌሰር መስፍን ሃሳቦች እምነት የተጎናጸፉ ሲሆኑ የሳርተር ሃሳቦች ግን ኢ-አማኒነታቸውን በይፋ ያውጃሉ፡፡ Existential Philosophy ለአማኙም ለኢ-አማኙም እኩል ሊተገበር እንደሚቻል ሳርተር ያረጋግጥልናል፡- However, it can be defined easily. Existentialists are either Christian, such as the Catholics Jaspers and Gabriel Marcel, or atheists like Heidegger and myself. What they have in common is to believe that existence comes before essence.›› በአማኝነት አመክንዮ ይሁን በኢ-አማኝነት አመክንዮ ስለ ሰውልጅ ኅልውና/መኖር፣ ስለ ሰው ምንነት እና ማንነት፤ ሰው የሚባለው ፍጡር ከመፈጠሩ በፊት የታሰበ ነበረ ወይስ ይህችን ዓለም ድንገት እንደ ማናቸውም ፍጥረታት ተቀላቀላትና እራሱን ወደ ማወቅ መጣ እያሉ በጥበብ የሚመራመሩ ሁሉ ኤግዚስተንሺያል ፈላስፎች ይባላሉ፡፡
‹‹ማንም ሰው ከእናቱ ማህፀን ሲወጣ በሰውነቱ ላይ የተለጠፈ ምንም ዓይነት ዝባዝንኬ የለም፤ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ባህል የሚባሉት ነገሮች ሁሉ የሚጫኑበት በኋላ ነው፤›› ይላሉ አዛውንቱ  ምሁር፡፡ የፈረንሳዩ ፈላስፋ ሳርተር ደግሞ፤ ‹‹Man becomes nothing other than what is actually done, not what he will want to be›› አባቶቻችን ሲያስተምሩ፤ እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው ከሁሉ ፍጥረታት በላይ አልቆ ነው ይላሉ፡፡ ይህንንም ሃሳባቸውን ሲያስረዱ፤ የሰው ልጅ የተፈጠረው እግዚአብሔር ሰውን መፍጠር ከጀመረበት ቀን መጨረሻ ላይ ነው ይሉናል፤ ከእርሱ በፊት የተፈጠሩት ፍጥረታት በሙሉ የእርሱን ክብር ለማሳየት የተፈጠሩ ናቸው እንጂ እርሱን ቀድመው በመፈጠራቸው መላእክትም በክብር አይበልጡትም(ልክ ሙሽራውን ወደ ቤቱ እንደሚያስገባ ሙሽራ፤ ቤቱን በሙሉ አሰናድቶ ነው የፈጠረው እንደማለት)፡፡
የሰው ልጅ እየተራባ ቁጥሩ ሲባዛና የዚህ ዓለም ፈተና ሲፀናበት መከራውን ለመቋቋም ሲል እራሱን በቡድን እያደራጀ ኃይል ያሰባስባል፤ ለምሳሌ በቤተሰብ፣ ማህበረሰብ፣ ጎሣ፣ ብሔረሰብ….ስለዚህም ጎሳም ሆነ ብሔር የሰው ልጅ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ ሲል ፈጠራቸው እንጂ፤ የሰው ልጅ የጎሣም የብሔርም ፍጡር አይደለም ማለት ነው፡፡ ‹‹ጎሳ ሰው አይደለም፤ ቆሞ ሲሄድ ያየው የለም፤ የሰው ሽርፍራፊዎች ስብስብ ነው፤ የራሱ አእምሮ፣ የራሱ ህሊና፣ የራሱ ምኞትና ፈቃድ የለውም፤ ይህ ማለት ጎሣ በውስጡ ካሉት ከእያንዳንዱ ግለሰብ ውጭ አእምሮም፣ ልብም የለውም፤ ልዩነት የሚባዛበት አንዱ መንገድ ይህ ነው፡፡›› ይላሉ የኅላዌ ፈላስፋው መስፍን ወልደ ማርያም፡፡ ስለ ሥነ-መንግስት የሚያትቱ ፈላስፋዎች በሙሉ የሚያጨቃጭቃቸው ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ፤ ‹ግለሰብ ይበልጣል ወይስ ማህበረሰብ?› ነው፤ ግለሰቡ ከማህበረሰቡ ከበለጠ የግለሰቡን መብት ሳናከብር የማህበረሰቡን መብት ልናከብር አንችልም ማለት ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ማህበረሰቡ ከግለሰቡ ከበለጠ፣ የማህበረሰብ መብት በሚባል ያልተጨበጠ ተለዋዋጭ ባህሪያት ምክንያት ‹አዳሜን› ፍዳዋን  እናበላታለን ማለት ነው፡፡
አንድ ግለሰብ ሲያሻው ኩሊ፣ ሊስትሮ፣ አናጢ፣ ግንበኛ፣ ሳይንቲስት፣ መምህር… ወዘተ መሆን ይችላል፤ የራሱን አቅም መገንባት እስከ ቻለበት እና መፍቀድ እስከ ቻለበት-- የግል ምኞቱ የሆነውን ሁሉ በዚህ ዓለም ላይ የማከናወን ብቃት አለው፡፡ዋናው የሚገድበው ነገር ማድረግ እችላለሁ ወይስ አልችልም ብሎ ከራሱ ጋር የተወያየው ቁም ነገር ብቻ ነው፤ ከዚያ በኋላ ያለው ጉዳይ አቅሙን የመገንባት የራሱ ቆራጥነት ብቻ ነው፡፡ በአባቶቻችን ትምህርት ‹ውኃውም እሳቱም ቀርቦልሃል፣ በፈቀድከው እጅህን ስደድ› የሚል ትልቅ ጽንሰ ሃሳብ አለ፤ የሰው ልጅ ሙሉ ፈቃድ ያለው በአምላኩ አምሳል የተፈጠረ ክቡር ፍጡር ነው፤ የራሱ ፈቃድ ባለቤት ለመሆን ሙሉ ስልጣን ተሰጥቶታል፤ የራሱ ስልጣን ባለቤት መሆኑንም ለማስመስከር የጥበብን ዛፍ ፍሬ ቆርጦ በልቷል (ያውም አትብላ እየተባለ)፤ ከፈጣሪው እንክብካቤ ወጣና በላቡ የሚያድር የዚህ ዓለም እንስሳ ሆነ፤ እነሆ በፈጣሪውም እንዲህ ተብሎ ተመሰከረለት፡- ‹‹አዳም ከኛ እንዳንዱ ሆነ….ክፉና ደጉንም ለየ፡፡››
 ‹‹በሰለጠነው አለም ውስጥ ግለሰቡ በሕግ ክልል ውስጥ ሆኖ አድራጊ ፈጣሪ ነው፤ በተቻለው መጠን ከአንዳንድ የተፈጥሮም ሆነ የባህል ግዴታዎች ነጻ ሆኖ የግለሰብ ልዕልናውን ለማስከበር የሚጥር ነው›› ይላሉ፤ መስፍን ወልደማሪያም፡፡ የፈረንሳዩ ፈላስፋ ደግሞ እንዲህ ይለናል፡- ‹‹All our acts of creating ourselves create at the same time an image of man such as we believe he must be . Thus, our personal responsibility is vast, because it engages all humanity… In fashioning myself, I fashion man.››
የሰው ልጅ የመረጠውን ሆኖ በዚህ ዓለም ላይ መኖር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል አሜሪካ የባሪያ ነፃነትን ስታውጅ፤ ‹አፍሪካ ውስጥ ነፃ ከመሆን፤ አሜሪካ ውስጥ ባሪያ መሆን ይሻላል› ብለው ባደባባይ ያወጁ ጥቁር አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ነበሩ፡፡  የዚህ ተቃራኒ የሚሆን ምሳሌ ለማንሳት ያህል፤ አንዱ ለጓደኛው “የአህያ ስጋ ይበላል ወይ?” ብሎ ይጠይቃል፤ ወዳጁም ቀበል አድርጎ፤ “ሲርብ ነው ሳይርብ?” አለው አሉ። የተቸገርን እለት መያዣው መጨበጫው ሲጠፋን መቼም የማንሰራው የለም፤ ነገር ግን የራሳችንን ፈቃድ መወሰን በምንችልበት ድባብ ውስጥ ሆነን፣ ከሰውነትና ከእንስሳነት ጥያቄ ውስጥ ገብተን የምንፋትር አይመስለኝም፡፡ አባቶቻችን በትምህርተ ህቡአት መጽሐፋቸው ውስጥ ዲያብሎስ እንዲህ ብሎ ለፈለፈ ይሉናል፡- ‹‹መኑ ውእቱ ዝንቱ ስጋ ለቢሶ ዘኢማስን… መኑ ውእቱ ዝንቱ ዘሞዓኒ›› (ይሔ ስጋ ለብሶ ደካማ መስሎ የማይዳከም፣ የማይስት ማነው?… ይሔ ስጋ ለብሶ ደካማ መስሎ ኃይለኛ የሆነብኝ ማነው? እንደማለት ነው) ለዛሬው ትርጉማችን፤ ጠረ ኢትዮጵያ መስሎ ኢትዮጵያን የሚወድ ማነው፣ ጠባብ መስሎ ትልቅነትን የሚሰብክ ማነው፣ ትንሽ መስሎ ያሸነፈኝ ማነው እያለ አጋንንት የስቅለት ዕለት በቀራንዮ አደባባይ ለፈለፈ፤ ይሉናል አባቶቻችን፡፡ የነፃ ፈቃድ እና ምርጫ ለሰው ልጅ ነው እንጂ አጋንንት ምንም ምርጫ የለውም፡፡
የሰው ልጅ ክቡር ሆኖ ተፈጥሮ ሳለ አእምሮ እንደ ሌላቸው እንደ ማያስቡት እንስሳት ሆነ ይላል የአባቶቻችን ትምህርት፡፡ እንስሳዊነት ክብርን አለማወቅ ነው፤ እንስሳዊነት አለማሰብ ነው፤ እንስሳዊነት አእምሮ ማጣት ነው፡፡ እንስሳ ስንሆን ማንም በዱላ እየነረተ፣ የፈለገውን ቆሻሻ ይጭነናል፤ እንስሳ ስንሆን ልጓም በመንጋጋችን ሰክተው ማንም እንደ ፈለገ ያሾረናል፤ እንስሳ ስንሆን በጠፍር ቆዳ እግራችን ተቀይዶ ወተታችንን ያልባሉ፣ አልያም ፍጥነታችንን ይቆጣጠራሉ፤ እንስሳ ስንሆን እንደ ጋሪ ፈረስ ፊታችን በመከለያ ተሸፍኖ  ግራ ቀኝ ማየት ተስኖን፣ ፊት ለፊት ብቻ በቅርብ እርቀት እያየን ጋሪ እንጎትታለን፡፡ ታላቁ የሩሲያ  የጥበብ ሰው ዶስቶቪስኪ እንዲህ ይለናል፡- ‹‹If God did not exist, everything would be permitted››
ፕሮፌሰር መስፍን የሚያደንቁትን  የፈረንሳዩን ፈላስፋ ሳርተር ሃሳብ አንስተው አይጠግቡትም። አባባሉን ደጋግመው ያነሱለታል፡- ‹‹Man is condemned to be free.›› የማሰብ ድክመት ከሌለብን በስተቀር፤ እራስን የማወቅ እንጭጭነት ካልተጸናወተን በስተቀር፤ የሕይወት ግንዛቤያችን አናሳ ካልሆነ በስተቀር፤ አሊያም አንዳች ኃያል ጉልበት ካልወደቀብን በስተቀር፤ የራሳችንን ነፃነት በራሳችን ፈቃድ አሳልፈን ልንሰጥ አንችልም፡፡ አገዛዞችን፣ ጭቆናዎችን፣ ጥቃቶችን አሜን ብሎ ለመቀበል ‹ሰው› መሆናችን አይፈቅድም። ‹‹አእምሮ ያለው የሚያስብና የሚያልም፣ የሚያቅድና ሀሳቡን የሚያውጅ ግለሰብ በጭቆና አገዛዝ ስር አይገኝም›› ይላሉ ፕሮፌሰሩ፡፡ በመስፍን ወልደማሪያም ‹እንዘጭ እንቦጭ የኢትዮጵያ ጉዞ›  መጽሐፍ በገጽ 86-87 ውስጥ አዳም ሲፈለጥ ሔዋን እንደወጣችው እናውቃለን፤ ሰው ማለት የራሱ አእምሮ ፣ ኅሊና፣ ምኞት፣ ፈቃድ ያሉት መሆኑን ተገንዝበናል፤ የህግ የበላይነት ካለ የግለሰብ ነፃነት እንደሚከበር አውቀናል፤ ጭቆና ማለት የአእምሮ ማሰብን ማለትም ማቀድን እና ሃሳብን ማወጅን የሚነጥቅ መሆኑን ተረድተናል እና ለኤግዚስተንሺያሊስት ፈላስፋው አዛውንቱ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፤ በእድሜ ላይ እድሜ ይጨምርላቸው፡፡

Read 1025 times