Monday, 07 May 2018 09:28

አጥንቱ (የአጭር አጭር ልቦለድ)

Written by  ከመሐመድ ነስሩ
Rate this item
(6 votes)

     ሼኽ ወይም ኡስታዝ ኡስማን የእስልምና ሃይማኖት ሊቅ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ለብዙ ዓመታት ዓሊሞች አሉ በተባሉበት ቦታ ሁሉ እየተገኙ ቀርተዋል፡፡ የሃይማኖት አዋቂ ለመሆን ብዙ ኪታቦችን አገላብጠዋል፡፡ አሁን በተራቸው የቃረሙትን ሁሉ ለሌሎች ለማካፈል ሲሉ ማስተማር ጀምረዋል፤ምላሳቸው የተባረከ ነው፡፡ የሃይማኖት ዕውቀትን ማሳወቅንና ተናግረው ማሳመንን ተክነውበታል፡፡
ተማሪዎቻቸው አፋቸውን ከፍተው ነው የሚያዳምጧቸው፡፡ “የኔ አንድም አስተዋፅኦ ወይም ታላቅ ጥረት ሳይታከልበት እንዲሁ እንደዘበት ይህን ተሰጥኦ ለሰጠኝ አላህ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ሲሉ ብዙ ጊዜ ተደምጠዋል፡፡
ሚስታቸውን እንኳን ለሌላ ነገር የሚመኝ ቀርቶ መልኳንና ቁመናዋን እንኳን የሚያውቅ የለም፡፡ ይህን የሚያውቁት እናትና አባትዋ፣ እህትና ወንድሞችዋ እና እስከ አጎትና አክስት ድረስ ያሉ ዘመዶችዋ ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎች መልክዋንም ሆነ ቁመናዋን ለማወቅና ለማድነቅ አልታደሉም፡፡ ምክኒያቱም በሰፊ ጥቁር አባያና ከላይ በምትደርበው ትልቅና ሰፊ ጅልባብ ሰውነትዋ ተሸፍኗል። መላው ፊትዋና ከአንገት በላይ ያለው የሰውነት ክፍልዋ በኒቃብ ኃይል ከሰው ዓይን ተጋርዷል፡፡
ይወድዋታል፡፡ የእሳቸው ብቻ ስለሆነች ደግሞ ኩራት ይሰማቸዋል፡፡ ይኮሩባታል፡፡
ሼኽ ወይም ኡስታዝ ኡስማን ቀይ ናቸው፡፡ ፂማቸው የተንዠረገገ ነው፡፡ ይህ የሆነው ፂም ማሳደግ ሱና ስለሆነ ነው፡፡ ራሳቸው (አናታቸው) ላይ ጥምጣም እንደጠመጠሙና ከላዩ ላይ ነጭ ኮፊያ እንዳጠለቁ ነው የሚውሉት፡፡ ዘወትር ሽክ የሚሉ ሰው ናቸው፡፡
“ምን ነው?” ቢሏቸው፤ “ንፅህና የኢማን ግማሽ ነው” ብለዋል ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ይላሉ፤ድብዳብ የመሰለውን ወፍራም ከንፈራቸውን ከጥርስ ግርዶሽነት አላቀው ፍንጭት ጥርሳቸውን እያሳዩ፡፡
ፈገግ ሲሉ ነጫጭ ጥርሶቻቸው መሀል ተሸንቁሮ ጠባብ መንገድ የመሰለው ፍንጭታቸው ለእይታ ይጋለጣል፡፡ ከልብስ ጀለቢያና ቶብ ያዘወትራሉ። በቅጥነታቸው ምክንያት እዛ ሰፊ “ድንኳን” ውስጥ ኢምንት መስለው ይታያሉ፡፡ ጥምጣም፣ ነጭ ኮፍያና፣ ነጭ ጀለብያ ወይም ቶብ መለያ ምልክቶቻቸው ናቸው።
ጀለብያ ወይም ቶብ ሆነ ወይም ሱሪያቸው ከቁርጭምጭሚታቸው በላይ የሚቀሩ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ይህም ሱና ነው፡፡
“ደረሳዎቼ ስሙ !” አሉ ከስራቸው የተኮለኮሉትን ወጣቶች አፈራርቀው እየተመለከቱ፡፡  
“ምንጊዜም ቢሆን ነፍሳችሁን ማሸነፍ አለባችሁ። ለምን? ብትሉ ነፍሲያ ቆሻሻ ነች፤ የማይሆን ቦታ ላይ ትጥላለች፤ የማይበጅ ጉድጓድ ውስጥ ሰውን ትከታለች” በእስልምና ሃይማኖት “ነፍስያህን አሸንፍ” የሚል አስተምህሮ አለ፡፡ ኡስታዝ ኡስማን እያስተማሩ ያሉት ይህንን ነው፡፡
‹‹የግል ፍላጎታችንን ለሌሎች ሰዎች ስኬትና ለወል ጥቅም ስንል ማሸነፍ አለብን፡፡ ለነፍስያ ውስወሳ ቦታ መስጠት የለብንም፡፡ ነፍስያ እኔ እኔ ማለትዋና ለኔ ለኔ እያለች መጮህዋ መቼም አይቀርም››
የተማሪዎቻቸውን የተለያዩ ፊቶች ቃኙ፡፡ ጥቁር ፊት አለ፡፡ ጠይም ፊት አለ፡፡ ቀይ ፊት አለ፡፡ ነገር ግን ከሁሉም ፊቶች ላይ የሚነበብ ጥልቅና ረቂቅ የሆነ ነገር አለ፡፡ ሃይማኖትን የማወቅና በኃይማኖቱ አስተምህሮ መሰረት ለመኖር የመመኘት ስሜት፡፡
ሁሉም የጀነት ቁልፍ እጁ ቢገባ ይወዳል፡፡ ከጀሀነም እሳት የመጠበቅና የጀነት ሰው ሆኖ ለመገኘት የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል የሚያስወስን ጥልቅ ፍላጎት አለ፡፡
እርግጥ ነው፡፡ ትዕዛዛትን ሁሉ አክብሮ፤ በአስተምህሮው መሰረት ህይወቱን በመምራት ለጀነት የሚበቃው ወይም ለጀነት የሚያበቃውን ስራ የሚሰራው ጥቂቱ ነው፡፡ ምክንያቱም ህይወት አለ፡፡ ገና ከሞት በኋላ የሚመጣውን ህይወት ማሰብ ሁለተኛ ነገር ነው፡፡ ዘላቂውንና አዋጩን ከመምረጥ፤ በእጃችን ላይ ያለውን ህይወት ማቅናትና ኑሮን ማሸነፍ ቀድሞ ይገኛል፤ ለብዙዎች፡፡
አሁንም እርግጥ ነው፤ የማይመኝ የለም፡፡ ግን ምኞትና ተግባር፤ፍላጎትና  ኑሮ ደቡብና ሰሜን የሚሆንበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡
“እና  . . . . . . .” አሉ ሼህ ኡስማን
“እና ፍላጎታችንን መጨፍለቅ፤ስሜታችንን መግራትና መልካም ተግባር ላይ መገኘት ይገባናል!›› አሉ፤ በጥርሳቸው የነከሱትን መፋቂያ እየነቀነቁ፡፡
“ለምሳሌ አንድ የወደድነውና የራሳችን ለማድረግ ያሰብነው ነገር ይኖራል፡፡ ወንድማችን ያንኑ ነገር መፈለጉን ካወቅን ነፍስያችንን አሸንፈን፣ ያንን ነገር ለወንድማችን ቅድሚያ በመስጠት መተው ይኖርብናል። እስልምና መስዋዕትነትን የሚያበረታታ እምነት ነው። ለኔ ከማለት ይልቅ ለወንድሜ ማለትን ማስቀደም አለብን--”
ተማሪዎቹ ዝም እንዳሉ ተቀምጠው የተማሩትን ትምህርት እንዴት አድርገው በህይወታቸው እንደሚተገብሩ እያሰቡ ትምህርቱን ይከታተላሉ፡፡
“ልብ በሉ ነፍስያ የዋዛ አይደለችም፡፡ ነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) ጦር ሜዳ ሄዶ ጠላትን ከማሸነፍ ይልቅ የመጀመሪያው እንዲሁም ትልቁና ዋናው ጀሀድ ነፍስያን ማሸነፍ ነው፡፡ ያሉትን አትዘንጉ፡፡ የሆነ ነገር ብንፈልግና ወንድማችን ያን ነገር የሚፈልግ ከሆነ፣ ነፍስያችን አትሰጠው አትስጠው ማለትዋ አይቀርም፡፡ እኛ ግን ነፍስያችንን በማሸነፍ፣ ያንን ነገር ለወንድማችን መተው ወይም መስጠት አለብን!”
ኡስታዝ ኡስማን ማስተማሩን ከጨረሱ በኋላ ከተማሪዎቻቸው ጋር በመሆን ሰሞኑን ወደ ተጠሩበት ቦታ ሄዱ፡፡ ቦታው የአንድ ሙስሊም ባለሀብት ቤት ነው። የተጠሩትም ለሰደቃ ነው፡፡
ቤቱ ደረሱ፡፡ ገቡ፡፡ ምግብ በአንድ ትሪ ላይ ሆኖ ለኡስታዙና ለተማሪዎቻቸው ቀረበ፡፡ ሼሁና ደረሳቸው የቀረበላቸውን ምግብ ጠቅልለው መጉረስ ጀመሩ። ቀይና አልጫ ስጋ ወጥ እንጀራ ላይ ፈሶ (አተኩረው ሲያዩት ጊቤ ወንዝን ይመስላል) ቀረበላቸው። እንጀራው መሀል ላይ አንድ አጥንት ወድቃለች፡፡ ኡስታዝ ኡስማን ፈጠን ብለው አጥንቷን በማንሳት መጋጥ ጀመሩ፡፡
ከተማሪዎቹ አንዱ፤ “ምነው ኡስታዝ?” አለ
“ምነው?” አሉት አጥንት እንዳገኘ ውሻ በመስገብገብ አጥንታቸውን እየጋጡ፡፡
“ቅድም ነብሲያችንን ማሸነፍ አለብን! ብለው እያስተማሩ አልነበር?!”
“እኮ!”
“ምነው ታዲያ አጥንትዋን ቀድመውን አነሱ?!” አለ ተማሪው በመደነቅ፡፡
“እኮ!” አሉ ኡስታዙ በድጋሚ፡፡
“ነፍስያዬ ስጥ ስጥ ስላለችኝ፣ እሷን አሸንፌ እየበላሁ ነው” አሉ ኡስታዝ ኡስማን፤እንደዋዛ ፈገግ ብለው፡፡
ተማሪዎቹ ሁሉ በሳቅ አውካኩ፡፡ “የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል” እንደተባለው መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡ ተማሪዎቹ በሳቃቸው መሀል እውነትና ዕውቀት፣ማስተማርና መሆን ምን ያክል እንደሚጣረሱ እያሰቡና እየተገረሙ ወደ ትሪው አጎነበሱ፡፡

Read 6299 times