Print this page
Monday, 07 May 2018 09:22

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)

 “ከዋሻው መጨረሻ … ብርሃን አለ!!”
                 

“… ፍትህ በሚገባ ይበየናል፤
ሻል ያለ ዓለምም ይታያል፡፡
ከእንግዲህ መታሰር ይብቃ
ተነሱ ባሮች ጣሉ ቀንበር፣
የዓለም መሰረት አዲስ ይሁን፣
ኢምንት ነን ዕልፍ እንሁን፡፡
… ኢንተርናሲዮናል -
    የሰው ዘር ይሆናል!!”
ከመጠጥ ቤት ቢወጡም መዘመራቸውን አላቆሙም። ድብን ብለው ሰክረዋል፡፡ ዛሬ የሜይ ዴይ ዋዜማ ነው። “የኮንስትራክሽን ዕቃዎች እጥረት አጋጥሞናል” ተብለው ከስራ ከተቀነሱ አንድ ወር ሊሞላቸው ነው፡፡ ሁለቱም ግንበኞች ናቸው … አጅሬና ጓደኛው!!
አጅሬው ቤቱ ደጃፍ ሲደርስ “ሜይ ዴይ ለዘለዓለም ይኑር!!” በማለት ጓደኛውን ተሰናበተ። … “እኛ መኖር ሳንችል እሱ እንዴት ይኖራል? … መዝሙሩ እንኳ ተረሳን … ቻዎ!” አለው ጓደኛው፤ … እጁን እያወዛወዘ፡፡
ሚስቱ በሩን እንደከፈተችለት እየተንገዳገደ ከወንበሩ ላይ ተዘረፈጠ፡፡ እንዲህ ሆኖ አይታው አታውቅም፡፡ … ተቆጣች፡፡ … ልክ፣ ልኩን ስትነግረው … “አትወደኝ ይሆን እንዴ?” ሲል ተጠራጠረ፡፡ መቀነቷን እየጎተተ፡-
“እኔ እንዳንቺ ብሆን ቢኖረኝ መቀነት
እርር፣ ድብን ስል እምታነቅበት …” እያለ ሲንተባተብባት …
“ከፈለግኸው እንካ … ውሰድና ታነቅ
ሳታደርገው ብትቀር ከልቤ ነው ምስቅ…” ብላ ወረወረችለት፡፡ … የድንገት ገጣሚነቷ በንዴቷ ውስጥ ሳቂ፣ ሳቂ እያላት፡፡ አጅሬው መቀነቱን እያንዘላዘለ መኝታ ቤታቸው ገብቶ በሩን ደረገመው፡፡
የመኝታ ሰዓት ሲደርስ …
“ሰውየው ክፈት ልተኛበት” … ብትለው … ድምፅ የለም፡፡
“አንተን‘ኮ ነው ክፈት!”
ዝም
“ራትህን አትበላም?”
ዝም፡፡
ቆይቶ እንደሚለምናት እያሰበች … “ተወዋ!” አለችውና አግዳሚዋ ላይ ጋደም አለች፡፡ … አልመጣም፡፡ … አኮረፈች። … ነጋ፡፡ ቁርስ አዘጋጅታ አስቀመጠችለትና ወደ ጉዳይዋ ሄደች። ስትመለስ ሁሉም እንደነበረ ጠበቃት፡፡ … ጉድ፣ ጉድ ስትል የምሳ ሰዓት ደረሰ፡፡ “ወጥቶ ሄዶ ይሆን?” በማለት አሰበች፡፡ በሩን ለመክፈት ስትሞክር እንደተጠረቀመ ነው፡፡ …
“አላበዛኸውም እንዴ?” ብላ በሩን በቁጣ ደበደበች፡፡ መልስ የለም፡፡ … እየተነጫነጨች በቁልፉ ቀዳዳ አጮለቀች። ያየችው አስደነገጣት፡፡ … ጩኸቷን አቀለጠችው፡፡ … ጎረቤት ተሰበሰበ፡፡ የሆነውን በየተራ እየተመለከተ “ጉድ!” አለ፡፡ ሚስት፤ “የኔ ጥፋት ነው! … የኔ ጥፋት ነው!” ኡኡኡ! አገር ይያዝልኝ” በማለት ራሷን መቆጣጠር አልቻለችም፡፡ … ድንገት የሽንኩርት መክተፊያዋን አንስታ ራሷን ወጋች፡፡
***
እውነተኛ ፍቅር የስጋና የነብስ ጋብቻ ያህል ነው። አንድ ነፍስ ያላቸው ሁለት ሰዎች የተጣመሩበት!! … ጋብቻ የስጋ ምሉዕነት (fulfillment of flesh) ብቻ አይደለም፡፡ … In true love it is the soul that embraces the body … እንደሚባለው፡፡ ጥሩ ባሎች ጥሩ ሚስት፣ ጥሩ ሚስቶች ጥሩ ባል ካላገኙ ትርፋቸው ሰላም፣ ፍቅርና ደስታ ሳይሆን ፀፀትና ኪሳራ ነው፡፡ ትዳር መረዳትን፣ ትዕግስትን፣ መቻቻልንና አስተውሎትን ይፈልጋል፡፡ ችግርና መሰልቸትን፣ አሉባልታና ቅናትን መቋቋም ለማይችሉ ትዳር በፍላጎት የገቡበት ገሃነም ይሆናል፡፡ ታላቁ ስፒኖዛ …” በትዳር ደስተኛ ሊሆኑ የሚችሉት ፈላስፋንና ጠቢባን ናቸው፡፡ … እነሱ ደግሞ አያገቡም፡፡ (Only philosophers can be happy in marriage and philosophers do not marry) ይለናል፡፡
ስፒኖዛዊ አስተሳሰብ ትንሽ ጫን ያለ ቢመስልም የሌሎች ብዙ ሊቃውንት ሃሳብም ከሱ በጣም የራቀ አይደለም፡፡ ትዳር አብሮ ከመብላትና ከመጠጣት፣ አብሮ ከመተኛትና ከመውለድ ባለፈ … የጋራ ፍልስፍናን፣ የህይወት ትርጉም መረዳትን፣ ለዕድገትና ለስልጣኔ መቆምን ምሰሶ ሊያደርግ ይገባል፣ ከራሳችን የተሻለ ትውልድ በማፍራት፣ የዛሬ ችግር ነገ እንዳይደገም ማድረግ መቻል አለበት፣ መጪው ጊዜ ለተረካቢዎቹ ምቹ እንዲሆን ጥርጊያውን ማሰናዳት ይኖርበታል በሚለው ይስማማሉ፡፡
በቂ ምግብ፣ በቂ መኖሪያ፣ በቂ ሃሳብ፣ በቂ ፍቅር ከሌለ የመንፈስ ሰላምና ደስታ አይኖርም፣ የ“ብዙ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሏት” ህግን በባዶ ሜዳ ስራ ላይ ማዋል ስህተት ነው በማለትም ይመክሩናል፡፡ በጥቅምና በአላፊ ሁኔታዎች እንዳንደለልም ያስጠነቅቃሉ፡፡
***
ወዳጄ፡- ባለፈው ማክሰኞ ሜይዴይን አክብረናል። ምንም እንኳ ትዝታ ብቻ የተወልን ቢመስልም። ዓለም ተቀይሯል፣ ጊዜው ተለዋውጧል፡፡ ትናንት በርግጥ የለም፣ ጥላው ግን ሄዶ አላለቀም፡፡ ትናንት የነበረው የሰራተኞች አንድነት በዓለም አቀፍ የሰው ልጆች ህብረት፣ ኢንተርናሲዮናል፣ በግሎባላይዜሽንና በኢንተርኔት፣ አድካሚና አሰልቺ የነበረው የጉልበት ሥራ በኤሌክትሮ ሜካኒካል ማሽነሪዎች እየተተካ ነው፡፡ ማሽን ደግሞ አይደራጅም፣ ሰልፍ አይወጣም አይሰበሰብም፣ በዓል አያከብርም፣ የቅጥር ውልና የህብረት ስምምነት እየጠቀሰ ለመብት አይሟገትም፡፡ ማሽን አይፈራም፣ አያዝንም፣ አያማርርም፡፡ … ይሰራል ወይ ይቆማል … በቃ!! … “ጥረህ … ግረህ ብላ” ተብሎ አልተረገመም ወይ አልተመረቀም፡፡ ትናንት “ወዝ አደር”፤ “ላብአደር” እየተባለ ያነታረከው ፕሮሎታሪያን (Proletarian) የሚለው ቃል … ቃሉ ብቻ ሳይሆን ሰውየው ራሱ ደብዝዟል፡፡ በምስጢር ወረቀት ፅፎ፣ አባዝቶ ማሰራጨት ተረት ሆኗል፡፡ … ዕድሜ ለኢንተርኔት!! … ከሞላ ጎደል የአውሮፓና አሜሪካ ባለሀብቶች አስተሳሰብ (mentality) ተቀይሯል፡፡ … ግብር አያጭበረብሩም፣ ሰራተኞቻቸው የኔነት መንፈስ (sense of belongingness) እንዲኖራቸው የትርፍ ማካፈልና የባለሀብትነት (share holding) መጠነኛ ድርሻ አላቸው። እነሱ ቢያልፉ ድርጅቱ የሚቀጥልበት አሰራር (Legacy) በመኖሩ የሰራተኛው የመኖር ዋስትና የተረጋገጠ ነው። ትርፋቸው በደሃው ህዝብ ላይ እንደፈለጉ የሚጭኑት ሳይሆን ዕቃው ተመርቶ በገበያ ላይ እስከዋለ ድረስ የፈጀው ወጭ ተሰልቶ፣ የተወሰነ ጭማሪ ብቻ (ብዙ ጊዜ ከ10-15 በመቶ) እንዲያደርጉበት ይፈቀድላቸዋል፡፡ ነጋዴውም በዕቃው ላይ ትክክለኛውን ዋጋ የመለጠፍ ግዴታ አለበት፡፡ ማታለል አደጋ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ያገኙትን ትርፍ ለሰብዓዊና ለተፈጥሯዊ ችግር ማቋቋሚያ ይለግሳሉ፡፡ በነዚህና በመሳሰሉት ምክንያት ሜይዴይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዘ እዚህ ደርሷል፡፡
አምራችና ድጋፍ ሰጭ፣ የቢሮና የፋብሪካ ሰራተኛ፣ የአእምሮና የጉልበት ወይም አውሮፓውያኑ ነጭ ኮሌታ (white colar) እና ሰማያዊ ኮሌታ ወይም ቱታ (blue colar) የሚሉት ነገር የመደብ ወይም የኢኮኖሚ ጉዳይ መሆኑ እየቀረ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እያንዳንዱ ሰው በዕውቀቱ፣ በችሎታውና በዝንባሌው በተለይ ደግሞ በፍላጎቱ የሚሰረባት ዕድል ካገኘ በተሰማራበት ቦታ ፍሬያማ መሆኑ በጥናት በመረጋገጡ ነው፡፡
***
ወደ መጀመሪያው ጨዋታችን እንመለስ፡፡ … ፖሊስ ሚስትን ወደ ሆስፒታል ልኮ መኝታ ቤታቸውን ለመስበር እንደተዘጋጀ ከውስጥ በኩል ተቆልፎ የነበረው በር በድንገት ተከፈተ፡፡ በቀዳዳ ሲታይ … የተሰቀለ ሰው የሚመስለው፣ ጨርቅ የተጠቀጠቀበት ቦላሌና ጃኬት በገመድ ጣርያው ላይ ተንጠልጥሏል፡፡ ለቀስተኛው ግራ ገባው፡፡ … አጅሬው ተደብቆ ከነበረበት ጥግ ብቅ አለ፡፡
“ተናድጄ ነበር፡፡ … ብሞት ምን እንደሚሰማት ለማወቅ ስለፈለግሁ የሞትኩኝ አስመሰልኩ” አለ፡፡ … ሚስቱን ባይኑ እየፈለገ፡፡ … ዝም ሲሉ … “ይቅርታ እናንተ ተቸገራችሁ … አሁን ወደየስራችሁ መሄድ ትችላላችሁ … አመሰግናለሁ!” አላቸው፡፡ ሚስቱ ህይወቷን ለማጥፋት በስለት ራሷን በመውጋቷ፣ ወደ ሆስፒታል እንደተወሰደች ነገሩት፡፡ በቆመበት ደረቀ፡፡
ፖሊሶቹና ጎረቤቶቹ ተጋግዘው በካቴና አሰሩት፡፡ ወደ ጣቢያው ሲወስዱት “ልሰናበታት” ብሎ ተማጠነ። … ወሰዱት፡፡ ህይወቷ መትረፉ ተነገረው፡፡ ከሰመመን እስክትነቃ ጠበቃት፡፡
“ምን ሆኛለሁ?” ስትል ጠየቀች፡፡ ባለሙያዎቹ ዝርዝሩን አስታወሷት፡፡ አጅሬው እግሯን እያሻሸ ይንሰቀሰቃል፡፡ ስትረጋጋ፤ ካቴናውንና ፊቱን ስታይ ሳቋ መጣ፡፡
“ምን ሆነህ ነው?” አለችው በቀስታ፡፡
“ሰክሬ”
“ኬት አምጥተህ ጠጣህ?”
“ተበድሬ”
“ለምን ተበድረህ ትጠጣለህ?”
“ተናድጄ”
“ምን አናደደህ?”
“ሜይ ዴይ!”
“እንዴ?... ምን ማለት ነው?”
… ከስራ ተቀንሻለሁ፣ ኑሮ ተወዷል፣ አንቺ ነፍሰ ጡር ነሽ … ምን ይውጠኛል? … ሜይዴይ እንኳ ካደን፣ መዝሙሩም ተረሳን”
“አይዞህ የአዲሱ ልጅ ገድ አይታወቅም” አለችው እየሳቀች፡፡
“እውነት ነው፡፡ ሞተሽ ቢሆን ኖሮ ….”
“አንተም ሞተህ ቢሆን …”
ሁለቱም የሚሉትን ሲያስቡ … ውሁድ ነፍሳቸው ጨረሰችላቸው፡፡
“ተስፋም ይሞት ነበር” ብላ!!
ወዳጄ፡- “ከዋሻው መጨረሻ ብርሃን አለ” … ያለን ማን ነው?
ሠላም!!

Read 1214 times