Print this page
Monday, 07 May 2018 09:17

“ባዶ እግር” ቲያትርን በፍልስፍና ዓይን

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፍልስፍና መምህር )
Rate this item
(0 votes)

 “ባዶ እግር” ቲያትርን በፍልስፍና ዓይን

     ‹‹እኔ ለአቴናውያን ከአማልክቱ የተላኩ ተናዳፊ ዝንብ (Gadfly) ነኝ፤ መንግስት ከስልጣኑ ብዛት የተነሳ ኃላፊነቱን ዘንግቶ እንደሚሰባ በሬ እየወፈረ እንዳይተኛ እኔ እየነደፍኩ አነቃዋለሁ፡፡ እኔን ከገደላችሁኝ ግን መንግስትን የሚያነቃና የሚቆነጥጥ ሌላ ሰው አታገኙም፡፡ ያን ጊዜ መንግስት በእናንተ ላይ አንባገነን ይሆናል፡፡››
     

    “ባዶ እግር” በታላቁ የጥንታዊ ግሪክ ፈላስፋ ሶቅራጠስ (470-399 ዓ.ዓ) ህይወትና አስተሳሰብ ላይ ተመስርቶ የተሰራ ቲያትር ነው፡፡ ተውኔቱ ማክስዌል አንደርሰን በተባለ አሜሪካዊ እ.ኤ.አ በ1951 ዓ.ም Barefoot in Athens በሚል ርዕስ የተፃፈ ሲሆን፣ ቲያትሩ እ.ኤ.አ በ1966 ወደ ፊልም ተቀይሯል። ድርሰቱን ወደ አማርኛ ተርጉሞ ያቀረበልን ደግሞ አስቻለው ፈቀደ ሲሆን የተውኔቱ ዝግጅት በራሄል ተሾመ ተሰርቷል፡፡ በትወናው ላይም አንጋፋና ወጣት አርቲስቶች ተሳትፈውበታል፡፡ እኔ የቲያትር ባለሙያ ስላልሆንኩ፣ ትያትሩ ላይ የማቀርበው አስተያየት ከፍልስፍናዊ ይዘቱ አንፃር ብቻ ነው፡፡
ጥንታዊ ግሪክን በጨረፍታ
ግሪክ በሜዲትራኒያን ባህር ላይ የሚገኙ የተለያዩ የከተማ መንግስታት (City States) ተሰባስበው የፈጠሯት ሀገር ናት፡፡ ከእነዚህ የከተማ መንግስታት ውስጥ አቴንስና ስፓርታ ይገኙበታል፡፡ አካባቢው ከፍተኛ የሆነ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ስለነበረ በተለይ ዋነኛ የነጋዴዎች መተላለፊያ የነበረችው አቴንስ፤ ሁልጊዜ በአዳዲስ ሰዎች የምትጎበኝና በዚህም የተነሳ አቴናውያን ለአዳዲስ ባህሎችና አስተሳሰቦች የተጋለጡ ነበሩ፡፡ የአቴናውያን ባህልና አስተሳሰብ በዚህ ተለዋዋጭ በሆነው ክስተት የተቀረፀ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በሐዋርያት ስራ ላይ ይሄንን መስክሯል፡፡
ትወናና የመድረክ ዝግጅት
ሶቅራጠስ አቴናዊ በመሆኑ በቲያትሩ ላይ የሶቅራጠስ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን፣ ፈላስፋው የወጣበት ባህል፣ የህዝቡ አስተሳሰብና የመንግስት ዘይቤያቸው ሁሉ የግድ መዳሰስ ነበረበት፡፡ በዚህ ረገድ ተዋናዮቹ የጥንት አቴናውያን የሚከተሉትን አለባበስ፣ የመንግስት ፕሮቶኮልና የፍትህ ሥርዓት አስመስሎ በማቅረብ ረገድ ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ ነው፡፡ ከመድረኩ ጀርባ የሚታየው ኪነ ህንፃም በትክክል የጥንት አቴናውያን ኪን ህንፃን ተከትሎ የቀረበ ነው፡፡
ሌላው፣ ትወናው ከአንድ ክስተት ወደ ሌላ ክስተት ሲሸጋገር የሚታየው የመሸጋገሪያ ትዕይንትም እንዲሁ የጥንት ግሪካውያንን ባህል መሰረት ያደረገ መሆኑ በጥሩ ጎኑ የሚታይ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የጥንት ግሪካውያን ለዓለም ካበረከቷቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ አትሌቲክስ ነው፡፡ በቲያትሩ ላይ የቀረበው የመሸጋገሪያ ትዕይንትም ይሄንን የግሪካውያንን አትሌቲክስ መሰረት ያደረገ ነው፡፡
የጥንት አቴናውያን ምሁራን
ወደ ቲያትሩ ፍልስፍናዊ ይዘት ስንሄድ በዋነኛነት የምናገኘው የሶቅራጠስንና የአቴናውያንን ምሁራዊ ጀብደኝነት ነው፡፡ ሶቅራጠስ በነበረበት በ5ኛው ክፍለ ዘመን (ቅድመ ልደት) በአቴንስ ሁለት ዓይነት ምሁራን ተነስተው ነበር፡፡ የመጀመሪያዎቹ ምሁራን ሶፊስቶች ናቸው፡፡ ሶፊስቶች ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ የመሳፍንትና የሐብታም ልጆችን በክፍያ የሚያስተምሩ ሲሆን አስተሳሰባቸውም በእውነትና በስነ ምግባር አንፃራዊነት ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ሶፊስቶች በንግግር የማሳመን ጥበብ ላይ ስለሚያተኩሩ፣ ትምህርታቸው በዋነኛነት ቋንቋና የንግግር ክህሎት ነው፡፡
‹‹ነባራዊ እውነት›› የሚባል ነገር የለም ብለው ስለሚያምኑ፣ እውነት ለሶፊስቶች ‹‹ማሳመን›› ነው። ከሶፊስት ምሁራን ውስጥ በጣም የታወቀውና በሶቅራጠስ ዘመን የነበረው ፕሮታጎረስ (490-420 ዓ.ዓ) ነው፡፡ ፕሮታጎረስ ይበልጥ የሚታወቀው ‹”Man is the measure of all things.” በሚለው አባባሉ ነው፡፡ በዚህ ፍልስፍና መሰረት እውነት፣ ስነምግባርና ውበት እንደ ተመልካቹ ስለሆነ አንፃራዊ ናቸው፡፡ ይህ የሶፊስቶች አመለካከት በኋላ ላይ ብዙ ተከታይ ባያገኝም ዘመናትን ተሻግሮ ግን እንደ ፍሬድሪክ ኒቸ እና የድህረ ዘመናዊነት ፈላስፋዎችን መፍጠሩ አልቀረም፡፡
የአቴናውያን ሁለተኛው የምሁራን ቡድን ደግሞ በሶቅራጠስ በኩል የመጣው ነው፡፡ ሶቅራጠስ የተነሳው የሶፊስቶችን ‹‹የአንፃራዊነት›› አስተምህሮ በመቃወም ነው፡፡ ሶቅራጠስ የሶፊስቶች አካሄድ የደቀነውን ሀገራዊ አደጋ በደንብ ተገንዝቧል፡፡ ሀገር የሚመሰረተው ሁሉም ዜጎች እኩል በሚስማሙበት የጋራ እሴቶች አማካኝነት ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ እውነት፣ ፍትህ፣ ውበት፣ ፍቅር፣ እኩልነትና መልካምነት ለእያንዳንዱ ዜጋ አንፃራዊ ከሆነ የጋራ ማህበረሰብና ሀገር የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ ይሄ ደግሞ አቴናውያንን የሚወዷትን ሀገራቸውን ያጠፋባቸዋል፡፡ ሶቅራጠስ ‹‹እሴቶች›› አንፃራዊ እንዳልሆኑ በጥያቄና መልስ ለወጣቶች ሲያሳያቸው የነበረውና ከሶፊስቶች ጋርም አብዝቶ ሲከራከር የነበረው ሀገሩን ከሶፊስቶች አደጋ ለማዳን ነው፡፡ ይህ የሶቅራጠስ ሀገርን የማዳን ጥረት በ‹‹ባዶ እግር›› ቲያትር ላይ የተገለፀው በመጠኑ ነው፡፡
‹‹እሴቶች አንፃራዊ ሳይሆኑ ነባራዊ ናቸው›› የሚለው የሶቅራጠስ ፍልስፍና ግን በፕሌቶና በአርስቶትል በኩል አድርጎ በአውሮፓ ውስጥ ጠንካራ የፍልስፍና ዘውግ መሆን ችሏል፡፡
የእውነትና የሀገር ፍቅር
በቲያትሩ ላይ በደንብ ጎልቶ የተገለፀው  ሶቅራጠስ ለእውነትና ለሀገሩ ያለው ፍቅር ነው፡፡ አቴና ከአካባቢው የከተማ መንግስታት በተለየ ሁኔታ ለዜጎቿ ፍትህን፣ ዲሞክራሲንና ነፃነትን አጎናፅፋለች፡፡ በዚህም አቴናውያን ለሀገራቸው ትልቅ ፍቅር አላቸው፡፡ በቲያትሩ ላይ ሶቅራጠስም እነዚህን የአቴና ገፀ በረከቶች እየዘረዘረ ገልጧል፡፡ አቴና በስፓርታ በተወረረችበት ወቅት የሶቅራጠስ ልጅ በቲያትሩ ላይ ያሳየው ቁጭት፣ አቴናውያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር በደንብ የተገለፀበት ነው፡፡ ይህ ቲያትር ሀገር በሁሉም ዜጎቿ የምትወደደውና የተቆርቋሪነት ስሜትንም የምታገኘው ሀገሪቱ በምታሰፍነው ነፃነት፣ እኩልነት፣ ፍትሐዊነትና ዲሞክራሲ መሆኑን በቅጡ  አሳይቷል፡፡
ሌላው፣ የአቴና የወቅቱ ገዥዎች ሶቅራጠስን ጠልፎ ለመጣል የተጠቀሙበት ክስ፣ ከእውነትና ከሀገር የትኛውን እንደሚያስበልጥ ያቀረቡለት የተንኮል ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ወጥመድ የአይሁድ ካህናት እየሱስን ‹‹ለቄሳር መገበር ይገባል ወይስ አይገባም›› በማለት ካቀረቡለት ወጥመድ ጋር ይመሳሰላል፡፡
ከሳሾቹ ለሶቅራጠስ ያቀረቡለት ወጥመድ ‹‹ከሀገርህና ከእውነት ማንን ትወዳለህ?›› የሚል ነበር፡፡ የከሳሾቹ ሐሳብ ‹‹ሶቅራጠስ ‹‹እውነትን አስበልጣለሁ›› ካለ ከአቴናውያን ጋር ይጣላል፤ ይሄም እሱ ላይ ለመፍረድ ጥሩ አጋጣሚን ይፈጥራል›› የሚል ነው፡፡ ሶቅራጠስ ፈላስፋ ስለሆነ የግድ ለእውነትም መወገን አለበት፡፡ እናም ‹‹ከሀገርህና ከእውነት አንዱን ምረጥ›› ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ፣ ሁለቱም እርስ በርስ የሚጣረሱ ነገሮች ሳይሆኑ ተደጋጋፊ መሆናቸውን በማስረዳት ወጥመዳቸውን አከሸፈባቸው፡፡ ‹‹ነገር ግን፣ የግድ አንዱን መምረጥ አለብህ የምትሉኝ ከሆነ ከሀገሬ ይልቅ እውነትን አስበልጣለሁ፤ ምክንያቱም ሀገር የሚገነባውም ሆነ መልካም ዜጎችን መፍጠር የሚቻለው እውነት በመንገር ስለሆነ›› በማለት ለነሱ ማስፈራሪያ እንደማይንበረከክ ዕቅጩን ነግሯቸዋል። በዚህ ወቅት ነበር ሶቅራጠስ ዳግም ወደ ከሳሾች ወጥመድ ውስጥ ሰተት ብሎ የገባላቸው፡፡ ይህ ክፍል በሶቅራጠስ ታሪክ ውስጥ በጣም ወሳኝ እንደመሆኑ በቲያትሩ ውስጥ ሳይዘነጋ መካተቱ በጥንካሬነት የሚታይ ነው፡፡
በሶቅራጠስ አስተሳሰብ በኩል የመጡ የግሪክ ፈላስፎች ከሚገለፁባቸው ባህርያት አንዱ ለእውነት ያላቸው ጥብቅና ነው፡፡ በቲያትሩ ላይ፤ ሶቅራጠስ ለእውነት ያለው ፍቅር ከሀገርና ከሚስቱ ፍቅር እንደሚበልጥ በግልፅ ተናግሯል፡፡ የሶቅራጠስ ተማሪ የሆነው ፕሌቶ ደግሞ እውነትን ከመለኮታዊ ባህሪዎች አንዱ ያደርገዋል፡፡ አርስቶትል መምህሩን (ፕሌቶን) ሲተች ያቀረበው መከራከሪያ፤ ‹‹ፕሌቶ የተወደደ ነው፤ እውነት ግን የበለጠ የተወደደች ናት›› የሚል ነበር፡፡
የእምነት ነገር
ሶቅራጠስ ለክስ ያበቃው ዋናው ነገር ‹‹ሃይማኖትም መፈተሽ አለበት›› ማለቱ ነው፡፡ ሶቅራጠስ ‹‹ያልተፈተሸ ህይወት ሊኖሩት አይገባም›› በሚለው የህይወት መመሪያው በመሄድ፣ እምነትን በወጣቶቹ ፊት አንደኛው የውይይት ርዕሰ ጉዳይ አድርጎ አቀረበው። እምነት በብዙ ማህበረሰቦች ውስጥ አይነኬ ነው፡፡ የሶቅራጠስ ዋና ከሳሽ ሜሊቶስ የተናገረውም ‹‹መነካት የሌለበትን እምነታችንን ነክተኻል›› በማለት ነው፡፡ በዚህ ክስ ላይ ሶቅራጠስ ለሜሊቶስ የመለሰለት መልስ ‹‹እኔ አማልክቱን በድፍረት እጠይቃለሁ፤ እናንተ ግን በዘልማድ ታመልካላችሁ፡፡ እምነት መፈተሽ የለበትም የምትሉት ለአንባገነንነታችሁ እንዲመቻችሁ ነው፤›› የሚል ነበር፡፡ እምነትን የተመለከተው እሰጣ ገባ ዋነኛው የሶቅራጠስ ክስ ማጠንጠኛ ስለሆነ በቲያትሩ ላይ በደንብ ትኩረት ተሰጥቶ መተወኑ ተገቢ ነው፡፡
እንግዲህ እምነትን የመፈተሽ ነገር አልፎ አልፎም ቢሆን ከሶቅራጠስ በፊት በነበሩ እንደነ ዜኖፌነስ ባሉ ፈላስፎችም ተሞክሯል፡፡ ይሄ ነገር ከሶቅራጠስም በኋላ በመጡ የግሪክ ፈላስፎች ተጠናክሮ ቀጥሏል። ምናልባት ግን እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ “ከሌሎች ማህበረሰቦች በተለየ እንዴት ግሪካውያን የእምነትን ነገር ለመፈተሽ ተዳፈሩ?” የሚለው ነው፡፡
ለዚህ ጥያቄ መልሱ - ግሪካውያን ‹‹አንድ የተገለጠ መለኮታዊ ኃይል ስላልነበራቸው ነው፤›› የሚል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ ግሪኮች የባህር ንግድ መተላለፊያ ኮሪደር ላይ ስለነበሩ ለተለያዩ አስተሳሰቦች የተጋለጡ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ አይሁዳውያን ‹‹አንድ የተገለጠ መለኮታዊ ኃይል›› ስላላቸው፣ ይሄንን መገለጥ በአንድ መፅሐፍ ላይ አስፍረው መተዳደሪያ ህግ አድርገውታል። ግሪኮቹ ግን እንደዚህ ዓይነት የተገለጠ አንድ እውነት ስላልነበራቸው ያንን መለኮታዊ ኃይል ፍለጋ ላይ ነበሩ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለስብከት ወደ አቴንስ ሲሄድ የአቴናውያን የአማልክት መሰዊያ ላይ ‹‹ለማይታወቀው አምላክ›› የሚል ፅሁፍ ያገኘው ለዚህ ነው፡፡ የሐዋ 17፡ 22፡፡ አቴናውያን የዚህ ‹‹የአንድ የተገለጠ እውነት›› ባለቤት አለመሆናቸው ግን እነሱን ብቻ ሳይሆን መላውን አውሮፓ ጠቅሞታል፡፡ እንዴት? አቴናውያን ‹‹አንድ የተገለጠ እውነት›› ስለሌላቸው ሁልጊዜ ያንን አንድ እውነት እንዲፈልጉና እንዲመራመሩ አድርጓቸዋል፡፡ ይሄም ሁሉም በየአቅጣጫው እንደፈለገ እንዲያስብ ነፃነትን አጎናፅፏቸዋል፡፡ እንግዲህ በዚህ ሂደት ነበር እጅግ አስደናቂ የሆኑትን ነገሮች በፍልስፍና፣ በስነ መንግስት፣ በሳይንስ፣ በአርት፣ በኪነ ህንፃ፣ በአስትሮኖሚ፣ በሒሳብ …ማፍለቅ የቻሉት። ሮማውያን እነዚህን የህሊና ትሩፋቶች ከግሪካውያን ወርሰው ይበልጥ አስፋፍተውታል፡፡ ሆኖም ግን ከ5ኛው ክ/ዘ (ድህረ ልደት) በኋላ ግሪካውያንና ሮማውያን የአይሁዳውያንን የ‹‹አንድ የተገለጠ እውነት›› አስተምህሮ መከተል ሲጀምሩ የህሊና ትሩፋቶቻቸውም መደብዘዝ ጀመሩ፡፡
እምነትን በተመለከተ ሶቅራጠስ ከከሳሹ ከሜሊቶስ ጋር ያደረገው ሙግት ግን ከተራ ክርክርነት አልፎ የምሁራንና የመንግስት ሚና ምን መሆን እንዳለበት አንድ መልዕክት አስተላልፏል፡፡ ይሄውም፣ የምሁራን ሚና ሐሳቦችና እሴቶች ላይ መመራመር፣ መፈተሽና ጉድፋቸውን ማጥራት ሲሆን  የመንግስት ሚና ደግሞ በምሁራን ተፈትሸው የቀረቡትን ሐሳቦች ማስፈፀም ነው፡፡ ሶቅራጠስ ይሄንን የምሁራንን ሚና ሲገልፅ እንዲህ ይላል፤ ‹‹እኔ ለአቴናውያን ከአማልክቱ የተላኩ ተናዳፊ ዝንብ (Gadfly) ነኝ፤ መንግስት ከስልጣኑ ብዛት የተነሳ ኃላፊነቱን ዘንግቶ እንደሚሰባ በሬ እየወፈረ እንዳይተኛ እኔ እየነደፍኩ አነቃዋለሁ፡፡ እኔን ከገደላችሁኝ ግን መንግስትን የሚያነቃና የሚቆነጥጥ ሌላ ሰው አታገኙም፡፡ ያን ጊዜ መንግስት በእናንተ ላይ አንባገነን ይሆናል፡፡›› እንግዲህ በ18ኛው ክ/ዘ ላይ ጆን ሎክና ሞንቴስኩ የተባሉ ፈላስፎች ‹‹መንግስት ተቆጣጣሪ አጥቶ እንዳይነቅዝና አንባገነን እንዳይሆን ስልጣኑ በ3 መከፈል አለበት - ህግ አውጭ፣ ህግ አስፈፃሚና ህግ ተርጓሚ (ፍ/ቤት) - በማለት ያቀረቡት ሐሳብ ስረ መሰረቱ ሶቅራጠስ ነው፡፡
የሶቅራጠስ ክስና የፍርድ ሂደት
በ‹‹ባዶ እግር›› ቲያትር ላይ፣ ወሳኝ የሆነው የሶቅራጠስ ክስና የፍርድ ሂደት በደንብ ተተውኗል፡፡ ሶቅራጠስ በ3 ነገሮች ነበር የተከሰሰው፡፡ 1) የአቴናውያንን አማልክት አያመልክም፣ 2)አዲስ ሃይማኖት አምጥቷል፣ እና 3)ወጣቶች ለአማልክቱ እንዳይታዘዙ በማድረግ ስነ ምግባራቸውን አበላሽቷል የሚል ነው፡፡ ሶቅራጠስ በትምህርቱ ብዙ ወጣት ተከታዮችን እያገኘ ስለነበር ከሳሾቹን ይበልጥ ያሳሰባቸው ሦስተኛው ክስ ነበር፤ ምክንያቱም ሶቅራጠስ ለ20 ዓመታት በቆየው ትምህርቱ ጠያቂ ትውልድ ፈጥሯል፡፡
አቴናውያን በዲሞክራሲያዊ እሴት ላይ የቆሙ ህዝቦች ስለነበሩ፣ የፍርድ ሂደታቸው የህግ የበላይነትና ግልፅነት የሰፈነበት ነው፡፡ የፍርድ ሂደታቸው ልክ እንደ ዘመኑ ችሎት በዳኞችና በህዝቡ ፊት፣ በአቃቤ ህግና በተከሳሽ መካከል ከሚደረጉ ክርክሮች በኋላ ነበር ብይን የሚሰጠው፡፡ ሆኖም ግን፣ በአሁኑ ዘመን ካለው የፍርድ ሂደት በተቃራኒ፣ የመጨረሻውን ብያኔ የሚሰጡት ዳኞች ሳይሆኑ በፍ/ቤት ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉ ስልጣን የተሰጣቸው ቁጥራቸው 500 የሆኑ ‹‹ነፃ ዜጎች›› ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት የሶቅራጠስ የሞት ፍርድ 279 በ221 የድምፅ ብልጫ ፀድቋል። ትያትሩ ይሄንን የግሪካውያኑን የፍትህ ስነስርዓት በመድረክ ዝግጅት፣ በአልባሳትና መንፈሱን በማምጣት በደንብ አሳይቷል፡፡
ከዚሁ ጋር አያይዤ ሌላም ነገር ልበል፡፡ የአቴና ምሁራን በግሪክ ዲሞክራሲ ተስፋ መቁረጥ የጀመሩትና ራሱ ዲሞክራሲ የሚባለው ፅንሰ ሐሳብ ላይ ጥያቄ ማንሳት የጀመሩት ሶቅራጠስ በድምፅ ብልጫ ከተገደለ በኋላ ነው፡፡ ፕሌቶም ሆነ አርስቶትል ዲሞክራሲን የነቀዘ መንግስታዊ ሥርዓት አድርገው የፃፉት በዚህ የተነሳ ነው፡፡
ደካማ ጎኖች
የሶቅራጠስ ታሪክ ለተውኔት እንዲበቃ ገፊ ኃይሉን የሚያገኘው ከሶቅራጠስ ፍፃሜ ነው - መርዝ ጠጥቶ እንዲሞት መደረጉ፡፡ ይህ ክፍል በሶቅራጠስ፣ በቤተሰቡና በጓደኞቹ ዘንድ ከፍተኛ ጭንቀትና የመንፈስ መረበሽ የሚታይበት የመጨረሻው አሳዛኝ (ትራጄዲ) ክፍል ቢሆንም፣ በቲያትሩ ላይ ግን ተቆርጦ ወጥቷል፡፡ ምናልባት ይህ ትራጄዲ የእንግሊዘኛው ድርሰት ላይ ባይኖር እንኳ፣ የአማርኛው ተርጓሚ ሊያካትተው ይገባ ነበር፡፡ ይህ ክፍል በተመልካቹ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የስሜት ጡዘት ሊያመጣ የሚችል ነበር። የዚህን ክፍል ዋጋ በንፅፅር መለካት ካለብን ከአፄ ቴዎድሮስ ፍፃሜ ጋር ነው፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ ተውኔት ላይ ንጉሱ ሽጉጥ የሚጠጡባት ክፍል ተቆርጣ ብትወጣ ተውኔቱ የሚያጣውን ሞገስ አስቡት፤ የሶቅራጠስም እንደዚህ ነው የሆነው፡፡ ሌላው፣ ቲያትሩ ፍልስፍናዊ ስለሆነ ተራው ተመልካች የማይረዳቸው በርካታ ነገሮች ይኖራሉ። ይሄም በተመልካቹ ዘንድ መሰላቸትን ሊያመጣ ይችላል፡፡ በመሆኑም፣ ይሄንን መሰላቸት ለመቀነስ ከአዘጋጁ ከፍተኛ ጥረትና ፈጠራ ይጠበቃል፡፡ ‹‹ባዶ እግር›› ቲያትር በአመዛኙ ሐሳብ ላይ ያተኮረ በመሆኑ፣ ተመልካቹ ያለምንም የስሜት መውጣትና መውረድ የሚመለከትበት ጊዜ ሰፊ ነው፡፡ በርግጥ ፌዶንና ክሪቶን ወክለው የተጫወቱት ተዋንያን፣ ይሄንን መሰላቸት በመጠኑ ሲቀንሱት ተስተውለዋል፡፡
በሦስተኛነት፣ ሶቅራጠስ በፍልስፍናው ዓለም ይበልጥ የሚታወቀው በክርክር የማስተማሪያ ዘዴው ነው፡፡ ምዕራባውያንም ይሄንን የሶቅራጠስ ውለታ ለመዘከር የማስተማሪያውን ዘዴ ‹‹ሶቅራጠሳዊ ስልት/Socratic Method›› በማለት በስሙ ሰይመውለታል። ሶቅራጠስ በዚህ የጥያቄና መልስ ዘዴ በመጠቀም ከወጣቶች ጋር በፍትህ፣ በፍቅር፣ በእውነትና በመልካምነት እሴቶች ዙሪያ ከሚያደርጋቸው ክርክሮች መካከል አንዱ ተቀንጭቦ በትያትሩ ላይ ቢቀርብ ጥሩ ነበር፡፡
ከአዘጋጁ፡- (ጸሃፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህርና ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› መፅሐፍ ደራሲ ናቸው)

Read 2143 times