Monday, 07 May 2018 09:13

“ዶክተር” ይመሬ ለምን ፈዘዘ? - (ምናባዊ ወግ)

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

 “-ለነገሩ መጫኛ ማቆም ምን ይሰራል?›› ብሎ ራሱን ጠየቀ፡፡ ‹‹ዝናብ ማዝነብም ጊዜ አልፎበታል፤ ጀርመኖቹ
በቴክኖሊጂ ደመና መፍጠር ችለዋል … የቆዳ በሽታም የተሻለ የሚያክሙ ሀኪሞች አሉ፡፡ ቴክኖሎጂ አዋቂ ላይ የመጣች የፈረንጅ ሰላቢ ናት.. እኔ የሚያዋጣኝ መስተፋቅር መስራቱ ነው፡፡-”
     
    የሲሲፈስ ድንጋይ ክብደቱ እያነሰ፣ ቅርፅ እየቀየረ … እየሟሟ እንደመጣ ሁሉ የጋሽ ይመሬ አስማትም ከጊዜ ወደ ጊዜ ኃይሉ እየደከመ መምጣቱን ልብ ብለዋል፡፡ ሀሳብ ገብቷቸዋል፡፡ ድሮ መጫኛ ገና  የበሬው ገላ ላይ እያለ ራሱ ማቆም ይችሉ ነበር፡፡
ጥንት የሚቀምሙት መድሀኒት የማያዳግም ነበር፡፡ መግደል የፈለጉትን ሰው በትንሽ ዶዝ ድብን ያደርጉታል፡፡ ወደሳቸው የሚመጡ ደንበኞቻቸው የሚከፍሉት ብር እየጨመረ፣ የሚያገኙት መፍትሄ ግን እየቀነሰ ስለመጣ ወሬ ያስወሩባቸው ጀምረዋል፡፡
ባለፈው አንዱ የሥራ ባልደረባውን ለማሳበድ መድሃኒት እንዲያዘጋጅለት ከመሀል ሀገር እሳቸው ያሉበት ገጠር ድረስ ተጉዞ የማያዳግም መፍትሄ ለባላንጣው ይዞ መመለሱን እርግጠኛ ሆኖ ነበር። ከሁለት ወር በኋላ እየተካለበ  ተመልሶ መጥቶ፣ እንዲያብድ የተፈለገው ሰው ጭራሽ አእምሮው እየተባ፣ በሥራው ላይም ብልጫ እያሳየ ማስቸገሩን ነገራቸው፡፡ … በድጋሚ አስከፈሉት፤ ጋሽ ይመሬ፡፡
‹‹የተከፈለበት መድሃኒት አይመለስም›› የሚል ማስጠንቀቂያ ከምድጃው በላይ ሰቅለዋል፡፡ ምድጃው ለሰውየው እንደ ላቦራቶሪያቸው ነው፡፡ ግድግዳው ላይ በብጫቂ ፌስታል የተቋጠሩ ብዙ ዱቄት መሰል ንጥረ ነገሮች ተሰካክተዋል፡፡ ከእያንዳንዱ ቋጠሮ አጠገብ በሚያስፈራ ቀይ እስኪሪብቶ የሰፈረ ፅሁፍ አለ፡፡ መሰረተ ትምህርትን በሽፍትነት የተወጣ የፅሁፍ አጣጣል ነው፡፡
ጋሽ ይመሬ በጭቃ ከፍ ብሎ የተሰራው መደባቸው ላይ እግራቸውን አጣምረው ሰፍረዋል፡፡ መደቡ ላይ 3 ኤፍ ፍራሽ ተደርቦበታል፡፡ ሰው እያናገሩ የሞባይል ስልካቸው ሲጠራ፣ እያነሱ ዝም ያሰኙታል፡፡
‹‹መድሀኒቱን እኔ እንደነገርኩህ ነው የተጠቀምከው?››
‹‹አዎ››
‹‹በምን ውስጥ ጨምረህ ሰጠኸው?››
‹‹በሚሪንዳ››
‹‹በጉሽ ጠላ ቢሆን ጥሩ ነበር››
“አዲስ አበባ ጠላ ጠፍቷል እኮ፤ ልጁ ደግሞ መጠጥ አይቀምስም››
‹‹ጫትስ ይቅማል?››
‹‹ይመስለኛል … ግን እርግጠኛ አይደለሁም … አብዝቶ ስለሚያነብ መቃሙ አይቀርም፡፡››
‹‹እንግዲያውስ ወደ ቤትህ ጋብዘውና ጫት እየበላችሁ እቺን ቀንበጥ ግንባርህ ላይ ለጥፋት፤ ይሄንን ወረቀት ላይ የፃፍኩልህን ቃል ሶስት ጊዜ ጮክ ብለህ ድገምበት››
የሰጡትን ወረቀት እና ቅጠሏን በጥንቃቄ ቋጥሮ ሊወጣ ሲል ብር እንዲከፍል ነገሩት፡፡ የሰውየው ሚስት ደረሰኝ ሳትሰጠው ብሩን ተቀብላ ጉያዋ ከተተችው። እሱ መውጣቱን ካረጋገጠች በኋላ ወደ ጉያዋ የከተተችውን ብር አውጥታ በጥሩ እጅ ቦርሳ ውስጥ አደረገችው፡፡
በወጣው ሰው ፋንታ ሌላ ደንበኛ ባሏ ወዳለበት ክፍል ላከች፤ “አብዛኞቹ ደንበኞች የተሰጣቸው ምክር ወይንም መድኃኒት አልሰራልንም” የሚሉ መሆናቸውን… ከጊዜ ወደ ጊዜ የጋሽ ይመሬ ሚስት ልብ እያለች መጥታለች፡፡ ወደፊት ደንበኞች ከእነ አካቴው እንዳይጠፉ በመስጋት ከባሏ ጋር ማታ ሲተኙ … የጨዋታ ዳር ዳርታ እየጀመረች፣ ደፍራ የመናገር አቅም ግን አነሳት፡፡
የድሮው ይመሬ ከጊዜ በኋላ መለወጡ ይሰማታል። ምናልባት ዘመኑ በመለወጡ የአዋቂዎች መድሀኒት ለዘመናዊው ሰው አልሰማም ብሎ ይሆናል ብላ ታስባለች፡፡
ጋሽ ይመሬ ሚስቱ የምታስበው ይገባዋል፡፡ ይሰማዋል፡፡ ግን የራሱ ጭንቀት በልጦበታል፡፡… ተራ የቆዳ ደዌ ይዘው የመጡ ደንበኞች እንኳን አምስት ወይ ስድስቴ ተመላልሰው ነው መፍትሄ የሚያገኙት። መፍትሄ ማግኘታቸውንም እርግጠኛ አይደለም። መመላለሱ ሰልችቷቸው በዛው እየቀሩም ሊሆን ይችላል፡፡
በዛ ላይ ሰውም ወደ ህክምናው ነው ትኩረቱ፡፡ የድሮው ሰው ጠንካራ ነበር፡፡ ብዙ ህክምና አይሻም። ጠላቱን ማጥቂያ ሁነኛ ቅጠል እንዲበጥስላቸው ነው ወደ እሱ ዘንድ ይመጡ የነበሩት፡፡ የድሮው ዘመን የኮሌጅ ተማሪ በመልካም ውጤት ለመመረቁ የይመሬ አስተዋፅኦ ምን ያህል እንደሆነ የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ ጎበዞቹን ተማሪዎች በማደደቡም ረገድ ይሁን ደደቦቹን በማጎበዝ የዘመኑ ተማሪዎች የደረሱበት ደረጃ ላይ የደረሱት በእሱ እርዳታ መሆኑን ሲያስብ ልቡ በኩራት ያብጣል፡፡ ቡና እየጠጣ ስልኩን ይጎረጉራል፡፡
‹‹ለነገሩ መጫኛ ማቆም ምን ይሰራል?›› ብሎ ራሱን ጠየቀ፡፡ ‹‹ዝናብ ማዝነብም ጊዜ አልፎበታል ፤ጀርመኖቹ በቴክኖሊጂ ደመና መፍጠር ችለዋል … የቆዳ በሽታም የተሻለ የሚያክሙ ሀኪሞች አሉ፡፡ ቴክኖሎጂ አዋቂ ላይ የመጣች የፈረንጅ ሰላቢ ናት.. እኔ የሚያዋጣኝ መስተፋቅር መስራቱ ነው፡፡ ግን እኔ በመፋቂያ ላይ የሚሰራውን መስተፋቅር ነው የማውቀው፡፡ ዘመናዊ ሰው በጥርስ ሳሙና ነው የሚፍቀው .. በመፋቂያ ላይ የምሰራውን ከጥርስ ሳሙና ጋር ሳቀላቅለው … ለምን እምቢ አለ? … ትንሽ ትምህርት ብጨምርበት ኖሮ ይሄኔ! ….›› ብሎ ጥርሱን ነከሰ፡፡
በመፋቂያ ላይ የሚሰራውን መስተፋቅር፣ በጥርስ ሳሙና ለምትጠቀም ዘመናዊ ወጣት ለመስጠት የሞከረ የይመሬ ደንበኛ፣ ልጅቱ “Capital P” ብላ ሰድባው፣ የስነ ልቦና ቀውስ ውስጥ ስለወደቀ ለራሱ ሌላ መድሃኒት አስፈለገው፡፡ … የስነልቦና በሽታ ጋሽ ይመሬ እውቀታቸውን ባደረጁበት ዘመናት እንግዳ ነበር፡፡ ሰው በአጠቃላይ ጠንካራ ነበር፡፡ በሽመል ሲደባደብ ውሎ ቤቱ የሚገባ እንጂ ስነልቦና የነበረው አይደለም፡፡
በክንድ ላይ የሚቀበር መድሃኒት በጋሽ ይመሬ ሰርጀሪ የተደረገላቸውም ገላቸው ከመድሀኒቱ ጋር እየተጣላ ስለተቸገሩ ሆስፒታል ሄደው እየተሸማቀቁ አስወጥተውታል፡፡ እንደዚሁ ባለፈው ንግዱ ስኬታማ እንዲሆን የሚቀባ ነገር የሰጡት ወጣት ነጋዴ፤ “በጠረኔ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም ገበያ ራቀኝ” ብሎ እዬዬ አለባቸው፡፡ በጣም ደካማ ትውልድ ነው፣ እሳቸው እጅ ላይ መጥቶ የደከመባቸው፡፡ ደካማ ሆኖ እሳቸውንም አደከማቸው፡፡ ደካማ ትውልድ ሰባኪ ነው እንጂ የሚፈልገው፣ መድሀኒት አዋቂ አይደለም፡፡
በጣም ተግተው ሲያስቡበት ከረሙ፡፡ ውሎ ሲያድር ነገሩ ተገለፀላቸው፡፡ … አስማት ወይንም ተአምር በየእለቱ በቴክኖሎጂ እየተወረሰ መጥቷል። ሀኪም ቤት የባህላዊ መድሀኒትን ምስጋና ሙሉ በሙሉ ተረክቧል፡፡ የቅኔው ትምህርት ቤት በአስኳላ ተማሪ ቤት ተወርሷል፡፡ ተአምር እለት በእለት እያየ ያደገ ትውልድ፤ከእሳቸው የሚፈልገው የለም፡፡ መጫኛ ሲቆም ቢያይ አይገርመውም፡፡ መጫኛ ምን እንደሆነ ጨርሶ ሲያውቅ አይደል፣ ቢቆም ይገርመው የነበረው?
በዛ ላይ ድሮ ሰው እሳቸው በተቀመመ መድሃኒት ሲያብድ እንኳን ጨርቁን ጥሎ ነበር የሚሄደው። አሁን የመጣው ዘመናዊ እብድ ልብሱን እንደለበሰ … ቤተሰቡን ሳይበትን… ስራ እየተመላለሰ ነው የሚያብደው፡፡ ማበድ እና አለማበዱ ፈፅሞ ሊለይ አይችልም፡፡ “ሴቶቹም ተለውጠዋል … ሲያፈቅሩ እና በፍቅር ሲከንፉ በዘመናዊ መንገድ ነው፡፡ የስነልቦና ባለሙያ ካልሆነ … የእኔ አይነቱ መድሀኒት አዋቂ፤ ፍቅር የሚያስይዝ እፅ ሊቀምምላቸው አይችልም ”… ብሎ ተከዘ፡፡
“ድሮ የወር ቀጠሮ ተሰጥቷቸው እኔው ጓሮ የሚከርሙ በሽተኞች አሁን የት ጠፉ? … በመሰረቱ እኔ ለራሴ ህመም እንኳን የቀበርኳቸው መድሀኒቶች፣ ክብደቴን ጨመሩት እንጂ መች መፍትሄ ሰጡኝ” … ይሄንን እያሰበ ጋሽ ይመሬ ስልኩን መጎርጎር ጀመረ፡፡ … በተከታታይ ለብዙ ቀናት ከጥቂት የመንደር አሮጊቶች በስተቀር ወደሱ ዘንድ አንድም ደንበኛ ዝር ሳይል ቀረ። አሮጊቶቹም የሚመጡት ለዘመናት ያስለመዳቸውን ምርቃት ለመቀበል ነበር፡፡ ግን ሲመርቃቸው በሙሉ መንፈስ አልነበረም ‹‹አሜን›› የሚሉት፡፡ መርቆ ምራቁን ሲተፋባቸው ሲጸየፉና በነጠላቸው ቀስ አድርገው ሲጠርጉ አይቶ ጋሽ ይመሬ ተሸማቀቀ፡፡
በተከታታይ ወራት ሰው ከነአካቴው ጠፋ። ይመሬም ስልኩን መጎርጎር መዝናኛው ሳይሆን መሸሸጊያው መሆኑን ሚስቱም ነቃችበት፡፡ ቀስ በቀስ ንቀት ሰተት ብላ ቤቱ ገባች። አንድ ማታ የጋሽ ይመሬ ሚሽት፤ በረባ ባልረባ ስትነጫነጭ ቆይታ … ድንገት ‹‹ሰውዬ እዚህ እንደ በሽተኛ መዘፍዘፍህን ትተህ ወጥተህ ስራ ፈልግ … ወይ ወደ ከተማ ገብተህ የባጃጅ ሹፌር ሁን… እዚህ ቤቱን በምራቅ ቱፍታ ስትሞላ አትዋል ..›› አለችው፡፡  
በእርግማን በቆመችበት ወደ ሀውልት ሊቀይራት ይችል ነበር፡፡ መቀየርም ፈልጓል፡፡ ድሮ ቢሆን፤ ሰውን ወደ ጨው ሀውልት ቀይሮ … ከሀውልቱ ላይ ዘግኖ ለቤት የጨው አስቤዛ የሚያስፈልገውን ያህል ከቀነሰለት በኋላ ወደ ጨው የለወጠውን ሀውልት መልሶ ሰው ያደርገው ነበር፡፡
ዛሬ ግን ራሱን ተጠራጠረ … አቀርቅሮ ቀረ። ተመልሶ እንደ ድሮው ገበሬ መሆን የማይታሰብ ነው። ራሱን ድንገት ለማጥፋት አሰበ፡፡ ከዚህ ቀደም እንደዚህ አይነት ሀሳብ ፈፅሞ በእሱ ውስጥ ተመላልሶ አያውቅም። ድንገት እየደከመ መሆኑ ገባው፡፡ እንደ ዘመናዊው ትውልድ ተዳክሞ፣ ስነልቦና አብቅሏል። በሽታውን ግድግዳ ላይ በተሰቀሉት መድሀኒቶች ሊፈውሰው አይችልም፡፡ … በሌላ መንፈስ ያነበው የነበረውን መጽሐፍ ቅዱስ፤ እንደ አዲስ ማንበብ ጀመረ። ትንሽ ካነበበ በኋላ ከዚህ ቀደም የሚያውቀው ሳግ በጉሮሮው መጥቶ ግጥም አለ፡፡ እየተንሰቀሰቀ ሲያለቅስ ዋለ፡፡ ሚስቱ እንዳትሰማው ድምፁን ለመቀነስ ምንም አይነት ጥረት አላደረገም፡፡

Read 1896 times