Monday, 07 May 2018 09:12

ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር

Written by  ባህሩ ሰጠኝ
Rate this item
(6 votes)

  “-አጼ ኃይለስላሴም አጼ ሚኒልክ የእርሻና የመስሪያ ቤት ሚኒስቴር ብለው ከሰየሙት ስያሜ ላይ ‘መስሪያ ቤት’ የሚለውን ሀረግ ቆርጠው ጣሉና በ1923 ዓ.ም “የእርሻ ሚኒስቴር” ብለው ሰየሙት፡፡ አጼ ኃይለስላሴ አገር አማን ብለው በተቀመጡበት ስልጣናቸውን በጉልበት የተረከበው ደርግ፣ በ1966 ዓ.ም ወታደራዊ የመንግስት ስርዓቱን ሲመሰርት ቀደም ሲል የእርሻና ደን ሚኒስቴር እና የመሬትና የህዝብ ማስፈር ሚኒስቴርን በአንድ ይዋሀዱ ዘንድ ሀሳብ አቀረበ፡፡--”
        
    እንዴት ሰነበቱ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ክፉ አይንካዎት፤መልካም አይለፍዎት፡፡ እንኳን ለአርበኞች ቀን አደረስዎት፡፡ እንዴት ነዎት፤ ቤተ መንግስቱ ሞቀዎት? ለነገሩ የጦፈ ጉብኝት ላይ ስለሆኑ ብዙም የተቀመጡበት አልመሰለኝም፡፡ የጉብኝትዎ ራዳር እጅግ ሰፊ ነው፤ ሁሉንም አቅጣጫዎች ያማከለ። ከአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ጀምሮ ከጂጂጋ እስከ አምቦ፣ ከጎንደር እስከ መቀሌ፣ ከባህር ዳር እስከ አዋሳ፣ ከአባይ ግድብ እስከ አሶሳ፣ ከውጭም ጂቡቲንና ሱዳንን አዳርሰዋል፡፡ የእርስዎ የድል ችቦ ዳር እስከ ዳር ተቀጣጠለ እኮ፤ በየሄዱበት ህዝቡ በድምቀት ተቀበለዎት እኮ፤ ኩራት ሊሰማዎት ይገባል፡፡ ነዋሪው በነቂስ ወጥቶ የሞቀ አቀባበል የሚያደርግልዎት ለምን ይመስልዎታል? ስለ አንድነት የሚዘምር መሪ ብርቅና ድንቅ ሆኖበት፤ አንድነታችን ናፍቆት እኮ ነው፡፡
በእርግጥ አንዳንድ ሰዎች ጠ/ሚኒስትሩ ጉብኝት አበዙ ብለው ሲያወሩ ሰምቻለሁ፡፡ በአዋሳው ንግግርዎ ምን ነበር ያሉት?! “ሁሉም ፈራጅ ሆኗል!” እውነት ብለዋል፡፡ ከባለሃብቶች ጋር በሸራተን አዲስ ሲወያዩ፤ “እኔ 7 days a week እሰራለሁ፤ እናንተም--” ብለው ነበር፡፡ የእርስዎን በአደባባይ እያየነው ነው፡፡ የባለሃብቶቻችንን ግን እንጃ!  
ሰሞኑን ሰዉ ስለርስዎ ምን እንዳለ የምሰማውን ሁሉ በትኩስ በትኩሱ አደርስዎታለሁ፡፡ ከጸሀይ በታች ለርስዎ የምደብቅዎት ምንም ሚስጥር እንደሌለ ላረጋግጥልዎት እወዳለሁ፤ የእኔ የ5 ዓመት ዋና ግቤ፤ በኔና በርስዎ መካከል ያለውን ሚስጥር ዜሮ ማድረግ ነው፤ እርስዎም ድህነትን ዜሮ ለማድረግ ያላሳለሰ ጥረት ያድርጉልን፡፡
ብዙ ሰዎች በብዙ ነገርዎ ይቀኑብዎታል፤ እኔ በበኩሌ ከሁሉ የቀናሁብዎት ብዙ ቋንቋ ተናጋሪ (multi lingual) በመሆንዎ ነው፡፡ የቋንቋ ብዝሀነት (diversity of language) ይሏል ይሄ ነው፡፡ ከአማርኛ እስከ ትግርኛ፣ ከኦሮምኛ እስከ ሶማልኛ (የሁሉንም ብሔረሰቦች በሚያስብል ሁኔታ) ምን የማይችሉት ቋንቋ አለ፤ በውነት መታደል ነው፡፡ ሶማሊያ ላይ በሶማልኛ ንግግር አደረጉ ብለን ስንደመም፤ ትግራይ ዘልቀው በትግርኛ ሲደግሙት አጃኢብ ከማለት ውጭ ምን ይባላል፡፡ የክልሉ የስራ ቋንቋ አማርኛ መሆኑ እንጂ፤ ከደቡብ ህዝቦች ቋንቋዎችም ሳይችሉ አይቀሩም፤ ቢያንስ አራት ያህሉን በንግግርዎ መግቢያ ተጠቅመዋላ፡፡
ከእርስዎ አንደበት ከፈለቁ ተወዳጅ ንግግሮችዎ መካከል በተለይ ለወጣቱ የለገሱት ምክር ከማር ከወተት ይጣፍጣል፡፡ የወጣቶች የተሳትፎና የተጠቃሚነት ጉዳይ ከጸጥታና ደህንነት ስጋቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው መሆኑን በአንክሮ አስምረውበታል። ስራ አጥነት ወጣቶችን ለወንጀል፣ ለሱስ፣ እንዲሁም ለስደት እንደሚዳርግ ጠቅሰው፤ ይህን ሁኔታ ለመቀየር መንግስት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡ ጥሩ አስበዋል፤ ይህን ትኩስ ሃይል በወግ በወጉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ወጣቱ በስራ መጠመድ ነው ያለበት። ስለ ወጣትነት ዘመን እውቁ ግሪካዊ ዩሪፒደስን ጠቅሰው፤ ”ሀብታም ለመሆን ከሁሉም የተሻለው ጊዜ ወጣትነት ነው፤ ድሃ ለመሆንም ከሁሉም የተሻለው ጊዜ  ወጣትነት ነው” ብለውናል፤ ጣፋጭ ምክር ነው፡፡
ግጥማዊ ንግግርዎ ደግሞ አጥንት ሰርስሮ የሚገባ አንዳች ዜማ አለው፡፡ “--ወጣትነት የእሳት ዘመን ነው፤ ይህን እሳት ወንዝ ጥለፉበት፣ ብረት አቅልጡበት፣ተራራ ናዱበት፣ ፋብሪካ ገንቡበት፣ ድልድይ አንጹበት….” በማለት ወጣቶች ትኩስ ጉልበታችንን እንጠቀምበት ዘንድ መክረውናል፡፡ እኛ ወጣቶችም ሰሚ ጆሮ ያድለን።
የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ፤ እጃቸው ንጹህና ሌብነትን የሚጠየፉ መሆናቸውን በአንደበትዎት መስክረው፣ ኒሻን ሸልመው፣ በክብር መሸኘትዎት ግሩም ነው፤ ይገባቸዋል፡፡ ስንቶቹ ጡረታ ወጥተው እንኳ ስልጣን የሙጥኝ ብለው አቶ ኃይለማሪያም በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ማስታወስዎም ሸጋ ነው፡፡ ስለ ሥልጣን ያለን አመለካከት በአንዴም ባይሆንም ቀስ በቀስ ይለወጣል  ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ቢያንስ የዘላለም ርስት እንዳልሆነ ግን ማስታወስ ሳያስፈልግ አይቀርም። በሥልጣን ላይ ላሉትም ወደፊት ለሚወጡትም። ዋናው ግን እርስዎ  እንዳሉት፤ የሥልጣን ዘመንን በህገ መንግስት መገደብ ነው፡፡ ታዲያ በቶሎ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ወሬውን ከሰማን እኮ ብዙ ዓመት አለፈው፡፡ መገደቡ ያሳሳቸው ባለሥልጣናት ይኖሩ ይሆን እንዴ?  
ስለ ልማትና ዴሞክራሲ በውጭ የሚጮኹ ኢትዮጵያዊያን፣ በግልም ሆነ በቡድን ተደራጅተው ውጭ ሳይሆን ቢሯቸውን አዲስ አበባ  እንዲያደርጉ  ጥሪ ማቅረብዎት እጅግ አስመስግኖዎታል፡፡ እንዴት ደስ ይላል፤ እነ ታማኝ በየነ፣ እነ አበበ ገላው፣ እነ ጁሀር መሀመድ …..ይመጣሉዋ? እነ ኢሳት እንደ አሸባሪ ስለሚታዩ ህዝብ እንዳይሰማቸው ሆን ተብሎ “ጃም” ሲደረጉ ነበር አሉ፤ (አሉ ነው፡፡) እነ ቪኦኤና ዶቼቬሌም የአበዳሪ መንግስታት ጣቢያ በመሆናቸው እንጂ በመንግስታችን ዓይን ከኢሳት ተለይተው የሚታዩ አይመስለኝም፡፡ አሁንማ ተመስጌን ነው፡፡ ሃሳብ ለማንሸራሸር ባህር ማዶ መቀመጥ አያስፈልጋችሁም ተብሏል፡፡    
የውጭ ምንዛሪ ችግርን ገና በ20 ዓመታትም አንፈታውም ሲሏቸው ባለሀብቶች አጨብጭበዋል። የአየር ማረፊያ እንዲሰራላቸው ጠይቀው “የሚሰራ አይመስለኝም፤ አርባ ምንጭ ሂዳችሁ ተሳፈሩ” የሚል ምላሽ ሲሰጧቸው የወላይታ ሶዶዎችም አጨብጭበዋል፡፡ ለምን መሰልዎት@ የሚሆነውን ”ይሆናል”፣ የማይሆነውን “አይሆንም” ብለው “እቅጩን” ስለተናገሩ እኮ ነው፡፡ እውነትን ተናግሮ ከመሸበት ማደር ይሉዎታል ይኼ ነው፡፡ እስካሁን የነበረው የኢህአዴግ ተሞክሮ ግን ይኼ አይደለም፤ ሁሉን “እሽ” እንጂ “አይሆንም” አይልም፡፡ ይባስ ብሎ የመሰረት ድንጋይ ይጥልና ህዝቡን በተስፋ አንበሻብሾ፣ የውሃ ሽታ ሆኖ ይቀራል፡፡ በተለይ ደግሞ የምርጫ ሰሞን፡፡ ከዚያ ተጋላገልን ማለት ነው፡፡
በሕገ መንግስታችን  ላይ ለስልጣን ገደብና ወሰን ሊያበጁለት እንደሆነ ሰማን፤ በስልጣን ኮርቻ ተፈናጦ ለዘላለም መኖር ተረት ተረት ሊሆን ነዋ? ይቀጥሉበትማ፤ ሰው ከኖረ ከሚስቱ ይወልዳል አሉ። እኛም ለዚህ በቃን፤ ተመስገን ነው፡፡ ለአዲስ ተሷሚዎችዎና ለነባር ሚኒስትሮችዎ ሁለቱን ቀይ መስመሮች (ሙስናና አገልግሎት አሰጣጥ) አስምረውባቸዋል፤ ጎሽ ደግ አደረጉ፡፡ እውነት ነው፤ እነዚህ ሁለቱ ቀይ መስመሮች ከተስተካከሉ ሁሉም ነገር ይስተካከላል፡፡ የማንለወጥበት ምክንያት የለም። መሬት አለን፤ ጉልበት አለን፤ ውሃ አለን፤ እውቀት አለን፤ የጎደለን የለም፡፡ እኛ የሚያስፈልገን ትክክለኛ መሪ ብቻ ነው፡፡ እርስዎ በአንክሮ እንደተናገሩት፤ ህዝቡ ፍትሃዊ አገልግሎት እንጂ የተለየ ሰርቪስ ወይም ወርቅ እንዲነጠፍለት አልጠየቀም፡፡ በአንድ ጀምበር ለውጥ እንደማይመጣም ህዝቡ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡
ንግግርዎ እንደ ማር እንደ ወተት ከጣፈጣቸው አያሌ ሰዎች በተቃራኒ፣ እንደ ኮሶ የኮመጠጣቸውም አልጠፉም። ሁለት ወጣቶች የአስፓልቱን ጠርዝ ይዘው እየሄዱ የጦፈ ክርክር ውስጥ ገብተዋል፡፡ ክርክሩም እርስዎ መቀሌ ላይ  ባደረጉት ንግግር  ነው። “እንዴት ዲያስፖራዎች ናቸው እንጂ [የወልቃይት] ጥያቄ የመሰረተ ልማት ነው” ይላሉ አለች፤ ሴቷ በብስጭት፡፡ “ዶክተር አብይ፣ ውስጤ ናቸው እንዳላልኩላቸው፣ ዶክተር አብይ፣ ነብይ ናቸው እንዳላልኩላቸው፤ የሞቀውን ሞራላችንን እንዴት ቀዝቃዛ ውሃ ይቸልሱበታል፡፡ ስንት ደም የፈሰሰበት መሆኑን ዘነጉት እንዴ! ድሮም ኢህአዴግ --” አለች፡፡ ወንዱ ደግሞ “እንዲያው የአፍ ወለምታ ይሆናል እንጂ ዶክተር አብይ ይህን ምላሽ ይሰጣሉ ብዬ አላምንም” በማለት ለርስዎ ማስተባበያ ሰጣት። “የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም አሉ፤ ገና የፈሰሰው ደም ሳይደርቅ” አለች ሲቃዋ እየተናነቃት፡፡ እቅፍ አድርጎ አባበላት፣ለካ ባልና ሚስት ናቸው፡፡ ከዚያም “ይቅርታ ጠይቀዋል እኮ” አላት ባሏ፡፡ “ምን ብለው?” አለች ሚስትየዋ። “ካጠፋሁ ቆንጥጡኝ  የሚል መሪ እስካሁን አይተሻል? ዶ/ር አብይ ጎንደር ሄደው ለአባቶች ካጠፋሁ ቆንጥጡኝ” ብለው ቀረቡ እኮ፡፡ “እኔ አላምንም!” አለች በአግራሞት። “እውነቴን ነው ካላመንሽ ይህን አድምጭው” ብሎ የጆሮ ማዳመጫውን ጆሮዋ ላይ አደረገላትና ያሉትን ንግግር ሲያሰማት “ወንዳታ!” ብላ ጮኸች፡፡ የእርስዎ “ካጠፋሁ ቆንጥጡኝ” ማለት ቁጣዋን አብርዶላት “ለነገሩ እንጨት ሆኖ የማይጨስ፣ ሰው ሆኖ የማይሳሳት የለም፤ ስህተታቸውን ማመናቸው ትልቅ ሰው ናቸው፡፡  ስህተቱን የሚያምን መሪ ጠፍቶ እኮ ነው ሰላማችን ደፍርሶ የከረመው” አለች፡፡
በርስዎ ጉዳይ ስንቱ ተከራከረ መሰልዎት፤ ያውም በነጻነት፡፡ ትንሽ እንደሄድኩ ሌሎች ሦስት  ወጣቶች ደግሞ በካቢኔ ሹም ሽርዎት ላይ ሲከራከሩ ሰማሁ። ለእንትን ሚኒስቴር ጥሩ ሰው ሾመዋል፤ እዚህ ላይም ጥሩ ነው፤ እያሉ ሹም ሽርዎትን ይገመግማሉ። አንደኛው፤ “እኔን በጣም የገረመኝ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፤ የግብርና ሚኒስትር ተደርገው መሾማቸው ነው፤ እዚህ ላይ ዶክተር አብይ ተሳስተዋል” እያለ የጉንጩን ሳይጨርሰው፤ “ደግሞ ሽፈራው የቱ ናቸው?” አለ ሁለተኛው፡፡ ሶስተኛው ቀበል አደረገና፤ “ትምህርት ሚኒስቴር፣ የማትሪክ ፈተና የተሰረቀባቸው” ሲል፤ ሁለተኛው ካፉ ላይ ቀማና፤ “እሳቸውማ  ከትምህርት ሚኒስቴር ተነሱ እኮ” አለ፡፡ “ታዲያ ከ[ትምህርት ሚኒስቴር] የተነሳ እንዴት [ግብርና ሚኒስቴር] ይገባል?” መለሰ ሁለተኛው፡፡ “እሱማ የሁሉም ጥያቄ ነው፤ ለመሆኑ የትምህርት ዝግጅታቸው ምንድነው?” ጠየቀ ሶስተኛው፡፡
“አካውንቲንግ ነዋ” አለ አንደኛው፤ “ታዲያ [አካውንቲንግ] እና [ግብርና] ምን አገናኛቸው?” ሲል ጠየቀ፤ ሁለተኛው፡፡ ሶስተኛው ቀበል አደረገና፤ “በተቋማት አመራርም 2ኛ ድግሪ አላቸው” አለ፡፡ “ኧረ ዶክትር ምን ነካቸው! ባይሆን ግብርና (Agriculture) የተማረ አመራር አጡ እንዴ?” አለ፤ ሁለተኛው በአግራሞት አገጩን በመዳፉ ጨብጦ፡፡ “በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚደረግ ምደባ በእውቀት፣ በክህሎትና በችሎታ ትክክለኛውን ሰው በትክከለኛው ቦታ እንደሚመድቡ ትላንት ቃል ገብተው እንዴት ባንድ ጀምበር ያፈርሳሉ?” አለ ሶስተኛው እየተበሳጨ፡፡  አንደኛው ቀጠለና፤ “አዎ፤ ቅድሚያ የተሻለ አወቃቀር፣ የተሻለ አመራር፣ የተሻለ በጀት የሚመደብለት ግብርና መሆኑንም ተናግረው ነበር” አለ፡፡ ሁለተኛው እንዲህ አለ፤ “ሰው መክሯቸው ይሆናል እንጂ እሳቸው ያደርጉታል ብዬ አላስብም” በነገራችን ላይ ይሄን ጉዳይ ሚዲያዎችም  አራግበውታል፡፡  
በ2008 ግብርና ሚኒስቴር ለሁለት መከፈሉን አያቴ ነገሩኝ፡፡ ምንና ምን ተብሎ አልኳቸው፡፡ [የጾም ሚኒስቴርና የፍስክ ሚኒስቴር] ብለውኝ እርፍ፡፡ (የጾሙ “የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚ/ር” ሲሆን የፍስኩ ደግሞ “የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ሚ/ር” መሆኑን ሲነግሩኝ በሳቅ ወደቅኩ)፡፡ ለሁለት ዓመታት [ግብርና] የሚባል መስሪያ ቤት ከአገራችን አወቃቀር ከእነ አካቴው ጠፍቶ ነበር (ከ2008 ጀምሮ)፡፡ ለምን? ግብርና ሚኒስቴር “የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚ/ር” እና “የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ሚ/ር” ተብሎ ለሁለት ተሰነጠቀ፡፡ የተወሰኑ ክልሎችም ከላይ የወረደላቸውን ትዕዛዝ በመቀበል ለሁለት ሸነሸኑት፡፡ አንዳንዶቹ ስያሜው አልዋጥላቸው ብሎ፣ ነገ ዛሬ እያሉ ሲያደናቁሩ  [ግብርና ቢሮ]  ቆዩና፣ ይኸው ዛሬ ሁለቱ መስሪያ ቤቶች ሲዋሃዱ እንኳንም ያልከፈልነው ብለው ጮቤ እረገጡ፤ እንኳን ደስ አላቸው፡፡ የቀበሌ ግብርና ባለሙያዎች እንኳ ለየትኛው መስሪያ ቤት አቤት እንደሚሉ ግራ ገብቷቸው፣ በግብርና ስራ ላይ ትልቅ ክፍተት እየተፈጠረ ነበር፡፡ በመሆኑም ይህን አውታር ሞተር ሆኖ የሚያንቀሳቅስ፣ አንድ ወጥ የሆነ መስሪያ ቤት ያስፈልጋል፡፡
የአሁኑ “የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚ/ር”፣ በተለያዩ የመንግስት ስርዓቶች የተለያዩ ስሜዎች እንደነበሩት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የዚህን መስሪያ ቤት ታሪካዊ ዳራ ስንመለከት፣ በርካታ ጊዜ ስሙ ተቀይሯል። መንግስታት ሲቀያየሩ ያለፈውን መንግስት ስርዓት ላለመቀበል ብቻ እያፈራረሱ ሌላ ስያሜ ሲሰጡት ቆይተዋል፡፡ የሚያሳዝነው ጉዳይ ይኼ ሁሉ የስያሜ ጋጋታ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ አላወጣንም፡፡ ይህ መስሪያ ቤት ስንት ጊዜ ተሰየመ መሰልዎት፡፡ በ1900 ዓ.ም በዳግማዊ አጼ ሚኒልክ ዘመን፤ ሹማምንቶች ተሰባስበው ግብርናውን በበላይነት እየመራ የሚያስተባብር ሚኒስቴር መስሪያ ቤት “ሀ” ብለው ሲያቋቁሙ፣ ስያሜው ምን መሆን እንዳለበት ተወያዩ። በመጨረሻ ሹማምንቱ ተስማምተው፤ “የእርሻና የመስሪያ ቤት ሚኒስቴር” ብለው አጸደቁት፡፡
አጼ ኃይለስላሴም አጼ ሚኒልክ “የእርሻና የመስሪያ ቤት ሚኒስቴር” ብለው ከሰየሙት ስያሜ ላይ ‘መስሪያ ቤት’ የሚለውን ሀረግ ቆርጠው ጣሉና፣ በ1923 ዓ.ም  “የእርሻ ሚኒስቴር” ብለው ሰየሙት፡፡ አጼ ኃይለስላሴ አገር አማን ብለው በተቀመጡበት ስልጣናቸውን  በጉልበት የተረከበው ደርግ፣  በ1966 ዓ.ም ወታደራዊ የመንግስት ስርዓቱን ሲመሰርት፣ ቀደም ሲል “የእርሻና ደን ሚኒስቴር” እና “የመሬትና የህዝብ ማስፈር ሚኒስቴር”ን በአንድ ይዋሀዱ ዘንድ ሀሳብ አቀረበ። እናም የወታደራዊ መንግስቱ ከፍተኛ አመራሮች ይህን ሃሳብ አሜን ብለው ተቀበሉና፤ “የእርሻና የህዝብ ማስፈር ሚኒስቴር” ብለው ሰየሙት፡፡ ደርግ በ1971 ዓ.ም “የእርሻና የህዝብ ማስፈር ሚኒስቴር”ን እንደገና “የግብርና ሚኒስቴር” ብሎ ሰየመው፡፡
አጼ ኃይለ ስላሴን ፈንግሎ ዙፋኑ ላይ የተቀመጠው ደርግ፤ እሱም ክፉኛ በኢህአዴግ ተፈነገለና ኢህአዴግም በ1983 ዓ.ም አገሪቱን መምራት ሲጀምር፣ “የግብርና ሚኒስቴር”ን መዋቅር ቀይሮ “የግብርናና የአካባቢ ጥበቃ ልማት ሚኒስቴር” ብሎ ሰየመው፡፡ “ግብርና ሚኒስቴር” ተጠሪነቱ “ለገጠር ልማት ሚኒስቴር” እንዲሆን፣ በአዋጅ ቁጥር 256/1994 በወርሃ ጥቅምት ተወሰነ፡፡ “የግብርና ሚኒስቴርን” እና “የገጠር ልማት ሚኒስቴር”ን በአንድ በማዋሀድ፣ በአዋጅ ቁጥር 380/1996 “የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር” ተብሎ ተዋቀረ፡፡
በ2002 ዓ.ም እንደገና “ግብርና ሚኒስቴር” ተብሎ ተሰይሞ እስከ ጥቅምት 2008 ዓ.ም ሲሰራ ከቆየ በኋላ “የእንሰሳትና ዓሳ ሀብት ዘርፍ” ከ”ግብርና ሚኒስቴር” ወጥቶ ራሱን የቻለ አደረጃጀት እንዲኖረው ለማድረግ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የቀድሞው የግብርና ሚኒስቴር በአዋጅ ቁጥር 916/2008 አንቀጽ 19 መሰረት፤ “የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት  ሚኒስቴር” የሚል መጠሪያ ሰጡትና በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 20 ላይ ደግሞ “የእንስሳትና ዓሳ ሀብት” ዘርፉን ራስህን ችለህ፣ በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ደረጃ ተቋቁመሃል አሉና፣ የራሱን ስልጣንና ተግባር አደሉት፡፡
እነሆ አሁን ደግሞ በርስዎ ዘመን በወርሃ ሚያዚያ በአዋጅ ቁጥር 1014/2010 መሰረት፤ “የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚ/ር” ተብሎ ተሰየመ፡፡ (“ግብርና ነበርክና ወደ ግብርና ትመለሳለህ“ ዓይነት ነው፡፡) አሰራራችንን ካልቀየርን በስተቀር ግብርናን ቢሰነጣጥቁት ለውጥ አያመጣም፤ እንኳንም አቀላቀሏቸው፡፡ አሁንም እንስሳት ወደ ግብርና ተዋህዷል ለማለት አያስደፍርም፤ ገና በአያያዝ ነዋ፡፡ [ግብርና] ማለት ምን ማለት ነው? [እርሻን]ና [እንስሳትን] አያጠቃልልም እንዴ? እርሻ፣ በሬና ገበሬ ተለያይተው ያውቃሉ? ኧረ አያውቁም። ታዲያ እርሻውን አንድ መስሪያ ቤት፣ በሬውን ሌላ መስሪያ ቤት፣ገበሬውንም ሌላ መስሪያ ቤት ማስተዳደር አለበትን? አርሶ አደር ቤት ሲገቡ ነጭ ጤፍ እንጀራ በእርጎ ያቀማጥልዎታል፤ እንጀራና እርጎ የግብርና ውጤት አይደሉ እንዴ፡፡ ብዙ ሰዎች ”እንስሳ“ ግብርና አይደለም ወይ? እያሉ ነው እኮ፡፡
በግብርናው ዘርፍ ብቻ አይደለም፣ ሌሎች መስሪያ ቤቶችም የአወቃቀር ችግር አለባቸው፡፡  ብቻ አሁን የጀመሩትን ዘመቻ ይቀጥሉማ፡፡ ስንቱ መስሪያ ቤት አንድ ዓይነት ዓላማ ይዞ ኤጀንሲ፣ ማዕከል፣ ባለስልጣን፣ ድርጅት፣ ኢንተርፕራይዝ፣ ኮሚሽን፣ ጽ/ቤት …. ምናምን ተብለው ተበታትነው መሰለዎት የሚኖረው፡፡  
በግብርናው ዘርፍ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት፣ በርሃዎችን ወደ ገነት ለመቀየር፣ የመስኖ ልማት ስራዎችን በስፋትና በተቀናጀ መልኩ፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ተገቢው ትኩረት እንደሚሰጥ ነግረውናል። በርሃዎቻችን ወደ ገነት ለመቀየር ደግሞ ትኩስ ወጣት ሃይል ያስፈልጋል፡፡ የወንዝ ውሃ ከመንደራችን አልፎ ወደ ውጭ አገር እየፈሰሰ ቆሞ የሚያይ ወጣት ይዘን እንዴት እንለወጣለን?  የጤፍ ማሳችን ወደ ጫት እየተቀየረ (ትራንስፎርም እያደረገ)፤ ወጣቱም ወደ ጫት ትራንስፎርም እያደረገ እንዴት ለውጥ እናመጣለን? በእርስዎ ምክርና ማነቃቂያ፣ ወጣቱ ምርታማ እንደሚሆን  ተስፋ አደርጋለሁ፡፡  
ሰላም አይለየን !

Read 4387 times