Print this page
Monday, 07 May 2018 09:08

“ስለ ፍቅር ሲባል ስለ ፀብ ካወራን ተሳስተናል

Written by  በታምራት መርጊያ
Rate this item
(2 votes)

   “ስለ ፍቅር ሲባል ስለ ፀብ ካወራን ተሳስተናል
አንድ ላይ ብንሆንም ተለያይተናል” -- (ቴዲ አፍሮ)
እነሆ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ስልጣን ከያዙ አንድ ወር ከሦስት ከቀናት ሆናቸው። ሰውየው በነዚህ አፍላ የስልጣን ጊዜያቸው ውስጥ ህዝቡን ለማረጋጋት፥ ጆሮ ተነፍጎፈ የኖረውን ሕብረተሰብ በቀጥታ ለማነጋገርና መከፋቱንና ህመሙን ፈረንጆቹ እንደሚሉት፤ ከፈረሱ አፍ (Horses Mouth) በቀጥታ ለመስማትና ምክር ለመቀበል ጭምር፥ በርከት ባሉ የሐገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወሩ ሳይታክቱ፣ ባልተለመደ መልኩ ሕዝቡን መስለው እያዳመጡ፥ ስለ ፍቅር፥ ስለ እርቅ፤ ስለ አንድነት፥ስለ መደማመጥ፤ እንዲሁም ስለ መደመርና አብሮነት ሰርክ በየተሰየሙበት መድረክ ይሰብካሉ። “.ስንደመር እንጠነክራለን። አንድነት የማይፈታው ችግር አይኖርምና አንድ እንሁን… አንድ ስንሆን አገር እንገነባለን…” ይላሉ።
ለወጣቱ ትውልድ፤ “….ኢትዮጵያ የናንተ ነች፣ መጭውም ዘመን ከሁሉ በላይ የእናንተ ነው፤ አገሪቷን በመገንባት ግንባር ቀደም ሆናችሁ መሳተፍ ይኖርባችኋል…።” በማለት ብሩህ ተስፋን ይፈነጥቃሉ። የዳበረ የዲሞክራሲ ባህል አለመኖር፣ ሥር የሰደደ ድህነት፣ የተደራጀ የሙስናና የብልሹ አሰራር መስፋፋት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር እጦት ተደማምረው፣ ሰፊና ውስብስብ ፈተና፣ ሐገሪቱ ላይ ደቅነዋል፤ የሚሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የመፍትሔ አቅጣጫዎችንም ያመላክታሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ስለ ሰብዓዊ መብት፤ ስለ ዴሞክራሲና ስለ እኩልነት በመጠየቃቸውና በመታገላቸው ብቻ፥ በውሃ ቀጠነ ዘብጥያ ይወረወሩ ለነበሩ፣ ከሐገር እንዲሰደዱ ለተገደዱ፤ አንዳንዴ ተቃዋሚዎች፥ ሌላ ግዜ ደግሞ አሸባሪዎች፤ ሲያልፍም የሻቢያና የግብፅ ተላላኪዎች እየተባሉ አፍራሽ የፍረጃ ታርጋ ይለጠፍባቸው የነበሩ ወገኖችን ስያሜ በማለዘብ፣ “የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች” በሚል አዎንታዊ ስያሜ እየጠሩ፤ “…..ከእንግዲህ እናንተን የምናይበት መነጽር እንደ ተቃዋሚ ሳይሆን እንደ ተፎካካሪ፣ እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣ አማራጭ ሀሳብ አለኝ ብሎ እንደመጣ አገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ ነው፡፡” በማለት ቃል ይገባሉ።
 እዚህ ጋ የእውቀቶች ሁሉ ምንጭ በሆነው በታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ምሳሌ ምዕራፍ 15  ቁጥር 1 ላይ እንደተጻፈው፤ ”የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች፤ ሻካራ ቃል ግን ቁጣን ታስነሳለች” ተብሎ የተገለጸው ልብ ሊባል ይገባል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)፥ “ተፎካካሪ ፓርቲዎች” በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ የተመቻቸና ፍትሃዊ የመወዳደሪያ ሜዳ እንዲኖር፣ በመንግስታቸው ጽኑ ፍላጎት ያለ መሆኑን እየገለጹ፤ “ስለ ሰላምና ፍትህ በልዩ ልዩ መንገድ ለሚታገሉ “የተፎካካሪ ፓርቲ” መሪዎች፣ አብሮነታችንንና ሰላማችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ፤ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንንም አሳልፈው የሚሰጡ የአስተሳሰብ መስመሮችን በአርቆ አስተዋይነትና ሀገራዊ ፍቅር፤ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተሻለ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር የምናደርገው ጥረት አግዙን” ሲሊ ትህትና በተሞላው አንደበታቸው ይማፀናሉ፡፡ ይሁን እንጂ፥ ሁሉም እንኳን ባይሆኑ፤ ቀላል ቁጥር የማይሰጣቸው፥ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላቸውና በጎ አሻራቸውን ያሳረፋ፥ የበቁ የነቁ ብለን የምናስባቸው ልሂቃን፥ ይህን በጎ የሆነ የሰውየውን መልካም ንግግር አባን ከና ያሉት አይመስልም።
ይልቁንም የዶክተሩን ንግግር እየሰነጣጠቁና የራሳቸውን ትርጉም እየሰጡ፣ በዶክተሩ ላይ የትችትና የውግዘት ጋጋታ በማዝነብ፣ የጭቃ ጅራፋቸውን ማጮህ መያያዛቸውን ለመታዘብ ችለናል። ሌሎቹ ደግሞ ዴሞክራሲ በረጅም ጊዜ ውስጥ የሚገነባ ሂደት መሆኑ ተዘንግቷቸው፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሯቸው መልካም ነገሮች ሁሉ በአንድ ጀምበር ተፈጽመው ካላየን አናምንም በሚል አይነት ስሜት፣ የጠቅላዩ ንግግሮች ሽንገላ ብቻ እንደሆኑ ሲገልጹ ይሰማሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የሰውዬው ንግግር ከፓርቲያቸው ባህል ያፈነገጠ ስለሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም በሚል ረብ የለሽ ትርክት፥ መልካም ነገርን በመልካምነቱ ከመቀበል ይልቅ ያልበላቸውን ማከክ የሚቀናቸውንም አዋቅት ለመታዘብ ችለናል። “እባብ ያየ በልጥ፥ ይበረያል..” እንዲል የሐገሬ ሰው፤እንዲሁ በደመነፍስ ጠቅላዩን፣ ከኢህአዴግ የመጣ ያው ኢህአዴግ ነው፥ “እሳት ካየው ምን ለየው” ሲሉ የሚገልጿቸውም አሉ።
የዴሞክራሲያዊ ስርዐት ዋና ምሰሶ ውይይትና ንግግር መሆኑን በቅጡ ያልተረዱቱ ደግሞ “ቃል ብቻውን ዋጋ የለውምና ወሬ ሰለቸን” ሲሉ የሰውየውን ጥረት ለማጣጣል ይሞክራሉ፡፡ እውነታው ግን ከድርጊት በፊት ቃል መቅደሙ ነው። አንዳንዶች ደግሞ “ለምን በፌደራል ቋንቋ አልተናገሩም፤ ለምን ለብሔሮች በቋንቋቸው ተናገሩ” በሚል እርባና ቢስ መከራከሪያ፣ አቧራ ለማስነሳት ሲሞክሩ ይስተዋላሉ። እነኚህ ወገኖች በዚህ ከቀጠሉ “ለምን አሜሪካ ሔደው ወይም በተባበበሩት መንግስታት ስብሰባ ላይ በእንግሊዘኛ ተናገሩ፤ አሊያም በአማርኛ ለምን አልተናገሩም” የሚል ልብ አውልቅ ክርክር ማንሳታቸው አይቀርም። ይህ ሁሉ እንግዲህ የአገራችን የወቅቱ ፖለቲካ ነው። የሆነው ሆኖ “ሁሉን መርምሩ መልካሙን አጽኑ” እንደሚባለው፤ መመርመሩ መልካም ሆኖ ሳለ፥ ሳይመረምሩ፣ የሠውን መልካም አቀራረብ በአሉታዊ ጎኑ ብቻ እየፈረጁ ማጣጣልና ማውገዝ፤ ፈጽሞ ተገቢ አይሆንም። የኢትዮጵያዊ ጨዋነትንም አይገልጽም።
እጅግ የተወሳሰበ ፖለቲካዊ፥ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስንክሳር በበዛበት ሐገር፥ ገና አንድ ወር እንኳን በቅጡ ያልሞላውን ጠቅላይ ሚኒስትር፥ ቃላት እየሰነጠቁና እያጣመሙ፥ በረባ ባረባው እንዲህ ከፍና ዝቅ አድርጎ ማብጠልጠል ከግብታዊነት የሚመነጭ አስተዛዛቢ ባህሪ እንደሆነ የሚያጠያይቅ አይደለም። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ አሁን ባሉበት ደረጃ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ለአቅመ ትችትም ሆነ አድናቆት ገና አልደረሱም። ለመተቸትም ሆነ ለማድነቅ ጊዜው እጅግ ገና ነው። ሠውየው በየመድረኩ እያደረጉ የሚገኙትን የአንድነት፤ የሠላምና የፍቅር ይዘት ያላቸው ንግግሮች በመመልከት፣ ቢያንስ መልካም ንግግሮቻቸውን በበጎ ጎኑ መውሰድ ግን ሐገር ወዳድና ጤናማ አመለካከት ካለው ዜጋ የሚጠበቅ ነው። በተቀረ የዚህ ኢ-አመክንዮአዊ ትችት አንድምታ የሚያሳየው፣”እኛ ሐገር ካልመራን ዴሞክራሲም ሆነ ፍትህ ሊመጣ አይችልም” ወይም “እኛ ያልወጠወጥነው ወጥ፥ ወጥ አይሆንም”፤ የሚል አይነት፣ የተለየ የስልጣን ፍላጎትና ዝንባሌን የሚያሳይ ብቻ ይሆናል።
በነገራችን ላይ የዚህች አጭር ጽሁፍ ዓላማ ለዶክተር አብይ ድጋፍ ለማሰባሰብ ወይም ከንቱ መወድስ ለማቅረብ የታለመ አድርጎ የተገነዘበ አንባቢ ካለ መሳሳቱን ለመግለጽ እወዳለሁ። ይልቁንም  ለማስተላለፍ የተፈለገው መልዕክት፥ መልካም ነገሮችን በመልካምነታቸው እንቀበል…። ስለ ፍቅር ሲነገር ስለ ፀብ አናውራ...። ነገሮችን በትክክለኛ ጊዜና ቦታቸው መርምረን ብያኔ እንስጥ...። ለመቃወም ብለን ብቻ ሁሉን አንቃወም፤ ምክንያቱም መቃወም ግዴታ አይደለምና...። መልካም ጅማሮዎችን እናበረታታ፥ ያን ስናደርግ የጅማሮው ባለቤት የሆኑትን ሰዎች በጀመሩት መንገድ እንዲገፉ አቅም ከመሆን ባለፈ የሞራል ሐላፊነት እንዲሰማቸው ማድረግ እንችላለን የሚል ነው።
እናም ቆም ብለን እናስብ፡፡ የሔደውንም የመጣውንም ሳንመረምር እየተቸንና እያወገዝን አንዘልቀውም። ለውዳሴውም ሆነ ለትችቱ እንደርስበታለን። ሁሉም ነገር በቦታውና በጊዜው (Time and Place requirements) ሲቀርብ ያምራልና። በተለይም ተጽዕኖአችሁ ከፍ ያለ ልሒቃን፥ ለውዳሴም ሆነ ለትችቱ ምክንያታዊ በመሆን አርዓያነት ያለው ተግባር በመፈጸም እንዲሁም ህብረተሰብን በማንቃት፥ ምክንያታዊ ማህበረሰብ የመፍጠር ሐገራዊና ሞራላዊ ግዴታ እንዳለባችሁ ልብ ልትሉ ይገባል።
ስለ ፍቅር ሲባል፣ ስለ ፀብ ካወራን ተሳስተናል! ቸር እንሰንብት!

Read 2847 times