Monday, 07 May 2018 09:06

“ከእንግሊዝ ቅርሶችን ማስመለስ የሚቻልባቸው አማራጮች አሉ”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 · የልዑል ዓለማየሁን አፅምና የቴዎድሮስን ሹርባ ማስመለስ እንችላለን
  · የጀነራል ናፒዬር ቤተሰቦች በቅርቡ አንድ ሀብልና ብራና መልሰዋል
  · የብሪቲሽ ሙዚየም ከመቅደላ የተዘረፉ 13 ታቦታት አሉት

    የኢትዮጵያ ወዳጅና ባለውለታ የነበሩት አንጋፋው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፤ በርካታ ኢትዮጵያዊ ጉዳዮች ላይ አተኩረው በመመራመር ጥናት ጠገብ ፅሁፎችንና መፃህፍትን ለንባብ ያበቁ ሲሆን በእንግሊዝ አገር የሚገኙ ከኢትዮጵያ ተዘርፈው የተወሰዱ በርካታ ቅርሶች እንዲመለሱም በተደጋጋሚ ፅፈዋል፤ሞግተዋል፡፡ የአክሱም ሐውልት አስመላሽ ኮሚቴ አባል በመሆንም ሐውልቱን ለማስመለስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ልጅ የሆኑት ዶ/ር አሉላ ፓንክረስት፣ የአባታቸውን ዱካ በመከተል የኢትዮጵያ ቅርሶችን ከእንግሊዝ አገር በማስመለስ እንቅስቃሴ ላይ በንቃት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ በቅርቡ በተከበረው የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ 150ኛ ዓመት ዝክረ በዓል ላይ ያቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍም የኢትዮጵያውያንን የተዘረፉ ቅርሶች ማስመለስ በሚቻልበት ዕድሎች ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ዶ/ር አሉላ እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት በእንግሊዝ ሙዚየሞችና ቤተ- መፃሕፍት የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶች ሊመለሱ የሚችሉበት ህጋዊና ዲፕሎማሲያዊ ዕድሎች አሉ፡፡ ተስፋ ሳይቆርጡ መልፋትና መትጋት እንደሚጠይቅ ግን አልሸሸጉም፡፡  
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሽዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ የትምህርት ክፍል በተባባሪ ፕሮፌሰርነት ላለፉት 16 ዓመታት ያገለገሉት ዶ/ር አሉላ ፓንክረስት፤በአሁኑ ወቅት ራሳቸው ባቋቋሙት የጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ የተለያዩ ጥናቶች የሚያካሂዱ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ በአራት የዓለም ታዳጊ አገራት ውስጥ በህፃናት ድህነት ላይ አተኩሮ የሚያጠናው “Young Lives” የተሰኘ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርም ናቸው፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ የተዘረፉ ቅርሶችን ከማስመለስ ጋር በተገናኘ ዓለም አቀፍ ህጎች ምን ይላሉ፤ ራሳቸው በጥናታቸው የጠቀሷቸው ህጋዊና ዲፕሎማሲያዊ አማራጮች ምን ያህል ያዋጣሉ፣ በእንግሊዝ የሚገኙ ቅርሶቻችንን ለማስመለስ ያለው ተስፋ ምን ያህል ነው--   በሚሉትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከዶ/ር አሉላ ፓንክረስት ጋር ተከታዩን ዕውቀትና ግንዛቤ የሚያስጨብጥ  ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ እነሆ፡-


    በእንግሊዝ የሚገኙ ቅርሶቻችንን ለማስመለስ የሚቻልባቸው እድሎች እንዳሉ ባቀረቡት ጥናት ላይ አመልክተዋል፡፡ ለመሆኑ ጥናቱን ለመስራት መነሻ የሆነዎት ምንድን ነው?
እኔ እንግዲህ የታሪክ ባለሙያ አይደለሁም፤ ግን በእንግሊዝ ስለሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶች የተሻለ ግንዛቤ አለኝ፡፡ ለጥናቱ መነሻዬ የአፄ ቴዎድሮስ 150ኛ ዓመት መታሰቢያ ዝክረ በዓል ነው፡፡ አብዛኞቹ ቅርሶችም ወደ እንግሊዝ የሄዱት በመቅደላ ጦርነት ጊዜ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ይሄ በዓል መከበሩ ትልቁ ነገር፣ ሁሉም ሰው በዚህ ቅርስ ማስመለስ ጉዳይ ላይ ግንዛቤ አግኝቶ፣ ትኩረት እንዲያደርግ እድል መፍጠሩ ነው፡፡ በዚህም ደስ ብሎኛል፡፡ የዚህ በዓል አከባበር ከእኔ ይልቅ አባቴ በህይወት ቢኖርና ቢመለከት እጅግ ደስተኛ ይሆን እንደነበር አልጠራጠርም፡፡
እኔም ይህንን የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስን አሳዛኝ የህይወት ታሪክ በፎቶግራፍ አስደግፌ ጥናቱን ለማቅረብ ያነሳሳኝ አንድም የዚህ ልጅ ታሪክ አሳዛኝ በመሆኑ ነው፡፡ ሁለትም ደግሞ የአባቴ ትዝታ ነው፡፡ አባቴ አፄ ቴዎድሮስ በዚህች አገር ላይ ያደረጉትን አስተዋፅኦ በጣም ያደንቅ ነበረ፡፡ በሌላ በኩል በዛን ወቅት የተዘረፉ ቅርሶች ለኢትዮጵያ እንዲመለሱ አባቴ በእጅጉ ጥሯል፡፡ ከኢትዮጵያ ህዝብ፣ መንግስትና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር በመሆን የተዘረፉ ታቦታት፣ ብራና፣ ዘውዶችና የተለያዩ ንብረቶች ለባለቤታቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲመለሱ በጣም ታግሏል፡፡ አባቴ ከእነ ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ ጋር በመሆን፣ ያኔ በተቋቋመው “አፍሮ ሜት” በተባለው ኮሚቴ በኩል በጋራ በመታገል፣ የተወሰኑ ቅርሶችን ለማስመለስ ችለዋል፡፡ ከዚያ በፊትም የእንግሊዝ መንግስት የመለሳቸው ቅርሶች ነበሩ፡፡
ቅርሶቻችንን ለማስመለስ የምንችልባቸው ህጋዊም ዲፕሎማሲያዊም አማራጮች አሉ ብለዋል፡፡ እስኪ ያሉትን አማራጮች ያብራሩልኝ?
የእንግሊዝ መንግሥት ቅርሶችን አይመልስም የሚል ምክንያት ቢቀርብም ሊመልስ የሚችልበት አራት ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው አፄ ዮሐንስ፤ ከአፄ ቴዎድሮስ ሞት በኋላ ሁለት ቅርሶች እንዲመለስላቸው ጠይቀው ነበር፡፡ አንደኛው “ክብረ ነገስት” ሲሆን ሌላኛው ደግሞ “ኩራተ ርዕሱ” የተሰኘ ስዕል ነው፡፡ ይህ ስዕል የኢየሱስ ክርስቶስ ምስል ነው፡፡ ብዙ የኢትዮጵያ መሪዎች ወደ ጦር ሜዳ ሲሄዱ፣ ይህን ስዕል ይዘው ነበር የሚሄዱት፡፡ አፄ ዮሐንስ እነዚህን ሁለት ቅርሶች ነበር የጠየቁት፡፡ የእንግሊዝ መንግስትና ንግስቲቱ፤ አፄ ዮሐንስን ማስቆጣት ስላልፈለጉ፣ ይመለስ የሚል ሀሳብ አቀረቡ፡፡ ከሁለቱ ክብረ ነገስቶች ቆንጆውንና ብዙ ስዕሎች ያሉበትን አስቀርተው ከዚያ የሚያንሰውን መልሰዋል፡፡ “ኩራተ ርዕሱ” የተባለውን ስዕል ግን ጠፋ አሉ፡፡ ነገር ግን አልጠፋም ነበር፡፡ ሆምዝ የተባለውና መቅደላ ላይ አብዛኛውን ቅርስ ለእንግሊዝ ሙዚየም የገዛው ግለሰብ በራሱ እጅ አስቀምጦት፣ አፄ ዮሐንስ ከሞቱና ይሄ ጥያቄ ከተረሳ በኋላ አውጥቶ ለግለሰብ ሸጠው፡፡ እስካሁንም የግለሰብ ንብረት ሆኖ ከአንዱ ሰው ወደ አንዱ እየተዘዋወረ፣ ፖርቹጋል የሚኖር ሰው እጅ ላይ ይገኛል፡፡
ከዚያ በኋላ ጃንሆይ አልጋወራሽ ሆነው ወደ እንግሊዝ አገር እ.ኤ.አ በ1924 ዓ.ም ሲሄዱ የእንግሊዝ መንግሥት፣ ለንግሥት ዘውዲቱ አንድ ስጦታ ማበርከት ፈልጎ፣ ከነበሩት አንድ የወርቅና አንድ የብር ዘውዶች፣ የብሩን ዘውድ ሲልኩ፣ የወርቁ ዘውድ ግን እስካሁን ቪክቶሪያን አልበርት ሙዚየም ውስጥ ይገኛል፡፡  
የሚያሳዝነው ነገር ግራዚያኒ ይህንን ቅርስ ዘርፎ ጣሊያን አገር ሲወስደው፣ በዛን ጊዜ ከኢትዮጵያ፣ ከሊቢያና ከሌሎች አገራት የሚወሰዱትን ቅርሶች ማስቀመጫ ሙዚየም ሊያቋቁሙ ነበርና ያንን ዘውድም እዚያ ሙዚየም ለማስገባት ነበር ያቀደው፡፡ ግራዚያኒ ግን ሃሳቡን ቀይሮ በግለሰብ ደረጃ ቀጥታ ለሞሶሎኒ ሰጠው፡፡ ሞሶሎኒ በእጁ አስቀምጦት ቆይቶ፣ መጨረሻ ላይ ሲሸነፍና ሲሸሽ አራት ዘውዶችን ይዞ ሸሸ፡፡
ሞሶሎኒ ይዟቸው የሸሸው እነማን ሲጠቀሙባቸው የነበሩትን ዘውዶች ነው?
ዘውዶቹ የአፄ ቴዎድሮስ፣ የአፄ ዮሐንስ፣ የኃይለሥላሴና ሌላ አንድ ዘውድ ነበሩ፡፡ በኋላ ሞሶሎኒ ተማረከ፡፡ ተማርኮ ፎቶግራፍ ሲያነሱት፣ ከበስተጀርባው ዘውዶች ይታዩ ነበር፡፡ አሁን እነዛ ዘውዶች ይሸጡ፣ አቅልጠዋቸው ይሁን በግለሰብ እጅ ይግቡ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ይሄ ሁለተኛው ምሳሌ ነው፡፡ እንግሊዞች ለንግሥት ዘውዲቱ የመለሱት የብር ዘውድ ማለቴ ነው፡፡ ሦስተኛው ምሳሌ፡- አሁን በህይወት ያለችው ንግሥት ኤልሳቤጥ፣ በ1965 እ.ኤ.አ ወደ አዲስ አበባ ስትመጣ፣ የአፄ ቴዎድሮስን ማህተምና አንድ ባርኔጣ ነገር ማምጣቷ ይታወሳል፡፡ እንደውም የአፄ ቴዎድሮስ ማህተም እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ውስጥ ይገኛል፡፡ እና ይሄ የሚያሳየው የእንግሊዝ መንግሥት ከፈለገ ቅርሶቹን መመለስ እንደሚችል ነው፡፡ አሁን ግን የእንግሊዝ መንግሥት አቋም፣ አንድ ጊዜ እቃዎች ሙዚየም ከገቡ ፓርላማው አዋጅ ካላወጀ በቀር ማውጣት አይቻልም የሚል ነው። ነገር ግን ሲፈልጉ ቀደም ባሉት ምሳሌዎች እንዳየነው፣ ሶስት ጊዜ አራት ቅርሶችን መልሰዋል፡፡
በግለሰብ ደረጃ የኢትዮጵያን ቅርሶች የመለሱ የውጭ ዜጎች እንዳሉም ይነገራል …
ትክክል ነሽ፡፡ ግለሰቦች በራሳቸው ተነሳሽነት የኢትዮጵያን ቅርሶች መልሰዋል፡፡ በግለሰብ ደረጃ የተመለሱትም አስራ ምናምን ይሆናሉ - ቁጥሩን እርግጠኛ ባልሆንም፡፡ እንግሊዞች አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን በሰዉበት ጊዜ መቅደላን አቃጠሉ፤ ብዙ ህዝብ ገደሉና እያንዳንዱ ወታደር ዝርፊያ ጀመረ። እየሄዱ የፈለጉትን ዘርፈው ይወስዱ ነበር። መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን በሩን አፍርሰው፣ ታቦታትን ሁሉ ዘርፈዋል፡፡ ይህ ወታደሩ በግሉ የዘረፈው ነው፡፡ የሚገርምሽን ነገር ልንገርሽ፡፡ ቅድም ሆምዝ ያልኩሽ ከእንግሊዝ ሙዚየም ብዙ ቅርስ የገዛው ግለሰብ፣ አንድ ወታደር የወርቅ ዋንጫ ዘርፎ ሲመለስ ሽጥልኝ አለው፡፡ ወታደሩ ያንን የሚያክል የወርቅ ዋንጫ በአራት ፓውንድ ብቻ ነው ለሆምዝ የሸጠለት። ይህ ሲሆን ጀነራል ናፒዬርና ሌሎቹ መሪዎች፣ ይህን ነገር ስርዓት ማስያዝ አለብን ብለው፣ እቃውን በሙሉ ወስደው ትልቅ ሜዳ ላይ ቆልለው በጨረታ መሸጥ ጀመሩ፡፡
ከዚያስ?
ከዚያማ ያንን የጨረታ ብር ሰብስበው ለወታደሮቹ አራት አራት ፓውንድ ሰጧቸው፡፡ ያን ጊዜ ነው “ኩራተ ርዕሱ” የተባለውን የኢየሱስ ክርስቶስን ስዕል የደበቀው ሆምዝ የተባለው ግለሰብ አብዛኛውን ቅርስ የገዛው፡፡ ብራናው ብቻ እንኳን በግምት ከ500 በላይ ነው በጨረታ የተሸጠው፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ከተለያየ ቦታ የሰበሰቡትና ያጠራቀሙት ነበር፡፡ በነዚህ ቅርሶች የተሞላው ብሪቲሽ ሙዚየም፤ ከራሱ አልፎ ለእነ ካምብሪጅ፣ ኦክስፎርድ፣ ኤድምብራ፣ ደብሊንና በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ባሉባቸው አካባቢዎች አሰራጨ፡፡ ቅርሶቻችን በአሜሪካ ሳይቀር ተበተኑ፡፡ የሚገርምሽና የሚያሳፍረው አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ሰውተው ሲንፈራፈሩ የደረሱ ወታደሮች፣ ልብሳቸውን ተቀራምተው እርቃናቸውን አስቀርተው፣ የአንገት ሀብላቸውን ወስደዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ አንድ ጋሻ ላይ ሶስት የእንግሊዝ ሬጅመንት (ባታሊዮኖች) ተጣልተው፣ ሶስት ቦታ ቆርጠው ተከፋፍለውታል። አሁንም ያ ጋሻ የተቀመጠው ሶስት ቦታ ተቆራርጦ ነው። ይህን ሲያይ አባቴ ተበሳጭቶ፤ “አሁን የዚህ ጋሻ አንድ ሶስተኛ ቁራጭ ምን ይጠቅማችኋል? ሶስቱንም አንድ ላይ አድርጋችሁ መልሱ” የሚል ክርክር አንስቶ ነበር፡፡ እስካሁን አልተሳካም፡፡
ወደ ዋናውና ግለሰቦች በተነሳሽነት ቅርስ መልሰዋል ወደሚለው ሃሳብ ስንመለስ፣ በተለይ ስኮትላንዶች ብዙ ቅርሶችን በግለሰብ ደረጃ መልሰዋል፡፡ ለምሳሌ ሁለት ታቦቶች፣ የአፄ ቴዎድሮስን ሀብል መልሰዋል፡፡ ብዙዎቹ ስማቸው እንዲገለፅ አይፈልጉም፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ከአያት ከቅድመ አያት እየተወራረሰ መጥቶ ምንነቱን ሳያውቁ አስቀምጠውት፣ “አፍሮ ሜት” (የአፍሪካ መቅደላ ትሬዠር አስመላሽ ኮሚቴ) ንቅናቄ ሲጀምር ሰምተው፣ ስሜታቸው ተነክቶ ነው የመለሱት። አንደኛው እንደውም ብራና ሲመልስ፡- “ህሊናዬ አልፈቀደም፤ ልጆቼም ጎተጎቱኝ፤ መመለስ አለብኝ ብዬ መለስኩ” ነው ያለው፡፡ የተወሰኑ ብራናዎች፣ መስቀሎችና ሀብሎች በግለሰቦች ተመልሰዋል፡፡ የጀነራል ናፒዬር (የእንግሊዝ ጦር አዛዥ) ቤተሰቦች ባለፈው ወር አንድ ሀብልና አንድ ብራና መልሰዋል፡፡ ይህ የሚደነቅ ነው፡፡ አብዛኛው ግን በመንግሥት እጅ ነው ያለው፡፡
በቅርቡ የእንግሊዝ መንግሥት፤ ቅርሶቹን “በረጅም ጊዜ ውሰት” ውሰዱ የሚል ጥያቄ ማቅረቡን ሰምተናል። ይህ ምን ማለት ነው?
በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ በረጅም ጊዜ ውሰት ውሰዱ የሚል ሃሳብ ያመጡት የቪክቶሪያን አልበርት ሙዚየም ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ይህን ለምን አሰቡ? ህጉ ቀጥታ ለመመለስ ስለማይፈቅድ ነው ይላሉ፡፡ ህጉ ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የነበረ ነው፡፡ ስለዚህ እንደ መጀመሪያ እርምጃ፣ በረጅም ጊዜ ውሰት ይውሰዱ አሉ፡፡ ነገር ግን ችግሩ ምንድን ነው? በውሰት ከሆነ፣ አሁንም ቢሆን ባለቤትነቱ የእንግሊዝ ለመሆኑ እውቅና መስጠት ነው ተባለ፡፡ ቅርሶቹ የኢትዮጵያ ናቸው፤ መቼና እንዴት እንደተዘረፉ ይታወቃል፤ ስለዚህ ሰው የራሱን ንብረት መዋስ አያስፈልገውም፡፡ ቅርሶቹ መመለስ አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ናቸው፡ አለቀ!
ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉ ትክክል ነው ይላሉ?
አዎ! ትክክለኛ እርምጃ ነው፡፡ ነገር ግን በምን መልኩ ማስመለስ ይቻላል የሚለው ነገር ላይ በደንብ መታሰብ አለበት፡፡
ቅርሶቻችንን ከእንግሊዝ የማስመለስ ተስፋው ምን ያህል ነው?
ተስፋዎች አሉ፡፡ አሁን ለምሳሌ በቅርቡ የወጣው የእንግሊዝ የፓርላማ አዋጅ፤ የሰው አፅምና ፀጉርን ጨምሮ ለአገሩ ባለቤት መመለስ አለበት እንጂ በእንግሊዝ መቀመጥ የለበትም ይላል፡፡ ይሄ አዋጅ ከአምስት ዓመት ወዲህ የወጣ ነው፤ ስለዚህ ይህን ህግ ተጠቅሞ የልዑል ዓለማየሁን አፅምና የአፄ ቴዎድሮስን ሹርባ ፀጉር ማስመለስ ይቻላል፡፡ እስካሁን የልዑል ዓለማየሁን አፅም ላለመመለስ የሚያቀርቧቸው ሁለት ምክንያቶች አሉ፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፣ ለኢትዮጵያ ሚሊኒየም በ2000 ዓ.ም በሄዱ ጊዜ ይመለስ ብለው ጠይቀው ነበር፡፡ የተሰጠው ምላሽ ሁለት ነው፡፡ አንደኛው፤ የዌንዘር ቤተ መንግስት ቤተ ክርስቲያንን (የቅዱስ ጊዮርጊስን ግንብ) ሊያናጋ ይችላል የሚል ነው፡፡
ይሄኛው የእንግሊዝ መንግስት መከራከሪያ አሳማኝ አይደለም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ በመቃብሩና በቤተ ክርስቲያኑ መካከል በቂ ርቀት በመኖሩ ፍፁም ግንቡን ሊያናጋ አይችልም የሚል ነው…
ትክክል ነው፡፡ በግንቡና በመቃብሩ መካከል ርቀት አለ፡፡ አፅሙ ተቆፍሮ ቢወጣ ግንቡን ሊያናጋ የሚችልበት አጋጣሚ ስለሌለ፣ ከላይ የተነሳው መከራከሪያ ማየሚያሻማ አይደለም፡፡ ሌላው እንግሊዞች ያቀረቡት ምክንያት፤ ልዑል አለማየሁ የተቀበረው ሌሎች ሰዎች በተቀበሩበት አካባቢ በመሆኑ፣ የእሱ አፅም የትኛው እንደሆነ ለመለየት ያስቸግራል የሚል ነው፡፡ ይሄኛውም አሳማኝ አይደለም፤ አሁን ቴክኖሎጂው ተራቅቆ የት በደረሰበት ሰዓት፣ ይሄ የሚያስጨንቅ ጥያቄ አይደለም፡፡
እንዴት ማለት?
በጣም ጥሩ፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ ፀጉር እዚያው አገር ሙዚየም ውስጥ አለ፡፡ የልዑል አለማየሁ አፅምም አለ፡፡ የዲኤንኤ (DNA) ቀላል ምርመራ አፅሙ የትኛው እንደሆነ በቀላሉ ይመልሰዋል፡፡ ሌላ በቅርቡ የደረስኩበት ጥናት የሚያረጋግጠው ነገር አለ፡፡ ንግስት ቪክቶሪያ፣ ልዑል ዓለማየሁን በጣም ትወደው ነበር፡፡ በጣም ትንከባከበው ነበር፡፡ በየቀኑ እሱን ወደሚያሳድጉት ሰዎች ቴሌግራም ትልክም ነበር። ሀኪሞች ሳይቀር ትልክለት ነበር፡፡ “የምፅፍለትን ደብዳቤ አንብቡለት” ትላቸው ነበር፡፡ አድጎ አንድ ደረጃ እንዲደርስ ሁሉ ትመኝ ነበር፡፡ በኋላ ሲሞት በጣም አዝና “ለማስታወሻ እንዲሆነኝ፣ ከፀጉሩ የተወሰነውን ላኩልኝ” ብላ ጠይቃ፣ ተልኮላታል፡፡ ይሄም አንድ ማረጋገጫ ይሆናል፡፡
ሃይማኖት ነክ ቅርሶችም ለባለቤቶች እንዲመለሱ የፓርላማቸው አዋጅ ይደነግጋል የሚባል ነገር አለ…?
አዎ! ለአንድ ሃይማኖት ወሳኝ የሆኑና ከሃይማኖት ጋር የተቆራኙ ነገሮች ሙዚየም ውስጥ በጭራሽ መታየት የለባቸውም የሚል ነው ሃሳቡ፡፡ ስለዚህ የብሪቲሽ ሙዚየም 13 ታቦታት አሉት፡፡ 11ዱ በእርግጠኝነት ከመቅደላ የተዘረፉ ናቸው፡፡ ሁለቱም ከዚያው የወጡ ይሆናሉ፡፡ በምንም ተዓምር ለህዝብ እንዳይታይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታግላ ነበረ፤ እነሱም አምነውበታል፡፡ በእንግሊዝ ፓርላማ አዋጅ ደግሞ እነዚህ ታቦታት ለዘላለም ሊታዩ አይችሉም፡፡ የአንድ ሙዚየም አላማ ደግሞ ያለውን ቅርስ ማሳየት በመሆኑ፤ ለኢትዮጵያ አለመመለሱ ትርጉም የለውም። ስለዚህ ከልዑል አለማየሁ አፅምና ከአፄ ቴዎድሮስ ሹርባ ቀጥሎ በቀላሉ ልናስመልሳቸው የምንችላቸው፤ ታቦታት፣ ብራናና የሃይማኖት መፅሐፍትን ነው። መስቀሎችንም ማስመለስ እንችላለን፡፡ በግለሰብ ደረጃም አንድ መስቀል ተመልሷል፡፡
በሌላ በኩል በአሁን ሰዓት ያለው ቴክኖሎጂ፣ በጣም በተመሳሰለ መልኩ በኮፒ ብራናም ሆነ ሌላ ለመስራት ቀላል ነው፡፡ ቻይናዎች በተለይ በዚህ ተራቀውበታል፡፡ በክረምት ብሪቲሽ ሙዚየም ሄጄ ያሳዩኝ ሁለት ብራናዎች ነበሩ፤ የኢትዮጵያ ግን አይደሉም፡፡ እነዚህ ሁለት ብራናዎች አንዱ ኦሪጂናሉ ሲሆን ሁለተኛው ኮፒው ነው፡፡ እዛ የሚሰራ ኢትዮጵያዊ “ሁለቱን ለይ” አለኝ ግን መለየት አልቻልኩም፡፡ ስለዚህ ቢቻል ኦሪጂናሎቹን ለእኛ ሰጥተው፣ ከፈለጉ ኮፒዎቹን ያስጎብኙ፡፡ በሌላ በኩል እንግሊዞች እስከ ዛሬ ለተጠቀሙበት ካሳ መክፈል ይገባቸዋል፤ ካሳቸው እንኳን ቢቀርና ኦሪጂናሉን ለመስጠት ህጉ ያስቸግራል፣ ለጊዜው አንችልም ካሉ፣ በጊዜያዊነት ኮፒዎቹ ተልከው እዚህ እንዲታዩ ቢደረጉና ህጉ ሲለወጥ መቀያየርና ኦሪጂናሎቹን ለእኛ መስጠት እንዲችሉ በጥብቅ መሰራት አለበት፡፡ ለኮፒው ስራውም ቢሆን የሚወጣው ቀላል ገንዘብ ስላልሆነ ባይሆን ህሊናቸው ወቅሷቸው ገንዘብ አውጥተው ኮፒ ማሰራት አለባቸው ባይ ነኝ፡፡
ሌላው የተወሰነ ቅርስ እንኳን ቢመለስና ቢጎበኝ ህዝቡ ይነቃቃል፤ ጋዜጠኞች ይፅፋሉ፤ ማህበራዊ ሚዲያው ይንቀሳቀስበትና በእንግሊዝም ሆነ በሌሎች መንግስታት ላይ ጫና ያሳድራል፡፡ የአክሱም ሀውልትን ያህል ነገር ማስመለስ የተቻለው ኮሚቴው ጠንካራ ስለነበር ነው፡፡ አባቴም ሲፅፍና ሲጎተጉት ነበር፡፡ ብዙ ሰው እኔን ጨምሮ ግን ይመለሳል የሚል እምነት አልነበረንም፡፡ ከተሰራና ከተለፋ የማይሳካ ነገር የለም፡፡ አባቴ ደግሞ ተስፋ አይቆርጥም ነበር፡፡ ሀውልት ሲመለስ የሰው አካል ማስቀረት በጣም አስነዋሪና የሚዘገንን ነገር ነውና መመለስ አለበት፡፡ ይህንን አሳምነን ከመለስን ሌላውን በዲፕሎማሲ፣ በሚዲያ ቅስቀሳ፣ በህዝብና በሃይማኖት አባቶች ተሳትፎ ማስመለስ እንችላለን። የእነሱ ስጋት አንዴ አንድ ነገር ከመለስን፣ ህጉም ያስገድደንና ሁሉንም ስንመልስ እንራቆታለን የሚል ነው፡፡ እንደውም የአውሮፓ ሙዚየሞች ተሰብስበው በህብረት “ቅርስ አንመልስም” የሚል ፒቲሽን እስከ መፈራረም ደርሰዋል፡፡
ነገር ግን የሰው አፅምና አካል እንዲሁም ከሃይማኖት ጋር የተቆራኙ ቅርሶችን ራሳቸው አምነውበት ባወጡት ህግ በቀላሉ ማስመለስ ስለምንችል፣ በዚህ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት አለበት የሚለው ላይ አፅንኦት መስጠት እፈልጋለሁ፡፡ እንደውም አንድ ምሳሌ ልጥቀስልሽ፣ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ማክሮም “የአፍሪካ ቅርሶች በአውሮፓ ሙዚየሞች ውስጥ እስረኛ ሆነው መቅረት የለባቸውም” የሚል አቋም ያንፀባረቀበትን፣ ወደ ምዕራብ አፍሪካ ሲሄድ የተናገረውን ለመተግበር፣ በአሁኑ ወቅት የድርጊት መርሀ ግብር (Action Plan) ያዘጋጀ ሲሆን በአስከፊ ጦርነቶች የተመዘበሩ እቃዎች ከየሙዚየሞች ተመልሰው፣ ህዝቡም ይቅርታ ተጠይቆና ካሳም ተከፍሎ፣ ቅርሶቹ ወደ ትክክለኛ ቦታቸው መመለስ አለባቸው የሚል አቋም ወስዷል፡፡ አንድ የአውሮፓ መሪ ነው ይህን ያለው፡፡ እንደ እንግሊዝ ያሉ አገራት መሪዎችም የእሱን ፈለግ ተከትለው፣ ድርጊቱ ትክክለኛ እንዳልሆነ አምነው፣ በየደረጃው የሰው ንብረት የሚመልሱበትን መንገድ ቢፈጥሩ ነው የሚሻለው፡፡
በአውሮፓ ያሉ አገራት፤ የሰው አገር ቅርሶች ላለመመለስ ከሚያቀርቡት ምክንያቶች አንዱ፣ ቅርሶቹ ቢመለሱ እንኳን ሳይበላሹ መቀመጥ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ የለም የሚል ነው ይባላል …
በትክክል! እርግጥ ነው ብራናዎቹን ወደ አውሮፓ ከመውሰዳቸው በፊት ለብዙ ዘመናት በየአብያተ ክርስቲያናቱ ኖረዋል፡፡ ሆኖም እዚህ ቅርሶች ሲመለሱ በጥሩ ሁኔታ እንዲቀመጡ የሙዚየሞቹን ጥራት ማሻሻልና ሌሎች ዘመናዊ ሙዚየሞችን መገንባት የግድ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ እንግሊዞችን ካሳ መጠየቅ ይቻላል፡፡ እነሱስ ስንት ዓመት ሙሉ አይደለም እንዴ የተጠቀሙበት፤ ስለዚህ ካሳ መክፈል አለባቸው።  በአሁን ወቅት ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ይመስለኛል፡፡ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣንም ይመለከተዋል፡፡ ሌላው ቅርስ ጥበቃ ላይ ያለውን የሰው ኃይል ለማጎልበት የተለያዩ ስልጠናዎችን መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የተበላሹ ቅርሶችን በመጠገን፣ ስዕሎችን በማደስና በተለያየ መልኩ ስልጠናዎች በመስጠት ኃይልን ማጠናከር ይጠበቃል፡፡ ይህን ኃይል ለማጠናከር እንዲያግዙን እነሱን እንደ ካሣ መጠየቅ ይቻላል፡፡
“አፍሮ ሜት” የውጭ ዜጎች እየመጡ ቅርሶችን በርካሽ እየገዙ ከአገር እንዳያስወጡ ብዙ ቅርሶችን ገዝቶ ተከላክሏል፤ ዜጎቻችንም እንዳይሸጡ ግንዛቤ ላይ ለመስራት ሞክሯል፡፡ ይሄም መጠናከር አለበት፡፡ በሌላ በኩል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መቅረፅና ምስል መስራት አንዱ ዘዴ ነው፣ ማይክሮ ፊልም፣ ማይክሮ ፊሽ የሚባል ጥበብ አለ፡፡ አሁን ደግሞ ቴክኖሎጂው ምስል መስራት ይችላል፡፡ ለምሳሌ የእንግሊዝ ህግ ተቀይሮ ቅርሶቹ መመለስ ባይችሉ እንኳን እዚህ ህዝብ እንዲያያቸው በፎቶግራፍ፣ በኮፒና በምስል ተሰርው መምጣት ይችላሉ፡፡
በአፄ ቴዎድሮስ 150ኛ ዓመት ዝክረ በዓል ላይ በጎንደር ዩኒቪርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ግቢ ለህዝብ እንደቀረበው የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን አይነት ሥራ መስራት ይቻላል፡፡ እዛ የቀረበው አውደ ርዕይ የአፄ ቴዎድሮስን፣ የልዑል አለማየሁን፣ የእቴጌ ጥሩወርቅን እንዲሁም የጦር መሳሪያና አልባሳትን የሚያሳይ ነው፡፡ የሌሎችም በዚህ መልክ መቅረብና መታየት ይችላል፡፡ ይሄ ሁሉ ባለድርሻ አካላት ጠንክረው ሊሰሩበት የሚገባ የቤት ስራ ነው፡፡ ይሄ ሲሆን የማስመለሱን እንቅስቃሴ ሊገፋፋና ሊያበረታታ ይችላል፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ የወርቅ ዘውድ በቪክቶሪያ አልበርት ሙዚየም መኖሩን ብዙ ኢትዮጵያዊ ላያውቅ ይችላል፡፡ ሌሎቹንም እንዲሁ። ምስሉ ቢኖረንና ህዝቡ ቢያይ ቁጭትን ሊቀሰቅስ ይችላል፡፡ ስለዚህ በርካታ ስራዎች ይጠበቅብናል፡፡     

Read 1759 times