Print this page
Monday, 07 May 2018 09:04

የዓመታት ወዳጅነት በሴኮንዶች…!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(8 votes)

  “--ዘንድሮ ገና ‘ሀ’ ብለው ከመጀመራቸው የእምቧይ ካብ የሚሆኑትን ትዳሮች ብዛት ስናይ… “እውን እነኚህ ጥንዶች ከመጀመሪያውም ከልባቸው ይዋደዱ ነበር!” እንላለን፡፡ “እውን ይሄ ጥምረት ሲወጠን የአብርሃምና የሳራን ይሆናል ተብሎ ታሰቦ ነበር! እንደዛ ከታሰበስ ገና በጠዋቱ ምን ማእበል መታው!” እንላለን፡፡--”
    
    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እሱዬው ትክዝ ብሎ ተቀምጧል፡፡ ለነገሩ ዘንድሮ ከተከዘ ይልቅ ያልተከዘ ሰው ማግኘት ነው የሚቀለው፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን ብዙ ጊዜ የተረጋጋ ሁኔታ የሚታይበት ሰው ድንገት ሲተክዝ ከወትሮው የተለየ ነገር ገጥሞታል ማለት ነው፡፡ እናማ… ጓደኛው ምን እንደሆነ ይጠይቀዋል፡፡ እሱም ሁለት አብሮ አደግ ጓደኞቹ እርስ በእርስ ተጋጨትውበት፣ ማስታረቀ እንዳቃተው ይነግረዋል፡፡
“ምን ሆነው ተጣሉ? ይህን ያህል ከባድ ጉዳይ ነው እንዴ!”
“አይደለም፣ እኔንም እሱ ነው ግራ የገባኝ፡፡”
ነገሩ የሆነው…አብሮ አደግ የተባሉት እንደ ሁልጊዜያቸውም እየተቀላለዱ ነበር፡፡ ታዲያ አሁንም እንደ ሁልጊዜያቸው አንደኛው የሆነ ቀልድ ጣል ያደርጋል፡፡ የሚጠብቀው ሳቅ ግን አልመጣም፡፡ ሌላ ጊዜ ፈገግ በማታሰኘው እንኳን ፍርፍር ይል የነበረው ጓደኛው ግን ከመሳቅ ይልቅ ፊቱ ይለዋወጣል፤ግንባሩን ይከሰክስበታል፡፡ ያኛውም ግራ ይገባውና “ምን ሆነሀል?” ይለዋል፡፡ የአብሮ አደጉን ግንባር መከስከስ እሱ ከተናገረው ቀልድ ጋር የሚያያዝበት ምንም ምክንያት አልነበረውም፡፡
“በአንተ ቤት ብልጥ መሆንህ ነው! በቀልድ አስመስለህ እኔን መስደበህ ነው!” ይለዋል፡፡
ለካስ ቀልዱን ጠምዝዞ፣ ጠምዝዞ ወደ ራሱ አምጥቶታል…ቀደም ሲል የሌለው ባህሪይ፡፡ እናም… ቀልዱ የተነገረው እንደ ሌላው ጊዜ ለመሳቅ፣ ለመጫወት መሆኑ ቀረና ‘ከጀርባው የሆነ ነገር ያዘለ’ ሆነና አረፈው፡፡
ይህኛው ጓደኛው የፈለገውን ያህል ሊያስረዳው ቢሞክር፣ ቢማጸነው፣ ቢለምነው በእጄ አላለውም። እናማ…ነገሩን ሰምቶ ሊያስታርቅ የሞከረው ተካዡ፣ ግራ የገባው ለዚሁ ነበር፡፡
እንዴት ነው ስሜታችን እንዲህ ስስ የሆነው? እንዴት ነው ትናንት እግራችንን ሰቅለን ለደቂቃዎች እንስቅበት የነበረው ማንንም፣ ምንንም የማይነካ ቀልድ፤ ዛሬ እንደ ‘ኬሚካል መሳሪያ ጥቃት’ አይነት የሆነብን! እንዴት ነው የአስርት ዓመታት ወዳጅነት፣ በአስር ሴከንድ ቀልድ የሚፈራርሰው! እናማ… ለሆድ ለመባባስ ቅርብ፣ በጣም ቅርብ ሆነናል፡፡ የሚኳረፈው፣ የሚጣላው፣ “መቃብሬ ላይ እንዳትቆም የሚባባለው የልብ ጓደኛና ዘመድ አዝማድ ብዛቱ የምርም አስገራሚ ነው፡፡ ችግሩ ደግሞ አብዛኛው ሰው እውነተኛውን የመጋጫ ምክንያት አለመናገሩ ነው፡፡ አድበስብሶት ያልፋል…አብዛኛው ምክንያት “ጉድ፣ እንዲህም አይነት ነገር አለ!” የሚያሰኝ ሳይሆን “አሁን ለዚህ ብሎ ሰው ይለያያል!” የሚያሰኝ ነውና፡፡
“እወደዋለሁ እንጂ ይወደኛል አትበል፣” የሚሏት ነገር አለች፡፡ ‘አንዳንድ’ (ቃሏ የ‘ኮፒራይት’ ጥያቄ ካላስነሳች…) የጥበብ ሰዎች፤ “ህዝቡ በጣም ነው የሚወደኝ፣” የሚሉት ምናልባት ይቺን ተረት የነገራቸው ሰው ስለሌለ ይሆናል፡፡ “ህዝብ ስንል እናንተ፣ እናንተን ቆጥረን አይደለም፣” ካላሉን በስተቀር ማለት ነው!
ዘንድሮ ገና ‘ሀ’ ብለው ከመጀመራቸው የእምቧይ ካብ የሚሆኑትን ትዳሮች ብዛት ስናይ… “እውን እነኚህ ጥንዶች ከመጀመሪያውም ከልባቸው ይዋደዱ ነበር!” እንላለን፡፡ “እውን ይሄ ጥምረት ሲወጠን የአብርሃምና የሳራን ይሆናል ተብሎ ታሰቦ ነበር! እንደዛ ከታሰበስ ገና በጠዋቱ ምን ማእበል መታው!” እንላለን፡፡
“ስሚ እከሌና እከሊት ተፋቱ እኮ!”
“እከሌና እከሊት ማለት…”
“ደግሞ ሰርጋቸውን ስልቅጥ አድርገሽ በልተሽ፣ መንፈቅ ሳይሞላሽ ረሳኋቸው ልትዪ ነው!”
“አፈር በበላሁ፣ ምን ሆኑ?”
“እኔ ምን አውቄ፣ ምን ዘንድሮ እንደሁ ሰርግ ሲጠሩ በምስጢር የማይታደስ የስድስት ወር ኮንትራት የተፈራረሙ ነው  የሚመስለው፡፡”
ጥንዶችን ማስታረቅ አስቸጋሪ ሆኗል ነው የሚባለው፡፡ በነገራችን ላይ…ተደጋጋሚ የፍቺ ብዛት በአስደንጋጭ ሁኔታ ስለማሻቀቡ ይነገራል። ሁልጊዜም እንደምንለው …የማህበራዊ ጥናት እና መሰል የሚመለከታቸው ባለሙያዎቻችን ለምንድነው ምንጥር አድርግው ከስረ መሰረቱ ምክንያቶቹን አጥንተው፣ መፍትሄውን የማይነግሩን! የምር ግን መቼ ነው… “የኢትዮጵያ ምሁራን ባጠኑት ጥናት መሰረት…” እየተባልን፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች  የምንነሳው! በዚህ ስማቸው የሚነሱ የአገር ልጆች ቢኖሩ እንኳን አብዛኛውን ጊዜ ውጪ ያሉ፣ በርካታ ዓመታት በሌላ ህብረተሰብ ውስጥ የኖሩ፣ ሲልም ፓስፖርት የለወጡ ናቸው፡፡ ምንም ቢሆን የደም ጉዳይ ነውና ስማቸው ሲነሳ ደስ ይለናል፡፡ የአገር ውስጥ የምርምር ባለሙያዎችን ያብዛልን፡፡
በነገራችን ላይ ‘እንደሚባለው’፤ የብዙ ትዳሮች መፍረስ ምክንያት በእንትን አለመጣጣም ነው፡፡ አኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ‘አለመጣጣም’ የሚለው እንዴት ነው የሚተረጎመው! አሀ ግራ ያጋባላ… “ማን ቀድሞ እጅ ሰጠ’ ነገር ነው! ‘ኢላማው’ን በእኩል ሰከንድ የመምታት ነገር ነው!  (ቂ…ቂ...ቂ…) የምር ግን ‘እሱ ነገር’ ዋና ምክንያት ነው ይባላል፡፡
እሺ ይሁን…ግን አኮ አብዛኞቹ በፊት ይተዋወቁ የለም እንዴ! ማራቶኑ ላይ ማን ስንተኛው ደቂቃ ላይ ‘ውሀ’ እንደሚያስፈልገው…ማን አቋርጦ እንደሚወጣ ምናምን ይተዋወቁ የለም እንዴ!
እና እንዴት ነው እንዲህ አይነት ምክንያቶች ትዳር በተመሰረተ ሁለትና ሦስት ዓመት ሳይሆን የሚፎርሹት! አንዳንዴ ‘ቻርጅ’ ሲደረግ መቶ ደፍኖ፣ ሁለትና ሦስት ጥሪ ብቻ ተደርጎበት በአርባ አምስተኛው ደቂቃ ዜሮ እንደሚሆን ‘ፎርጅድ’ ባትሪ ይመስላል፡፡ ከትዳር በፊት ‘ኦሪጂናል’ የነበረው በኋላ እንዴት ‘ፎርጅድ’ ይሆናል!
ሀሳብ አለን…ሰማንያ ምናምኑ ላይ የሆኑ አንቀጾች ይካተቱ፡፡ “ትዳር በተመሰረተ በመጀመሪያው አስር ዓመት የማንኛውም ወገን ጉልበት ከ1.5 በመቶ በላይ ከቀነሰ፣ ያኛው ወገን የ‘ይታይልኝ’ ጥያቄ ሊያቀርብ ይችላል፣” ምናምን ይባልልን፡፡
ደግሞ ተሞክሮ ያላቸው ሰዎችም በሚዲያ ይቅረቡልን፡፡
“እህታችን፤ ከተጋባችሁ ስንት ጊዜያችሁ ነው?”
“አንድ ዓመት ከ…አራት፣ አይደለም… ከአምስት ወር፡፡”
“ከዚያ በፊት ለስንት ጊዜ ትተዋወቁ ነበር?”
“አምስት ዓመት ያህል አብረን ቆይተናል፡፡”
“ታዲያ ይሄን ያህል የምትተዋወቁ ከሆነ፣ እንዲህ በፍጥነት ለፍቺ ያደረሳችሁ ምክንያት ምንድነው…ትዳራችሁ መሀል ሰዎች ገቡባችሁ እንዴ?”
“ሰው እንኳን አልገባም…ግን፣ እሱ ነው፣ ማለቴ…”
«እኮ ንገሪና…ዋናው ነገር እኮ ከእናንተ ልምድ ሌሎች ትምህርት እንዲቀስሙ ነው…እሱ ነው ስትይ…ምን ማለት ነው፡፡»
“ለፍቺ ምክንያቱ እሱ ነው፡፡”
“ማለት... ይጠጣል፣ ወይስ በትዳሩ ላይ መማገጥ ጀመረ?”
“እንደሱ ሳይሆን…በቃ በየቀኑ ከስራ ሲመጣ ደከመኝ ብሎ እየተጋደመ፣ ጠዋት ነው የሚነሳው…የሆነ ነገር ከጀመርን ደግሞ ወዲያው ቁና ቁና ይተነፍሳል…”
“ልታብራሪው ትችያለሽ?”
“ሌላ የምለው የለኝም… ሚስቱ ነኝ እንጂ ነርሱ ነኝ እንዴ!”
የምር ግን ከቃለ መጠይቅ አቅራቢው፣ ለተመልካቾቹ የሚያስተላልፈውን መልእክት ብንሰማ አሪፍ ነበር፡፡ አስቸጋሪ ነዋ!
“እንግዲህ ባሎች እንደሰማችሁት፤ ትዳራችሁን ለማሰንበት ቁና፣ ቁና ከመተንፈስ በፊት ጂን ቤት ማሳደድ ትታችሁ ወደ ጂም ሂዱ፡፡” አሪፍ አይደል!
“ታዲያ ችግር ቢፈጠር ተመካከሮ ለመፍታት ትሞክራላችሁ እንጂ ምን ለፍቺ የሚያስቸኩል ጉዳይ አለ?”
“ይህ ምን ችኮላ ነው! ስንት ወር እንደታገስኳት እኔ ነኝ የማውቀው…”
“አሁንም እንግዳችን ፍርጥ አድርገህ እኮ ምክንያቱን አልነገርከንም…”
«ምን መሰለህ --- በቃ ከተጋባን ከወር ገዳማ ጀምሮ ሚስትነቷን ትታዋለች..እሷ ካልመሰላት ምንም ነገር የለም..»
“ስትል…”
“ስልማ… ባሏ አይደለሁ እንዴ! እሷ የትኛውን ወፍጮ ስትፈጭ ነው በየቀኑ ደክሞኛል የምትለው!”
“ወይ ባለሙያ ዘንድ ብትሄዱ…”
“ልንገርህ አይደል… በገዛ ሚስቴ የባልነቴን ወግ ለማግኘት፣ ምንም ባለሙያ የማማክርበት ምክንያት የለም፡፡ ወደ መጨረሻ እኮ ጭራሽ ‘በምትፈልግ ጊዜ አስቀድመህ ማመልከቻ ጻፍልኝ፣’ ልትለኝ ምንም አልቀራትም!”
የምር ግን…ይሄ እያጥለቀለቀን ያለውን በሆነ፣ ባልሆነው የቤተሰብ መፍረስ ወረርሽኝ የሚያጠፋ ዘዴና ብልሀት ይፍጠርልንማ!
የአሰርት ዓመታት ወዳጅነቶች በሰኮንዶች የሚፈርስበትን ‘ቁጣ’ የሆነ አውሎ ነፋስ ጠራርጎ ይውሰድልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4241 times