Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Sunday, 06 May 2012 14:04

“እንደገና ስኳር እንደገና”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ልጅ እያለሁ ከማስታውሰው እና ከማውቀው ልጀምር፡፡ እቤታችን የቀበሌያች ቁጥር የተፃፈበት የቀበሌ የሸማቾች ካርድ ነበረን፡፡ በዚሁ ካርድም፣ በየወሩ ከቀበሌ በቤተሰaባችን ቁጥር ልክ በኪሎም ሆነ በሊትር ከሚሰፈረው አንድ፣ አንድ እየለካ ወር ጠብቆ፣ አሰልፎ መንግስት የቀበሌው ነዋሪነታችንን ድርጎ ይሰጠን ነበር፡፡ እኔን ደስ የሚለኝ ግን ቀበሌ እናቴ ወይ ደግሞ እህቴ ይዘውኝ ሲሄዱ ሰልፍ እስኪደርስ ድረስ ከእድሜ እኩዮች ጋር የምጫወተው ጨዋታ ነው፡፡ ኳስ እንጫወታለን፣ ድብብቆሽ አባሮሽ፣ የቁም እርግጫ፤  ክረምት ሲመጣ ደግሞ ኳስ ጨዋታውን በብይ እንቀይር እና መጫወት ነው፡፡ አ. . .ቤ. . . ት. . .!!! ደስ ሲል፡፡ የማይጠገብ የልጅነት ጨዋታዬን፤ ምነው ሰልፉ ባይደርስ እያልኩ እጫውት ነበር፡፡ ከጨዋታዬ በተጨማሪም ወር መድረሱን እንድናፍቅ የሚያደርገኝ ደግሞ የቀበሌው ህብረት ሱቅ ሻጭ ያስለመደችን ጉርሻ ነበር፡፡ ሰልፈኛውን እየገረመመች አልፋ ወደ መሸጫ ሱቅ ትገባና ስራ ከመጀመርዋ በፊት ወይ ገንዘብ ተቀባይዋ ሂሳብ ተቀብላ  ሸማች ወደ እሷ እስከሚመጣ እኛን ታሰልፍ እና በርጥበት የጠጠረውን ስኳር ትሰጠን ነበር፡፡ እኛም ለእሷ ለየት ያለ ፍቅር ነበረን፡፡ ቤተሰቦቻችን ግን አይወዷትም ነበር፡፡ ሚዛን ትሰርቃለች፣ ታዳላለች ይላሉ፤ እኛ ግን እንወዳት ነበር፡፡ የቀበሌው ጣጣ አልቆ የተሰጠንን ስኳርም ሆነ ጨው፤ ዘይትም ሆነ ሳሙና አንዱ ካንዱ እንዳይቀላቀል በአንሶላ ጨርቅ ወይ ደግሞ በከረጢት እንቆጣጥር እና በሳጠራ ዘንቢላችን ከተን ወደ ቤት - ከእናቴ ወይ ከእህቴ ጋር፡፡

ታዲያ ይህ ከቀበሌ የሚመጣ ስኳር እና ዘይት ወር ሳይደርስ ሲያልቅ ሰፈር ውስጥ ካሉ የችርቻሮ ሱቆች እንገዛለን፡፡ የምላከውም ታዲያ እኔ የቤቱ ትንሽ ልጅ ነኝ፡፡ ተጠርቼ የዘይት ቡትሌ እና ሳንቲሟ እየተሰጠችኝ፣ ሰፈራችን ያለው ባለ ኪዮስክስ ስም እየተነገረኝ፣ ቶሎ ገዝተህ ና ስትመለስ የማድረግልህን አታውቀውም እባላለሁ፡፡ ምን እንደሚደረግልኝ ግን በደንብ አውቀዋለሁ፤ እናፍቀዋለሁ፡፡ ግን ሁልግዜም አታውቀውም እየተባልኩ እላካለሁ፡፡ ሳንቲሜን እና የዘይት መግዣ ቡትልዬን ይዤ ወደ ተነገረኝ ሱቅ ብንንንንንንን- በሩጫ፡፡ ከቤትም ልላክ ለጎረቤት ወደዛች ኪዮስክ ሁልግዜ በሰብበ አስባቡ እሄዳለሁ፤ ከቤት ስጦታዬ በተጨማሪ ባለሱቁ ያስለመደኝ የኮሾ ከረሜላ ጉርሻ ነበረኝ፡፡ የተላኩትን ቆጣጥሬ፣ ከረሜላዬን በኪሴ ይዤ በሩጫ ወደ ቤት እመላሳለሁ፡፡ እቤትም፤ እናቴ ከወፍራም ምርቃት ጋር ቤት ያለውን አሹቅም ሆነ ቆሎ ወይም ዳቦ ትሰጠኛለች፡፡ የተሰጠኝን በኪሴ ይዤ ወደ ጨዋታ፡፡ ወደ ጨዋታ ከመሄዴ በፊት ግን ከግቢያችን ውስጥ ቆም ብዬ በአጥር ቀዳዳ አጮልቄ ከሰፈራችን ልጆች እነማን እንዳሉ አያለሁ፡፡ የቢጥም ጨዋታ የተዋዋሉኝ ልጆች ካሉ ቀድሜ ስማቸውን “. . . ባይጥም፣ . . . .ባይጥም” እላቸዋለሁ፡፡ ቀድመው ቢጥም ካሉኝ ግን  አካፍላቸዋለሁ፡፡ ያላሉኝን ግን  እንቁልጭልጭ  እያልኩ ከፊታቸው እበላለሁ፡፡ ያቁለጨለጩኝም ካሉ በተራዬ አቁለጨልጫቸዋለሁ፡፡ እንዲያው ነገሩን እንጂ አንማረርም፡፡ ትንሽ ካቁለጨለጭኩዋቸው በኋላ ግን ለእነሱም እሰጣቸዋለሁ፤ እየተጫወትን አብረን እንበላለን፡፡ አንጨካከንም፤ የበላይነትን ለማስጠበቅ ያህል ግን ትንሽ ጎርደድ ጎርደድ እያልን የልጅነት ጉረራ እንጎርራለን፡፡ ከዛም ወደ ጨዋታችን እንመለሳለን፡፡ ይሄ የልጅነቴ ነው፡፡

ድምጤም ጎርንኖ፣ ፊቴ ጠጉር አብቅሎ እና ሰውነቴም ጎልምሶ ለህይወት ወግ ደረስኩና ስራ ስይዝ  የሆነውን ደግሞ ልንገራችሁ፡፡ ዘይት ከአስር እስከ አስራ ሁለት ተነስታ እጥፍጥፍ ብላ በሊትር ከሃያ አራት እስከ አርባ ስምንት ብር ደርሳለች፡፡ ከዚህ ዋጋ በላይ ገበያ ውስጥ ስላለው የዘይት ዋጋ እኔንና መሰሎቼን አይመለከተንም፡፡ ባለጉዳዩ ይጨነቅበት፡፡ ኦሆይ፣ እሱ ስለምን ይጨነቃል? “ላለው በሰማይ መንገድ አለው” አይደል የሚባለው? ለእኛ ግን የሃያ አራትዋ ገበያ ላይ ከተገኘች እሰየው ነው፡፡ የባለ ሃያ አራትዋ ብር ግን የማትገኝባቸው ግዜያት ይበዛል፡፡ ድንግት ስውር ትላለች፡፡ ከዛማ እንደ መስቀል ወፍ . . . ያው አሁንማ ለምደነዋል፡፡ ድሮ ልጅ እያለሁ፣ ወር ተጠብቆ ከቀበሌ የህብረት ሱቆች ትገኝ የነበረችው ዘይት አሁን የጀሪካን ዳና እየተከተሉ ከችርቻሮ ሱቆች ወይ ዘይት ሲመቻት ወይ ነጋዴያኑ ሲመቻቸው ነው የምናገኛት፤ ተናፋቂዋን ዘይት፡፡

የችርቻሮ ሱቆች የመሰረታዊ የምግብ ፍጆታ ሸቀጦች ላይ የተተመነላቸውን የመሸጫ ጣሪያ ዋጋዎቻቸውን በሚታይ ቦታ እንዲለጥፉ በተደረገው መሰረት፤ ከየሱቆቻቸው መስኮት እና በሮቻቸው ላይ ለጥፈዋል፡፡ ስኳር 14.50 ዘይት ባለ ሶስት ሊትር 71 ብር ከምናምን ሳንቲም፣ ዱቄት፣ የዱቄት ወተት፣ . . . በዚህ ሰሞን ግን ዋጋቸው እንጂ አይነቶቹ የሉም፡፡ ከተገኙም በስንት ድካም ነው፡፡ ዘይት ከሌለች የለችም፤ ስኳር ግን ከተገኘችም ከአንድ ኪሎ በላይ መግዛት አይቻልም፡፡ ሻጩም በጄ አይል ከአንድ ኪሎ በላይ፡፡ “ለምን ብትሉት?” ምላሹ “ክልክል ነው፡፡” ነው መልሱ፡፡ ፍትሃዊ የስኳር ስርጭት እንዲኖር ታስቦ የተደረገ ይመስላል፡፡ ይሁን መልካም ነው፡፡ ግን አንዳንዴ ስኳርም የበላት ጅብ  አልጮህ ይላል፡፡ ታዲያ ይህን ግዜ

እኔ አልናገረው እኔ አልተነፍሰው

ስንት ነገር አለ ውስጤ ‘ሚላወሰው፣

እንዳለው አዝማሪው፡፡ ከቤት ስንት ነገር አለ፡፡ ወተት የሚፈልጉ ጨቅላ ሕፃናት ይኖራሉ፣ ስንት ጣፋጭ የለመዱ ልጆች ይኖራሉ፡፡ ኧረ ሚስቶችም አይጠፉ፤ ያኔ ህፃናት ወላጆቻቸው ላይ፣ ወላጆች ነጋዴያን ላይ፣ ነጋድያን መንግስት ላይ ጣታቸውን ይቀስራሉ፡፡ መንግስትስ ምኑ ሞኝ፤ መልሶ ጣቱን ስግብግብ ነጋድያን ላይ ይቀስራል፡፡ ተቀሳስሮ ኑሮ፡፡ ስኳር ግን የለም፡፡

መቀሳሰር ሲጀመርም፤ ቤታችን ያለው ቴሌቭዥን መጋዘን ሙሉ ድርድር ስኳር ከጀርባ እያሳየን አንዱን ተመራጭ ሹም ከፊት አስቀድሞ፣ . . . የስራ ድርሻቸውን እና ኃላፊነታቸውን አስከትሎ በምሽት ዜና እወጃው፤ ሃገሪቱ ውስጥ ምንም አይነት የስኳር እጥረት አለመኖሩን አስታወቁ ይለናል፡፡ እሺ ሲነጋስ? ሲነጋማ ስኳር ላይኖር ይችላል ወይም ደግሞ ስኳር የለም፡፡

የስኳርን መጥፋት ተከትሎ ህዝብ ይጮሃል፡፡ የፈረደበት ጋዜጠኛ የህዝብን ብሶት ያሰማል፡፡ የችርቻሮ ሱቆችን ከኋላው ያደርግና አንዱን የሱቅ ባለቤት ወይ ሸማች ከፊት አስቀድሞ የስኳር እጥረቱ አለመቀረፉን ይዘግባል፡፡ ስኳር በገበያ ውስጥ የለም፡፡ የሸማቾችን እና የችርቻሮ ሱቅ ባለቤቶችን በዋቢነት ያቀርባል፡፡ ስኳር የለም፡፡ እንደገና ሌላ ዘገባ ይሰራል፤ ይኸው ጋዜጠኛ፡፡ በቀደም እለት ያሳየንን ተመራጭ ሹም ወይም ደግሞ ምክትላቸውን ዛሬም ከቴሌቭዥናችን መስኮት ብቅ ያደርግና፤ የቀረቡት ሰውየም፣ ምንም አይነት የስኳር የምርት እጥረት በሃገሪቱ እንደሌለ እና በስግብግብ ነጋዴዎች ምክንያት የአቅርቦት እና የስርጭት ችግር እንደተከሰተ እና በቀጣይ ጥቂት ቀናት ስኳር በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች በበቂ ሁኔታ እንደሚሰራጭ ይነግሩናል፡፡ ደስ ይለናል፡፡ አያይዘውም ይቀጥላሉ፣ መንግስት ችግሩን ለመቅረፍም የቁጥጥር ስርዓት አዘጋጅቶ ችግሩን የፈጠሩት ነጋዴዎችም የሚቀጡበትን መንገድ ተግባራዊ ስላደረገ፣ ህብረተሰቡ ከመንግስት አካላት ጋር በመተባበር ጥቆማ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አቅርበው የዜና ዘገባው ያበቃል፡፡ ኑሮአችን ግን ይቀጥላል፡፡ ለነገሩ በዚህ ሁኔታ የተማረረው ህብረተሰብም ስንት ጥቆማ አቅርቦ ጥቂት የማይባሉ ሱቆችን እንዳሻሸገ ይታወሳል፡፡ ችግሩ ግን ነጋድያን በቅጣት የሚማሩ አይነት አይደሉም፡፡

እሰይ ሰበር ዜና! የስኳር ፋብሪካዎችን ግንባታ በየዜና ዘገባው እንሰማለን፡፡ የስኳር ጠኔያችንን የሚያስታግሱ ፋብሪካዎች ለመገንባት መንግስት በሰፊው ገባበት፤ ብቻውንም እንደማይሆንለት ሲረዳም ፍላጎት እና አቅም ላላቸው ባላሃብቶች መስኩን ክፍት አደረገ፡፡ ፋብሪካዎቹ ግንባታቸው አልቆ ወደ ምርት ሲገቡ፣ እኛም እዚያ ዘመን ስንደርስ “የለም፣ ስኳር የለም” እንላለን፡፡ እስከዚያው ግን የልማት አሳላጭ ጋዜጠኞቻችን በየዘገባዎቻቸው አሁን አሁን በሚያስብል ወኔ፣ ስሜታዊ ሆነው የፕሮጀክቶቹን የግንባታ ሂደት እና ሲጠናቀቁም የሚትረፈረፈውን  የስኳር ምርትን በምናብ ያስቅሙናል፡፡ ይህም ተስፋ ነው፡፡

ዛሬ ግን፤ “ስኳር፣ ስኳር” የሚለውን ዘፈን ያለ ዜማ እያንጎራጎርን ነው፡፡ አንድ ቀን በሰፈራችን የሚገኙትን የችርቻሮ ሱቆች በሙሉ አዳርሼ ስኳር የለም፡፡ አንዱ ወደ አንዱ እየጠቆሙኝ እኔም ተስፋ ሳልቆርጥ ስዞር ከአንድ ሩህሩህ  ነጋዴ ሱቅ ውስጥ የማዳበሪያ ርጋፊ ስኳር አገኘሁ፡፡(የነጋዴ ሩህሩህ እምምምም!) ግን ሩህሩህ ያስባለኝን ነገር ልንገራችሁ፡፡ ሩብ ኪሎ መዝኖ ሰጠኝ፡፡ ጨምርልኝ ብዬ ደለልኩት አልሆነልኝም፣ ለመንኩት አልሆነልኝም፣ ተቅለስልሼም ተለማምጬም ላግባባው ሞከርኩ፤ እሱ ግን አሻፈረኝ አለ፡፡ ያለችውን ለሁሉም ላዳርሳት በቃህ አለኝ፡፡ ሩህሩህ አይደል? ለኔ ይበቃኛል ሩብ ኪሎ ስኳሬን ይዤ “ቤቴ ጌጤ”ን እየዘፈንኩ ወደ ቤቴ፡፡ በቁጠባ ስኳሬን ተጠቀምኳት፤ አጣጣምኳት፡፡ ስጨርሳት “እንደገና፣ ስኳር እንደገና”ን እያንጎራጎርኩ፣ ስኳር ፍለጋ ወጣሁ፡፡ ዛሬም ተመስገን ነው! ስኳር የለም፡፡ አማርሬ የት ልደርስ?  ስኳር ባይኖርም ግን “ለ. . . ወረዳ ነዋሪዎች በሙሉ፣ በወረዳችን ምንም አይነት የስኳር እጥረት የሌለ መሆኑን ተገንዝባችሁ ስኳር የለም የሚሏችሁን የወረዳውን ነጋዴዎች ለወረዳው ንግድ እና ኢንዱስትሪ በሚከተሉት ስልክ ቁጥሮች መጠቆም የምትችሉ መሆኑን እንገልፃለን፡፡” (የጠፋው ስኳር አፈላላጊ ኮሚቴ) እኔ ያልፃፍኳቸው ስልክ ቁጥሮቹ ከስር አሉ፡፡ በቅንፍ ያለችውን እኔ ማስታወቂያውን ለለጠፉት የሰጠኋቸው ስያሜ ነው፡፡ ታዲያ ተመስገን አይደለም እንዴ! ቢያንስ ቅሬታ ሰሚ አቤት የምንልበት ተገኘ፡፡ እኔ የካላንደር ተንቀሳቃሽ! እንዴት ልደውል? ስልኬ የምትሞላበት ቀን ገና ነው፡፡ ምስጋና ለቴሌ (call me back) “እባክህ ደውልልኝን” ለጀመረው! እና እባክህ ደውልልኝ አልኩ በተለጠፈው ቁጥር፤ ግን መልስ የለም፡፡ ሳንቲም ሞልቼ ደወልኩ ስልኩ አይነሳም፡፡ ሞከርኩ ስልኩ አይነሳም፡፡ ቅዳሜ ስለሆነ ይሆን? ልብ በሉልኝ! የተለጠፉት ስልክ ቁጥሮች ግን የተንቀሳቃሽ (የሞባይል) ስልክ ቁጥሮች ናቸው፡፡ በማግስቱም በሰንበቱ ይሁን በመዝናናት ምክንያት ስልኪቱ መልስ አልነበራትም፡፡  ምናልባትም ሞባይሊቱ የቢሮ ሳትሆን አትቀርም፡፡ በሰንበት አትነሳም!!

ሰኞ መጣ፡፡ በጠዋቱም የዞረ ድምር እና ድካም ይሁን እንጃ … በተደጋጋሚ ስደውልባት ጠዋት ላይ መልስ አልነበራትም፡፡ ቴሌ በቅርቡ አስቀርፆ መልስ እንድትሰጥ ያዘጋጃት ማሽን “ይቅርታ፣ የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም፤ እባክዎ ትንሽ ቆይተው ይደውሉ፡፡” የሚል ድምፅ በአማርኛና በእንግሊዝኛ በተደጋጋሚ ሲያስተናግደኝ ቆየ፡፡ ወደ ረፋዱ ግድም ግን ስልኩ ተነሳ፡፡ “ሀሎ” “ሀሎ” ተባባልን፡፡

“ሀሎ፣ እባክህ ባለ ሱቆች እኛ ሰፈር ስኳር የለም እያሉኝ ነው” አልኩት፡፡ “የት አካባቢ?” አለኝ?፡፡ ሰፈሬን ነገርኩት፡፡ “እንዴት?” አለኝ፡፡ “አልቋል አሉኝ፡፡”

“ታዲያማ አትጨርስ አይባል፤ መጥቶ እንዲወስድ ንገረው፡፡ ስኳር የለም ካላለህ ምንም አይደለም እስኪወስድ ነው፡፡ ‘የለም’ ማለት ነው የማይቻለው” አለኝ “እሺ” አልኩና ሌላ ጥያቄ አስከተልኩ “ከአንድ ኪሎ በላይ አልሰጥ ብሎኛል ምን ይሻለኛል?” አልኩ፡፡ “ማነው ያለህ?” አለኝ “ባለሱቁ” መለስኩ “እንዴት?” “እኔ ምን አውቃለሁ?” ከአንድ ኪሎ በላይ እንዳንሸጥ ታዘናል አለኝ” አልኩ ከጠያቂነት ወደ ተጠያቂነት ዞርኩ፡፡ “አገናኘኝ አለኝ” በሰአቱ እሱቁ አካባቢ ስላልነበርኩ ባለሱቁን ላገናኘው እንደማልችል ነገርኩት፡፡ “በል ሱቅ አካባቢ ስትሄድ እንድታገናኘኝ አለኝ” እሺ ብዬ ስልኬን ዘጋሁ፤ ከቆይታ በኋላ ሱቅ ሄድኩ፡፡ አሁን የምሄደው ስኳር ልገዛ አይደለም፤ ለዚህች ፅሁፍ ፍጆታ የማውላትን መረጃ ፍለጋ ነው፡፡

“ባለ ሱቅ፣ ስኳር አለ?” “አለ” አለኝ

“አምስት ኪሎ ስጠኝ” አልኩት፡፡ እንደማይሰጠኝ ልቦናዬ ያውቀዋል፤ ግን ጠየቅሁት ለማረጋገጥ፡፡

“እኔ የምሰጥህ አንድ ኪሎ ብቻ ነው፡፡ ሌላውን ከሌላ ሱቅ ዞረህ ልቀም” አለኝ

“ለምን?” “የተሰጠን ትዕዛዝ ነው፡፡ እኛ የለም ማለት ስለማንችል ብቻ ነው፡፡ ከአንድ ኪሎ በላይ ግን አልሸጥልህም” አለኝ ኮስተር ብሎ፡፡

“ማነው የከለከለው አልኩት?”

ኮስተር እንዳለ፣”ቀበሌዎች ከልክለዋል፡፡ ለማዳረስ አንድ አንድ ኪሎ ብቻ ነው የምንሸጠው” አለኝ፡፡ የተለጠፈውን የስልክ ቁጥር እያሳየሁት “የለም ማለት እንጂ፤ ሁሉም ሰው በሚፈልገው መጠን መግዛት እንደሚችል ክልከላ እንደሌለው ነገርኩት፡፡ ደውዬ እንዳረጋገጥኩ ነገርኩት”

“ማነው ያለው አለኝ?” ደግሜ ስልኩን እየጠቆምኩ “ቀበሌዎች” አልኩት፡፡

“እኔ በስልክ አላምንም አለኝ፡፡” ታዲያ ይህን ሰው ደውዬ ባገናኘው፣ ሁለቱን ከማነታረክ ውጭ ምንም ፋይዳ አይኖረውም ብዬ ለስልኬም ሳንቲም ሳስቼ፤ እኔ መረጃውን እንጂ የነሱ ንትርክ ምን ሊረባኝ ብዬ ተውኩት፡፡ የቁጥጥር ስርዓቱን ለዘረጋችሁ ጥቆማዬን በድጋሚ በዚህ በኩል እነሆ፡፡

ስኳር ጥርዥ ብርዥ፡፡ ስኳር ወጣ ገባ፤ ከገበያ ፡፡ ይመጣል እንቃመሳለን ያልቃል፡፡ ደግመን እስኪመጣ ጠብቀን እንቃመሳለን ፡፡ ሩህሩህ ነጋዴዎች በእኩል በእኩል እንደ አመጣጣችን እና እንደ ድርሻችን እያፈሱ አንድ አንድ ኪሎ ይሰጡናል፡፡ ይህን ያህል ከላስን እኛም ይበቃናል፡፡

 

 

Read 3138 times Last modified on Sunday, 06 May 2012 14:09