Monday, 07 May 2018 08:56

“አሁን እዚችም ሆድ ውስጥ እህል አለ?” አለች፤ በቆሎ ጤፍን አይታ

Written by 
Rate this item
(12 votes)

 በአንድ አገር በጀግንነት የተደነቀ አንድ ተወዳጅ ሰው ነበር፡፡ በመንደሩ ያሉት ሰዎች ሁሉ ስለ አንበሳነቱ ሲያወሩ አድረው፣ ሲያወሩ ቢውሉ፤ አይሰለቻቸውም፤ አይደክማቸውም፡፡
አንድ ቀን ሽፍቶች በመንደሩ ዙሪያ ለወረራ እየተዘጋጁ ነው የሚል መረጃ መጣ፡፡ አገሬው ተረበሸ፡፡ የአገር ሽማግሌዎች ተሰበሰቡና ምን እናድርግ ተባባሉ፡-
አንደኛው - “በየቤታችን ያለንን ጦርም ይሁን ገጀራ እናሰባስብና በክፍል በክፍል ሆነን እንግጠማቸው” አሉ።
ሁለተኛው - “የለም እኛ ያንን እስክናደርግ ጊዜ አይሰጡንም፡፡ ስለዚህ ፈጥነን የጎበዝ አለቆች አንድ ሶስት መርጠን፣ አካባቢያቸውን እናጥቃ” አሉ፡፡
ሦስተኛው፡- “የለም እንደዚያ እንዳናደርግ ስልት ይጎድለናል፡፡ ስለዚህ ዋና የጎበዝ አለቃችን አድርገን ጀግናችንን እንምረጥና ሄደን እንንገረው፡፡ እሱ በሚሰጠን ትዕዛዝ እንንቀሳቀስ” አሉ፡፡
በሦስተኛው የአገር ሽማግሌ ሃሳብ፣ ሁሉም ተስማሙ እና ወደ ጀግናው ቤት ሄዱ፡፡
ጀግናው - “እንዴት አመሻችሁ? ዛሬ ምን እግር ጣላችሁ?” ሲል ጠየቀ፡፡
የሽማግሌዎቹ ተወካይ፤
“ጀግናችን ሆይ!
እንደምታውቀው ወይም እንደሰማኸው፤ ወራሪዎች ወደ መንደራችን እየገሰገሱ ነው፡፡ እኛ ደግሞ በቅጡ አልተዘጋጀንም፡፡ ፈጥኖ ጋሻ መከታ ይሆነናል ብለን የመረጥነው ሰው አንተን ነው፡፡ እሺ ካልከን በመረጥከው ዘዴ፣ ይሄን ይሄን አድርጉ በለን፡፡ ያዘዝከንን እንፈፅማለን” አሉ፡፡
ጀግናው - “ይሄ ቀላል ነገር ነው፡፡ እኔ ከናንተ ቃል አልወጣም፡፡ ዛሬውኑ ዝግጅት እጀምራለሁ፡፡ እናንተ የሽፍቶቹን መረጃ እያሰባሰባችሁ ትልኩልኛላችሁ”
ሽማግሌዎቹ በአንድ ድምፅ፤
“አምላክ ውለታህን ይክፈልህ፡፡ ፈጣሪ ያንተን ዓይነት ጀግና አያሳጣን! አጣዳፊ መረጃዎችን እያደራጀን፣ መልዕክተኛ እንልክብሃለን” ብለው አመስግነው ወጡ፡፡
የሽፍቶቹ መንደሪቱን መክበብ ወሬ፣ እየገነነ መጣ፡፡ ሽማግሌዎቹ ፍርሃት፣ ሽብርና ጭንቀት ከሰዓት ሰዓት እየወጠራቸው መጣ፡፡ የመንደሩ ሰው በየደቂቃው ‹ኧረ አንድ ነገር ይደረግ› ይላቸዋል፡፡ ውጥረት በውጥረት ሆነ መንደሩ፡፡
ሽማግሌዎቹ በየሰዓቱ፤
“ምነው ዝም አልክ?”
“ምነው ባንተ ተማምነን ጉድ አደረከን?”
“ኧረ እየገቡ ነው ይባላል?”
…እያሉ አጣዳፊ መልዕክቶችን ያዥጎደጉዱለታል፡፡
ጀግናው የሰበሰባቸውን መሳሪያዎች ይወለውላል፡፡ እየፈታ ይገጥማል፡፡ ዝናሩን በጥይት ይሞላል፡፡ ጠመንጃዎች በመልክ በመልክ ይኮለኩላል፡፡ ገምባሌና የጦር ልብስ ያዘጋጃል፡፡
ሽማግሌዎቹ ትዕግስታቸው አልቆ ሲሮጡ መጡ፡፡
“ህዝቡ እኛን ወጥሮ ሊገለን ነው፡፡ የመጨረሻውን ቃል ንገረንና ይሄን ትዕዛዝ ይዘን እንሂድ፡፡ ሽፍታውኮ ደጃፋችን ላይ እያፏጨ ነው?”
ጀግናው የመለሰው አንድ ነገር ብቻ ነው፤
“ጌቶቼ፣ ሞቼ ልጠብቀው እንዴ?! ለመሆኑ እናንተስ እኔን ብቻ ነው የምትጠብቁት? ህዝቡን አታደራጁትም?” አለ፡፡
*   *   *
ያለ ዝግጅት፣ ያለ ድርጅት፣ ያለ ስነ አዕምሯዊ ብቃት፣ ያለ ልበ ሙሉነት፣ የትም አይደረስም፡፡ “አንድ አይነድ አንድ አይፈርድ” የሚለውን የአበው አነጋገር አንዘንጋ፡፡ ከሁሉም አስቀድሞ ማህበረሰባዊ የአዕምሮ ዝግጅት፣ የአዕምሮ ስክነት ያስፈልጋል፡፡ ቀጥሎ በየግል የየራስ ኃላፊነትን መወጣትን ይጠይቃል፡፡ “እኔስ ምን እያደረኩ ነው? ገደሉን ለመሙላት ምን ጠጠር ልጣል?! ምን ሀሳብ ላዋጣ?” ማለት እጅግ ተገቢ ነገር ነው፡፡ ከቶውንም “እናቴን ያገባ ሁሉም አባቴ ነው” ከሚል አመለካከት መላቀቅም ለመጠነ - ሰፊ አስተሳሰብ አጋዥ ግብዓት ነው፡፡
“ለጌሾው ወቀጣ ማንም ሰው አልመጣ
ለመጠጡ ጊዜ ከየጎሬው ወጣ”
የሚለውን ጥንታዊ አባባል እንደ ትዝብት መነፅር እናስቀምጠው፡፡ ህብረ - ሱታፌ ወሳኝ ነገር ነው። “አይሆኑም” ብለን ቃል የገባንላቸው ጉዳዮች የማይሆኑት ስለተመኘናቸው አይደለም፡፡ ከእነ ችግራቸው በተግባር ልናስተናግዳቸው ስንችል ነው፡፡ ቀጥሎ ሁነኛ ከባቤ አየር (conduvive atmosphere) ሲኖር ነው። ይሄን ከባቤ አየር እኛም ተጨምረን ልንፈጥረው ስንችል ነው፡፡ “ሁለት ያለው አንዱን ለሌለው ይስጥ” እያሉ ሲያስተምሩ ያረፈዱት ሰባኪ”፤ ሚስታቸው ለተቸገሩ ሰዎች ልብሳቸውን ሰጥታ ጠበቀቻቸው፡፡ ተናደው “ለምን አደረግሽ?” ቢሏት፣ “እርሶ ባስተማሩት መሰረት ነው”፤ አሁንም ሰባኪው ብስጭት ብለው፤ “እኔ ስጡ አልኩ እንጂ ልስጥ አልኩ እንዴ?!” አሉ፤ አሉ፡፡ የምንለውን ሁሉ እራሳችንን ውስጡ አድርገን እናስብ! ሁሉም የሀገር ጉዳይ፣ የሁላችንም ጉዳይ ነው፤ እንበል!
በለውጥ ጉዟችን ላይ ዕውቀትን እየገነባን እንሂድ፡፡ እያወቅን ስንሄድ እያወቅንበት እንራመዳለን፡፡ በአንድ እጅ አይጨበጨብም፤ ይሏል፡፡ እንደ አገሩ ችግር ጥልቀት ግን በሁለትም ላይቻል ይችላል፡፡ ስለዚህም መጠነ ሰፊ የመተባበርር የማስተባበር፣ የማደራጀትና የመደራጀት ሥነ - ልቦና ያስፈልጋል፡፡ “መነሳትና ሳይነሱ እንነሳ ማለት ይለያያሉ” ይላሉ ሩማኒያውያን፡፡ ተነሱ አትበል፤ ራስህ ተነስ፤ እንደማለት ነው፡፡
ድክመቶቻችን ብዙ መሆናቸውን ካወቅን፣ አያሌ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ስንወተውት፣ ስናሳስብ፣ ወይ የሚለን አጣን፣ የሰሚ ያለህ ስንል ወቅቶች አልፈዋል፡፡ የዓለም የጤና ቀን፣ የዓለም የመረጃ ቀን፣ የዓለም የፕሬስ ቀን … የዓለም፣ የዓለም …  የዓለም … ባልን ቁጥር ጉዳዩን በዓለም አኳያ እናወጋለን፤ ጉዳዬ ነው እንለዋለን፡፡ ጣጣው የሚመጣው የእኛስ ቀን አለን ወይ? ያልን ዕለት ነው፡፡ የእኛ ቀን እንዲኖር እኛ ልባዊ ህልውና ያስፈልገናል። ፍቅራችን፣ አንድነታችን፣ ዝማሬያችን፣ ሐዘናችን ቃናው መቀራረብ አለበት፡፡ ጥረታችን መቀራረብ አለበት፡፡ ተስፋችን መዛመድ አለበት!
ከሁሉም ይበልጥ አሳሳቢ ከሆኑት ችግሮቻችን አንዱና ጉልሁ መናናቃችን ነው፡፡ በንቀት ምክንያት ማንም ማንንም ለማዳመጥ ፈቃደኝነት አጥቷል፡፡ ፖለቲካዊ ንቀት፣ ኢኮኖሚያዊ ንቀት፣ ትምህርታዊ ንቀት ከቦናል፡፡ “እሱን አናውቀውም እንዴ?” ብለን ጀምረን … “የእሱን ነገር አታንሳብኝ” ጋ ለመድረስ አፍታ አይፈጅብንም፡፡ የሀገራችን ፖለቲካዊ አመለካከት እመርታ ያስፈልገዋል፡፡ አለበለዚያ “አሁን እዚችም ሆድ ውስጥ እህል አለ?” አለች በቆሎ፤ ጤፍን አይታ፤ ከሚለው ተረት አንወጣም!  

Read 6174 times