Print this page
Sunday, 06 May 2018 00:00

ከግንዛቤ ርቀናል? ሚዛን ጠልተናል? ሦስቱ የክፉ መዘዝ መለያ ምልክቶች - በስታዲዬሞች ውስጥ!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(2 votes)

• የስታዲዬም አምባጓሮ፣ ረብሻና ነውጥ፤ የሰው ሕይወትን ለጥፋት የሚዳርግ አደገኛ የወንጀል ጉዳይ ነው።
• “የስፖርታዊ ጨዋነት” ጉዳይ እየመሰለን፣… ወይም እያስመሰልን ስንናገርስ? ከግንዛቤ ርቀናል ማለት ነው።
• 3ቱ የክፉ መዘዝ ልዩ ምልክቶችን ተመልከቷቸው። የስታዲዬም አምባጓሮ፣ የፀብ ቅስቀሳ፣ ረብሻና ግርግሮች…
• እየተዛመቱ ነው - እየተሰራጩ! ከአንዱ ቦታ ሳይቀንስ ወደ ሌላ ይስፋፋሉ - እንደ ወረርሽኝ፣ እንደ ቫይረስ።
• በቀላሉ ይባባሳሉ፣ ይጦዛሉ። በእንካሰላንቲያ የማጦዝ ማባባሻ ዘዴ ሞልቷል - ከነ ሰበቡና ከነ ማመካኛው!
• በፍጥነት እየተደጋገሙ ነው። እየተዘወተሩ! “የክፋት ሙከራ ድግግሞሽ” ደግሞ፣ የከፋ መዘዝን አይቀሬ ያደርጋል።
    

   “የጨዋነት ጉድለት” አንድ ነገር ነው። የጨዋነት ጉድለት ተባብሶ፣ ሰው ላይ ጥቃት መፈፀም… ሌላ ነገር! ወንጀል ነው። የሁለቱን ነገሮች ልዩነት መሳት፣… አንዳንዴ የአላዋቂነት ውጤት ሊሆን ቢችልም፣ አሁን የሚታየው አዝማሚያ ግን፣ ከአላዋቂነትም የባሰ ነው። ለማወቅ አለመፈለግ፣ ማድበስበስና ማምታታት እየገነነ ነው። ይሄ፣… ከግንዛቤ ለመሸሽ አይንን የመጨፈን ዝንባሌ፣… በጭራሽ፣  የጤና አይደለም። መጨረሻውም አያምርም።
ብዙ ሺ ሰዎች በተሰባሰቡበት ቦታ ውስጥ፣… ለዚያውም ጠባብ መውጪያና መግቢያዎቹ ጭንቅንቅ የሚፈጥሩና ለመተላለፍ የማያመቹ መሆናቸውን ስታስቡት፣… ስታዲዬምን በመሳሰለ ቦታ ውስጥ፣ በግርግር ሳቢያ ሊከሰት የሚችለው ችግር፣ ክፉና ከባድ ነው። ግን ቀላል ከመሰለንስ?… ከዚያም አልፈን ለማቅለል ከሞከርንና ካስመሰልንስ?… ይሄ፣ ከሚዛን ጋር እንደተጣላን ይመሰክራል።
እንደ ስታዲዬም በመሳሰሰሉ ቦታዎች፣ በማንኛውም ሰበብ የሚለኮስ ረብሻ፣ ግርግርና ነውጥ፣ መዘዙ ቀላል አይደለም። ብዙ ሰው የሚሞተው፣ በግፊያ እየወደቀና እየተረገጠ፣ አንዱ በሌላው ላይ እየተደረበና እየተፋፈገ ነው። ይህንን ማመዛዘን ያቅተናል? ይህንን ለማመዛዘን፣… የሩቅ አገርና የሩቅ ዘመን ታሪክ ማጣቀስም ሆነ በሃሳብ መራቀቅ ያስፈልጋል? ብዙ ሰው በተሰበሰበበት ቦታ ውስጥ የሚለኮስ ረብሻና ግርግር፣ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ፣ መጠኑን ለመለካት፣…  “እንዲህ አይነት አስከፊ የጥፋት ክስተትኮ፣ በየአገሩና በየዘመኑ ሲፈጠር ታይቷል” የሚል ማስረጃ መሰብሰብም አይኖርብንም።
ከአምና እና ካቻምና ሳንርቅ፣ እዚሁ አገራችን ውስጥ፣ አስከፊና አሳዛኝ መዘዞችን አይተናል - የብዙ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። የብዙዎች አካል ጎድሏል።
በስታዲዬም አምባጓሮ፣ ረብሻና ነውጥስ? የቱን ያህል አደገኛና መዘዘኛ እንደሆነ፣ መጠኑንና ግዝፈቱን ለመለካት፣… ብዙ ሰው እስኪሞት ድረስ መጠበቅ አለብን?
እስከዚያው ድረስ፣ ስለ “ስፖርታዊ ጨዋነት” እያወራን ለመቀጠል ያምረናል? “የክለቦች አወቃቀር፣ የአሰልጣኞች አቀጣጠር፣ የቲፎዞዎች አደረጃጀትና አለባበስ”… እያልን፣ ስለ ቅሬታና አቤቱታም በየጣልቃው እየጨመርን በሰፊው መዘክዘክና መፈትፈት፣ ዋና ቁምነገር መሆኑ ነው። “የመሃል ባለፊሽካና የመስመር አራጋቢ፣… ብጫና ቀይ ካርድ፣… የጎል እና የፍፁም ቅጣት ስህተት፣… ድብደባና ቅሬታ”… እያልን መነታረክ እንደአዋቂነት ይቆጠርልናል ማለት ነው። “ለ5 ጨዋታ የማገድ” ወይም “3 ሺ ብር የመቅጣት ውሳኔ”፣ “የፌደሬሽን ሃላፊዎች አስቸኳይ ስብሰባና አጀንዳ”፣… ሌላም ሌላም እያከታተልን፣… “ስፖርታዊ ጨዋነት” ከሚል ዜማ ጋር ስንደጋግም መዋል ትርጉሙ ምንድነው?
ስፖርታዊ ጨዋነት? ይሄኮ፣ አንድ ተጫዋች በአጋጣሚ ተጎድቶ ቢወድቅ፣ የሌላኛው ቡድን ተጫዋች፣ ምንም ጥፋት ባይፈፅምም፣ ምንም ግዴታ ባይኖርበትም፣ ኳስን ወደ ውጭ አውጥቶ ሲተባበር፣ የጨዋነት ተግባር ሰራ ማለት እንችላለን - የተግባሩን ጠቃሚነትና ዋጋውን በመመዘን። የጨዋነት ተግባር የሚያዘወትርና ከሰብዕናው ጋር ያዋሃደ ተጫዋች ስናይም፣ “የጨዋነት ባህርይ ባለቤት” ብለን ማድነቅ እንችላለን - በግል ተግባሩና በባህርይው ልክ፣ ሳናዛንፍ፣ በንፅህና የሰውን ማንነት ስንዳኝ።
እንዲህ አይነቶቹ ነገሮች፣ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉዳዮች ናቸው። “አዋቂ ነው”፣ “ታታሪ ነው”፣ “ወረፋ ላይ ያተራው ጣልቃ የመግባት ፍላጎት የለውም”፣ “የሰውን የጥረት ስኬት ማየት ደስ ይለዋል”…  ሌላም ሌላም የጨዋነት ባህርይዎችን መዘርዘር እንችላለን። አዋቂና ታታሪ የመሆን የህግ ግዴታ የለም። ለሰውን የጥረት ስኬት በማየት መደሰትም፣ በአዋጅ የሚመጣ ግዴታ አይደለም። ጉዳዩ፣ የጨዋነት ጉዳይ ነው። አዋቂ ወይም ታታሪ ስለመሆን ስናወራ፣ ዋናው ቁምነገራችን፣ “የመልካም ስነምግባርና የጨዋነት ጉዳይ” ነው። “የጨዋነት ባህርይ ባለቤት” መሆንና አለመሆን ላይ ያተኮረ ጉዳይ ነውና።
ያለ ወረፋ ጥሶ የመግባት ምኞትስ? ጨዋነት የጎደለው ባህርይ ቢሆንም፣ ምኞት ብቻ ሆኖ እስከቀረ ድረስ በህግ አይከለከልም። ለምን? ጉዳዩ…  የጨዋነት ጉዳይ ነው። ከዚህ አልፎ፣… ወረፋ ጥሶ ለመግባት ሲሞክርና ሰውን ለመጉዳት ሲቃጣስ? ድብድብ ሲጀምርስ? ያኔ፣ የፖሊስና የፍርድቤት ጉዳይ ወደ መሆን ይሸጋገራል። “የጨዋነት ባህርይ ባለቤት መሆን ወይም የጨዋነት ባህርይ ጉድለት” በማለት ብቻ የምንዳኘው አይሆንም። “የጨዋነት ጉድለቱ”፣ “የወንጀል ጉዳይ” ሆኗልና።  
ወረፋ ለመጣስ መመኘት አንድ ነገር ነው። ወረፋ ለመጣስ፣ ሰውን መደብደብ ደግሞ ሌላ ነገር ነው። “ሁለቱ ነገሮች ይለያያሉ” ማለት፣… “ዋና ጉዳያቸው ይለያያል” ማለት ነው። ጨዋነት ከጎደለው ምኞት አልፎ፣ ጨዋነት ወደ ጎደለው ድብደባ ሲሻገር፣… ያኔ    ጉዳይ”… “ዋናው ቁምነገር”፣ ምን ይሆናል? የወንጀል ጉዳይ ይሆናል። አሁንም “ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት” ብቻ የምናወራ ከሆነ፣ ከግንዛሬ ርቀናል ማለት ነው - አላዋቂነት ልትሉት ትችላላችሁ። ግን ከዚህም ይብሳል። ከግንዛቤ ጋር ለመራራቅ መሸሸንም ያመለክታል። “አለማየት” ብቻ ሳይሆን፣ “ላለማየት አይንን መጨፈን” እንደማለት ነው።
ሰዎች፣… የስታዲዬሞች ችግር፣ “የስፖርታዊ ጨዋነት ጉዳይ” ከሚል ወሬ ያለፈ፣ የወንጀል ጉዳይ እንደሆነ እንገንዘብ።
ግን፣ ይህንን መገንዘብ ብቻ በቂ አይደለም። አዎ፣ ማገናዘብ ያስፈልጋል። ግን ማመዛንም ጭምር ያስፈልጋል - ልኩን፣ መጠኑን፣ ሚዛኑን ለማወቅ።

ሁሉም ድብደባ፣… ሁሉም ወንጀል እኩል አይደለም።
ባልታሰበ አጋጣሚ፣ ብዙ ሰው በሌለበት ሰፊ ቦታ ላይ የሚከሰት ድብደባ አንድ ነገር ነው። አንድ ወንጀል ነው። ግን፣ ተጨማሪ መዘዞችን ላያስከትል፣ ያለ ተጨማሪ ጉዳት ለማስቆምም ላይቸግር ይችላል።
ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ውስጥ የሚቆሰቆስ ፀብና የሚፈፀም ድብደባ ግን፣ ብዙ መዘዞችን ሊያስከትል ይችላል። ደግሞም፣ በስታዲዬሞች ውስጥ በተደጋጋሚ የምናያቸው የፀብ ተግባራትና አምባጓሮዎች፣ ተራ ፀብና አምባጓሮ አይደሉም።
የጅምላ ፀብ ለመፍጠር ጭምር የሚፈፀሙ የክፋት ቅስቀሳዎች እየተበራከቱ እንደመጡ መካድ፣ የክፋት ግብረአበር ከመሆን ወይም ራስን ከማሞኘት ያለፈ ትርጉም አይኖረውም።
ብዙ ሰዎችን በሰበብ አስባቡ በጠላትነት ለማቧደን፣… አንደ እንስሳ በመንጋ ወደ ፀብ ለማንጋጋት፣ በክለብ ቲፎዞነት ሰበብ፣ በብሄር ብሄረሰብ ዘረኝነትም ሆነ በሃይማኖት ተከታይነት እልፍ ሰዎችን በጭፍን የመንዳትና የመነዳት፣ በሰፈርና በመንደርም ቢሆን ለማቧደንና ለማናከስ የሚካሄዱ፣… እርቃናቸው የሚታዩ የክፋት ተግባራትና ባህርያት በዝተዋል።
የእነዚህ ክፋቶች ምንነት አለመገንዘብ፣ አላዋቂነት ወይም አይንን የመጋረድ ጭፍንነት ነው። ሰዎችን በጭፍን ለማቧደንና ለፀብ ለማነሳሳት መቀስቀስ፣… “የስፖርታዊ ጨዋነት” ጉዳይ ሳይሆን፣ የወንጀል ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ እንጀምር። ግን፣ ሚዛንም ያስፈልገናል - መዘዙ ከባድ እንደሆነ ማመዛዘንም አለብን።
ከላይ እንደጠቀስኩት፣… ከመውጪያና ከመግቢያ በር በስተቀር ሌላ መተላለፊያ አማራጭ በሌለበት ቦታ፣… ለዚያውም “በርካታ ሰዎች” ብቻ ሳይሆኑ፣ “ብዙ ሺ ሰዎች ባጥለቀለቁት ቦታ ውስጥ፣… እንኳንና የክፋት ቅስቀሳ ተጨምሮበት ይቅርና፣ ባልታሰቡ ድንገተኛ አጋጣሚዎች አማካኝነትም ብዙ ጉዳት ሊፈጠር ይችላል።
ሰዎችን እንደ እንስሳ በመንጋ ወደ ፀብ የማንጋጋት የክፋት ቅስቀሳ ሲጨመርበትማ፣… ይህም በብዛት ሲሆንማ፣ ያለማቋረጥ የሰበብና የማመካኛ መዓት እየተደረደረ እለት በእለት ሲዘወተርማ… አደጋውና መዘዙ በጣም በጣም ከባድ ነው። እስካሁንም የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ የአካል ጉዳት ደርሷል። የከፋና የባሰ ተጨማሪ ጉዳት፣ የእስካሁኑ ጉዳት ቢበቃና፣ በፍጥነት መፍትሄ ብናበጅለት ይሻላል።
አደጋውንና መዘዙን፣ በግልፅ ለመገንዘብና ለማመዛዘን፣ የብዙ ሰዎች ሕይወት እስኪጠፋ ድረስ መጠበቅ የለብንም። አለበለዚያኮ፣ መዘዙ አይቀሬ ነው - ዋና ዋና ምልክቶቹ ይመሰክራሉ።
ሦስቱ የክፉ መዘዝ መለያ ምልክቶችን ተመልከቷቸው።
የስታዲዬም አምባጓሮ፣ የፀብ ቅስቀሳ፣ ረብሻና ግርግሮችን ታዘብዋቸው።
እየተዛመቱ ነው - እየተሰራጩ! ከአንዱ ቦታ ሳይቀንስ ወደ ሌላ ይስፋፋሉ - እንደ ወረርሽኝ፣ እንደ ቫይረስ።
በቀላሉ ይባባሳሉ፣ ይጦዛሉ። በእንካሰላንቲያ የማጦዝ ማባባሻ ዘዴ ሞልቷል - ከነ ሰበቡና ከነ ማመካኛው!
በፍጥነት እየተደጋገሙ ነው። እየተዘወተሩ! “በተደጋጋሚ የክፋት ሙከራ አማካኝነት፣ የከፋ መዘዝ አይቀሬ ይሆናል።
እነዚህ ሦስት የክፉ መዘዝ መለያ ምልክቶችን ተመልከቷቸው። ምልክቶቹ የሉም፣ አይታዩኝም ካላችሁ፣… በቃ… መረጋጋት ትችላላችሁ። የክፉ መዘዝ ልዩ ምልክቶቹ፣… አፍጥጠው አግጥጠው የሚታዩ ከሆነ ግን፣… ለመፍትሄው መፍጠን አለባችሁ።

Read 2773 times