Sunday, 29 April 2018 00:00

ኢትዮጵያ በፕሬስ ነጻነት ከ180 አገራት 150ኛ ደረጃን ይዛለች ተባለ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

 በፕሬስ ነጻነት አፈና ሰ/ ኮርያና ኤርትራ አለማችንን ይመራሉ

    የአለማችን አገራትን የፕሬስ ነጻነት አጠቃላይ ሁኔታ በመገምገም በየአመቱ ደረጃ የሚሰጠው ሪፖርተርስ ዊዛውት ቦርደርስ፣ ከሰሞኑም የ2018 አመት የአገራትን ደረጃ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በፕሬስ ነጻነት ከ180 የአለማችን አገራት 150ኛ ደረጃን መያዟን አመልክቷል፡፡
በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት አፈናዎች ላይ ይህ ነው የሚባል መሻሻል አልታየም ያለው የተቋሙ ሪፖርት፣ በአገሪቱ ኢንተርኔትና ማህበራዊ ድረገጾች በተደጋጋሚ እንደሚዘጉ፣ የመገናኛ ብዙሃንን ለማፈን በጋዜጠኞች ላይ ጥቃቶች፣ ያለአግባብ እስርና ክስ  እንደሚፈጸም አመልክቷል፡፡
የጸረ-ሽብር ህጉ ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ ጋዜጠኞችን ለማጥቃት በጥቅም ላይ ሲውል እንደነበር፣ ከሽብር ጋር በተያያዘ የተከሰሱ ጋዜጠኞች የረጅም ጊዜ እስር እንደሚፈረድባቸውና ለተራዘመ ጊዜ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በእስር እንደሚቆዩም ገልጧል፡፡ የአገሪቱ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጠቀም የሰላ ሂስ በማቅረብ የሚታወቁ ጋዜጠኞችን ሊያስርና ህብረተሰቡ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃንን እንዳይከታተል ሊከለክል ይችላል ሲልም ተቋሙ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በዘንድሮው አለማቀፍ የፕሬስ ነጻነት ሁኔታ አመልካች ሪፖርት መሰረት፣ በፕሬስ ነጻነት አፈና ከአለማችን አገራት ሰሜን ኮርያ ቀዳሚነቱን ስትይዝ ኤርትራና ቱርኬሚኒስታን በሁለተኛና በሶስተኛነት እንደሚከተሉ አስታውቋል፡፡
የ2018 የፈረንጆች አመት አለማቀፍ የፕሬስ ነጻነት ሁኔታ አመልካች ሪፖርት እንደሚለው የፕሬስ ነጻነት በአለማቀፍ ደረጃ አምና ከነበረበት ዘንድሮ ወደከፋ ሁኔታ የገባ ሲሆን፣ በርካታ የአለማችን አገራት ጋዜጠኞችም የተለያዩ አፈናዎችና ጥቃቶች ደርሶባቸዋል፡፡
በአፍሪካ ለጋዜጠኞች ምቹና የተሸለ የፕሬስ ነጻነት ያለባት አገር ጋና ናት ያለው ተቋሙ፣ ጋና በአለማችን አገራት የፕሬስ ነጻነት ደረጃ 23ኛ ላይ መቀመጧንና፣ ናሚቢያ 26ኛ ደቡብ አፍሪካ 28 ደረጃን መያዛቸውን አመልክቷል፡፡
የስካንዲኒቪያን አገሮች ዘንድሮም መልካም የፕሬስ ነጻነት በማስፈን በቀዳሚነት የተቀመጡ ሲሆን፣ አምና በፕሬስ ነጻነት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር የነበረቺው የኖርዌይ ጋዜጠኞች ዘንድሮም ከተቀረው አለም አገራት በሙሉ በነጻነት እንዲሰሩ ተፈቀደላቸው ዕድለኞች ናቸው ተብሏል፡፡ ስዊድንና ኔዘርላንድስም በፕሬስ ነጻነት ከአለማችን አገራት ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
ተቋሙ በ180 የአለማችን አገራት የፕሬስ ሁኔታ ላይ የሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ ባለፈው ረቡዕ ይፋ ባደረገው መረጃ እንዳለው፣ ከአለማችን አገራት የፕሬስ ነጻነትን በከፍተኛ ሁኔታ ያሻሻለቺው ቀዳሚዋ አገር ጋምቢያ ስትሆን፣ የፕሬስ ነጻነት ሁኔታቸው ከአምናው በከፍተኛ ሁኔታ የከፋባቸው አገራት በአንጻሩ ማልታ፣ ሞሪታኒያ እና ቼክ ሪፐብሊክ ናቸው፡፡

Read 5206 times