Sunday, 29 April 2018 00:00

በሰዓሊተ ምሕረት ካቴድራል፤ ‘ደኅንነት ነኝ’ በሚል አጭበርብረዋል የተባሉትን ግለሰብ ፖሊስ እየመረመረ ነው

Written by 
Rate this item
(8 votes)

 ከሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ጋር አለኝ ያሉት ግንኙነት ትኩረት ስቧል
   ሥራ አስኪያጁ፣ ለሠራተኛ ቅጥር 100ሺሕ ብር ጉቦ መቀበላቸው ታወቀ

     በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል፣ ከሀብት ምዝበራና ብክነት እንዲሁም ከሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ጥሰት ጋራ በተያያዘ ማኅበረ ምእመናኑ በአስተዳደር ሓላፊዎች ላይ ያቀረቡትን አቤቱታ ለማጣራትና ወራት ያስቆጠረውን አስተዳደራዊ ችግር ለመፍታት፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መምሪያ ተልኬያለሁ ያሉ ግለሰብን ፖሊስ አስሮ እየመረመረ ነው፡፡
በካቴድራሉ የተፈጠረው ችግር ከአቅሙ በላይ እንደኾነ በመግለጽ ለመፍትሔው ትብብር እንዲደረግለት፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መምሪያ የፖሊቲካ ጉዳዮች ጽ/ቤት የጻፈውን ደብዳቤ በመያዝና በሕገ ወጥ መታወቂያ ተጠቅመው ራሳቸውን የመሥሪያ ቤቱ ባልደረባ በማስመሰል፣ የማጣራት ሒደቱን አስቀጥላለሁ በማለት የተንቀሳቀሱ ሲኾን፤ አኳኋናቸው በተጠራጠሩ የአጥቢያው ማኅበረ ምእመናን ዐቢይ ኮሚቴ አባላት ጥቆማ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡
ኃይለ ኢየሱስ ተፈራ የተባሉት እኚሁ ግለሰብ፣ መጋቢት 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ካቴድራሉ አምርተው ከአጥቢያው ማኅበረ ምእመናን ዐቢይ ኮሚቴ ጋራ በተገናኙበት ወቅት፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መምጣታቸውን ገልጸው እንደተዋወቋቸው የጠቀሱ ምንጮች፤ የካቴድራሉን አስተዳደራዊ ችግር የማጣራት ሒደት በእርሳቸው አማካይነት እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ፍላጎት እንደኾነና ለዚህም ደብዳቤ እንደደረሳቸው ለኮሚቴው ማስታወቃቸውን ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ በተደረገው ስብሰባ፣ ቀደም ሲል የተጀመረው የማጣራት ሒደት የተስተጓጎለበትን ምክንያት ኮሚቴው ያስረዳ ሲኾን፣ በምክክርና በሰላማዊ መንገድ በአስቸኳይ እንዲፈታ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፡፡ ለዚህም፣ አቤቱታ የቀረበባቸውና በሕዝብ የታገዱት የአስተዳደር ሓላፊዎች በአካል ተገኝተው ከማስመርመር የዘለለ ተግባር ማከናወን እንደማይችሉ እንዲሁም ሀገረ ስብከቱ በአዲስ መልክ ከሚመድባቸው አጣሪዎችና ‘ደኅንነት ነኝ’ ካሉት ግለሰብ በተጨማሪ፥ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤትና ፖሊስ መምሪያ፣ ከቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 07 አስተዳደር ጽ/ቤትና ስድስት የአጥቢያው ምእመናን ተወካዮች እንደሚሳተፉ የጋራ ስምምነት ተደርሶ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡
በበነጋው መጋቢት 20 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ የካቴድራሉ የአስተዳደር ሓላፊዎች ፈጽመውታል የተባለውን የሀብት ምዝበራና ብክነት እንዲሁም የሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ጥሰት የሚገልጹና ምእመናን በየመግቢያ በሮች ላይ የሰቀሏቸውን ባነሮች እንዲያነሡ ማድረግን በተመለከተ ግለሰቡ ባስያዙት አጀንዳ፣ ከዐቢይ ኮሚቴው ጋራ ተወያይተዋል፡፡ ባነሮቹ ተፈላጊውን መልእክት በማስተላለፋቸው በሚመለከተው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት እንዲነሡ መታዘዙን ግለሰቡ በቅድመ ኹኔታ መልክ ቢገልጹም፤ ባነሮቹ እንደተሰቀሉ እንዲቆዩ የተደረገው፣ ሀገረ ስብከቱ ማጣራት እንደሚጀምር ቃል ከገባ በኋላ ጥር 18 ቀን በፍ/ቤት የሁከት ይወገድልኝ ክሥ በመመሥረቱ እንደኾነ በኮሚቴው አባላት ተነግሯቸዋል፡፡ ከአንድ ሺሕ በላይ የካቴድራሉ ምእመናን የሀገረ ስብከቱን አካሔድ በመቃወም፣ የካቲት 2 ቀን ለቋሚ ሲኖዶስ አቤቱታ አቅርበው አምስት አባላት ያሉት አጣሪ ልኡክ ቢመደብም ሒደቱ በአስቸኳይ ተፈጻሚ ባለመኾኑ ወርዶ የተቀመጠው ባነር ተመልሶ መሰቀሉን አስረድተዋቸዋል፡፡
በዚሁ ዕለት በግለሰቡ ላይ የተመለከቱት ኹኔታ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መ/ቤት መምጣታቸውን እንዲጠራጠሩ እንዳደረጋቸው የተናገሩት የኮሚቴው ምንጮች፤ ካቴድራሉ ለሚገኝበት የቦሌ ክ/ከተማ አስተዳደር የጸጥታ አካል ስለጉዳዩ በመጠቆም፣“ደኅንነት ነኝ” የሚሉት አቶ ኃይለ ኢየሱስ ተፈራ በክትትል ውስጥ እንዲገቡ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ መጋቢት 21 ቀን፣ ግለሰቡ ባስያዙት ቀጠሮ መሠረት፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መ/ር ጎይትኦም ያይኑና ሁለት የአስተዳደር ጉባኤ አባላት ከዐቢይ ኮሚቴው ጋራ በጽ/ቤቱ ተገናኝተው ስለማጣራት ሒደቱ አፈጻጸም በተነጋገሩበትም ወቅት ክትትሉ ቀጥሎ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ የማጣራት ሒደቱን ለመጀመር ስምምነት በተደረሰበትና ግለሰቡ በካቴድራሉ ቅጽር በተገኙበት መጋቢት 25 ቀን፣ አስቀድሞ መረጃው ደርሷቸው ሲከታተሏቸው በቆዩ የፖሊስና የጸጥታ አካላት ያለምንም ውዝግብ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጋቸው ታውቋል፡፡
ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መ/ቤት ተልከው ስለመምጣታቸው የሚያረጋግጥ ትክክለኛ ማስረጃ ማቅረብ እንዳልቻሉና ደርሶኛል ካሉት የሀገረ ስብከቱ ደብዳቤ ጋር በተያያዘ ሥራ አስኪያጁን መ/ር ጎይትኦም ያይኑን የተመለከተም ምርመራ እየተካሔደባቸው መኾኑን ለማወቅ ተችሏል።
በአ/አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ መ/ር ጎይትኦም ያይኑ ቲተርና ፊርማ ወጪ በተደረገውና ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መምሪያ የፖሊቲካ ጉዳዮች ጽ/ቤት በተጻፈው የትብብር መጠየቂያ ደብዳቤ፣ ግለሰቡ በካቴድራሉ ተገኝተው ስለጉዳዩ አጭር ሪፖርት እንዲያቀርቡ የሚያዝ ምሪት ተሰጥቶበታል። የመሥሪያ ቤቱን ትብብር በደብዳቤ መጠየቃቸውን ለቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በጽሑፍ በሰጡት ምላሽ ያረጋገጡት ሥራ አስኪያጁ በበኩላቸው፤ የካቴድራሉን ሰላም ለመመለስ ከመጣር ውጪ፣ ግለሰቡን እንደማያውቋቸው፣ ደብዳቤውንና በአባሪነት የተያያዘውን 35 ገጽ ሰነድም ለግለሰቡ እንዳልሰጧቸው ገልጸዋል፡፡
ሀገረ ስብከቱን በበላይነት የሚመሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፤ ባለፈው ሳምንት ኃሙስ ከቀትር በኋላ፣ የካቴድራሉን ወቅታዊ ኹኔታ በተመለከተ በጽ/ቤታቸው ተቀብለው ላነጋገሯቸው የማኅበረ ምእመናኑ ዐቢይ ኮሚቴ አባላት፣ ሥራ አስኪያጁ እና “ደኅንነት ነኝ” ባዩ ግለሰብ አላቸው ስለሚባለው ግንኙነት ማንሣታቸው ተጠቅሷል፡፡“የሁለቱን ግንኙነት ነጥብ በነጥብ ዘርዝረን ለቅዱስነታቸው አስረድተናቸዋል፤” ብለዋል የኮሚቴው አባላት፡፡ ፓትርያርኩም፤ “ደኅንነት ነኝ የሚለው ግለሰብ አሳስቶት ነው ወይስ አምኖበት?” በማለት እንደጠየቋቸውና “ኾን ብለው ተማክረው እንዳደረጉትና ኹሉንም ነገር መ/ር ጎይትኦም እንደሚያውቅ፤ ጉዳዩም በሕግ እንደተያዘና እኛም ፍትሕ እንደምንሻ ገልጸንላቸዋል፤” ብለዋል፡፡
ሀገረ ስብከቱ የመሠረተባቸውን ክሥ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ውድቅ ቢያደርገውም፣ የጠየቀው ይግባኝ እንዲቋረጥ ትእዛዝ እንዲሰጡላቸውና ቋሚ ሲኖዶሱ የመደባቸው ልኡካን ማጣራቱን እንዲጀምሩ በአጽንኦት ያመለከቱት የዐቢይ ኮሚቴው አባላት፤ ሒደቱ በመዘግየቱ ከላይ ለተጠቀሱት ዐይነት ትንኮሳዎች እየዳረጋቸው መኾኑን ለፓትርያርኩ አስረድተዋል፡፡ የካቴድራሉ አስተዳደር ሓላፊዎች በሕዝቡ ተቃውሞ ከተባረሩበት ታኅሣሥ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ሰላሙ ተጠብቆ ዓመታዊና ወርኃዊ በዓላት መከበራቸውን፤ የውስጥ አገልግሎቱና ስብከተ ወንጌሉም ያለአንዳች እንከን እየተከናወነ እንደኾነም ነግረዋቸዋል፡፡ በሦስት ክብረ በዓላት በሙዳየ ምጽዋት የተሰበሰበው ገንዘብ፣ የሀገረ ስብከቱና የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነቱ ተወካዮች በተገኙበት የተቆጠረበትን ቃለ ጉባኤና የባንክ ሰነዱን አሳይተዋቸዋል፡፡
“የአስተዳደር ሓላፊዎቹ እያሉ በሁለት የባንክ ሒሳቦች የነበረውን የገንዘብ መጠንና ከእነርሱ በኋላ 1ነጥብ2 ሚሊዮን ብር የሁለት ወራት የካህናት ውዝፍ ደመወዝ ተከፍሎም ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ እንደሚገኝ በመጥቀስ ቤተ ክርስቲያናችንን እየጠበቅን እንዳለ አስረድተናቸዋል፤”ብለዋል የኮሚቴው አባላት፡፡
ኮሚቴው ባቀረበው የሥራ ክንውን መደሰታቸውን የገለጹት ፓትርያርኩ፣ “ቢሮዎቹን ባታሽጉ ኖሮ አትንከራተቱም ነበር፤ እግዚአብሔር በሚያውቀው እንዲጣራ እፈልጋለሁ፤ ለዚህም ወዲያው መርቼበት ነበር፤” ማለታቸውን የዐቢይ ኮሚቴው ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በሀገረ ስብከቱ የተመሠረተውን ክሥ በተመለከተም፣ ጉዳዩ በፍ/ቤት በመያዙ ውሳኔውን እየጠበቁ እንደኾነ ያስታወቁት አቡነ ማትያስ፤ “ለቤተ ክርስቲያን ሲባል ነው የተከሰሣችሁት፤ የፍ/ቤቱ ጉዳይ አይቆምም፤” እንዳሏቸው ተገልጿል፡፡ ከውሳኔው በፊት ተተኪ አስተዳዳሪ መመደብ የማይመልሱት ችግር ውስጥ እንደሚከታቸው ፓትርያርኩ ቢጠቁሙም፣ “ስላለው ነገር ልመካከርበትና እነግራችኋለሁ፤” በማለት የዐቢይ ኮሚቴውን አባላት በቡራኬ እንዳሰናበቷቸው ምንጮቹ አክለው ተናግረዋል፡፡
ደኅንነት ነኝ ባዩን ግለሰብ በቁጥጥር ሥር አውሎ በተለይ በደብዳቤው በተሰጠው ምሪት ላይ ያተኮረ የቴክኒክ ምርምራ እያካሔደ ያለው የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ፤ ተጠርጣሪውን ሁለት ጊዜ ፍ/ቤት አቅርቦ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ እንደጠየቀባቸውና ለሦስተኛ ጊዜም የፊታችን ሚያዝያ 25 ቀን ፍ/ቤት እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡ በተያያዘ ዜና፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የደብረ ገሊላ ቅዱስ ዐማኑኤል ካቴድራል የትሩፋት(ነፃ) አገልጋይ የኾኑ ዲያቆን፣ ወደ ቢሮ ሥራ ለመመደብ በሚል ለሥራ አስኪያጁ መ/ር ጎይትኦም ያይኑ 100ሺሕ ብር ጉቦ መስጠታቸውን፣ ከግለሰቡ የተገኘው ማስረጃ አጋለጠ፡፡ ፈቀደ ተስፍዬ የተባሉት አገልጋዩ፣ በአንድ የግል ባንክ በተከፈተ የሥራ አስኪያጁ የቁጠባ ሒሳብ፣ ባለፈው ዓመት ሐምሌ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ገንዘቡን እንዳስገቡ፣የገቢ ማዘዣ ሰነዱ(Cash Deposit Voucher) ያረጋግጣል፡፡
በአካውንቲንግ ሞያ በብድርና ቁጠባ ተቋም እንደሠሩና በካቴድራሉ ከ15 ዓመታት ያላነሰ በደጀ ጠኚነት በዲቁና እንዳገለገሉ የሚናገሩት ግለሰቡ፤ ምደባ የጠየቁበት የቢሮ ሥራ፣ ሒሳብ ሹምነት እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡ ኾኖም እጅ መንሻ የሰጡበትና በአንድ ከፍተኛ የካቴድራሉ ሓላፊ አማካይነት ለማስፈጸም የሞከሩትን ምደባ በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ባለማግኘታቸው፣ ገንዘባቸውን ባለፈው ማክሰኞ በሓላፊው አማካይነት ማስመለሳቸው ታውቋል፡፡
በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሠራተኞች ቅጥር የሚፈጸመው ጥያቄው በአድባራት ሲቀርብ፣ በሀገረ ስብከቱ እንደኾነና አሠራሩም የቅጥር ኮሚቴ በማዋቀርና ማስታወቂያ በማውጣት በውድድር እንደሚፈጸም፣ ባለፈው መጋቢት አጋማሽ ከአዲስ አድማስ ጋራ ቃለ ምልልስ ያደረጉት ሥራ አስኪያጁ መ/ር ጎይትኦም ያይኑ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ከአሠራሩ ውጭ የሠራተኛ ቅጥር “አልፎ አልፎ የሚፈጸመው” በአድባራቱ እንደኾነና ከአቤቱታ አቅራቢዎች ጋር አለመግባባት የሚፈጠርበት አንድ መንሥኤ እንደኾነም መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
ሥራ አስኪያጁ ይህን ይበሉ እንጅ፣ ከደብረ ገሊላ ቅዱስ ዐማኑኤል ካቴድራል ነፃ አገልጋይ ቅጥር ጋር በተያያዘ አስተያየት የሰጡ ምንጮች፤ “ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እስከ ሀገረ ስብከቱ ሹማምንት ድረስ በተለይ ለጽ/ቤት ሓላፊዎች ቅጥርና ዝውውር የተዘረጋውን የሙስና ሰንሰለትና የሚያካብቱትን ሕገ ወጥ ሀብት የሚያረጋግጥ ነው፤” ብለዋል፡፡ የማስረጃ ሰነዱ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መድረሱን ያመለከቱት ምንጮቹ፤ በሰነዱ ትክክለኛነትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማጣራቱ እንደተጠናቀቀ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ርምጃ ይወሰዳል ተብሎ ይጠበቃል፤ ብለዋል፡፡

Read 6733 times