Sunday, 29 April 2018 00:00

የተመድ የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ከፖለቲከኞችና አባ ገዳዎች ጋር ተወያይተዋል

Written by 
Rate this item
(2 votes)


             “ለመለወጥ የተዘጋጀ አዲስ አመራር ነው የገጠመኝ”

    የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛይድ አል ሁሴን፤ በኢትዮጵያ በነበራቸው የሦስት ቀናት ጉብኝት ከእስር ከተፈቱ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና ሲቪል ማህበራት አመራሮች እንዲሁም አባ ገዳዎች ጋር በአገሪቱ የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ መነጋገራቸው ታውቋል፡፡
ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ከእስር ከተፈቱ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ጋዜጠኞች፣ጦማሪያን፣የዋልድባ መነኮሳትና ከሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ጋር  ባደረጉት ውይይት፣ በእስር ቤቶች ውስጥ ስለሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ተነግሯቸዋል፡፡ በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበረው  ጋዜጠኛ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ እስክንድር ነጋ፤በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አሰቃቂ እንደሆኑ ኮሚሽነሩ መረዳታቸውን  ጠቁሟል፡፡ ኮሚሽነሩ በሀገሪቱ ስለሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ብቻ ሳይሆን  በቀጣይ እንዴት ጥሰቶቹን ማስቀረት ይቻላል በሚለውም ላይ ከተሳታፊዎች ጋር እንደመከሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሀገሪቱ የሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ከምንጫቸው ሊደርቁ የሚችሉት ጠ/ሚኒስትር ስለተቀየረ ወይም አዲስ ካቢኔ ስለተቋቋመ አሊያም ማዕከላዊ ስለተዘጋ ሳይሆን በአጠቃላይ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ሲረጋገጥ መሆኑን  መግባባት ላይ መደረሱን የውይይቱ ተሳታፊዎች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
“በተቃውሞ ላይ በመሳተፋቸውና መንግስት ላይ ከሰነዘሩት ትችት ጋር በተያያዘ ታስረው የነበሩ ጦማርያንን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ሌሎችም ከእስር መለቀቃቸውን እንደሚያደንቁ የገለጹት ዛይድ አል ሁሴን፤በዚህ ጉብኝታቸውም ከጥቂቶቹ ጋር በግል ለመነጋገር ዕድል ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡  
በኦሮሚያ ከክልሉ ባለሥልጣናትና አባ ገዳዎች ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸውን የገለጹት ከፍተኛ ኮሚሽነሩ፤ከክልሉ ባለሥልጣናትና አባ ገዳዎች ጋር የተደረገውን ይህን የመጀመሪያ ግንኙነት መንግስት በማመቻቸቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ አባ ገዳዎች በክልሉ ያልተመጣጠነ ሃይል በመጠቀም በዜጎች ላይ ግድያ የፈጸሙ ወገኖች ተጣርተው፣ ለህግ እንዲቀርቡና የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰብአዊ መብቶች እንዲከበር መጠየቃቸውንም የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፤በክልሉ ለረዥም ዘመን የዘለቀውን የሰብአዊ መብት ችግሮች ከአዲሱ አመራር ጋር በመሥራት እንፈታዋለን ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ  ገልጸውልኛል ብለዋል፡፡ ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በአገሪቱ የሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳይ ላይ ያደረጉት ውይይትም ውጤታማና ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል- ኮሚሽነር ዛይድ አል ሁሴን፡፡
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ቢሮም፣ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች  የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መመርመር እንደሚፈልግ ያስታወቁት ከፍተኛ ኮሚሽነሩ፤ይህም የሰብአዊ መብት አያያዝን የተሻለ ለመገምገም፣መንግስት የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋትና  ለሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነትን ለማስፈን በሚያደርጋቸው ጥረቶች ለማገዝ የሚያስችል ይሆናል፡፡” ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ኮሚሽነሩ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፣ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚአብሄር እንዲሁም ከጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጋር በሀገሪቱ የሰብአዊ መብቶች ይዞታ ላይ የመከሩ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ 17 አገሮችን የሚሸፍን ፅ/ቤቱን በአዲስ አበባ ለመክፈት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር  ስምምነት ተፈርሟል፡፡
የተመድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ዛይድ አል ሁሴን፣ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አጠናቅቀው  ለውጭ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፤”በኢትዮጵያ ለመለወጥ የተዘጋጀ አዲስ አመራር ነው የገጠመኝ” ብለዋል፡፡

Read 3306 times