Sunday, 29 April 2018 00:00

ስለ ዶ/ር ዐቢይ የህዝብ ፍቅር ትርጉም ፍለጋ

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(5 votes)


        “--ዶ/ር አቢይ በፓርቲያቸው ድጋፍ የመጡ ናቸው፡፡ ሆኖም ብዙዎቹ ንግግራቸው ለፓርቲያቸው ሳይሆን ለህዝቡ ቅርብ መሆን መፈለጋቸውን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ስርዓት የሚወዳደሩ ብዙ መሪዎች፤ በምርጫ ፉክክሩ ወቅት ይዘው የመጡትን ጠባብ የምርጫ አጀንዳ ከምርጫ በኋላ በመተው ሐገርን በሙሉ የሚያቅፍ አጀንዳ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፡፡ የእርሳቸው ሁኔታም እንዲህ ያለ ነገር አለው፡፡--”
 
    አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ከተሾሙ ሦስት ሣምንት ይሆናቸዋል፡፡ በእነዚህ ቀናት በርካታ ሥራዎችን የሰሩ በመሆኑ፤ በዚሁ ሥራቸው ብዙ ጊዜ የቆዩ ይመስላል። ግን ሦስት ሣምንታት ብቻ ነው፡፡ ዶ/ር አቢይ ወደ ሥልጣን የመጡት በተለየ ሁኔታ ነው። በድርጅታቸው ኢህአዴግ ሳይሆን በህዝብ ተመርጠው ወደ ሥልጣን የመጡ ይመስላል፡፡ የሐገራችን የመንግስት ስርዓትም ከፓርላሜንታዊ ወደ ፕሬዚደንታዊ የመንግስት ሥርዓት የተቀየረ ይመስላል። ትኩረቱ ከድርጅት ወጥቶ ወደ ግለሰብ የሄደበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ፓርቲ ሁለተኛ ነገር ሆኗል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታይ እውነታ ነው። በበርካታ የዓለም ሐገራት ፓርቲዎች በተለያየ ሁኔታ እየተዳከሙ፤ ትኩረቱ በግለሰብ ተመራጭ ላይ እየሆነ መምጣቱን  አይተናል፡፡ መራጮች ትኩረታቸውን ከፓርቲ አንስተው ወደ ግለሰብ ወስደዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በፕሬዚደንታዊ የምርጫ ስርዓት አስገራሚ አይደለም፡፡ ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ፓርላሜንታዊ የመንግስት ሥርዓት ባለበት ሐገር ትንሽ አስገራሚ ነው፡፡
ሆኖም ዶ/ር አቢይ ወደ ሥልጣን የመጡት በፓርቲ (ዎች) ድጋፍ መሆኑ ምንም የሚያጠራጥር አይደለም። ከብሔራዊ ድርጅታቸው ኦህዴድ ሙሉ ትብብር አግኝተው ለውድድር የቀረቡ ናቸው፡፡ የኢህአዴግ የምክር ቤት ጉባዔ ከመካሄዱ በፊት በብሔራዊ ድርጅታቸው የተካሄደው የመሸጋሸግ እርምጃን እናስታውሳለን፡፡ ዶ/ር አቢይ የኦህዴድ ፕሬዚደንት የሆኑት፤ የኢህአዴግ ምክር ቤት ጉባዔ ከመካሄዱ ትንሽ ቀደም ብሎ ነው፡፡ ከዚያም የግንባሩ ምክር ቤት አባላት መርጠው በተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸው ጸድቆላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑ በመሆናቸው ያለ ፓርቲያቸው ድጋፍ ጠ/ሚ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል አይኖርም፡፡ ሆኖም ይህ የተለመደው ሂደት ከወትሮው በተለየ አውድ የተከናወነ ነበር። ሂደቱ በሰፊ የህዝብ አስተያየት የታጀበ በመሆኑ የተለየ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በአጭሩ፤ በድርጅታቸው በኢህአዴግ በህግ የተመረጡ (de jure) ሲሆን፤ ህዝቡም በኩነት (de facto) መርጧቸዋል። ይህ አስተያየት ችግር ሊኖርበት ይችላል፡፡ ግን እንድታዩልኝ የፈለግኩትን አንድ ነገር ሊያሳይ ይችላል፡፡ 
ዶ/ር አቢይ የህዝብ አስተያየት ድጋፍ ነበራቸው። ሰፊ ወይስ ጠባብ የሚለው አስፈላጊ አይደለም፡፡ የህዝብ ድጋፍ ነበራቸው ማለቱ በቂ ነው፡፡ ይልቅስ ዶ/ር አቢይ ከሚሰሩበት ወይም ይበልጥ ከሚታወቁበት ክልል የተሻገረ የህዝብ ድጋፍ ያገኙት፤ ምን ለመሥራት እንዳሰቡ ተናግረው አይደለም፡፡ ይልቅስ ከዚያ በፊት ነው። ድጋፉም የዋዛ አልነበረም፡፡ እርሳቸው ጠ/ሚ ሆነው በተመረጡ ዕለት ሌሊቱን ግብዣ፣ ዳንስ እና ‹‹እንኳን ደስ ያለህ›› በርክቶ ነበር፡፡ ሁኔታው አስገራሚ ነበር፡፡ ድጋፉ የኢህአዴግን መልካም ነገር ለመስማት ከማይፈቅዱ ሰዎች ጭምር ነበር፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች በአንድ ጀንበር አስተያየታቸውን ለውጠው ስናይ ትንሽ ግር ሊለን ይገባል፡፡ ድጋፍ ብቻ አልነበረም፡፡ እነዚሁ ሰዎች የደስታ መልዕክት ሲለዋወጡም አይቻለሁ። በእርሳቸው መመረጥ የተደሰቱትና ደስታቸውንም በአደባባይ የገለፁት፤ ለጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ሲገቡ የተሰሙት የኢህአዴግ ተቃዋሚ የሆኑ ፓርቲዎች አባላት ጭምር ናቸው፡፡
አስገራሚ ነው፡፡ ኢህአዴግን ‹‹ጥቁር ወተት አምጣ›› ብለው ቢያስጨንቁት ደስ የሚላቸው ሰዎች ሁሉ፤ ህዝቡ በአንድ ጀምበር ለውጥ በመፈለግ እንዳያስጨንቃቸው መልዕክት ያስተላልፉ ነበር፡፡ ‹‹ችግሩ በአንድ ጀንበር ሊቃለል የሚችል አይደለም፡፡ ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል›› የሚል የትብብር መንፈስ አሳይተዋቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ በቃለ መሐላው ቀን በምክር ቤት ንግግር ካደረጉ በኋላ አይደለም፡፡ ይህ ቢሆን ንግግራቸው የፈጠረው ስሜት ነው ለማለት ይቻል ነበር፡፡ ግን እንዲያ አልነበረም፡፡ ከዚህ ሁሉ ቀድሞ ነው፡፡
በእውነት ለመናገር የኢህአዴግ ቀንደኛ ተቃዋሚዎች፤ ኢህአዴግን በጦርነት ለመፋለም የወሰኑ ቡድኖች አመራሮች፤ የዲያስፖራ አክቲቪስቶች፤ ወጣቶች፣ አዛውንቶች፣ ሴቶች፣ ፖለቲካ ባጠገባቸው ቢጠበስ የማይሸታቸው ሰዎች ሁሉ፤ በእርሳቸው መመረጥ ደስተኞች ሆነው አይቻለሁ፡፡ ተገርሚያለሁ። አንድ ሰው፤ ለኢህአዴግ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች እንዴት እኩል እዩኝታ (appeal) ይኖረዋል? ይህ ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ ግን ብዙዎች እንዲህ ዓይነት ነገር አይፈልጉም፡፡ በቃ እየተደሰቱ ነው፡፡
የሆነ ሆኖ ዶ/ር አቢይን መፍቀድ (መምረጥ - በስሜት)፤ ኢህአዴግን መምረጥ መሆኑን የሚያስብ ሰው አልገጠመኝም፡፡ ብዙዎች ዶ/ር አቢይን መምረጥ፤ ኢህአዴግን መምረጥ ሆኖም አልታያቸውም። ተቃዋሚዎች፤ በአዲስ ምርጫ አዲስ መንግስት ቢመጣ ሊፈጠር የሚችለውን ደስታ አጣጥመዋል፡፡ የኢህአዴግ ደጋፊዎችም የድርጅቱ ስልጣን በመረጋጋቱ ተደስተዋል። ሁለቱም በአንድ ሰው የተነሳ ተደስተዋል። ወለፌንድ ይሉሃል ይህ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሐቅ እንዴት ሊፈታ ይችላል?  እኔ በ‹‹The Tipping Point›› አንጻር ለማየት ሞከርኩ፡፡ ግን ‹‹The Tipping Point››ን ከማንሳቴ በፊት አንድ ሐሳብ ልጨምር፡፡
ዶ/ር አቢይ ጠ/ሚ ሆነው ከተሾሙ ወዲህ ባለው ሁኔታ አሁን አስተያየት መስጠት አልፈልግም፡፡ አስተያየቶቼ በተሟላ ግንዛቤ የተመሠረቱ እንዲሆን በመፈለግ ብቻ አይደለም። ለሐገራችንና ለህዝቧ የሚጠቅም ሥራቸውን በአዝማሚያ ጠቋሚ ፍንጮች ላይ ብቻ ተመስርቼ፤ የተፈጠረውን የፖለቲካ ካፒታል የሚጎዳ አስተያየት ከመስጠት መቆጠብ እፈልጋለሁ። በዙሪያዬ ያለውም የሰዎች አስተያየት ይህን የሚፈቅድ ነው፡፡ ሆኖም ዶ/ር አቢይ ባለፉት ጥቂት ቀናት ባከናወኗቸው ሥራዎች፤ የሐገሪቱን ችግር ለመፍታት ቁርጠኛ መሆናቸውን ማሳየት የቻሉ ይመስለኛል። ህዝብ የሚመስጥ ንግግር የማድረግ ችሎታ እንዳላቸውም አሳይተውናል፡፡ በቋንቋቸው የገጣሚ ስሜት ያላቸው መሆናቸውን አይቻለሁ። የሚሰሩትን የሚያውቁ መሪ መሆናቸውን ለመመስከር የሚያስችል በቂ አብነቶች ሰጥተውናል፡፡ ይህን ለሥራ ጉብኝት በመረጧቸው ክልሎችና በጉብኝታቸው ቅደም ተከተል ለመረዳት እንችላለን፡፡ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች ይነሱ ለነበሩ ጥያቄዎች ይሰጧቸው የነበሩ ምላሾችም የአመራር ዘዬአቸውን ይጠቁሙናል፡፡ ከጓዶቻቸው ለየት ባለ ዘዬና የቃላት ምርጫ ለመናገር መድፈራቸውም ስለ እርሳቸው የሚናገረው ነገር አለ፡፡ ይህም ቀላል ነገር አይደለም። በፖለቲካ የቃላት አጠቃቀም ተራ ነገር አይደለም፡፡ ርዕዮተ ዓለም እስከ መሆን ይደርሳል፡፡
ቅድም እንዳልኩት፤ ዶ/ር አቢይ በፓርቲያቸው ድጋፍ የመጡ ናቸው፡፡ ሆኖም ብዙዎቹ ንግግራቸው ለፓርቲያቸው ሳይሆን ለህዝቡ ቅርብ መሆን መፈለጋቸውን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ስርዓት የሚወዳደሩ ብዙ መሪዎች፤ በምርጫ ፉክክሩ ወቅት ይዘው የመጡትን ጠባብ የምርጫ አጀንዳ ከምርጫ በኋላ በመተው ሐገርን በሙሉ የሚያቅፍ አጀንዳ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። የእርሳቸው ሁኔታም እንዲህ ያለ ነገር አለው፡፡ በእስካሁኑ ሂደት የንግግራቸው ትኩረት ውጫዊ ግንኙነትን (ኤክስተርናል ሊንክ) የመፍጠር እንጂ ውስጣዊ ህብረትን (ኢንተርናል ሊንክ) ለመፍጠር ትኩረት የሰጡ አይመስልም፡፡ ሆኖም በእርስ በእርስ መጠራጠር ሲሰቃይ የቆየው ድርጅታቸው ውስጣዊ ህብረት እንደሚያስፈልገው ዘንግተውት አይመስለኝም፡፡ የቅደም ተከተል ጉዳይ ይሆናል፡፡ የስልጣናቸው መሠረት የሆነው የድርጅታቸው ህብረት አንደሚያሳስባቸው አልጠራጠርም፡፡
ለምሣሌ፤ ብዙዎቹ የአሜሪካ ፕሬዚንደንቶች ከምርጫ ውድድር ወቅትና ከተመረጡ በኋላ የተለያዩ ናቸው፡፡ በቅስቀሳ ወቅት ለታማኝ ደጋፊዎች ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ ከተመረጡ በኋላ ግን ሁሉን አካታች ይሆናሉ፡፡ ከአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ከዶናልድ ትራምፕ በቀር ሁሉም በምርጫ ካሸነፉ በኋላ በቻሉት መጠን የፖሊሲም ባይሆን የሞራል ክበባቸውን ያሰፋሉ። ትራምፕ ግን ዛሬም ድረስ በምርጫ ዘመቻቸው ለመራጮቻቸው ቃል የገቧቸውን ነገሮች ለማስፈጸም የሚሰሩና የአሜሪካን ህዝብ የሚከፋፍል አጀንዳ ውስጥ ተውጠው ቀርተዋል፡፡ በዚህም ሐገራቸውን እየጎዱ ነው፡፡
የዶ/ር አቢይ አካሄድ በደርጅታቸው ውሳኔ የሚገዛ መሆኑ የማይቀር ቢሆንም፤ የሞራል ክበባቸው (ሰርክል) እጅግ ሰፊ ነው፡፡ ለዲያስፖራ ጥሪ ሲያደርጉ በሰፊው ነው፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያቀርቡት ግብዣም እንደዛው ነው፡፡ ዶ/ር አቢይ ወደ ጠ/ሚ ኃላፊነት የመጡት መሪው ድርጅት ኢህአዴግና መንግሥት የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ በጀመሩት የጥልቅ ተሃድሶ ሂደት በመሆኑም፤ ከህዝቡ ጋር እየተገናኙ የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች የተሃድሶው ሐሳቦችና ውጤቶች መሆናቸውን መገመት ቀላል ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሐገሪቷን ህዝቦች አንድነት ለማጠናከር የሚረዱና በመንግሥት የመምራት ብቃት ላይ የህዝቡን መተማመን ለማጎልበት እየሰሩ ነው፡፡ ታዲያ አንዳንድ ሰዎች በዶ/ር አቢይ አማካኝነት ከኢህአዴግ ለመገላገል የሚችሉ እስኪመስለው ድረስ የሄዱት ለምን ነው? እነዚህ ሰዎች ኢህአዴግ የሾማቸውን ሰው እንዲህ የተቀበሉት እንዴት ነው? ይህን ጥያቄ ለመመለስ ነው፤ ወደ ‹‹The Tipping Point›› የሄድኩት፡፡
አሜሪካዊው የኒዮርክ ታይምስ ጋዜጠኛ ማልኮልም ግላድዌል  (MALCOLM GLADWELL) ‹‹The Tipping Point፡ How Little Things Can Make a Big Difference›› ሲል የጻፈው እና በ2000 ዓ.ም (እኤአ) የታተመ መጽሐፍ አለው፡፡ ይህ አሜሪካን ያነቃነቀ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ በሚሊየን ቅጂዎች የተሸጠ ነው፡፡ ለፀሐፊውም በመድረክ አርባ ሺህ ዶላር እየተከፈለው ለተሰበሰቡ ሰዎች ገለጻ የማድረግ ዕድል የፈጠረለት መጽሐፍ ነው፡፡ ፀሐፊው በህዝብ ዘንድ ያለ የአመለካከት ለውጥን ከወረርሽኝ ጋር አነጻጽሮ ይገልፀዋል፡፡
ግላድዌል፤ ሦስቱ የወረርሽኝ ህግጋት (The Three Rules of Epidemics) የሚለው ነገር አለ፡፡ የህግጋቱን አሰራር ለመግለጽ በሽታዎች እንዴት የወረርሽኝ መልክ እንደሚይዙ ያብራራል፡፡ በትይዩም ማህበራዊ ጉዳዮችን ያሳየናል፡፡ በሁለቱም አካባቢ (በተፈጥሮና በማህበራዊ) ያለው ነገር በተመሳሳይ ህግ እንደሚገዙ ሊያሳየን ይሞክራል፡፡ ደራሲው ማልኮልም ግላድዌል፣ በመጀመሪያ የሚያነሳው በ1990ዎቹ አጋማሽ በአሜሪካ ባልቲሞር በተባለ ከተማ የተከሰተውን የቂጥኝ በሽታ ወረርሽኝ ነው፡፡ ከ1995 እስከ 1996 ዓ.ም (እኤአ) ባለው የአንድ ዓመት ጊዜ፤ በቂጥኝ በሽታ ተይዘው የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር በ500 በመቶ ጨምሮ ታየ፡፡ የዚህን በሽታ ስርጭት የሚያሳየውን ግራፍ  ስትመለከቱ፤ ቀጥ ያለ መሥመር ይዞ ይጓዝና፣ በ1995 ዓ.ም እንደ ምሰሦ ቀጥ ያለ መስመር ይሆናል፡፡ የበሽታው ስርጭት በተጠቀሰው ዓመት በድንገት እና በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ይታያል፡፡ ይህ ሁኔታ ለምን ተከሰተ? ሦስት አካላት ሦስት የተለያየ ነገር ያነሳሉ፡፡
የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ መስሪያ ቤት ጥናት አደርጎ፤ የበሽታው መጨመር ‹‹ኮኬይን›› ከሚባለው አደንዛዥ ዕጽ ጋር የሚገናኝ መሆኑን ተናገረ፡፡ ኮኬይን ጥንቃቄ የጎደለው ወሲባዊ ግንኙነት እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ይህም እንደ ቂጥኝና ኤችአይቪ/ኤድስ ያሉ የአባለዘር በሽታዎች እንዲስፋፉ ምክንያት ይሆናል። ኮኬይን የሚፈልጉ ሰዎች ዕጽ ፍለጋ ወደ ድሆች መንደር ይሄዳሉ፡፡ ወሲባዊ ግንኙነት ያደርጋሉ፡፡ ከዚያም በሽታውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ያዛምታሉ። ለወትሮው የማይገናኙ ሰዎች በዕጹ ምክንያት ይገናኛሉ። ይህ የማህበራዊ ግንኙነትም በሁለት የተራራቁ የመኖሪያ መንደሮች ያሉ ሰዎችን ያገናኛል። የቂጥኝ በሽታ ወደ ወረርሽኝ ለመቀየር የሚፈልገው ትንሽ ገፊ ነገር ነው፡፡ ያቺን ትንሽ ግፊት የኮኬይን ግብይት ፈጠረለት፡፡ እናም ወረርሽኙ ተስፋፋ አለ - የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ መስሪያ ቤት፡፡
ባልቲሞር በሚገኘው የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ባልደረባና የአባለዘር በሽታዎች ኤክስፐርት የሆነው ጆን ዜኒልማን (John Zenilman) ደግሞ ለችግሩ ምክንያት የሚለው ሌላ ነገር ነው፡፡ በእርሱ ጥናት፤ የወረርሽኙ መንስዔ፤ በከተማው ያለው የድሆች መንደር የጤና አገልግሎት መዳከሙ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ‹‹ከ1990-91 ባለው አንድ ዓመት በከተማዋ የአባላዘር በሽታዎች ክሊኒኮች የተመዘገበው የበሽተኞች ቁጥር 36 ሺህ ነበር›› የሚለው ዜኒልማን፤ ‹‹ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት የከተማው አስተዳደር እጅ አጥሮት የሚመድበውን በጀት በመቀነሱ፤ 17 የነበረው የሐኪሞች ቁጥር ወደ 10 ወረደ፡፡ ወደ ክሊኒክ የሚመጡት ሰዎች ቁጥር ቀነሰ፡፡ መድኀኒትም ይቸግራቸው ጀመረ፡፡ በዚህ ሁኔታ ከድንበሩ ሳያልፍ ተገድቦ የቆየው በሽታ ድንገት ወረርሽኝ ለመሆን ከሚችልበት ነጥብ ደረሰ፡፡ ከዚያም ከደቀቀው የከተማው ክፍል የተነሳው በሽታ እንደ ሰው የከተማውን አውራ ጎዳና ተከትሎ ወደ ከተማው እምብርት ዘልቆ ገባ፡፡ ምክንያቱም፤ ቀደም ሲል በአንድ ሣምንት ወደ ክሊኒክ ይመጡ የነበሩት ሰዎች አሁን በቶሎ አይመጡም፡፡ ስለዚህ በሽታውን ይዘው አራት ሣምንት ድረስ ሰው እየበከሉ ይቆያሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ወረርሽኙ ተከሰት የሚል ትንታኔ አቀረበ፡፡
ሌላ ሦስተኛ ትንታኔ አለ፡፡ በአሜሪካ ከሚገኙ እውቅ ኤፒደሞሎጂስቶች አንዱ የሆነው ጆን ፖቴራት (John Potterat) የተባለ ሰው ደግሞ የቂጥኝ ወረርኝ በባልቲሞር ሊከሰት የቻለው፤ የበሽታው ምሽግ በነበረው የከተማው ክፍል የነበሩት የመንግስት መኖሪያ ቤቶች (በ1960ዎቹ አሮጌ ህንጻዎች) በ1990ዎቹ አጋማሽ በመፍረሳቸውና በዚያ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ወደ ሌላ አካባቢ ሄደው በመስፈራቸው መሆኑን አመለከተ።። የወንጀልና የበሽታ ማህደር በሆኑት የምሥራቅና የምዕራብ ምዕራብ ባልቲሞር የነበሩት ቤቶች ፈርሰው ነዋሪዎቹ ወደ ሌላ አካባቢ ሲሄዱ ቂጥኛቸውንና ሌሎች ባህርያቸውን ወደ ሌላ የከተማው ከፍል እንዲዛመት አደረጉ፡፡ ለዓመታት በዚህ አካባቢ ታስሮ የቆየው በሽታ ተፈታ፡፡ ወረርሽኝ ሆነ፡፡
እንግዲህ ሦስቱም ለበሽታው መስፋፋት ተጠቃሽ ያደረጉት ነገር የተለያየ ነው፡፡ በአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠር መስሪያ ቤት ጥናት፤ ምክንያቱ ኮኬይን ነው። ግን ኮኬይን ከ1995 ዓ.ም (እኤአ) በፊት የሌለ ስለሆነ አይደለም፡፡ ኮኬይን በአካባቢው ለዓመታት ይሸጥ ነበር፡፡ ነገር ግን በ1991 አጋማሽ የኮኬይን አጠቃቀሙ የተወሰነ ዕድገት በማሳየቱ ችግሩ ተባባሰ፡፡ በዜኒልማን ጥናትም ችግሩ የተከሰተው፤ በአባላዘር ክሊኒኮች ጨርሶ መዘጋት አይደለም፡፡ ይልቅስ፤ የሐኪሞቹ ቁጥር ከ17 ወደ 10 በመውረዱ ነው፡፡ ፖቴራትም፤ በከተማው ያሉት የመንግስት ኮንዶሚኒየሞች ፈረሱ አላለም፡፡ የፈረሱት ጥቂት ህንጻዎች ናቸው፡፡ ከዚህ የምንረዳው በከተማው ተረጋግቶ የነበረውን የጨብጥ በሽታ ወደ ወረርሽኝ የቀየረው፤ በትንሽ ለውጦች የተነሳ መሆኑን ነው፡፡ የተሰጡት ሦስቱ ትንታኔዎች፤ ለወረርሽኝ መከሰት ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ሦስት ሁኔታዎችን ያመለክታሉ፡፡  የበሽታ ቁጥጥር መ/ቤቱ፤ የአደንዛዥ ዕጽ ወደ አንድ አካባቢ መግባት ወይም የአጠቃቀሙ መጨመር፤ አካባቢያዊ ሁኔታውን በመቀየር በከተማው ጨብጥ በወረርሽኝ መልክ እንዲስፋፋ ምክንያት መሆኑን ያስረዳናል፡፡ ዜኒልማን የበሽታውን ጉዳይ ነው ያነሳው፡፡ እርሱ ያስረዳን የክሊኒኮች አገልግሎት ሲቀንስ ጨብጥ ህይወቱን ለማራዘም ወይም ለመዛመት ዕድል አግኝቶ አደገኛ ባህርይ መያዙን ነው። ቀደም ሲል በአንድ ሰው ላይ የተከሰተ የጨብጥ በሽታ የነበረው የመዛመት ዕድል በሣምንት የተወሰነ ነበር፡፡ ሆኖም  የክሊኒኮች አገልግሎት ሲዳከም፤ በሽታው ለሣምንታት የረዘመ የመዛመት ዕድል አገኘ፡፡ የፖቴራት ትንታኔ ደግሞ በጨብጥ በተያዙት ሰዎች ላይ ያተኮረው ነው፡፡ ‹‹ጨብጥ የሚዛመተው በተወሰኑ ዓይነት ሰዎች ነው›› የሚል ነው፡፡ ድሆች፣ አደንዛዥ ዕጽ ተጠቃሚዎችና በአንድ ሰው የማይረጉ ሰዎች ለበሽታው መዛመት ምክንያት መሆናቸውን የሚያስረዳ ትንታኔ ነው፡፡ እንደዚህ ያሉ ሰዎች ይኖሩበት ከነበረው ቀዬ ወጥተው፤ ከዚህ ቀደም ጨብጥ ባልነበረበት የከተማው አካባቢ ሲሄዱ፤ በሽታው ወረርሽኝ የመሆን ዕድል ተፈጠረለት እያለን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ወረርሽኝ ከአንድ በላይ በሆኑ መንገዶች ሊከሰት መቻሉን የሚያስረዱ ትንታኔዎች ናቸው፡፡
በአጭሩ፤ ወረርሽኝ የአስተላላፊ ኤጀንቱ፤ የበሽታ አምጪ ኤጀንቱ እንዲሁም እነዚህ ኤጀንቶች የሚከሰቱበት አካባቢያዊ ሁኔታ በመተባበር የፈጠሩት ችግር መሆኑን መረዳት እንችላለን፡፡ ስለዚህ ወረርሽኝ የሚከሰተው፤ በሽታው ሚዛኑን ጠብቆ ከመቆየት እንዲያወጣ የሚያደርግ አንድ ችግር ሲፈጠር ነው፡፡ ይህም በብዙ ቦታዎች ሳይሆን በአንድ (ሁለት ወይም ሦስት አካባቢዎች) የሚከሰት ለውጥ ነው፡፡
እንግዲህ ግላድዌል እነዚህን ሦስት የለውጥ ኤጀንቶች መሠረት አድርጎ፤ ሦስት የለውጥ ህጎችን ፈጠረ፡፡ የመጀመሪያውን የጥቂቶች ህግ (Law of the Few) አለው፡፡ ሁለተኛው፤ የሙጥኝ ሥራ (the Stickiness Factor) አለው፡፡ ሦስተኛውን፤ የአውድ ኃይል (the Power of Context) አለው፡፡
ዝርዝሩን ነገር ትተን፤ የጥቂቶች ህግ (Law of the Few) የሚለው የሚያስረዳን፤ በአንድ ሂደት ወይም ስርዓት ለውጥ እንዲመጣ የሚያደርጉት ከሌሎች ሰዎች የበለጠ ሚና መጫወት በሚችሉ የተወሰኑ ሰዎች አማካኝነት መሆኑን ነው፡፡ ‹‹ይህ ቀላል እና የተለመደ ነገር ይመስላል፡፡ ግን በጣም መሠረታዊ እና ከቁም ነገር መያዝ ያለበት ጉዳይ ነው›› ይላል ፀሐፊው፡፡ ኢኮኖሚስቶች ብዙ ጊዜ የሚያነሱት 20/80 የሚሉት አንድ መርህ አለ (አንድ የኢትዮጵያ የኮንዶሚኒየም መርሐ ግብርም በተመሣሣይ ስም ይጠራል)፡፡ ሆኖም ኢኮኖሚስቶቹ 20/80 የሚሉት መርህ፤ በማናቸውም ሁኔታ 80 በመቶው የሚሆነው ሥራ የሚሰራው በስራው ተሳታፊ በሆኑ 20 በመቶ በሚሆኑ ሰዎች መሆኑን ለመግለጽ የሚጠቀሙበት አገላለጽ ነው። በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነው ወንጀል የሚፈጸመው 20 በመቶ በሆኑት ሰዎች ነው። 80 በመቶውን የሞተር ሳይክል አደጋ የሚያደርሱት 20 በመቶ የሚሆኑት ሞተር ሳይክል ነጂዎች ናቸው። 80 በመቶ የሚሆነውን ቢራ የሚጠጡት 20 በመቶ የሚሆኑት ቢራ ጠጪዎች ናቸው፡፡ ይህ ነገር በወረርሽ ጉዳይ ሲታይ ከረር ይላል፡፡ ከፍተኛ ወረርሽኝ የሚከሰተው ከ20 ፐርሰንት በታች በሆኑ ሰዎች ነው፡፡
ለምሣሌ፤ በኮሎራዶ ስፕሪንግ የጨብጥ በሽታን በተመለከተ ጥናት ያደረገው ፖቴራት፤ ለስድስት ወራት በአንድ የመንግስት የጤና ጣቢያ ባደረገው ክትትል፤ በተጠቀሰው ጊዜ ለህክምና ወደ ጤና ጣቢያ የመጡት ሰዎች፤ ከኮሎራዶ ስፕሪንግ ከተማ የቆዳ ስፋት 6 በመቶ ገደማ ሊሸፍኑ ከሚችሉ አራት የከተማው ሰፈሮች ነው። በተጨማሪም፤ ከእነዚህ 6 በመቶዎች ውስጥ ግማሾቹ ሰዎች በከተማው በሚገኙ 6 ቡና ቤቶች መዝናናት የሚያዘወትሩ ሰዎች ናቸው። አጥኚው ፖቴራት፤ በዚህ ቡና ቤት ከሚጠጡትና ጨብጥ ከያዛቸው ሰዎች መካከል ለ768 ሰዎች ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸው ነበር፡፡ እናም 600 የሚሆኑት ሰዎች በሽታውን ወደ ሌላ ሰው ያላስተላለፉ ወይም ለአንድ ሰው ብቻ ያስተላለፉ ናቸው፡፡ በሽታውን በኮሎራዶ ስፕሪንግ በወረርሽኝ መልክ እንዲዛመት ያደረጉት ወይም ለሁለት፣ለሦስት፣ ለአራት፣ ለአምስት ሰዎች በሽታውን ያስተላለፉት 168 ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከ100 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ባሏት የኮሎራዶ ስፕሪንግ ከተማ የጨብጥ በሽታ በወረርሽኝ መልክ እንዲዛመት ምክንያት የሆኑት በአራት ትናንሽ የከተማው ሠፈሮች የሚኖሩና አዘውትረው በ6 ቡና ቤቶች የሚጠጡ 168 ሰዎች ናቸው ይላል ማልኮም ግላድዌል፡፡ እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው? ብሎ የሚጠይቀው ፀሐፊው፤ በአጭሩ ከብዙዎቻችን የተለየ ህይወትና ባህርይ ያላቸው፣ በየዕለቱ መጠጥ ቤት የሚሄዱ፣ ከሚገመተው በላይ የወሲብ ጓደኛ ያላቸው ሰዎች ናቸው ይላል፡፡
ይህን ጉዳይ ወደ ሐሳብና ወደ ፋሽን እንውሰደው። የሐሳብ ‹‹ወረርሽኝ›› አለ፡፡ የፋሽን ወረርሽኝም አለ። እናም ማልኮልም ግላድዌል ሊለን የፈለገው፤ አንድ ፋሽን ወይም ሐሳብ ድፍን ሐገሩን ሲያጥለቀልቀው ካያችሁ፤ ነገሩ የ‹‹168›› ሰዎች ሥራ መሆኑን አትጠራጠሩ ነው፡፡ ይህ የጥቂቶች ህግ (Law of the Few) ሲል ከገለጸው አንጻር ነው፡፡ ጉዳዩ ከሌሎቹ ህጎች አኳያም ሊታይ የሚገባው ነው፡፡
ይህን እዚህ ለማድረግ አልቻልኩም። ሆኖም እናንተም እንደኔ ምናልባት ግራ ተጋብታችሁ፤ ‹‹ምክንያቱ ባይገባኝም ዶ/ር አቢይ አህመድ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ፍቅር አትርፋዋል?›› የሚል ጥያቄ ለግላድዌል ብታቀርቡ፤ ‹‹አትጠራጠሩ በሦስቱ ህጎች የተነሳ ነው›› ብሎ፤ ምክንያት ሳያገኝ እረፍት ለማይሰማው ህሊናችሁ ማስታገሻ ይሰጣችኋል። ዶ/ር አቢይ አህመድ የኢትዮጵያውያን ፍቅር ያገኙት በ‹‹168›› ሥራ ነው ይላችኋል፡፡ ጉዳዩን በሌሎቹ ህጎች ብናየው ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ጋዜጣ ሰፊ ነገር አይወድም፡፡

Read 1834 times