Sunday, 29 April 2018 00:00

ሁሉንም ለማርካት መሞከር ማንንም አለማርካት ነው!

Written by 
Rate this item
(11 votes)

 ደራሲ ከበደ ሚካኤል ከፃፏቸው አስገራሚ ተረቶች መካከል የሚከተለው ተረት ደጋግሞ ቢነገር እንኳ የማይሰለችና ትምህርታዊ ተምሳሌት ነው፡፡
አንድ ፈረሰኛ ወደ አንድ ከፍተኛ ተራራ ይጓዝ ነበር፡፡ ወደ ተራራው ወገብ ላይ ሲደርስ አንድ ምስኪንና አንድ እግሩ ሽባ የሆነ ሰው እንዳቅሙ ቋጥኙን እየቧጠጠ ለመውጣት ሲፍጨረጨር ያገኛል፡፡
ፈረሰኛው፤
ወዳጄ፤ ይህን የሚያህል ተራራ እንዲህ ተንፏቀህ የሚገፋ አይደለም፡፡ ስለዚህ እንደምንም ፈረሴ ላይ ላውጣህና አፈናጥጬ ዳገቱ ጫፍ ላይ ላድርስህ?
ሰውዬው፤
እግዚአብሔር የባረከህ ሰው ነህ! ግን ሥጋቴ እንዳላጣብብህ ነው፡፡ ለማፈናጠጥ ይበቃል ብለህ ነውን?
ፈረሰኛው፤
እንደምንም ተጣበን እንወጣዋለን እንጂ በዚህ ሁኔታ በፍፁም ጥዬህ ብሄድ ግፍ ይሆንብኛል፡፡ ሰው እንኳ ባይኖር ተራራውም ይታዘበኛል፡፡ ስለዚህ ና ውጣ ግዴለህም፡፡
ሰውዬው፤
ፈጣሪ ምስክሬ ነው፤ ለእኔ የተላክ ውድ አዳኝ መልዐክ ነህ፡፡ አምላክ ውለታህን ይክፈልህ!
ፈረሰኛው ተሸክሞ ፈረሱ ላይ አስቀመጠውና ተራራውን ተያያዙት፡፡ ጥቂት እንደሄዱ ግን፤
ሰውዬው
ወዳጄ፤ ቅድም እንደፈራሁት በጣም ተጣበናል፡፡ ብወርድልህ ይሻላል፡፡
ፈረሰኛው፤
እንደሱማ አይሆንም፡፡ ባይሆን የተወሰነውን ዳገት እኔ በእግሬ ልሞክረው፤ አንተ ፈረሱን ያዝ አለውና ፈረሱን ሰጥቶት ወረደ፡፡ ሰውየው እየጋለበ ዳገቱን እየወጣ እየራቀ ሄደ፡፡
ፈረሰኛው በእግሩ ዳገቱን ተያያዘው፡፡ ሆኖም ባለፈረሱ እየራቀ ሄደ፡፡ ፈረሰኛው ሥጋት እየገባው በተቻለው ፍጥነት ሊከተለውና ሊጠጋው ቢሞክርም ሰውዬው ፈረሱን ይብስ አፈጠነው፡፡
ፈረሰኛው መጣራት ጀመረ፡፡ ወይ የሚለው ግን አጣ፡፡ ሰውዬው ፈረሱን ይዞ ሊጠፋ መሆኑ ለፈረሰኛው ገባው፡፡
“አንተ ሰው፤ ግዴለም ፈረሱን ይዘኸው ትሄዳለህ፡፡ ግን አንድ ነገር ቆም ብለህ ስማኝ እባክህ፡፡ እንደማልደርስብህ ታውቃለህ፡፡ ጆሮህን ብቻ አውሰኝ?” ሲል ለመነው፡፡
ሰውዬው ርቀቱን በደንብ ካረጋገጠ በኋላ፤
“እሺ ምንድነው ልትነግረኝ የፈለከው?”
ፈረሰኛውም፤
“ወዳጄ፤ መቼም አንድ ቦታ ወርደህ ከሰው መቀላቀልህ አይቀርም፡፡ አደራህን ይሄን አሁን እኔን የሰራኸኝን ነገር ለማንም ሰው እንዳትነግር፡፡ አለበለዚያ ደግ የሚሰራ ሰው ይጠፋል!”
*   *   *
የሚያጪበጭቡልን፣ የሚያሞግሱን፣ የሚያወድሱን ሁሉ ደግ ላይሆኑ እንደሚችሉ አንርሳ! ሰዎች ለችግራቸው የደረሰላቸውን ሰው እንኳ ውለታውን መመለስ ቀርቶ ጭራሹን ተንኮል ሊሰሩበት፣ ግፍ ሊውሉበት ይችላሉ፡፡ ደግ የሚሰራ እንዳይጠፋ የሰራነውን ክፉ ነገር ለሰዎች ባንነግር መልካም ነው፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ችግር ባለቤት ናት፡፡ የብዙ ፀጋም ባለቤት ናት፡፡ ከእነ ችግሮቹ ሀገሩን አሳቢ ብዙ ንቁ ዜጋ፣ ብዙ ልባም ሰው፣ ብዙ የተማረ፣ አስተዋይና አገር ሊለውጥ የሚችል አዋቂ አላት፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ሰው በዲዮጋን ፋኖስም ቢሆን ፈልጎ ማግኘት ተገቢ ነው፡፡ ሰዓሊ ገ/ክርስቶስ ደስታ ብራውኒንግን ጠቅሶ እንደፃፈው፤
“… ደግሞም፤ ማወቅ ማለት፤
ከውጪ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ የበራውን እንዲወጣ ማድረግ”
… ወቅታዊነት ያለው ጥበብ ነው፡፡
ሀገራችን የብዙ ካህናት፣ የአያሌ ጠቢባን፣ የበርካታ አበው ፈላስፎች አገር ሆና ሳለ፤ የትምህርት ሥርዓቷ እየተዳከመ፣ ምሁር ማፍራቷ እየተመናመነ መምጣቱ ቢያንስ ሊያስቆጨን የሚገባና አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን መረዳት ይጠበቅብናል፡፡ የትምህርት ድክመት የሀገርን ድክመት የሚጠቁም ከባድ የመከራ ደወል ነው፡፡ ባለሙያ የምናፈራው ከዚህ የዕውቀት ማሳ ነው፡፡ “ኩሉ አመክሩ ወዝሰናየ እፅንዑ” (ሁሉንም ሞክሩ የተሻለውን አፅኑ) የሚለው የጥንቱ ዲግሪ ላይ የተፃፈው መልዕክት፤ ተምረን በየአቅጣጫው ጥረት ማድረግና አገርን የማሳደግ አደራ እንዳለብን ጠቋሚ ጥቅስ ነበር፡፡፡ አሁንም በነበር መቅረት ያለበት ሀሳብ አለመሆኑን ማስተዋል ይጠበቅብናል! መንገዱ መኖሩን እያየን አላየንም ማለት ሐጢያት ነው፡፡ መማር እየቻልን አለመማርም ሐጢያት ነው፡፡ ለሐጢያታችን ሥርየት የምናበጀው ዕውቀት ሲኖር ነው፡፡ አገር የምትድነው በአዋቂዎቿ የተከፈተ ዐይን ነው፡፡
“ይቺን ጨቅላ መጥሐፍ የምታነቡ ሁሉ
አደራ ስለኔ ማርያም ማርያም በሉ፡፡
ከሃያ ስድስቱ ወንዶች ፊደላት
አርግዣለሁና መዝገበ - ቃላት
ከሆዴ ያለውን የትምህርት ሽል
ያለጭንቅ እንድወልድ እንድገላገል!
ስንት እልፍ አበው ናቸው አርግዘው የሞቱ
ቀኝ እጃቸው አጥሮ ፊደል በማጣቱ
ለትምክህት አይደለም ይህን መናገሬ
ለማስቀናጠ እንጂ ሰነፉን ገበሬ!
ሐዋርያው ሲናገር ወደ ምዕመናኑ
ለምትበልጥ ፀጋ ይላል ቅኑ አስቀኑ”
በተባለባት አገር የትምህርት ደሀ ልትሆን አይገባም፡፡ መልሰን ራሳችንን ለመፍጠር መፍረምረም አለብን። ብልሃቱንና መላውን ካበጀን የማንወጣው ዳገት አይኖርም፡፡ እጅ ለእጅ ከተያያዝን፣ አዕምሮ ለአዕምሮ ከተናበብን፤ መሻሻል ግዴታችን ይሆናል፡፡
ሁሉንም አዳርሰን ስናበቃ እያንዳንዱን በተናጠልና በጥበብ ካቀድን፣ ለሀገር ቅጥ ቅጥ ማበጀት አያቅተንም። መልካም እንሰራለን ያልነው ሁሉ ላይሳካ ቢችልም፤ ለዛም መዘጋጀት አንድ መልካም ነገር ነው፡፡ ሁሉንም ሰው እናረካለን ብለን አናስብ፡፡ ፈረንጆቹ፤ “To satisfy all is to satisfy none” የሚሉት ወደው አይደለም - ዕውነትም “ሁሉንም ለማርካት መሞከር ማንንም አለማርካት ነው!”

Read 8226 times