Sunday, 29 April 2018 00:00

በዶ/ር ዐቢይ አዲስ አመራር - ተስፋና ስጋቴ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

• ኢትዮጵያ ውስጥ ነገዳዊ ብሔርተኝነት የጠነከረ ስር የለውም
• በኢህአዴግ ውስጥ አሁንም በዝምታ ያደፈጠ ኃይል አለ
• ጠ/ሚኒስትሩ ፍኖተ ካርታቸውን ሊሰጡን ይገባል

    ዶ/ር አብይ አህመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበሩ ላይ ከተሰየሙ ዛሬ 26ኛ ቀናቸውን ይዘዋል፡፡ በእነዚህ ቀናት ውስጥ
ያከናወኗቸው ጉብኝቶች፣ ለህዝብ ያደረጓቸው ንግግሮች፣ ያዋቀሩት ካቢኔ --- ምን ዓይነት አቅጣጫን ያመላክታሉ? ሁሉም በጠ/ሚኒስትሩ መርከብ ላይ ተሳፍሯል ወይ? ከኢህአዴግ ጎምቱ አመራሮች ያላቸው ድጋፍ ምን ያህል ነው? ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ምን ይጠበቃል? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አንጋፋው ምሁር ዶ/ር አለማየሁ አረዳ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ሰፊና ጥልቅ ትንታኔ ሰጥተዋል፤ተስፋና ስጋታቸውንም ገልጸዋል፡፡ ሃሳባቸውን በርዕሰ ጉዳይ ከፋፍለን እንደሚከተለው አጠናቅርነዋል፡፡

    ከየት ተነስተን ዶ/ር አብይ ላይ ደረስን?
ከዚህ በፊት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ቃለ ምልልስ የምሰጠው ብዙም ተስፋ በማላደርግበት ሁኔታ ነበር፤ ዛሬ ግን በትንሹም ቢሆን በተስፋ ብርሃን ውስጥ ሆኜ ነው የምናገረው፡፡ እንደውም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ምሁር፣ እኔም የራሴን ድርሻ እንደምወጣ አስቤ ነው፣ በተረዳሁት መጠን ለመተንተን የምሞክረው፡፡ በአሁን ሰዓት ዶ/ር አብይ በቃል የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች እኔም ልቦና ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹን “ምሁሩ” በሚለው መፅሐፌ ውስጥም በመጠኑ ጠቅሻቸዋለሁ፡፡ እኔ አሁን ሂሳዊ ድጋፍ እየሰጠሁ፣ እንደ አንድ ምሁር በሀገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ እሳተፋለሁ፡፡
ከየት ተነስተን ዶ/ር አብይ ላይ ደረስን የሚለውን ለማየት፣ ትንሽ ወደ ኋላ መለስ ብለን ነገሮችን መገምገም መቻል አለብን፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ ይብዛም ይነስም የህዝብ ተቃውሞዎች ሲያጋጥሙት ቆይቷል፡፡ እነዚያን በስርአቱ ላይ የሚቀርቡ ተቃውሞዎች፣ ኢህአዴግ በልዩ ልዩ መንገዶች እያለፋቸው ነው ዛሬ ላይ የደረሰው። ግምገማም ሲያካሂድ ኖሯል። ብዙ ጊዜ ለምሳሌ ኪራይ ሰብሳቢነት አስቸገረኝ፤ የመልካም አስተዳደር ጉድለት አለብኝ እያለ ሲገመግም ቆይቷል። ብዙ ጊዜም  ፖሊሲው ትክክል ነው፤ ችግራችን የአፈጻጸም ጉድለት ነው ሲባል ነበር የምንሰማው። ህዝቡም ይሄንን እየሰማ በዝምታ ሲያልፍ ኖሯል፡፡ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በተለይ ከ2008 ወዲህ ግን አዲስ ክስተት ተፈጠረ፡፡ ህዝቡ ከዳር እስከ ዳር በተቃውሞ ተነሳ። ብሶትና ምሬቱን አምርሮ በአደባባይ መግለጽ ጀመረ፡፡ ህብረተሰቡ ለኢህአዴግ ያስተላልፍ የነበረው መልዕክትም፡- “ከእንግዲህ በለመድከው መንገድ ልትገዛን አትችልም” የሚል ነው፡፡
የህዝቡ እንቅስቃሴ ምላሽ ሳያገኝ በቆየ ቁጥር ደግሞ ድርጅቱ ውስጥ መንገጫገጭ ፈጥሯል። ከዚህም ድርጅቱ በመጠኑ ትምህርት ወስዷል። ከዚያም 17 ቀናት የፈጀ ግምገማ ነው ያካሄደው፡፡ በዚህ ግምገማ እንደከዚህ ቀደሙ እንዲሁ ሾላ በድፍን የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው  በሚለው ላይ አልቆመም፡፡ ይብዛም ይነስ ከሞላ ጎደል ችግሮቹን ዘርዝሯቸዋል፤ ነገር ግን አላብራራቸውም፡፡ ማብራራቱ በእርግጥ የኛ ሥራ ነው፡፡ እያየነውም የነበረ ነገር ስለሆነ ማብራራቱ ከኛ ይጠበቃል፡፡
ለምሳሌ በመጀመሪያ ኢህአዴግ ያነሳው ችግር፣ የመድብለ ፓርቲ ስርአቱ እንዲጎለብት አላደረግሁም፤ አዳክሜያለሁ የሚለውን ነው፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው? የመድብለ ፓርቲ ስርአቱን አዳክሜያለሁ ማለት ለሀገሪቱ አማራጭ ሃሳብ ይዘው የሚመጡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳይኖሩ አድርጌያለሁ ማለት ነው፤ ህብረተሰቡ አማራጭ የፖለቲካ ሃሳብ እንዳይኖረው እንቅፋት ነበርኩ  ማለት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የፖለቲካ ስርአቱን እኔ ራሴ ተጭኜው ይዤ ነበረ እንደ ማለት ነው የሚወሰደው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ኢህአዴግ ችግሬ ነው ብሎ የጠቀሰው ሚዲያው ኃላፊነቱን እንዲወጣ አለማድረጉን ነው፡፡ ሚዲያው በአግባቡ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አላደረግሁም ብሏል፡፡ ይሄ ማለት ምን ማለት ነው? ሚዲያ በመንግሥትና በህብረተሰቡ መካከል የሚገኝ ድልድይ ነው፤ ይሄ ድልድይ ሃሳብ እንዳይንሸራሸርበት ከልክያለሁ ነው ያለን፡፡ በተግባርም የምናውቀው፣ ሚዲያው የአንድ ሃሳብ አራማጅ መሆኑን ነው፡፡ ኢህአዴግ በሚዲያው የቁጥጥር ስርአት ነው የዘረጋው እንጂ የመስሪያ ሜዳውን አላመቻቸለትም፡፡ በዚህም ህብረተሰቡ ነፃ ሃሳብ አላገኘም፡፡ ሌላው የሲቪል ማህበረሰቡን የተመለከተ ነው፡፡ ይህም ከፍተኛ የቁጥጥር ስርዓት ዘርግቶ፣ የሚያገኙትን ፋይናንስ በመቆጣጠር ማዳከም እንጂ ለዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ አላጎለበተም፡፡ ሌላው ችግር ተብሎ የተጠቀሰው ግንባሩን በመሰረቱ ድርጅቶች መካከል መርህ አልባ ግንኙነት ተፈጥሮ ስህተት ተሰርቷል የሚል ነው፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው? በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል ባሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ውስጥ የጥቅም ግንኙነት ተፈጥሮ የመሬት ዘረፋ ተፈጽሟል፣ ኮንትሮባንድ ተካሂዷል፣ ሙስና ተስፋፍቷል፣ ህግ እንዳይከበር ተደርጓል ማለት ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ ስህተቶቼ ናቸው ብሎ በይፋ አስታውቋል፡፡
ኢህአዴግ በዚህ አላበቃም፤ በግምገማው ስህተቶቹን ከዘረዘረ በኋላ ማን ነው ይሄን የሰራው? የሚል ጥያቄም ጠይቋል፡፡ ስህተቱን የፈጸመውም ከፍተኛው የአመራር አካል ነው ብሏል፡፡ ይሄን ከማለቱ በፊት ደግሞ ጎምቱ የሆኑ የኢህአዴግ አመራሮች፤ “ሥራ አስፈፃሚውን የሚቆጣጠረው ጠፋ”፣ “ሥራ አስፈፃሚው አስቸገረን፣አይሰማም” ብለውናል፡፡ ስህተቶቹ በሙሉ የተደፈደፉት በአመራሩ ላይ ነው፡፡ ከአመራሩ ደግሞ ቁንጮው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው። በነገራችን ላይ በሰለጠነ ሃገር ፖለቲካ ቢሆን ኖሮ፣ እነዚህን ሁሉ ስህተቶች በራሱ አንደበት ፈፅሜያለሁ የሚል ስርአት፣ የመንግስት ሥልጣን ይለቅ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፍቃዳቸው ስልጣን መልቀቃቸው ተነግሮናል፡፡ እነዚህ ሁሉ ስህተቶች ተፈፅመው ግን “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ለቀዋል፤ እኛ ግን እንቀጥላለን” ማለት አግባብ  አይደለም፡፡  
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን መልቀቃቸው  መልካም ነው፡፡ የእሳቸው መልቀቅ ደግሞ ድርጅቱ ውስጥ የነበረውንና ለብዙዎች አልታይ ብሎ የከረመውን ችግር ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል፡፡ ይህ የታየው የድርጅቱን ሊቀ መንበር በመምረጥ ሂደት ላይ ነው፡፡ ከዚህ አብዮት መሰል እንቅስቃሴ ውስጥ ነው፣ ዶ/ር አብይ የወጡት፡፡ ዶ/ር አብይ ለኛ አዲስ ያልሆነ፣ ለኢህአዴግ ግን አዲስ የሆነ ቋንቋ ነው ይዘው የመጡት፡፡ የኢህአዴግ ቋንቋ ነገዳዊ ብሔርተኝነት ነው፡፡ ዶ/ር አብይ አህመድና እነ አቶ ለማ፣ በዚህ ነገዳዊ ብሔርተኝነት ውስጥ ነው ብቅ ብለው፤ “እኛ ኢትዮጵያውያን ሰርገኛ ጤፍ ነን፣አብረን እንፈጫለን፣ አብረን እንቦካለን፣ አብረን እንጋገራለን አብረን እንበላለን” ያሉት። ይሄ ኢህአዴግ ያስለመደን ቋንቋ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ተናግሮትም አያውቅም፡፡ እነዚህ ሰዎች ቀጠሉና፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ብድግ አደረጉና “ዋጋ አለው፣ ታሪካችንን አንጣል፣ መልካሙን እንያዝ፣ ከመጥፎውም እንማር” የሚለውን ሃሳብ አስተጋቡ። ይሄም የለመድነው የኢህአዴግ ቋንቋ አልነበረም። እኛም ስንለው የነበረውን ነው እነዚህ ሰዎች ደግመው ያቀነቀኑት፡፡ ይሄን ጊዜ ኢትዮጵያውያን ሁሉ መንፈሳችን በረደ፣ ውጥረታችን ላላ፣ ተስፋ አደረግን፡፡ አሁን እዚህ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ይህቺ ተስፋ ናት አሁን ይዛን፣ ቀጣዩን ለማየት ጉጉት ውስጥ የዶለችን፡፡   
በቃል ነው ነገሩን ጀምረው ያበረዱን፣ የተራራ ላይ ስበከት ይመስላል ንግግራቸው፣ ግን አስፈላጊ ነበር፤ ምክንያቱም የጋለው፣ የተወጠረው፣ የሞቀው መንፈሳችን መቀዝቀዝ ነበረበት፡፡ በጎ አመለካከትና የይቅርታ ስሜት ያስፈልገን ነበር። ይሄን ነው ዶ/ር አብይ የሰጡን፡፡ ይሄ ግን ለውጡ የሚፈልገው የመጀመሪያ ደረጃ ረቂቅ ነው። አስፈላጊ ረቂቅ ነው። አሁን እዚህ ረቂቅ ላይ አድርሰውናል፡፡
ከሃገር ማረጋጋት እስከ እርቅ
ዶ/ር አብይ ራሳቸው እንደተናገሩት፤ አንድ ወደ ቀውስ እያመራ በነበረ ሃገር ላይ ስልጣን የያዘ መሪ፣ የመጀመሪያ ግቡ መሆን ያለበት ሃገር ማረጋጋት ነው። አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ነው እያደረጉ ያሉት። በመጀመሪያ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በላይ ስለ ብሄሩ ሲሰበክ የነበረውን ህዝብ፣ በኢትዮጵያዊነት መርከብ ላይ ማሳፈር ያስፈልጋል፡፡ ልክ ኖህ ፍጥረታቱን ከጥፋት ውሃ ለማዳን እንደሰበሰባቸው ሁሉ፣ ዶ/ር አብይም በተለያየ ሃሳብ የተበታተነውን ህዝብ፣ ኢትዮጵያ ወደምትባል መርከብ መሰብሰብ ነበረባቸው፡፡ ይህቺ ሃገር እንዳትፈርስ ለማድረግ የተበተነውን የህዝብ መንፈስ መሰብሰብ አስፈላጊ ነበር። ይሄ በየክልሉ እየሄዱ የሚያደርጉት ንግግር እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ባህርዳር ላይ አንድ መምህር እንዳሉት፤ እንደውም ሁሉንም እያሳተፈ፣ የእርቅ መንፈስ እየፈጠረ ነው መሄድ ያለበት፡፡
ዶ/ር አብይ ከቃል ብዙ ነገር እያስተማሩን ነው፤ የኔ ስጋት ግን ይሄ የዜግነት፣ ሃገራዊነት አጀንዳ የማን አጀንዳ ነው? የሚለው ጥያቄ ነው። የዶ/ር አብይና የጥቂት የራሳቸው ቡድኖች አጀንዳ ነው? ወይስ የኢህአዴግም ነው? ይሄ ያስጨንቀኛል፡፡ ኢትዮጵያዊነትና የሃገር ታሪክ፣ የኢህአዴግ አጀንዳ ነው ወይ? ከጥቂት ወራት በፊት እኮ “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር” ማለት የነፍጠኛ ምልክት ተደርጎ ነበር የሚወሰደው። “ፈጣሪ ህዝቧንና ሃገሪቱን ይባርክ” ማለት እኮ ለድርጅቱ አባላት አስቂኝ ነበር፡፡ በእርግጥ አሁን ዶ/ር አብይ ይሄን ሲሉ፣ ኢህአዴጎች እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ተቀብለውታል ወይ? ለምንድን ነው በዚህ ላይ ሃሳብ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበው በዝምታ የተዋጡት? ጎምቱ የሚባሉት የኢህአዴግ ነባር ታጋዮች፣ አሁን ለምን ዝምታን መረጡ? የመንግስት ሚዲያውስ ለእነዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሮች ከዜና ሽፋን በመለስ ጠለቅ ያለ ትንታኔ ሲያቀርብ ለምን አናይም? ምንድን ነው ዝም ብሎ የመታዘቡ ምስጢር? የሚለው ነገር በጣም ያሳስበኛል፡፡ ይሄን ሂደት ለማደናቀፍ የተዘጋጀ ድብቅ ኃይል ይኖር ይሆን? የሚል ጥያቄ አለኝ፡፡ ይሄን ኢህአዴግም ዶ/ር አብይም ሊመልሱት ይገባል፡፡
የዶ/ር አብይ ቡድን በኢህአዴግ ውስጥ ያለውን ያረጀ አስተሳሰብ አሸንፎታል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ሊያሸንፍ አይችልም፡፡ የፖለቲካ ታሪካችንም ይሄን አያሳይም፡፡ ምናልባት የህዝቡ ስሜት ስለጎለበተና ወጀቡ ስለበዛ ጎንበስ ያለ ያደፈጠ ኃይል ይኖር ይሆን? የሚለው በጣም ያሰጋኛል፡፡ የዚህ ስጋት ደግሞ ምልክቱ እየታየ ነው፡፡ ዶ/ር አብይ የሃይማኖት ድርጅት አይደለም የሚመራው፣ ሃገር ነው፤ ከተራራ ላይ በሚዘንብ ስብከትና ምስማክ ብቻ እስከ መጨረሻው ይዞን ሊዘልቅ አይችልም፤ በተግባር ማሳየት አለበት። በተግባር ካላሳየን ስልጣን እንለቃለን ብሏል፡፡ ይሄ የራሱ ብቻ ነው ወይንስ የኢህአዴግም አቋም ነው? እነዚህ የሚያስጨንቁኝ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
ዶ/ር አብይ እና ካቢኔያቸው
የካቢኔ አወቃቀሩን ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡ አስር አዳዲስ የካቢኔ አባላት ተሹመዋል፡፡ ለኔ አዲሶቹም ሆኑ ነባሮቹ የመጡበት መመዘኛ፣ የተለመደው የኢህአዴግ መመዘኛ ነው፡፡ አሮጌው መመዘኛ ነው ዋና መስፈርት ሆኖ ያገለገለው፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ የነበራቸው የፖለቲካ ታማኝነት ነው መስፈርት የነበረው፡፡ ዶ/ር አብይ ደግሞ አዲስ አገራዊ አጀንዳ ነው ይዘው የመጡት፡፡ እነዚህ የካቢኔ አባላት፣ ከነባሩ የኢህአዴግ ባህል ወጥተው፣ ምን ያህል ዶ/ር አብይ ለዘረጉት አዲስ አገራዊ አጀንዳ ይመጥናሉ? የሚለው ነው ወሳኙ ጥያቄ።
የካቢኔ አባላቱ ኢትዮጵያውያንን በእኩልነትና በፍትሃዊነት ያለ ልዩነት ማገልገል የሚችሉ ናቸው ወይ? ከድርጅታቸው ታማኝነት በላይ ለሆነው ለኢትዮጵያዊነት ታማኝ ይሆናሉ ወይ? ሰዎቹ ሲሾሙ እነዚህ ወሳኝ ጉዳዮች በመመዘኛ ውስጥ አልገቡም። ይሄ ሊሆን የቻለው ደግሞ በኢህአዴግ የካቢኔ ሹመት ስርአት ውስጥ ሁልጊዜ ብሄራዊ ድርጅቶች የበላይነት ያላቸው በመሆኑ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደ ዶ/ር አብይ አስተሳሰብ ካልመጡ፣ ከአሮጌው እርሾ ተቀድተው፣ ወደ አዲሱ ሁኔታ ውስጥ የገቡ ባይተዋር ነው የሚሆኑት፡፡ ከሙያና ትምህርት አንፃር የተሰጡ ምደባዎችን አይተው የሚተቹ አሉ፤ ለኔ ደግሞ እሱ አይደለም አሁን ዋናው ጉዳይ፡፡ ዶ/ር አብይ ራሳቸው ገብተዋቸዋል ወይ? የሚለው ነው። እነሱ እና እኛ ከሚለው መርህ ወጥተው አንዳችን ለሁላችን፣ ሁላችን ለአንዳችን የሚለው የዶ/ር አብይ አመለካከት ገዝቷቸዋል ወይ? እነዚህ ስጋቶች አሉኝ። ለምሳሌ መንግስት ስናዋቅር የዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ መርህ ማስቀመጫ የሆኑ መስሪያ ቤቶች፣ ጥሩ ስም በሌላቸውና ፀረ ዲሞክራሲ በሆነ አቋማቸው የሚታሙ ሰዎችን መሾም ምን ማለት ነው? ለዚህ ነው እኔ ያደፈጠ ኃይል አለ የምለው፡፡ ይሄ ያደፈጠ ኃይል፣ አቶ ለማንና ዶ/ር አብይን አንገዋሎ ነቅሎ እስከ ማስወገድ የሚደርስ ጉልበት እንዳይኖረው እሰጋለሁ። ዛሬም የመስመር ጥራትን ማስቀጠል እየተወራ ነው። እነዚህ የመስመር ጥራት ጉዳይን የሚያወሩ ሰዎች ስለ የትኛው መስመር ነው እየተናገሩ ያሉት? ዶ/ር አብይ እኮ የድሮውን መስመር ገልብጠውታል፡፡ እኛ መርከባቸው ላይ የተሳፈርን ሰዎች እኮ በአፉ ቆሞ የነበረውን ጠርሙስ፣ በቂጡ አስቀመጡት እያልን ነው ያለው፡፡ የኢህአዴግን መስመር እስካስቀጠሉ ድረስ አብረናቸው ነን ማለት ምን ማለት ነው? ስለ የትኛው መስመር ነው የሚወራው? ስለ ነገዳዊ - ብሔርተኝነቱ መስመር ነው? ህዝብን ከህዝብ ሲያጋጭ ስለነበረው መስመር ነው? ሰላምን፣ መግባባትን፣ እርቅን ለማጣት የማይጨነቀው መስመር ነው የሚቀጥለው? የትኛው መስመር ነው እንዲቀጥል የሚፈለገው? እነዚህ ጉዳዮች ናቸው የወደፊት ስጋቶች፡፡ በነገራችን ላይ ዶ/ር አብይ የያዙትን ሃሳብ ለመቀልበስ የሚሰራ፣ ያደፈጠ ኃይል የለም ብሎ መዘናጋት ትልቁ ስህተት ይመስለኛል፡፡  
 ዶ/ር አብይ ፍኖተ ካርታውን ሊያሳዩን ይገባል
በመጀመሪያ ደረጃ ዶ/ር አብይ በየቦታው ሄደው ለህዝብ የገቡት ቃል፤ ከህዝብ ጋር ያደረጉት ውይይት የኢህአዴግ አጀንዳ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ሁለተኛ ከአሁን በኋላ ህብረተሰቡ አሁን ካለው የዘለለ ለውጥ ከኢህአዴግ ይመጣል ብሎ እጁን አጣጥፎ መቀመጥ የለበትም፣ በለውጡ አጋዥ ሆኖ መሳተፍ አለበት፡፡ ዶ/ር አብይ የሚናገሩት ነገር ማሳጅ የማድረግ ባህሪ አለው፤ መንፈሳችንን ማሳጅ አድርጎታል። ነገር ግን ከማሳጅ ማለፍ አለብን፡፡ ዶ/ር አብይ ዛሬ የተናገሩትን አሁኑኑ ይተግብሩ ማለት አንችልም፡፡ ነገር ግን ፍኖተ ካርታውን ሊያሳዩን ይገባል፡፡ ፍኖተ ካርታው (ሮድ ማፑ) ምንድን ነው? ለምሳሌ የፍትህ ስርአቱና ደህንነቱ፣ የህዝብን ሰብአዊ መብት እንዳይገፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡ እንዴት ነው ሊያደርጉት ያሰቡት? ፍኖተ ካርታቸውን ማወቅ አለብን፡፡ አውቀን ከጎናቸው ቆመን፣ ጥረታቸው እንዲሳካ እንድንረዳቸው ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ኮምፓሳቸው ወዴት እንደሚያመለክት አይተን እንድንከተላቸው ከፈለጉ፣ ፍኖተ ካርታውን ሊሰጡን ይገባል፡፡ እኛ አሁኑኑ ውጤት ያምጡ ሳይሆን አቅጣጫቸውን ያሳዩን ነው የምንለው። ፍኖተ ካርታቸውን ደግሞ ከኢህአዴግ ጋር ብቻ አይደለም ሊሰሩ የሚገባው፤ ነፃ አስተሳሰብ ካላቸው፣ ለሃገሪቱ ከሚቆረቆሩ ምሁራን ጋር ሆነውም መስራት አለባቸው። የኢህአዴግ መዋቅርን ይዘው ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የኢህአዴግን መዋቅር መቶ በመቶ ማመን ለራሳቸውም ቢሆን ስህተት ነው፡፡ አሁን ካነገቡት ሃሳብ አንፃር የኢህአዴግን መዋቅር አምነው መሄዳቸው ስህተት ይሆናል፡፡ ሌላው ቅደም ተከተሉን የማወቅ ጉዳይ ነው፡፡ ቅደም ተከተሉን በዝርዝር ይንገሩን፤ ለምሳሌ ለሚዲያው የሚሰጠው ነፃነት የፋይናንስ ወጪ አይጠይቅም፤ ከልዩ ልዩ ቁጥጥር ነፃ ማድረግ በቂ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች የራሳቸውን ድክመት አስወግደው ጠንክረው እንዲወጡ ለማድረግ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ገንዘብ አይጠይቅም፤ ጊዜም አይጠይቅም፡፡ ሲቪል ማህበረሰቡ የተሳትፎ ፖለቲካውን እንዲያፋፍም ከተፈለገ፣ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና እላዩ ላይ የተጫነበትን አሰራር ማንሳት አለበት፤ ይሄ ገንዘብ አይጠይቅም፡፡ ህብረተሰቡን ማሳተፍና አቅጣጫ መስጠት ለለውጡ በቂ ነው፡፡ እሳቸው ብቻ ተናግረው፣ የተሳሳተውን አርመው ዘላቂ ውጤት ማምጣት  አይችሉም፡፡
የዶ/ር አብይ ሃሳብና የኢህአዴግ ቁመና
ዶ/ር አብይ የያዙትን ሃሳብ፣ ኢህአዴግ አሁን ባለው ቁመና መሸከም አይችልም፡፡ የእሳቸውን የሃገር አንድነት አጀንዳ ለመሸከም ኢህአዴግ ግንባር መሆኑ ቀርቶ አንድ ድርጅት መሆን አለበት፡፡ አሁን በግንባሩ ያሉ አራቱ ድርጅቶች ይዘውት ያለው አቋም በአላማም ሆነ በመርህ እርስ በእርስ የሚጣረስ ነው፤ አንዱ ስለነባሩ መስመር ጥራት ሲጨነቅ፣ ሌላው የለም ነባሩ ለያይቶናል፤ አንድነት ያስፈልገናል እያለ ነው፡፡ በሌላ በኩል ብአዴን ንቅናቄ ነው፣ ደህኢዴን ንቅናቄ ነው፣ ኦህዴድ ደግሞ ድርጅት ነኝ ይላል፣ ህውሓት ነፃ አውጪ ነኝ ይላል፡፡ እነዚህ ስሞች  ብዙ ትርጉም ይሰጣሉ፡፡ ይሄን ጉዳይ አጥርተው መፈተሽ አለባቸው። ይሄን አስታርቀው አንድ ድርጅት መሆን አለባቸው። በነሐሴው ጉባኤ፣ ኢህአዴግ አንድ ድርጅት መሆን አለበት፡፡ ኢህአዴግ አንድ ድርጅት ከሆነ፣ በውስጥ ያለው መሳሳቡ ይቀራል፡፡ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ብቁ ቁመና ሊኖረውም ይችላል፡፡ እውነቱን ለመናገር ኢህአዴግ ወደዚህ ቁመና መጥቶ፣ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን አስተሳሰብ ከደገፈ፣ እውነተኛ ባለውለታ ድርጅት ይሆናል፡፡ ይሄን ሳላፍር ነው የምናገረው፡፡ ይሄን ካደረገ እውነተኛ ባለውለታ ድርጅት ይሆናል፤ ታሪክ ይሰራል፡፡  ባለው ቁመና ተገትሮ ከቀረ ግን በውስጥ ያሉትን ተቃርኖ ማስታረቅ ስለማይችል፣ አሁን የመጣውን አስተሳሰብ ከማደናቀፍ ምንም አያቅበውም፡፡
 የመቀልበስ አደጋው ከየት ሊመጣ ይችላል?
ይህ አየሩን የሞላው የለውጥ አስተሳሰብ አደጋ ካጋጠመው፣ የሚያጋጥመው ከራሱ ከኢህአዴግ ውስጥ ነው፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ የኢትዮጵያዊነት፣ የአብሮነት ተጠሪ ነን የሚሉ በውጭም በሀገር ውስጥም ያሉ ድርጅቶች ነበሩ፡፡ አሁን አጀንዳቸው ተወስዷል። ከእነዚህም ወገኖች ሊመጣ የሚችል ችግር ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ዋናው አደጋ የሚመጣው ከኢህአዴግ ከራሱ ውስጥ ነው፡፡ ዶ/ር አብይ እያቀነቀኑ ያሉት ርዕዮት የሃገራዊነት፣ የዜግነት ብሔርተኝነት ነው። ይሄ ዜጋዊ ርዕዮትን የሚያጎለብት አካሄድ ነው፤ ይሄን ለመድፈቅ ደግሞ ነገዳዊ ብሔርተኝነት በተጠንቀቅ ሆኖ ነው የሚጠብቀው፡፡ ሁለቱ ተጣጥመው አያውቁም፡፡ ይሄ ዶ/ር አብይን ያሰጋቸዋል፡፡ ለዚህ ነው ኢህአዴግ የዶ/ር አብይን ሃሳብ ተቀብሏል ወይ? የምንለው፡፡ ግን ይሄን ሁኔታ የሚቀለብስ ወይም ለማዳፈን የሚሞክር፣ ከእንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ቦታ እንደማይኖረው ማወቅ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ቀኝ ኋላ ዙር አታውቅም፤ ኢትዮጵያውያን ለዶ/ር አብይ እድል እንሰጣቸዋለን ሲል በጥልቅ ምክንያታዊነት ነው፡፡ ይሄን ለመቀልበስ የሚያስቡ ሰዎች፣ ኒውክለር ቦንብ ሊፈነዳባቸው እንደሚችል አድርገው ነው ማሰብ ያለባቸው፡፡
ነገዳዊ ብሔርተኝነትና ኢትዮጵያዊነት እንዴት ይታረቁ?
  “እኔ ብቻ ነኝ የተበደልኩት፣ እኔ ብቻ ነኝ ለዚህች ሃገር የሰራሁት፣ እኔ ብቻ ነኝ ጀግና” የሚል አሰተሳሰብ ሲከስም ነው፣ ኢትዮጵያዊነት እያበበ የሚሄደው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአማራው ለሃገሩ ብሎ ካራማራ ላይ መሞት፣ የኦሮሞው አድዋ ላይ መሞት፣ የትግሬው መተማ ላይ መሞትን ያለ ምክኒያት አላነሱም፡፡ እኔ ብቻ ነኝ የሚለውን የነገዳዊ ብሔርተኝነት አስተሳሰብ ለመስበር ነው፡፡ ሃይማኖት፣ ዘር፣ ቋንቋ ሳይለየን ነው ለሃገራችን የወደቅነው የሚል ትርጉም ያለው ንግግር ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ዶ/ር አብይ በአፋጣኝ ለምሁራኑ ፍኖተ ካርታቸውን ሰጥተው መፍትሄ እንዲያፈላልጉ ማድረግ አለባቸው፡፡ 27 ዓመት ሙሉ የተገነባው ነገዳዊ ብሔርተኝነት ስር እንደሌለው መረዳት አለብን። የጠነከረ ስር ቢኖረው ኖሮ፣ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በተደረገ ንግግር፣ የጉዳዩን አቀንቃኞች ወደ ዝምታ አይገፋም ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊነት የጠነከረ ስር አለው፡፡ እርግጥ ነው ታሪካችን የተገነባው በጎራዴ እንደመሆኑ ብዙ ስህተቶች አሉበት፤ ግን ያም ሆኖ ኢትዮጵያዊነት ጠንካራ ስር አለው፡፡
ከተቃዋሚዎች ምን ይጠበቃል?
በመጀመሪያ ደረጃ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለአቅመ ተቃዋሚነትም ያልደረሰ፣ የባላንጣነት ፖለቲካ ነው። ዶ/ር አብይ ተፎካካሪ ብለዋል፡፡ ግን ተፎካካሪነት የሚኖረው በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ መግባባትና ስምምነት ሲኖር ነው፡፡ በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ላይ ድርድር መቀመጥ ሳይስፈልግ ስንግባባ ነው። አንድ ሰው በቋንቋው ስለተናገረ፣ ሃገር ፈረሰች ብሎ መደንፋት አያስፈልግም፡፡ ህዝብ በራሱ ሰዎች መተዳደርን መምረጡ ስህተት አይደለም፡፡ የፉክክር ፖለቲካ የሚሰራው፣ የመርህና አጠቃላይ ድባባዊ ልዩነት ሳይኖር፣ በአሰራርና በፖሊሲ ልዩነት ውስጥ ብቻ ለምርጫ መቅረብ የሚችል ፓርቲ ሲኖር ነው። እኛ የባላንጣነትና የነፃ አውጪነት ፖለቲካን ነው ስናካሂድ የኖርነው፡፡ ለዚህ ነው ዶ/ር አብይ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት አለባቸው የምንለው፡፡ ምናልባት ይህ ሲሆን በአዲስ አስተሳሰብ የተቃኙ ፓርቲዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያን ከአደጋ የሚታደገው ቀስ በቀስ የሚደረግ ለውጥ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ችግሮች ቢኖሩባቸውም፣ ራሳቸውን ከባላንጣ ፖለቲካ በማላቀቅ፣ የለውጥ አቀንቃኞች መሆን አለባቸው፡፡
አሁን ያሉት ተቃዋሚዎች ሁለት ነገር ማድረግ አለባቸው፡፡ አንደኛ የውስጥ ንትርካቸውን ትተው፣ እዚህ ጀልባ ላይ አለን፣ የለንም ብለው ራሳቸውን ይጠይቁ፡፡ ሁለተኛ ህዝብ የሚወክሉ መሆን አለባቸው። ከህዝብ ጋር ተገናኝተው ሃሳባቸውን ሸጠው፣ ድጋፍ ማሰባሰብ አለባቸው፡፡ አሁንም እንደ ድሮው እዚያው ተቸክለው፣ ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥምን የሚዘምሩ ከሆነ፣ ስህተት ነው፡፡ የለውጡ አካል የሚያደርጋቸውን ስልት መንደፍ አለባቸው። አንዳንዶቹ ፖለቲካውን አያውቁትም፤ስለዚህም ለአዲሱ ትውልድ መድረኩን ሊለቁ ይገባል፡፡      

Read 2140 times