Sunday, 29 April 2018 00:00

ምንኩስናና የኢትዮጵያ ፍልስፍና

Written by  ዳዊት ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

 (በደ/ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ መምህር)

    የኢትዮጵያ ፍልስፍና እና/ወይም የአፍሪካ ፍልስፍና አለ/የለም የሚለው ትርክት እንዳለ ሆኖ በኢትዮጵያ የፍልስፍና ስራዎችና እሳቤዎች ላይ ይህ ነው የሚባል ሥራ ተሰርቶበታል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። እንደ ሌሎቹ ዘርፎች የኢትዮጵያ ፍልስፍና ላይ ይህ ነው የማይባል ባይሆንም በሃገር ውስጥና በውጭ ተመራማርያን የተሰሩ አንዳንድ ጥናቶች ከዚህ በመቀጠል በተዛማጅ ጥናት ተዳሰዋል፡፡ በሌላ በኩል፣ በጣልያንና፣ በጀርመንኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋ የተሰሩ ጥናቶችን ከቋንቋዎቹ እጥረት የተነሳ መዳሰስ አልተቻለም፡፡ በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛና በግእዝ (እንደ አስፈላጊነቱ) ያሉ ድርሳናትና ጥናቶች ናቸው የተዳሰሱት፡፡
የኢትዮጵያን ፍልስፍና በማጥናትና በዓለም በማሳወቅ የክላውድ ሰምነርን ያክል ውለታ ለኢትዮጵያ የዋለ የለም ማለት ይቻላል፡፡ የዘርአ ያዕቆብን ብሎም ሌሎቹን የኢትዮጵያ የፍልስፍና ስራዎችና ሰዎች በማጥናት ቀዳሚ ነው፡፡ በተከታታይ የመጽሐፍ ቅጾችና የጥናት ጽሑፎች የኢትዮጵያን ፍልስፍና በሚገባ አጥንቶታል፡፡ The Source of African Philosophy. The Ethiopian Philosophy of Man የተባለው ስራው አንዱ ነው፡፡ መጽሐፉ ሶስት ክፍሎች ሲኖሩት፤ አንደኛው፣ Vertical Dimension of Ethiopian Philosophy በሚለው ክፍል ስር ስለ ሃገሪቱ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ኃይማኖት፣ ጎሳዊ ቅድመ መገኛ፤ እንዲሁም ፍልስፍናዊ ስራዎችን ማለትም መጽሐፈ ፈላስፋ፣ መጽሐፈ ስክንድስ፣ ፊሳልጎስ፣ እና የዘርአ ያዕቆብና ወልደ ሕይወት ድርሰቶች ጠቅላላ መረጃና የይዘት ማብራሪያ ይሰጣል፡፡ ሁለተኛው ክፍል Horizontal Dimension of Ethiopian Philosophy የተሰኘው ደግሞ ስለ ጥበብ፣ እሳቤ፣ ሰው፣ ማኅበረሰብ፣ ሞራሊቲ/ግብረ ገብ፣ ዓለም፣ ሥነ ምግባር እና መሰል ጭብጦችን መጻሕፍቱ ላይ ይተነትናል፡፡ ሶስተኛው The Pearls of Ethiopian Sapientail and Philosophical Literature የተሰኘው ክፍል ከላይ የተጠቀሱትን አምስቱን ድርሳናት እንደወረደ በእንግሊዝኛ ትርጉም ያቀርባቸዋል፡፡
የዚህ ጽሑፍ ትኩረት፣ የብሩህ ዓለምነህ የኢትዮጵያ ፍልስፍና የዘርአ ያዕቆብና የወልደ ሕይወት ሐተታዎች ትንታኔ ከነሐተታቸው የተሰኘው በ2009 ዓ.ም የታተመው መጽሐፍ የዘርአ ያዕቆብንና የወልደ ሕይወትን ፍልስፍና በጥልቀት ለመዳሰስ የሞከረ በአማርኛ የቀረበ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ በሶስት ክፍሎች የተከፈለ ነው፡፡ የመጀመሪያው ክፍል ትንታኔ ይሰኛል፣ በውስጡ 14 የሚሆኑ ንዑሳን ክፍሎች አሉት፡፡ የዘርአ ያዕቆብ የሕይወት ታሪክ፣ የፍልስፍና አምዶች፣ ስለ ምንኩስናና ተያያዥ ጉዳዮች፣ ልቦና የዘርአ ያዕቆብ የማስተማሪያ ዘዴዎች፣ ስለ ተፈጥሮ፣ ልቦናና እግዚአብሔር፣ ህልውናነት፣ ስለ ኢትዮጵያዊነቱ ክርክር፣ ስለ ነገረ ሴት፣ የዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ እይታ በዘርአ ያዕቆብ ላይ እንዲሁም የወልደ ሕይወት ፍልስፍናና ማጠቃለያ በዚህ ክፍል የቀረቡ ናቸው፡፡ ሁለተኛው ክፍል ሃገራዊ ቁጭት ይሰኛል። አክሱማዊነትና ላሊበላዊነት፣ የኢትዮጵያ ስልጣኔ እንዳውሮፓ ለምን መቀጠል አልቻለም በሚል ሃሳብ ስር ጥንታዊውን ስርዓተ ትምህርትና የነገሥታቱን የዘመናዊነት ፕሮጀክት ያለው እይታ አቅርቦበታል። በሶስተኛው ክፍል ደግሞ የዘርአ ያዕቆብና የወልደ ሕይወት ሐተታዎች (የዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ ትርጉም) እንዳለ ቀርበዋል፡፡    
ስለ ዘርአ ያዕቆብና ወልደ ሕይወት ፍልስፍናዎች፣ ከፍልስፍና ዘርፎችና እይታዎች አንጻር ጥሩ ትንተናዎችንና እይታዎችን አስቀምጧል፡፡ አንዳንድ ደግሞ ጭፍን ድምዳሜ ያስቀመጠባቸው ነጥቦች አሉ፤ አንደኛው ምንኩስና ነው፡፡ ጸሐፊው ምንኩስናን የስንፍናና የስራ ፈትነት መገለጫ ያደርገዋል፤ አልፎም በኢትዮጵያ ለፍልስፍና አለመዳበር/አለመቀጠል ተጠያቂ አድርጎ ይፈርጀዋል፡፡
ምንኩስናው በራሱ ከፍተኛ የሆነ የስራ ባህል ያለበት ነው፡፡ የስራ ፈጠራ ባለሙያዎች የሚያበረታቱት አንድ ብሂል አለ፤ “ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል” ይላል፡፡ ካለመስራት መስራት ይሻላል፡፡ አእምሮ ስንፍና (ኃጢአት) እንዳይሰለጥንበት ሰው (ስጋ) ያለ እረፍት መስራት እንዳለበት በመነኮሳት ዘንድ ይታመናል፡፡ መጽሐፈ መነኮሳት ላይ “በሰነፍ አእምሮ ኃጢአት ይነግሳል” አይነት መንፈስ ያለው አባባል አለ፡፡ በምንም አይነት ሁኔታ ስንፍና አይደለም ዕረፍት አይፈቀድም፡፡ ለስራ መትጋት ደንቡ ነው። በገዳም ውስጥ የሚኖሩ አባቶችና እናቶች ከፍተኛ የሆነ የስራ ባህል ያላቸው ሲሆኑ የስርዓቱ ዘዬም ለስራ ያስገድዳቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ብዙዎቹ ገዳማት በልማት የበለጸጉ ናቸው፡፡ ጸሎት ብቻ እያደረሰ ስራ ፈትቶ የሚቀመጥ መነኩሴ የለም፡፡ በኢትዮጵያ የጥንታዊው ዘመን ውስጥ በሥነ ጽሑፍና ኪነ ሕንጻ ላይ መነኮሳቱ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ የጥንታዊ ዘመን ትርጉም ሥነ ጽሑፎች አብዛኞቹ በተሰዓቱ (በዘጠኙ) ቅዱሳንና አቡነ ሰላማ (ፍሬምናጦስ) (ምንም እንኳ መነኩሴ ባይሆኑም የክርስትና መምህርና በኋላም የመጀመሪያው ጳጳስ የነበሩ) የተተረጎሙ ናቸው። የተሰዓቱ ቅዱሳን ገዳማት አብዛኞቹ በዘመናቸው የታነጹ ሲሆኑ ስራቸው ላይ ተሳትፎአቸው ሳይኖር አይቀርም፡፡ በጥንታዊው ዘመን መጠነኛ ጅማሮ አድርጎ በዛጉዌና ዘመን ዳብሮ በነበረው የድንጋይ ላይ የኪነ ሕንጻ ጥበብ መነኮሳቱ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ከድንጋይ ላይ ገዳም/ቤተ ክርስቲያን የማነጹ ስራ በወሎና በሸዋ አካባቢዎች የቀጠለ ሲሆን በገዳም የሚኖሩ መነኮሳት ራሳቸው በመዶሻ እየጠረቡ ውብ የኪነ ህንጻ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ህንጻ አብያተ ክርስቲያናት ይገነባሉ፡፡ ስለዚህ ምንኩስናንና መነኮሳትን በደፈናው በዓለም የሚከናወነውን ነገር ሁሉ እየተቃወሙ እንዲሁ ስራ ፈትቶ የሚቀመጡበት የኋላ ቀርነት ምሳሌ አድርጎ ማውሳት ስህተት ነው፡፡
ብሩህ፤ ዶ/ር ዳኛቸው “ነገሩን” ብሎ ያስቀመጠውን ቃል ለመቀበል የሚቸግር ነው፡፡ “የሥራ ባህላችን ላይ መሰረታዊ ችግር መፈጠር የጀመረው (የምንኩስና) ክርስትናን ከተቀበልን በኋላ ቁሳዊውን ስልጣኔ እርግፍ አድርገን ትተን መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ብቻ የሙጥኝ በማለታችን ነው፡፡” (ብሩህ፣ 2009፡ 177-178) ኢትዮጵያውያን መጽሐፍ ቅዱስን ባልተገባ መንገድ ተርጉመው ስራን ትቶ “ወደ ሰማይ ማንጋጠጥ”ን መርጠዋል ይላል፡፡ ከክርስትና በኋላ ግን በሥነ ጽሑፍ (ትርጉምና ወጥ ድርሰቶች፣ ቅኔና በትርጓሜው መራቀቅ) በፍልስፍናም፣ በኪነ ህንጻ (በተለይ ላሊበላ)፣ በሥነ ዜማ (ቅዱስ ያሬድ፣ አባ ጊዮርጊስ፣ አባ ፅጌ ድንግል) እና በሌሎችም ስልጣኔው ቀጥሎ ነበር፡፡ ከተጠቀሱት አብዛኞቹ ከክርስትና መምጣት በኋላ የተተገበሩ ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያ ስልጣኔ መውደቅ ምክንያቱን በክርስትና ማላከኩ አዋጭ አይደለም፡፡ ይልቁንም በቀይባህርና በዘይላ የባህር በሮች ላይ የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ ከእስልምና መነሳት በኋላ መዳከሙ፣ ጦርነቶች፣ እና መሰል በታሪክ ባለሙያዎች የሚጠቀሱ ምክንያቱን ማስቀደሙ የተሻለ ሳይሆን አይቀርም። የኢትዮጵያ ጥንታዊው ለምን (እንደ ምዕራባውያኑ ሁሉ) መቀጠል አልቻለም? ብሎ መቆጨቱ መልካም ሆኖ ሳለ፣ ክርስትናን ብቻ ለዚህ ተጠያቂ ማድረጉ ግዘፍ አይነሳም፡፡ ከተጠቀሰም በአመክንዮና መረጃ ተደግፎ እንደ አንድ ምክንያት መሆን ሲገባው፣ ሙሉ ለሙሉ ተጠያቂ ማድረጉ አግባብነት የለውም፡፡   
ክርስትናው እግረ መንገዱን ያበለጸገው ለሃገር የሚጠቅም በርካታ ትሩፋቶችም እንዳሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ የሌሎች ሃገሮች ኃይማኖቶች (ክርስትናም ይሁን ሌላ) ለየሃገራቱ እድገት የራሳቸው አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ሁሉ የኢትዮጵያ ክርስትናም ነበረው፡፡ አንድ ኩነት ስህተት ነው ተብሎ ሲነቀፍ፣ በመጀመሪያ ስህተት ተብሎ የሚቀርበው ጉዳይ በጠንካራ መረጃ የተደገፈ መሆን ይኖርበታል፤ ሲቀጥል የሚነቀፈው ኩነት ያበረከታቸው አወንታዊ  በረከቶች አብረው ቢወደሱ መልካም ነው፡፡
በእርግጥ የምንኩስና ሕይወት ዓለምን ስለ መናቅና ሰማያዊ ሕይወትን ስለ መሻት ተግቶ ይመክራል። ነገር ግን ሕይወቱ ለመነኮሳቱ ብቻ የተገደበ ነው፤ እንጂ ጠቅላላ ኢትዮጵያ ገዳም አልገባችም። መነኮሳቱ ዓላማቸው ስለ ሕዝብ/አገር መጸለይና ሰማያዊ ጽድቅን መፈለግ ነው፡፡ በዓለም የሚኖሩት ማለትም ዓለማዊ ሕይወትን የሚገፉት፣ የተቀረው ማኅበረሰብ ግን ዓለማዊ ስራን ከመስራት የሚያግደው ነገር የለም፡፡ በተጨማሪም ምንኩስና ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የተጀመረና የተተገበረ ነገር አይደለም፡፡ በምዕራባውያኑም ሆነ በምስራቃውያኑ ዘንድም የነበረ ነው፤ የሩቅ ምስራቆቹ (የቻይና፣ የጃፓን፣ የሕንድ) እምነቶችም ከምንኩስና ጋር የሚቀራረብ የብህትውና ሕይወት አላቸው፡፡ ስህተቶቹም፤ መልካምነቶቹም አብረው ነው እሚወሱት፡፡ የእኛ ሃገር ልሂቃን ድክመት ሆኖ በአብዛኛው የሚነቀሰው በኃይማኖት ረገድ በተለይ በክርስትና ላይ ድክመት ሲተቹ በአጥጋቢ ምክንያት ታጅበው ያለመሆንና አበርክቶትን ሳያካትቱ በጭፍን ድምዳሜ ላይ ቆመው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ክርስትና በመካከለኛው ዘመን ሳይንቲስቶችንና ፈላስፋዎችን በአደባባይ ያቃጠለች የሮማን (የአውሮፓ በአብዛኛው) ቤተ ክርስቲያን ያክል በዓለማዊ ምርምር ላይ ጥቃት አልፈጸመችም፡፡ ሌሎች (ባህል፣ ማኅበራዊ ህይወት፣ ስነ ልቦናዊ ስሪት፣ አስተሳሰብ፣ ኃይማኖቶችንና እምነቶችንም ጨምሮ) እድገታችንን በአጭር የቀጩ ምክንያቶችን መፈለጉና የጋራ ስምምነት ላይ ደርሶ መቅረፍ ለቀጣዩ ሁለንተናዊ መለወጣችን ፋይዳ አለው፡፡  
የኢትዮጵያ ፍልስፍና በሚለው የብሩህ መጽሐፍ ላይ ምንኩስናን አስመልክቶ የቀረበ ሌላ ስህተት አለ። ግርማ ሞገስን ጠቅሶ “ለዚህ ችግር” ብሎ ለጠራው የምንኩስና ሕይወት ዋነኛ ተጠያቂው “የአሌክሳንድርያ የኦርቶዶክስ ካህናት ናቸው” የሚለው ነው፡፡ ይቀጥልና “የምንኩስና ክርስትናን ለኢትዮጵያ ያስተዋወቁት፣ ያስተማሩትና የመጀመሪያዎቹንም ገዳማት የቆረቆሩት በ5ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ ላይ ከአሌክሳንድርያ የመጡ ዘጠኙ ቅዱሳን ናቸው” (መስመር የተጨመረ) ይላል፡፡ አስከትሎም ክርስትና ስለ ስጋዊና ዓለማዊ (አንድ ናቸው፣ ምናልባት አንደኛውን ምንኩስና/ብሕትውና ለማለት ይሆን?) ሕይወት የተለያዩ አተረጓጎሞች እንዳሉ ገልጾ “እኛ ግን በዘጠኙ ቅዱሳን ከአሌክሳንድር የተቀበልነው የምንኩስና ክርስትና ስጋዊና ዓለማዊ ሕይወትን  የሚጠየፍ፣ `ክርስትና ማለት ብህትውና ነው፣` የሚለውን ነው” (መስመር የተጨመረ)፡፡ ብሩህ ሁለት አይነት አንድምታ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላትን ያስቀምጣል፡፡ የመጀመሪያው መስራትን የሚያበረታታ (ስንፍናን የሚቃወም) ሲሆን ሌላኛው ደግሞ “ፍጹም መሆን ከፈለክ ያለህን ሁሉ ለድሆች አከፋፍልና ተከተለኝ” “(መንኩስ)” ያለው ነው (የማቲዎስ ወንጌል 19፡ 21)፡፡ ከሁለቱ ኢትዮጵያውያኑ ሁለተኛውን (ምንኩስናን) መርጠው ዓለማዊ ሕይወትን ፈጽመው እንደተጠየፉ ይነግረናል፡፡
እስክንድርያም ሆነች ኢትዮጵያ ኃይማኖቱን የተቀበሉት (ያመጡት) ከመካከለኛው ምስራቅ ነው። ክርስትናን በመቀበል ኢትዮጵያ ከእስክንድርያ ትቀድማለች (የሐዋርያት ሥራ 8፡ 26-40 - ክርስትና ከኢየሩሳሌም ሳይወጣ ገና በ34 ዓ.ም ከኢየሩሳሌም ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ቅዱስ ፊሊጶስ የተባለው ሐዋርያ እንደሰበከውና አምኖ ተመልሷል። ከዚያም በቤተ መንግስቱ ዙሪያ መስበክ እንደጀመረ ይታመናል)። ስለዚህ ከእስክንድርያ ጫና ሊደረግብን አይችልም፡፡ ከእስክንድርያ ጳጳስ ይመጣ ነበር፤ ክርስትናው ግን ከእስክንድርያ አልመጣም፤ ቀኖናና ዶግማም ቢሆን ክርስትና በአብዛኛው በአንድነት የሚመራበት ስርአት አለው፡፡ ቀኖና/ስርአት እንደየቤተ ክርስቲያኑ አውድ ሊሰራ ይችላል፡፡ አንድ የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት ከተለያዩም የየራሳቸውን ስርዓትና እምነት ሊገነቡ ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያና እስክንድርያ ከዋናው የኃይማኖቱ ግንድ እኩል ይወርሳሉ እንጂ አንዱ በአንዱ ላይ አይጭንም፡፡ ለምሳሌ በአላትን ብንወስድ ብዙ ሰው እስክንድርያውያኑ በኢትዮጵያ ላይ የጫኑት ያስመስሉታል፡፡ እስክንድርያም፣ ኢትዮጵያም ሆኑ ሮማ የሚዘክሯቸው የቅዱሳን መታሰቢያ በአላት አሏቸው፡፡ ኢትዮጵያም ከ30 እስከ 30 በዓልም ስታከብር አትኖርም፣ አልኖረችም፤ ከጥቂቶቹ በቀር አብዛኛው በዓልም ታስቦ፣ በሚዘከረው ቅዱስ የሕይወት መንገድ ሌላው ሰው እንዲጓዝ በማለም ታስቦ ይውላል። ምንኩስናንም እንደዚሁ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በምንኩስና ውስጥ ሆነው አርፈው አይደለም እሚቀመጡት፤ ከመንፈሳዊው ባሻገር ለስጋ የሚሆናቸውን ስራም ይሰራሉ፡፡ እንዲሁም ሁሉም ስለማይመነኩሱ፣ አብዛኛው ህዝብ ዓለማዊ ሕይወትን የሚመራ ነው፡፡ ሌሎች ምክንያቶች ከሌሉ በቀር ዘመናዊ ብልጽግናን የሚያጎናጽፍ ነገር ላለመቀበል የጥቂት ምንኩስናን ምርጫቸው ያደረጉ ሰዎች በምንኩስና መኖር አያግደውም፡፡  
ዘጠኙ ቅድሳን ከእስክንድር መጡ ያለው ስህተት ነው፡፡ ከዘጠኙ ቅዱሳን ውስጥ አባ አረጋዊ፣ አባ ገሪማ እና አባ ጴንጤሌዎን የመጡት ከሮም፤ አባ አፍጼ እና አባ ይምዓታ ደግሞ የመጡት ከታናሽ እስያ (ቱርክ)፤ አባ ጎባ ከልቅያ (ምስራቅ አርመን)፤ አባ ሊቃኖስ እና አባ ጽሕማ ከቁስጥንጥንያና ከአንጾኪያ (በግሪክ ግዛት ስር የነበሩ) እና አባ አሌፍ ከቂሣርያ የመጡ ናቸው። ስለዚህ ዘጠኙ ቅዱሳን ከእስክንድርያ ሳይሆን ከአውሮፓና እስያ በኃይማኖት ግጭት ሳቢያ ተሰደው የመጡ ናቸው፡፡
ማንኛውም ኃይማኖት የሚሰብከው ሰማያዊውን ወይም ከሞት በኋላ የሚመጣውን ሕይወት ነው፡፡ አንድም ኃይማኖት ምድራዊ ሕይወትን አይሰብክም። አስተምህሮን ዓለምን ንቆ ለዘላለማዊው ዓለም ያጋደለ ማድረግ፣ የአብዛኛዎቹ ኃይማኖቶች አሰራር ነው፡፡ እዚህ ላይ ዋናው ነገር ኃይማኖቱ በዓለም የሚከናወነውን ስልጣኔ “ውጉዝ”፣ እርኩስ አድርጓል ወይ? የሚለው ጉዳይ ነው። እንደምናውቀው ክርስትና ኑሮን ለማቅለል የሚደረጉ ዘመናዊ ግኝቶችንና ሥልጣኔዎችን አይቃወምም። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ይህን ታራምዳለች፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊም ነው፡፡ ለምሳሌ አውሮፕላን ቢሰራ፤ እግረ መንገዱንም በአውሮፕላኑ ላይ ቦንብ ተጭኖ ሚስኪናንን ቢገድል ግፉን ትቃወማለች፡፡ እናም በዓለም ላይ ዝሙት፣ ስካር፣ ግድያ፣ ስርቆት፣ ውሸት፣ ክፋት የመሰሉ ኢ-ፍትሃዊነትና መጥፎ እሴቶች ይተቻሉ፡፡ ይሄን ደግሞ ዓለማዊው እውቀትም (ፍልስፍና፣ ሳይንስ) ይጋራዋል፡፡ እንደ አቶ ብሩህ አቀራረብ ግን ምንኩስናን ክፉ አድርጎ ከመክሰሱ ባሻገር በዓለም ላይ የሚከናወነውን (በጎም ቢሆን) ድርጊት አውግዞ፣ ገዳም ውስጥ እጅና እግርን አጣጥፎ ያለ ስራ መቀመጥ ነው፡፡
በክርስትና የተለያዩ አስተምህሮዎች አሉ፡፡ ዓለማዊ ሕይወት አለ፣ በጋብቻ ውስጥ ሆኖ ጽድቅን መስራት፤ በምናኔ/ በብህትውና/ በገዳማዊ ሕይወት መኖር አለ፡፡ እንግዲህ የምንኩስና ሕይወት በክርስትና አስተምህሮ ካሉት የመንፈሳዊ ሕይወት መንገዶች አንዱ ነው፡፡ እንደ ኃይማኖቱ አስተምህሮ የድህነት አንዱ መንገድ ተደርጎ ይታመናል፡፡ በኃይማኖት ዓይን አንድ ሰው በምንኩስናም ኖረ በዓለም ዋናው ቁም ነገር ከመንፈሳዊ ትዕዛዛት ሳይወጡ፣ ኢ-ፍትሃዊ ግብርን ሳይፈጽሙ፣ መልካም ትሩፋትን እየፈጸሙ መኖር ነው፡፡ ክፋት ተብለው ከተፈረጁት፣ ጽድቅን ያሳጣሉ ተብለው ከተፈረጁት ውጭ ሌሎች በዓለም የምንመለከታቸው ዘመናዊ ግኝቶች ሁሉ የሚኮነኑ አይደሉም፡፡ እናም ክርስትና ማለት ብህትውና ወይም ምንኩስና ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ክርስትና ኢየሱስ ክርስቶስን መምሰል ነው፡፡ ክርስቶስ ያስተማረውን የሕይወት መስመር መከተል ነው፡፡ በወንጌል ክርስቶስ ካስተማራቸው ውስጥ በርካታ ነገሮች አሉ፤ ምንኩስና አንዱ ብቻ ነው። ኢትዮጵያውያኑም ለዘመናት ይከተሉና ይተገብሩት የነበረው ይህንኑ ነው፡፡ ስለሆነም ክርስትና ማለት በርካታ የሕይወት ዘይቤዎች የተካተቱበት እንጂ ምንኩስና ብቻ ነው ብለው ተረድተዋል የተባለው ስህተት ነው፡፡ ለሃገሪቱ የስልጣኔ ታሪክ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተን ህዝብ “… ዓለምን ረስተን፣ ዓለምም እኛን ረስቶን፣ ማረሻችንንም እዚያው ማሳ ላይ ትተን ወደ ሰማይ ማንጋጠጥ ጀመርን፣ ዓለማዊ ህይወትን ንቆ በየገዳማቱ መመንኮስን ሙያ አደረግነው” (ብሩህ፣ 2009፡ 179)፡፡ ብሎ መግለጽ ምን ማለት ነው? በቃ ኢትዮጵያውያን በጠቅላላ በራችንን ዘግተን ለምህላ ተቀምጠን ነበር ማለት ነው? ሁሉም ዓለምን ዘግቶ መነነ ማለት ነው? እንዲያስ ከሆነ ዘራችን አንዴት ሊቀጥል ቻለ? የሚል ጥያቄም ሊነሳ ይችላል። ጸሐፊው ለምንኩስና ያለው አረዳድ አሉታዊና አድሏዊ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ ዘርአ ያዕቆብና ወልደ ሕይወት ምንኩስናን አይደግፉትም፣ ያጣጥሉታል፣ ሌላ የሕይወት ዘዴን ብሎም መንፈሳዊ የሕይወት ዘይቤን ይጠቁማሉ፡፡ የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ግን ስሜታዊነት በግልጽ እየተነበበበት፣ ህዝበ ምእመናኑንም ሆነ ቤተ ክርስቲያኗን በአንኳሰሰ መልኩ ነው የገለጻቸው፡፡ ለኢትዮጵያ ቀደምት ስልጣኔ በመሀል መቋረጥ ወይም አለመቀጠል እንደ ብቸኛ ምክንያት ያነሳው ምንኩስናን አለፍ ሲልም ካህናትን ነው፡፡ (ፈላስፎቹ ዘርአ ያዕቆብንና ወልደ ሕይወትን ጨምሮ አያሌ አሰላሳዮችና ልሂቃን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የቤተ ክህነትን ትምህርት የተማሩ ናቸው፡፡ ተራማጅና አብርሆትን ያቀጣጠሉ ነገሥታት (በአብዛኛው) የቤተ ክህነት ትምህርት የተማሩና ካህናትም የነበሩ ናቸው፡፡ ቤተ ክህነትም ለአያሌ ዘመናት የልሂቀት ማእከል ሆና አገልግላለች፤ ትምህርትን መርታለች፣ አቀጣጥላለች፡፡ ልሂቃኑ ለነቀፌታ የሚፈጥኑትን ያክል ለውዳሴም የዚያውን ያክል መትጋት (ውለታ መቁጠር) አስፈላጊ ነው፡፡ በዋናነት ግን ለጥንታዊ ስልጣኔያችን ጸንቶ አለመቀጠል ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን ኃይማኖታዊ እሳቤውንም ጨምሮ ሌሎችንም ሁሉ መዳሰስና መመርመር ያስፈልጋል፡፡
ይህ መሆኑ ለሁለንተናዊ መለወጥ አስፈላጊ ነው፡፡) በአንድ ህዝብ የስልጣኔ ጉዞ ላይ ለሚፈጠሩ መሰናክሎች በርካታ ምክንያቶች እንደየ አውዱ ከየማእዘኑ ሊጤኑ ይገባል። አንድን ንዑስ ኩነት በዚያ ላይ ቁንጽል እይታና ማስረጃ ይዞ መደምደም ተራ ውንጀላ እንጂ ምሁራዊ ብያኔ ሊሆን አይችልም፤ የክፍተቱ ጥንተ-መሰረትም ከጨበጣ ኩናኔና ጭፍን ችኩል ድምዳሜ ባለፈ ጥልቅና ሰፊ ምርምር ያሻዋል፤ ለጋራ መንገዳችን፡፡

Read 1293 times