Print this page
Sunday, 29 April 2018 00:00

የውይይትና ንግግር መጋረጃዎች ይገለጡ!

Written by  አብርሃም ገብሬ
Rate this item
(1 Vote)

       አገር እንድትበለጽግም ሆነ እንድትጎሳቆል የሚያደርጓት የራሷ ሰዎች ናቸው፡፡ የአንዲት አገር ሰዎች ሲደማመጡ፣ መተባበርና መደጋገፍ ይጀምራሉ። የውይይትና የክርክር ባህልም ያዳብራሉ። በመወያየታቸውና በመከራከራቸው፣ አገራቸውን ሊያበልጽጉ የሚችሉ አማራጭ ሃሳቦችን ያመነጫሉ። ልዩነትና ቅራኔ በመካከላቸው ቢፈጠርም፣ ተወያይተው ለመግባባት አይቸገሩም፡፡ የዚህ አይነቱን ባህል ዕውን  ያደረጉ ህዝቦች ያሉባት አገር፣ ሰርክ ወደ ተሻለ ዕድገትም ታዘግማለች፡፡ ለውይይት በራቸውን የከረቸሙ ሰዎች የበዙባት አገር ግን፣ ከመተባበርና ከመደጋገፍ ይልቅ፣ መነጣጠልና መጠላላት ሙያቸው ይሆናል፡፡ በመሃላቸው መደማመጥ ይከስምና መነታረክ በየስፍራው ይናኛል፡፡ ሰላም ይጨፈለቅና አመጽ የነገሮች ሁሉ ማዳወርያ ይሆናል፡፡ መከባበር ወደ ዳር ይገፋና መጠላላት የሰዎቹ አብይ መገለጫ መሆን ይጀምራል፡፡ ይህ የእርስ በርስ የመጠላለፍ ዳፋም፣ ለአገር ይተርፋል፡፡ የዚህ አይነቱ ልማድ መዳረሻው፣ የአገሩም የሰዉም መጎሳቆል ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው የአንዲት አገር ልማት፣ የሰዎቿ ጥረትንና ትጋትን ሲያመለክት፣ የአገሪቱ ጉስቁልና ደግሞ የሰዎቿ ስንፍናንና ግዴለሽነትን የሚጠቁመው፡፡
ለመተባበርና ለመደጋገፍ ዝግጁ ባለመሆን፣ ሃገራችን ወደተሻለ ደረጃ ለመሸጋገር የምትችልባቸው ታሪካዊ ዕድሎች በተደጋጋሚ ተጨናግፈዋል። የተለያዩ ዕድሎች በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠሙ ቢሆንም፣ አልተጠቀምንባቸውም። ባለመተባበርና ባለመደጋገፍ  ነበር - ወርቃማ ዕድሎቹ የትም ባክነው የቀሩት፡፡  ባመለጡት ዕድሎች በመቆጨት፣ ወደፊት የሚመጡ  ሌሎች  እድሎች እንዳይጨናገፉ ለማድረግ ብልሃቱና ትግስቱ ይጎድለናል፡፡ ከጥቂቶች እፍኝ ጥቅም ተሻግሮ፣ በትልቁ ምስል ስር ለመሰባሰብ ብልሃቱም ሆነ ቀናነቱ ያጥረናል፡፡
እርግጥ ነው ኢትዮጵያውያን በታሪክ መድረክ ላይ የሚታወሱላቸው ብዙ አኩሪ ዕሴቶች ባለቤት ናቸው። በተደጋጋሚ የተቃጣባቸውን የውጭ ወረራዎች፣ ‘አሻፈረኝ’ በማለት የነጻነት ተምሳሌት መሆን ችለዋል። በህዝቦች መተባበርና መደጋገፍ፣ ለአገራቸው ነጻነት የተዋደቁባቸው ድንቅና አኩሪ ድሎችም በታሪክ መዝገብ አጽፈዋል። ህብረት በመፍጠር፣ ታላቅ የነጻነት ተጋድሎ አድርጎ ማሸነፍ እንደሚቻል ለሌሎችም ጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት ሆነዋል፡፡ በገዢዎቹ ተበድሎና ተገፍቶም፣ ‘አገርህ ተወረረች’ ሲሉት ግን፣ ለአገሩ ሉዓላዊነትና ነጻነት ህይወቱን ለመስጠት ወደ ኋላ የማይል፤ ጥልቅ የአገር ፍቅር ዕሴት እንዳላቸውም በተደጋጋሚ አስመስክረዋል፡፡ የባህልና የሃይማኖት ዥንጉርጉርነት ያልጋረደው፣ በህብራዊ ቀለማት ያጌጡ የመቻቻል ዕሴቶች ባለቤት ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ  እነዚህ እሴቶች፣ የአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ሊውሉ አልታደሉም፡፡ ለሃገር ህልውናና ብልጽግና ሲባል የህብረት አስፈላጊነትን ከታሪክ ማህደር መማር አልተቻለም፡፡ የመተባበር ውጤት የነበረው የአድዋ ድል መንፈስ፣ ወደ ፖለቲካችን መንደር ዘልቆ እንዲገባም አልተደረገም፡፡ “አመልህን በጉያህ…” ተብሎ ለአድዋ ዘመቻ የተላለፈው የጥሪ መልዕክት፣ የፖለቲካ ባህላችንን ለማሻሻል አልተጠቀምንበትም፡፡ ልዩነትን እንደያዙ አንድ በሚያደርጉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ዛሬም ድረስ ዳተኝነቱ አለቀቀንም፡፡
ሊኖሩን ሲገባ የሌሉን፤ ልንሞክራቸው ሲገባ ያልሞከርናቸው  ነገሮች በጣም ያስቆጫሉ፡፡ በሌሎች ኣገራት ሲተገበሩ ስናይና ስንሰማ፣ ‘ምነው አገራችን የዚህ አይነቱን ባህል ጸንሳ መውለድ ተሳናት?’ የሚያስብሉን፣ ዓይኖቻችን እንባ አቅርረው የሚያብሰከስኩን የሰው አገር እሴቶች አሉ፡፡ እኛ ያላዳበርናቸው፣ እነዚህ የሌሎች አገራት እሴቶች፤ ጠርዝና ጠርዝ ቆሞ በነገር ከመጠዛጠዝ ይልቅ፣ መሃል መንገድ ላይ ተገናኝቶ የመወያየት፤ የራስን ሃሳብና አስተያየት ‘በህዝብ ስም’ ወደ ታች ከመጫን ይልቅ፣ በመከራከርና የሃሳቦች ፍጭት እንዲኖሩ በማስቻል፣ ነጥሮ የወጣውን ሃሳብ የመቀበልና የማንበር፤ ‘ሃሳቤን አልተቀበለም’ በሚል፣ የተለያዩ ታርጋዎች ለጥፎ ከማሳደድና ከማሰር ይልቅ፣ የሃሳብ ዥንጉርጉርነት ተፈጥሮአዊ መሆኑን በመገንዘብ ምቹ ከባቢ መፍጠርን፣ ልንሞክራቸው እየተገባ ያልሞከርናቸው፤ ሊኖሩን እየተገባ ከሌሉን ውስጥ የሚጠቀሱ  ናቸው፡፡ ለታይታ ካልሆነ በስተቀር፣ ሃቀኛ ውይይትና ክርክር አድርገን፣ ትልቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትርጉም ያላቸው ውሳኔዎች ሲተላለፉ ያየንባቸው ወቅቶች እምብዛም ናቸውና፡፡
በታሪክ መጽሐፍቶቻቸው የምናውቃቸው ተ/ጻዲቅ መኩሪያ፣ ‘‘የህይወቴ ታሪክ’’ በተሰኘው ግለ-ታሪካቸው ውስጥ፣ በፈረንሳይ - ፓሪስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጸሃፊ ሆነው በተሾሙበት ወቅት፣ የተደነቁባቸውና የተገረሙባቸውን ነገሮች በመጽሐፋቸው አስፍረዋል። ያስገረማቸው ኢትዮጵያውያን የሌለንና ልናዳብረው ያልቻልነው ጉዳይ፣ የፈረንሳያውያን የፓርላማ ውስጥ የጦፈ ክርክርና የሃሳብ ፍጭት ባህላቸው ነበር፡፡ እሳቸው ፓሪስ የነበሩበት ያን ወቅት ደግሞ፣ ፈረንሳያውያን በሁለት ጎራ የተከፈሉበት ወቅት ነበር፡፡ በአንድ በኩል ‘ፈረንሳይ ከአልጄርያ አሁኑኑ ትውጣ’ በሚሉ የግራ ሃይሎች፣ በሌላ በኩል ‘ፈረንሳይ የባህር ማዶ ግዛቷ ከሆነችው አልጄርያ መውጣት የለባትም’ በሚሉ አክራሪ ብሄርተኞች መካከል፣ በፓርላማ ውስጥና በህብረተሰቡ መካከል የጦፈ ክርክር የሚደረግበት ወቅት ነበር፡፡ ተ/ጻዲቅም ከዕለታት በአንዱ የፈረንሳይ ፓርላማ ይታደሙና በህዝብ እንደራሴዎች መካከል ያዩትን ዱላ ቀረሽ ክርክር፣ ከሃገራቸው ሁኔታ ጋር በማነጻጸር ቁጭታቸው እንደሚከተለው አስፍረዋል፤»…እኔ በባልኮኒ ውስጥ ተሸጉጬ፤ ግራና ቀኝ የሁሉንም ነጻ ክርክር እያዳመጥሁ፤አንዳንድ ጊዜ ክርክሩ ወደ ሁካታና ወደ ጭብጨባ ሲለወጥ፣አሳቤ ወደ አገሬ እየሄደ፣ ‘እኛ ኢትዮጵያውያን መቼ ይሆን እንደዚህ ያለው እድል ላይ የምንደርሰው’ የሚል አሳብ ይመላለስብኛል።…የህዝብ ወኪሎች በምክር ቤትና ከምክር ቤት ውጭም፣ ጋዜጠኛውም ማናቸውም የህብረተሰብ አባል ያሰበውን ተናግሮ [እና] ጽፎ በመንግስቱ ላይ ነቀፋውን በመሰለው መንገድ ወርውሮ፣ በነጻ ወደ ቤቱ መሄዱ» ነበር አግራሞትና አድናቆት ያሳደረባቸው። የሃገራቸውን ሁኔታ ከፈረንሳያውያን የዳበረ የክርክር ባህል ጋር ሲያነጻጽሩት ነው የተንገበገቡት፡፡ የተቆጩትም፡፡ ይህ ቁጭት ግን ዛሬም ድረስ ዘልቋል። የተ/ጻድቅ ቁጭት፣ ግማሽ ምዕተዓመት ቢያልፈውም  የመወያየት፣ የመከራከር… በዚህ ሂደት ሃሳብን አንጥሮ በማውጣት የምናነብርበት የፖለቲካ ባህል አላዳበርንም፡፡ ኧረ እንዲያውም ከነበርንበት  ብዙም እንኳ ፈቅ አላልንም፡፡ እዚያው ተገትረን የቀረን ነው እሚመስለው፡፡ በዕውቀቱ ስዩም፣ በስብስብ ግጥሞቹ ውስጥ “ዘመን ሲታደስ” በተሰኘው ግጥሙ፣ ይኸው ቆሞ ቀርነታችንን ማለፊያ አድርጎ ይነግረናል፤
‘‘እኛ’ኮ ለዘመን
ክንፎቹ ኣይደለንም
ሰንኮፍ ነን ለገላው
በታደሰ ቁጥር፣ የምንቀር ከኋላው’’ -- በማለት፡፡
ኢትዮጵያን የተሻለች አገር ለማድረግ በተደጋጋሚ እንቅፋት ሆነው ከታዘብናቸው ነገሮች መካከል፣ ስልጣን የጨበጡትም ሆነ፣ የስልጣን ወንበር ላይ ለመቀመጥ ላይ ታች የሚሉት ልሂቃን፤ የ‘እኔ አውቅልሃለሁ’ ሰንካላ አካሄድ አንዱ ነው፡፡ በልሂቃኑ ‘የፖለቲካ’ መዝገበ ቃላት ውስጥ፣ እነሱ የማይቆጣጠሩት ቡድንም ሆነ ግለሰብ አራሽ ሃይል ነው፡፡ ‘አካሄዳችሁ ትክክል አይደለም’ ብሎ የሚተቻቸው ሰው፣በአንድ ወገን ‘ጸረ ሰላምና ጸረ ልማት’ ነው፤ ትችቱ በሌላኛው ወገን ከሆነ ደግሞ ‘የወያኔ ተላላኪ’ የሚል ታርጋ ሲያሰጥ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ‘የዕውቀትም የዕውነትም ምንጮች እኛ ብቻ ነን’ የሚያስብለው መንገድ ነው - የውይይትና የክርክር ጠር ሆኖ እዚህ የዘለቀው፡፡ የራስን ሃሳብ የበላይነት እንዲይዝ ለማድረግ፣ የሌሎችን ሃሳብ መድፈቅ እንደ አማራጭ መውሰድ ነው- ስንኩሉ አስተሳሰብ። ብዙኃኑ የራሱን ፍላጎትና ጥቅም እንደማያውቅ በመቁጠር፣ ራስን የብዙኃኑ ጥቅም አስከባሪ አድርጎ መሾም ነው - የፖለቲካችን ህመም፡፡ ሌላው የራሱ አስተያየትና ሃሳብ የሌለው ይመስል ፣ የእነርሱን ሃሳብ ብቻ እንደ ዶግማ ተቀብሎ እንዲፈጽም የመጠበቅ አካሄድ ነው - የፖለቲካችን ደዌ፡፡ በዚህ አይነቱ ፍረጃ ነው የፖለቲካችን መንገድ ተቀይሶ እዚህ የዘለቀው፡፡
የሃሳብ ዥንጉርጉርነት ወደ ዳር በመገፋቱ ምክንያት፣ ሃገራችንን ብዙ ዋጋ አስከፍሏታል፡፡ በፖለቲካ ከባቢያችን ውስጥ የጠርዘኝነት እንክርዳድ ስር እንዲሰድድ ሆኗል፡፡ ይኸው ዛሬም ድረስ ጠርዝና ጠርዝ ተቁሞ የነገር አሎሎ መወራወሩ  አላከተመም። እንዲያውም ተሟሙቆ ቀጥሏል እንጂ፡፡ መሃል መንገድ ላይ ተገናኝቶ የመነጋገርያና መወያያ መድረክ ባለመፈጠሩ፤ የሃሜትና የጥላቻ እንክርዳድ ተዘርቶ በየቦታው እየታጨደ ነው፡፡ ‘እኔ እናገራለሁ’፣ ‘አንተ ደግሞ ታዳምጠኛለህ’ ከሚለው አጥፊ መንገድ መውጣት አልተቻለም፡፡ ጤነኛ ውይይት ተካሂዶ የውይይቱ አሸናፊን ሃሳብ አንጥሮ በማውጣት፣ ገዢ ሃሳብ የሚሆንበት ከባቢም ሆነ መደላድሉ አልተበጀም።
በተቃዋሚው ሰፈርም ቢሆን የውይይትና የክርክር ባህሉ የቀጨጨ ነው፡፡ የሃሳብ ልዩነቶችን ተፈጥሮአዊ አድርጎ ከመገንዘብ ይልቅ፣ የጠብና የቅራኔ ምንጮች ሲሆኑ በተደጋጋሚ አስተውለናል፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ይመሰረትና አባላቱ ውስጥ የሃሳብ ልዩነት ሲፈጠር፣ ልዩነቱን እንደያዙ አንድ በሚያደርጉ ሃሳቦች ጥላ ስር ከመሰባሰብ ይልቅ፣ መከፋፈሉ ነው - ዋንኛው አማራጭ የሚሆነው፡፡ ከክፍፍሉ በኋላም አንዱ ወገን ቀድሞ የነበረውን ድርጅት ይዞ ሲያስቀጥል፣ ሌላኛው ደግም አዲስ ድርጅት መስርቶ ብቅ ይላል። ከዚያም አንጃና ክሊክ እየተባባሉ የነገርና የሃሜት ጦር መወራወር ይጦፋል፡፡ አንዱ ሌላኛውን ለማሳጣት እንቅልፍ አጥቶ ያድራል፡፡ ሁሉም በራሱ ጎራ አዛዥና መሪ መሆኑ እንዲታወቅለት መንጎራደድ ይሆናል፤ነገረ ስራው፡፡ የጎንዮሽ መጠዛጠዝ ይሆናል፤አላማና ግቡ፡፡ ነጥብ ማስቆጠር ይሆናል፤አንጃ ወይም ክሊክ በሚሉት ‘ባላንጣቸው’ ላይ፡፡ የሰከነ ክርክርና ውይይት አድርጎ፣ በሰላም የመለያየቱ ባህል በተቃዋሚው ሰፈርም ገና ጨቅላ ነው፡፡ የሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን፣ ‘‘እሳት ወይ አበባ’’  የተሰኘው ግጥም ውስጥ የሰፈሩት ስንኞች፣ የሃገራችን  ህመም  ምንጩን  የሚጠቁሙ ይመስለኛል፤
‘‘ይቅር ብቻ አንናገርም፣
እኔና አንቺ አንወያይም፣
ለውይይት አልታደልንም
እንዲያው ዝም እንጂ፣ዝም….ዝም…’’
 ዛሬ እኮ ትናንት አይደለም - ‘እውነትም መንገድም እኛ ነን’ የሚባልበት፡፡ ‘የእውነት ምንጭ ገዢዎች ናቸው’ የሚባልበት ዘመንም ዛሬ ታሪክ ሆኗል፡፡ ‘እውነት አንጻራዊና ከተለያዩ አውታራዊ ምንጮች ትቀዳለች’ ነው፤የዛሬው ዘመን ገዢ ሃሳብ፡፡ ሃሳቦችና አስተያየቶች ከተለያዩ አውታራዊ እይታዎች መምጣታቸውን ማበረታታት የመዘመን ምልክት ነው፡፡ደግሞም ረብ ያለው አገራዊ ተዋስኦ የሚኖረውና የሚበለጽገው ሃሳቦችን በመገደብ ሳይሆን፣ ወደ መድረኩ እንዲወጡ በማድረግ  ነው፡፡ ስለዚህ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት መኖር የሚያምን ማንኛውም ግለሰብ፣ የሚፈልገውንና የሚወድደውን ሃሳብ ብቻ ሳይሆን፣ የማይፈልገውንና የሚጠላውን ሃሳብ ጭምር፣ ወደ አደባባይ እንዲወጣ ፍላጎት ማሳየትና ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ይህንን በማድረጉም የመጀመርያ ተጠቃሚ እርሱ እራሱ እንጂ፣ ሌላ ሰው አለመሆኑንም መገንዘብ ያሻል፡፡
በዚች ሃገር ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማዋለድም ሆነ ለመገንባት፣ የንግግር ነጻነት በወረቀት ላይ ማኖር ብቻ ሳይሆን፣ ተተግባሪ እንዲሆን ተቋማዊ ጥበቃ የማግኘቱ ነገር ነው - እጅግ አስፈላጊው፡፡ መሬት ላይ ወርዶ ይበልጥ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ፤የንግግር ነጻነትን የሚገድቡ ሰንካላ አሰራሮች መነሳት ይኖርባቸዋል፡፡ ‘በህዝብ’ ስም የተሰየሙ መገናኛ ብዙኃንን፣ የእውነትም የህዝብም ማድረግ ያሻል፡፡ የተቆለፈባቸው የመናገርያ ቅጥሮች ከተከፈቱ፤ ህዝቡ በአገሩ ጉዳይ ላይ  አለኝ የሚለውን ሃሳብ ያዋጣል፡፡ መጋረጃዎቹ ከተገለጡ፣ ውይይቶችና ክርክሮች ይዳብራሉ፡፡ የተለያዩ አማራጭ ሃሳቦች ወደ መድረኩ የሚመጡ ከሆነ፣ የቸከው  የፖለቲካ ከባቢያችን ይነቃቃል፡፡ ህዝቡም ፍዝ ተመልካች ሳይሆን፣በንቃት ይሳተፋል፡፡

Read 1246 times