Print this page
Sunday, 29 April 2018 00:00

‘የአንድ ሰሞን አብሾ…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)


     “--እዚህ አገር ምን አለ መሰላችሁ… ‘የአንድ ሰሞን አብሾ’ አይነት ነገር፡፡ ልክ አትሌቶች የኦሎምፒክ ሜዳሊያ ባገኙ ቁጥር አገር ሁሉ ሯጭ ካልሆንኩ እንደሚለው፡፡ መለስ ብላችሁ ብታዩ፤ በ‘አንድ ሰሞን አብሾ’ ተጀምረው የቀሩ ነገሮች መአት ናቸው፡፡--”
        እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የምር ግን…ጥሬ ስጋ ለመቁረጥ የምናሳየውን ጥንቃቄና ትጋት ለሌላውም ሥራ ብናደርገው ኖሮ  “ማን፣ ኸረ ማን፣ ይደርስብን ነበር…” የሚባለው ዘፈን ብቻ ሆኖ አይቀርም ነበር፡፡ የምር እኮ…የዚች ለገለጻ አስቸጋሪ እየሆነች የመጣች ከተማችን ነገር ግራ ይገባል፡፡ እየዘመነች ነው አልተባለም እንዴ! አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች… “ምን አለ በሉኝ፣ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ኒውዮርክና ፓሪስን ባትስተካከል” ይሉን አልነበር እንዴ!  እናላችሁ…ይሄ የመንገድ ሥራ ነገር ግራ ይገባል፡፡ አሪፍ መንገድ ማየት ማን ይጠላል? “መሠራቱ ጥሩ ነው” ምናምን ስንል ከርመናል፡፡ ጥሩማ ነው! ግን ህዝቡ እስከ መቼ ነው እንደ ልቡ መዘዋወር የሚያቅተው? እስከ መቼ ነው የሚረገጥ መሬት ፍለጋ ወደ ዋናው አስፋልት እየገባ ራሱን ለችግር የሚያጋለጠው?!
“ለልማት ነው የፈረሱት” እየተባለ እንዲሁ በፍርስራሽ ተሞልተው ስንት ዓመት ባዷቸውን መክረማቸው ሲገርመን፣ አሁን ደግሞ መንገዶች! ተቆፍረው ምንም ነገር ሳይጀመርባቸው፣ በኮረትና በአቧራ ተሞልተው እንዲሁ የሚከርሙት ለምን እንደሆነ ግራ ይገባል፡፡ ልከ ነዋ… ከተገለባበጡ በኋላ ወዲያው የማይሠሩ ከሆነ ለምን መጀመሪያውንስ ይፈርሳሉ! ለምን መጀመሪያውንስ ከመሬት ውስጥ የጥንት ቅርሶች እየተፈለገ ይመስል ይገለባበጣሉ! እግረኛውስ መረማመጃ አጥቶ ለምን ይጉላላል!
አንዳንድ ስፍራዎች በአሪፍ መልክ ጽድት ብለው የተሠሩ መኖራቸው ጥሩ ነው። ከዓይንና ከዶማ ይሰውራቸው ያስብላል፡፡ ግን ደግሞላችሁ አንዳንድ ስፍራዎች ይጀመሩና የተወሰነ ርቀት ሄደው ለሳምንታት ቀጥ ይላሉ። በቃ ቀጥ! ይሄ ደግሞ የባሰው ነው፡፡ ያቺውም የተሰራችው መፈነቃቀል የጀመረባቸው፣ ጡቦቹ የተሰባበሩባቸው ስፍራዎች በርካታ ናቸው፡፡ ለሀያ ምናምን ኮንትራክተሮች ነው የተሰጠው አይደለም እንዴ የተባለው! የምር ግን…አንዳንድ አካባቢ የመንገድ ሥራው፣ አየር በአየር ሊመስል ምንም አይቀረው፡፡
እናላችሁ…ዘንድሮ ብዙ ስፍራ የግብር ይውጣ ሥራ፣ ነገሮችን እያበላሸ ነው፡፡ ይሄ የግብር ይውጣ ነገር፣ ይሄ የይድረስ ይድረስ ነገር…ይሄ “በል አፍርስልኝና የሚሆነው ይሆናል” አይነት ነገር ቀሺም ነው፡፡ ገና ለገና “ብቻ አዲስ አበባን ከመሬት መንቀጥቀጥ ይሰውራት!” የሚባልላቸው ህንጻዎች እዚህም፣ እዛም ስለበቀሉ እንደ መዘመን ምልክት ማየቱ ልክ አይደለም፡፡
እዚህ አገር ምን አለ መሰላችሁ… ‘የአንድ ሰሞን አብሾ’ አይነት ነገር፡፡ ልክ አትሌቶች የኦሎምፒክ ሜዳሊያ ባገኙ ቁጥር አገር ሁሉ ሯጭ ካልሆንኩ እንደሚለው፡፡ መለስ ብላችሁ ብታዩ፤ በ‘አንድ ሰሞን አብሾ’ ተጀምረው የቀሩ ነገሮች መአት ናቸው፡፡
‘አንድ ሰሞን’ መሥሪያ ቤቶች ዋና መግቢያቸው ላይ የተለያዩ ቢሮዎች ያሉባቸውን ፎቆችና የቢሮዎቹን ቁጥር መጻፍ ጀምረው ነበር። ማን ይጀምረው ማን ብቻ በአንድ ጊዜ የህንጻው መግቢያ ሁሉ በቢሮ መረጃዎች አሸበረቁ፡፡ እንደውም ፉክክሩ መረጃዎቹን በትላልቅ ፊደላት ጽፎ ዋናው በር ላይ ማድረግ ብቻ መሆኑ ቀርቶ ማሳመሩ ላይ ነበር፡፡ አሁን ግን… ብዙ ስፍራዎች ላይ እነኚህ የቢሮዎች መረጃዎች ወይ ተነስተዋል፣ ወይ ደግሞ ወይበውና አርጅተው እንዲሁም ፊደላቱ ተቆራርሰው ለማንበብ ያስቸግራሉ፡፡
አንድ ድርጅት ትሄዱና የሆነ ቢሮ ትፈልጋላችሁ፡፡ የጥበቃ ሠራተኛውን...
“የአቶ እከሌ ቢሮ ስንተኛ ፎቅ ላይ ነው?”
“የማን አልከኝ?”
“የአቶ እከሌ…”
“እንደዛ የሚባል ሰው እዚህ መሥሪያ ቤት አለ ብለህ ነው!”
“የጠቅላላ አግልግሎት ሀላፊ ናቸው፡፡”
የጥበቃ ሠራተኛው አንዱን ከርቀት ይጠራና… “ስማ፣ አቶ እከሌ የሚባል ሰው እኛ መሥሪያ ቤት አለ እንዴ?” ሲል ይጠይቃል፡፡ ከዚህ ሁሉ እሰጥ አገባ መጀመሪያ በሩ ላይ ተቀምጦ የነበረው መረጃ አይሻልም ነበር!
ምን ይደረግ…ነገርዬው ሁሉ የአንድ ሰሞን አብሾ ነበራ!
ለምሳሌ፣ አንድ ሰሞን የንግድ ሱቆች ሁሉ እቃዎቻቸው ላይ የመሸጫ ዋጋቸውን ይለጥፉ ተባለ፡፡ ከትንሽ እስከ ትልቅ የከተማችን ንግድ ቤቶች ለጠፉ፡፡ እኛም “እሰይ…” አልን፡፡ “መሰልጠን ማለት እንዲህ፣ እንዲህ ነው እንጂ” አልን፡፡ ቢያንስ፣ ቢያንስ ያለ አቅማችን አፋችንን አናጠፋማ! ግን ብዙም ሳይቆይ ዋጋ የሚገልጹት ጽሁፎች መነሳት ጀመሩ፡፡ ወዲያው ሁሉም እንደ ቀድሞው ሆነ። “ዘ ሴም ኦልድ ስቶሪ!” እንዲሉ የውጪ ሰዎች። ተመልሰን “ቀንስ…” “አልቀንስም…” ልምዳችን ውስጥ ገባን፡፡
“ይሄ ሱሪ ስንት ነው?”
“ስምንት መቶ ብር”
“ለዚህ! ይልቅ ቀንስልኝና ልውሰደው”
“እሺ ለአንተ ስል ሰባት መቶ ሀምሳ ብር ውሰደው”
“እዛ ማዶ ሱቅ እኮ አምስት መቶ ብር ብሎኛል”
“ታዲያ ለምን እዛው አትገዛም?”
ከዚህ ሁሉ ንትርክ ዋጋ መለጠፉ ቢቀጥል አይሻልም ነበር?
ምን ይደረግ…ነገርዬው የ‘አንድ ሰሞን አብሾ’ ነበራ! አለ አይደል… “እንቁልልጭ” አይነት ነገር ነበራ!
ለምንድነው መጀመር እንጂ መጨረስ የሚያቅተን! ያውም ብዙ ጊዜ አጀማመራችን ራሱ “የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” አይነት ሆኖ ማለት ነው፡፡ እናላችሁ…የምር እኮ ኮሚክ ነው፡፡ አንድ ነገር አንድ ሰሞን በቃ እንደ ጉድ ‘ሃይ፣ ሃይ’ ይባልና…ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቄሱም መጽሐፉም ዝም፡፡
አንድ ሰሞን የትራፊክ ቁጥጥሩ የጉድ ይሆናል። ብቻ ትንሽ ጥፋት ከታየች “ቁም” ብቻ ነው፡፡ የመኪና መስተወት ላይ ከቦሎ በስተቀር ሌሎች ለእይታ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች መለጠፍ አይቻልም ምናምን ይባላል፡፡ የመኪና መስታወቶች ሁሉ ጥርት ይላሉ፡፡ እንደውም መስታወቶቹ ላይ በተለጣጠፉ ወረቀቶች ብዛት አምፖል መብራት የሌለው ጓዳ ይመስላሉ፡፡ አንድ ሳምንት፣ ሁለት ሳምንት ይሆንና ሁሉም ነገር ቦታው ይመለሳል። የመኪና መስታወቶች የከተማዋን የኤሌትሪክ ምሰሶዎች ይመስል ወረቀት በወረቀት ይሆናሉ፡፡
ምን ይደረግ…ነገርዬው የአንድ ሰሞን አብሾ ነበራ!
በዛን ሰሞን ቢ.ፒ.አር. ነው የሚሉት ነገር መጣና በየመሥሪያ ቤቱ የምናየው የሥራ ፍጥነትና ትጋት ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ ተለወጡ። ሳምንታትና ወራት መመላለስ ቀረና ነገሮች በደቂቃዎች ማለቅ ጀመሩ፡፡ ግንባር ላይ ሀያ ምናምን እርከን ሠርቶ ያጠፋ ህጻንን እንደሚቆጡ አይነት “ምን ነበር?” ማለት ቀረና “ጌታዬ ምን ልርዳዎት?” አይነት ለመንግሥተ ሰማያት ጥቆማ የሚያበቃ አገልግሎት አሰጣጥ ተጀመረ፡፡ በርካታ መሥሪያ ቤቶች በእንቅስቃሴያቸው “በዚህ አይነት አገልግሎትማ ዓለም አቀፍ ሽልማት ያስፈልጋቸዋል” የሚባልላቸው አይነት ሆኑ፡፡
ሆኖም…ብዙ ሳይቆይ ነገሮች እንደገና ወደ ኋላ መንሸራተት ጀመሩ፡፡ ቀስ በቀስም “የዛሬ ሳምንት ተመለስ” ማለት፣ ግንባርን መከስከስ አይነት ነገሮች እንደገና ተመለሱ፡፡ ይሄ ቢ.ፒ.አር. የ‘አንድ ሰሞን አብሾ’ ነበር እንዴ!
ምን ይደረግ…ነገርዬው የአንድ ሰሞን አብሾ ነበራ!
እናማ…ይሄ የ‘አንድ ሰሞን አብሾ’… አለ አይደል… ‘ቦተሊካችን’ ውስጥም እንደ ልብ አለላችሁ፡፡ አንድ ሰሞን በቃ ነገሩ ሁሉ “ጭር ሲል አልወድም…” አይነት ይሆናል፡፡ ‘ንቃተ ህሊናችንን ለማዳበር’ የሚሞክረው የምሁሩ ብዛት መአት፣ የፖለቲካ ተንታኝ ብዛት፣ ንቃተ ህሊናችንን ለማዳበር የቴሌቪዥን፣ የሬድዮና የጋዜጣ፣ የዚህ ቡድን የዛ ቡድን አመራር ብዛት ለጉድ ይሆናል፡፡ አይደለም ማውራት ምናምን… ማስነጠስ እንኳን ፖለቲካ፣ ፖለቲካ ሊሸት ምንም አይቀረው፡፡
ከዛ ደግሞ የሆነ ነፋስ ይመስል የነበረው ነገርዬ ቀዝቀዝ ይላል፡፡ ይሄኔ ወላ ምሁር፣ ወላ ተንታኝ፣ ወላ ፖለቲካ መሪ ሁሉ እምጥ ይግባ ስምጥ ግራ ይገባል! ያ ሁሉ ፉከራስ! ያ ሁሉ “ሊበራል ምናምን…” “ኒኦ ምናምንስ?’ “ቦተሊካ ነፍሴ” አይነት ነገር ሌላ ዙር ይጠብቃላ!  ሌላ ነፋስ እስኪመጣ ይጠብቃላ! እናማ…ይሄም ሁሉ የ‘አንድ ሰሞን አብሾ’ ነው፡፡
ከ‘አንድ ሰሞን አብሾ’ ይሰውረን!!
ደህና ሰንብቱልኝማ

Read 5779 times