Sunday, 29 April 2018 00:00

አፍታ ለማለፊያዎቻችን

Written by 
Rate this item
(4 votes)

       የሥነ-ጥበብን ውስጥ ውስጡን ለመመርመርና ለማድነቅ ይቅርና ላይ ላዩንም ለመነካካት ቸልታ ከሚያሳይ ማኅበረሰብ የፈለቁት የሃገራችን ሠዓልያንና የሥነ-ጥበብ ማኅበረሰቡ፣ለሠፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ “ባርጤዛ” ሆነው ቆይተዋል። ሆኖም ሠዓሊውና የሥነ-ጥበብ ማኅበረሰቡ ይህ ተቃርኖ መኖሩን ፈጽሞ የማያውቅ እስኪመስል ለሙያው ባለው ልባዊ ፍቅርና ጽናት፣ ድንበሮቹን እየገፋ፣ ጭላንጭል ለውጦችን የሚያይበት ጊዜ እየመጣ ይመስላል፡፡ እዚህ ላይ በተለይ መንግስት ለሥነ-ጥበብ ያለው ጥልቅ ዝንጋዔ መቼ ሊሻሻል እንደሚችል ግምትም ሆነ መላምት ለማስቀመጥ አዳጋች ነው፡፡ እንዲህ ድንግዝግዝ ባለ ሁኔታ ስለ ሥነ-ጥበብ ማሰብና ማለም ደግሞ የጥበብ ልግስና ነውና ደስ ያሰኛል፡፡ ከላይ የጠቀስኩት ተቃርኖን የሚቃረን መልክ ባለው ገጽ ደግሞ የሃገር ባለ ውለታ የሆኑ አያሌ ሠዓልያን የሚገኙባት ሃገር ውስጥ መኖራችን የሚያስገርም ነው፡፡ ይህ ተለቅ ሲል ደግሞ እነዚህ የሃገር ባለ ውለታ የሆኑ ሠዓልያንን ያፈራ ታላቅና አንጋፋ ት/ቤትን እናገኛለን፡፡ ይህ ት/ቤት እንደ ተቋም በመንግስት ቢተዳደርም፣ ሕልውናው የተመሰረተውና የጸናው ግን ለሙያው ፍቅርና ቦታ ባላቸው ታላላቅ ሠዓልያን መስዋዕትነት ነው። ይሄ ደግሞ ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ እንደ ዜጋ የሚያኮራ፣ መንፈስና ነብስን የሚያጠግብ እንዲሁም የሕሊና ምቾት የሚሰጥ ነው፡፡ የዚህ አጭር ጽሁፍ ዓላማ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ውስጥ ለረዥም ዘመናት ያስተማሩትንና በቅርቡ ያረፉትን ቀራጺ ታደሰ በላይነህን በጣም በጥቂቱ ለማውሳት ነው፡፡
ቀራጺ ታደሰ በላይነህ ባጋጠማቸው ሕመም ለሶስት ወራት ህክምና ሲከታተሉ የነበሩ ሲሆን መጋቢት 29 ቀን 2010 ዓ.ም እስኪያርፉ ድረስ በት/ቤቱ ለሃምሳ ዓመታት በመምህርነት አገልግለዋል። እነዚህ ሃምሳ አመታት የማስተማር ብቻ ሳይሆን ሃገራችን የሥነ-ጥበብ ሙያተኞችን እንድታገኝ የማስቻል ኃላፊነትንም የሚጨምር ነበር፡፡ ለአስተዋጽኦዋቸው የሚመጥን ብሔራዊ እውቅና ባይቸራቸውም ባለፈው ሃሙስ በት/ቤቱ የመታሰቢያ ዝግጅት ተሰናድቶ የተዘከሩ ሲሆን ያስተምሩበት የነበረው አንዱ ስቱዲዮም በስማቸው ተሰይሟል፡፡
በቀድሞ ስያሜው የአዲስ አበባ ሥነ-ጥበብ ት/ቤት በመባል የሚታወቀው ይህ ተቋም የተመሰረተው ከስድሳ ዓመት በፊት ሲሆን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በልደታቸው ቀን ሐምሌ 16 ቀን 1950 ዓ.ም ነበር መርቀው የከፈቱት፡፡ የትምህርት ቤቱ መስራች አሁን በስማቸው የሚጠራው ሠዓሊ አለ ፈለገሰላም ሕሩይ ሲሆኑ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎችን ማስመረቅ ብቻ ሳይሆን ከተመረቁም በኋላ ወደ ውጪ ሃገራት በመላክ፣ ተምረው ሲመለሱም በትምህርት ቤቱ በመምህርነት እንዲቀጥሉ እድል መክፈት ችሏል፡፡ በዚህ እድል ተጠቃሚ ሆነው ወደ ቀድሞ ሶቭየት ሕብረት በማቅናት ትምህርታቸውን በLeningrad Repin Academy of Art ኪነ-ቅርጽ ያጠኑትና ወደ ሃገር ተመልሰውም በትምህርት ቤቱ ማስተማር ከጀመሩት ቀደምት መምህራን አንደኛው ታደሰ በላይነህ ናቸው፡፡
ጋሽ ታደሰ በላይነህ ከመምህርነታቸው ባሻገር በሙያቸው የተለያዩ ግልጋሎቶችን አበርክተዋል። በአዲስ አበባና በተለያዩ ክፍለ ሃገራት በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ቅርጾችን የሰሩ ሲሆን በጎላ ሚካኤልና በየካ ሚካኤል የሰሯቸው ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በዩጎዝላቪያ FORMA VIVA በተሰኘው የዓለም ቅርጻ-ቅርጽ አዋቂዎች ድርጅት ባደረጉት ተሳትፎና በቆይታቸው በሰሩት ስራም የዲፕሎማ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በአለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ከ1983 እስከ 1989 የኃላፊነት ቆይታቸውም፤ ትምህርት ቤቱን በዳይሬክተርነት የመሩ ሲሆን ተቋማዊ የኔነት እንደነበራቸውም በመታሰቢያቸው ላይ በሰፊው ተወስቷል፡፡ ለትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና መምህራን የመማሪያና የመስሪያ ስቱዲዮዎችን በማስገንባት ት/ቤቱ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋምነት እንዲሸጋገር የተጀመረውን ትግል አጠናክረው በመቀጠል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን እንዲቀላቀል ከፍተኛውን ድርሻ እንደተወጡ ተባባሪ ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን ገልጸዋል፡፡  
በሌላ በኩልም ጋሽ ታደሰ በላይነህ፤ የእንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ሲቋቋም፣ ምስረታውን በማገዝና አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፋቸውን በመቸራቸው የሚወሱ ታላቅ የሃገር ባለውለታ ናቸው፡፡ ጋሽ ታደሰ በላይነህ ካጠኗቸውና በአደባባይ ላይ ሊቀመጡ ከሚገቡ ቅርጾች መካከል የአጼ ቴዎድሮስ ኪነ-ቅርጽ እንደሚገኝበት የጠቆሙት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፤ በከተማችን ስለሚገኙና በውጭ  ዜጎች ስለተሰሩት ኪነ-ቅርጾች መሰረት ያለውና የተብራራ እውቀት እንደነበራቸውም  አውስተዋል፡፡
ይህች አፍታ እንደ ቀራጺና መምህር ጋሽ ታደሰ በላይነህ ያሉ ባለውለታዎቻችንን ለመዘከር እጅግ ቁንጽል ብትሆንም ጊዜና እርጋታው ተገኝቶ የሥነ-ጥበብ ታሪካችንን ለማጥናትና ለመሰነድ፤ የሥነ-ጥበብ ፍቅርና አክብሮት የሚኖረው ትውልድ ለመፍጠር የሚያስችሉ ጥረቶች በመንግስትና ሌሎች አጋዥ የማኅበረሰብ ክፍሎች እስኪጎለብቱ፣ማለፊያ የሆኑ ሥነ-ጥበባዊ ማንነቶችን ማውሳቱ ተገቢ ነው፡፡

Read 765 times