Sunday, 29 April 2018 00:00

የድሮና ዘንድሮ ወግ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

 “… እማማ ጠንካራ ናት፡፡ የታመመ ሰውን ሁሉ ትጠይቃለች፡፡ ያንን ሁሉ ሰው ስትጠይቅ ምግብ ሰርታ ትወስዳለች፡፡ ለቅሶ ቤት አካባቢ አትጠፋም፡፡ ብዙ ልብስ የላትም፣ ብዙ ቀሚስ አትቀይርም፡፡ ስትቀይርም ከበፊቱ ጋር ልዩነቱን ከእሷ በስተቀር ባሏም አያውቅም፡፡…”
   
    ዛሬ ታክሲ ውስጥ ድሮ “እ-ማ-ማ” ብለን የምንጠራትን አይነት ሴት አየሁኝ፡፡ ልጅ እንደ ድሮው በጀርባዋ አዝላለች፡፡ ጥቅል ጎመን የሚመስሉ ትልልቅ አበባ ያለበት ትልቅ ቀሚስ አድርጋለች፡፡
…ገና ሳያት “እማማ መጣች” አልኩኝ፡፡ የእኔ እናት መጣች ማለቴ አይደለም፡፡ በቃ “እማማ” የሚለው አብስትራክት ቃል፣ እኔ እንደሚገባኝ ሆኖ በሴት መልክ ሲገለፅ፣ ይቺን ሴትዮ ይመስለኛል ማለቴ ነው፡፡
እማማ ብዙም ውስብስብ አይደለችም፡፡ ትልልቅ ጡት አላት፤ ግን ለውበት ሳይሆን ለስራ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ …እማማ ታክሲ ውስጥ ገብታለች፡፡ breeders hip የሚባለውን ትልቁን ዳሌዋን ይዛ፡፡ ዳሌዋ ልጆች ወልዶ ለማሳደግ እንደተሰራ ያስታውቃል። ቢወለድበት… ቢወለድበት የማይደክም ነው፡፡ ፋሽን ሾው ለማሳየት ወይም ውድ ልብሶችን ለመልበስ የተሰራ አይደለም፡፡
…የታቀፈችውን ልጅ ወዲያው እንደተቀመጠች ማጥባት ጀመረች፡፡ የጡቶቿ ጫፍ እንደ ጡሩንባ አፍ ህፃኑ ላይ ለመጣበቅ የተሰሩ ናቸው፡፡ … እማማ ስለ ፖለቲካ አያገባትም፡፡ የሽንኩርት መወደድ ወሬ ከተነሳ ግን ጆሮዋን ጣል ታደርጋለች፡፡ በታክሲው መስታወት በግ እየነዳ የሚያልፈውን ነጋዴ ሳይሆን በጎቹን በደንብ በአይኗ ለካቻቸው፡፡ … በጉን አርደው በልተው ሲሰጧት፣ ማድቤት ውስጥ እንዴት ሙያ እንደምታስይዘው ታውቃለች፡፡ … የእማማ ሀሳቧ መሬት መግዛት ወይም ፎቅ መስራት አይደለም፡፡ ልጆቿን መመገብ ነው፡፡ ልጆቿን ከሰው እንዳያንሱ አድርጎ ማሳደግ፡፡ … ታክሲ ውስጥ ሰውን አታይም። ታስባለች፡፡ የምታስበው ስለ ወር አስቤዛና ስለ ልጆቼ ጤና ነው፡፡ የእጅ ቦርሳ አላት፡፡ እንደ ኤሮግራም ብዙ ቦታ ታጥፎ አንድ ቦታ የሚቆለፍ፡፡ … እማማ መጭበርበር አትወድም፡፡ ወያላውን መልስ እንዲሰጣት ደጋግማ ትነግረዋለች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴር፣ ኦህዴድ፣ ብአዴን… ብትላት ግር ሊላት ይችላል፡፡ ግን ፖለቲካው ላይ ችግር እንዳለ፣ ገበያ ሄዳ ሁሉም ነገር ሲወደድባት ታውቀዋለች፡፡
እንደዚህ አይነቷን ትልቅ ጡት፣ ትልቅ ዳሌና ትልቅ ኃላፊነት ያለባትን እማማ የሚመጥን፣ ሱሪውን ከፍ አድርጎ በመጠነኛ ቦርጩ ላይ የሚታጠቅ፣ ብዙውን ጊዜ ኮት፣ የተቀረውን ጊዜ ካፖርት የሚለብስ አባባ ይኖራል፡፡ ለአመት በዓል እንደምንም ብሎ በግ የሚገዛ። መኪና የሚይዝ ግን የሚይዘው መኪና የመስሪያ ቤት የሆነ፡፡ … በኪራይ ቤት እማማና ልጆቿን የሚያኖር አባባ አለ፡፡ ትልቅ ጥቁር ከዘራ የሚያክል ዣንጥላ ያለው፡፡ ሚስቱ የምታቀርብለት ምግብ ላይ የሚያማርር … ግን ቢያማርርም ጥርግ አድርጎ ሳይበላ የማይነሳ አባባ ይኖራል፡፡ … ድምፅ ቀንሶ ኢ-ሳት ቴሌቪዥን የሚያዳምጥ፡፡ የረባ ጋዜጣ ባይኖርም ቅዳሜ ጋዜጣ ገዝቶ ለምሳ የሚመለስ … ይዞ የተመለሰውን ጋዜጣ የሚያነብ፡፡ እማማ ጋዜጣውን አሳ ለመጥበሻ ወይ መስታወት ለመወልወያ ስታውልበት “ሀገር ይያዝ” ብሎ የሚጮህ የእማማ አባባ ይኖራል፡፡ ልጆቹን እግሩ ላይ ቼ - ፈረሴ እያለ እስከ አምስት ዓመታቸው ድረስ የሚያጫውት፡፡ … ከአምስት እስከ አስራ አምስት ዓመት ድረስ ልጆቹን በፊት ለፊት ሁሉም ነገር ላይ የሚቆጣ … በጓደኞቹ ፊት ስለ ልጆቹ ጉብዝና፣ “በተለይ ትንሽዋ እሳት ናት” እያለ የሚያወራ፡፡
…ሴትየዋን እያየሁ እማማና አባባ ትዝ አሉኝ፡፡ እኔ የማውቃቸውን አብስትራክት እማማነትና አባባነት አስታወሱኝ፡፡
…እማማ ጠንካራ ናት፡፡ የታመመ ሰውን ሁሉ ትጠይቃለች፡፡ ያንን ሁሉ ሰው ስትጠይቅ ምግብ ሰርታ ትወስዳለች፡፡ ለቅሶ ቤት አካባቢ አትጠፋም። ብዙ ልብስ የላትም፣ ብዙ ቀሚስ አትቀይርም። ስትቀይርም ከበፊቱ ጋር ልዩነቱን ከእሷ በስተቀር ባሏም አያውቅም። ከነጠላው ስር ተካፋች ሹራብ ታደርጋለች፤ እማማ ትምህርት አልተማረችም፡፡ ወይም እስከ አራተኛ ክፍል ተምራ ሊሆን ይችላል፡፡ አባባ አስራ ሁለተኛ ክፍል ጨርሷል፡፡ “ምን ከዘንድሮው ዲግሪ የድሮው ስድስተኛ ክፍል ይሻላል” የሚል ነው። ልጆቹ ግን ስድስተኛ ክፍል እንዲቀሩ አይፈልግም። ኮሌጅ በጥሰው ውጭ ሃገር ሄደው እንዲማሩለት ያልማል፡፡ ዘመድ ቢኖረው አሜሪካ ቢሰዳቸው ምኞቱ ነው፡፡ ግን ለጊዜው እንደ ምንም ተሟሙቶ የግል ት/ቤት ያስተምራቸዋል፡፡ … እንግሊዝኛ ቢጠላም … ህፃናቱ በእንግሊዝኛ የተማሩትን መዝሙር ሲያዜሙለት ልቡ በኩራት ይሞላል፡፡
…አባባና እማማ እንግዲህ እነዚህ ነበሩ። አሁን ቪትዝ የሚይዝ አባት መጥቷል፡፡ አባባ ልትለው አትደፍርም። እስኪኒ ሱሪና ቲ-ሸርት ነው የሚለብሰው። ሚስቱም እማማ አይደለችም፡፡ … ስሟም ሚጣ ነው። እናቷ “አዛለች” የሚል ስም ይዛ ነው ስምንት ልጅ አሳድጋ የዳረችው፡፡ ሚጣ አንድ ልጅ ወልዳ ደክሟታል። ትልቅ ጡት ቢኖራትም ብዙ አታጠባም። ብዙ ብታጠባም ማጥባቷ እንዳይታወቅ ደብቃ ነው፡፡ … ዘንቢል ተሸክማ ሾላ ገበያ ውላ መምጣት አትፈልግም፡፡ የወር አስቤዛ ከሱፐርማርኬት መሸመት ነው የሚቀላት። … ሰራተኛዋ አታከብራትም፡፡ የእናቷ ሰራተኛ ድሮ እንደምታደርገው፣ ውሃ አሙቃ የእማማና አባባን እግር አታጥብም፡፡ ሰራተኞቹ በሙሉ ከሚጣ የሚስተካከል ስፋት ያለው እስማርት ፎን አላቸው። ቃና ድራማ ሲያዩ ነው የሚውሉት፡፡ እነሱም አረብ ሃገር የመሄድ ህልም አላቸው፡፡
እማማና አባባ ሚጢና ጆኒ ሆነዋል፡፡ ኮንዶሚኒየም ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡ በቀላሉ ይወፍራሉ፡፡ ብዙ ሰዓት ቴሌቪዥን ላይ ያፈጣሉ፡፡ እድር የላቸውም። ከኤቲኤም ገንዘብ ያወጣሉ፡፡ ያወጡት ገንዘብ እንዴት እንደሚያልቅ አያውቁትም፡፡ … ሚጢና ጆኒ መስታወት ፎቆች ውስጥ የቢሮ ሰራተኛ ናቸው። … ሁለቱም የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው፡፡ ማስተርስ መስራት ይፈልጋሉ፡፡ ራዕይ ግን የላቸውም፡፡ … ከዚህ በፊት ብዙ የንግድ ሃሳቦችን አውጥተው አውርደው በአጠቃላይ ሀገሩ ላይ ተስፋ የሚሰጥ ነገር በማጣታቸው ትተውታል፡፡ እነሱን ያሳደጓቸው አባባና እማማ እነሱን ሲያሳድጉ በትምህርታቸው ቢገሩ የትናየት መድረስ እንደሚችሉ ባለሙሉ ተስፋ ነበሩ፡፡ ሚጢና ጆኒ ግን ልጆቻቸውን ሲያድጉ ምን እንደሚሆኑ ብዙም አያስቡም፡፡ … ድሮ ጆኒ ፓይለት መሆን ይመኝ ነበር፡፡ ሚጡም ሆስተስ መሆን በልጅነቷ ሳትመኝ መቼም አትቀርም፡፡ አሁን ግን ሁለቱም ምኞታቸው ባለመሳካቱ ደስተኛ ናቸው፡፡ እነሱ ሲያድጉ ፓይለትነት ተራ ነገር ሆኗል፡፡ … ዘፋኝነት የተሻለ ታዋቂ ያደርጋል። ፓይለትነት፣ ዶክተርነት፣ ኢንጅነርነት፣ ሳይንቲስትነት ድሮ ልጅ እያሉ ይሰጥ የነበረውን ትርጉም አሁን አይሰጥም፡፡ ገንዘብ መያዙ ይሻላል … ብለው ሚጡና ጆኒ ትንሽ ተፍጨረጨሩ፤ ግን ጥሩ ገንዘብ የሚያዘው በመፍጨርጨር እንዳልሆነ እነሱ በደረሱበት የፖለቲካ ዘመን ተረዱ፡፡ ተስፋ ባይቆርጡም - ተስፋ ማድረግ ግን አቆሙ፡፡  
…በሽፋን ደረጃ ሲታዩ ኮንዶሚኒየም ፎቅ ላይ መኖራቸው … ቪትዝ መኪና መግዛታቸው… ኮሌጅ መበጠሳቸው… ከወላጆቻቸው እማማና አባባ የተሻሉ ቢያስመስላቸውም … ግን እንዳይደሉ ያውቁታል፡፡
…ሚጡ እንደ እማማ ጣት የሚያስቆረጥም ምግብ ከወዳደቀ ነገር መስራት አትችልበትም፡፡ መብላትም ሆነ መስራት የሚችሉት ምግብ ጥብስ ብቻ ነው። ጆኒም በግ መግፈፍ አይችልም፡፡ እንጨት ላይ ሚስማር ለመምታት ይፈራል፡፡
እንደ አባቱ የእጅ መታጠቢያውን ፈትቶ አፅድቶ መልሶ መግጥም ስለማይችል ሰራተኛ ይቀጥራል፡፡ የቀጠረው ሰራተኛ ለቀላሉ ስራ የሚጠይቀውን ከፍ ያለ ብር ተደራድሮ ማስቀነስ አይችልም፡፡ ሥራውን ስለማያውቀው ያፍራል፡፡ ሴተኛ አዳሪ ጋ ለመተኛት እንደሚደራደር ሰው ብዙም ሳይከራከር ሰራተኛውን ከፍሎ ይሸኘዋል፡፡ … መኪናውን የሚያሳጥበው፣ ጫማውን የሚያስጠርገው፣ የወለዳቸውን ልጆች ቂጥ መጥረጊያ ዋይፐር የሚገዛው ገንዘብ ከፍሎ ነው። … በእሱ እድሜ ያሉትም ከእሱ የተለዩ አይደሉም፡፡ እነሱም ሚጢ የሆነች ሚስት አለቻቸው፡፡ … ቪትዝ የሚያስገዛ የኑሮ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ ከዛ በላይ የሱፐር ማርኬት የሸመታ ተመንን የሚሸፍን ስራ አላቸው፡፡
በቀጣይ ዓመታት የተስፋው መጠን ሳይሆን የልጆቻቸው ቁጥር እንደሚጨምር ይገመታል፡፡ የወላጆቻቸው ህልም ተሳክቷል፡፡ የልጆቹ ህልም ግን ባለበት እየረገጠ ነው፡፡ ባለበት የመርገጡን ምክንያት ከፖለቲካና ሀገራዊ ርዕዮተ ዓለም ጋር በቀላሉ ያያይዙታል፡፡ የተቃዋሚ ፖለቲከኞችን መጽሐፍ ይገዛሉ፡፡ ይገዛሉ እንጂ አያነቡም፡፡ … አባባና እማማን ለአመት በዓል እንደ ምንም በግ ገዝተው ሄደው ይጠይቃሉ። አባባና እማማ ብዙም አላረጁም፤ ልጆቻቸው ግን ሽበት በፍጥነት እየወረሳቸው ነው፡፡   

Read 1809 times