Sunday, 29 April 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(3 votes)


             “አገር ከነቃ መመለሻ የለውም”
              
    በቀደመው ዘመን “እውነተኛ ማርክሲስት እኛ ነን፤ እናንተ በራዦች ናችሁ” በሚል መንፈስ አንዱ ሌላውን አብሽቋል፡፡ እርስ በርስም ተበሻሽቋል፡፡
በወቅቱ ብዙ ህዝባዊ ስብሰባዎች ተደርገዋል። በአንዱ ላይ በተደረገ የሃሳብ ፉክክርና ውይይት፣ አንዱ ተናጋሪ የሶሺያሊዝምን ጥቅምና አስፈላጊነት አብራራ፡፡ የአካባቢው ህዝብ ለሃይማኖቱ ያለውን ጥብቅነት የሚያውቀው ተቀናቃኝ ደግሞ ተናጋሪውን ለማሳጣት፤ “እናንተ ሶሺያሊስቶች እግዜር የለም ትላላችሁ፣ እውነት ነው? … አይደለም?” በማለት ጠየቀ። ተናጋሪው፤ “አዎም” “የለምም…” ቢል ‹ጉድ!› ሊፈላ ነው፡፡ ተሰብሳቢው ይጣላዋል፡፡ “እግዜር የለም አንልም” ካለ ደግሞ … “እናንተን ብሎ ማቴሪያሊስት” ተብሎ መሳለቂያ ሊሆን ነው … ያውም በማስረጃ!! ሰውየው ማሰብ ጀመረ … ምን ይመልስ ይሆን?
***
ከኤሚሊ ዲክሰን ግጥሞች አንዷን እናንብብ፡-
Fame is bee;
It has songs,
It has sting,
O! God!
It also has wings … የምትለውን፡፡
የግጥሟ መንፈስ እንደገባኝ፣ እንዲህ የሚል ይመስለኛል፡-
ማስተዋል ነው ቁሞ፣
ማድመጥ ነው  በአርምሞ፣
መኖር ነው መሆን …፣
ሲታመሙ ታሞ፣
ሲድኑ መዳንን፡፡
ካላወቁበቱ -
   መደነስ በስልቱ፣
በሙዚቃው ቃና፣
ያነክሳል ጊዜ - ቀን ይነክሰውና!
አይጣልብህ እንጂ
ክፉ - ‹ቀን ጎዶሎ፣
አላልኩህም ይልሃል -
 የሚለውን ብሎ፡፡  
‹ብር› ብሎ ሊከንፍ
    ራቁትክን ጥሎ!!
‹ያንተ ያለህ!› ብትል
ማን ይሰማል ያኔ፣
‹ዝና› ንብ‘ኮ ነው -
‹ከቶ› አይረጋም … ወይኔ!!
ወዳጄ፡- እያንዳንዱ ሰው ከሌላው እሚለየው የራሱ ፀጋ አለው፡፡ ለዚህም ነው … አንዳችን ለሌላችን ተማሪዎች የምንሆነው፡፡ … ሁሉም ት/ቤት ብትሄድ መምህርህ ሰው፣ መጽሃፍ ብታነብ ደራሲው ሰው፣ ሬዲዮ ብታዳምጥ የሚያወራልህ ሰው!! … ልዩነቱ ዓይኖች ሁሉ ዕኩል አለማየታቸው፣ ጆሮዎች ዕኩል አለማዳመጣቸው፣ አፍንጫ ዕኩል አለማሽተቱ፣ ምላስ ዕኩል አለማጣጣሙ፣ እግሮች ዕኩል አለመሮጣቸው ወዘተ … ሊሆን ይችላል፡፡ አቀባበላችንና አረዳዳችን እንደሚለያይ አተረጓጎማችንም ይለያያል፡፡ ፀጋችን ለየቅል ነው ስንል፣ ዕውቀትና ችሎታችንን አጠቃቀማችንም ለየብቻ ነው ማለታችን ነው፡፡
አንድ ጥናታዊ ፀሐፊ፡- “በአንባቢዎች ሃገር ሰዎች በቀለም ይታጠባሉ፣ ቀለም አንዳንዶቹን ውብ፣ ቆንጆና አዲስ ያደርጋቸዋል፣ አንዳንዶቹን ይመርዛቸዋል፣ አንዳንዶቹን ይደብቃቸዋል” ይላል። የምታነቡትንና የምትሰሙትን ምረጡ ማለቱ ነው፡፡ … የምናነበውን ነገር ከመረጥን ከጠቢባን ጋር እናወራለን፣ እርስ በርስ በመነታረክና ቡቱቶ ስናግበሰብስ ዕድሜያችን አይባክንም። … ቀምሰን የምንተዋቸው መጽሐፍቶች ብዙ ናቸው፤ አንዳንዶቹን እንዳሉ እንውጣቸዋለን፣ ጥቂቶቹን ግን አኝከን፣ አጣጥመን እንመገባቸዋለን (Some books are to be tested, others to be swallowed, and some few to be chewed and digested) የሚለን ፍራንሲስ ቤከን ነው፡፡
ብዙ ሊቃውንት አእምሮ ማለት ሰውየው፣ ዕውቀት ደግሞ አእምሮ ነው፡፡ ሃሳቡና ሰውየው ሲጋቡ ብሩህ፣ ጤነኛና ጠንካራ ሰው ይወለዳል፡፡ ስፖርት ለሰውነታችን ጥንካሬ እንደሚያሻ፣ ንባብ ለአእምሯችን ግድ ነው (As exercise is to the body, reading is to the mind)… ይላሉ፡፡
ወዳጄ፡- “አንባቢዎች መሪዎች ናቸው” (Readers are leaders) ይባላል፡፡ እውነት ነው። ይህ ማለት ግን ስልጣን ሳይሆን ተግባርን፣ ሹመት ሳይሆን ችሎታን፣ ከስልጣኔ፣ ከኃላፊነትና ከግብረ ገብነት ጋር በማዛመድ የታሰበ አባባል ነው። … በንፅፅር ሲታይ፤ አንባቢዎች በጎሳ፣ በቀለም፣ በሃይማኖትና በአኗኗር ልዩነት የማያምኑ ወይም ያልተበከሉ (None infected) ናቸው፡፡ አንባቢዎች ሌሎችን የሚያስቀድሙ፣ የማይዋሹ፣ የማያታልሉ፣ የማያዳሉ፣ የማይፈሩ፣ ለመብትና ለነፃነት የሚሟገቱ፣ ማንም እንዲጎዳ የማይፈልጉ፣ በራሳቸው የሚቆሙ በመሆናቸው ፍትሃዊነት አላቸው፡፡ አርአያ (Examplery) ይሆናሉ ለማለት ይመስላል፡፡
ህይወት የተፈጥሮ ስጦታ ብትሆንም በነፃነት ለመኖር ወይም በምክንያት ለመሞት የሚቻለው ከማወቅ በሚገኝ የማሰብ ፀጋ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ እንደ አርስቶትልና ፍራንሲስ ቤከን መሳይ ሊቃውንቶች፤ በሂሳብ ወይም በምህንድስና ስሌት ‹ልክ› ወይም ‹ትክክል› የሚባለው ነገር በኑሯችን ትግልና በስነ ምግባራችን ውስጥም አግባብነት እንዲኖረው ያስገነዝቡናል። ለዚህም መካከለኛው መንገድ (Middle way) የሚሉትን የባህርይ አቋም ማለትም ፈሪ ወይም ጀብደኛ ከመሆን ጎበዝ፣ ልቅና ጭምት ከመሆን ጨዋ፣ በጥድፊያ በስንፍና መሃል ልዝብነት እንዲኖረን፣ በጉራና በዝምተኛነት መሃል ተግባቢ እንድንሆን፣ በችኮላና በማቅማማት መሃል ራሳችንን መግዛት እንድንለምድ ይመክሩናል፡፡ እነዚህ ባህሪያት እንደ ሁኔታው የሚወሰኑ መሆናቸውንም አልደበቁም፡፡
ወዳጄ፡- እስቲ አንድ ጥያቄ ተቀበለኝ፡- … እውቀት፣ ባህርይም ሆነ ልምድ ለምን ያስፈልጉናል ትላለህ? ... እኔ እንደሚገባኝ፡- ተገቢን ነገር በተገቢው ቦታ ለማድረግ፣ ሚዛናዊና ምክንያታዊ ለመሆን፣ ሌሎችን ለመርዳትና ስልጣኔን ለማገዝ በተለይ ደግሞ አስቸጋሪ ፈተናዎችን በዘዴ ለማለፍ እንድንጠቀምባቸው ይመስላል፡፡
አርስቶትል መምህሩ የነበረው ፕሌቶን ይወደው እንደነበር ሲጠየቅ፤ “ፕሌቶን እወደዋለሁ፤ እውነት ደግሞ ይበልጥ ይወደዳል” (Plato is dear, but dearer still is truth) በማለት ነበር የመለሰው፡፡ ብሩተስም ስለ ቄሳር በተጠየቀበት ጊዜ፤ “ቄሳርን እወደዋለሁ፤ ሮምን ግን የበለጠ እወዳታለሁ” (Brutus loved not ceasar less, but Rome more) ማለቱ ተፅፏል፡፡ ጥያቄዎቹ ፈታኝ ቢሆኑም ብልህ መልስ አግኝተዋል። … ሁሉንም ትልቅ አድርገዋቸዋልም!!
***
ወደ መጀመሪያው ጨዋታችን እንመለስ። ተናጋሪ፡- “በእግዜር መኖር ታምናላችሁ አታምኑም?” ተብሎ ሲጠየቅ፣ ጥያቄውን በጥያቄ ነበር የመለሰው፡-
“ኢትዮጵያዊ ነህ አይደለህም? … እዚህ የተሰበሰብነው በማን ፈቃድ ይመስልሃል?” በማለት፡፡ … ተሰብሳቢው አጨበጨበ፡፡ አልገባውም፡፡
ወዳጄ፡- ኤሚሊ ዲክሰን፡-
“ካላወቁበቱ
መደነስ በስልቱ፣
በሙዚቃው ቃና፣
ያነክሳል ጊዜ
ቀን ይነክሰውና!!”
… ማለቷን እንዳትረሳ፡፡ ለዚህ ነበር የጠራናት፡፡
በነገራችን ላይ “አገር ከነቃ መመለሻ የለውም (Once a nation begins to think, it is impossible to stop it.) ያለው ማን ነበር? ምርጫ ልስጥህ፡-
ሀ) ቮልቴር
ለ) ቮልቴር
ሐ) ቮልቴር
መ) ሁሉም ልክ ነው!
ሠላም!!

Read 685 times