Sunday, 29 April 2018 00:00

ድማሚት (1+1=3)

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የአንዳንድ መጽሐፍ አርዕስቶች ለየት ማለት ቀልብ ይስባል፡፡ ይኼ አንዱ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የሽፋኑ አርእስት በአሀዝም በፊደልም ‹‹አንድ ሲደመር አንድ እኩል ይሆናል ሶስት›› ነው የሚለው፡፡ ONE PLUS ONE EQUALS THREE. ጸሐፊው DAVE TROTT ስለ መጽሐፉ ፋይዳ በመግቢያ ገጹ ላይ ያሰፈረው አጭር ማስታወሻም...
which is the point of this book.
under the old system 1+1=2
 under the new system 1+1=3
በነባሩ ስሌት ውጤቱ ሁለት የነበረው፤ በአዲሱ አተያይ/ቀመር ሦስት ሲሆን እንደ ማለት፡፡
 1. HERD THINKING - መንገኝነት
ከጥቂት ዓመታት በፊት አፍሪቃ (ኮንጎ) ውስጥ ለማረፍ ያኮበኮበ አይሮፕላን በድንገት ተከሰከሰ፡፡ አንድ ተሳፋሪ ብቻ ተርፎ ወደ ሆስፒታል ሲወሰድ፣ ሌሎቹ ሀያ ተሳፋሪዎችና ሁለቱ አብራሪዎች ህይወታቸው አለፈ፡፡ አይሮፕላኑ ዘመናዊና በቴክኒክ አቋሙ የተሟላ፣አብራሪዎቹ በቂ ልምድና ብቃት ያላቸው፣ የአየር ንብረት ሁኔታው ለበረራ በጣም አመቺ ስለነበር የአደጋውን መንስኤ ለማወቅ በጣም አስቸገረ። በመጨረሻም ተርፎ ሆስፒታል የገባውን ሰው መጠየቅ ግድ ሆነ፡፡
ሰውየው ሲመሰክርም፤ ከተሳፋሪዎቹ መካከል አንዱ በድብቅ ትንሽዬ አዞ ይዞ ገብቶ ነበር፡፡አይሮፕላኑ ለማረፍ ሲያዘቀዝቅ አዞው ከነበረበት ቦርሳ ወጣ፡፡ ተሳፋሪዎቹ ሲያዩት በፍርሀት እየተንደረደሩ ወደ አብራሪዎቹ አቅጣጫ መነባበር ያዙ፡፡ ካፒቴኑ ባሉበት እንዲቆዩ ትእዛዝ ቢሰጥም ሰሚ አጣ፡፡ አይሮፕላኑ አፍንጫውን ቁልቁል ወደ መሬት ባደረገበት በዚያ ቅጽበት፤ ተሳፋሪዎቹ ሁሉ ባንድ ላይ ተሰባስበው ወደፊት ስለመጡ ሚዛኑን ስቶ ክፉኛ ባፍጢሙ ተከሰከሰ፡፡
ሚጢጢው አዞ በማንም ላይ አደጋ ለማድረስ የማይችል ገና ለአቅመ አዞነት ያልደረሰ መሆኑን ለማስተዋል ፋታ የወሰደ አልነበረም፡፡ የችግሩ ዋንኛ መንስኤም ይኸው ነበር - ከተሳፋሪዎቹ መካከል አንዳቸውም በተለየ መንገድ ማሰብ አለመቻላቸው፡፡ አንዱ ያደረገውን ኮርጆ ሌላውም ስለቀጠለበት ለከፋ አደጋ ተጋለጡ፡፡
በአለም ላይ ለሚከሰቱ የመከራና ሰቃይ፣ ጦርነት፣ ሽብር፣ ጅምላ ጭፍጨፋ . . .ወዘተ መነሻ ፍርሀት የሚፈጥራቸው አጉል ውሳኔዎች ናቸው፡፡ መላው ዜጋ ብቻውን እንደተተወ፣ባይተዋርነት፣ የመገለል ስሜት ሲያድርበት፤ከሌላ እንደሱ በፍርሀት ቆፈን ውስጥ ካለ ዜጋ ጋር መሆንን ምርጫው ያደርጋል፡፡ ፍርሀት አመክንዮን፡እንዴትና ለምን ብሎ መጠየቅን፣ምክንያታዊነትንና ማመዛዘንን ሁሉ ነጥቆ በስሜታዊነት ይነዳል፡፡ ለዚህም ነው ጥርስን ነከስ ሀሞትን ዋጥ ማድረግን የሚጠይቀው ውሳኔ በቁርጥ ቀን ላይ ግድ ይላል መባሉ፡፡ ከመንጋው መካከል ነጠል ብሎ በግል በራስ መወስን ለመቻል፡፡
ባለቅኔው  እንዲል...
ከሰው መንጋ እንገንጠል
ላንዳፍታ እንኳ እንገለል
በእፎይታ ጥላ እንጠለል... እንዲል ባለቅኔው
2. MOTIVATION - ማፋፋም
ቢል ሻንክሊ የሊቨርፑል ቡድንን ተጫዋቾች በከፍተኛ የአሸናፊነት መንፈስ ቅስቀሳ በማድረግ ከሁለተኛ ዲቪዚዮን አውጥቶ ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን ወሰደው፡፡ አሁንም እያነሳሳ የዲቪዚዮኑ አሸናፊ አደረጋቸው፡፡ በእንግሊዝ ውስጥ ምርጥ ቡድን እንዲሆኑ አራገባቸው - ሆኑ፡፡ ቀጥሎም በአውሮጳ ዙሪያ ግጥሚያ በማድረግ ድል እንዲቀዳጁ አቀጣጠላቸው - ድል በድል ሆኑ፡፡ በ1965 የጀርመን አሸናፊ ከነበረው EC Cologne ቡድን ጋር ተጋጠሙ፡፡ ኮሎኝ ውስጥ አሸነፉ፡፡በመልስ ጨዋታውም ራሳቸው ሜዳ ላይ እንዲሁ፡፡ እናም በመጨረሻው ወሳኝ ግጥሚያ ከሁለቱም ሜዳ ውጪ ሮተርዳም ውስጥ ፍልሚያ የሚሰኝ ግጥሚያ አድርገው፣ በተጨማሪ ሰአት አሸነፉ እና ስማቸው ገነነ፡፡ ቡድኑም ወደ ኢንግላንድ ተመለሰ፡፡ ከሦስት ቀናት በኋላ ከቼልሲጋ ግጥሚያ ይጠብቃቸዋል፡፡
ተጫዋቾቹ መልበሻ ክፍል ውስጥ በድካም ዛል ብለው እንደተቀመጡ ሻንክሊ ገብቶ ፊት ለፊታቸው ቆሞ ትክ ብሎ አያቸው፡፡ እውነትም ድካም ይነበብባቸዋል፡፡ እናም እንዲህ አላቸው፡- ‹‹ልጆች መናገር ያልነበረብኝ ቢሆንም መደበቅ ደሞ አልችልምና ልንገራችሁ...›› አለና ወደ ኪሱ ገብቶ በደማቅ ወረቀት ላይ የታተመ ጽሑፍ አውጥቶ እያሳያቸው፣ ‹‹ይኼ ቼልሲዎች ስለ ናንነተ አሳትመው ያሰራጩት ነው፡፡ እናም ባለፈው ጨዋታችሁ ትንቅንቅ ስታደርጉ አቅማችሁን ሁሉ ስላሟጠጣችሁ ዛሬ በዝረራ እንደሚያሸንፏችሁ ጉራ ነፍተው የጻፉት ነው፡፡ እና እንዴት ነው እንዳሉትም ደክማችኋል እንዴ!››
በተጫዋቾቹ መሀል መጀመሪያ ቅሬታ ከዚያም የመጠቃት መንፈስ፣ ከዚያም እንደ ግስላ እመር አመር እያሉ በእልህ ይጎፈሉ ጀመር፡፡ ጨዋታውን እንደለመዱት በድል ካጠናቀቁት በኋላ፤ ሻንክሊ ወደ ቼልሲ አሰልጣኝ ሄዶ ሰላምታ ሲሰጠው አሰልጣኙ ቶሚ ዶቼቲ በጣም ተገርሞ፤ ‹‹ከዚያ የሮተርዳም ግጥሚያ በኋላ ልጆችህ በምን ተአምር እንዲህ አይነት ብቃት ይዘው ሊገኙ ቻሉ!›› ሲል ጠየቀው። ሻንክሊ ‹‹ይህን ስላስነበብኳቸው ነው›› ብሎ ያቺን ደማቅ ወረቀት አውጥቶ ሰጠው፡፡ ቶሚ ወረቀቱን አይቶ ‹‹ይኼ የምን እንቶ ፈንቶ ነው!›› ብሎ ጮኸ፡፡ ወረቀቷ በሌላ በማንም እጅ ያልነበረችና ልጆቹን አቀባብሎ ለመተኮስ ራሱ ሻንክሊ ያዘጋጃት አንዲት ኮፒ ብቻ ነበረችና፡፡ አለ አይደል በቃ ትንሽ ለመቆስቆስ፡፡
3. MIND BLOWING - እፎይታ
 በ1866 አሜሪካ የnitroglycerineን ፍንዳታ ጥቅም ላይ በማዋል ተራራና ቋጥኞችን ነድሎ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ለመስራትና መላ አህጉሩን ለማገናኘት ቋምጠው ነበር። ጉዳዩ ቢሳካ ለነዳጅ ፍለጋና ማእድን ቁፋሮ የሚባክነውን በመቶ የሚቆጠሩ ሰራተኞችን ጉልበትም ቆጣቢ ነው ተብሎ ነበር፡፡ ችግሩ nitroglycerine ፈሳሽ ስለነበር እርሱን ለማጓጓዝ በተደረጉ ሙከራዎች የብዙዎች ህይወት ተቀጠፈ። በመርከብና የተለያዩ ስፍራዎች ካለቁት ሰዎች በተጨማሪ ድንገተኛ ፍንዳታው ከተከሰተበት ግማሽ ማይል ርቀው ባሉ መኖሪያ ቤቶች 3ኛ ፎቅ ደርሶ መስኮት በመገነጣጠል የአንድ ሰው ክንድ እስከመጉመድና በመንገድ ላይ ተፈነጣጥረው የተገኙ የሰው ጀርባ አጥንት ዜናዎች መነጋገሪያ ሆኑ፡፡
ከሁለት አመት በፊት በ1864  በዚሁ የፍንዳታ ጦስ ታናሽ ወንድሙን ያጣ ሰው ነበረ - አልፍሬድ ኖቤል፡፡ ኖቤል ሳይንቲስት እና ጦርነት የማይወድ (Scientist and Pacifist) ሰው ነበረ፡፡ እናም nitroglycerineን በቀላሉ ለመያዝና ለማጓጓዝ የሚያስችል ፈጠራ ፈጠረ፡፡የፈጠራውንም ስም Dynamite (ድማሚት) ብሎ ሰየመው፡፡ ጥሩ ማሸጊያም ስለሰራለት የሚፈለገው ቦታ ደርሶ እስኪፈነዳ ድረስ ምንም ጉዳት እንዳያመጣ በማድረጉ የብዙዎችን ህይወት ታደገ። በዚያም እጅግ ብዙ ገቢ ለማግኘት ቻለ፡፡ እንደ አንድ ጦርነትን እንደሚጸየፍ Pacifist ሰውም የተሻለች ዓለም በመፍጠር ረገድ አቅሙ የፈቀደውን እገዛ ማድረጉ ተሰማው፡፡ ታላቅ ወንድሙ ታምሞ እስኪሞት ድረስ፡፡
አንድ የፈረንሳይ ጋዜጣ ዜናውን አወጫብሮ የወንድሙን ሞት ራሱ አልፍሬድ ኖቤል እንደሞተ አድርጎ ዘገበው፡፡ አርእስተ ዜናው እንዲህ ነበር የሚለው፡- ...‹‹ነጋዴው ኖቤል ሞተ››
ኖቤል ክው ብሎ ደነገጠ፡፡
ጋዜጣው ሀተታውን ሲቀጥልም፡- ‹‹የሰው ልጆችን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በፍጥነት እንዲሞቱ መንገድ የቀየሰ ሰው›› ይላል፡፡ ኖቤል ማመን አቃተው፡፡
እርሱ ስለ ራሱ የሚያስበው የነበረው እውነት፤ ድማሚትን በመፍጠሩ የሌሎችን ሕይወት የታደገ ግብረ ሰናይ ሰው መሆኑን ነበር፡፡ በዓለም ገሀድ እውነት ዓይን ሲታይ ግን ዳይናማይትን መፍጠር በጭራቅ እንዲመሰል አድርጎት ኖሯል ለካንስ!
ስለዬህም ኖቤል በጋዜጣ ላይ ከተገለፀበት መልኩ በተለየ በሌላ መልካም ስም ይታወስ ዘንድ በጽኑ ፈለገ፡፡ እናም የኖቤል ሽልማት የተሰኘውን የሽልማት ድርጅት አቋቋመ፡፡
በየዓመቱ በሳይንስ፣ ኬሚስትሪ፣ ህክምና፣ ሥነ ጽሑፍና ልዩ የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማት ተሸላሚ በሚል ዘርፍ ሽልማቱ መሰጠት ተጀመረ፡፡ ይኸውም ሽልማት ዛሬ በዓለም ላይ ያሉ ሳይንቲስቶች፣ የሀገር መሪዎችና ልዕለ ሰብእናዎች ሁሉ የሚጓጉለት ሽልማት ለመሆን በቃ፡፡
እናም ኖቤል የሚለው ስም አሁን እርሱ በፈለገው መንገድ የሚታወስ ለመሆን በቃ፡፡ የሞት ነጋዴው በሚለው አጉል መጠሪያ ሳይሆን በዓለም ላይ ካሉ ሽልማቶች ሁሉ ላቅ ባለውና የግብረ ሰናይነት መገለጫ በሆነው ስሙ- የኖቤል ሽልማት፡፡ እፎይ፡፡

Read 1824 times