Print this page
Sunday, 29 April 2018 00:00

ኳስና ፖለቲካ!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ - (አተአ)
Rate this item
(7 votes)


    ድሮ ነው፡፡ ከእለታት አንድ ዕለት፣ ቁርስ እንኳ በየቤታችን ተቆርሶ ሳይበላ በፊት፡፡ በማለዳ ጀምሮ ሰፈሩን በጫጫታ አውከነዋል፡፡ ከተለመደው የየሳምንት ጨዋታችን በጣም የረዘመ ማለዳ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ናሆም አዲስ ኳስ ተገዝቶለት ስለነበር ነው፡፡ ያን ዕለት በጧት ተነስቼ ከቤቴ ለመውጣትና በአዲሷ ኳስ ለመጫወት አልነጋ ብሎኝ ነበር ያደርኩት፡፡ ብዙዎቹ የሰፈር ማቲዎች ተመሳሳይ ረዥም ለሊት አሳልፈን በለሊት ናሆምን ከቤቱ ቀሰቀስነው፡፡
እናም ይኸው ከንጋት ጀምሮ የናሆምን ኳስ እያነጠርን ሰፈሩን በጫጫታ ሞላነው፡፡
***
ናሆም… ከአብዛኞቻችን በዕድሜ ባይበልጥም፣ በአካል ግዝፈት ግን ከሁላችንም እጅጉን ይልቃል፡፡ ሌላ ጊዜ ቢሆን ማንም በቡድኑ አያስገባውም ነበር፤ዛሬ ግን የኳሱ ባለመብት ስለሆነ በፈለገው ቡድን ገብቶ ይጫወታል፡፡ ሲደክመው ደግሞ ድቡልቡል ሰውነቱን ከጎላችን አጠገብ ካለው ለምለም ሳር ላይ ያሳርፍና ላቡን እያንዠቀዠቀ ይጋደማል፡፡
ጨዋታው በተለያዩ ሶስት ቡድኖች መካከል በየተራ የሚደረግ ግጥሚያ ነው፡፡ አብዛኞቹ ህጻናት በባዶ እግራቸውና በጎማ ጫማ ናቸው፡፡ ጥፍራቸው የተነቀለና የደረቁ ቁስሎች በጣቶቻቸው ጫፍ የሚታይ የምንዱባን ሰፈር ምንዱባን ውሪዎች ነበርን። ምንም አይነት መለያ የለበሰ ልጅ ወይም ቡድን የለም። በየቡድኑ ስድስት ስድስት አባላት ያሉ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ጨዋታ ሲያልቅ ተረኛውና ዳኛ ሆኖ የቆየው ቡድን ይገባል፡፡
***
በጠዋቱ፣ መሃል አናት ከሚቀደው ከዚህ የማለዳ ጸሃይ ሙቀት የተነሳ ወዲያና ወዲህ የሚል ሰው ብዙም አይታይም፡፡ ጭር ካሉት የሰፈራችን ጎዳናዎች ላይ ህፃናት ሲሯሯጡ ይታያሉ፡፡ ህጻናት ብቻ በሚሯሯጡበት በዚህ ሰዓት ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ  ከመንደሩ መሃል የምናደርገውን ጨዋታ በጽሞና የሚከታተልና የሚያስተውል ጋሼ ጳውሎስ ብቻ ነው። አንዳንዴ ከዳር ይቆምና… ‹‹አንተ አቀብለው እንጂ ደካማ! …. ያዘው … ተከተለው! … አንተ የዕጣን ፊኛ ደክሞሃል አረፍ በል …  ›› እያለ እንደ አሰልጣኝ ሲጮህ ያረፍዳል፡፡ እናም ያን ዕለት ማለዳ ተክዞ ተቀምጦ ነገሩን እያመሰጠረ፣ ያለ ጩኸት እያስተዋለን እያለ አባቴ ሲያልፍ አገኘው፡፡
ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ አባቴ ጋሽ ጳውሎስን ይጠይቀዋል ‹‹ምን የረባ ነገር አለ ብለህ ነው፣ እነዚህ የሰፈር አሸባሪዎችን የምታጠናው ጳውሎስ››
‹‹ይገርምዎታል፡፡ እነዚህን ልጆች ሳይ አንድ ነገር ትዝ ይለኛል፤ ጨዋታቸውን ደጋግሜ እያየሁ ብዙ ነገር አስባለሁ፡፡ የዛሬ ጨዋታቸው ደግሞ ለየት ይላል፣ ለሚቀጥለው ሳምንት ፕሮግራሜ የሚሆን ሀሳብ ነበር ያገኘሁት››
‹‹…ሃሃሃሃ …. ደግሞ ብለህ ብለህ የነሱን ጨዋታ በራዲዮ ልታሰማን ነው! አንተ ሰው የማታደርገው ነገር የለም መቼም፡፡ በል በል ራዲዮናውን የልጆች ጨዋታ ታደርግና የመንግስት ሰዎች እንዳይቃወሙህ››
‹‹ግዴለም፡፡ ይጠብቁ ብቻ፡፡ ምን አይነት ፕሮግራም እንደማዘጋጅ አሳይዎታለሁ፡፡ ግሩም ሀሳብ ነው ያገኘሁት...››
ጋሽ ጳውሎስ እኛ ሰፈር የሚኖር የመንግስት ተቀጣሪ ጋዜጠኛ ነው፡፡ በተለይ ቅዳሜ ከሰዓትና እሁድ ጠዋት በራዲዮ ጣቢያው በሚቀርበው ዝግጅት ላይ ለወጣቶች የሚሆኑ ዝግጅቶችን ነበር አሰናድቶ የሚያቀርበው፡፡ እናም እንደተለመደው በዚህ የክረምት ማለዳ ከዳኞቹ ልጆች ውጪ ቁጭ ብሎ የሚያስተውለን እሱ ብቻ ነበር፡፡ እናም በጥሞና የሚያጠናን ስራውን እያሰበ ኖሯል፡፡
***
በሚቀጥለው እሁድ ማለዳ በለሊት ተነስቼ፣ ጎረቤቴ ከሚገኘው የካቶሊክ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን መዝሙር ሳጠና ቆይቼ (ያው የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ብሆንም! ትንሽ ሆኜ መዝሙር የምለማመደው እዚያ ነበር፣ ወላጆቼም ምንም አይሉም፡፡ አንዳንድ ቀን ብቻ አያቴ … ‹ምፅ! አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ!› ትለኛለች፡፡ የቄስ ትምህርቴን ትቼ እዚህ ስዘምር ስለምውል መሰለኝ፡፡)
የዚያን ዕለት ማለዳ ስመጣ አባቴ በረንዳ ላይ ተቀምጦ ፊሊፕስ ራዲዮዎውን በግራ እጁ ከፍ አድርጎ ትከሻው ላይ አንጠልጥሎ፣ የማለዳ ፕሮግራም ያዳምጣል፡፡ የሬዲዮው ድምፅ ገና የአጥሩን በር ከፍቼ ሳልገባ፣ ከውጪ ጀምሮ የሚሰማ ቢሆንም … አባቴ ግን ትከሻው ላይ ወደ ጆሮው አስጠግቶ ለምን እንደሚይዘው አይገባኝም፤ የጆሮውን ጤነኛ መሆን ግን አውቃለሁ፡፡
የአጥሩን በር ዘልቄ ስገባ በረንዳው ላይ አጠገቡ በሚገኘው ዱካ ላይ እንድቀመጥ በምልክት አሳየኝ፡፡ የራበኝ ቢሆንም ብስጭትጭት ብዬ ነጠላዬን ከአንገቴ ላይ አውርጄ ክንዴ ላይ እየጠቀለልኩ ተቀመጥኩ፡፡ በግማሽ ልብ ሆኜ፣ ወደ ቤት ውስጥ እያጮለኩም ቢሆን መቀመጥ ግድ ነው፡፡ የዕጣንና ቅመም ያለው ሻይ ጠረን ያውደኛል፡፡ ትንሷ ሆዴ በርኃብ ታጉረመርማለች፡፡
ለካ በራዲዮው ውስጥ የሚያወራው ጋሽ ጳውሎስ ነበር፡፡ አስገምጋሚ ድምፁ የማለዳውን አየር ሞልቶታል፡፡ የእሁድ ማለዳ ዝግጅቱን እያቀረበ ነበር፡፡ እንዲህ ሲል ሰማሁት…
‹‹… በዚያ ማለዳ የሰፈሬን ህፃናት ጨዋታ ስመለከት የታሰበኝ የወቅቱ ፖለቲካና አመራሮች ናቸው፡፡ ህጻናቱ ሁሉ ያለምንም መለያ የሚጫወቱ ቢሆንም ሁሉም ልጅ የሚያቀብለው ለራሱ የቡድን ጓደኛ መሆኑ ገርሞኝ አስተውላቸው ነበር፡፡ እንዴት አይሳሳቱም፣ እንዴት ነው የሚተያዩት እያልኩ እንዳስብም አድርገውኛል፡፡
የወቅቱ ፖለቲካና ስልጣን ትክክለኛ መገለጫ ማለት ይህ ነው፡፡ አያችሁ ፖለቲካው ውስጥ ስልጣን ላይ የሚጫወቱ ሰዎችም የራሳቸውን ቡድን ሰው ለይተው የሚቀባበሉበት የማይታይ መለያ አላቸው። ሳይነጋገሩ የሚግባቡበትና ሳይተያዩ የሚቀባበሉበት ደመ ነብስ አላቸው፡፡ ለዚህም ነው እኛ በቀላሉ ለይተን የማናውቃቸው፡፡ እነርሱ ግን ይተዋወቃሉ …››
‹‹ወይ ጉድ! ወይ ግሩም ይሔ ጳውሎስ የሚባል ሰውዬ ቀላል አይደለም፤ ተንኮለኛ ነው ፡፡ ጌታመሳይ አዳምጥ የሚለውን…›› ይላል አባቴ ጮክ ብሎ፣ ፈገግታው ከፊቱ ሳይጠፋ እያስተዋለኝ፡፡ እኔም ጋሽ ጳውሎስ ምን እንደሚል ባይገባኝም እንደታዘዝኩት አዳምጣለሁ፡፡
ጋሽ ጳውሎስ ቀጥሏል … ‹‹…የኳሱ ባለቤት በአካል ከሌሎቹ ህጻናት ግዙፍ ቢሆንም ጨዋታው ላይ ግን ደካማ ስለሆነ በዚያ ሰፈር ብዙ ግዜ ስመላለስ እንደማያስገቡት ነበር የማስተውለው፡፡ ያን ዕለት ግን የራሱን ኳስ የያዘ በመሆኑ በሁሉም ጨዋታዎች ላይ ያለከልካይ ተሳታፊ ነበር …››
… ‹‹ጌታ መሳይ፤ ይህ የሚለው ልጅ ማነው?…››
‹‹… ናሆምን ነው አባባ …››
‹‹… የዘውዴን ልጅ ነው’ንዴ፡፡ እርሱስ እውነቱን ነው! … ወይ ጉድ! በየራዲዎናው እንዲህ መቀለጃ ያድርገን እንጂ ይህ ዚቀኛ ሰውዬ…›› ይላል አባቴ እየሳቀ…
ጋሽ ጳውሎስ ይቀጥላል … ‹‹ይህ ልጅ በፖለቲካ ውስጥ ያለችሎታ የሆነ ነገር በማድረግና በውለታ ብቻ ሁሉም ነገር ውስጥ ጥልቅ የሚሉትን ካድሬዎች ይመስላል፡፡ እነዚህ ካድሬዎች ሁሉም ቦታ ስለሚገቡ ሁሉንም ነገር የሚያውቁ ይመስላቸዋል፤ እውነቱ ግን … በፍርሃት በተያዙ ሰዎች ዝምታ ተተክለው ያደጉ ናቸው፡፡ ስለጨዋታው ምንም የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ የፖለቲካውን መጫወቻ ጆከር በአጋጣሚ ከሳቡ በኋላ ተመቻችተው የተንሰራፉ ናቸው፡፡ ኳሷ የግላቸው ነችና በሚያዩት የሚያምር ጨዋታ ውስጥ ሁሉ እኛም አለንበት እያሉ ዘው! … የሚሉት ናቸው… ››
አባቴ  ‹‹… ሃሃሃሃ …›› እያለ ከት ብሎ ይስቃል፡፡
‹‹…የእያንዳንዱ ቡድን መሪ (አምበል) የሆኑት ህፃናት ከሌሎቹ በጉልበታቸው ጠንከር ያሉና በሆነው ባልሆነው ጉልበታቸውን ለመጠቀም የሚሞክሩ ናቸው። በድንጋይ በተሰሩት ጎሎች አናት የሚበሩትን ኳሶች ሁሉ ጎል ነው! (አይደለም!) በሚል ጦርነት ይከፍታሉ፡፡ እንደ ደንቡ ቢሆን ዳኞች የወሰኑትን መከተል ይቀል ነበር፣ በዚህ የሰፈራችን የህፃናት ጨዋታ ላይ ግን ዳኛ የሆኑት ህፃናት ራሱ የጉልበተኞቹን አለቆች ግልምጫና ግፊያ ሊቋቋሙት አይቻላቸውም። መጀመሪያ አልገባም ያሉትን አንዱ አምበል አይኑን አፍጥጦ ሲመጣባቸው ይሽሩታል፤ በመቀጠል ከሌላኛው አምበል ጋር ጦርነት ይከፍታሉ፡፡ ደቂቃዎች ይባክናሉ፣ ግዜ ያልፋል፡፡ … በመጨረሻ በዳኛው ውሳኔ ሳይሆን በአንዱ ጉልበተኛ ውሳኔ ይጠናቀቃል፡፡ የተወሰነባቸው ቡድን አባላት እየተነጫነጩ ይመለሳሉ። በቅሬታና በጩኸት ነው ውሳኔውን የሚቀበሉት፡፡
“የየቡድኑ አምበሎች አምባገነን የአገር መሪዎችን ይመስላሉ፤ በየአገሩ ዳኞችና ፍትሃዊ ሰዎች የሚወስኑትን አይቀበሉም፡፡ በነዚህ አገሮች ሁሉም ፍርዶች የሚሰጡት የነዚህን አምባገነኖች ፊት በማየትና በማጥናት ይሆናል፡፡ በተለይ በታዳጊና በድሃ አገር … መሪዎች ፍጹም አምባገነኖች ሲሆኑ፣ ዳኞች ግን ምንም ተፅዕኖ የማያሳድሩና የአምባገነኖች ውሳኔ አስፈፃሚ ሃይሎች ብቻ ናቸው፡፡ ሲሸነፉ ቦታ አይለቁም። ጨዋታውም የሚቀጥለው እነርሱ እስከሚያሸንፉ ወይም የሚያሸንፉባትን ጎል እስከሚያስቆጥሩ ድረስ ለዝንተዓለም ይሆናል፡፡ የእነርሱ ጎል ባይገባም የሚፀድቅ ሲሆን የሌሎቹ ግን ቢገባም ያልገባ ነው፡፡ ››
 ‹‹…ኸረ ጉድድድድ! … ሃሃሃሃ … ይሄ ሰው እውነትም አብዷልና ጌታመሳይ፤ ሰዎቹን የሚላቸውን ትሰማለህ ወይ! ጳውሎስ ጭራሽ አሁንስ በአደባባይ ይሳደብ ጀመርኮ! …››  ይላል አባባ እየተገረመና የሚንፎለፎል ሳቁን እየሳቀ፡፡ ምንድን ነው የሚለው! ብዬ ይበልጥ ለማዳመጥ እሞክራለሁ፣ ምን ዋጋ አለው! አባቴ ከሚነግረኝ ይልቅ የማዳምጠው ወቅታዊ ረሃቤን ነበር!
‹‹…ልጆቹ የሚጫወቱበትን ሜዳ ክልል አስምረውታል፡፡ ሆኖም አንዳንድ ግዜ ኳሷ ከወሰኑ አልፋ ትሔዳለች፡፡ እንደ ደንቡ ከወሰን ያለፈን ኳስ ከእንደገና በስርዓት መጀመር የሚኖርበት ቢሆንም፤ በሰፈራችን ጨዋታ ግን ብዙ ግዜ አልፏል /አላለፈም/ የጦርነትና የብጥብጥ መነሻ ነው፤ እንደተለመደው ውሳኔው የሚተላለፈው ግን በጉልበተኞቹ ነው፡፡ ብዙ ግዜ የእነርሱ ቡድን ከሆነ አይወጣም … (የሌላው ከሆነ ወጥቷል! ይላሉ) …
(… ‹‹ደሞ ምን ሊለው ነው ይህንን! … ›› ይላል አባቴ በለሆሳስ …)
“ይህ የሰፈራችን ልጆች መጫወቻ ሜዳ ክልልና ወሰን አሰማመር እንዲሁ የአገሬን ድንበርና የክልሎች ወሰን አከላል ይመስላል፡፡ ወዲያና ወዲህ የኛ ነው፣ የእናንተ ነው! በሚል ሁል ጊዜ የወሰን አተካራ የሚነሳበት ቢሆንም ውሳኔው የሚተላለፈው ግን እውነትን በማጥናት ሳይሆን በሚሰጠው ጥቅም ልክ ይሆናል፡፡ በጉልበተኞቹ ውሳኔ እንጂ የተበድለናል ጫጫታን በማድመጥ አይደለም፡፡  ነዋሪዎች አልቅሰው ምለው ቢገዘቱም እነሱ የሚሉት እውን አይሆንም። እውን የሚሆነው የጉልበተኞች ትርታ ብቻ ነው፡፡ ጥላሁን ገሰሰ ….
ዛሬ ጥሩ ሰርቶ ነገ ማበላሸት
ፍቅር ፍቅር ማለት የውሸት የውሸት፣
የምድራችን ስፋት ለኛ መች አነሰን
ያመል ጠባብነት ነው የሚያናክሰን …
……እያለ እንዳዜመው መሆኑ ነው፡፡ ድንበሩና ወሰኑ የሚለየን ሳይሆን፣ የልቡና ፍቅር የሚያገናኘን አንድ ህዝብ መሆን የነበረብን ቢሆንም ቅሉ! …››
አባቴ ድንገት ‹‹….ኸረረረረ በገይ ሥላሴ! (አልፎ አልፎ ሲገረም በልጅነት ያደገበትን ታቦት ይጠራል!)…. ይህንን ጨዋታማ ከሰፈሩ ሰው ሁሉ ጋር ማዳመጥ አለብኝ…›› አለና ብድግ አለ፡፡ የተንጠለጠለ ኩታውን እየሰበሰበ… ‹‹ሂድ ቤት ግባ ጌታመሳይ! አንተም ቁርስ ብላ፣ እኔም ከወዳጆቼ ጋር ተጫውቼ ልመለስ !…››
በፍጥነት ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ለመስፈንጠር ስመቻች፣ አባቴ ወደ ውጪ ራዲዮዎውን አንጠልጥሎ ሲወጣ የጋሽ ጳውሎስ ድምፅ እየራቀኝ ቢሄድም ይሰማኝ ነበር …
‹‹…የህፃናቱ ጨዋታ የተጠናቀቀው ድንገት ነበር። ተሸናንፈው ወይም ደክሟቸው አልነበረም፤ የሰፈሬ ልጆች የእለቱን ጨዋታ ያጠናቀቁት ብዙ ጨዋታ የተጫወተውና የደከመው የኳሱ ባለቤት የሆነው ልጅ በቃኝ ብሎ ኳሱን አንስቶ ልሂድ በማለቱ ነበር። ጥቂቶቹ መብቱ ነው! ብለው ቢናገሩም ያኮረፉ ሲሆን፣ ጉልበተኞቹ ግን ጥቂት ቡጢ ሳያቀምሱ አልለቀቁትም። ቢሆንም የዕለቱ ጨዋታ የፈረሰው እንዲያ ነበር፡፡ መሪዎቻችንም ከዚህ የሚመሳሰሉት ኳሷን በቃን ደክሞናል ብለው አይተውልንም፣ ወይም ደግሞ ፋታ ስጡን ብለው ኳሷን አንስተው አይሄዱም። የእኛ መሪዎች የሚሞቱት ኳሷን እንደታቀፉ ነው። የእኛ መሪዎችና ፖለቲከኞች በሁሉም ጨዋታ ላይ በባለቤትነት ጥልቅ እያሉ ዘመናቸውን ይገፋሉ፡፡ ሁሉንም የምችለው እኔ ነኝ፣ ሁሉም ጨዋታ የሚሳካው እኔ ስኖርበት ነው፣ አገር እንደ አገር የምትቆመው እኔ ካለሁ ብቻ ነው! ብለው ስለሚያስቡ ጨዋታው በሰላም አይጠናቀቅም፡፡ …››
***
አባቴ ድንገት የግቢው በር አካባቢ ቆም አለና … ‹‹ጌታመሳይ! እውነቱን ነው’ንዴ! … የዘውዴን ልጅ ቡጢ አቀመሳችሁት!››
‹‹…ኸረ አልመታነውም አባባ፡፡ ራሱ ኳሷን ወደግቢያቸው ወረወረና ሮጦ ገባ…››
በቀስታ እየወጣ እንዲህ አለ፤ ‹‹…ይህቺ የራሱ ቅርደዳ ናት ማለት ነዋ! ይሄ ቀዳዳ ጋዜጠኛ! ደግሞ ቀጥሎ ሰዎቹ ንብረታቸውን ወደ ጎረቤት ካሸሹ በኋላ ይጠፋሉ ሊለን ይሆናላ … ሃሃሃ …››
የአባቴ ሳቅ ሲንፎለፎል በሩቁ እየተሰማኝ፤ ቶሎ ቁርሴን ለመብላት የሳሎኑን በር ገፋ አድርጌ ስገባ ሰራተኛችን በር ላይ አገኘችኝ … ‹‹አልዬ፤ ቶሎ ብርርር … ብለህ ከሸማቾች ዳቦ ገዝተህ ና!››
የታችኛው ከንፈሬን ቁልቁል እየጣልኩ በንዴት፤ ‹‹…እኔ እርቦኛል! አልሰማሽም!…››
‹‹…ታዲያ ቢርብህ ዳቦ ካልገዛህ ምን ልትበላ ነው! ሌላ ምንም ቁርስ አልተሰራም፡፡ እማማ ናቸው በጠዋት ከተመለሰ ገዝቶ ይብላ ያሉትና ብር የተውልህ፡፡ ይልቅ ሮጥ ብለህ ገዝተህ ና!…›› ብሯን ወርወር አድርጋ ጠረጴዛው ላይ ጣለችና፣ ወደ ጓዳዋ በዳንስ መሳይ አካሄዷ እየተውረገረገች ገባች፡፡ ደንዝዤ በቆምኩበት አሰብኩት፡፡ አሁን ከእንደገና ተመልሼ፣ አስፋልት ድረስ ሄጄ፣ የዳቦ ሰልፍ ተሰልፌ፣ ገዝቼ እስክመለስ ታሰበኝ፡፡ መቼም እስከዚያ ምሳ ሰዓት ሳይደርስ አይቀርም፡፡
በእጄ የጠቀለልኳትን ነጠላ ወርውሬ፣ የሳሎኑን በር ክስክስ አድርጌ ዘጋሁና ወደ ዋናው መንገድ ሮጥኩ፡፡ መብላት ካለብኝ መግዛት አለብኝ፣ መግዛት ካለብኝ ደግሞ መፍጠን ይጠበቅብኛል የሚል ሀሳብ እያመሰጠርኩ በረርኩ፡፡ ያንን ከንፋስ የፈጠነ ሩጫ ስሮጥ፣ ሰራተኛዋ ጠረጴዛ ላይ ያስቀመጠቻትን ብር እንኳ አለመያዜን አላጤንኩም ነበር፡፡
… አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ! … አለች አያቴ! እውነቷን ነው!
***
(የተረኩት ሀሳብ የሌሎች፣ ማስፋፊያውና ታሪክ ፈጠራ የእኔ ነው፡፡)

Read 3692 times