Monday, 30 April 2018 00:00

በሳኡዲ በ4 ወራት 48 ሰዎች ተቀልተው ተገድለዋል ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ባለፉት 4 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ 48 ሰዎችን አንገታቸውን በመቅላት መግደሉን አለማቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም ሂውማን ራይትስ ዎች ማስታወቁን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ሳኡዲ አረቢያ አንገት በመቅላት ብዙ ሰዎችን በመግደል በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ የአለማችን አገራት አንዷ ናት ያለው ተቋሙ፤ በአገሪቱ መንግስት በ2018 የፈረንጆች አመት የመጀመሪያዎቹ አራት ወራት፣ አንገታቸው ተቀልቶ ከተገደሉ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ የከፋ ወንጀል ያልፈጸሙ መሆናቸው እርምጃውን ኢ-ፍትሃዊ  ያደርገዋል ብሏል፡፡
በአገሪቱ ባለፈው አመት ብቻ 150 ያህል ሰዎች ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ አንገታቸውን ተቀልተው መገደላቸውንና እ.ኤ.አ ከ2014 መጀመሪያ አንስቶ ባለው ጊዜ ውስጥ በ600 ያህል ሰዎች ላይ የአንገት መቀላት ፍርድ ተፈጻሚ መሆኑን ያስታወሰው ተቋሙ፤ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑትም ቅጣቱ የተጣለባቸው ከአደንዛዥ ዕጾች ዝውውር ጋር በተያያዘ ተከስሰው መሆኑን አመልክቷል፡፡
የሳኡዲው ልኡል ሞሃመድ ቢን ሳልማን በቅርቡ ከታይም መጽሄት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ አገሪቱ ከነፍስ ማጥፋት ወንጀል በስተቀር በሌሎች ክሶች የሚሰጡ የሞት ፍርዶችን ወደ እድሜ ልክ እስራት ዝቅ የማድረግ ሃሳብ እንዳለ መናገራቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡

Read 1940 times