Print this page
Saturday, 21 April 2018 13:53

የሉሲ ቃለ መጠይቅ - (ምናባዊ ወግ)

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(3 votes)


   “… ደስተኛ አድርጎሻል ነው ያልከኝ?” አለች፡፡ “ምን ደስታ አለ፡፡ ሰንሰለቱ አንገቴ ላይ ዝጎ ቲታነስ ሊያሲዘኝ ምንም
አልቀረውም፡፡ የሰራችሁልኝ ቤት ጣራው ያፈሳል፡፡ መብራት አስገባልሻለሁ ብላችሁ አሁንም በግቢ መብራት
እየተጨናበስኩ ነው የምተኛው፡፡ …”
        ሉሲ ቤተሰቦቼ ቤት ውስጥ የኖረች ውሻ ናት። ወይም ነበረች፡፡ አሁን እኔም ቤተሰቦቼ ቤት አልኖርም። ሉሲም አርጅታ ወይ ታማ ከሞተች ሁለት ዓመት ገደማ ሞልቷታል። … ከመሞቷ በፊት ቃለ መጠይቅ አድርጌላት ነበር፡፡ … እንዳጋጣሚ ወረቀቶች ሳገላብጥ ቃለ መጠይቋን አገኘሁት። …. ያኔ የተናገረችውን ቁብ አልሰጠሁትም ነበር። አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው በጣም አሳቀኝ፡፡ እየሳቅሁም ሳግ ጉሮሮዬ ላይ ይቋጠራል፡፡
ሉሲ ከተማ ውስጥ ተወልዳ በመሀከለኛ ገቢ የሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ እንደ ዘበኛም እንደ ጓደኛም ሆና የኖረች ውሻ ናት፡፡ እንደ ከተማ ተወላጅ፣ የተፈጥሮ የውሻ ባህሪዋን ሳትለቅ፣ የከተማ ልጅ አራድነትም አዳብራለች፡፡ … እንደ ውሻ አጥንት፣ እንደ ጦጣ ሙዝ ትበላለች፡፡ ምቾትን እንደ እንስሳ ትጠየፋለችም፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ትደግፋለች። የቤተሰቡን አባላት ስታይ አንዳንዴ ጭራዋን ትቆላለች … ሌላ ጊዜ አርፍዶ የመጣ የቤቱ ሰው ላይ እንደ ባዳ ትጮሃለች፡፡ …
የቧንቧ ውሃ እየተበላሸ መጥቷል በተባለ ሰሞን፣ ቤተሰቡ ውሃ እያፈላ መጠጣት ሲጀምር፣ እሷም ከቧንቧ ውሃ ታቅባ ነበር፡፡ የሚያቀብጣት ካገኘች ማስቲካም ስጡኝ ብላ ታኝካለች፡፡ ገላዋን መታጠብም ለምዳለች፡፡ ከታጠበች በኋላ ጠጉሯ ሳይደርቅ አፈር ላይ ትንደባለላለች። ሙዚቃ ከቤተሰቡ እኩል ታዳምጣለች፡፡ ጥሩ ሙዚቃ ሲከፈት በጸጥታ ተኝታ ትሰማለች፡፡ መጥፎ ሙዚቃ ሲሆን ትቆጣለች። በውሻነትና በሰውነት ወይም በመሀል ተምታቶባታል። ድመት ማሳደድ ትታለች። እንዲያውም ሳትፈራቸው አትቀርም። ሰው እያያት ከሆነ ግን ድመቱን አለመፍራቷን ለማሳየት አክሮባት ትሰራለች፡፡ አራዳ ናት፡፡
… መብራት ከጠፋ ደጅ መቀመጥ አትችልም፤ ሳሎን ውስጥ ገብታ አልወጣም ትላለች። መብራት ሲመጣ ከማጨብጨብ ባልተናነሰ ጭራዋን ትቆላለች። አሁን ከሞተች ሁለት ዓመት ሞልቷታል። በቤተሰቦቹ አባላት እንደ ሰው ታዝኖላታል፡፡ እንደ ተስካር የመሰለ የቡና ቁርስ ፕሮግራም መላው ቤተሰቡ ከያለበት ተጠራርቶ አከናውኖላታል፡፡
ትዝ ይለኛል … ቃለ መጠይቁን ያደረግሁላት ቀን፣ ትንሽ ቅንጥብጣቢ ስጋ ከፍሪጅ አውጥቼ ወረወርኩላትና ከፊት ለፊቷ ቁጢጥ አልኩኝ። … ሰውን ክትፎ ጋብዘኸው እየተስገበገበ ሲበላ ለማየት ለጠጥ ብለህ፣ እየተኩራራህ፣ በመመፃደቅ እንደምትመለከተው … እኔም ሉሲን ተመለከትኳት። … ግን ሉሲ አራዳ ናት፤ ስጋውን እንዳላየች ችላ አለችው፡፡ “ብርቄ አይደለም …. በስጋ መብላት ረገድ ያልፈሳሁበት ዳገት የለም” እንደ ማለት ተመልሳ ተኛች፡፡ በስንት መከራ ጭንቅላቷን አሻሽቼ፣ ስትበላ እንዳላያት ዞር ብዬላት … ትንሽ ቆይቼ ተመለስኩኝ። ስመለስ ስጋውን በልታ … ቡና ተጠጥቶ ጭላጭ እንደ ማስቀረት አይነት ለክብሯ የሚመጥን የስጋ ትራፊ ትታለች፡፡
“ሉሲ?” አልኳት፡፡
“እመት” አለች፡፡
“አንዴ ላናግርሽ?”
“ስለ ምን? …” ብላ እንደ አራድነቷ ሳትቸኩል፣ ግን መጓጓቷን ለመደበቅ እየጣረች፣ ሰንሰለቷን እየጎተተች ከውሻ ቤቷ ወጣች፡፡ የሰንሰለቱን ዘለበት ከአንገቷ ላይ አወለቅሁላት፡፡ … የቂሊንጦ እስረኞች እንኳን ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ካቴና ይወልቅላቸዋል፡፡ የኋላ እግሮቿ ላይ ቂጢጥ ብላ ጥያቄውን መጠበቅ ጀመረች፡፡
“ሉሲ … የአባትሽን ስም ስለማላውቀው በምትኖሪበት የቤት ቁጥር ስም ብጠራሽስ አትቀየሚም አይደል?”
“አልቀየምም … በጋሼ ስምም ልትጠራኝ ትችላለህ … በሀበሻ ስሜ ድንቅነሽ ልትለኝም ትችላለህ…” አለች። ከሰው ጋር ያላትን ዝምድና ለማረጋገጥ የምትጥረው ሰው መሀል ስትሆን ነው። ውሾች መሀል ስትሆን ሌላ ባህርይ ነው ያላት።
“ሉሲ፤ ተመችቶሻል? እዚህ ቤት በአባቴ ኃላፊነት ስር መኖርሽ ደስተኛ አድርጎሻል?”
ይሄንን ጥያቄ የጠየቃት አባቴ ቢሆን ኖሮ መልሷ ሌላ ነው፡፡ … ከእኔ ጋር ስትሆን አባቴን ልታማ ሁሉ ትችላለች። … የውጭ ሰው ከመጣ ግን ቀለብ ለሚቆርጥላት ቤተሰብ ወይም መንግሥት ነው የምትቆመው፡፡ አንዳችንን አንድ ሰሞን አኩርፋ፣ ሌላ ሰሞን ሽርኳ የነበረውን ትጣላለች፡፡ የውጭ ሰው ከመጣ ግን ለቤተሰቧ ወይም ለቤቷ ነው የምትቆመው።
“…ደስተኛ አድርጎሻል ነው ያልከኝ?” አለች፡፡ “ምን ደስታ አለ፡፡ ሰንሰለቱ አንገቴ ላይ ዝጎ ቲታነስ ሊያሲዘኝ ምንም አልቀረውም፡፡ የሰራችሁልኝ ቤት ጣራው ያፈሳል፡፡ መብራት አስገባልሻለሁ ብላችሁ አሁንም በግቢ መብራት እየተጨናበስኩ ነው የምተኛው፡፡ … በዛ ላይ ሰዎች በሩን ሲያንኳኩ ለምን ቀስ እንደማይሉ አላውቅም … በመሸማቀቅ ብዛት የስነ ልቦና ቀውስ ውስጥ  ተዘፍቄአለሁኝ። … ሳለከልክ ምላሴን ያመኛል … በዛ ላይ ሰፈር ቀይረው የመጡ አዲስ ድመቶች ግቢውን መቆጣጠር ይፈልጋሉ፡፡ … ከቤት የሚሰጠኝን ምግብ ሁለት ሆነው ለመንጠቅ እየሞከሩ፣ ህይወቴን ስጋት ውስጥ ከተውብኛል፡፡ ድመቶቹን ተከትለው የመጡ ኃይለኛ የዱር አይጦችም አሉ፡፡ … ወጥመድ አስገዛልኝ ብልህ አልሰማ አልክ … እና በጣም ደስተኛ አይደለሁም።” ብላ አይኗን ሁለት ጊዜ በፍጥነት ጭምቅ አደረገች፡፡ እየተጣቀሰች ይሁን እያለቀሰች እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እልም ያለች አራዳ ናት፡፡ ምስኪን መስላ ድንገት ልትለወጥ ትችላለች፡፡
“…ተይ ተይ ተመችቶሻል! ወፍረሻል … ፀጉርሽ እንደ ወርቅ ያንፀባርቃል፡፡ … ይልቅስ የቤቱን ባለቤት አመስግኚ… ይሄንን የመሰለ ህይወት ስለሰጠሽ። … ሌሎቹ የመንደር ውሾች ምን እንደመሰሉ አታውቂም መሰለኝ፡፡ … ከተማ ያሉ ውሾች መንገድ በተሰራበት ሁሉ በመኪና ተደፍጥጠው አልቀዋል፡፡ … ስንቱ ውሻ መሰለሽ ይኖር የነበረው ቤት በልማት ሲፈርስ ባለቤቶቹ ኮንዶሚኒየም ይዘውት መግባት ስለማይችሉ፣ ሜዳ ጥለውት በርሃብ የሞተ… ስለዚህ ጥጋበኛ አትሁኚ …” አልኳት፡፡
አውቄም ይሁን ሳላውቅ የመጣልኝን ነበር የተናገርኩት። ንግግሬ ኮሰኮሳት … ከተቀመጠችበት እመር ብላ ተነስታ፣ ዘራፍ እንደ ማለት፣ አንድ ሁለቴ ጮኸች፡፡ ጩኸቷ በታክሲው ውስጥ መልስ ስጠኝ ብሎ ለመቆጣት እንደሚሞክር … በእፍረትና ይሉኝታ እንደተጨናነቀ የከተማ ነዋሪ፣ መቅለስለሷ ተድበስብሶ … ጩኸት ሳይሆን ሳል መሰለ።
“…አሁንስ እንደናንተ ልማታዊ መንግሥት ሆንክብኝ … አሻሻልኩሽ … ስልጣኔ አስተማርኩሽ .. ባቡር አስገባሁልሽ ገለመሌ! …. እኔ ተንከባከበኝ ብዬሃለሁኝ … ማን አምጥተህ ቤትህ ውስጥ እሰረኝ አለህ? … እንዲያውም የጎዳና እና የገጠር ውሻ ህይወት በስንት ጣዕሙ፡፡ ምግብ ፈልጌ እንዳልበላ ፍርፋሪህን አስለምደኸኝ … በብርሃን ፋንታ የአምፖል ጥገኛ አድርገኸኝ … ልትኮሪ ይገባሻል ትለኛለህ?! … እንደ አንዳንድ የከተማ ነዋሪ መሰልኩህ እንዴ … አንተ እንድል የምትፈልገውን ጩኸት የማስተጋባልህ?! ደግሞ በዛ ላይ ጠግበህ የወረወርክልኝ ፍርፋሪ አልፈጭ ብሎ ሆዴ ቢወጠር … ጭንቄን በውፍረት ተርጉመህ፣ የውፍረቴ ደራሲ ልትሆን ትፈልጋለህ፡፡ …. አቦ ተወኝ!” ዘራፍ እንደ ማለት የደካማ ጩኸቷን ጦር ሰብቃ፣ ጠጋ ጠጋ ትለኝና … ተመልሳ ሸሸት … ሸሸት ትላለች፡፡ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ መስማት የሰለቸኝን የሽለላ ድራማ፣ በውሻ ቅርፅ በማየቴ አልተገረምኩም። ሉሲ አራዳ ናት። ገና ከመነሻው ለባህር ማዶም ለሀገር ውስጥም የሚሆን ስም ሲወጣላት ነው ግራ የተጋባችው። ስለ ኢቮሉሽንም ስለ ክርኤሽንም ሽንጧን ገትራ ልትከራከር ትችላለች። ሀይማኖታዊም … ኢ-አማኒም ቅርፅ ልትይዝ ትችላለች። ያደገችበት ከተማ ባህሪ ነው፡፡ ወይም በከተማው ውስጥ የገነነው ባህል ነፀብራቅ።
“በይ ተረጋጊ! አምስት አጫጭር ጥያቄዎች ልጠይቅሽ ነበር … ግን ሙድሽ ትንሽ ያስፈራል … ስለዚህ ሌላ ጊዜ ላድርገው”
“…አይ ማለቴ … ተመችቶሻል ስትለኝ ነው እንጂ መናደድስ አልተናደድኩም ነበር፡፡ መጠየቅ ትችላለህ ጥያቄውን … ጥያቄውን ሬዲዮ ላይ ነው የምታቀርበው ወይስ ጋዜጣ ላይ…. ጋዜጦቹ ሾቀዋል … አባትህ እንኳን መግዛት አቁሟል፡፡ ሬዲዮኖቹ ደግሞ አዝግ ሆነዋል፡፡ እከታተላለሁ እኮ! አልሰማም እንጂ እከታተላለሁ፡፡ .. ሀገሩ በረብሻ ተበጥብጧል አሉ…። በኦሮሚያና በአማራ ነው አሉ የበረታው። … ለነገሩ የሰው ዜና ምን ያደርግልኛል … የውሻ ጉዳይ ማንም መጣ ማን አይቀየርም፡፡ … “የውሾን ጉዳይ ያነሳ ውሾ ይሁን” ተብሏል፡፡ እሱን ታሪክ ታውቀዋለህ?! አንተ ከልጅነቴ ጀምሮ ታውቀኛለህ … እዚሁ ሰንሰለቴ እንኳን ሳይቀየርልኝ ልሞት ነው። አንተ ግን ቢያንስ ቤት ቀይረሃል…፡፡ እዚሁ ቤት አስራችሁኝ … በሬዲዮ ጩኸት፣ በማይስማማኝ ምግብ አደንዝዛችሁ፣ የፍርፋሪ ሱሰኛ አድርጋችሁ አስቀራችሁኝ፡፡ … እኔን ተጠግተህ የምትቀዳው ለጋዜጣ ወይም ለሬዲዮ አይደለም፤ ነቃሁብህ! ያልኩትን ቀድተህ ለአባትህ ልታስደምጥ ነው አይደል? … አንድ ለአምስት ተደራጅታችሁብኛል። ቃሌን ለማስረጃ ልትቀበልና አባትህ፤ ያ ክትባት እያለ ውሃ እየወጋ በየስድስት ወሩ ብር የሚቀበለውን … የእንስሳት ሀኪም ነኝ የሚለውን ጠርቶ… የውሻ መግደያ መርፌ እንዲያስወጋኝ ለማድረግ ነው --- አይደል?! ቅዳ -- በደንብ አድርገህ ቅዳ … አምስት ጥያቄ ልጠይቅሽ ትለኛለህ --- የከተማ ውሾች ህይወትና የሥነ ልቦና ጉስቁልናን በጋዜጣ የምታሳትም አስመስለህ!
“ልንገርህ አይደል … ከከተማ ሰው ይልቅ የገጠር ሰው ይሻለኛል፡፡ ቢያንስ እንደ ተፈጥሮዬ በነፃነት እኖራለሁኝ…። አሁን አርጅቻለሁ፤ ገጠር ገብቼ ከገበሬ ጋር ልኑር ብል እንኳ አልችልም፡፡ የሱሴ ብዛት ራሱ ከዕድሜዬ ቁጥር የትና የት ነው፡፡ ንገረው አባትህን፣ አንካሳ ዶሮ ሳይቀድምህ … የቢራ ጠርሙስ በረንዳ ላይ ሲደረደር ሁሌ … ጭላጩን እንደምጠጣ! ንገረው!…። መጽሐፍም አነባለሁ። ምን ያልሆንኩት አለ? በቃ ውሻ ስለሆንኩ የማስበው የሌለኝ ይመስልሃል፡፡ …ስሜትም አእምሮም አለኝ፡፡ እሳት ወይ አበባ የሚለው መድበል ላይ ያለውን ግጥም በሬዲዮ ደጋግሜ ሰምቼ በቃሌ ይዠዋለሁኝ … ልበልልህ? … በቃ ለዓመት በዓል የበግ ጭንቅላት ሲጣልልኝ ከመጋጥ ከፍ ያለ ህልም ያለኝ አይመስልህም አይደል፡፡ አቦ ሰው ነኝ እያላችሁ አትኩራሩ! ደግሞ የከተማ ልጅ ሰው ነው? … የሀይላንድ ውሃ ቢቋረጥ በተቅማጥ ትሞታለህ እያንዳንድህ … እና ቅዳ … በደንብ አድርገህ ያልኩትን ቅዳ! አንት የቤተሰብህ ካድሬ!…”
እየተመላለሰች፣ እየተራመደች፣ አልፎ አልፎ እየተቀመጠች ስታወራ … የሚያብረቀርቀው ፀጉሯ ሽበት መሆኑን ተመለከትኩኝ፡፡ ውሻን ያሸበተ ከተማ፤ ሰውን ምን ሊያደርገው እንደሚችል ማሰብ አልፈለግሁም፡፡ … ውሻ ከዚህ ቀደም እንደሚያብድ የማውቀው “በሬቢስ” በሽታ ሲጠቃ ብቻ ነበር። ለሀጩ ሲዝረበረብ … ሰው ሲናከስ፡፡ እያለቀሰ፣ እየተነፋረቀ … አይኑ ቀልቶ እየጮኸ የሚያብድ ሰው ነበር፤ ድሮ። ሉሲን ልጠይቃት ያሰብኩት ጥያቄዎች ጠፉብኝ። እንደው ለጨዋታ ያህል ነበር እንጂ ስራዬ ብዬ ያዘጋጀሁት ጥያቄ የለም፡፡ … ሉሲ ደስተኛ አለመሆኗ ግልፅ ሆነልኝ። አለመሆኗ አይገርምም … ውሻ ሁሌም እንደተልከሰከሰ ኖሮ የሚሞት ፍጡር ነው፡፡ ሉሲ ደስተኛ አለመሆኗን በእኔ ቋንቋ በመግለጿ፣ እንደ ውሻ ችላ ልላት አልቻልኩም። … ቀዳሁዋት። ደግሞ ዛሬ መልሼ አስታወስኳት፡፡ ሁለት ዓመት ቆይታ ሞተች። ያ የእንስሳት ሀኪም ሊያድናት በጣም ሞክሮ ነበር አሉ። ለሙከራው ሁሉ ጥሩ አድርጎ አባቴን አስከፍሎታል። ሉሲ ስትሞት ቤተሰቡ ሁሉ አዘነ፡፡
እኔም በመቅጃ የቀዳሁትን እንደ ሰው ቃለ መጠይቅ፣ ለከተማዋ አራዳ ውሻ ክብር ስል ወደ ወረቀት ድምጿን ገለበጥኩት። እዛው ግቢው ውስጥ ነበር የተቀበረችው። የቀብር ሥነ-ሥርዓቷ ላይ አልተገኘሁም፡፡ ስልክ ተደውሎ ሲነገረኝ ግን የትምህርት ቤት ጓደኛ ወይ የሞያ ባልደረባ ሲሞት ከማዝነው ባልተናነሰ አዘንኩኝ። የተቀበረችው አጥር ስር ነበር፡፡ መንገድ ሲሰራ አጥሩ ጥቂት ሜትር ወደ ግቢው ፈርሶ እንዲጠጋ ተደርጓል። አሁን የሉሲ መቃብር ብዙ መኪና ሲወጣና ሲወርድ የሚውልበት … ብዙ የሚንከወከው ውሻ ከሰፈር እየወጣ የሚጨፈለቅበት አስፋልት ሆኗል፡፡

Read 1176 times