Saturday, 21 April 2018 13:51

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(3 votes)

 “--ታላላቅ መሪዎች ደሃውን ህዝብ ያከብራሉ፡፡ ህመሙን ይታመማሉ፣ ረሃቡን ይራባሉ፣ ሞቱን ቀድመው ይሞታሉ፡፡ ሲድንም ይድናሉ፣ ሲጠግብም ይጠግባሉ፣ በትንሳኤውም ይነሳሉ፡፡ ህዝባቸው ትልቅ ሲሆን እነሱም ትልቅ ይሆናሉ፡፡--”
    
   በአንዲት የአውሮፓ ሃገር ነው አሉ፡፡ ሁለት መንገደኞች ጎን ለጎን ተቀምጠው በባቡር ሲጓዙ፡-
“አየሩ ቀዝቃዛ ነው” አለ አንደኛው፤ ከጎኑ ለተቀመጠው፡፡
“አዎ ይቀዘቅዛል፤ እንደ‘ኔ ደርበህ መውጣት ነበረብህ”  መለሰለት፤ሌላኛው፡፡
“የአየሩን ፀባይ ገና አለመድኩትም”
“እንግዳ ነህ?”
“አዎ”
“የምን አገር ሰው ነህ?”
“አሜሪካዊ ነኝ”
“ኦ! … እንኳን ደህና መጣህ፡፡ አገራችን አገርህ ነው። ያለ ጥርጥር የተመቸ ጊዜ ይኖርሃል፡፡”
“አመሰግናለሁ!”
“እኔም አገሬን ለመጎብኘት በመምጣትህ አመሰግንሃለሁ፤ ደስ ብሎኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ አገራችሁ አሜሪካ የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት፣ የዜጎች ነፃነት የተከበረባት በመሆኑ አድናቆቴን ተቀበለኝ”
“እንደገና አመሰግናለሁ፡፡ እንዳልከው አገራችን የህዝቦቿን ጥቅም በሚያስከብር ህገ መንግስት ላይ በተመሰረተ ዴሞክራሲ የምትተዳደር ሃገር ናት፡፡ መሪዎቿም እኛን ለማገልገል የሚፎካከሩ በመሆናቸው እንኮራባቸዋለን፡፡ አገራችንን ለገነቡት የቀድሞ አባቶች ምስጋና ይሁንና!!… እናንተስ?”
“እኛም እንደ እናንተ የህዝቦችን መብትና ነፃነት በሚያስከብር ህገ መንግሥት ላይ በተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የምንተዳደር ነን፡፡ ለዚህ ነው ህዝባችን ሃብታም፣ የሰለጠነና እንግዳ አክባሪ የሆነው፡፡ እኛ ሃገር ባለስልጣናት ከስራቸው ውጭ እንደ ማንኛውም ዜጋ ነፃ ናቸው፡፡ የትም ቢሆን ማለትም ሬስቶራንት፣ ሲኒማ ቤት፣ የህዝብ መጓጓዣ የመሳሰሉት ቦታዎች ልታገኛቸውና በፈለግኸው ጉዳይ ልታወራቸው ትችላለህ። ቅሬታ ካለህም ለጓደኛህ እንደምትነግረው ያህል ያደምጡሃል፡፡ ለምሳሌ …”  ጨዋታቸውን ሳይጨርሱ ባቡሩ ቆመ፡፡ ሁለቱም ሰዎች ወረዱ፡፡
*   *   *
የመጀመሪያው ሰው የሃሳብ ውልደት ነው። “ሰውን በአምሳላችን ፈጠርን” ሲባል የፀጉር፣ የአፍንጫ፣ የቁመናና የቀለም ጉዳይ አይደለም፡፡ ምናልባት የህዋስና የሞለኪዩል ወይም የአእምሮና የልብ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰዎች ሁሉ ኢየሱስን አይመስሉም፡፡ ጥቁር ሆነው ንፁህ ልብና ብሩህ አእምሮ ያላቸው፣ ነጭ ሆነው ጨካኝና ደንቆሮዎች ሞልተዋል፡፡ ኢ-አማንያንና በአዝጋሚ ለውጥ ለሚያምኑ ደግሞ ሰው፣ ‹ሰው› ከመሆኑ በፊት አውሬ ወይም እንስሳ ስለነበረ ነገሩ እዛ ላይ ያበቃል፡፡ ወይም እዛ ጋ ይጀምራል፡፡፡
እንደ እስልምና አይነቶቹ (Monotheist) እምነቶች፣መለኮታዊ ባህሪን እንጂ የህላዌ ሥጋን (Physical essence) መኖር ይጠራጠራሉ፡፡ አምላክ አይወልድም፣ አይወለድም፣ አይታይም፣ አይገለጥም ይላሉ፡፡ ነገር ግን ከነሱ በፊት የነበሩት የአይሁድና የብሉይ ነቢያትና ካህናትን ይቀበላሉ፡፡
ከሁሉም በላይ ብዙ ተከታዮች ያሏቸው፣ ዕድሜ ጠገቦቹ .. የሂንዱ፣ ቡድሂዝም፣ ጃኒዝም፣ ታኦኢዝም፣ ሺንቶኢዝምና ፓንቴኢዝም የመሳሰሉት እምነቶች፤ ከጁዳኢዝም፣ ከክርስትናና እስልምና ጋር በነገረ መለኮትና በፍጥረት ታሪክ ጨርሶ አይግባቡም። ነገር ግን እንደ አስርቱ ትዕዛዛትና የወርቃማው ህግ ምሳሌዎች ውብ የሆኑ የእውቀት ፀጋዎችን በፍቅር ይጋራሉ፡፡ እንደውም የእምነታቸው መሰረት እነሱ መሆናቸውን ያስተምራሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ እንዲሁ የየራሳቸው መንገድና እሳቤ አላቸው - በግልም በጋራም። ለምሳሌ፡- ስነ ፍጥረት ረቂቅ ነው የሚለው ወንድምህ እንዲህ ያስባል፡-
God is order,
Nature is change,
We are music
You and me,
Dancing stars,
Singing birds,
Past, present and the future,
They are all ‹Now› and here!
“Far in the eyes”,
Near to the mind.
Like u and me, united!!       
*   *   *
በፍጥረት ህግ “ብዙ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሏት” ተብሎ ተደንግጓል፡፡ ባይፃፍላቸውም .. ሸረሪት ጉንዳንና አሜባ የመሳሰሉትን ጨምሮ ፍጥረታት ይባዛሉ፡፡ መንገዱ ይለያይ እንጂ። የሌሎቹ ፍጥረታት የ‹አስተሳሰብ መንገድ› ባይገባንም፣ የሰው ልጅ ራሱን ብቻ ሳይሆን ትልልቅ ሃሳቦችንም ይወልዳል፤ ያባዛል፡፡
ሌሎቹን ሃሳቦች እንደ ‹መናጆ› ከጎን አቁመን፣ “ሰውን በአምሳላችን ፈጠርን” የሚለውን ዓረፍተ ነገር ስናስብ … ካህሊል ጅብራን ‹Power of individual Wisdom› በሚለው መጣጥፍ፡- “ይቺ ትልቅ፣ የብዙ ፍጥረታት ‹አገር” የሆነችው እናት ምድር ድንቅ ናት፡፡ ይቺ የጋራ ቤት የተዋበችው በትላልቅ አእምሮ ውስጥ በተፈጠሩ ሃሳቦች ነው። ፒራሚድንና ታጅመሃልን ጨምሮ የዓለም ድንቃድንቅ አርክቴክቸሮች፤ በትላልቅ አእምሮ የተፀነሱ ሃሳቦች ናቸው” ይልና፤ ዛሬም የኒውክሊየር መሳሪያዎችን ጨምሮ ዓለምን የሚንጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና የእምነት ድርጅቶች የግለሰቦች ሃሳብ መሆናቸውን ያስታውሰናል፡፡
ጅብራን ሊነግረን የፈለገው፣ ሰዎች በተፈጥሮ አቋማቸው እንደሚለያዩ ሁሉ የአእምሮ ብቃታቸውም እንደሚበላለጥ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ትልልቅ ሃሳቦችን ያመነጫሉ፣ አንዳንዶች ከነሱ ያነሰ ወይም ያልተሻለ፣ አንዳንዶች ደግሞ ትንሽ ወይም የማይረባ፡፡
“እኩልነት በሌለበት እኩልነትን መጠበቅ ቅዠት ነው” (Men are by nature unequal, he, who seeks equality among unequals is absurd” የሚለን ደግሞ ታላቁ ስፒኖዛ ነው፡፡
ወዳጄ፡- እዚህ ጋ አንድ ነገር ልብ በል፡፡ ትላልቅ አእምሮ ያላቸው ሊቃውንትና ጠቢባን ወይም መሪዎች የህዝብ አገልጋዮች ነበሩ፡፡ አሁንም ናቸው። ህዝባቸው እንዲያውቅ፣ እንዲሰለጥንና ራሱን እንዲችል አብቅተውታል፡፡ የነበሩበት ጊዜ ላይ ቆመው “መጪውን እነሆ” (Here is the future) ብለውታል፡፡
ታላላቅ መሪዎች አላዋቂና ደሃውን ህዝብ ያከብራሉ፡፡ ህመሙን ይታመማሉ፣ ረሃቡን ይራባሉ፣ ሞቱን ቀድመው ይሞታሉ፡፡ ሲድንም ይድናሉ፣ ሲጠግብም ይጠግባሉ፣ በትንሳኤውም ይነሳሉ፡፡ ህዝባቸው ትልቅ ሲሆን እነሱም ትልቅ ይሆናሉ፡፡
ከክርስቶስ ልደት በፊት 400 ዓመታት ገደማ ላይ የኖረው ታላቁ እስክንድር፤ ያለ ምክንያት አልነበረም ‹ታላቅ› የተባለው፡፡ ሃገሩ ሜቄዶኒያ በሳይንስና በስነ ጥበብ እንድታድግ ያላደረገው ትግል አልነበረም፡፡ ሌላው ቀርቶ በሊቁ አርስቶትል የሚመራ ተመራማሪ ቡድን (Expeditionists) አቋቁሞ፣ በቂ ገንዘብና ቁሳቁስ በመመደብ፣ የአባይ ወንዝ መነሻን አስጠንቷል። ኦጋዴንን የሚያክል ግዛት እንኳ የሌላቸው እንደ ጣሊያን፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ ያሉ ትንንሽ አገሮች ምንም እንኳ ለተሸናፊውና ለተገዢው አበሳ ቢሆኑም አለምን እየተፈራረቁ በመግዛት፣ ህዝባቸውን ስልጡንና ገናና አድርገዋል፡፡
ወዳጄ፡- መሻልን ማሳወቅ የሚቻለው ተሽሎ በመገኘት ነው፡፡ ሌሎችን በማጥላላትና በማናናቅ ትልቅነት አይገኝም፡፡ ታላቁ ኮንፊዩሸስ፤ “ሁሌ ስለ ጨለማ ከማውራት አንዲት ሻማ ማብራት ይበልጣል” ይለናል!!
*   *   *
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- ሁለቱ ሰዎች ከባቡር ወርደው ሊሰነባበቱ እንደቆሙ አሜሪካዊው ቀደም ብሎ፤ “እንግዲህ እንዳንረሳሳ እገሌ እባላለሁ” በማለት ለአዲሱ ጓደኛው ስሙን ተናግሮ እጁን ሲዘረጋ፣ ሰውየው እቅፍ አደረገውና፤ “እኔም እገሌ እባላለሁ፤ የዚህ ሃገር ጠቅላይ ሚኒስትር ነኝ” አለው። አድራሻውንና ስራውን የሚገልጽ ካርድም (visiting card) ሰጠው፡፡ ደስ ብሏቸው እየተሳሳቁ ተለያዩ!!
ወዳጄ፡- የኛ ‹መሪዎች› ለምንድን ነው ቁጣ ቁጣ የሚላቸው?! እነሱም የሃሳብ ውልድ ናቸው። መጀመሪያ ቃል ነበረ እንዲሉ!! በነገራችን ላይ … “ሰው የሌለውን አይሰጥም” ይባላል፡፡ እውነት ነው፤ ከሌለው ከየት ያመጣል፡፡  
ሰላም!!

Read 1351 times