Saturday, 21 April 2018 13:49

የድምፃዊ ታምራት ደስታ አስደንጋጭ ህልፈት!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 (የሙያ ባልደረቦቹ ምን ይላሉ?)

    ድምፃዊ ታምራት ደስታ ከሻሸመኔ አለፍ ብሎ በሚገኘውና የሃዋሳ አጎራባች በሆነው ጥቁር ውሃ በ1971 ዓ.ም ተወለደ፡፡ ዕድሜው ለትምህርት እንደደረሰ በአካባቢው ትምህርቱን የተከታተለው ታምራት ደስታ፤ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ወደ ሙዚቃው ኢንዱስትሪ በመቀላቀል “ሀኪሜ ነሽ” የተሰኘውን የመጀመሪያ አልበሙን ለአድማጭ ጆሮ በማድረስ ከፍተኛ  ተወዳጅነትን ተቀዳጅቷል፡፡
ከዚያም የ“አንለያይም”፣ “ካንቺ አይበልጥም” እና “ከዚያ ሰፈር” የተሰኙ ተወዳጅ አልበሞችን ያወጣ ሲሆን አምስተኛ አልበሙን በማገባደድ ላይ ሳለ ነው ሞት በድንገት የቀደመው፡፡ ከድምፃዊነት ባሻገር የግጥምና ዜማ ደራሲ የሆነው ታምራት፤ የአምስት ልጆች አባት ሲሆን ሦስቱ ልጆቹ እዚሁ፣ ሁለቱ ደግሞ በጣሊያን እንደሚኖሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አርቲስቱ ባለፈው ረቡዕ ድንገት ባጋጠመው ህመም፣ ለህክምና በራሱ መኪና ከቤቱ ወጥቶ ሳይመለስ ቀርቷል፡፡ ወዳጆቹ እንደሚሉት፤ በአንድ የግል ክሊኒክ መርፌ በተወጋ በ30 ደቂቃ ውስጥ ነው ህይወቱ ያለፈው፡፡
ከትናንት በስቲያ ከቀኑ 9፡00 ሰዓትም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተፈፀመ ሲሆን በቀብር ስነ ሥርዓቱ ላይ በርካታ የሙያ አጋሮቹ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ገበየሁ ወርቅነህ፣ ቴዲ አፍሮ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ነዋይ ደበበ፣ ቀመር የሱፍ፣ ደረጀ ደገፋው እንዲሁም አድናቂዎቹ፣ ቤተሰቦቹና የቅርብ ጓደኞቹ ተገኝተዋል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በድምፃዊው ድንገተኛ አሟሟት ዙሪያ የሙያ አጋሮቹን አስተያየት አሰባስባ እንደሚከተለው አጠናቅራዋለች፡፡

     “ታምራት ከተረጋጉ ጥቂት ድምፃዊያን አንዱ ነበር”
(ድምፃዊ ደረጀ ደገፋው)
ከታምራት ደስታ ጋር የረጅም ጊዜ ትውውቅ ነው ያለን፡፡ በተለይ “አንለያይም” የሚለውን አልበሙን ከሰራ በኋላ ከጥበቡ ወርቅዬ ጋር አሜሪካ መጥተው ነበረ፡፡ ሳልለያቸው ነበር የማስተናግዳቸው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አድናቂው ሆንኩኝ፡፡ ከዚያ በኋላ በተለያየ አጋጣሚ መገናኘትና ጓደኝነታችንን ማጠናከር ጀመርን፡፡ የሚገርምሽ የዛሬ 10 ቀን፣ ገርጂ መብራት ኃይል የሚባል አካባቢ አብረን ቁርስ በልተናል (ረጅም ለቅሶ)፡፡ ዛሬ (የቀብሩ ዕለት ማለት ነው) ከሰዓት በኋላ የሙዚቃ ሥራ ለመስራትና በዚያውም ለመነጋገር ቀጠሮ ነበረን (አሁንም ለቅሶ ..) እውነቴን ነው በጣም አዝኛለሁ፡፡
ባህሪውን በተመለከተ ከተረጋጉ ዘፋኞች አንዱ ነው፡፡ አንዳንዶች እንደኔ “ታዋቂ ነኝ” በሚል፣ ልታይ ልታይ የሚሉ አሉ፡፡ ታምራት አንገቱን የደፋና እጅግ ሥነ ሥርዓት የተላበሰ ልጅ ነው፡፡ ማሪያምን ነው የምልሽ … የሱን ፀባይ ሳይ እሱን ባደረገኝ ሁሉ እላለሁ። የተረጋጋ፣ ልታይ ልታይ የማይል፣ ሰዎች ሙዚቃ እንዲሰሩ የሚገፋፋና ዜማ ካልሰራሁላችሁ ብሎ የሚለምን ነው፡፡ የዛሬው ቀጠሯችን ለእኔ ግጥምና ዜማ ሊሰራልኝ ነበር፡፡ ገርጂ ስቴዲዮ ያለው ወንድምአገኝ አሰፋ የተባለ አቀናባሪ አለ፡፡ የታሜ የቅርብ ጓደኛ ነው፡፡ ትላንት ደወለልኝና የታሜን ሞት ነገረኝ፡፡ “ምን አይነት ቀልድ ነው? እንዴት በዚህ ይቀለዳል? ለምን ታሟርታለህ” ብዬ ስልኩን ዘጋሁት፡፡ እንደገና ደወለና፤ “ለማመን ይከብዳል አይደል?!” አለኝ፡፡ እሱም ያለቅስ ነበር፤ እኔም እንደዛው፡፡ ሰው መኪና እያሽከረከረ ሄዶ፣ እንዴት በሳጥን ይመለሳል? የመጠየቂያ ሁለትና ሶስት ቀንኮ አለ (ረጅም ለቅሶ…) ሆስፒታል ደርሶ ቢሆን፣ የመዳን እድል ይኖረው ነበር፡፡ በአጠቃላይ የታሜ ነገር እጅግ ልብ ይነካል፡፡ ለሙዚቃው ዘርፍም ትልቅ ጎደሎ ነው፡፡ ከህይወት ታሪኩ ስሰማ አምስት ልጆች አሉት፡፡ እናቱም በህይወት አሉ፡፡ ልጆቹ እንዳይለያዩ፤ እንዳይቸገሩ … የበኩላችንን ማድረግ ይኖርብናል። ለታምራት ልጆች፣ ለመላ ቤተሰቡ፣ ለአድናቂዎቹና ለወዳጅ ዘመዶቹ መፅናናትን እመኛለሁ፡፡

ለዛሬ 9፡00 ሰዓት የቀጠረኝ እንድቀብረው ይሆን እላለሁ”
(አርቲስት ካሌብ አርአያሥላሴ)
ከታምራት ጋር የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ነው ያለኝ። ድሮ የምሽት ክበብ ነበረኝ፤ እዛ ሲመጣ ከነበረን ደንበኝነት ጀምሮ ነው የምንተዋወቀው፡፡ እሱ እነ ጎሳዬንና ሌሎችንም ይዞ ሲመጣ ቤቱ ይሞቃል፤ በጣም ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ታምራት የምሬን ነው የምልሽ … የፈጣሪ ስራ ሆነ እንጂ በዚህ ሰዓት ሞት አይገባውም ነበር፡፡ ሞት ለማንኛችንም የማይቀር ቢሆንም እንደ ቀልድ ከቤቱ ወጥቶ መቅረት የሚገባው ልጅ አልነበረም፡፡ በጣም አዝኛለሁ፤ መቀበል አቅቶኛል። ታሜ ዛሬ በህይወት ካጠገባችን ስለራቀ አይደለም፤ እጅግ የዋህ፣ ደግና ሩህሩህ ሰው ነበር፡፡ ሰው ካልሄደ ወይ ካልሞቱ አይመሰገንም ይባላል፡፡
ከታሜ ጋር እሁድ ጠዋት አብረን ቁርስ በልተን ነበር፡፡ ባልደራስ አካባቢ ቁርስ ስንበላ በርካታ የአካባቢው ህዝብ አይቶን ነበር፡፡ ሞተ ሲባል ብዙ ሰዎች እየደወሉ፤ “በቀደም አብራችሁ አልነበራችሁ? … ምን ሆነ? እውነት ነው?” እያሉ ጠይቀውኛል፡፡ ዛሬ 9 ሰዓት ላይ ቀጠሮ ነበረን፡፡ የቡና አስጨፋሪው አዳነና ሌሎች ለዛሬ ስንቀጣጠር ሰምተዋል፡፡ ዛሬ የተቀበረው 9 ሰዓት ላይ ነው፡፡ “ለዛሬ የቀጠረኝ እንድቀብረው ይሆን” እላለሁ፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡
ታሜ እናት ማለት ነው፡፡ በመዝናናትና በጨዋታ መሃል እንኳን ገብቶ ምክር የሚሰጥና የሚያበረታታ፣ በቁም ነገር የተሞላ ሰው ነው፡፡ ደግ ነው፡፡ በእድልም በልምድም ከሱ የሚበልጡ ግን የሚያከብሩት አርቲስቶች አሉ፡፡ እሱ ወረድ ብሎ ከእኛ ጋር ነው ጊዜ የሚያሳልፈው፡፡ እኛ ያልነውን ሁሉ ይሰማል። የሚዝናናው እንኳ አነስ ያለ ቤት ነው፡፡ በትህትና የተሞላ ሰው ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው፤ ድንገት ተነጠቅን።
ለዛሬ የተቀጣጠርነው ለእኔ የሚሆን ስራ እንዳለውና አንዳንድ ነገር ሊያደርግለኝ ፈልጌ ነው። ነገር ግን ምን እንዳሰበልኝ እንኳን ሳላውቅ ነው ያጣሁት። ፈጣሪ ለልጆቹ፣ ለቤተሰቡ፣ ለአድናቂዎቹና ለእኛም ለጓደኞቹ መፅናናትን ይስጠን እላለሁ፡፡
በቀጣይ ለልጆቹ እንክብካቤ በማድረግ፣ ለቁም ነገር ልናበቃቸው ይገባናል፡፡ በዚህ ላይ ሁሉም ቢያስብበት መልካም ነው፡፡ ልጆቹ ስለ ምንም ሳይጨነቁ ትምህርታቸውን መማር፣ ለቁም ነገር መብቃት አለባቸው፡፡ በተለይ አረጋኸኝ ወራሽ የማስተባበርና የማቀናጀት ተሰጥኦና ነፍስ ስላለው፣ እርሱ በዋናነት ኃላፊነቱን ወስዶ ለልጆቹ ዘላቂ የሆነ ነገር ቢደረግ እላለሁ፡፡
“እንደ ቀልድ መርፌ እየተወጉ ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ጉዳይ ትኩረት ያሻዋል”
(አርቲስት ንዋይ ደበበ)
ከሁሉ በፊት ለኢትዮጵያ ህዝብና ለቤተሰቦቹ መፅናናት እመኛለሁ፡፡ አየሽ ልጁ በጣም ተወዳጅ ነው። በጣም ትልቅ ተሰጥኦ ያለውና እጅግ የምናከብረው ልጅ ነው፡፡ ዜማ ያወጣል፣ ግጥም ይፅፋል፣ በድምፁ ይጫወታል፡፡ ይህ ደግሞ በእኔና በእርሱ መካከል የባህሪ ውርርስ ይፈጥራል፡፡ እጅግ ከማከብርለት ነገር መካከል ዋናው የፈጠራ ሰው … መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግነቱ ለጉድ ነው። ልጁ የዋህ ነው፤ ሩህሩህ ነው፡፡ የታምራትን ደግነት፣ ትዕግስት፣ ፀባይና ሥነ - ሥርዓት ይሄ ነው ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ ሰላማዊ ነው፣ ፍቅር ፈላጊ። ከጓደኞቹ ጋር አብሮ መብላትና ጊዜ ማሳለፍ ይወዳል። ለዚህ ነው እንደምታይው፣ ሰው ሁሉ አልቅሶ የማይበቃው፡፡
የወላይታን አንድ የልማት መዝሙር አብረን ሰርተናል፡፡ በወላይታ ልማት ማህር (ወ.ል.ማ) ማለት ነው፡፡  ለመሆኑ የድምፁን ቃና ሰምተሽዋል? በጣም ማር ማር የሚል፣ የማይጠገብ ልጅ ነበር፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር ለመንግስተ ሰማያት ያብቃው፤ ለቤተሰቡና ለወዳጆቹ መፅናናትን እመኛለሁ፡፡
በመጨረሻ በአፅንኦት መናገር የምፈልገው፤ ለመሆኑ ስንት ሰዎች ናቸው እንደዚህ መርፌ እየተወጉ የሚሞቱት የሚለውን ነው፡፡ የዚህ ልጅ ጉዳይ ጎልቶ የወጣው ታዋቂ ስለሆነ ነው፡፡ የህክምና ስህተት ተፈጥሯል አልተፈጠረም የሚለውን ሙያዬ ስላልሆነ የማውቀው ነገር የለም፤ ነገር ግን መኪናውን እያሽከረከረ ወጣ፤ መርፌ ተወጋ፤ በ30 ደቂቃ ውስጥ ህይወቱ አለፈ፡፡ በመኪና ወጥቶ በሳጥን ሲመለሽ ትንሽ አይከብድም? እስኪ ንገሪኝ … ቅር አያሰኝም ወይ? (በከፍተኛ ብስጭትና ቁጭት) እርግጥ የምርመራ ውጤቱ በቀጣይ ይፋ ይሆናል፤ ግን መንግስት ይሄን ጉዳይ በከፍተኛ ሁኔታ ተከታትሎ አንድ ነገር ላይ መድረስ አለበት፡፡ ሌላውም እየሄደ በደቂቃ ልዩነት ህይወቱን ማጣት የለበትም፡፡ ከፍተኛ ክትትልና ማጣራት መደረግ አለበት፡፡
ልጆቹን በሚመለከት እኛ አለን፤ የኪነ ጥበቡ ማህበረሰብ አላቸው፡፡ በተለይ አሁን ላይ በከፍተኛ ደረጃ በማህበር እየተደራጀን ነው ያለነው፤ እግዚአብሔር ፈቃዱ ከሆነ ወደፊት እንደዚህ ወጣት የሙያ አጋሮቻችን ድንገት ሲቀጠፉ፣ ቤተሰባቸውን እንዴት ማገዝ እንዳለብን እንመክራለን፤ እንተገጋገዛለን።
“ታሜ ለጥበብ የተፈጠረ ሰው ነው”
(አርቲስት ታደለ ገመቹ)
ከታሜ ጋር ከ18 ዓመት በላይ የዘለቀና የጠበቀ ጓደኝነት አለን፡፡ ሞቱን የሰማሁት ማመን በሚያቅተን መልኩ ነበር፡፡ የሱ ዜና እረፍት በሶሻል ሚዲያ ላይ ወጥቶ፣ ለእኔ እጅግ በርካታ ስልክ ይደወልልኝ ነበር። እኔ ደግሞ ስቱዲዮ ውስጥ ሆኜ ስልክ መመለስ አልቻልኩም፡፡ ከዚያ ወጥቼ ስሰማ ማመን ነው ያቃተኝ፡፡ ሰው ጋር ከመወደሌ በፊት ለተወሰነ ጊዜ ግራ ገብቶኝ፣ ደንዝዤ ነበር፡፡ ትንሽ ቆይቼ ነው እንቅስቃሴ የጀመርኩት፡፡ አረጋኸኝ ጋ ደውዬ፤ እውነት መሆኑን ሲነግረኝ፣ እንዴት ቤቱ እንደደረስኩም አላውቅም፣ በርሬ መጣሁ፡፡
እንደነገርኩሽ ከ18 ኣመት በፊት ተዋወቅን፣ ከዚያ በኋላ አብረን ብዙ ነገር አሳልፈናል፡፡ እንግዲህ ትውውቃችን እኔም እሱም አልበም ከማውጣታችን በፊት፣ ክለብ ውስጥ ስንሰራ ነው፡፡ ስለ ታሜ ብዙ ነገር ተብሏል፡፡
ዋናው ነገር ታሜ ለጥበብ የተፈጠረ ልዩ ሰው ነው፡፡ ለጓደኞቹና ለሰው ሁሉ ያለው ፍቅርና አመለካከት ልዩ ነው፡፡ በአጠቃላይ የጥሩ ሰው መመዘኛና መለኪያ ነው፡፡ ይህ አባባሌ “ሰው ሲሞት ነው የሚመሰገነው” በሚለው ባይወሰድብኝ ደስ ይለኛል፡፡ ታሜ ለሰው የሚኖር፣ ትሁትና ሽቁጥቁጥ፣ በጣም ጨዋ ልጅ ነው፡፡ ፈጣሪ ነፍሱን ለገነት ያብቃት ነው የምለው፡፡

Read 4360 times