Saturday, 21 April 2018 12:19

አዲሶቹ ሚኒስትሮች ምን ይላሉ?

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(14 votes)

   ከትናንት በስቲያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሾሙት ሚኒስትሮች፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መመሪያና በህግ አግባብ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት እንደሚጥሩ ገለፁ፡፡
አዲሱ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ በአገሪቱ አለ የሚባለው የፍትህ መጓደልና አግባብ ያልሆኑ አካሄዶች የሚፈጠሩት ከህግ ውጪና ህግን መሰረት ያላደረጉ አሰራሮች ሲተገበሩ መሆኑን ጠቁመው፤ የወንጀል ፍትህ ስርዓቱና አካሄዱ፣ ክትትልና ማስረጃ ማደራጀት ላይ መሰረት ያደረገ መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ትልቁ መሰረት ህዝብን ማሳተፍ ነው ይላሉ፡፡
“ህግ ማስተማሪያ እንጂ በቀል አይደለም” ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፤ “ሰዎችን ቀድሞ በመያዝ አስሮ መመርመር ተገቢ ነው ብዬ አላምንም” ብለዋል፡፡
“ዋናው ጉዳይ ሰው መቀየሩ አይደለም፤ ይልቁንም አሰራሩን መቀየርና ህዝቡን ተሳታፊ ማድረግ ነው” ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፤ “ማሰር መፍትሄ ሊሆን አይችልም” ይላሉ፡፡ “ህዝቡ በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ ያለውን ጉልህ ድርሻ በአግባቡ እንዲጠቀምበት ማድረግና የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማብዛት ከጠቅላይ አቃቤ ህጉ የሚጠበቅ ተግባር ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
“የፍትህ አካላት፡- ፖሊስ፣ አቃቤ ህግና ዳኛው መስራት የሚችሉት ግማሹን ብቻ ነው፤ ግማሹ ሥራ ከህብረተሰቡና ከሌሎች አካላት የሚጠበቅ ነው፤ ስለዚህም ህብረተሰቡን ማሳተፍ መሰረታዊና የማይታለፍ ተግባር ነው” ብለዋል፡፡
አዲሱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር አሚር አሚን በበኩላቸው፤ በተሰጣቸው ኃላፊነት የህብረተሰቡን እሮሮና ችግር ለመቀነስ በሚያስችል መልኩ ስራቸውን ለመስራት መዘጋጀታቸውን ጠቁመው፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አቅጣጫና መመሪያ በመከተል የአገሪቱ የዕድገትና የለውጥ ግንባታ አካል ለመሆን እንደሚተጉም ተናግረዋል፡፡
የህብረተሰቡን ምሬት መቀነስና ህዝቡን በስራዎቹ ውስጥ ማሳተፍ ተገቢ መሆኑን እንደሚያምኑበት ጠቁመው፤ ለዚህም አጥብቀው እንደሚሰሩ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
ተሰናባቹ አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ደግሞ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብን ውክልና ያገኙ ሰዎች የሚመክሩበት ጉባኤ እንደመሆኑ መጠን ሊጠናከርና የህዝብ ድምፅ ሊሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡ ህዝቡ በም/ቤቱ ማመንና መርካት ይኖርበታል ያሉት አባዱላ፤ ብዙ ጊዜ የምክር ቤቱ ችግር ተደርጎ የሚነሳው የህዝብ ችግርና ብሶቶችን አለማንሳቱና በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አለማሳለፉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “ጠንካራ ምክር ቤት ያስፈልገናል፤ በሁሉም ደረጃ ያሉት የህዝብ ተወካዮች ህዝብን መወከልና በደንብ መጠናከር አለባቸው፤ መንግስትም ለዚህ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል” ብለዋል - የቀድሞው አፈ ጉባኤ፡፡ ከአዲሷ አፈ ጉባኤ ብዙ እንደሚጠበቅ የተናገሩት አባዱላ፤ በእሳቸው የአፈ ጉባኤነት ዘመን ሳላደርገው ቀረሁ ብለው የሚፀፀቱበትና የሚቆጩበት ምንም ነገር እንደሌለ ጠቁመው፤ አቅማቸው፣ እውቀታቸውና ሁኔታዎች በፈቀዱላቸው መጠን አገራቸውንና ህዝባቸውን ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡
አገሪቱ ወጣቶች የማይሰደዱባት፣ ረሃብ የሚወገድባት፣ ድህነት ተሰርዞ ክብር ያለው ህዝብ የሚኖርባት እንድትሆን እመኛለሁ ያሉት አቶ አባዱላ፤ በቀሪው ጊዜያቸውም ከግማሽ በላይ የህይወት ዘመናቸውን ያሳለፉበትን ትግል በመቀጠል፣ መንግስታቸውንና ድርጅታቸውን እንደሚያገለግሉ ተናግረዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያዋ ሴት አፈ ጉባኤ ሆነው የተሾሙት ወ/ሮ ሙፈሪአት ካሚል በበኩላቸው፤ የተጣለባቸውን ከባድ የአገርና የህዝብ ኃላፊነት ለመወጣት ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልፀው፤ መንግስት የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝና ህዝቡን በብቃትና በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ ነኝ ብለዋል፡፡  

Read 7063 times