Saturday, 21 April 2018 12:17

በጥብቅ መመሪያ የታጀበው የጠ/ሚ የካቢኔ ሹመት

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(4 votes)

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፤ አዲሱ ካቢኔ ህዝቡ የሚያነሳውን ጥያቄ ለመመለስና እየታየ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት አሳሰቡ፡፡
ከትናንት በስቲያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስድስት ነባርና የአስር አዳዲስ ሚኒስትሮች ሹመት ባስፀደቁበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚኒስትሮች ሽግሽግ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል ብለዋል፡፡ የካቢኔ ሽግሽጉ የተደረገው ከፍተኛ ጥናትና ግምገማ ከተካሂደ በኋላ መሆኑን የገለፁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የአስፈፃሚ አካላት የማስፈፀም ብቃትን እንዲሁም የሰው ሃብትና ሰርቪስ አገልግሎት ሱፐርቪዥንና የዋናው ኦዲተር ሪፖርትን በመገምገም ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስትሮቹ የአቅምና የችሎታ ውስንነት ካለባቸውና ለመማር ዝግጁ ከሆኑ በመደጋገፍ ክፍተቱን መሙላት እንደሚቻል ጠ/ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ሚኒስትሮች በአራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡ እነዚህም ሙስናን መዋጋት፣ ብክነትን መከላከል፣ የሥራ ትጋት ባህልን መቀየርና የአገልጋይነት መንፈስን ማዳበር ናቸው፡፡
ሙስና አገሪቱን ለከባድ ችግርና ፈተና ዳርጓታል ያሉት ዶ/ር አብይ፤ ሚኒስትሮቹ በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ የመንግስትና የህዝብ ሀብት ያለአግባብ እንዲባክን እየተደረገ መሆኑን በመጥቀስም፤ አገሪቱ በሌላት ሀብት ብክነት ሲታከልበት ጉዳቱ ከፍተኛ ይሆናል ብለዋል፡፡ የመንግሥት ተቋማት የስብሰባ ባህልና ልማድ መሻሻል እንዳለበት የገለፁት ዶ/ር አብይ፤ ስብሰባዎች ቅዳሜና እሁድ አሊያም ከስራ ሰዓት ውጪ እንዲደረጉ አሳስበዋል፡፡
ጠ/ሚ አብይ አህመድ ለአዲሶቹም ሆነ ለነባር ሚኒስትሮች በሰጡት የስራ መመሪያ፤ ህዝቡ በመንግስት ላይ ቅሬታ የሚያቀርብባቸውን ችግሮች መቀየር ግዴታቸውና ቀይ መስመር መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ “ህዝብ ብዙ ነገር አይጠይቃችሁም፤ ግን መታወቂያ ለማውጣት ቀበሌው ሄዶ ገንዘብ እንዲከፍል ወይም ጉዳዩ እንዲፈፀምለት ለዘመድ እንዲያስደውል መገደድ የለበትም፡፡ እንደ ዜጋ ሊደረግለት የሚገባው ነገር ሁሉ በአግባቡና ያለአድልዎ ሊደረግለት ይገባል” ብለዋል፡፡ ዶ/ር አብይ “ቀይ መስመር ነው” ብለው ያሰመሩበት ሌላው ጉዳይ በተደራጀ ሁኔታ ህዝብን እያሰቃየ ያለው የሙስና ጉዳይ ነው፡፡ ሚኒስትሮቹ ራሳቸው ባይሳተፉበትም በሚመሩት መ/ቤት ሙስና እንዳይፈፀም ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ ሌላው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀይ መስመር፤ የመንግስትና የህዝብ ሃብትን ያለአግባብ ማባከን ነው፡፡ እነዚህን ቀይ መስመሮች አልፎ መገኘት ይቅር የማይባል ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
ከምክር ቤቱ አባላት ጥቂት ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን ሴቶችን ወደ ከፍተኛ የአመራር ቦታዎች በማምጣት ረገድ አሁንም ውስንነት ይታያል በሚል ለቀረበው አስተያየት አዘል ጥያቄ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፣ እስከ አሁን ድረስ የካቢኔ አባላትን የማደራጀቱ ተግባር የዘገየው የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሆነ ጠቁመው፤ አሁን ከተሾሙት ሴቶች ከተሰጠው ሹመት በተጨማሪ ብቃት ያላቸውና ቶሎ የማይሰበሩ ሴቶችን በቀጣይም እንደሚሾሙ ተናግረዋል፡፡
በአዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔ ሹመት ስድስት ሚኒስትሮች ካሉበት የሚኒስትር መ/ቤት ወደ ሌላ ተሸጋሽገዋል፡፡ በዚህም መሰረት የአገር መከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል። የማዕድን ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሞቱማ መቃሳ፣ የአገር መከላከያ ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል፡፡ የትራንስፖርት ሚኒስትር የነበሩት አቶ አህመድ ሺዴ መሀመድ፤ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ወ/ማሪያም፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል ዋና አስተባባሪ የነበሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ የግብርናና የእንስሳት ሀብት ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡
በቤልጅየም ብራስልስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር የነበሩት አቶ ተሾመ ቶጋ አዲስ ከተሾሙት አስር ሚኒስትሮች አንዱ ሲሆኑ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ዶ/ር አሚር አማን፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር፣ የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊና የገጠር ዘርፍ የፖለቲካ አደረጃጀት ኃላፊ የነበሩት አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ፣ ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ በአማራ ክልላዊ ብሔራዊ መንግሥት የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ጃንጥራር አባይ ይግዛው፣ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ኡመር ሁሴን አባ፣ በሚኒስትር ማዕረግ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር፣ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ኮሚሽነር የነበሩት ወ/ሮ ኡባ መሀመድ፣ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክጅኖሎጂ ሚኒስትር፣ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እምባ ጠባቂ የነበሩት ወ/ሮ ፎዚያ አሚን፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር፣ የአማራ ክልላዊ መንግስት ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር የነበሩት አቶ መላኩ አለበል፣ የንግድ ሚኒስትር እንዲሁም የትግራይ ክልል ምስራቃዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የነበሩት ያለምፀጋዬ አስፋው ደግሞ የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡
በሌላ በኩል ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባኤነታቸው በፈቃዳቸው በለቀቁት አቶ አባዱላ ገመዳ ምትክ፣ ወ/ሮ ሙፈሪያት ከማል የም/ቤቱ አፈ ጉባኤ ሆነው ተሾመዋል፡፡ አቶ አባዱላ ገመዳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ በመሆን ተሾመዋል፡፡ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ደግሞ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (INSA) ዋና ዳይሬክተር፣ አቶ አለምነው መኮንን፣ በሚኒስትር ማዕረግ የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ፕሬዚዳንት፣ ወ/ሮ ዳሚቱ ሀምቢሳ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር፣ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ፣ አቶ ያሬድ ዘሪሁን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል፣ ዶ/ር በቀለ ቡላዶ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር፣
አቶ ሞገስ ባልቻ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል የጥናትና ፐብሊኬሽን ዘርፍ አስተባባሪ፣ አቶ አህመድ አብተው በሚኒስትር ማዕረግ የፖሊሲ ትናትና ምርምር ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል፡፡

Read 7802 times