Sunday, 22 April 2018 00:00

የአገራችንን ኢኮኖሚ ያቃወሰ፣ የዜጎችን ኑሮ ያሽመደመደ፣ የዘመናችን “ቁልፍ በሽታ” ላይ ያላተኮረ መፍትሄ አያዋጣም!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(4 votes)

“የመንግስት ፕሮጀክቶችን እንደ አሸን የመፈልፈል ዘመቻ” - ይሄ ነው ቁልፉ በሽታ (“ስትራቴጂክ ነቀርሳ” እንዲሉ)።
“በየዓመቱ፣ ብዙ ቢሊዮን ብር የድሃ አገር ሃብትን በብክነት የሚያጠፋ ነው” - ቁልፉ በሽታ።
ዋና ዋና የአገራችን የኢኮኖሚ ቀውሶች፣ እየከፉና እየበረከቱ የመጡት በዚሁ ቁልፍ በሽታ ሳቢያ ነው።
የኢኮኖሚ መዘዞቹ፣ ከዚያም የፖለቲካና የትርምስ አደጋዎቹ
የግል ኢንቨስትመንትን የሚያሽመደምድ፣ ኤክስፖርትን የሚያደነዘዝ፣ የውጭ ምንዛሬን የሚያራቁት ነው - ቁልፉ ነቀርሳ።
550 ሚ. ዶላር ለዓመት ለወለድ ብቻ መክፈል? በኢትዮጵያ አቅም… ይሄ የጤንነት ሳይሆን የበሽታ ምልክት ነው።
የመንግስትን የውጭ እዳ፣ በአስር ዓመት ውስጥ ወደ አስር እጥፍ (ወደ 25 ቢ.ዶላር) ያደረሰም ነው - በሽታው።
ተመራቂ ወጣቶችን ሳይቀር በስራ አጥነት ለስደት የሚዳርግ፣ የኑሮ ቅሬታን የሚያባበስና የአገርን ህልውና ለትርምስ የሚያጋልጥ “የደህንነት አደጋም” ሆኗል።
በዋጋ ንረትንና በኑሮ ውድነት፣ የዜጎች ሕይወት የተመሰቃቀለውም በሌላ ምክንያት አይደለም። ማለትም፣ ብር የረከሰው፣… መረን የለቀቀ የገንዘብ ሕትመት የተጧጧፈው፣… ለአባካኝ የመንግስት ፕሮጀክቶችና ድጎማዎች በጀት ለማፍሰስ ነው። ከዚያስ?
ጥፋትን ለማድበስበስ ተጨማሪ ጥፋቶች - የመዘዝ መዘዞች
የዋጋ ንረትን፣ በነጋዴዎች ላይ ለማላከክ ምን ተደረገ? አምራቾችንና የግል ኢንቨስትመንቶችን ክፉኛ የሚዳክም፣ የመንግስት የዘፈቀደ ቁጥጥርና የዋጋ ተመን ተበራከተ። የመንግስት ፕሮጀክቶች መዘዝ ብዙ ነው።
የስንዴና የዳቦ እጥረት ለዓመታት እየከበደ የመጣው ለምን ሆነና? … የመንግስት የዋጋ ቁጥጥርና የድጎማ ውጤት ነው። እጥረትን የሚፈታ ሳይሆን፣ እጥረትን ወደ እጦት የሚያባብስ።
መፍትሄውስ? ፍቱን ሁነኛ መፍትሄ፣ እና የውሸት ከንቱ “መፍትሄዎች”
ከሁሉም በፊት የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት፣ የመንግስት ፕሮጀክቶችን ከመፈልፈል መታቀብና በዚያ ምትክ የግል ኢንቨስትመንቶች እንዲስፋፉ መፍቀድ ነው።
ማለትም፣… መንግስት በዘመቻ ከገባበት “የሶሻሊዝም ግርሻ” ለመላቀቅ፣… “የነፃ ገበያ መርህን” አጥብቆ ለመያዝ፣ እና “ወደ ካፒታሊዝም ስርዓት” ለመራመድ በእውቀትና በብርታት መጣር ነው መፍትሄው - በሽታውን እየቀረፉ በጤንነት ለመተካት መትጋት።  
ሚኒስትሮችን በመለወጥ፣ ባለስልጣናትን በመበወዝ ብቻ መፍትሄ አይገኝም። ቁልፉ ነቀርሳ ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ 100 ቅርንጫፍና ተቀጥላ የበሽታ ምልክቶችን ሲዘረዝሩና ሲያሳድዱ መዋልም ትርፍ የለውም - ጊዜንና ሃብትን ከማባከን፣ በሽታውንም ከማባባስ በቀር።

   የእለት የእለቷ ላይ ብቻ የማፍጠጥ አባዜ ነው፣ አገራችንን ጉድ የሰራት። ወሎ አድሮ የሚያመጣብንን መዘዝ ላለማየት፣ በጭፍንነት የመደናበር ሱስ ነው፣… የአገሪቱን ችግሮች እያባባሰ የኢኮኖሚ ውጥንቅጥ ውስጥ የዘፈቃት። የዛሬ የዛሬው ላይ አፍጥጠን፣ ለነገ የሚያስከትለውን ውጤት ለማሰብ አለመፍቀዳችን መፍትሄ አይደለም። በማግስቱ፣ አዳዲስ ቀውሶች እየተፈጠሩ፣ ለከርሞ እየተፈለፈሉ፣ ትብታቧ እየበዛ፣ መያዣ መጨበጫ እየጠፋባት የምትንከላወስ አገር ሆናለች። ምን ይጠየቃል? ዙሪያችንን ማስተዋል እንችላለን።
የዜጎች ኑሮ ሲናጋና የኑሮ ቅሬታ ሲደራረብ፣ ተመራቂ ተማሪዎች ሳይቀሩ በስራ አጥነት ሲማረሩ፣ በጦርነት እየፈራረሰች በምትገኝ በየመን አቅጣጫ ሲሰደዱ፣… የአገራችን ችግሮች ምንኛ ስር እንደሰደዱ ይመሰክራሉ። እናማ፣ በማንኛውም ሰበብና ግፊት፣ ወደ ስርዓት አልበኝነትና ወደ ትርምስ ለመግባት የተቃረበች አገር ሆናለች።
መንስኤዎቹ፣ ድብቅ ሚስጥሮች አይደሉም። መንግስት፣ በአዲሱ ሚሊዬንየም ዋዜማ፣ “የሶሻሊዝም በሽታ” ያገረሸበት ይመስል፣ የአገሬው ኢኮኖሚ ላይ እጅጉን ለመግነንና አለቅጥ ለመስፋፋት ግዙፍ ዘመቻ የጀመረ ጊዜ ነው፣ በርካታ የቀውስ መንስኤዎች የተፈለፈሉት።

ለብክነት የመጣደፍ ዘመቻ!
ከወዲህ በኩል፣ የጀመራቸው የኮንዶሚኒዬም ቤት ግንባታዎች እየተብረከረኩ እያየም፣… ከወዲያ በኩል ለተጨማሪ ግንባታዎች በጀት ይመድባል። የትናንቱ የገጠር ድጎማ፣ በየዓመቱ ወጪዎችን ከማሳበጥ ያለፈ ውጤት እንዳልተገኘለት እየታወቀ፣… ከግራና ከቀኝ፣… “የጤና ኢንሹራንስ”፣ “የከተማ ምግብ ዋስትና”፣ “የህፃናት ተማሪዎች ምገባ”… እያለ አዳዲስ ድጎማዎችንና ዘመቻዎችን ይፈለፍላል።
የድሃ አገር ሃብትን በከንቱ የሚያባክኑ የነፋስ ተርባይኖችን በብድር ሲገዛ ከርሞ፣ ከ10 ቢሊዮን ብር በከንቱ ማባከን ያነሰ ይመስል፣ አዳዲስ የብክነት ፕሮጀክቶችን ለማራባት ይጣደፋል። “የፀሃይ ሃይል ኤሌክትሪክ” እያለ፣ በጥቂት ወራት እድሜ የሚበላሹ ቁሳቁሶችን በብድር እያስመጣ፣ በርካታ ቢሊዮን ብሮችን ለማባከን ይራወጣል። ብዙም አልቆየም፣ አብዛኞቹ ስለተበላሹ፣ እንደገና ቁሳቁስ ለመግዛትና ለመጠገን በርካታ ቢሊዮን ብሮችን ከዓለም ባንክ አምጥቶ የብክነት ጉዞውን ተያይዞታል።
በወዲያ በኩል፣ ብዙ ቢሊዮን ብር የሚፈጁ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በደርዘን በደርዘን ይጥዳል። ከወዲህ በኩል፣ የመንግስት ፋብሪካዎችን በጅምላ እተክላለሁ ብሎ ወከባ ይጀምራል።
እንዲሁ ስታስቡት፣ “የፋብሪካውን ዲዛይኑንና የፋብሪካ ተከላውን ጎን ለጎን እናካሂዳለን። የፕሮጀክቱን ጥናትና ግንባታውን ጎን ለጎን እንሰራለን” ተብሎ የቢሊዮን ዶላሮች ፕሮጀክት በዘፈቀደ ይጀመራል? የስካር ፕሮጀክት ካልሆነ በቀር ማለቴ ነው። መንግስት ግን፣ አንድ ፕሮጀክት ወይም አንድ ፋብሪካ አይደለም፤… በደርዘን የሚቆጠሩ፣ 100 ቢሊዮን ብርና ከዚያ በላይ የሚፈጁ፣ በደርዘን የሚቆጠሩ ፕጀክቶችን ነው በአንድ ጊዜ የቀፈቀፈው።
(የዚህን ያህል የሚሳከርበት የግል ኢንቨስትመንት ብዙ የለም። ጥቂት ቢኖር እንኳ፣ የዜጎችን ሃብት ሳይሆን የራሱን ሃብት አባክኖ ነው የሚደኸየው። የመንግስት ባለስልጣናትና ሃላፊዎች ግን፣ ፕሮጀክት ቢሳካም ሆነ ቢሊዮን ብር ቢባክን፣… ኪሳቸው የሚገባ ትርፍም ሆነ ከኪሳቸው የሚጎድል ነገር የለም። የመንግስት ፕሮጀክቶችን ብክነትንና በሽታን ለመቅረፍ፣ ሚኒስትርና ባለስልጣንን መበወዝ ብቻ በቂ የማይሆነውም በዚህ ምክንያት ነው። ይህንን እውነታ ለማየትና ለመገንዘብ አለመፍቀድ፣… የምናብ አለም ውስጥ እየተንሳፈፉ እውኑ ዓለም ውስጥ በችጋርና በቀውስ መተራመስ ነው ትርፉ። የመንግስት ፕሮጀክቶችን በማስቀረት፣ አልያም በመቀነስ፣ ካልሆነ ደግሞ… ቢያንስ ቢያንስ ግንባታዎቹን ለግል ኩባንያ በኮንትራት በመስጠት ነው ቁልፉን በሽታ ማቃለል የሚቻለው)።
ባለስልጣንና ሃላፊ መለወጥ ብቻውን እንደመፍትሄ ከታየ ግን፣… ያው እስከዛሬ በተግባር እንዳየነው፣ ብክነቱና በሽታው እየተስፋፋ፣ ሌሎችንም እየመረዘ፣ ወደ ባሰ ተስፋ የለሽ ቅርቃር ውስጥ ገብተን ከመቅለጥ አንድንም። መንግስት፣ በቀድሞው ዘመቻና አያያዝ ለመቀጠል የሚሞከር ከሆነኮ፣…
ካሁን በኋላም እንደድሮው? በወጪ ላይ፣ እጥፍ ድርብ ወጪ፣ በሩጫ የመከመር ፉክክር? “በብክነት ላይ የባሰ ብዙ ብክነትን በፍጥነት የመፈልፈል እሽቅድምድም” ቢባል ይሻላል። በእዳ ቁልል ላይ፣ ከባድ የብድር እዳ የማምጣት ሽሚያና አዲስ ሬከርድ የማስመዝገብ ውድድር ነበር የሚመስለው።
መንግስትን ለማሳበጥ ከተጀመረው ዘመቻና ከብክነት እሽቅድምድሙ ጋር፣… የወጪም በዚያው ፍጥነት እየተለጠጠ ከዓመት ዓመት ያብጣል። ሌላ ምን ያደርጋል፣ ከዚህም ከዚያም ገንዘብ ለመሰብሰብ፣ ያንንም ያንንም ለማራቆት ቀን ከሌት ይካለባል። በወዲህ በኩል፣ ተጨማሪ የታክስ ሸክም ይጭናል። በወዲያ በኩል፣… “ምንም አይነት የብድር ሽታ አያምልጠኝ” የማለት ያህል፣ ነጋ ጠባ በአገር ውስጥ የተገኘውን ብድር ሁሉ እያግበሰበሰ ዕዳውን መከመር ይያያዘዋል። ከመንግስት ባንኮች ብቻ አይደለም። የፈቀደውን ያህል ብድር ከግል ባንኮች ለመውሰድስ ማን ይከለክለዋል? ካሰኘው ያስገድዳቸዋል። ለዚያውም እንደሌላ ተበዳሪ፣ በ10%፣ በ15% ወለድ ሳይሆን፣ በ3% በ4% ወለድ ከግል ባንኮች እበደራለሁ ሲል፣ ማን ከለከለው? እንደፈቀደው አድርጓል - የዘፈቀደ ስልጣን እንዲህ ነው።
በጥቅሉ፣ ከአገር ውስጥ ብድር ውስጥ 65% ያህሉ መንግስት እንደሚወስደው የአለም ባንክ መረጃ ያመለክታል - በአብዛኛውም ቢሊዮን ብሮችን በየዓመቱ ለሚያባክኑ ፕሮጀክቶቹ።
የመንግስት ፕሮጀክቶች፣ በታክስና በብድር አማካኝነት የተሰበሰበውን የድሃ አገር ሃብት በገፍ እና በዘመቻ ማባከናቸው ብቻ አይደለም ችግሩ። ኢንቨስትመንትን በማዳከም ስራ አጥነትን የማባባስ መዘዝንም ያስከትላሉ። የታክስ ሸክም በላይ በላዩ የተጫነባቸው የአገሪቱ አምራቾችና የግል ኢንቨስትመንቶች፣ እንደምንም ለማንሰራራት ቢሞክሩ እንኳ፣ በብድር እጥረት ሳቢያ ፈተና ላይ ይወድቃሉ።
በታክስ ጫናና በብድር እጥረት፣ የግል ኢንቨስትመንቶች ቀስ በቀስ እየተደካሙ ሲሄዱ፣ የኋላ ኋላ ነገር እንደሚበላሽ እንዴት አይታያቸውም? እንዴት አይታየንም? የዛሬ የዛሬውን ብቻ የምናይ ከሆነ፣… አዎ የነገው መዘዝ አይታየንም፣ አይታያቸውም።  የዘንድሮውን በጀት ብቻ እያዩ፣ የምናብ ዓለም ሪፖርቶችን ማዘጋጀት እንደቁምነገር ከተቆተረ፣… ለከርሞ የሚመጣው መዘዝ አይታያቸውም። “ፕሮጀክቶቹ፣ በተያዘላቸው እቅድና፣ በታቀደላቸው የጊዜ ሰሌዳ እየተከናወኑ ነው” የሚሉ የውሸት ሪፖርቶችን ለተከታታይ ዓመታት ተነብቦልናል - ቃል በቃል። ግን እስከመቼ? “ፕሮጀክቶቹ፣ በተያዘላቸው አቅጣጫ እየተከናወኑ ነው” የሚል አገላለፅ የተፈጠረው፣ ከጊዜ በኋላ ነው። ጭንቀታቸው፣ ሪፖርቶችን የማሳመር ጉዳይ ሆኖ አረፈው። የመንግስት ቢዝነስ እንደዚህ ነው። የዛሬ የዛሬው ላይ ብቻ ከማፍጠጥ ባሻገር፣ ለከርሞ ምን እንደሚከሰት የማስተዋል ፍላጎት ከየት ይመጣል?
መንግስት፣ የታክስ ሽክም በመጫንና የብድር ምንጮችን በማጨናነቅ ብቻ የማይመለሰውም በዚህ ምክንያት ነው። ወደ ሌሎች ዘዴዎች ይዘምታል። መቼም፣… “ማለቂያ የሌለው ታክስ ሸክም” ወይም “የማይሟጠጥ የብድር ምንጭ”፣ በአገሬው ውስጥ ሊኖር አይችልም። ቢሆንም ግን፣ መንግስት ይህንን በመገንዘብ፣ ወደ ህሊናው አልተመለሰም። የመስፋፋት ዘመቻውና የብክነት ሩጫውም አልተገታም።
አምራቾችና የግል ኢንቨስትመንቶች እየተዳከሙ፣ ለብድርና ለታክስ የሚሆን ተጨማሪ ምርትና ሃብት በአገር ውስጥ ሲጠፋ፣ መንግስት አርፎ አልተቀመጠም። የውጭ ብድር በገፍ አምጥቷል።

ለውጭ እዳ በዓመት ለወለድ የሚከፈል - ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ!
የመንግስት የውጭ እዳ፣ በጥቂት አመታት ውስጥ አስር እጥፍ ሆኗል - 2.5 ቢሊዮን ዶላር የነበረው የውጭ እዳ፣ ወደ 25 ቢሊዮን ዶላር የእዳ ክምር የተለወጠው በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው - ከ2000 ዓ.ም ወዲህ። በአብዛኛውም ለአባካኝ የመንግስት ፕሮጀክቶች። ዛሬ፣ የእዳው ክምር ብቻ ሳይሆን፣ የወለድ ክፍያው ብቻ ሲታይም ያስደነግጣል።
ለወለድ ክፍያው፣ በዓመት 550 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል። በዚያ ላይ የዋናው እዳ ክፍያም አለ። እናም በዓመት፣ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ነው፣ ለወለድና ለእዳ ክፍያ የሚገፈግፈው።
ኤክስፖርት እንደሆነ፣ ላለፉት አምስት አመታት፣ ስንዝር እድገት አላሳየም። የመንግስት ፕሮጀክቶችን ለማሳስፋፋት በተጀመረው ዘመቻ ምክንያት፣ አምራቾችና የግል ኢንቨስትመንቶች እየተዳከሙ፣… እንዴት ብሎ ኤክስፖር ያድጋል? በዚያ ላይ፣ በኤክስፖርት ያመጡትን ዶላር፣ መንግስት በአነስተኛ ምንዛሬ ነው የሚረከባቸው - መንግስት ራሱ በሚቆጣጠረው የምንዛሬ ተመን። እናማ፣ በኤክስፖርት ከሚገኘው 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ውስጥ፣ ግማሹ የውጭ እዳና ወለድ ለመክፈል የሚውል ሆኗል።
ዋናዎቹ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ገፅታዎች፣ እነዚህ ናቸው - የኤክስፖርት ድንዛዜና ከጣሪያ በላይ የጋሸበ የውጭ እዳ ክፍያ። የእነዚህ ሁለት ገፅታዎች ዋና መንስኤ ደግሞ፣ የመንግስት ፕሮጀክቶች እንደአሸን የፈሉበት ዘመቻ ነው - የሃብት ብክነትና መዘዞቹ ናቸው፣ ኤክስፖርትን አደንዝዘው፣ የውጭ እዳ ቁልልን ያስከተሉት።

የኤክስፖርት ገቢ፣ እንደመንግስት እቅድ ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ 15 ቢሊዮን ዶላር ይደርስ ነበር። ግን፣ ቀነሰ እንጂ አልጨመረም፣ የኋሊት ተንሸራተተ እንጂ ለመሻሻል ፎቀቅ አላለም - ባለፉት አምስት ዓመታት።
 ዓ.ም    ኤክስፖርት
2002    2.0 ቢ. ዶላር
2003    2.7 ቢ. ዶላር
2004    3.2 ቢ. ዶላር
2005    3.1 ቢ. ዶላር
2006    3.3 ቢ. ዶላር
2007    3.0 ቢ. ዶላር
2008    2.9 ቢ. ዶላር
2009    2.9 ቢ. ዶላር

እዳው ግን፣ በፍጥነት አድጓል። የወለድ ክፍያው ብቻ፣ በአስር ዓመታት ውስጥ በ10 እጥፍ ጨምሯል።
 እ.ኤ.አ    ወለድ    የዋና እዳ ክፍያ    የብድር ክፍያ
2008    39
ሚ. ዶላር    72
ሚ. ዶላር    111
ሚ. ዶላር
2009    41
ሚ. ዶላር    62
ሚ. ዶላር    103
ሚ. ዶላር
2010    54
ሚ. ዶላር    130
ሚ. ዶላር    184
ሚ. ዶላር
2011    93
ሚ. ዶላር    259
ሚ. ዶላር    352
ሚ. ዶላር
2012    103
ሚ. ዶላር    328
ሚ. ዶላር    431
ሚ. ዶላር
2013    161
ሚ. ዶላር    503
ሚ. ዶላር    664
ሚ. ዶላር
2014    193
ሚ. ዶላር    572
ሚ. ዶላር    765
ሚ. ዶላር
2015    311
ሚ. ዶላር    732
ሚ. ዶላር    1,042
ሚ. ዶላር
2016    416
ሚ. ዶላር    828
ሚ. ዶላር    1,244
ሚ. ዶላር
2017    550
ሚ. ዶላር    950
ሚ. ዶላር    1,500
ሚ. ዶላር

ብቻ ምናለፋችሁ! አገሪቱን ያቃወሱ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ችግሮች በሙሉ፣ ከአባካኝ የመንግስት ፕሮጀክቶች ጋር በተበራከቱት ብክነቶች፣ የመንግስት ድጎማዎችና የዘፈቀደ ቁጥጥሮች ሳቢያ፣ እየተባባሱ የመጡ ችግሮች ናቸው - የግል ኢንቨስትመንት መዳከሙ፣ የስራ አጥነት ምሬት መበርታቱ፣ ኤክስፖርት መደንዘዙ፣ የውጭ እዳ ቁልሉ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ውጥረቱ፣… እና ሌሎች በርካታ ችግሮችንም መጥቀስ ይቻላል - የዋጋ ንረቱና የኑሮ ውድነቱንም ጭምር።

ቅጥ ባጣ የገንዘብ ሕትመት፣ ብር ረክሶ፣ በዋጋ ንረት የተናጋ ኑሮ!
ለብድርና ለታክስ የሚሆን ተጨማሪ ምርትና ሃብት በአገር ውስጥ ቢሟጠጥ፣ የውጭ እዳ ቢቆለል… ምን ችግር አለው? የገንዘብ ኖት ሕትመት አለለት - የወረቀት ገንዘብ ይመቸዋል። ያው፣ ከአገሬው የኢኮኖሚ (የምርት) እድገት ጋር የማይመጣጠን፣ በሁለት በሦስት እጥፍ የገንዘብ ሕትመትን አጧጧፈው። ግን፣… መዘዙስ? ከወር በኋላ፣ ከመንፈቅ በኋላ ምን እንደሚያስከትል ማወቅ ይከብዳል? ያው፣ መንግስት ወጪዎቹን አደብ ከማስገዛት ይልቅ፣ በብክነት ጎዳናው ለመቀጠል ሲል በሚያካሂደው “ቅጥ ያጣ የገንዘብ ሕትመት” ሳቢያ፣ ብር ይረክሳል። ማለትም የሸቀጦች ዋጋ ይንራል። ማለትም፣ ኑሮ ይወደዳል፣ የብዙ ዜጎች ኑሮ ይናጋል። ኢኮኖሚው ይንገራገጫል።
ምን ይሄ ብቻ። መቼም በዋጋ ንረት ኑሮ ሲወደድና የብዙ ዜጎች ሕይወት ሲናጋ፣… በዚያው ልክ የዜጎች ችግርና ቅሬታ ይበራከታል። አምርሮ፣… መሰሎቹን የሚያማርር ዜጋ መብዛቱስ መች ይቀራል?
ምን ዋጋ አለው? መንግስት ቆም ብሎ ለማሰብ፣ የተከማቹ ጥፋቶቹንና ስህተቶቹን ለማረም የሚጥር መሰላችሁ። አይጥርም። በአቋራጭ ለማምለጥ ሰበቦችንና ማመካኛዎችን ይደረድራል። እንደተለመደው፣ “ስግብግብ ነጋዴዎች” እያለ፣ ጥፋቱን ያላክካል። የዋጋ ቁጥጥርን ያውጃል። “በጥናት ላይ በመመስረት”፣ ከመቅፅበት በዘፈቀደ የዋጋ ተመኖችን ይወስናል። ወይም ከአራት አመት በፊት ጥናት አካሂጃለሁ ብሎ ሌላ የዋጋ ተመን ያመጣል - “የዘፈቀደ ተመን”። ገበያው ይረበሻል፣ አምራቾችንና የግል ኢንቨስትመንቶችን የሚያዳክም ተጨማሪ ችግር ወለደ ማለት ነው።
የመንግስት የዘፈቀደ ስልጣን፣ “እጥረትን ወደ እጦት ያባብሳል”!
እነ ቢራ እና ለስላሳ መጠጦች፣ ከሳሙናና ከፓስታ ጋር፣ “መሰረታዊ ሸቀጦች” ተብለው የዋጋ ተመን ሲወጣላቸው ምን ማለት ነው - “በጥናት ላይ የተመሰረተ የዋጋ ቁጥጥርና የዋጋ ተመን” ሊባል ነው? “የዋጋ ቁጥጥርና ተመን” ማለት፣ በተፈጥሮው ሌላ ትርጉም ሊኖረው አይችልም። የመንግስት ቢሮክራቶች እንዳሻቸው የሚፈጥሩት፣ “የዘፈቀደ ቁጥጥርና ተመን” ማለት ነው።
አብዛኞቹ የዋጋ ተመኖች፣ ለተወሰኑ ወራት ገበያውን አተራምሰው፣ የባሰ ግርግር ፈጥረው፣ ተሰርዘዋል። እስከ ዛሬ የዘለቁ የዘፈቀደ ቁጥጥሮችና የዋጋ ተመኖች ግን አሉ - የስኳር፣ የስንዴ እና የዳቦ።
በመንግስት የዋጋ ቁጥጥርና የዋጋ ተመን፣ ምን ውጤት ተገኘ? የተለየ ውጤት አልተገኘም። ያው የስኳር፣ የስንዴና የዳቦ እጥረት ተባብሷል። የመንግስት ቁጥጥርና ተመን፣… ችግርን እንደሚያባብስ ደግሞ ይታወቃል። አዲስ ነገር አይደለም። የዛሬ ሰባት ዓመት በግላጭ ታይቷል። በደርግ ዘመን ታሪክም፣ ከዚህ የተለየ የውጤት ታሪክ አልተመዘገበም - ውድቀትንና ችግርን የማባባስ ውጤት ብቻ ነው የታየው።
የመንግስት ቢሮክራቶች፣ እንደ አምራች እንደ ነጋዴ አይደሉም። የስንዴ አምራቾችና ነጋዴዎች፣ የኑሯቸው መሰረት፣ ሌላ ሳይሆን፣ ስንዴ ማምረትና ስንዴ ማቅረብ ነው። ከተሳካላቸው ይጠቀማሉ። ለኪሳቸውና ለኑሯቸው ሽልማት ያገኙበታል። የገቢ ምንጫቸው ነው። እንጀራቸው ነው። አለበለዚያ ግን፣ ጉዳት ይደርስባቸዋል።ስንዴ ካላመረቱና ካላቀረቡ፣  ይከስራሉ። የገቢ ምንጫቸውን ያጣሉ። ኪሳቸውና ኑሯቸው ይጎድላል።
የመንግስት ቢሮክራቶች ግን፣ ስንዴ ባይኖር፣ መጋዝን ቢራቆት፣ በዱቄት እጥረት ዳቦ ቢጠፋ፣… ምንም አይጎድልባቸውም። ደሞዛቸው እንደሆነ ቀነስባቸውም። ለዚያውም፣ ለመናኛ ደሞዝ። ተግቶ፣ ስንዴውን በጊዜ የሚያደርስ፣ ዱቄትና ዳቦ እንዳይጠፋ የሚጣጣር የመንግስት ቢሮክራትስ? ቢሳካለት ባይሳካለት ልዩነት የለውም። ደሞዝ አይጎድልበትም፣ አይጨምርለትም። የሚያገኘውም ሆነ የሚያጣው ጥቅም የለም።
ይሄንን ሃቅ፣ እንዲህ በእውን የሚታየውን እውነት ላለማየት “የምንተጋ” ጭፍኖች ካልሆንን በቀር፣ በመንግስት ቢሮክራቶች ቁጥጥርና ኮታ አማካኝነት፣ የስንዴም ሆነ የዳቦ፣ የስኳርም ሆነ የታክሲ እጥረት ይቃለላል ብሎ ማሰብ፣… ምን የሚሉት ቂልነት ሊሆን ይችላል?
ግን በቂላቂልነት ብቻ ቢያበቃስ? አያበቃም።
የመንግስት ቢሮክራቶች የዘፈቀደ ቁጥጥርና የዋጋ ተመን፣ በአገሬው የስንዴ እርሻ ላይ ምን አይነት መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል አስቡት። ወይም ደግሞ፣ የአስር አመታት መረጃዎችን እጥር ምጥን አድርገን ለማነፃፀር እንሞክር።
ከስንዴ ይልቅ፣ ለበቆሎ፣ ለማሽላና ለጤፍ
ዋና ዋናዎቹ የእህል ምርቶች ናቸው - ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላና ጤፍ። ለዚህም ነው፣ አራቱን የምናነፃፅራቸው።
እና ባለፉት አስር ዓመታት የእህል ምርት ምን ያህል ጨመረ። ያው የሕዝብ ብዛትም እየጨመረ ስለሆነና ከመነሻው በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ፣ በኑሮ ላይ ብዙም ለውጥ ላይታይ ይችላል እንጂ፣ የእህል ምርት ጨምሯል። ምን ያህል? የስታትስቲክስ ኤጀንሲ የየአመቱ ሪፖርት እንደሚለው ከሆነ፤… የቆሎ፣ የማሽላና የጤፍ ምርት ከእጥፍ በላይ ሆኗል - ከ105% በላይ አድገዋል። የስንዴ ግን በ84% ብቻ።
ስንዴ የሚመረትበት የመሬት ስፋትም እንዲሁ ብዙ አልጨመረም። ጤፍ፣ በቆሎና ማሽላ የሚመረትበት መሬት፣ በዓስር ዓመታት ውስጥ፣ ወደ 30 በመቶ እና ከዚያ በላይ ጨምሯል። የዚህ ግማሽ ያህል ብቻ ነው፣ ለስንዴ የሚውለው የእርሻ መሬት የጨመረው።
     1999    2009    የመሬት ስፋት ለውጥ
ጤፍ    2.2 ሚ.ሄክታር    3.0 ሚ.ሄክታር    34%
በቆሎ    1.5 ሚ.ሄክታር    2.1 ሚ.ሄክታር    40%
ማሽላ    1.5 ሚ.ሄክታር    1.9 ሚ.ሄክታር    28%
ስንዴ    1.5 ሚ.ሄክታር    1.7 ሚ.ሄክታር    16%

Read 2489 times