Saturday, 28 April 2012 14:40

የማንችስተር ደርቢ ተወዷል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ሰኞ የሚደረገው የማንችስተር ደርቢ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ታሪክ ውዱ ፍልሚያ ተባለ፡፡ ለጨዋታው ለሁለቱ ቡድኖች የሚገቡ ቋሚ ተሰላፊዎች ዋጋ 600 ሚሊየን ዶላር እንደሚያወጣ ተገምቷል፡፡ ሲቲ በሜዳው ኢትሃድ ዩናይትድን ሲገጥም በ3 ነጥብ ተበልጦ ነው፡፡ በሜዳው  ዩናይትድን ካሸነፈ መሪነቱን በግብ ክፍያ ብልጫ በማግኘት መሪነቱን የሚረከብ ከመሆኑም በላይ በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ካሸነፈ ደግሞ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የሊጉ ሻምፒዮን የመሆን እድል ይኖረዋል፡፡ ማንሲቲ ከማንዩናይትድ በኋላ ከሜዳው  ውጭ ኒውካስትል ሲቲን በሜዳው ደግሞ ኪውፒአርን ይገጥማል፡፡ በሌላ በኩል ማን ዩናይትድ የደርቢ ጨዋታውን ማሸነፍ ከቻለ መሪነቱን በስድስት ነጥብ ልዩነት ያሰፋዋል፡፡ ከቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አንዱን በድል መውጣቱ ብቻ ለማን. ዩናይትድ 20ኛውን ሻምፒዮናነት ያረጋግጠለታል፡፡ ከደርቢው በኋላ ማን ዩናይትድ በሜዳው ስዋንሲ ሲቲን እንዲሁም ከሜዳው ውጭ ደግሞ ሰንደርላንድን ያገኛል፡፡

ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በስራ ዘመናቸው ትልቁ ደርቢ ብለው በጠሩት የማንችስተር ክለቦች ፍልሚያ የሚመዘገብ ውጤት ለሲቲ የሻምፒዮናነት ህልም ወሳኝ እንደሆነ ሁሉ ለኛም የዋንጫ ድል ተመሳሳይ ጥቅም ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ዋንጫውን ማሸነፍ የሚችለው አንድ ክለብ ብቻ ነው ያሉት ፈርጊ በ3 ነጥብ ብልጫ ሊጉን በመምራት ላይ በመሆናችን ሻምፒዮናነቱ በእጃችን ነው በማለት ለሲቲ አነስተኛ ግምት ሰጥተዋል፡፡

ዘንድሮ የማንችስተር ደርቢ የኮሚኒቲ ሺልድ ጨዋታን ጨምሮ ከሰኞው የሊጉን ሻምፒዮን ወሳኝ ፍልሚያ ጋር ለአራተኛ ግዜ ይካሄዳል፡፡ በኮሚኒቲ ሺልድ የዋንጫ ፍልሚያ አሸንፎ የሊጉን ውድድር በዋንጫ ድል የጀመረው ዩናይትድ ነው፡፡ሁለቱ ክለቦች በኤፍኤካፕ ሶስተኛ ዙር ሲገናኙም ዩናይትድ 3ለ2 ሲቲን አሸንፎታል፡፡ ሁለቱ የማንችስተር ክለቦች በሊጉ የመጀመርያ ዙር ጨዋታ ኦልድትራፎርድ ሲገናኙ ግን ሲቲ በ10 ተጨዋቾች የተፋለመውን ማንዩናይትድ ያሸነፈው 6ለ1 ነበር፡፡

 

 

Read 3750 times Last modified on Saturday, 28 April 2012 14:43